በስብከቱ ሥራ እድገት የምታደርግ ሁን
1 የሰማዩ አባታችን፣ አገልጋዮቹ መንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ ይደሰታል። መንፈሳዊ እድገት ደግሞ ጎልማሳና ውጤታማ የምሥራቹ ሰባኪ መሆንን ይጨምራል። ጳውሎስ፣ የበላይ ተመልካች የነበረው ጢሞቴዎስ ማደጉን ለማሳየት የሚያደርገውን ጥረት እንዲገፋበት አበረታቶታል። (1 ጢሞ. 4:13-15) ተሞክሮ ያካበትን አስፋፊዎች ብንሆንም እንኳ ሁላችንም የአገልግሎታችንን ጥራት ለማሻሻል መጣር ይኖርብናል።
2 ግብ አውጣ:- አንድ ሰው እድገት ማድረግ ከፈለገ ግብ ማውጣት ይኖርበታል። ልናወጣቸው የምንችላቸው አንዳንድ ግቦች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? መንፈሳዊ ሰይፋችን የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ረገድ ያለንን ችሎታ ይበልጥ ለማሻሻል መጣር እንችላለን። (ኤፌ. 6:17) መንገድ ላይ እንደ ማገልገል፣ በስልክ እንደ መመሥከር አሊያም በንግድ አካባቢዎች እንደ መሥራት ያሉ ማሻሻያ ልናደርግባቸው የሚያስፈልጉ አንዳንድ የአገልግሎት መስኮች ይኖሩ ይሆናል። ምናልባት ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ ተመላልሶ መጠየቆችን በማድረግ በኩል ማሻሻያ ማድረግም ያስፈልገን ይሆናል። ሌላው እጅግ አስፈላጊ የሆነው ግብ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማግኘትና የመምራት ችሎታችንን ማሻሻል ነው።
3 ሊረዱህ የሚችሉ ዝግጅቶች:- የጉባኤ ስብሰባዎች በተለይም የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ፣ እድገት የምናደርግ የምሥራቹ ሰባኪ እንድንሆን ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። ለስብሰባዎች ጥሩ ዝግጅት ለማድረግ፣ በጉባኤ ለመገኘት ብሎም የሚሰጡትን ትምህርቶች ተግባራዊ ለማድረግ ይበልጥ በጣርን ቁጥር የምናገኘው ጥቅም እየጨመረ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም።—2 ቆሮ. 9:6
4 እድገት ለማድረግ እርስ በርስ መረዳዳትም አለብን። (ምሳሌ 27:17) አብረውን የሚያገለግሉት ወንድሞች የሚጠቀሙበትን መግቢያ በትኩረት ማዳመጣችን ማሻሻያ እንድናደርግ ያስችለናል። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ጥናታችን የበላይ ተመልካች በግል እርዳታ እንድናገኝ ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል። በስብከቱ ሥራ ውጤታማ እንድንሆንም ሆነ ከአገልግሎት ከፍተኛ ደስታ እንድናገኝ የሚረዳን ልምድ ያለው አቅኚ አሊያም ሌላ አስፋፊ ማግኘት እንዴት ያለ በረከት ነው! በመጽሐፍ ጥናታችን ውስጥ አዲስ አስፋፊ አለ? ምናልባት ቅድሚያውን ወስደን አብሮን እንዲያገለግል ልንጠይቀው እንችላለን።
5 በዛሬው ጊዜ በመከናወን ላይ ካሉ ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ነው። ለይሖዋ ‘የምስጋና መሥዋዕት’ ስናቀርብ ምርጣችንን መስጠት እንፈልጋለን። (ዕብ. 13:15) በስብከቱ ሥራችን እድገት ለማድረግ የምንጣጣር ከሆነ ‘የማያፍርና የእውነትን ቃል በትክክል የሚያስረዳ’ ሠራተኛ እንሆናለን።—2 ጢሞ. 2:15