የውጭ አገር ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች መስበክ
1. በክልላችን ውስጥ የስብከቱን ሥራ ስናከናውን አገልግሎታችንን ለማስፋት የሚያስችል ምን አጋጣሚ ሊከፈትልን ይችላል?
1 ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥራቹ “ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን” በምድር ዙሪያ እንደሚሰበክ አስቀድሞ ተናግሯል። በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ የሚካፈሉ ሁሉ ኢየሱስ ለተናገረው ለዚህ ሐሳብ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስንካፈል ከእኛ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ የተለያየ አገር ዜጎችን ልናገኝ እንችላለን። እነዚህም ሰዎች ቢሆኑ አስፈሪው የይሖዋ ቀን ከመምጣቱ በፊት የመንግሥቱን መልእክት ለመስማትና ከእውነት ጎን ለመቆም የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። (ሚል. 3:18) በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ የውጭ አገር ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች በመስበክ አዲስ የአገልግሎት መስክ መክፈት የምንችለው እንዴት ነው?
2. ሌላ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ከመስበክ ጋር በተያያዘ ይሖዋን መምሰል የምንችልበት መንገድ የትኛው ነው?
2 ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አንጸባርቁ፦ በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች በሙሉ ምንም ባለማዳላት የይሖዋን ፍቅር ማንጸባረቅ ከፈለግን ሰዎቹ የሚናገሩት ቋንቋ ምንም ይሁን ምን ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋ ትክክለኛውን እውቀት እንዲቀስሙ የመርዳት ልባዊ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። (መዝ. 83:18 NW፤ ሥራ 10:34, 35) በዋነኝነት ትኩረት የምናደርገው ጉባኤያችን የሚመራበትን ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች ላይ ቢሆንም ሌላ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎችም ትኩረት መስጠትና የመንግሥቱን መልእክት ለእነሱ ለማካፈል የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች መፈለግ ይኖርብናል። ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ችላ ማለት ይሖዋ ለምድር ሕዝቦች ሁሉ ምሥክርነት እንዲሰጥ ካለው ዓላማ ጋር ይጋጫል። ታዲያ የእኛን ቋንቋ መናገር የማይችሉ ሰዎችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
3. ጠቃሚ የሆነ ምን መሣሪያ ተዘጋጅቶልናል? በዚህ መሣሪያ ለመጠቀምስ ምን ዝግጅት ማድረግ እንችላለን?
3 ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለውን ቡክሌት ተጠቀሙ፦ ይህ ቡክሌት የተዘጋጀው ከእኛ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ እንድንጠቀምበት ታስቦ ነው። ይህ ቡክሌት በማንኛውም ጊዜ ከእናንተ አይለይ፤ እንዲሁም የቡክሌቱን የተለያዩ ገጽታዎች በሚገባ ለማወቅና በአገልግሎት ላይ ለመጠቀም የሚያስችላችሁን ዝግጅት ለማድረግ ጣሩ። የምትፈልጉትን ቋንቋ በቀላሉ ማውጣት እንድትችሉ በክልላችሁ ውስጥ የሚያጋጥሟችሁን የተለያዩ ቋንቋዎች በቡክሌታችሁ ላይ ምልክት አድርጉ። በእነዚህ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች ካሉ የተወሰኑትን ይዘን ወደ አገልግሎት መውጣታችን ለምናገኘው ሰው በቡክሌቱ ላይ ያለውን መልእክት ካሳየነው በኋላ ጽሑፍ እንድናበረክትለት ያስችለናል።
4. ለሰዎች ሁሉ የተባለውን ቡክሌት በአገልግሎታችን ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
4 በአገልግሎት ላይ ሳላችሁ ሌላ ቋንቋ የሚናገር ሰው ካገኛችሁና የሚናገረውን ቋንቋ ለይታችሁ ማወቅ ካልቻላችሁ በቅድሚያ በቡክሌቱ ሽፋን ላይ ያለውን ሥዕል አሳዩት። ከዚያም በሽፋኑ ውስጠኛ ክፍል ላይ የሚገኘውን የዓለም ካርታ አውጡና በእጃችሁ ራሳችሁን ካመለከታችሁ በኋላ የምትኖሩበትን አገር ከካርታው ላይ አሳዩት፤ በመቀጠልም ግለሰቡ የየት አገር ሰው እንደሆነና ምን ቋንቋ እንደሚናገር ማወቅ እንደምትፈልጉ በምልክት ንገሩት። ምን ቋንቋ እንደሚናገር ካወቃችሁ በኋላ ወደ ማውጫው ሄዳችሁ በቋንቋው የተጻፈው መልእክት ስንተኛው ገጽ ላይ እንደሚገኝ ተመልከቱ፤ ከዚያም በዚያ ገጽ አናት ላይ የሚገኘውን ደመቅ ብሎ የተጻፈውን ዓረፍተ ነገር በማሳየት ግለሰቡ መልእክቱን እንዲያነብ ጋብዙት። ግለሰቡ አንብቦ ሲጨርስ በቋንቋው የተዘጋጀ አንድ ትራክት አበርክቱለት፤ አሊያም በራሱ ቋንቋ የተዘጋጀ ጽሑፍ በሌላ ጊዜ ልታመጡለት እንደምትፈልጉ የሚገልጸውን በግራጫ ቀለም ምልክት የተደረገበትን ዓረፍተ ነገር አሳዩት። ቀጥላችሁ ደመቅ ብሎ የተጻፈውን “የእኔን ስም” የሚለውን ሐረግ ካሳያችሁት በኋላ ስማችሁን እሱ በሚገባው መንገድ ንገሩት። ከዚያም ደመቅ ብሎ የተጻፈውን “የእርስዎንም ስም” የሚለውን ሐረግ በመጠቆም ስሙን እንዲነግራችሁ አድርጉ። በመጨረሻም ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ቁርጥ ያለ ቀጠሮ ያዙ።
5. ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በምናገኝበት ጊዜ ተገቢውን እርዳታ እንዲያገኙ ምን ማድረግ አለብን?
5 ተከታትሎ ለመርዳት የሚያስችል ዝግጅት፦ ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የሚናገሩት ቋንቋ ምንም ይሁን ምን ተመላልሶ መጠየቅ እንዲደረግላቸው ማንኛውም ዓይነት ጥረት ሊደረግ ይገባል። ያነጋገርነው ግለሰብ ስለ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት እንዳለው ከተገነዘብን ቋንቋውን የሚናገር ሰው ግለሰቡን ሄዶ እንዲያነጋግረው ለማድረግ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የተባለውን ቅጽ መሙላትና ለጉባኤያችን ጸሐፊ በአፋጣኝ መስጠት ይኖርብናል። ከዚያም ጸሐፊው ቅጹን ለቅርንጫፍ ቢሮው ይልከዋል፤ ቢሮውም ቅጹን በዚያ ቋንቋ ለሚመራው ቡድን ያስተላልፈዋል። ቡድኑ ቅጹ እንደደረሰው ሳይዘገይ ግለሰቡን ለማነጋገር ዝግጅት ያደርጋል። የጉባኤው ጸሐፊ ቅጹን ፎቶ ኮፒ አድርጎ ለአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ሊሰጠው ይችላል፤ ይህ ደግሞ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በክልሉ ውስጥ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ ለማወቅ ያስችለዋል። ይህን ቅጽ መጠቀም የሚኖርብን ግለሰቡ ልባዊ ፍላጎት ካለው ብቻ ነው።
6. ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ፍላጎት ያለው ሰው በምናገኝበት ጊዜ ምን የማድረግ ኃላፊነት አለብን?
6 S-43 ቅጽ ከተላከበት ጊዜ አንስቶ ቋንቋውን የሚናገር አስፋፊ ግለሰቡን አግኝቶ እስኪያነጋግረው ድረስ የተወሰነ ጊዜ ማለፉ የማይቀር ነው። በመሆኑም ቋንቋውን የሚችለው አስፋፊ ግለሰቡን አግኝቶ እስኪያነጋግረው ድረስ S-43 ቅጽን የሞላው የመጀመሪያው አስፋፊ ግለሰቡን ተከታትሎ በመርዳት ፍላጎቱን ማሳደጉን ሊቀጥል ይችላል። አስፋፊው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የሚያስፈልገው ጊዜም ሊኖር ይችላል። ይሁንና ይህ አስፋፊ ቋንቋውን የሚችል አስፋፊ ግለሰቡን አግኝቶ እስኪያናግረው ባለው ጊዜ ውስጥ ለግለሰቡ የሚሰጠው በቋንቋው የተዘጋጀ ጽሑፍ ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?
7. በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችን ለማግኘት የሚያስችል ምን ዝግጅት አለ?
7 ለሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚሆኑ ጽሑፎች፦ ጉባኤዎች በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችን በብዛት መያዝ የለባቸውም። በቅድሚያ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በክልሉ ውስጥ የየትኛው አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች ለእውነት ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ ለይቶ ለማወቅ ጥረት ያደርጋል፤ ከዚያም አስፋፊዎች በአገልግሎት ላይ የሚጠቀሙባቸው በዚያ ቋንቋ የተዘጋጁ መጠነኛ ብዛት ያላቸው ጽሑፎች በጉባኤ ውስጥ ቢኖሩ ጥሩ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። በዚያ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች በጉባኤው ከሌሉ ማዘዝ ይቻላል። ጽሑፎቹ እስኪደርሱ የተወሰነ ጊዜ ይወስድ ይሆናል። በመሆኑም www.watchtower.org ከሚለው ድረ ገጽ ላይ ጽሑፎችን በወረቀት ማተም የሚቻልበት ዝግጅት አለ። በመቶ በሚቆጠሩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች በድረ ገጹ ላይ የሚገኙ ሲሆን አስፋፊው ወይም ፍላጎት ያሳየው ግለሰብ ጽሑፎቹን ከድረ ገጹ ላይ ማግኘት ይችላል። ሌላ ቋንቋ የሚናገር ፍላጎት ያሳየን ግለሰብ ተከታትሎ ለመርዳት ይህ ዝግጅት ጠቃሚ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
8. ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተከታትለን በመርዳት ረገድ ጉባኤዎች ምን ሚና ይጫወታሉ?
8 የጉባኤው ኃላፊነት፦ ቁጥራቸው እየተበራከተ የሚመጣ የአንድ አገር ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች በክልሉ ውስጥ ቢኖሩም በቋንቋቸው የሚመራ ጉባኤ በአቅራቢያው ላይኖር የሚችልበት አጋጣሚ አለ። በመሆኑም ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ከእናንተ ጋር እንዲሰበሰቡ ልትጋብዟቸው ይገባል። ሞቅ ያለ አቀባበል የምታደርጉላቸው ብሎም ልባዊ አሳቢነት የምታሳዩአቸው ከሆነ አዘውትረው በስብሰባ ላይ ለመገኘት ሊበረታቱ ይችላሉ። መጀመሪያ ላይ የቋንቋና የባሕል ልዩነት እንቅፋት ሊሆንባችሁ ይችላል፤ በይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የሚታየውን እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር ለማሳየት ግን እንቅፋት የሚሆን ነገር የለም። (ሶፎ. 3:9፤ ዮሐ. 13:35) ሌላ ቋንቋ አቀላጥፈህ መናገር ትችላለህ? የምትችል ከሆነና በዚያ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ተከታትለህ ለመርዳት ፈቃደኛ ከሆንክ ይህን መረጃ ለቅርንጫፍ ቢሮው እንዲያስተላልፍ ለጉባኤያችሁ ጸሐፊ ንገረው። ቅርንጫፍ ቢሮው ይህን መረጃ ማግኘቱ ፍላጎት ያለውን ሰው የሚረዳ አስፋፊ ለመመደብ ያስችለዋል።
9. የቋንቋ ትምህርት ለአስፋፊዎች እንዲሰጥ ዝግጅት የሚደረገው ምን ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ነው? ይህ ዝግጅት ተግባራዊ የሚሆነውስ እንዴት ነው?
9 የቋንቋ ትምህርት፦ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን እየረዳችሁ ከሆነና በቋንቋቸው የሚመራው ጉባኤ ብዙ የማይርቃቸው ከሆነ እዚያ እንዲካፈሉ ብታበረታቷቸው የተሻለ ነው። ይህ የማይቻል ከሆነ ግን አንዳንድ አስፋፊዎች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ይበልጥ ለመርዳት ቋንቋውን ለመማር ሊወስኑ ይችላሉ። በዚያ ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ በአቅራቢያው ከሌለ ቅርንጫፍ ቢሮው ከሌላ አገር የመጡ ወይም የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ በቋንቋው የሚጠቀሙ ሰዎችን ብዛት ግምት ውስጥ በማስገባት የቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ ሊወስን ይችላል። ቅርንጫፍ ቢሮው እንዲህ ለማድረግ ከወሰነ ማኅበረሰቡ በሚገኝበት አካባቢ ላሉት ጉባኤዎች ሁኔታውን በማሳወቅ ቋንቋውን ለመማር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የሚገልጽ ማስታወቂያ እንዲነገር ያደርጋል። የቋንቋውን ትምህርት ለመውሰድ የሚያመለክቱ ሁሉ ዓላማቸው በዚያ ቋንቋ ወደሚመራው ቡድን ወይም ጉባኤ በመዛወር የተከፈተውን አዲስ የአገልግሎት መስክ በማስፋት ረገድ ድጋፍ መስጠት ሊሆን ይገባል።
10. በውጭ አገር ቋንቋ የሚመራ ቡድን ለማቋቋም የትኞቹ መሥፈርቶች መሟላት ይኖርባቸዋል? ውሳኔ የሚያገኘውስ እንዴት ነው?
10 ቡድን ማቋቋም፦ በሌላ ቋንቋ የሚመራ ቡድን ለማቋቋም መሠረታዊ የሆኑ አራት መሥፈርቶች መሟላት አለባቸው። (1) ቋንቋውን የሚናገሩ ፍላጎት ያላቸው በርከት ያሉ ሰዎች ሊኖሩ እንዲሁም ቡድኑ እድገት የማድረግ ተስፋ የሚታይበት ሊሆን ይገባል። (2) የተወሰነ ቁጥር ያላቸው የቡድኑ ቋሚ አባላት ቋንቋውን የሚችሉ አሊያም በመማር ላይ ያሉ ሊሆኑ ይገባል። (3) ግንባር ቀደም ሆኖ ቡድኑን የሚመራ እንዲሁም ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ በዚያ ቋንቋ ስብሰባ መምራት የሚችል ብቃት ያለው አንድ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ መኖር አለበት። (4) የሽማግሌዎች አካል ቡድኑን ለመደገፍ ፈቃደኛ መሆን አለበት። እነዚህ መሥፈርቶች በበቂ ሁኔታ ከተሟሉ የሽማግሌዎች አካል ቡድኑን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎችን ለቅርንጫፍ ቢሮው በመጻፍ በጉባኤው ሥር ያለው በውጭ አገር ቋንቋ የሚመራው ቡድን እውቅና እንዲያገኝ ጥያቄ ማቅረብ ይችላል። (የተደራጀ ሕዝብ ከገጽ 106-107ን ተመልከቱ።) ግንባር ቀደም ሆኖ አመራር የሚሰጠው ሽማግሌ “የቡድን የበላይ ተመልካች” ተብሎ ይጠራል፤ የጉባኤ አገልጋይ ከሆነ ደግሞ “የቡድን አገልጋይ” ይባላል። እነዚህ ወንድሞች ቡድኑን የመንከባከብ ኃላፊነት አለባቸው።
11. በክልላችን ውስጥ ለሚገኙት የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች በመስበክ አዲስ የአገልግሎት መስክ መክፈት ትልቅ መብት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
11 በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪ ሰዎች በመስበክ አዲስ የአገልግሎት መስክ መክፈት፣ ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የጀመረው ዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ ካሉት ጉልህ ገጽታዎች አንዱ ነው። በመሆኑም የተሰጠንን ተልእኮ በቅንዓት በማከናወን የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ፤ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ ዛሬም አሕዛብን በማናወጥ ምርጦቹን ወደ ቤቱ ሲያመጣ የማየት አጋጣሚ እናገኛለን። (ሐጌ 2:7 የ1954 ትርጉም) በዚህ ረገድ የሚደረገውን ጥረት በሙሉ ልባችን መደገፋችን ከፍተኛ እርካታ ያስገኝልናል! ሁላችንም በክልላችን ውስጥ ለሚገኙት የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች በመስበክ አዲስ የአገልግሎት መስክ ለመክፈት የምናደርገውን የጋራ ጥረት ይሖዋ እንዲባርከው ምኞታችን ነው። የሰዎች ቋንቋ መለያየቱ እንቅፋት ቢፈጥርም አምላክ መስኩን እንደሚያሳድገው ምንጊዜም እናስታውስ!—1 ቆሮ. 3:6-9