አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ
1. ምን አስፈላጊ ሥራ እየተከናወነ ነው?
1 ኢየሱስ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት ከመሠከረ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” አላቸው። (ዮሐ. 4:35, 36) በወቅቱ መንፈሳዊው የመከር ሥራ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን ኢየሱስ ሥራው ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንደሚኖረው አስቀድሞ ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ ከሰማይ ሆኖ የመከሩን ሥራ ሲደግፍ ቆይቷል። (ማቴ. 28:19, 20) ይህ ሥራ የሚጠናቀቅበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚጠቁሙ ምን ማስረጃዎች አሉ?
2. ዓለም አቀፉ የመከር ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ የሚጠቁሙ ምን እድገቶች እየታዩ ነው?
2 ዓለም አቀፉ የመከር ሥራ፦ በ2009 የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ በአስፋፊዎች ቁጥር ረገድ 3.2 በመቶ ጭማሪ ተገኝቷል። የስብከቱ ሥራ የታገደባቸው አገሮች 14 በመቶ ጭማሪ ነበራቸው። በየወሩ ሪፖርት የተደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር ከ7,619,000 ይበልጥ የነበረ ሲሆን ይህ ቁጥር በዚያ ዓመት ከተመዘገበው ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር የሚበልጥ ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ ቁጥሩ በ2008 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት ከተደረገው የጥናቶች ቁጥር በግማሽ ሚሊዮን ገደማ ይበልጣል። በብዙ አካባቢዎች ሥራው በፍጥነት እየተስፋፋ በመሆኑ በጊልያድ ትምህርት ቤት የሠለጠኑ ተጨማሪ ሚስዮናውያን አስፈልገዋል። በብዙ አገሮች በውጭ አገር ቋንቋዎች የሚሰጠው ምሥክርነት አመርቂ ውጤት እያስገኘ ነው። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ በመከሩ ሥራ መገባደጃ ላይ ሥራውን እያፋጠነው ነው። (ኢሳ. 60:22) እናንተስ በአካባቢያችሁ ስለሚገኘው “አዝመራ” አዎንታዊ የሆነ አመለካከት አላችሁ?
3. አንዳንዶች በአካባቢያቸው ስለሚከናወነው የመከር ሥራ ምን ይሰማቸዋል?
3 በአካባቢያችሁ ያለው የመከር ሥራ፦ አንዳንዶች “እኔ የማገለግልበት ክልል ያን ያህል ውጤታማ አይደለም” ይሉ ይሆናል። እርግጥ ነው አንዳንድ ክልሎች የሌሎችን ያህል ውጤታማ አይመስሉ ይሆናል፤ ወይም ከዚህ በፊት የነበረውን ያህል ፍሬ ላይገኝባቸው ይችላል። ከዚህ የተነሳ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች እነሱ በሚኖሩበት አካባቢ አዝመራው እንደተሰበሰበና የቀረው ሥራ ቃርሚያ ከመሰብሰብ ጋር እንደሚመሳሰል ይሰማቸዋል። ይሁንና እውነታው እንደዚያ ነው?
4. አገልግሎታችንን በተመለከተ ምን ዓይነት ተገቢ አመለካከት ማዳበር ይኖርብናል? ለምንስ?
4 የመከር ወቅት፣ ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ ሥራ የሚበዛበት ጊዜ ነው። ኢየሱስ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ ምን ያህል የጥድፊያ ስሜት እንደሚያንጸባርቅ ተመልከት፦ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ጌታ ወደ መከር ሥራው ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” (ማቴ. 9:37, 38) ይሖዋ የመከሩ ሥራ ጌታ እንደመሆኑ መጠን ምርቱ መቼና የት መሰብሰብ እንዳለበት ያውቃል። (ዮሐ. 6:44፤ 1 ቆሮ. 3:6-8) ታዲያ የእኛ ድርሻ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ጠዋት ላይ ዘርህን ዝራ፤ ማታም ላይ እጅህ ሥራ አይፍታ” የሚል መልስ ይሰጠናል። (መክ. 11:4-6) አዎን፣ የመከሩ ሥራ የሚገባደድበት ጊዜ ስለተቃረበ እጃችን ሥራ መፍታት አይኖርበትም!
5. ውጤታማ በማይመስሉ ክልሎች ውስጥ በቅንዓት መስበካችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
5 በመከሩ ሥራ መካፈላችሁን ቀጥሉ፦ ክልላችን በተደጋጋሚ ጊዜ የተሸፈነና ምንም ውጤት የሌለው ቢመስልም እንኳ በቅንዓትና በጥድፊያ ስሜት እንድንሰብክ የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት አለን። (2 ጢሞ. 4:2) በዓለማችን ላይ የሚታየው አለመረጋጋት ሰዎች አመለካከታቸው እንዲለወጥና ስለ ወደፊቱ ጊዜ በቁም ነገር እንዲያስቡ እያደረጋቸው ነው። ወጣቶች እያደጉ ሲሄዱ ደኅንነትና ውስጣዊ ሰላም የማግኘት ጉዳይ ያሳስባቸው ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ በምናሳየው ጽናት ይማረኩ ይሆናል። አዎን፣ ከዚህ ቀደም መልእክታችንን መስማት የማይፈልጉ ሰዎች ጥሩ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። መልእክቱን ሆን ብለው ለማይቀበሉ ሰዎችም እንኳ ማስጠንቀቂያውን ማሰማት ይኖርብናል።—ሕዝ. 2:4, 5፤ 3:19
6. ተፈታታኝ በሆነ ክልል ውስጥ የምንሰብክ ከሆነ ቅንዓታችን እንዳይጠፋ ምን ሊረዳን ይችላል?
6 ተፈታታኝ በሆነ ክልል ውስጥ የምንሰብክ ከሆነ ቅንዓታችን እንዳይጠፋ ምን ሊረዳን ይችላል? ምናልባትም ከቤት ወደ ቤት ከምናደርገው አገልግሎት በተጨማሪ በንግድ አካባቢዎች እንደ መስበክና በስልክ እንደ መመሥከር ባሉ ሌሎች የአገልግሎት መስኮችም መካፈል እንችላለን። ወይም ደግሞ እንዳይሰለቸን አቀራረባችንን መቀያየር እንችላለን። አሊያም በፕሮግራማችን ላይ ማስተካከያ በማድረግ ምሽት ላይ ወይም ሰዎች በአብዛኛው ቤታቸው በሚገኙበት ሰዓት ላይ ማገልገል እንችላለን። ምናልባትም ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች ለማዳረስ አዲስ ቋንቋ መማር እንችል ይሆናል። የዘወትር አቅኚ በመሆን አገልግሎታችንን የበለጠ ማስፋትም እንችላለን። ወይም ደግሞ የመከሩ ሠራተኞች ጥቂት ወደሆኑበት አካባቢ ተዛውረን በመሄድ ልናገለግል እንችላለን። ለመከሩ ሥራ ትክክለኛ አመለካከት ካዳበርን በዚህ አስፈላጊ ሥራ ላይ በተቻለን መጠን የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን።
7. መከሩን በመሰብሰቡ ሥራ የምንካፈለው እስከ መቼ ድረስ ነው?
7 ገበሬዎች ሰብላቸውን ለመሰበሰብ የሚኖራቸው ጊዜ ውስን ስለሆነ ሥራቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ዘና አይሉም ወይም ሥራቸውን በዝግታ አያከናውኑም። መንፈሳዊው የመከር ሥራም በዚህ ዓይነት የጥድፊያ ስሜት መከናወን ይኖርበታል። መከሩን በመሰብሰቡ ሥራ የምንካፈለው እስከ መቼ ነው? ‘በሥርዓቱ መደምደሚያ’ ዘመን በሙሉ ማለትም “መጨረሻው” እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ መስበካችንን እንቀጥላለን። (ማቴ. 24:14፤ 28:20) የይሖዋ ዋነኛ አገልጋይ እንደሆነው እንደ ኢየሱስ የተሰጠንን ሥራ መፈጸም እንፈልጋለን። (ዮሐ. 4:34፤ 17:4) ስለዚህ ፍጻሜው እስከሚመጣ ድረስ አገልግሎታችንን በቅንዓት፣ በደስታና አዎንታዊ በሆነ አመለካከት ማከናወናችንን እንቀጥል። (ማቴ. 24:13) የመከሩ ሥራ ገና አልተጠናቀቀም!
[ከገጽ 5 የተቀነጨበ ሐሳብ]
የመከር ወቅት፣ ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ ሥራ የሚበዛበት ጊዜ ነው