ነቢያትን አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው—ሚክያስ
1. ሚክያስ የትኛው ጥያቄ ተፈጥሮበት ሊሆን ይችላል? ያከናወነው የስብከት ሥራ ከንቱ ሆኖ አልቀረም የምንለውስ ለምንድን ነው?
1 ‘ይህ ብልሹ ሥርዓት የሚወገደው መቼ ነው?’ ነቢዩ ሚክያስ በእስራኤልና በይሁዳ መንግሥታት ላይ የይሖዋን የፍርድ መልእክት ባወጀበት ወቅት ይኸው ጥያቄ ተፈጥሮበት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ያከናወነው የስብከት ሥራ ከንቱ ሆኖ አልቀረም። በሰማርያ ላይ የተነገረው የይሖዋ የፍርድ መልእክት በ740 ዓ.ዓ. ሚክያስ በሕይወት እያለ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ሚክ. 1:6, 7) ቆየት ብሎም በ607 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌም ጠፍታለች። (ሚክ. 3:12) ይሖዋ የሚወስደውን የፍርድ እርምጃ እየተጠባበቅን ባለንበት በዛሬው ጊዜ ሚክያስ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
2. የይሖዋን ቀን ስንጠባበቅ ትዕግሥት የምናሳየው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?
2 በትዕግሥት ጠብቁ፦ ሚክያስ “እኔ ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አደርጋለሁ፤ አዳኜ የሆነውን አምላክ እጠብቃለሁ” ሲል ጽፏል። (ሚክ. 7:7) እርግጥ ነው፣ እንዲህ ሲባል ሚክያስ መጨረሻው እስኪመጣ ድረስ እጁን አጣጥፎ ይጠብቅ ነበር ማለት አይደለም። ይሖዋ የሰጠውን የነቢይነት ሥራ በትጋት ከማከናወን ወደኋላ አላለም ነበር። እኛም የይሖዋን ቀን እየተጠባበቅን ባለንበት በዚህ ወቅት ‘ቅዱስ ሥነ ምግባር መከተልና ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮች መፈጸም’ ይኖርብናል። (2 ጴጥ. 3:11, 12) ይሖዋ መታገሡ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ንስሐ የሚገቡበት ጊዜ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። (2 ጴጥ. 3:9) ስለሆነም ነቢያት ትዕግሥት በማሳየት ረገድ የተዉትን አርዓያ እንድንከተል የተሰጠንን መለኮታዊ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።—ያዕ. 5:10
3. ይሖዋ፣ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን መለመን ያለብን ለምንድን ነው?
3 ይሖዋ ኃይል እንደሚሰጣችሁ ተማመኑ፦ ሚክያስ ፈታኝ ተልእኮ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ተልእኮውን ለመወጣት የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠው ይሖዋን ለምኗል። (ሚክ. 3:8) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በሚሰጠን ኃይል እንድንታመን የሚያበረታታን ያለ ምክንያት አይደለም። የተሰጧቸውን ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች መወጣት ይችሉ ዘንድ ይሖዋ ለደከሙት ይህ ነው የማይባል ኃይል ይሰጣቸዋል። (መዝ. 84:5, 7፤ ኢሳ. 40:28-31) እናንተስ ቅዱስ በሆነው አገልግሎት ስትካፈሉ ይህ እውነት መሆኑን በሕይወታችሁ ያያችሁበት ጊዜ አለ? ይሖዋ ከፍተኛ ኃይል ያለውን ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጣችሁ ዘወትር ትጸልያላችሁ?—ሉቃስ 11:13
4. የሚክያስ ሕይወት ለእኛ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?
4 ሚክያስ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። በሚኖርበት አካባቢ የሥነ ምግባር ብልሹነት ተስፋፍቶ የነበረ ቢሆንም እሱ ግን በታማኝነት ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። በተመሳሳይ እኛም በየዕለቱ ንጹሕ አቋማችንን የሚፈታተኑ ነገሮች ያጋጥሙናል። ስለዚህ “በአምላካችን በይሖዋ ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም” ለመሄድ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ሚክ. 4:5 NW