የጥናት ርዕስ 2
ሌሎችን ‘በእጅጉ ማጽናናት’ ትችላለህ
“ለአምላክ መንግሥት አብረውኝ የሚሠሩት እነዚህ . . . ናቸው፤ እነሱም በእጅጉ አጽናንተውኛል።”—ቆላ. 4:11 ግርጌ
መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ
ማስተዋወቂያa
1. በርካታ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ ነው?
በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ውጥረት የሚፈጥሩ ይባስ ብሎም ስሜትን የሚጎዱ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ ነው። አንተስ በጉባኤህ ውስጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠማቸው ወንድሞችንና እህቶችን ታውቃለህ? አንዳንድ ክርስቲያኖች በጠና ታመዋል አሊያም የሚወዱትን ሰው በሞት አጥተዋል። ሌሎች ደግሞ የቤተሰባቸው አባል ወይም የቅርብ ወዳጃቸው እውነትን መተዉ ጥልቅ ሐዘን አስከትሎባቸዋል። በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ብዙ ችግር የደረሰባቸው ክርስቲያኖችም አሉ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ እነሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?
2. ሐዋርያው ጳውሎስ ማጽናኛ ያስፈለገው ለምንድን ነው?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ በተደጋጋሚ ጊዜያት ሕይወቱ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። (2 ቆሮ. 11:23-28) በተጨማሪም “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” ያለው ነገር ያስከተለበትን ሥቃይ መቋቋም ነበረበት፤ ይህ እሾህ የጤና ችግር ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮ. 12:7) ከዚህም ሌላ በአንድ ወቅት የሥራ አጋሩ የነበረው ዴማስ “በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት ወዶ” ጥሎት መሄዱ ሐዘን አስከትሎበት ነበር። (2 ጢሞ. 4:10) ጳውሎስ ሌሎችን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ የሚያገለግልና ደፋር የሆነ ቅቡዕ ክርስቲያን ነበር፤ ሆኖም እሱም እንኳ ተስፋ የቆረጠባቸው ጊዜያት ነበሩ።—ሮም 9:1, 2
3. ይሖዋ፣ ጳውሎስ ማጽናኛና ድጋፍ እንዲያገኝ ያደረገው በምን መንገድ ነው?
3 ጳውሎስ የሚያስፈልገውን ማጽናኛና ድጋፍ አግኝቷል። በምን መንገድ? ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ጳውሎስን እንዳጠናከረው ጥርጥር የለውም። (2 ቆሮ. 4:7፤ ፊልጵ. 4:13) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ጳውሎስን ለማጽናናት በእምነት ባልንጀሮቹ ተጠቅሟል። ጳውሎስ ስለ አንዳንድ የሥራ አጋሮቹ ሲናገር “በእጅጉ አጽናንተውኛል” ብሏል። (ቆላ. 4:11) በስም ከጠቀሳቸው መካከል አርስጥሮኮስ፣ ቲኪቆስና ማርቆስ ይገኙበታል። እነዚህ ክርስቲያኖች ጳውሎስን በማበረታታት እንዲጸና ረድተውታል። ለመሆኑ እነዚህ ሦስት ወንድሞች ጥሩ አጽናኝ እንዲሆኑ ያስቻሏቸው የትኞቹ ባሕርያት ናቸው? እኛስ አንዳችን ሌላውን ስናጽናና እና ስናበረታታ የእነሱን መልካም ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
እንደ አርስጥሮኮስ ታማኝ ሁን
4. አርስጥሮኮስ ለጳውሎስ ታማኝ ወዳጅ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
4 መቄዶንያ ውስጥ የምትገኘው የተሰሎንቄ ክርስቲያን የሆነው አርስጥሮኮስ ለጳውሎስ ታማኝ ወዳጅ መሆኑን አሳይቷል። ስለ አርስጥሮኮስ የሚናገር ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የምናገኘው ጳውሎስ በሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ኤፌሶንን እንደጎበኘ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ነው። በወቅቱ ከጳውሎስ ጋር የነበረው አርስጥሮኮስ በቁጣ በተሞሉ ሰዎች እጅ ወደቀ። (ሥራ 19:29) በኋላ ላይ አርስጥሮኮስ ሲለቀቅ፣ አደጋ ወደሌለበት ቦታ ከመሸሽ ይልቅ በታማኝነት ከጳውሎስ ጋር ቆይቷል። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ግሪክ ውስጥ ተቃዋሚዎች ጳውሎስን ለመግደል ሴራ እየጠነሰሱ በነበረበት ጊዜም እንኳ አርስጥሮኮስ ከጎኑ አልተለየም። (ሥራ 20:2-4) በ58 ዓ.ም. ገደማ ጳውሎስ እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም በተወሰደበት ወቅት አርስጥሮኮስ ረጅሙን መንገድ አብሮት ተጉዟል፤ ጳውሎስ በጉዞው ላይ የመርከብ አደጋ በገጠመው ወቅት አርስጥሮኮስ አብሮት ነበር። (ሥራ 27:1, 2, 41) ሮም ከደረሱ በኋላም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከጳውሎስ ጋር ታስሮ የነበረ ይመስላል። (ቆላ. 4:10) በእርግጥም ጳውሎስ እንዲህ ባለው ታማኝ አጋሩ መበረታታቱና መጽናናቱ አያስገርምም!
5. በምሳሌ 17:17 ላይ እንደተገለጸው ታማኝ ወዳጅ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
5 እንደ አርስጥሮኮስ ሁሉ እኛም በደህናው ጊዜ ብቻ ሳይሆን ‘በመከራ ቀንም’ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጎን በመቆም ታማኝ ወዳጅ ልንሆናቸው እንችላለን። (ምሳሌ 17:17ን አንብብ።) ወንድማችን ወይም እህታችን ያጋጠማቸው ችግር ካለፈ በኋላም እንኳ ማጽናኛ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሁለቱንም ወላጆቿን በካንሰር ያጣችው ፍራንስስb እንዲህ ብላለች፦ “ከባድ መከራ ሲገጥመን ሥቃዩ ለረጅም ጊዜ እንደሚቀጥል ይሰማኛል። ወላጆቼ ከሞቱ የተወሰነ ጊዜ ቢያልፍም አሁንም ሐዘኑ እንዳልወጣልኝ የሚረዱ ታማኝ ጓደኞች ስላሉኝ አመስጋኝ ነኝ።”
6. ታማኝነት ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?
6 ታማኝ ወዳጆች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለመርዳት ሲሉ መሥዋዕት ይከፍላሉ። ፒተር የተባለ ወንድም ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ፒተር በፍጥነት እየተባባሰ የሚሄድና ሕይወቱን የሚያሳጣው ሕመም እንዳለበት ተነገረው። ባለቤቱ ካትሪን እንዲህ ብላለች፦ “ፒተር ስላለበት በሽታ በሰማንበት ቀን ወደ ሕክምና ቀጠሯችን የወሰዱን በጉባኤያችን የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት ነበሩ። እነዚህ ባልና ሚስት ዜናውን እንደሰሙ፣ በዚህ አስጨናቂ ወቅት ምንጊዜም ከጎናችን ለመሆን ወሰኑ፤ ደግሞም እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ አልተለዩንም።” በእርግጥም የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጽናት እንድንቋቋም የሚረዱ እውነተኛ ወዳጆች በእጅጉ ያጽናኑናል!
እንደ ቲኪቆስ እምነት የሚጣልብህ ሁን
7-8. በቆላስይስ 4:7-9 መሠረት ቲኪቆስ እምነት የሚጣልበት ሰው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
7 በሮም ግዛት ውስጥ ካለችው ከእስያ አውራጃ የመጣው ቲኪቆስ እምነት የሚጣልበት የጳውሎስ አጋር ነበር። (ሥራ 20:4) በ55 ዓ.ም. ገደማ ጳውሎስ በይሁዳ ላሉት ክርስቲያኖች እርዳታ እንዲዋጣ ዝግጅት አድርጎ ነበር፤ ጳውሎስ ከዚህ አስፈላጊ ሥራ ጋር በተያያዘ እገዛ እንዲያበረክት የመደበው ቲኪቆስን ሳይሆን አይቀርም። (2 ቆሮ. 8:18-20) ከጊዜ በኋላም ጳውሎስ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ በታሰረበት ወቅት ቲኪቆስ መልእክተኛው ሆኖ አገልግሎታል። ቲኪቆስ፣ ጳውሎስ የጻፋቸውን ደብዳቤዎችና ማበረታቻ የያዙ መልእክቶች በእስያ ለሚገኙ ጉባኤዎች አድርሷል።—ቆላ. 4:7-9
8 ከጊዜ በኋላም ቲኪቆስ እምነት የሚጣልበት የጳውሎስ ወዳጅ ሆኖ ቀጥሏል። (ቲቶ 3:12) በዚያ ወቅት እንደ ቲኪቆስ እምነት የሚጣልባቸው ሁሉም ክርስቲያኖች አልነበሩም። በ65 ዓ.ም. ገደማ ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜ ታስሮ በነበረበት ወቅት፣ በእስያ ግዛት የሚገኙ በርካታ ወንድሞች ከእሱ ጋር መተባበራቸውን እንዳቆሙ ጽፏል፤ እነዚህ ወንድሞች ይህን ያደረጉት ተቃዋሚዎችን ፈርተው ሊሆን ይችላል። (2 ጢሞ. 1:15) በሌላ በኩል ግን ቲኪቆስ እምነት የሚጣልበት ሰው ስለነበር ጳውሎስ ተጨማሪ ኃላፊነት ሰጥቶታል። (2 ጢሞ. 4:12) ጳውሎስ እንደ ቲኪቆስ ያለ ጥሩ ወዳጅ በማግኘቱ አመስጋኝ እንደነበረ ጥያቄ የለውም።
9. ቲኪቆስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
9 እኛም እምነት የሚጣልብን ወዳጅ በመሆን ቲኪቆስን መምሰል እንችላለን። ለምሳሌ፣ ችግር የገጠማቸውን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንደምንረዳቸው ቃል በመግባት ብቻ ሳንወሰን እነሱን በተግባር መርዳት ይኖርብናል። (ማቴ. 5:37፤ ሉቃስ 16:10) እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወንድሞች በቃላችን እንደምንገኝ ማወቃቸው በእጅጉ ያጽናናቸዋል። አንዲት እህት ይህ የሆነበትን ምክንያት ስትገልጽ “‘እንደሚረዳን ቃል የገባልን ሰው በሰዓቱ መጥቶ የተናገረውን ነገር ይፈጽም ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ሌላ ሐሳብ አይጨምርባችሁም” ብላለች።
10. በምሳሌ 18:24 ላይ እንደተገለጸው አስቸጋሪ ሁኔታ ወይም ያልጠበቁት መጥፎ ነገር ያጋጠማቸው ሰዎች መጽናኛ ማግኘት የሚችሉት ከማን ነው?
10 አስቸጋሪ ሁኔታ ወይም ያልጠበቁት መጥፎ ነገር ያጋጠማቸው ሰዎች፣ እምነት ለሚጥሉበት ወዳጃቸው የልባቸውን አውጥተው መናገራቸው ብዙውን ጊዜ ያጽናናቸዋል። (ምሳሌ 18:24ን አንብብ።) ልጁ ከክርስቲያን ጉባኤ በመወገዱ ስሜቱ በጣም የተጎዳው ቢጄ “እምነት ለምጥልበት ሰው ስሜቴን አውጥቼ መናገር ፈልጌ ነበር” ብሏል። ካርሎስ ደግሞ በሠራው ስህተት ምክንያት በጉባኤ ውስጥ ያለውን የሚወደውን መብት አጣ። ካርሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ይኮንነኝ ይሆን ብዬ ሳልፈራ ስሜቴን አውጥቼ የምነግረው ሰው ፈልጌ ነበር።” የጉባኤው ሽማግሌዎች ለካርሎስ እንዲህ ዓይነት ወዳጅ በመሆን ችግሩን እንዲወጣ ረድተውታል። ካርሎስ፣ ሽማግሌዎቹ የነገራቸውን ነገር በሚስጥር እንደሚይዙት ማወቁም አጽናንቶታል።
11. ሌሎች እምነት የሚጥሉብንና ሚስጥራቸውን የሚያካፍሉን ወዳጅ ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
11 ሌሎች እምነት የሚጥሉብንና ሚስጥራቸውን የሚያካፍሉን ወዳጅ ለመሆን ትዕግሥትን ማዳበር ያስፈልገናል። ዣና ባለቤቷ ጥሏት በሄደበት ወቅት ለቅርብ ወዳጆቿ ስሜቷን አውጥታ መናገሯ አጽናንቷታል። “አንድ ዓይነት ነገር በተደጋጋሚ ጊዜ ብናገርም እንኳ በትዕግሥት ያዳምጡኝ ነበር” ብላለች። አንተም ጥሩ አድማጭ በመሆን እውነተኛ ወዳጅ መሆንህን ማሳየት ትችላለህ።
እንደ ማርቆስ ለማገልገል ፈቃደኛ ሁን
12. ማርቆስ ማን ነበር? የፈቃደኝነት መንፈስ ያሳየውስ እንዴት ነው?
12 ማርቆስ ከኢየሩሳሌም የመጣ አይሁዳዊ ክርስቲያን ነበር። በብዙዎች ዘንድ የታወቀ ሚስዮናዊ የሆነው የበርናባስ ዘመድም ነበር። (ቆላ. 4:10) የማርቆስ ቤተሰብ ጥሩ ኑሮ የነበራቸው ይመስላል፤ ያም ቢሆን ማርቆስ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሰጠው ለቁሳዊ ነገሮች አይደለም። ማርቆስ በሕይወቱ ሁሉ ሌሎችን ለማገልገል ራሱን በፈቃደኝነት አቅርቧል፤ ይህን ማድረግም ያስደስተው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በተለያዩ ጊዜያት ከሐዋርያው ጳውሎስና ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር አብሮ በማገልገል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ረድቷቸዋል፤ የማርቆስ ኃላፊነት የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ማቅረብ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 13:2-5፤ 1 ጴጥ. 5:13) ጳውሎስ ስለ ማርቆስ ሲናገር ‘ለአምላክ መንግሥት አብረውት ከሚሠሩት’ አንዱ እንደሆነና “የብርታት ምንጭ” እንደሆነለት ገልጿል።—ቆላ. 4:10, 11
13. ማርቆስ በታማኝነት ያከናወነውን አገልግሎት ጳውሎስ ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው 2 ጢሞቴዎስ 4:11 የሚያሳየው እንዴት ነው?
13 ማርቆስ ከጳውሎስ የቅርብ ወዳጆች አንዱ ነበር። ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ጳውሎስ በ65 ዓ.ም. ገደማ ሮም ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ በታሰረበት ወቅት ለጢሞቴዎስ ሁለተኛ ደብዳቤ ጽፎለት ነበር። በዚያ ደብዳቤ ላይ ጳውሎስ፣ ማርቆስን ይዞ ወደ ሮም እንዲመጣ ጢሞቴዎስን ጠይቆታል። (2 ጢሞ. 4:11) ጳውሎስ፣ ማርቆስ ቀደም ሲል በታማኝነት ያከናወነውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ እንደተመለከተው ጥርጥር የለውም፤ በመሆኑም በዚያ ወሳኝ ወቅት አብሮት እንዲሆን ፈልጓል። ማርቆስ ለጳውሎስ አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮች ያደርግለት ምናልባትም ምግብ ወይም ለመጻፍ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ያቀርብለት ነበር። ጳውሎስ ከመሞቱ በፊት ባሉት የመጨረሻ ቀናት የማርቆስን ማበረታቻና ድጋፍ ማግኘቱ እንዲጸና ረድቶት መሆን አለበት።
14-15. ማቴዎስ 7:12 ሌሎችን የሚጠቅም ነገር ማድረግ የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ምን ያስተምረናል?
14 ማቴዎስ 7:12ን አንብብ። አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ፣ ወዳጆቻችን የሚያስፈልጉንን ነገሮች በማከናወን ሲያግዙን በጣም እንደሰታለን! አሳዛኝ በሆነ አደጋ አባቱን ድንገት ያጣው ራያን እንዲህ ብሏል፦ “ሐዘን ውስጥ በምትሆኑበት ወቅት ብዙዎቹን የዕለት ተዕለት ሥራዎች ማከናወን ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ ይሰማችኋል። በመሆኑም ትናንሽ በሚመስሉ ነገሮችም እንኳ ሌሎች የሚያደርጉላችሁ እርዳታ በእጅጉ ያጽናናል።”
15 ለሌሎች ትኩረት የምንሰጥና ሁኔታዎችን የምናስተውል ከሆነ እነሱን መርዳት የምንችልባቸው መንገዶች ማግኘታችን አይቀርም። ለምሳሌ፣ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ፒተርንና ካትሪንን ለመርዳት አንዲት እህት ምን እንዳደረገች እንመልከት፤ ይህች እህት የሕክምና ቀጠሮ ሲኖራቸው የሚወስዳቸው ሰው ለማመቻቸት በራሷ ተነሳስታ ዝግጅት አደረገች። ፒተርም ሆነ ካትሪን መኪና መንዳት ስላቆሙ ይህች እህት ፈቃደኛ የሆኑ የጉባኤው አባላት ተራ ገብተው እንዲያመላልሷቸው ፕሮግራም አወጣች። ታዲያ ይህ ዝግጅት ባልና ሚስቱን ጠቅሟቸዋል? ካትሪን “ትልቅ ሸክም እንደቀለለልን ተሰማን” ብላለች። ቀላል የሚመስሉ ጠቃሚ ነገሮችን ማድረጋችሁ ሌሎችን በእጅጉ ሊያጽናና እንደሚችል አትዘንጉ።
16. ሌሎችን ከማጽናናት ጋር በተያያዘ ከማርቆስ ምን አስፈላጊ ትምህርት እናገኛለን?
16 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ደቀ መዝሙሩ ማርቆስ በሥራ የተጠመደ ክርስቲያን እንደነበረ ጥያቄ የለውም። በስሙ የሚጠራውን የወንጌል ዘገባ መጻፍን ጨምሮ ከባድ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች ነበሩት። ያም ቢሆን ማርቆስ ጳውሎስን ለማጽናናት የሚሆን ጊዜ አላጣም፤ ጳውሎስም ቢሆን የእሱን እርዳታ ለመጠየቅ አልተሳቀቀም። ከቤተሰቧ አባላት አንዱ የተገደለባት አንጀላ በሐዘኗ ያጽናኗት ወዳጆቿ እንዲህ ዓይነት የፈቃደኝነት መንፈስ ስለነበራቸው አመስጋኝ ናት። እንዲህ ብላለች፦ “ወዳጆችህ ከልባቸው ሊረዱህ እንደፈለጉ ካስተዋልክ የእነሱን እርዳታ መጠየቅ አይከብድህም። እንዲህ ያሉ ወዳጆች፣ አንተን መርዳት እንደከበዳቸው እንዲሰማህ አያደርጉም።” እንግዲያው ‘የእምነት ባልንጀሮቼ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ፈቃደኛ በመሆኔ እታወቃለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው።
ሌሎችን ለማጽናናት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ
17. በ2 ቆሮንቶስ 1:3, 4 ላይ ማሰላሰል ሌሎችን ለማጽናናት የሚያነሳሳን እንዴት ነው?
17 ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ወንድሞችና እህቶች ለማግኘት ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም። እነዚህን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለማጽናናት፣ ሌሎች እኛን ሲያጽናኑ የነገሩንን የሚያበረታታ ሐሳብ ማካፈል እንችላለን። አያቷን በሞት ያጣችው ኒኖ “እኛ ራሳችንን ካቀረብን ይሖዋ ሌሎችን እንድናጽናና ሊጠቀምብን ይችላል” ብላለች። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4ን አንብብ።) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ፍራንስስም እንዲህ ብላለች፦ “በ2 ቆሮንቶስ 1:4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በእርግጥም እውነት ነው። እኛ ባገኘነው ማጽናኛ ሌሎችን ማጽናናት እንችላለን።”
18. (ሀ) አንዳንዶች ሌሎችን ማጽናናት የሚያስፈራቸው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ሌሎችን በማጽናናት ረገድ እንዲሳካልን ምን ሊረዳን ይችላል? ምሳሌ ስጥ።
18 ሌሎችን ማጽናናት ቢያስፈራንም እንኳ ይህን ማድረግ ይኖርብናል። በጣም አስጨናቂ ሁኔታ ያጋጠመውን ሰው ለማጽናናት ምን ማለት ወይም ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ እንጋባ ይሆናል። ፖል የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ፣ አባቱ ከሞተ በኋላ አንዳንድ ወዳጆቹ እሱን ለማጽናናት ያደረጉትን ጥረት አይረሳውም። “እኔን ቀርበው ማናገር ከብዷቸው እንደነበር ታውቆኛል። ምን እንደሚሉ ጨንቋቸው ነበር። ያም ቢሆን እኔን ለማጽናናትና ለመደገፍ በመፈለጋቸው አመስጋኝ ነበርኩ” ብሏል። በተመሳሳይም በሚኖርበት አካባቢ በደረሰ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዳ ታጆን የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “እውነቱን ለመናገር ከመሬት መንቀጥቀጡ በኋላ በነበሩት ቀናት ሰዎች የላኩልኝን መልእክቶች በሙሉ አስታውሳለሁ ማለት ይከብደኛል፤ የእኔ ደህንነት ያሳሰባቸው መሆኑን ግን መቼም ቢሆን የምረሳው ነገር አይደለም።” እኛም ለሌሎች እንደምናስብ የምናሳይ ከሆነ ማጽናኛ በመስጠት ረገድ ይሳካልናል።
19. ሌሎችን ‘በእጅጉ ለማጽናናት’ ቁርጥ ውሳኔ ያደረግከው ለምንድን ነው?
19 ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ይበልጥ እየቀረብን ስንሄድ የዓለም ሁኔታዎች እየተባባሱ እንደሚሄዱና ሕይወት ይበልጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን እንጠብቃለን። (2 ጢሞ. 3:13) ከዚህም ሌላ ፍጹማን ባለመሆናችን በምንሠራቸው ስህተቶች የተነሳ ማጽናኛ ሊያስፈልገን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ በታማኝነት መጽናት እንዲችል የረዳው አንዱ ነገር የእምነት ባልንጀሮቹ የሰጡት ማጽናኛ ነው። እንግዲያው እኛም እንደ አርስጥሮኮስ ታማኝ፣ እንደ ቲኪቆስ እምነት የሚጣልብን እንዲሁም እንደ ማርቆስ ሌሎችን በፈቃደኝነት የምናገለግል ሰዎች እንሁን። ይህን ስናደርግ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ መርዳት እንችላለን።—1 ተሰ. 3:2, 3
a ሐዋርያው ጳውሎስ በሕይወቱ ውስጥ በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። በእነዚያ ከባድ ጊዜያት፣ አንዳንድ የሥራ አጋሮቹ በእጅጉ አጽናንተውታል። እነዚህ የሥራ አጋሮቹ እሱን በማጽናናት ረገድ እንዲሳካላቸው ያደረጉ ሦስት ባሕርያትን በዚህ ርዕስ ላይ እንመረምራለን። በተጨማሪም የእነሱን ምሳሌ መከተል የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመለከታለን።
b በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ጳውሎስ የመርከብ መሰበር አደጋ በገጠመው ወቅት አርስጥሮኮስ አብሮት ነበር።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ ቲኪቆስ የጳውሎስን ደብዳቤዎች ለጉባኤዎቹ እንዲያደርስ አደራ ተሰጥቶት ነበር።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ ማርቆስ፣ ጳውሎስ የሚያስፈልጉትን ነገሮች አድርጎለታል።