የጥናት ርዕስ 30
በእውነት ውስጥ መመላለሳችሁን ቀጥሉ
“ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም።”—3 ዮሐ. 4
መዝሙር 54 “መንገዱ ይህ ነው”
ማስተዋወቂያa
1. በ3 ዮሐንስ 3, 4 ላይ እንደተጠቀሰው የሚያስደስተን ነገር ምንድን ነው?
ሐዋርያው ዮሐንስ እውነትን እንዲማሩ የረዳቸው ሰዎች ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ እንደሆነ ሲሰማ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን አስቡት! እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ብዙ ችግር አጋጥሟቸዋል፤ ዮሐንስም የመንፈሳዊ ልጆቹን እምነት ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር። እኛም በተመሳሳይ ልጆቻችንም ሆኑ ጥናቶቻችን ራሳቸውን ለይሖዋ ሲወስኑና እሱን በጽናት ሲያገለግሉ በእጅጉ እንደሰታለን።—3 ዮሐንስ 3, 4ን አንብብ።
2. የዮሐንስ ደብዳቤዎች ዓላማ ምን ነበር?
2 በ98 ዓ.ም. ዮሐንስ ይኖር የነበረው በኤፌሶን ውስጥ ወይም በአቅራቢያዋ ሳይሆን አይቀርም። እዚያ የሄደው በግዞት ይኖር ከነበረባት ከጳጥሞስ ደሴት ከወጣ በኋላ ሊሆን ይችላል። በዚያ ወቅት የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ሦስት ደብዳቤዎችን እንዲጽፍ አነሳሳው። የእነዚህ ደብዳቤዎች ዓላማ ታማኝ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩና በእውነት ውስጥ መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታታት ነበር።
3. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?
3 በወቅቱ በሕይወት የቀረው ሐዋርያ ዮሐንስ ብቻ ነበር፤ ዮሐንስ ሐሰተኛ አስተማሪዎች በጉባኤዎቹ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አሳስቦት ነበር።b (1 ዮሐ. 2:18, 19, 26) እነዚህ ከሃዲዎች አምላክን እንደሚያውቁ ቢናገሩም የይሖዋን ትእዛዛት አያከብሩም ነበር። እስቲ ዮሐንስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ምክር እንመርምር። ይህን ስናደርግ ሦስት ጥያቄዎችን እንመልሳለን፦ በእውነት ውስጥ መመላለስ ሲባል ምን ማለት ነው? እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮች የትኞቹ ናቸው? በእውነት ውስጥ ለመጽናት አንዳችን ሌላውን መርዳት የምንችለውስ እንዴት ነው?
በእውነት ውስጥ መመላለስ ሲባል ምን ማለት ነው?
4. በ1 ዮሐንስ 2:3-6 እና በ2 ዮሐንስ 4, 6 መሠረት በእውነት ውስጥ ለመመላለስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 በእውነት ውስጥ ለመመላለስ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት ማወቅ ይኖርብናል። በተጨማሪም ‘የይሖዋን ትእዛዛት መፈጸም’ አለብን። (1 ዮሐንስ 2:3-6ን እና 2 ዮሐንስ 4, 6ን አንብብ።) ይሖዋን በመታዘዝ ረገድ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። በመሆኑም ይሖዋን መታዘዝ የምንችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል ነው።—ዮሐ. 8:29፤ 1 ጴጥ. 2:21
5. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል?
5 በእውነት ውስጥ መመላለሳችንን ለመቀጠል ይሖዋ የእውነት አምላክ መሆኑንና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚነግረን ነገር በሙሉ እውነት መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይኖርብናል። በተጨማሪም ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለብን። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መሾሙን ይጠራጠራሉ። ዮሐንስ ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ በሚገልጸው እውነት ላይ ጠንካራ እምነት የሌላቸውን ሰዎች ሊያታልሉ የሚችሉ “ብዙ አሳቾች” እንዳሉ ተናግሮ ነበር። (2 ዮሐ. 7-11) “ኢየሱስን፣ ክርስቶስ አይደለም ብሎ ከሚክድ በቀር ውሸታም ማን ነው?” በማለት ዮሐንስ ጽፏል። (1 ዮሐ. 2:22) ራሳችንን ከእነዚህ አሳቾች መጠበቅ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ የአምላክን ቃል ማጥናት ነው። ይሖዋንና ኢየሱስን ማወቅ የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። (ዮሐ. 17:3) እውነትን ማግኘታችንን እርግጠኛ መሆን የምንችለውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው።
እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
6. ወጣት ክርስቲያኖች ከሚያጋጥሟቸው እንቅፋቶች አንዱ ምንድን ነው?
6 ሁሉም ክርስቲያኖች በዓለማዊ ፍልስፍና ላለመታለል መጠንቀቅ አለባቸው። (1 ዮሐ. 2:26) በተለይ ወጣት ክርስቲያኖች በዚህ ወጥመድ ላለመያዝ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በፈረንሳይ የምትኖረው የ25 ዓመቷ አሌክሲያc እንዲህ ብላለች፦ “ተማሪ እያለሁ በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብና በሌሎች ዓለማዊ ፍልስፍናዎች ምክንያት ግራ ተጋብቼ ነበር። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያሉት ትምህርቶች ይማርኩኝ ነበር። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ለመረዳት ጥረት ሳላደርግ በትምህርት ቤት የምማረውን ነገር ብቻ ማመን ተገቢ እንዳልሆነ ተሰማኝ።” አሌክሲያ ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (በአማርኛ አይገኝም) የተባለውን መጽሐፍ አጠናች። ከዚያም ያደረባት ጥርጣሬ ሁሉ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተወገደ። አሌክሲያ እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን እንደያዘ ለራሴ አረጋገጥኩ። እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መመራት ደስታና ሰላም እንደሚሰጠኝ ተገነዘብኩ።”
7. ምን ከማድረግ መቆጠብ አለብን? ለምንስ?
7 ወጣት አዋቂ ሳይል ሁሉም ክርስቲያኖች ሁለት ዓይነት ሕይወት ከመምራት መቆጠብ አለባቸው። ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት እየመራን በእውነት ውስጥ መመላለስ እንደማንችል ዮሐንስ ተናግሯል። (1 ዮሐ. 1:6) አሁንም ሆነ ወደፊት የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለግን የምናደርገው ነገር በሙሉ በይሖዋ ፊት የተገለጠ መሆኑን እንደምናውቅ በሚያሳይ መንገድ ሕይወታችንን መምራት አለብን። ደግሞም ድብቅ ኃጢአት የሚባል ነገር የለም፤ ምክንያቱም ይሖዋ የምናደርገውን ነገር በሙሉ ይመለከታል።—ዕብ. 4:13
8. የትኛውን አመለካከት መቃወም ይኖርብናል?
8 ዓለም ለኃጢአት ያለውን አመለካከት መቃወም ይኖርብናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “‘ኃጢአት የለብንም’ ብለን የምንናገር ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐ. 1:8) በዮሐንስ ዘመን ከሃዲዎች አንድ ሰው ሆን ብሎ በኃጢአት ጎዳና እየተመላለሰ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንደሚችል ያስተምሩ ነበር። በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ሰዎችም ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው። ብዙዎች በአምላክ እንደሚያምኑ ቢናገሩም ይሖዋ ለኃጢአት ያለውን አመለካከት በተለይ ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ የሚሰጠውን መመሪያ አይቀበሉም። ይሖዋ እንደ ኃጢአት አድርጎ የሚቆጥራቸውን ድርጊቶች የምርጫ ጉዳይ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል።
9. ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ለማክበር ጥረት ማድረጋቸው ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?
9 በተለይ ወጣት ክርስቲያኖች ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ አብረዋቸው የሚማሩ ልጆች ወይም የሥራ ባልደረቦቻቸው ያላቸውን አመለካከት እንዲቀበሉ ጫና ሊደረግባቸው ይችላል። አሌክሳንደር እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ተማሪ እያለሁ አንዳንድ ሴቶች የፆታ ግንኙነት እንድፈጽም ሊገፋፉኝ ይሞክሩ ነበር። የሴት ጓደኛ የሌለኝ ግብረ ሰዶማዊ ስለሆንኩ እንደሆነ ይናገሩ ነበር።” አንተም እንዲህ ያለ ፈተና ሊያጋጥምህ ይችላል፤ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ለማክበር ጥረት ማድረግህ ለራስህ አክብሮት እንዲኖርህ፣ ጤንነትህ እንዲጠበቅ፣ ስሜትህ እንዳይጎዳ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለህ ወዳጅነት የጠበቀ እንዲሆን እንደሚረዳህ አስታውስ። የሚያጋጥምህን ፈተና በተቋቋምክ ቁጥር ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ቀላል እየሆነልህ ይሄዳል። ደግሞም ዓለም ስለ ፆታ ሥነ ምግባር ያለው የተዛባ አመለካከት የሚመነጨው ከሰይጣን እንደሆነ አትርሳ። በመሆኑም የዓለምን አመለካከት ስትቃወም ‘ክፉውን እያሸነፍክ’ ነው።—1 ዮሐ. 2:14
10. አንደኛ ዮሐንስ 1:9 ይሖዋን በንጹሕ ሕሊና እንድናገለግል የሚረዳን እንዴት ነው?
10 ይሖዋ የትኞቹ ድርጊቶች ኃጢአት እንደሆኑ የመወሰን መብት እንዳለው እንገነዘባለን። እንዲሁም ኃጢአት ላለመሥራት የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። ሆኖም ኃጢአት ከሠራን በደላችንን ለይሖዋ በጸሎት እንናዘዛለን። (1 ዮሐንስ 1:9ን አንብብ።) ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን ደግሞ ይሖዋ እኛን እንዲንከባከቡ የሾማቸውን ሽማግሌዎች እርዳታ እንጠይቃለን። (ያዕ. 5:14-16) ያም ቢሆን ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት መዋጥ አይኖርብንም። ለምን? ምክንያቱም አፍቃሪ አባታችን የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ ሲል ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቶናል። ይሖዋ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ሙሉ በሙሉ ይቅር ይላል። በመሆኑም ይሖዋን በንጹሕ ሕሊና ከማገልገል ሊያግደን የሚችል አንድም ነገር የለም።—1 ዮሐ. 2:1, 2, 12፤ 3:19, 20
11. እምነታችንን ሊያዳክሙ ከሚችሉ ትምህርቶች አእምሯችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
11 የከሃዲዎችን ትምህርት መቃወም አለብን። የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ዲያብሎስ በርካታ አታላይ ሰዎችን በመጠቀም በአምላክ ታማኝ አገልጋዮች አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ ለመዝራት ሲሞክር ቆይቷል። በመሆኑም እውነቱን ከውሸቱ የመለየት ችሎታ ልናዳብር ይገባል።d ጠላቶቻችን በኢንተርኔት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቅመው በይሖዋ ላይ ያለንን እምነትና ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ለማዳከም ሊሞክሩ ይችላሉ። እንዲህ ካለው ፕሮፓጋንዳ በስተ ጀርባ ያለው ማን እንደሆነ በማስታወስ አጥብቃችሁ ተቃወሙት!—1 ዮሐ. 4:1, 6፤ ራእይ 12:9
12. ለተማርናቸው እውነቶች ያለንን አድናቆት ማሳደግ ያለብን ለምንድን ነው?
12 የሰይጣንን ጥቃቶች ለመቋቋም በኢየሱስና እሱ በአምላክ ዓላማ ውስጥ በሚጫወተው ሚና ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ይኖርብናል። በተጨማሪም ይሖዋ በዚህ ዘመን ድርጅቱን ለመምራት በሚጠቀምበት ብቸኛ መስመር ላይ እምነት ማሳደር አለብን። (ማቴ. 24:45-47) የአምላክን ቃል አዘውትረን በማጥናት እምነታችንን ማጠናከር እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ እምነታችን ሥሩን መሬት ውስጥ በጥልቀት እንደሰደደ ዛፍ ይሆናል። ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኘው ጉባኤ በጻፈበት ወቅት ተመሳሳይ ሐሳብ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደተቀበላችሁት ሁሉ ከእሱ ጋር በአንድነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ፤ በተማራችሁት መሠረት በእሱ ላይ ሥር ሰዳችሁና ታንጻችሁ ኑሩ፤ እንዲሁም በእምነት ጸንታችሁ መኖራችሁን ቀጥሉ።” (ቆላ. 2:6, 7) እምነቱን ለማጠናከር ጥረት የሚያደርግ ክርስቲያን ሰይጣንም ሆነ ግብረ አበሮቹ በሚሰነዝሩት ጥቃት አይናወጥም።—2 ዮሐ. 8, 9
13. ምን መጠበቅ ይኖርብናል? ለምንስ?
13 ዓለም እንደሚጠላን መጠበቅ ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 3:13) ዮሐንስ ‘መላው ዓለም በክፉው ቁጥጥር ሥር እንደሆነ’ ተናግሯል። (1 ዮሐ. 5:19) ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው በተቃረበ መጠን የሰይጣን ቁጣም እየጨመረ ይሄዳል። (ራእይ 12:12) በመሆኑም ዲያብሎስ እንደ ሥነ ምግባር ፈተናና እንደ ከሃዲዎች ትምህርት ያሉ ስውር ጥቃቶችን በመሰንዘር ብቻ አይወሰንም። የኃይል ጥቃትም ይሰነዝራል። ሰይጣን የስብከቱን ሥራ ለማስቆም ወይም እምነታችንን ለማዳከም መሞከር የሚችልበት ጊዜ እያለቀ እንደሆነ ያውቃል። ከዚህ አንጻር በተለያዩ አገሮች ውስጥ ሥራችን የታገደ ወይም ገደብ የተጣለበት መሆኑ አያስገርምም። ያም ቢሆን በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጸንተው ቆመዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ክፉው ምንም ዓይነት ጥቃት ቢሰነዝር ድል ማድረግ እንደምንችል የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።
በእውነት ውስጥ ለመጽናት እርስ በርስ ተረዳዱ
14. ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በእውነት ውስጥ እንዲጸኑ መርዳት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
14 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እውነት ውስጥ እንዲጸኑ ለመርዳት ርኅራኄ ማሳየት ያስፈልገናል። (1 ዮሐ. 3:10, 11, 16-18) ሁሉ ነገር በተመቻቸበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜም ጭምር እርስ በርስ መዋደድ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚወደውን ሰው በሞት በማጣቱ ምክንያት ማጽናኛ ወይም ሌላ ዓይነት እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው ታውቃለህ? አሊያም ደግሞ አንዳንድ ወንድሞች በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ንብረታቸውን እንዳጡ እንዲሁም የስብሰባ አዳራሻቸው ወይም ቤታቸው ጥገና እንደሚያስፈልገው ሰምተህ ይሆን? ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅርና ርኅራኄ ጠንካራ መሆኑ በዋነኝነት የሚታየው በንግግራችን ሳይሆን በተግባራችን ነው።
15. በ1 ዮሐንስ 4:7, 8 ላይ እንደተገለጸው ምን ማድረግ ይኖርብናል?
15 እርስ በርስ በመዋደድ በሰማይ የሚኖረውን አፍቃሪ አባታችንን መምሰል እንችላለን። (1 ዮሐንስ 4:7, 8ን አንብብ።) ፍቅር ማሳየት የምንችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ እርስ በርስ ይቅር መባባል ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ስሜታችንን ከጎዳው በኋላ ይቅርታ ሊጠይቀን ይችላል። ይህን ሰው ይቅር በማለትና በደሉን በመርሳት ፍቅር ማሳየት እንችላለን። (ቆላ. 3:13) አልዶ የተባለ ወንድም እንዲህ ያለ ፈተና አጋጥሞት ነበር፤ አልዶ አንድ የሚያከብረው ወንድም የእሱን ጎሳ በሚመለከት ደግነት የጎደለው ንግግር ሲናገር ሰማ። አልዶ “ስለዚህ ወንድም አሉታዊ አመለካከት ላለመያዝ እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ በተደጋጋሚ ጸለይኩ” በማለት ተናግሯል። ሆኖም አልዶ በዚህ ብቻ አልተወሰነም። ያንን ወንድም አብሮት አገልግሎት እንዲወጣ ጠየቀው። አብረው ሲያገለግሉ አልዶ ወንድም በተናገረው ነገር ስሜቱ እንደተጎዳ ገለጸለት። አልዶ እንዲህ ብሏል፦ “ወንድም እሱ በተናገረው ነገር ስሜቴ እንደተጎዳ ሲሰማ ይቅርታ ጠየቀኝ። በተናገረው ነገር ምን ያህል እንደተጸጸተ ከድምፁ ቃና መረዳት ቻልኩ። ከዚያም ቅሬታችንን ፈተን ወዳጅነታችንን አደስን።”
16-17. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
16 ሐዋርያው ዮሐንስ ለወንድሞቹ ፍቅር ስለነበረው ለመንፈሳዊ ደህንነታቸው ከልቡ ያስብ ነበር፤ በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው ሦስት ደብዳቤዎች ላይ የሰጠው ምክር ይህን በግልጽ ያሳያል። እንደ እሱ ያሉ ወንዶችና ሴቶች ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች ለመሆን እንደተቀቡ ማወቅ ምንኛ የሚያበረታታ ነው!—1 ዮሐ. 2:27
17 እስካሁን የተመለከትናቸውን ምክሮች በተግባር ማዋል ይኖርብናል። በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ይሖዋን በመታዘዝ በእውነት ውስጥ ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የአምላክን ቃል አንብቡ፤ እንዲሁም በቃሉ ተማመኑ። በኢየሱስ ላይ ጠንካራ እምነት አዳብሩ። ዓለማዊ ፍልስፍናዎችንና የከሃዲዎችን ትምህርት ተቃወሙ። ሁለት ዓይነት ሕይወት ከመምራትና በኃጢአት ከመውደቅ ተቆጠቡ። ይሖዋ ባወጣቸው ላቅ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተመሩ። እንዲሁም የበደሉንን ይቅር በማለትና እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ በማበርከት ወንድሞቻችን ጸንተው እንዲኖሩ እንርዳቸው። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በእውነት ውስጥ መመላለሳችንን መቀጠል እንችላለን።
መዝሙር 49 የይሖዋን ልብ ማስደሰት
a የምንኖረው የውሸት አባት የሆነው ሰይጣን በሚገዛው ዓለም ውስጥ ነው። በመሆኑም በእውነት ውስጥ መመላለስ ከፍተኛ ትግል ይጠይቅብናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ፈተና አጋጥሟቸው ነበር። ይሖዋ እነዚህን ክርስቲያኖችም ሆነ እኛን ለመርዳት ሲል ሐዋርያው ዮሐንስ ሦስት ደብዳቤዎችን እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል። እነዚህ ደብዳቤዎች የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች ለይተን ለማወቅ እንዲሁም ፈተናዎቹን ማሸነፍ የምንችልበትን መንገድ ለመገንዘብ ይረዱናል።
b “የዮሐንስ ደብዳቤዎች የተጻፉበት ዓላማ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
c አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
d በነሐሴ 2018 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የተሟላ መረጃ አለህ?” የሚለውን የጥናት ርዕስ ተመልከት።
f የሥዕሉ መግለጫ፦ ትምህርት ቤት ያለች አንዲት ወጣት ግብረ ሰዶማዊነትን በሚያበረታታ ብዙ ፕሮፓጋንዳ ተከባለች። (በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የቀስተ ደመና ቀለሞች ግብረ ሰዶማዊነትን ያመለክታሉ።) በኋላም በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ላይ ያላትን እምነት ለማጠናከር ጊዜ ወስዳ ምርምር ታደርጋለች። ይህም ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማት ለመቋቋም ረድቷታል።