የጥናት ርዕስ 35
“እርስ በርስ ተናነጹ”
“እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።”—1 ተሰ. 5:11
መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ
ማስተዋወቂያa
1. በ1 ተሰሎንቄ 5:11 መሠረት ሁላችንም በየትኛው ሥራ እንካፈላለን?
ጉባኤያችሁ የስብሰባ አዳራሽ ገንብቶ ወይም አድሶ ያውቃል? ከሆነ በአዲሱ አዳራሽ ያደረጋችሁትን የመጀመሪያ ስብሰባ እንደምታስታውስ ጥያቄ የለውም። ይሖዋን በጣም አመስግነኸው መሆን አለበት። እንዲያውም የደስታ እንባ ስለተናነቀህ የመክፈቻውን መዝሙር መዘመር ከብዶህ ሊሆን ይችላል። በጥራት የተገነቡት የስብሰባ አዳራሾቻችን ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣሉ። ሆኖም በሌላ ዓይነት የግንባታ ወይም የማነጽ ሥራ ስንካፈል ለይሖዋ ይበልጥ ውዳሴ እናመጣለን። ይህ ሥራ ቃል በቃል ሕንፃዎችን ከማነጽ የበለጠ ዋጋ አለው። ሥራው ወደነዚህ የአምልኮ ቦታዎች የሚመጡ ሰዎችን ማነጽን ይጠይቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ የጭብጡ ጥቅሳችን የሆነውን 1 ተሰሎንቄ 5:11ን የጻፈው ይህን ምሳሌያዊ የማነጽ ሥራ በአእምሮው ይዞ ነው።—ጥቅሱን አንብብ።
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን በማነጽ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ስሜታቸውን ይረዳላቸው ነበር። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ጳውሎስ ወንድሞቹና እህቶቹ (1) ፈተናዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ፣ (2) እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆኑ እንዲሁም (3) በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። እኛም የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል በዛሬው ጊዜ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ማነጽ የምንችለው እንዴት እንደሆነም እንመለከታለን።—1 ቆሮ. 11:1
ጳውሎስ ወንድሞቹና እህቶቹ ፈተናዎችን በጽናት እንዲቋቋሙ ረድቷቸዋል
3. ጳውሎስ ሚዛናዊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
3 ጳውሎስ ወንድሞቹን በጣም ይወዳቸው ነበር። እሱ ራሱም የተለያዩ ችግሮችን አስተናግዷል፤ በመሆኑም የእምነት ባልንጀሮቹ ፈተና ሲያጋጥማቸው ሊራራላቸውና ስሜታቸውን ሊረዳላቸው ችሏል። በአንድ ወቅት ጳውሎስ ገንዘብ ስላለቀበት ራሱንና የአገልግሎት አጋሮቹን ለማስተዳደር ሥራ መፈለግ ነበረበት። (ሥራ 20:34) ጳውሎስ ድንኳን የመሥራት ሙያ ነበረው። ቆሮንቶስ ሲደርስ መጀመሪያ ላይ እንደ እሱ ድንኳን ሠሪዎች ከሆኑት ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር ይሠራ ነበር። ሆኖም “በየሰንበቱ” ለአይሁዳውያንና ለግሪካውያን ይሰብክ ነበር። ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመጡ በኋላ ደግሞ “ጳውሎስ ቃሉን በመስበኩ ሥራ በእጅጉ ተጠመደ።” (ሥራ 18:2-5) ጳውሎስ የሕይወቱ ዋነኛ ዓላማ ይሖዋን ማገልገል መሆኑን ዘንግቶ አያውቅም። ጳውሎስ ተግቶ በመሥራት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ስለነበር ወንድሞቹንና እህቶቹን ማበረታታት ችሏል። የሕይወት ውጣ ውረድ እንዲሁም ቤተሰብን የማስተዳደር ኃላፊነታቸው “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ማለትም ከይሖዋ አምልኮ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ችላ እንዲሉ እንዳያደርጋቸው አሳስቧቸዋል።—ፊልጵ. 1:10
4. ጳውሎስና ጢሞቴዎስ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ስደትን እንዲቋቋሙ የረዷቸው እንዴት ነው?
4 በተሰሎንቄ ያለው ጉባኤ ከተቋቋመ ብዙም ሳይቆይ አዲሶቹ አማኞች ከባድ ተቃውሞ አጋጠማቸው። በቁጣ የተሞሉት ተቃዋሚዎች ጳውሎስንና ሲላስን ሲያጧቸው “አንዳንድ ወንድሞችን እየጎተቱ ወስደው የከተማዋ ገዢዎች ፊት በማቅረብ ‘[እነዚህ ሰዎች] የቄሳርን ሕግ የሚቃረን ነገር ያደርጋሉ’” በማለት ጮኹ። (ሥራ 17:6, 7) አዲሶቹ ክርስቲያኖች የከተማዋ ሰዎች እንደተነሱባቸው ሲያዩ ምን ያህል ተደናግጠው ይሆን! ሁኔታው የአገልግሎት ቅንዓታቸውን ሊያቀዘቅዝባቸው ይችል ነበር፤ ሆኖም ጳውሎስ ይህ እንዲሆን አልፈለገም። እሱና ሲላስ ከተማዋን ለቀው ለመሄድ ቢገደዱም አዲሱ ጉባኤ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያገኝ አድርገዋል። ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እምነታችሁ ይጠነክር ዘንድ እንዲያጸናችሁ እንዲሁም እንዲያበረታታችሁ ጢሞቴዎስን ላክንላችሁ፤ . . . የላክነውም ማንም በእነዚህ መከራዎች እንዳይናወጥ ነው።” (1 ተሰ. 3:2, 3) ጢሞቴዎስ ባደገባት ከተማ በልስጥራ ስደት አጋጥሞት እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። ጳውሎስ በዚያ ያሉትን ክርስቲያኖች እንዴት እንዳበረታታቸው ተመልክቷል። በተጨማሪም ጢሞቴዎስ፣ ይሖዋ የልስጥራን ክርስቲያኖች እንዴት እንደባረካቸው አይቷል፤ በመሆኑም ይሖዋ እነሱንም እንደሚረዳቸውና እንደሚባርካቸው በመግለጽ አዲሶቹን ክርስቲያኖች ሊያበረታታቸው ይችላል።—ሥራ 14:8, 19-22፤ ዕብ. 12:2
5. ብራያንት የተባለ ወንድም አንድ ሽማግሌ ከሰጠው እርዳታ የተጠቀመው እንዴት ነው?
5 ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን ያበረታታቸው ሌላስ በምን መንገድ ነው? ጳውሎስና በርናባስ ልስጥራን፣ ኢቆንዮንን እና አንጾኪያን በድጋሚ በጎበኙበት ወቅት “በየጉባኤው ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው።” (ሥራ 14:21-23) እነዚህ ሽማግሌዎች ለጉባኤዎቹ የመጽናኛ ምንጭ እንደሆኑላቸው ምንም ጥያቄ የለውም። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም ለወንድሞች የመጽናኛ ምንጭ ናቸው። ብራያንት የተባለ ወንድም የሰጠውን ሐሳብ እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “የ15 ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ትቶን ሄደ፤ እናቴ ደግሞ ተወገደች። ብቻዬን እንደተተውኩ ተሰማኝ፤ ቅስሜ ተሰብሮ ነበር።” ብራያንት ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ቶኒ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ በስብሰባዎች ወቅትና በሌሎች ጊዜያት ያዋራኝ ነበር። ፈተና ቢያጋጥማቸውም ደስታቸውን ስለጠበቁ ሰዎች ይነግረኝ ነበር። መዝሙር 27:10ን አነበበልኝ፤ እንዲሁም አባቱ ጥሩ ምሳሌ ባይሆንለትም ይሖዋን በታማኝነት ስላገለገለው ስለ ሕዝቅያስ ብዙ ጊዜ ይነግረኝ ነበር።” ብራያንት በዚህ መልኩ ያገኘው እርዳታ የጠቀመው እንዴት ነው? እንዲህ ብሏል፦ “በቶኒ ማበረታቻ ከጊዜ በኋላ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል እርካታ የሚያስገኝ ሕይወት መምራት ጀመርኩ።” ሽማግሌዎች፣ እንደ ብራያንት የሚያበረታታ “መልካም ቃል” መስማት የሚያስፈልጋቸውን ክርስቲያኖች ለመርዳት ንቁ ሁኑ።—ምሳሌ 12:25
6. ጳውሎስ ወንድሞቹንና እህቶቹን ለማበረታታት የሕይወት ታሪኮችን የተጠቀመው እንዴት ነው?
6 ጳውሎስ በይሖዋ እርዳታ ፈተናዎችን መቋቋም የቻለ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” እንዳለ የእምነት ባልንጀሮቹን አስታውሷቸዋል። (ዕብ. 12:1) ጳውሎስ ወንድሞችና እህቶች፣ ባለፉት ዘመናት የተለያዩ ዓይነት ፈተናዎችን በጽናት የተቋቋሙ የአምላክ አገልጋዮችን የሕይወት ታሪክ መስማታቸው ድፍረት እንደሚሰጣቸውና ‘በሕያው አምላክ ከተማ’ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚረዳቸው ተገንዝቦ ነበር። (ዕብ. 12:22) በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ ጌድዮንን፣ ባርቅን፣ ዳዊትን፣ ሳሙኤልንና ሌሎችን እንዴት እንደረዳቸው አንብቦ ያልተበረታታ ማን አለ? (ዕብ. 11:32-35) በዛሬው ጊዜ ስላሉ የእምነት ምሳሌዎችስ ምን ማለት ይቻላል? በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ በዘመናችን የኖሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችን የሕይወት ታሪክ በማንበባቸው እምነታቸው እንደተጠናከረ የሚገልጹ ደብዳቤዎችን ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ይልካሉ።
ጳውሎስ ወንድሞቹና እህቶቹ እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል
7. በሮም 14:19-21 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው የጳውሎስ ምክር ምን ትምህርት እናገኛለን?
7 በጉባኤ ውስጥ ሰላም ለማስፈን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ማነጽ እንችላለን። የአመለካከት ልዩነት እንዲከፋፍለን አንፈቅድም። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ’ ብለን ድርቅ አንልም። አንድ ምሳሌ እንመልከት። በሮም በነበረው ጉባኤ ውስጥ ከአይሁዳውያንም ሆነ ከአሕዛብ የተውጣጡ ክርስቲያኖች ነበሩ። የሙሴ ሕግ ሲሻር አንዳንድ ምግቦችን ከመብላት ጋር በተያያዘ የነበሩት ገደቦች ተነሱ። (ማር. 7:19) ከዚያ ጊዜ አንስቶ አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ሁሉንም ዓይነት ምግብ ለመብላት ነፃነት ይሰማቸው ነበር። ሌሎች አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ግን ይህን ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አልተሰማቸውም። በዚህም የተነሳ በጉባኤው ውስጥ ክፍፍል ተፈጠረ። ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የሰላምን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል፦ “ወንድምህ የሚሰናከልበት ከሆነ ሥጋ አለመብላት፣ የወይን ጠጅ አለመጠጣት ወይም ማንኛውንም የሚያሰናክል ነገር አለማድረግ የተሻለ ነው።” (ሮም 14:19-21ን አንብብ።) በዚህ መንገድ ጳውሎስ፣ እንዲህ ያሉት ግጭቶች ግለሰቦችንም ሆነ መላውን ጉባኤ እንደሚጎዱ የእምነት ባልንጀሮቹን አስገንዝቧቸዋል። ከዚህም ሌላ ጳውሎስ ሌሎችን ላለማሰናከል ሲል ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። (1 ቆሮ. 9:19-22) እኛም በተመሳሳይ ለምርጫ በተተዉ ጉዳዮች ረገድ ድርቅ ባለማለት ሌሎችን ማነጽና ሰላም ማስፈን እንችላለን።
8. በአንድ አስፈላጊ ጉዳይ የተነሳ የጉባኤው ሰላም ሊደፈርስ በተቃረበበት ወቅት ጳውሎስ ምን አደረገ?
8 ስለ አስፈላጊ ጉዳዮች አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜም ሰላም በማስፈን ረገድ ጳውሎስ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው ጉባኤ ውስጥ አንዳንዶች ወደ ክርስትና የመጡ አሕዛብ መገረዝ እንዳለባቸው ይናገሩ ነበር፤ ይህን ያሉት የሌሎችን ትችት ለማስቀረት ብለው ሊሆን ይችላል። (ገላ. 6:12) ጳውሎስ ይህን አመለካከት ጨርሶ አልተቀበለውም፤ ሆኖም ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ’ ብሎ ድርቅ ከማለት ይልቅ ትሕትና በማሳየት ጉዳዩን በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች መራው። (ሥራ 15:1, 2) ጳውሎስ ጉዳዩን በዚያ መንገድ መያዙ በጉባኤው ውስጥ ሰላምና ደስታ እንዲሰፍን አድርጓል።—ሥራ 15:30, 31
9. የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
9 ከባድ አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ፣ ይሖዋ ጉባኤውን እንዲንከባከቡ ከሾማቸው አካላት መመሪያ በመፈለግ ሰላም ለማስፈን ጥረት እናደርጋለን። ብዙውን ጊዜ በጽሑፎቻችን ወይም ድርጅቱ በሚያወጣቸው መመሪያዎች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ማግኘት እንችላለን። የራሳችንን አመለካከት ከማራመድ ይልቅ እነዚህን መመሪያዎች በመከተል ላይ ትኩረት ካደረግን በጉባኤው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።
10. ጳውሎስ በጉባኤው ውስጥ ሰላም ለማስፈን ሌላስ ምን አድርጓል?
10 ጳውሎስ በወንድሞቹና በእህቶቹ ደካማ ጎን ላይ ሳይሆን በጠንካራ ጎናቸው ላይ በማተኮር ሰላም ለማስፈን ጥረት አድርጓል። ለምሳሌ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ መደምደሚያ ላይ በርካታ ሰዎችን በስም ጠቅሷል፤ ከብዙዎቹ ጋር በተያያዘ ደግሞ ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫ ወይም አዎንታዊ ሐሳብ አስፍሯል። እኛም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስላሏቸው መልካም ባሕርያት አዘውትረን በመናገር የጳውሎስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይበልጥ እንዲቀራረቡ እንረዳቸዋለን፤ ይህ ደግሞ ጉባኤው በፍቅር እንዲታነጽ ያደርጋል።
11. አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ሰላም ማስፈን የምንችለው እንዴት ነው?
11 አንዳንድ ጊዜ በጎለመሱ ክርስቲያኖች መካከልም እንኳ አለመግባባት ወይም ጭቅጭቅ ሊያጋጥም ይችላል። በጳውሎስና የቅርብ ጓደኛው በሆነው በበርናባስ መካከል እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ሁለቱ ሰዎች በቀጣዩ የሚስዮናዊ ጉዟቸው ላይ ማርቆስን ከመውሰድ ጋር በተያያዘ አለመግባባት አጋጥሟቸው ነበር። “በመካከላቸው ኃይለኛ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ተለያዩ።” (ሥራ 15:37-39) ሆኖም ጳውሎስ፣ በርናባስና ማርቆስ በመካከላቸው የተፈጠረውን ግጭት ፈትተዋል፤ ይህም ለጉባኤው ሰላምና አንድነት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ ያሳያል። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ስለ በርናባስና ስለ ማርቆስ አዎንታዊ ነገር ተናግሯል። (1 ቆሮ. 9:6፤ ቆላ. 4:10) እኛም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር አለመግባባት ሲፈጠር ችግሩን ወዲያውኑ ፈትተን በመልካም ጎናቸው ላይ ማተኮራችንን መቀጠል ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ሰላምና አንድነት እናሰፍናለን።—ኤፌ. 4:3
ጳውሎስ የወንድሞቹንና የእህቶቹን እምነት አጠናክሯል
12. ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የትኞቹ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል?
12 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ በመርዳት እነሱን ማነጽ እንችላለን። አንዳንዶች ከቤተሰቦቻቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ወይም አብረዋቸው ከሚማሩ ልጆች ፌዝ ይደርስባቸዋል። ሌሎች ከከባድ የጤና እክል ጋር ይታገላሉ፤ የስሜት መጎዳት ያጋጠማቸውም አሉ። ሌሎች ደግሞ ከተጠመቁ በርካታ ዓመታት ስላለፏቸው የዚህን ሥርዓት መጨረሻ ለረጅም ዘመን ሲጠብቁ ቆይተዋል። እነዚህ ሁኔታዎች በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችን እምነት ሊፈትኑ ይችላሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ አባላትም ተመሳሳይ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል። ታዲያ ጳውሎስ የወንድሞቹንና የእህቶቹን እምነት ለማጠናከር ምን አደረገ?
13. ጳውሎስ በእምነታቸው ምክንያት ፌዝ የሚደርስባቸውን ክርስቲያኖች የረዳቸው እንዴት ነው?
13 ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅሞ የወንድሞቹንና የእህቶቹን እምነት አጠናክሯል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የማያምኑ ቤተሰቦቻቸው የአይሁድ እምነት ከክርስትና እምነት የተሻለ እንደሆነ በመግለጽ ይተቿቸው ይሆናል፤ ምን ብለው እንደሚመልሱላቸውም ግራ ሊገባቸው ይችላል። ጳውሎስ ለዕብራውያን የጻፈላቸው ደብዳቤ እነዚህን ክርስቲያኖች አበረታቷቸው እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። (ዕብ. 1:5, 6፤ 2:2, 3፤ 9:24, 25) ጳውሎስ የተጠቀመባቸውን ጠንካራ የመከራከሪያ ነጥቦች በመጠቀም የተቃዋሚዎቻቸውን አፍ ማዘጋት ይችላሉ። በዛሬው ጊዜም ፌዝ የሚደርስባቸው የእምነት አጋሮቻችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ተጠቅመው ለእምነታቸው መሠረት የሆኑትን ማስረጃዎች እንዲያብራሩ ልንረዳቸው እንችላለን። ወጣቶች በፍጥረት በማመናቸው የተነሳ የሚፌዝባቸው ከሆነ ደግሞ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እንዲሁም የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች በሚሉት ብሮሹሮች ውስጥ የሚገኙትን መረጃዎች ተጠቅመው በፍጥረት የሚያምኑት ለምን እንደሆነ እንዲያብራሩ ልንረዳቸው እንችላለን።
14. ጳውሎስ በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ የተጠመደ ቢሆንም ምን አድርጓል?
14 ጳውሎስ ወንድሞቹና እህቶቹ ‘በመልካም ሥራዎች’ አማካኝነት ፍቅር እንዲያሳዩ አበረታቷቸዋል። (ዕብ. 10:24) ወንድሞቹንና እህቶቹን በንግግሩ ብቻ ሳይሆን በተግባሩም ረድቷቸዋል። ለምሳሌ በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች ረሃብ ባጋጠማቸው ወቅት ጳውሎስ ለእነሱ እርዳታ በማከፋፈሉ ሥራ ተካፍሏል። (ሥራ 11:27-30) እንዲያውም ጳውሎስ በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ የተጠመደ ቢሆንም ቁሳዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ክርስቲያኖች ለመርዳት ሁልጊዜ አጋጣሚ ይፈልግ ነበር። (ገላ. 2:10) እንዲህ በማድረግ፣ የእምነት ባልንጀሮቹ ይሖዋ እንደሚንከባከባቸው ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ ረድቷቸዋል። በዛሬው ጊዜም በአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ ለመካፈል ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ችሎታችንን ስናውል የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን እምነት እናጠናክራለን። ለዓለም አቀፉ ሥራ አዘውትረን መዋጮ ማድረጋችንም ተመሳሳይ ውጤት ያስገኛል። በእነዚህና በሌሎችም መንገዶች፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይተዋቸው እንዲተማመኑ እንረዳቸዋለን።
15-16. እምነታቸው የተዳከመባቸውን ክርስቲያኖች እንዴት ልንይዛቸው ይገባል?
15 ጳውሎስ እምነታቸው የተዳከመባቸውን ክርስቲያኖች ተስፋ አልቆረጠባቸውም። ርኅራኄ ያሳያቸው ከመሆኑም ሌላ ፍቅር በሚንጸባረቅበትና አዎንታዊ በሆነ መንገድ አነጋግሯቸዋል። (ዕብ. 6:9፤ 10:39) ለምሳሌ ያህል፣ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ “እኛ” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ይጠቀም ነበር፤ ይህም የሰጠውን ምክር እሱም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልገው አምኖ እንደተቀበለ ያሳያል። (ዕብ. 2:1, 3) እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም እምነታቸው የተዳከመባቸውን ክርስቲያኖች ተስፋ ሳንቆርጥ መርዳታችንን እንቀጥላለን። ለእነሱ ከልባችን ትኩረት በመስጠት እናንጻቸዋለን። በዚህ መንገድ ፍቅራችንን እናረጋግጥላቸዋለን። ሌሎችን የሚያንጸው የምንናገረው ቃል ብቻ ሳይሆን ፍቅርና ገርነት በሚንጸባረቅበት የድምፅ ቃና መናገራችንም እንደሆነ መዘንጋት የለብንም።
16 ጳውሎስ፣ ይሖዋ መልካም ሥራቸውን እንደሚያውቅ በመግለጽ ወንድሞቹንና እህቶቹን አጽናንቷቸዋል። (ዕብ. 10:32-34) እኛም እምነቱ የተዳከመበትን ክርስቲያን በምንረዳበት ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን። ወደ እውነት የመጣበትን መንገድ እንዲነግረን ልንጠይቀው እንዲሁም የይሖዋን እርዳታ ያየባቸውን ጊዜያት መለስ ብሎ እንዲያስብ ልናበረታታው እንችላለን። ከዚያም ይሖዋ ቀደም ሲል ያሳየውን ፍቅር እንዳልረሳ እንዲሁም ወደፊትም እንደማይተወው ልናረጋግጥለት እንችላለን። (ዕብ. 6:10፤ 13:5, 6) እንዲህ ያለው ውይይት፣ ግለሰቡ በይሖዋ አገልግሎት ለመቀጠል እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል።
“እርስ በርስ ተበረታቱ”
17. የትኞቹን ችሎታዎች ማዳበር እንችላለን?
17 አንድ የግንባታ ባለሙያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ክህሎቱን እያሻሻለ እንደሚሄድ ሁሉ እኛም ሌሎችን በማነጽ ረገድ ችሎታችንን ማሻሻል እንችላለን። ወንድሞቻችን የሚያጋጥማቸውን ፈተና በጽናት እንዲቋቋሙ ለመርዳት፣ ቀደም ሲል የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት የተቋቋሙ ሰዎችን ምሳሌ ልናካፍላቸው እንችላለን። ሌሎች ስላሏቸው መልካም ባሕርያት በመናገር፣ ሰላማችን አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ችግሩን ለመፍታት ጥረት በማድረግ እንዲሁም አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ለጉዳዩ እልባት በማበጀት ሰላም ማስፈን እንችላለን። በተጨማሪም ወሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በማካፈል፣ ተግባራዊ እርዳታ በመስጠት እንዲሁም በመንፈሳዊ የተዳከሙትን በመርዳት የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን እምነት ማጠናከር እንችላለን።
18. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
18 በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚካፈሉ ሰዎች ደስታና እርካታ ያገኛሉ። በመንፈሳዊው የግንባታ ወይም የማነጽ ሥራ በምንካፈልበት ጊዜም ደስታና እርካታ እናገኛለን። በጊዜ ሂደት ከሚያረጁትና ከሚፈራርሱት ሕንፃዎች በተለየ መልኩ መንፈሳዊው የማነጽ ሥራችን የሚያስገኘው ውጤት ለዘላለም ይዘልቃል። እንግዲያው ሁላችንም ‘እርስ በርስ መበረታታታችንን እንዲሁም እርስ በርስ መተናነጻችንን’ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—1 ተሰ. 5:11
መዝሙር 100 እንግዳ ተቀባይ ሁኑ
a በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሕይወት ከባድ ነው። የእምነት ባልንጀሮቻችን ብዙ ጫና ይደርስባቸዋል። እነሱን ማበረታታት የምንችልባቸውን መንገዶች የምንፈልግ ከሆነ በእጅጉ ልንረዳቸው እንችላለን። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ መመርመራችን ይጠቅመናል።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ አባት ልጁ ገና እንድታከብር የሚደርስባትን ተጽዕኖ ለመቋቋም በጽሑፎቻችን ውስጥ ያለውን ምክር መጠቀም የምትችለው እንዴት እንደሆነ ሲያሳያት።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ባልና ሚስት ወደ ሌላ የአገራቸው ክፍል ሄደው በአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ ሲካፈሉ።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እምነቱ የተዳከመበትን ወንድም ሄዶ ሲጠይቅ። ከዓመታት በፊት አብረው በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ሲካፈሉ የተነሷቸውን ፎቶግራፎች ያሳየዋል። ወንድም ፎቶግራፎቹን ሲመለከት ያሳለፉትን አስደሳች ጊዜ ያስታውሳል። ወንድም ይሖዋን ያገለግል በነበረበት ወቅት ይሰማው የነበረውን ደስታ መናፈቅ ይጀምራል። ከጊዜ በኋላ ወደ ጉባኤው ይመለሳል።