ይሖዋን በትዕግሥት ስትጠባበቁ ደስተኞች ሁኑ
ይሖዋ ክፋትን በሙሉ አስወግዶ ሁሉንም ነገር አዲስ የሚያደርግበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቃችሁ ነው? (ራእይ 21:1-5) ምንም ጥያቄ የለውም! ሆኖም በተለይ ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቅ ቀላል ላይሆን ይችላል። የዘገየ ተስፋ ልባችንን ሊያሳምመው ይችላል።—ምሳሌ 13:12
ያም ቢሆን ይሖዋ፣ እሱ በወሰነው ጊዜ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ በትዕግሥት እንድንጠብቅ ይፈልጋል። ይሖዋ እንዲህ እንድናደርግ የሚፈልገው ለምንድን ነው? ይሖዋን ስንጠባበቅ ደስተኞች ለመሆን የሚረዳንስ ምንድን ነው?
ይሖዋ በትዕግሥት እንድንጠብቅ የሚፈልገው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት ይጠባበቃል፤ ምሕረት ሊያሳያችሁም ይነሳል። ይሖዋ የፍትሕ አምላክ ነውና። እሱን በተስፋ የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።” (ኢሳ. 30:18) ኢሳይያስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ግትር ለሆኑት አይሁዳውያን ነበር። (ኢሳ. 30:1) ሆኖም በአይሁዳውያኑ መካከል አንዳንድ ታማኞች ነበሩ፤ እነዚህ ቃላት ለእነሱ ተስፋ ፈንጥቀውላቸዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም ከእነዚህ ቃላት ተስፋ ማግኘት ይችላሉ።
ስለዚህ ይሖዋ በትዕግሥት እየጠበቀ ስለሆነ እኛም በትዕግሥት ልንጠብቅ ይገባል። ይሖዋ ይህን ሥርዓት የሚያጠፋበትን ቀን ቀጥሯል፤ ያ ቀንና ሰዓት እስኪደርስ ድረስ እየጠበቀ ነው። (ማቴ. 24:36) ያ ጊዜ ሲደርስ፣ ዲያብሎስ በይሖዋና በአገልጋዮቹ ላይ የሰነዘረው ክስ ሐሰት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል። ያኔ ይሖዋ ሰይጣንንና ግብረ አበሮቹን ያጠፋቸዋል፤ ለእኛ ግን ‘ምሕረት ያሳየናል።’
እስከዚያው ግን፣ ይሖዋ ችግሮቻችንን ላያስወግድልን ቢችልም እንኳ በትዕግሥት በምንጠባበቅበት ጊዜ ደስተኞች መሆን እንደምንችል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ኢሳይያስ እንደገለጸው መልካም ነገር እስክናገኝ በተስፋ በምንጠባበቅበት ጊዜ ደስተኞች መሆን እንችላለን። (ኢሳ. 30:18) እንዲህ ያለውን ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ አራት ነገሮችን እንመልከት።
በምንጠብቅበት ጊዜ ደስተኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ አተኩሩ። ንጉሥ ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ብዙ ክፋት አይቷል። (መዝ. 37:35) ያም ቢሆን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በይሖዋ ፊት ዝም በል፤ እሱንም በተስፋ ተጠባበቅ። የጠነሰሰውን ሴራ በተሳካ ሁኔታ እየፈጸመ ባለ ሰው አትበሳጭ።” (መዝ. 37:7) ዳዊት በመዳን ተስፋው ላይ በማተኮር ይህን ምክር ሠርቶበታል። በተጨማሪም ከይሖዋ ላገኛቸው በረከቶች በሙሉ አመስጋኝ ነበር። (መዝ. 40:5) እኛም በዙሪያችን ባሉ አሉታዊ ነገሮች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ በሕይወታችን ውስጥ ባሉ አዎንታዊ ነገሮች ላይ ካተኮርን ይሖዋን መጠባበቅ ቀላል ይሆንልናል።
ይሖዋን በማወደስ ተጠመዱ። የመዝሙር 71 ጸሐፊ “እኔ ግን አንተን መጠባበቄን እቀጥላለሁ፤ በውዳሴ ላይ ውዳሴ አቀርብልሃለሁ” ብሏል። (መዝ. 71:14) ይህን መዝሙር የጻፈው ዳዊት ሳይሆን አይቀርም። ዳዊት ይሖዋን የሚያወድሰው እንዴት ነው? ስለ ይሖዋ ለሌሎች ይናገራል፤ እንዲሁም የውዳሴ መዝሙር ይዘምርለታል። (መዝ. 71:16, 23) እንደ ዳዊት እኛም ይሖዋን ስንጠባበቅ ደስታ ማግኘት እንችላለን። በአገልግሎታችን፣ በጭውውቶቻችን እንዲሁም በመዝሙሮቻችን አማካኝነት እናወድሰዋለን። በቀጣዩ ጊዜ የመንግሥቱን መዝሙር ስትዘምሩ አበረታች በሆኑት ስንኞች ላይ ለምን ትኩረት አታደርጉም?
ከወንድሞቻችሁና ከእህቶቻችሁ ማበረታቻ አግኙ። ዳዊት ፈተና ባጋጠመው ጊዜ “በታማኝ አገልጋዮችህ ፊት በስምህ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት ለይሖዋ ዘምሯል። (መዝ. 52:9) እኛም ከታማኝ የእምነት አጋሮቻችን ማበረታቻ ማግኘት እንችላለን። እንዲህ ያለውን ማበረታቻ የምናገኘው በስብሰባዎችና በአገልግሎት ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አጋጣሚዎች ስንገናኝም ጭምር ነው።—ሮም 1:11, 12
ተስፋችሁን አጠናክሩ። መዝሙር 62:5 “ዝም ብዬ አምላክን እጠባበቃለሁ፤ ምክንያቱም ተስፋዬ የሚመጣው ከእሱ ዘንድ ነው” ይላል። ጠንካራ ተስፋ በእርግጠኝነት መጠበቅን ይጨምራል። በተለይ የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በጠበቅነው ጊዜ ካልመጣ እንዲህ ያለው ጠንካራ ተስፋ ያስፈልገናል። ይሖዋ የገባው ቃል እስኪፈጸም ረጅም ጊዜ መጠበቅ ቢያስፈልገንም እንኳ ተስፋው መፈጸሙ እንደማይቀር ልንተማመን ይገባል። የአምላክን ቃል በማጥናት ተስፋችንን ማጠናከር እንችላለን። ለምሳሌ ትንቢቶችን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑን እንዲሁም ይሖዋ ስለ ራሱ የገለጠልንን ዝርዝር ጉዳዮች ማጥናት እንችላለን። (መዝ. 1:2, 3) በተጨማሪም ይሖዋ የሰጠን የዘላለም ሕይወት ተስፋ እስኪፈጸም በምንጠባበቅበት ወቅት ከእሱ ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንዲኖረን ‘በመንፈስ ቅዱስ መጸለያችንን’ ልንቀጥል ይገባል።—ይሁዳ 20, 21
እንደ ንጉሥ ዳዊት እናንተም ይሖዋ እሱን በትዕግሥት የሚጠባበቁትን በትኩረት እንደሚመለከት እንዲሁም ታማኝ ፍቅሩን እንደሚያሳያቸው እርግጠኞች ሁኑ። (መዝ. 33:18, 22) በሕይወታችሁ ውስጥ ባሉት አዎንታዊ ነገሮች ላይ በማተኮር፣ ይሖዋን በማወደስ፣ ከእምነት አጋሮቻችሁ ማበረታቻ በማግኘት እንዲሁም ውድ የሆነውን ተስፋችሁን በማጠናከር ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቃችሁን ቀጥሉ።