የጥናት ርዕስ 32
መዝሙር 44 የተቸገረ ሰው ጸሎት
ይሖዋ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ ይፈልጋል
“ይሖዋ . . . ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።”—2 ጴጥ. 3:9
ዓላማ
ንስሐ ምን እንደሆነ፣ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ይሖዋ ሁሉም ዓይነት ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
1. ንስሐ ምን ያካትታል?
ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ንስሐ መግባታችን የግድ አስፈላጊ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አንድ ሰው ንስሐ ገባ የሚባለው አንድን ምግባር በተመለከተ አመለካከቱን ሲቀይር፣ ያንን ድርጊት መፈጸሙን ሲያቆም እንዲሁም ድርጊቱን ላለመድገም ቁርጥ ውሳኔ ሲያደርግ ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፍቻ ላይ “ንስሐ” የሚለውን ተመልከት።
2. ሁላችንም ስለ ንስሐ መማር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ነህምያ 8:9-11)
2 ሁሉም ሰው ስለ ንስሐ መማር ያስፈልገዋል። ለምን? ምክንያቱም ሁላችንም በየዕለቱ ኃጢአት እንሠራለን። የአዳምና የሔዋን ዘሮች እንደመሆናችን መጠን እያንዳንዳችን ኃጢአትንና ሞትን ወርሰናል። (ሮም 3:23፤ 5:12) ከዚህ ነፃ የሆነ አንድም ሰው የለም። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉ ጠንካራ እምነት የነበራቸው ሰዎችም እንኳ ከኃጢአት ጋር መታገል አስፈልጓቸዋል። (ሮም 7:21-24) ይሁንና ይህ ሲባል በኃጢአታችን ምክንያት ሁልጊዜ መቆዘም ያስፈልገናል ማለት ነው? በፍጹም። ይሖዋ መሐሪ ነው፤ ደግሞም ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። በነህምያ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት። (ነህምያ 8:9-11ን አንብብ።) ይሖዋ ቀደም ሲል በፈጸሟቸው ኃጢአቶች የተነሳ በሐዘን ከመዋጥ ይልቅ ለእሱ በሚያቀርቡት አምልኮ ደስተኞች እንዲሆኑ ፈልጓል። ይሖዋ ንስሐ መግባት ደስታ እንደሚያስገኝ ያውቃል። ስለ ንስሐ የሚያስተምረን ለዚህ ነው። ለፈጸምናቸው ኃጢአቶች ንስሐ ከገባን መሐሪ የሆነው አባታችን ይቅር እንደሚለን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 እንግዲያው ስለ ንስሐ ይበልጥ ለማወቅ እንሞክር። በዚህ ርዕስ ውስጥ ከዚህ ጋር የተያያዙ ሦስት ነጥቦችን እንመለከታለን። በመጀመሪያ፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ስለ ንስሐ ምን እንዳስተማራቸው እናያለን። ቀጥሎም ይሖዋ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ ለመምራት ምን እንዳደረገ እንመለከታለን። በመጨረሻም ኢየሱስ ንስሐን በተመለከተ ለተከታዮቹ ምን እንዳስተማራቸው እንመረምራለን።
ይሖዋ ለእስራኤላውያን ስለ ንስሐ ምን አስተምሯቸዋል?
4. ይሖዋ ለእስራኤላውያን ስለ ንስሐ ምን አስተምሯቸዋል?
4 ይሖዋ እስራኤላውያንን በብሔር ደረጃ ባዋቀረበት ወቅት ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። የሰጣቸውን ሕጎች ካከበሩ እንደሚጠብቃቸው እንዲሁም እንደሚባርካቸው ቃል ገብቶላቸዋል። እነዚህን ሕጎች በተመለከተ እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቷቸዋል፦ “እኔ ዛሬ የማዝህ ይህ ትእዛዝ ለአንተ ያን ያህል ከባድ አይደለም፤ ከአንተም የራቀ አይደለም።” (ዘዳ. 30:11, 16) ይሁንና ሌሎች አማልክትን በማምለክ ወይም በሌላ መንገድ በእሱ ላይ ካመፁ በረከቱን ይወስድባቸዋል፤ እነሱም ለመከራ ይዳረጋሉ። ሆኖም ከዚያ በኋላም እንኳ የአምላክን ሞገስ መልሰው ማግኘት ይችሉ ነበር። ‘ወደ አምላካቸው ወደ ይሖዋ መመለስና ቃሉን መስማት’ ይችላሉ። (ዘዳ. 30:1-3, 17-20) በሌላ አባባል፣ ንስሐ መግባት ይችላሉ። እንዲህ ካደረጉ ይሖዋ ወደ እነሱ ይቀርባል፤ እንዲሁም በድጋሚ በረከቱን ያፈስላቸዋል።
5. ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ ተስፋ እንዳልቆረጠባቸው ያሳየው እንዴት ነው? (2 ነገሥት 17:13, 14)
5 የይሖዋ ሕዝቦች በተደጋጋሚ ዓምፀውበታል። ጣዖት ያመለኩ ከመሆኑም ሌላ ሌሎች አስጸያፊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል። በዚህም የተነሳ ለመከራ ተዳርገዋል። ይሁንና ይሖዋ ዓመፀኛ በሆኑት ሕዝቦቹ ላይ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። በተደጋጋሚ ወደ እነሱ ነቢያትን በመላክ ንስሐ እንዲገቡና ወደ እሱ እንዲመለሱ ያበረታታቸው ነበር።—2 ነገሥት 17:13, 14ን አንብብ።
6. ይሖዋ የንስሐን አስፈላጊነት ለሕዝቦቹ ለማስተማር በነቢያቱ የተጠቀመው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
6 ይሖዋ ነቢያቱን ተጠቅሞ ሕዝቦቹን ለማስጠንቀቅና ለማረም በተደጋጋሚ ሞክሯል። ለምሳሌ አምላክ በኤርምያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፣ ተመለሽ . . . እኔ ታማኝ ስለሆንኩ እናንተን በቁጣ አልመለከትም . . . ለዘላለም ቅር አልሰኝም። ብቻ የሠራሽውን በደል አምነሽ ተቀበይ፤ በአምላክሽ በይሖዋ ላይ ዓምፀሻልና።” (ኤር. 3:12, 13) በኢዩኤል አማካኝነት ደግሞ ይሖዋ “በሙሉ ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ” ብሏል። (ኢዩ. 2:12, 13) በተጨማሪም በኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤ ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አስወግዱ፤ መጥፎ ድርጊት መፈጸማችሁን አቁሙ።” (ኢሳ. 1:16-19) ከዚህም ሌላ በሕዝቅኤል አማካኝነት እንዲህ ሲል ጠይቋል፦ “እኔ በክፉ ሰው ሞት ደስ እሰኛለሁ? . . . እኔ ደስ የምሰኘው ከመንገዱ ቢመለስና በሕይወት ቢኖር አይደለም? እኔ በማንም ሰው ሞት ደስ አልሰኝም . . . ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።” (ሕዝ. 18:23, 32) ይሖዋ ሰዎች ንስሐ ሲገቡ ሲያይ ይደሰታል። ምክንያቱም በሕይወት መኖራቸውን እንዲቀጥሉ፣ አልፎ ተርፎም ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል! ስለዚህ ይሖዋ ኃጢአተኛ ለሆኑ ሰዎች የእርዳታ እጁን ለመዘርጋት ንስሐ እስኪገቡ ድረስ አይጠብቅም። ይህን የሚያሳዩ ሌሎች ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።
7. ይሖዋ የነቢዩ ሆሴዕንና የሚስቱን ምሳሌ በመጠቀም ለሕዝቦቹ ምን አስተምሯቸዋል?
7 ይሖዋ የነቢዩ ሆሴዕንና የሚስቱን የጎሜርን ምሳሌ በመጠቀም ለሕዝቦቹ ምን እንዳስተማራቸው ልብ በል። ጎሜር ምንዝር ከፈጸመች በኋላ ሆሴዕን ትታ ወደ ሌሎች ወንዶች ሄደች። ታዲያ ጎሜር ምንም ተስፋ የላትም ማለት ነው? ልብን ማንበብ የሚችለው ይሖዋ ሆሴዕን እንዲህ አለው፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሌሎች አማልክትን የሚከተሉ . . . ሆነው ሳለ ይሖዋ እንደወደዳቸው ሁሉ፣ አንተም ሄደህ በሌላ ሰው የተወደደችውንና ምንዝር የምትፈጽመውን ሴት ዳግመኛ ውደዳት።” (ሆሴዕ 3:1፤ ምሳሌ 16:2) በወቅቱ የሆሴዕ ሚስት ከባድ ኃጢአት መፈጸሟን እንዳላቆመች ልብ በል። ያም ቢሆን፣ ሆሴዕ ቅድሚያውን ወስዶ ይቅር እንዲላትና እንዲታረቃት ይሖዋ ነግሮታል።a በተመሳሳይም ይሖዋ ልበ ደንዳና በሆኑት ሕዝቦቹ ላይ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። በከባድ ኃጢአት ተጠላልፈው የነበረ ቢሆንም እንኳ ይወዳቸው ነበር፤ እንዲሁም ንስሐ እንዲገቡና አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ለመርዳት መሞከሩን ቀጥሏል። ይህ ምሳሌ፣ አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት መፈጸሙን ባያቆምም እንኳ ‘ልብን የሚመረምረው’ ይሖዋ ቅድሚያውን ወስዶ ይህን ሰው ወደ ንስሐ ለመምራት እንደሚሞክር ያሳያል። (ምሳሌ 17:3) ይህን ጉዳይ በስፋት እንመልከት።
ይሖዋ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ የሚመራው እንዴት ነው?
8. ይሖዋ ቃየንን ወደ ንስሐ ለመምራት የሞከረው እንዴት ነው? (ዘፍጥረት 4:3-7) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
8 ቃየን የአዳምና የሔዋን የበኩር ልጅ ነበር። ከወላጆቹ የኃጢአት ዝንባሌን ወርሷል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “የእሱ ሥራ ክፉ” እንደነበር ይናገራል። (1 ዮሐ. 3:12) መሥዋዕት ባቀረበበት ወቅት ይሖዋ ‘ቃየንንና ያቀረበውን መባ በጥሩ ፊት ያልተመለከተው’ ለዚህ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ቃየን አካሄዱን ከማስተካከል ይልቅ “በጣም ተናደደ”፤ እንዲሁም “እጅግ አዘነ።” (ዘፍጥረት 4:3-7ን አንብብ።) ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? ቃየንን አነጋገረው። መልካም ነገር ካደረገ ሞገሱን እንደሚያሳየው በደግነት ነገረው፤ እንዲሁም አካሄዱ ኃጢአት ወደመፈጸም ሊመራው እንደሚችል አስጠነቀቀው። የሚያሳዝነው፣ ቃየን ይሖዋን ለመስማት አሻፈረኝ አለ። ይሖዋ ወደ ንስሐ እንዲመራው ፈቃደኛ አልሆነም። ታዲያ ይሖዋ፣ ቃየን በጎ ምላሽ ስላልሰጠ ከዚያ በኋላ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ ለመምራት መሞከሩን አቆመ? በጭራሽ!
9. ይሖዋ ዳዊትን ወደ ንስሐ የመራው እንዴት ነው?
9 ይሖዋ ንጉሥ ዳዊትን በጣም ይወደው ነበር። እንዲያውም “እንደ ልቤ የሆነ” በማለት ጠርቶታል። (ሥራ 13:22) ይሁን እንጂ ዳዊት ምንዝርንና ነፍስ ግድያን ጨምሮ ከባድ ኃጢአቶችን ፈጸመ። በሙሴ ሕግ መሠረት ዳዊት ሞት ይገባው ነበር። (ዘሌ. 20:10፤ ዘኁ. 35:31) ያም ቢሆን ይሖዋ በደግነት ጣልቃ ገባ።b ንጉሡን እንዲያነጋግረው ነቢዩ ናታንን ላከው። በወቅቱ ዳዊት ምንም የንስሐ ምልክት አላሳየም ነበር። ናታን የዳዊትን ልብ ለመንካት የሚያስችል ግሩም ምሳሌ ተጠቀመ። ዳዊት ልቡ በጥልቅ ስለተነካ ንስሐ ገባ። (2 ሳሙ. 12:1-14) ያቀናበረው ከልብ የመነጨ መዝሙር በድርጊቱ ምን ያህል እንደተጸጸተ ያሳያል። (መዝ. 51 አናት ላይ ያለው መግለጫ) ይህ መዝሙር ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ኃጢአተኞች አጽናንቷቸዋል፤ እንዲሁም ንስሐ እንዲገቡ አነሳስቷቸዋል። ይሖዋ የሚወደውን አገልጋዩን ዳዊትን ወደ ንስሐ በመምራቱ ምንኛ አመስጋኞች ነን!
10. ይሖዋ ለኃጢአተኞች ስለሚያሳየው ትዕግሥትና ይቅርታ ስታስብ ምን ይሰማሃል?
10 ይሖዋ ማንኛውንም ዓይነት ኃጢአት ይጠላል። (መዝ. 5:4, 5) ሆኖም ሁላችንም ኃጢአተኞች እንደሆንን ያውቃል፤ ደግሞም በጣም ስለሚወደን ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ትግል ሊረዳን ይፈልጋል። የከፋ ኃጢአት የሚፈጽሙ ሰዎችን እንኳ ወደ ንስሐ ለመምራትና ወደ እሱ እንዲቀርቡ ለመርዳት ይሞክራል። ይህን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ስለ ይሖዋ ትዕግሥትና ይቅር ባይነት ማሰላሰላችን ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ ለመሆን እንዲሁም ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ቶሎ ብለን ንስሐ ለመግባት እንድንነሳሳ ያደርገናል። ከዚህ በመቀጠል ኢየሱስ ለተከታዮቹ ስለ ንስሐ ምን እንዳስተማራቸው እንመለከታለን።
ኢየሱስ ለተከታዮቹ ስለ ንስሐ ምን አስተምሯቸዋል?
11-12. ኢየሱስ አባቱ ምን ያህል ይቅር ባይ እንደሆነ ያስተማረው እንዴት ነው? (ሥዕሉን ተመልከት።)
11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መሲሑ መጣ። ባለፈው የጥናት ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ ስለ ንስሐ አስፈላጊነት ለማስተማር መጥምቁ ዮሐንስንና ኢየሱስ ክርስቶስን ተጠቅሟል።—ማቴ. 3:1, 2፤ 4:17
12 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት አባቱ ምን ያህል ይቅር ባይ እንደሆነ አስተምሯል። የአባካኙን ልጅ ምሳሌ በመናገር ይህን ግሩም በሆነ መንገድ ገልጿል። ያ ወጣት ለተወሰነ ጊዜ ያህል የኃጢአት ጎዳና ለመከተል መርጦ ነበር። ያም ቢሆን “ወደ ልቦናው ሲመለስ” ወደ ቤቱ ሄደ። በዚህ ጊዜ አባቱ ምን አደረገ? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “[ልጁ] ገና ሩቅ ሳለም አባቱ አየው፤ በዚህ ጊዜ አንጀቱ ተላወሰ፤ እየሮጠ ሄዶም አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው።” ልጁ ከአባቱ አገልጋዮች እንደ አንዱ ተደርጎ ለመቆጠር ፈቃደኛ ነበር። አባቱ ግን “ይህ ልጄ” በማለት ጠርቶታል፤ በድጋሚ የቤተሰቡ አባል አድርጎም ተቀብሎታል። አባቱ “ጠፍቶ ነበር፤ ተገኝቷል” ብሏል። (ሉቃስ 15:11-32) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ሰማይ ላይ ሳለ አባቱ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች እንዲህ ያለ ርኅራኄ ሲያሳይ እንደተመለከተ ምንም ጥያቄ የለውም። ኢየሱስ የተናገረው ልብ የሚነካ ታሪክ አባታችን ይሖዋ እጅግ መሐሪ እንደሆነ ያሳያል። ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው!
13-14. ጴጥሮስ ስለ ንስሐ ምን ተምሯል? ምንስ አስተምሯል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
13 ሐዋርያው ጴጥሮስ ንስሐንና ይቅርታን በተመለከተ ከኢየሱስ ብዙ ተምሯል። ጴጥሮስ በተደጋጋሚ ይቅርታ አስፈልጎታል፤ ኢየሱስም በልግስና ይቅር ብሎታል። ለምሳሌ ጴጥሮስ ኢየሱስን አላውቀውም ብሎ ሦስት ጊዜ ከካደው በኋላ በጥፋተኝነት ስሜት ተደቁሶ ነበር። (ማቴ. 26:34, 35, 69-75) ያም ቢሆን ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለጴጥሮስ ተገለጠለት፤ ምናልባትም የተገለጠለት ጴጥሮስ ብቻውን እያለ ሳይሆን አይቀርም። (ሉቃስ 24:33, 34፤ 1 ቆሮ. 15:3-5) በዚያ ወቅት ኢየሱስ ንስሐ የገባውን ሐዋርያውን ይቅር እንዳለውና እንዳጽናናው ምንም ጥርጥር የለውም።—ማር. 16:7
14 ጴጥሮስ በሕይወቱ ያየው ነገር ስላለ ለሌሎች ስለ ንስሐና ስለ ይቅርታ ሊያስተምር ችሏል። ከጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ ጴጥሮስ አማኝ ላልሆኑ አይሁዳውያን ንግግር ባቀረበበት ወቅት መሲሑን እንደገደሉት ነግሯቸዋል። ሆኖም እንዲህ የሚል ፍቅራዊ ማሳሰቢያ ሰጣቸው፦ “ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱም፤ ከይሖዋም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል።” (ሥራ 3:14, 15, 17, 19) በዚህ መንገድ ጴጥሮስ፣ ንስሐ አንድን ኃጢአተኛ እንዲመለስ ማለትም የተሳሳተ አስተሳሰቡንና ምግባሩን እንዲያስተካክል እንዲሁም አምላክን የሚያስደስት አዲስ ጎዳና እንዲከተል እንደሚያነሳሳው አሳይቷል። በተጨማሪም ጴጥሮስ፣ ይሖዋ ኃጢአታቸውን እንደሚደመስስላቸው ነግሯቸዋል። ከበርካታ ዓመታት በኋላም ጴጥሮስ ለክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቷቸዋል፦ “ይሖዋ . . . እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።” (2 ጴጥ. 3:9) ከባድ ኃጢአት ብንፈጽምም እንኳ ይሖዋ ይቅር እንደሚለን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው!
15-16. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ይቅርታ የተማረው እንዴት ነው? (1 ጢሞቴዎስ 1:12-15) (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
15 ንስሐ መግባትና ይቅርታ ማግኘት እጅግ ካስፈለጋቸው ሰዎች አንዱ የጠርሴሱ ሳኦል ነው። ሳኦል የክርስቶስን ውድ ተከታዮች ክፉኛ ያሳድድ ነበር። አብዛኞቹ ክርስቲያኖች፣ ሳኦል ንስሐ ሊገባ እንደማይችል አስበው መሆን አለበት። ይሁንና የኢየሱስ አመለካከት እንዲህ ካለው የተሳሳተ ሰብዓዊ አስተሳሰብ በእጅጉ የላቀ ነው። እሱና አባቱ፣ ሳኦል መልካም ባሕርያት እንዳሉት ተመልክተዋል። ኢየሱስ ‘ይህ ሰው ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነው’ ብሏል። (ሥራ 9:15) እንዲያውም ኢየሱስ ሳኦልን ወደ ንስሐ ለመምራት ሲል ተአምር ፈጽሟል። (ሥራ 7:58–8:3፤ 9:1-9, 17-20) ሳኦል ክርስቲያን ከሆነና ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ መጠራት ከጀመረ በኋላ፣ ለተደረገለት ደግነትና ምሕረት አመስጋኝነቱን በተደጋጋሚ ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 1:12-15ን አንብብ።) በአመስጋኝነት ስሜት ተነሳስቶ ‘አምላክ በደግነቱ ወደ ንስሐ ሊመራችሁ እየሞከረ ነው’ ሲል አስተምሯል።—ሮም 2:4
16 ጳውሎስ በቆሮንቶስ በሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የፆታ ብልግና እንደተፈጸመ ሲሰማ ጉዳዩን የያዘው እንዴት ነው? ጉዳዩን የያዘበት መንገድ ስለ ይሖዋ ፍቅራዊ ተግሣጽ እንዲሁም ምሕረት ማሳየት ስላለው አስፈላጊነት ብዙ ትምህርት ይሰጠናል። በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይህን ዘገባ በዝርዝር እንመረምራለን።
መዝሙር 33 ሸክማችሁን በይሖዋ ላይ ጣሉ
a ይህ ታሪክ እንደ አጠቃላይ መመሪያ የሚያገለግል አይደለም። በዛሬው ጊዜ፣ ምንዝር የተፈጸመባቸው ሰዎች ከምንዝር ፈጻሚው ጋር በትዳር ተጣምረው እንዲቀጥሉ ይሖዋ አይጠብቅባቸውም። እንዲያውም ምንዝር የተፈጸመባቸው ሰዎች ከፈለጉ ፍቺ መፈጸም እንደሚችሉ በልጁ አማካኝነት ግልጽ አድርጓል።—ማቴ. 5:32፤ 19:9
b በኅዳር 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የይሖዋ ይቅር ባይነት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?” የሚለውን ርዕስ ገጽ 21-23 አን. 3-10ን ተመልከት።