የአንባቢያን ጥያቄዎች
የሰለሞን ቤተ መቅደስ በረንዳ ከፍታው ምን ያህል ነበር?
በረንዳው “ቅድስት” ተብሎ ለሚጠራው የቤተ መቅደሱ ክፍል መግቢያ ሆኖ ያገለግል ነበር። ከ2023 በፊት የወጡት የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ እትሞች እንዲህ ይላሉ፦ “ከቤቱ ፊት ያለው በረንዳ ርዝመቱ 20 ክንድ ሲሆን ይህም ከቤቱ ወርድ ጋር እኩል ነው፤ ከፍታው ደግሞ 120 ነው።” (2 ዜና 3:4) ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችም የበረንዳው ከፍታ 120 ክንድ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ይህም ሲባል 53 ሜትር ገደማ ከፍታ አለው ማለት ነው።
ይሁንና የአዲስ ዓለም ትርጉም የ2023 እትም የሰለሞን ቤተ መቅደስ በረንዳ ‘ከፍታው 20 ክንድ’ ማለትም 9 ሜትር ገደማ እንደሆነ ይናገራል።a ለዚህ ማስተካከያ ምክንያት የሆኑ አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት።
የበረንዳው ከፍታ 1 ነገሥት 6:3 ላይ አልተጠቀሰም። ኤርምያስ ይህን ጥቅስ ሲጽፍ የበረንዳውን ርዝመትና ወርድ እንጂ ከፍታውን አልጠቀሰም። ከዚያም በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ስለ ቤተ መቅደሱ ሌሎች ጉልህ ገጽታዎች በዝርዝር ገለጸ፤ ከእነዚህም መካከል ከቀለጠ ብረት የተሠራው ባሕር፣ አሥሩ ጋሪዎች እንዲሁም ከበረንዳው አጠገብ የቆሙት ሁለት የመዳብ ዓምዶች ይገኙበታል። (1 ነገ. 7:15-37) በረንዳው በእርግጥ ከ50 ሜትር በላይ ቁመት ያለውና ከሌላው የቤተ መቅደሱ ክፍል ከፍ ብሎ የሚታይ ቢሆን ኖሮ ኤርምያስ ከፍታውን አይጠቅስም ነበር? በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ የነበሩ የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊዎችም እንደዘገቡት የበረንዳው ከፍታ ከሌሎቹ የሰለሞን ቤተ መቅደስ ክፍሎች የሚበልጥ አልነበረም።
ምሁራን የቤተ መቅደሱ ግድግዳ 120 ክንድ ከፍታ ያለውን በረንዳ መደገፍ የሚችል መሆኑን ይጠራጠራሉ። በጥንት ዘመን የነበሩ ከፍተኛ ቁመት ያላቸው ከድንጋይና ከጡብ የተሠሩ ግንቦች፣ ለምሳሌ በግብፅ የነበሩ የቤተ መቅደስ በሮች ከታች በጣም ሰፊ የነበሩ ሲሆን ወደ ላይ እየጠበቡ ይሄዳሉ። የሰለሞን ቤተ መቅደስ ግን ከዚህ የተለየ ነበር። አንዳንድ ምሁራን እንደሚገልጹት የሰለሞን ቤተ መቅደስ ግድግዳ ከ6 ክንድ ወይም ከ2.7 ሜትር የሚበልጥ ውፍረት አልነበረውም። የሥነ ሕንፃ የታሪክ ምሁር የሆኑት ቴዎዶር ቡሲንክ ከዚህ በመነሳት የሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፦ “[በቤተ መቅደሱ መግቢያ] ላይ ያለው ግድግዳ ካለው ውፍረት አንጻር በረንዳው 120 ክንድ ከፍታ ሊኖረው አይችልም።”
በ2 ዜና መዋዕል 3:4 ላይ ያለው ሐሳብ የገልባጭ ስህተት ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች እዚህ ጥቅስ ላይ “120” የሚሉ ቢሆንም ተአማኒነት ያላቸው ሌሎች ቅጂዎች፣ ለምሳሌ በአምስተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀው ኮዴክስ አሌክሳንድሪነስ እና በስድስተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀው ኮዴክስ አምብሮሲያነስ የበረንዳው ከፍታ 20 ክንድ እንደሆነ ይገልጻሉ። ታዲያ አንድ ገልባጭ በስህተት “120” ብሎ ሊጽፍ የሚችለው እንዴት ነው? በዕብራይስጥ “መቶ” እና “ክንድ” የሚሉት ቃላት መልካቸው ይመሳሰላል። ስለዚህ አንድ ገልባጭ “ክንድ” በማለት ፋንታ “መቶ” ብሎ ጽፎ ሊሆን ይችላል።
እርግጥ ነው፣ እነዚህን ዝርዝር ነገሮች መረዳትና የሰለሞን ቤተ መቅደስ ምን እንደሚመስል በትክክል መግለጽ ብንፈልግም በዋነኝነት ትኩረት የምናደርገው ያ ቤተ መቅደስ ጥላ በሆነለት ነገር ማለትም በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ላይ ነው። ይሖዋ ሁሉንም አገልጋዮቹን በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲያመልኩት በመጋበዙ ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ዕብ. 9:11-14፤ ራእይ 3:12፤ 7:9-17
a ጥቅሱ እንደሚከተለው የሚል የግርጌ ማስታወሻ አለው፦ “በእጅ የተጻፉ አንዳንድ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ‘120’ የሚሉ ሲሆን ሌሎች ቅጂዎችና አንዳንድ ትርጉሞች ደግሞ ‘20 ክንድ’ ይላሉ።”