ሃይማኖት ፖለቲካ ውስጥ መግባቱ ተገቢ ነው?
በዓለም ዙሪያ ያሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ፖለቲካ ውስጥ የጎላ ተሳትፎ ያደርጋሉ። አንዳንዶች ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶቻችንን ያራምዱልናል ብለው የሚያስቧቸውን እጩ ተመራጮች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ይደግፋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ፖለቲከኞች ሥነ ምግባራዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት የሃይማኖተኞችን ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። የሃይማኖት መሪዎች የፖለቲካ ሥልጣን ለማግኘት መወዳደራቸውም ቢሆን የተለመደ ነው። በተወሰኑ አገሮች ደግሞ ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ሃይማኖቶች የመንግሥት ሃይማኖት ወይም ብሔራዊ ሃይማኖት የሚል ለየት ያለ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
አንተ ስለዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ? የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ፖለቲካ ውስጥ መግባታቸው ተገቢ ነው? ኢየሱስ የተወው አርዓያ መልሱን ለማግኘት ይረዳናል። ኢየሱስ “እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:15) ታዲያ ኢየሱስ ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምን አርዓያ ትቷል?
ኢየሱስ ፖለቲካ ውስጥ ገብቷል?
በፍጹም። ኢየሱስ በዚህ ዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ አልገባም።
ኢየሱስ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ አልፈለገም። ሰይጣን ዲያብሎስ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ” እንደሚሰጠው ግብዣ ቢያቀርብለትም ኢየሱስ የእነዚህ መንግሥታት ገዢ ለመሆን ፈቃደኛ አልሆነም። (ማቴዎስ 4:8-10)a በሌላ ወቅት ደግሞ የኢየሱስን የአመራር ብቃት ያስተዋሉ አንዳንድ ሰዎች ፖለቲካ ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ሞክረው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ወቅት ኢየሱስ ስላደረገው ነገር ሲዘግብ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ሰዎቹ መጥተው ሊይዙትና ሊያነግሡት እንዳሰቡ ስላወቀ ብቻውን ዳግመኛ ወደ ተራራ ገለል አለ።” (ዮሐንስ 6:15) ኢየሱስ የሕዝቡን ጥያቄ አልተቀበለም። ፖለቲካ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ አልሆነም።
ኢየሱስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ከማንም ጋር አልወገነም። ለምሳሌ ያህል በዘመኑ የነበሩ አይሁዳውያን ለሮም መንግሥት ግብር መክፈላቸው ያበሳጫቸው ነበር፤ የተጣለባቸው ግብር ፍትሐዊ እንዳልሆነና እንደ ሸክም እንደተጫናቸው ይሰማቸው ነበር። አንዳንዶች ኢየሱስ በጉዳዩ ላይ አንደኛውን ወገን እንዲደግፍ ለማድረግ ሞክረው ነበር፤ ሆኖም ኢየሱስ ‘የተጣለው ግብር ፍትሐዊ ነው ወይስ አይደለም?’ የሚለው ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ አልገባም። “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” አላቸው። (ማርቆስ 12:13-17) ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ፖለቲካ ውስጥ ባይገባም ቄሳር ማለትም የሮም ባለሥልጣናት የሚጠይቁትን ግብር መክፈል ተገቢ እንደሆነ ገልጿል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው የመንግሥት ባለሥልጣናትን መታዘዝ ያለበት በገደብ እንደሆነ ጠቁሟል። አምልኮን ጨምሮ ለአምላክ የሚገባውን ነገር ለመንግሥት መስጠት ተገቢ አይደለም።—ማቴዎስ 4:10፤ 22:37, 38
ኢየሱስ የደገፈውና ሌሎችን ያስተማረው በሰማይ ስላለው የአምላክ መንግሥት ነው። (ሉቃስ 4:43) አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ የሚያሳካው የአምላክ መንግሥት እንጂ የሰዎች መንግሥታት እንዳልሆኑ ኢየሱስ ያውቅ ነበር፤ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ያልፈለገው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 6:10) የአምላክ መንግሥት በእነዚህ መንግሥታት እንደማይጠቀም፣ ከዚህ ይልቅ እነሱን አስወግዶ ምድርን እንደሚያስተዳድር ተገንዝቦ ነበር።—ዳንኤል 2:44
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ክርስቲያኖች ፖለቲካ ውስጥ ገብተዋል?
አልገቡም። የኢየሱስ ተከታዮች ‘የዓለም ክፍል እንዳይሆኑ’ የተሰጣቸውን መመሪያ ታዝዘዋል። (ዮሐንስ 15:19) የኢየሱስን አርዓያ በመከተል ከዚህ ዓለም ፖለቲካ ራሳቸውን አግልለዋል። (ዮሐንስ 17:16፤ 18:36) ፖለቲካ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ኢየሱስ ያዘዛቸውን ሥራ አከናውነዋል፤ ይህም ስለ አምላክ መንግሥት መስበክና ማስተማር ነው።—ማቴዎስ 28:18-20፤ የሐዋርያት ሥራ 10:42
የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ከማንም በላይ የሚታዘዙት አምላክን ነበር፤ ሆኖም የመንግሥት ባለሥልጣናትን ማክበር እንደሚጠበቅባቸውም ያውቁ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 5:29፤ 1 ጴጥሮስ 2:13, 17) የሚያወጧቸውን ሕጎች ይታዘዙ እንዲሁም ግብር ይከፍሉ ነበር። (ሮም 13:1, 7) በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ባይገቡም መንግሥት ለዜጎች ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ተጠቅመዋል፤ ለምሳሌ፣ ሕጋዊ ከለላ ለማግኘት መንግሥት የሰጣቸውን መብት ይጠቀሙ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 25:10, 11፤ ፊልጵስዩስ 1:7
በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ገለልተኞች ናቸው
መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያሳየው ኢየሱስም ሆነ የመጀመሪያ ተከታዮቹ ፖለቲካ ውስጥ አልገቡም። በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ክርስቲያን እንደመሆናቸው መጠን ከፖለቲካ ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ናቸው። እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ ኢየሱስ ያዘዛቸውን ሥራ ያከናውናሉ፤ ይኸውም ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ ይሰብካሉ።—ማቴዎስ 24:14
a ኢየሱስ ለሰይጣን መልስ ሲሰጥ ‘ይህን ግብዣ የማቅረብ ሥልጣን የለህም’ ብሎ አልተከራከረውም። እንዲያውም በሌላ ጊዜ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዢ” ብሎ ጠርቶታል።—ዮሐንስ 14:30