የወጣቶች ጥያቄ
ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?—ክፍል 4፦ ፈጣሪ እንዳለ ለሰዎች ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?
ፈጣሪ መኖሩን ታምናለህ፤ ሆኖም በትምህርት ቤት ውስጥ በሌሎች ፊት ይህን መናገር ያስፈራህ ይሆናል። ምናልባትም የትምህርት ቤት መጽሐፎችህ የዝግመተ ለውጥ ሐሳብን የሚደግፉ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በመሆኑም አስተማሪዎችህና አብረውህ የሚማሩት ልጆች በእምነትህ የተነሳ እንዳያሾፉብህ ፈርተህ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ስለ ፈጣሪ መኖር ያለህን እምነት በድፍረት ማስረዳት የምትችለው እንዴት ነው?
ማስረዳት ትችላለህ!
እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል፦ ‘ሳይንስ ነክ ስለሆኑ ጉዳዮች ለመወያየትም ሆነ ስለ ዝግመተ ለውጥ ለመከራከር ብቃቱ ያለኝ አይመስለኝም።’ ዳንዬል የተባለች ወጣት እንዲህ ተሰምቷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ከአስተማሪዬ እና አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች ጋር መከራከር አልፈልግም ነበር።” ዳያናም በዚህ ሐሳብ ትስማማለች፤ “ሳይንሳዊ ቃላትን እየተጠቀሙ ሲከራከሩኝ ግራ ይገባኝ ነበር” ብላለች።
ይሁን እንጂ ዓላማህ በክርክር ማሸነፍ አይደለም። በዚያ ላይ ደግሞ ሁሉንም ነገሮች የፈጠረ ፈጣሪ እንዳለ የምታምነው ለምን እንደሆነ ለማስረዳት የሳይንስ ሊቅ መሆን አያስፈልግህም።
ይህን ለማድረግ ሞክር፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዕብራውያን 3:4 ላይ የሚገኘውን አሳማኝ ነጥብ ተጠቅመህ ለማስረዳት ሞክር፤ ጥቅሱ “እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው” በማለት ይናገራል።
ካሮል የተባለች አንዲት ወጣት በዕብራውያን 3:4 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተጠቅማ ሰዎችን ስታስረዳ እንዲህ ትላለች፦ “ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ እየሄዳችሁ እንዳለ አድርጋችሁ አስቡ። በአካባቢው ሰው ድርሽ ብሎ የሚያውቅ አይመስልም። ነገር ግን ድንገት ወደ መሬት ስትመለከቱ አንድ ስቴኪኒ ወድቆ አያችሁ። በዚህ ጊዜ ምን ታስባላችሁ? አብዛኞቹ ሰዎች ‘የሆነ ሰው ወደዚህ አካባቢ መጥቶ ነበር’ ብለው ማሰባቸው አይቀርም። እንደ ስቴኪኒ ያለ ትንሽ እና ውስብስብ ያልሆነ ነገር እንኳ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንዳለ የሚጠቁም ከሆነ ጽንፈ ዓለምና በውስጡ ያሉ ነገሮች ከሁሉ የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንዳለ ማስረጃ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይሆንም?”
አንድ ሰው እንዲህ ቢልህስ? “ሁሉም ነገሮች የተገኙት በፍጥረት ከሆነ ታዲያ አምላክን ማን ፈጠረው?”
እንዲህ ብለህ መመለስ ትችላለህ፦ “ፈጣሪን በተመለከተ ልንረዳቸው የማንችላቸው ነገሮች መኖራቸው ብቻ ፈጣሪ የለም ብለን ለመደምደም መሠረት አይሆነንም። ለምሳሌ፣ የያዝከውን የሞባይል ስልክ የሠራው ማን እንደሆነ አታውቅ ይሆናል፤ የሆነ ሰው እንደሠራው ግን ታምናለህ አይደል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] የሚገርምህ ነገር፣ ፈጣሪን በተመለከተ ማወቅ የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እንዲያውም ስለ እሱ ማወቅ የምትፈልግ ከሆነ እኔ የማውቀውን ልነግርህ እችላለሁ።”
በደንብ ተዘጋጅ
መጽሐፍ ቅዱስ ‘እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁዎች ሁኑ፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን’ በማለት ይመክራል። (1 ጴጥሮስ 3:15) በመሆኑም ለሁለት ነገሮች ይኸውም ምን እና እንዴት እንደምትናገር ትኩረት ሰጥተህ ተዘጋጅ።
ምን መናገር ትችላለህ? አምላክን የምትወደው ከሆነ ስለ እሱ ለመናገር መነሳሳትህ አይቀርም። ነገር ግን አምላክን ምን ያህል እንደምትወደው ስለተናገርክ ብቻ ሰዎች ሁሉንም ነገር የፈጠረው አምላክ እንደሆነ ያምናሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ፈጣሪ እንዳለ ማመን ምክንያታዊ እንደሆነ ለማስረዳት የፍጥረት ሥራዎችን እንደ ምሳሌ ተጠቀም።
እንዴት መናገር አለብህ? በራስ መተማመን ይኑርህ፤ ሆኖም አነጋገርህ ሌሎችን እንደምትንቅ ወይም ራስህን እንደምታመጻድቅ የሚያሳይ ሊሆን አይገባም። ሰዎች የምታምንበትን ነገር ስትናገር ሊያዳምጡህ ፈቃደኛ የሚሆኑት እነሱ የሚያምኑበትን ነገር እንደምታከብር እንዲሁም የፈለጉትን የማመን መብት እንዳላቸው አምነህ እንደምትቀበል ሲመለከቱ ነው።
“የሌሎችን አመለካከት አለማንቋሽሽ ወይም ‘ሁሉን አውቃለሁ’ ባይ አለመሆን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማኛል። አንድ ሰው ራሱን እንደሚያመጻድቅ በሚያሳይ መንገድ የሚናገር ከሆነ ጥሩ ውጤት አያገኝም።”—ኢሌይን
እምነትህን ማስረዳት እንድትችል የሚያግዙ መሣሪያዎች
አሊሲያ የተባለች ወጣት “በደንብ ካልተዘጋጀን፣ ለኃፍረት እንዳንዳረግ በመፍራት ዝም ማለታችን አይቀርም” ብላለች። አሊሲያ እንደተናገረችው አንድ ሰው ስኬታማ መሆን ከፈለገ ዝግጅት ማድረጉ ወሳኝ ነው። ጄና ደግሞ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ቀላልና በደንብ የታሰበበት ምሳሌ ማዘጋጀት፣ ከሰዎች ጋር ስለ ፈጣሪ መኖር ስነጋገር ይበልጥ ቀላል እንደሚያደርግልኝ አስተውያለሁ።”
ታዲያ እንዲህ ዓይነት ምሳሌዎችን ከየት ማግኘት ትችላለህ? ብዙ ወጣቶች የሚከተሉትን ጽሑፎች ጠቃሚ ሆነው አግኝተዋቸዋል፦
ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው?
የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች
አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር ይገልጣሉ (ቪዲዮ በእንግሊዝኛ)
“ንድፍ አውጪ አለው?” በሚል ዓምድ ሥር በንቁ! መጽሔት ላይ የሚወጡት ተከታታይ ርዕሶች። (የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ገብተህ በፍለጋ ሣጥኑ ላይ “ንድፍ አውጪ አለው” የሚለውን ሐረግ [ከነትእምርተ ጥቅሱ] በመጻፍ ርዕሶቹን ፈልግ)
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍትን ተጠቅመህ ተጨማሪ ምርምር አድርግ።
“ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?” በሚል ርዕስ ሥር ከዚህ በፊት የወጡ ርዕሶችን መመልከትህም ሊጠቅምህ ይችላል።
ይህን ለማድረግ ሞክር፦ አንተን ይበልጥ ያሳመኑህን ምሳሌዎች ምረጥ። እንዲህ ማድረግህ ምሳሌዎቹን በቀላሉ ለማስታወስና ይበልጥ አሳማኝ በሆነ መንገድ ለማስረዳት ያስችልሃል። ስለምታምንበት ነገር ሌሎችን ማስረዳት የምትችልበትን መንገድ ተለማመድ።