መጽሐፍ ቅዱስ አረጋውያን ወላጆችን መጦርን በተመለከተ ምን ይናገራል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ልጆች አዋቂ ከሆኑ በኋላ አረጋውያን ወላጆቻቸውን የመጦር ኃላፊነት አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች “የራሳቸውን [ቤተሰብ] በመርዳትና ለወላጆቻቸውም ብድራትን በመመለስ ከሁሉ በፊት እምነታቸውን በተግባር ለማሳየት መማር ይገባቸዋል፤ ይህ [አምላክን] ደስ የሚያሰኝ ነውና” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 5:4 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) አንድ ሰው አረጋውያን ወላጆቹን ሲጦር መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆቻችንን እንድናከብር የሚሰጠንን መመሪያ በሥራ ላይ እያዋለ ነው።—ኤፌሶን 6:2, 3
መጽሐፍ ቅዱስ አረጋውያን ወላጆችን መጦር ስለሚቻልበት መንገድ ዝርዝር መመሪያዎችን አይሰጥም። ሆኖም ወላጆቻቸውን ስለጦሩ የእምነት ሰዎች ይናገራል። በተጨማሪም ለአረጋውያን እንክብካቤ ለሚያደርጉ ሰዎች የሚጠቅሙ ግሩም ምክሮች ይሰጣል።
በጥንት ዘመን አንዳንዶች አረጋውያን ወላጆቻቸውን የጦሩት እንዴት ነው?
በጥንት ዘመን የኖሩ ሰዎች አረጋውያን ወላጆቻቸውን የጦሩት በተለያየ መንገድ ነው።
ዮሴፍ የሚኖረው ከአረጋዊ አባቱ ከያዕቆብ ርቆ ነበር። ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ግን ያዕቆብን እሱ ወደሚኖርበት አካባቢ አስመጣው። ከዚያም ለያዕቆብ መጠለያና ቀለብ ያቀረበለት ከመሆኑም ሌላ ጥበቃ አድርጎለታል።—ዘፍጥረት 45:9-11፤ 47:11, 12
ሩት ወደ አማቷ አገር በስደት ከሄደች በኋላ በትጋት በመሥራት አማቷን ተንከባክባታለች።—ሩት 1:16፤ 2:2, 17, 18, 23
ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ እናቱን ማርያምን የሚንከባከብ ሰው መድቦ ነበር፤ በወቅቱ ማርያም መበለት የነበረች ይመስላል።—ዮሐንስ 19:26, 27a
መጽሐፍ ቅዱስ አረጋውያንን ለሚንከባከቡ ሰዎች ምን ጠቃሚ ምክር ይሰጣል?
አረጋውያንን መጦር አካልንም ሆነ ስሜትን ሊያደክም ይችላል፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ኃላፊነት ለሚወጡ ሰዎች የሚጠቅሙ ግሩም ምክሮችን ይዟል።
ወላጆቻችሁን አክብሩ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አባትህንና እናትህን አክብር።”—ዘፀአት 20:12
ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ወላጆቻችሁ አቅማቸው የሚችለውን ነገር በራሳቸው እንዲያደርጉ በመፍቀድ አክብሮት አሳዩአቸው። እንዲሁም በተቻለ መጠን የሚደረግላቸውን እንክብካቤ በተመለከተ ራሳቸው እንዲወስኑ አድርጉ። ከዚህም ሌላ እነሱን ለመርዳት የቻላችሁትን ሁሉ በማድረግ አክብሮት ልታሳዩአቸው ትችላላችሁ።
ስሜታቸውን ተረዱላቸው፤ እንዲሁም ይቅር ባይ ሁኑ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል፤ በደልንም መተዉ ውበት ያጎናጽፈዋል።”—ምሳሌ 19:11
ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? አረጋውያን ወላጆቻችሁ ደግነት የጎደለው ነገር ቢናገሩ ወይም አመስጋኝ እንዳልሆኑ ቢሰማችሁ ‘እንዲህ ያለ የአቅም ገደብ ቢኖርብኝ ምን ይሰማኝ ነበር?’ በማለት ራሳችሁን ጠይቁ። ስሜታቸውን ለመረዳትና ይቅር ባይ ለመሆን ጥረት ካደረጋችሁ ሁኔታውን ከማባባስ መቆጠብ ትችላላችሁ።
ሌሎችን አማክሩ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።”—ምሳሌ 15:22
ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ወላጆቻችሁ ያለባቸውን የጤና እክል በተመለከተ ምርምር አድርጉ። በአካባቢያችሁ ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት የተደረገ ዝግጅት መኖሩን አጣሩ። አረጋውያን ወላጆቻቸውን የተንከባከቡ ሰዎችን አነጋግሩ። ወንድሞችና እህቶች ካሏችሁ ስለ ወላጆቻችሁ ሁኔታ፣ እነሱን መንከባከብ ስለሚቻልበት መንገድ እንዲሁም ኃላፊነቱን እንዴት ልትጋሩ እንደምትችሉ ተነጋገሩ።
ልካችሁን እወቁ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።”—ምሳሌ 11:2
ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ያለባችሁን የአቅም ገደብ አምናችሁ ተቀበሉ። ሁሉም ሰው ያለው ጊዜና ኃይል ውስን ነው። በመሆኑም ያለባችሁ የአቅም ገደብ ለወላጆቻችሁ ማድረግ የምትችሉትን ነገር እንደሚወስነው የታወቀ ነው። ስለዚህ አረጋውያን ወላጆቻችሁን መጦር ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ ከተሰማችሁ ከሌሎች የቤተሰባችሁ አባላት ወይም ከባለሙያዎች እርዳታ ጠይቁ።
ራሳችሁን ተንከባከቡ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የገዛ አካሉን የሚጠላ ማንም ሰው የለምና፤ ከዚህ ይልቅ ይመግበዋል እንዲሁም ይሳሳለታል።”—ኤፌሶን 5:29
ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ወላጆቻችሁን የመጦር ኃላፊነት እንዳለባችሁ ግልጽ ነው፤ ሆኖም ራሳችሁንም ሆነ ትዳር ከመሠረታችሁ ደግሞ የራሳችሁን ቤተሰብ የመንከባከብ ኃላፊነት አለባችሁ። በመሆኑም የተመጣጠነ ምግብ ተመገቡ፤ እንዲሁም በቂ እንቅልፍ ተኙ። (መክብብ 4:6) አልፎ አልፎ እረፍት መውሰድም ያስፈልጋችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ ወላጆቻችሁን ለመጦር የሚያስፈልገው ስሜታዊ፣ አእምሯዊና አካላዊ ጥንካሬ እንዲኖራችሁ ያስችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ አረጋውያን ወላጆቻችንን መንከባከብ ያለብን ቤት ውስጥ እንደሆነ ይገልጻል?
መጽሐፍ ቅዱስ አረጋውያን ወላጆች መጦር ያለባቸው የት እንደሆነ በዝርዝር አይናገርም። አንዳንድ ቤተሰቦች አረጋውያን ወላጆቻቸው አብረዋቸው እንዲኖሩ ይፈልጉ ይሆናል። በኋላ ላይ ግን ወላጆቻቸው በአረጋውያን መጦሪያ ተቋም ውስጥ እንክብካቤ ቢያገኙ የተሻለ እንደሆነ ሊያስቡ ይችላሉ። ቤተሰቡ የተሻለው አማራጭ የቱ እንደሆነ ለመወሰን በጋራ ሊወያይ ይችላል።—ገላትያ 6:4, 5
a አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ ይህን ዘገባ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በወቅቱ ዮሴፍ [የማርያም ባል] ከሞተ ረጅም ጊዜ ስላለፈው ኢየሱስ ማርያምን ይደግፋት የነበረ ይመስላል፤ ታዲያ እሱ ሲሞት ማን ይንከባከባታል? . . . እዚህ ላይ ክርስቶስ ልጆች በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን መደገፍ እንዳለባቸው አስተምሯል።”—ዚ ኤንአይቪ ማቲው ሄንሪ ኮሜንታሪ ኢን ዋን ቮልዩም፣ ገጽ 428-429