የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ኤርምያስ 29:11—“ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ”
“‘ለእናንተ የማስበውን ሐሳብ በሚገባ አውቀዋለሁና’ ይላል ይሖዋ፤a ‘ለእናንተ የማስበው ጥፋትን ሳይሆን ሰላምን እንዲሁም የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን ነው።’”—ኤርምያስ 29:11 አዲስ ዓለም ትርጉም
“‘ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጥ፣ እናንተንም የሚጠቅም እንጂ የሚጐዳ አይደለም።’”—ኤርምያስ 29:11 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
የኤርምያስ 29:11 ትርጉም
የኤርምያስ 29:11 አውድ
ይህ ጥቅስ ከኢየሩሳሌም በግዞት ተወስደው በባቢሎን ለሚኖሩት እስራኤላውያን የተጻፈው ደብዳቤ ክፍል ነው።b (ኤርምያስ 29:1) አምላክ በግዞት የተወሰዱት ሰዎች ለረጅም ጊዜ በግዞት ስለሚቆዩ ቤት እንዲሠሩ፣ አትክልት እንዲተክሉና ልጆች እንዲወልዱ ነግሯቸው ነበር። (ኤርምያስ 29:4-9) አክሎ ግን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በባቢሎን የምትኖሩበት 70 ዓመት ሲፈጸም ትኩረቴን ወደ እናንተ አዞራለሁ፤ ወደ [ኢየሩሳሌምም] መልሼ በማምጣት፣ የገባሁትን ቃል እፈጽማለሁ።” (ኤርምያስ 29:10) በመሆኑም አምላክ እንደማይረሳቸውና ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ ያላቸው ተስፋ እውን እንደሚሆን አረጋግጦላቸዋል።—ኤርምያስ 31:16, 17
አምላክ ለእስራኤላውያን የገባውን ቃል ጠብቋል። አስቀድሞ እንደተናገረው ባቢሎን በፋርሱ ንጉሥ በቂሮስ ድል ተደረገች። (ኢሳይያስ 45:1, 2፤ ኤርምያስ 51:30-32) ከዚያ በኋላ ቂሮስ አይሁዳውያኑ ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቀደላቸው። ለ70 ዓመት በግዞት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።—2 ዜና መዋዕል 36:20-23፤ ዕዝራ 3:1
በኤርምያስ 29:11 ላይ የሚገኘው ትንቢት መፈጸሙ በዛሬው ጊዜ ላሉ አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች ማረጋገጫ ይሰጣል። አምላክ ቃል ከገባቸው ነገሮች መካከል ክርስቶስ ኢየሱስ በሚገዛው መንግሥት አማካኝነት ዓለም አቀፍ ሰላም እንደሚሰፍን የሰጠው ተስፋ ይገኝበታል።—መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ኢሳይያስ 55:11፤ ማቴዎስ 6:10
ሰዎች ስለ ኤርምያስ 29:11 ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ
የተሳሳተ ግንዛቤ፦ አምላክ ለእያንዳንዱ ሰው የተወሰነ “ዕቅድ” አለው።
እውነታው፦ አምላክ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚመሩበትን መንገድ በተመለከተ የራሳቸውን ምርጫ እንዲያደርጉ ፈቅዶላቸዋል። በኤርምያስ 29:11 ላይ የሚገኘውን መልእክት የተናገረው በባቢሎን ለሚኖሩ እስራኤላውያን በቡድን ደረጃ ሲሆን አምላክ ለዚህ ቡድን ያሰበው ሐሳብ ነበር፤ ይህም ወደፊት ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖሩ ነው። (ኤርምያስ 29:4) ሆኖም እያንዳንዱ ሰው አምላክ ከሰጠው ተስፋ ተጠቃሚ ለመሆን ወይም ላለመሆን የየራሱን ምርጫ እንዲያደርግ ተፈቅዶለት ነበር። (ዘዳግም 30:19, 20፤ ኤርምያስ 29:32) አምላክን ለመፈለግ የመረጡ ሰዎች ወደ እሱ ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብ እሱን ማግኘት ይችሉ ነበር።—ኤርምያስ 29:12, 13
ኤርምያስ ምዕራፍ 29ን አንብብ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግርጌ ማስታወሻዎቹንና ማጣቀሻዎቹን ተመልከት።
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18
b ዚ ኤክስፖዚተርስ ባይብል ኮሜንታሪ የተባለው መጽሐፍ ኤርምያስ 29:11ን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ያህዌህ [ይሖዋ] በግዞት ለተወሰዱት ለእነዚህ ሰዎች ያለውን ርኅራኄ የገለጸበት ብሎም በመጨረሻ አዎንታዊ እንዲሆኑና ብሩሕ ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያስችል ተጨባጭ ምክንያት የሰጠበት ከዚህ የተሻለ ተስፋ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አይገኝም።”—ጥራዝ 7 ገጽ 360