ሰኞ፣ መስከረም 26
ሙታን የማይነሱ ከሆነማ “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ።”—1 ቆሮ. 15:32
ሐዋርያው ጳውሎስ እስራኤላውያን የነበራቸውን ዝንባሌ የሚገልጸውን ኢሳይያስ 22:13ን እየጠቀሰ ሊሆን ይችላል። እስራኤላውያን ወደ አምላክ ከመቅረብ ይልቅ ተድላን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት ይመሩ ነበር። በሌላ አባባል እነዚህ እስራኤላውያን “ሺህ ዓመት አይኖር” ያሉ ያህል ነው፤ እንዲህ ያለው አመለካከት ዛሬም በስፋት ይታያል። ይሖዋ ሙታንን እንደሚያስነሳ ማወቃችን በጓደኛ ምርጫችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚገባ ጥርጥር የለውም። በቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩ ወንድሞች ትንሣኤን ከሚክዱ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ላለመመሥረት መጠንቀቅ ነበረባቸው። ከዚህ ግሩም ትምህርት እናገኛለን፤ ለዛሬ ብቻ የሚኖሩ ሰዎችን ጓደኛ አድርገን መምረጣችን ጎጂ ነው። አንድ እውነተኛ ክርስቲያን እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፉ በአመለካከቱና በሥነ ምግባሩ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል፤ ይባስ ብሎም አምላክ የሚጠላውን ዓይነት ሕይወት እንዲከተል ማለትም በኃጢአት ጎዳና እንዲመላለስ ሊያደርገው ይችላል። በመሆኑም ጳውሎስ “ጽድቅ የሆነውን በማድረግ ወደ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአት መሥራትን ልማድ አታድርጉ” የሚል ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።—1 ቆሮ. 15:33, 34፤ w20.12 9 አን. 3, 5-6
ማክሰኞ፣ መስከረም 27
የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ . . . የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ [ነው]።—1 ቆሮ. 11:3
ይህ ጥቅስ፣ ይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰቡን እንዴት እንዳደራጀ ይገልጻል። የራስነት ሥርዓት ሁለት ቁልፍ ነገሮችን የያዘ ነው፤ እነሱም ሥልጣንና ተጠያቂነት ናቸው። የሁሉም “ራስ” ወይም የመጨረሻው ባለሥልጣን ይሖዋ ነው፤ ሁሉም ልጆቹ ማለትም መላእክትም ሆኑ የሰው ልጆች በእሱ ፊት ተጠያቂ ናቸው። (ሮም 14:10፤ ኤፌ. 3:14, 15) ይሖዋ ለኢየሱስ በጉባኤው ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል፤ ሆኖም ኢየሱስ እኛን የሚይዝበትን መንገድ በተመለከተ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ነው። (1 ቆሮ. 15:27) ይሖዋ ለባልም በሚስቱና በልጆቹ ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል። ታዲያ ጥሩ የቤተሰብ ራስ መሆን የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ይሖዋ የሚጠብቅበትን ማወቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም ይሖዋ የራስነት ሥርዓትን ያቋቋመበትን ምክንያት በተለይ ደግሞ ይሖዋና ኢየሱስ የተዉትን ምሳሌ መከተል የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገዋል። እንዲህ ማድረግ የሚጠበቅበት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ ለቤተሰብ ራሶች የተወሰነ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ይህን ሥልጣናቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ይጠብቅባቸዋል።—ሉቃስ 12:48ለ፤ w21.02 2 አን. 1-3
ረቡዕ፣ መስከረም 28
የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ . . . እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።—ኢሳ. 48:17
አንዳንድ ነገሮችን በመርሳት ይሖዋን መምሰላችን ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ፍጹም የሆነ የማስታወስ ችሎታ ቢኖረውም ለሠራነው ጥፋት ንስሐ ከገባን ስህተታችንን ይቅር ለማለትና ለመርሳት ፈቃደኛ ነው። (መዝ. 25:7፤ 130:3, 4) እኛም የበደሉን ሰዎች በሠሩት ጥፋት ከተጸጸቱ ተመሳሳይ ነገር እንድናደርግ ይሖዋ ይጠብቅብናል። (ማቴ. 6:14፤ ሉቃስ 17:3, 4) አስደናቂ ስጦታ ለሆነው አንጎላችን ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ስጦታውን የሰጠንን አካል በሚያስከብር መንገድ አንጎላችንን መጠቀም ነው። አንዳንዶች አንጎላቸውን የሚጠቀሙበት ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ የራሳቸውን መሥፈርት ለማውጣት ነው። ይሁን እንጂ ፈጣሪያችን ይሖዋ ስለሆነ፣ የእሱ መሥፈርቶች እኛ ለራሳችን ከምናወጣቸው ከየትኞቹም መሥፈርቶች የላቁ እንደሆኑ ጥያቄ የለውም። (ሮም 12:1, 2) የይሖዋን መሥፈርቶች ስንከተል ሰላማዊ ሕይወት መምራት እንችላለን። (ኢሳ. 48:18) በተጨማሪም ፈጣሪያችንን እና አባታችንን በሚያስከብርና እሱን በሚያስደስት መንገድ ስለምንኖር ሕይወታችን እውነተኛ ዓላማ ያለው ይሆናል።—ምሳሌ 27:11፤ w20.05 23-24 አን. 13-14