ቤተሰቦችን ለመርዳት የተደረገ ዝግጅት
1. ሳምንታዊው የሰንበት እረፍት ለእስራኤላውያን ቤተሰቦች ምን ጥቅም ያስገኝላቸው ነበር?
1 ሰንበት ለቤተሰቦች ጥቅም የሚያስገኝ የይሖዋ ፍቅራዊ ዝግጅት ነበር። እስራኤላውያን በዚያ ቀን ከዕለት ተዕለት ተግባራቸው ያርፉ የነበረ ከመሆኑም በላይ በይሖዋ ጥሩነትና ከእሱ ጋር በመሠረቱት ወዳጅነት ላይ ለማሰላሰል ጊዜ ያገኙ ነበር። ወላጆች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ሕጉን ለመትከል ይህን አጋጣሚ መጠቀም ይችሉ ነበር። (ዘዳ. 6:6, 7) በየሳምንቱ የሚመጣው የሰንበት እረፍት የይሖዋ ሕዝቦች ለመንፈሳዊነታቸው ትኩረት እንዲሰጡ አጋጣሚ ይፈጥርላቸው ነበር።
2. የሰንበት እረፍት ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?
2 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ዛሬ ያሉት ቤተሰቦች ሰንበትን እንዲያከብሩ አይጠብቅባቸውም። ይሁንና ይህ ሕግ ስለ አምላካችን የሚያስተምረን ነገር አለ። ይሖዋ የሕዝቡ መንፈሳዊ ደኅንነት ምንጊዜም ቢሆን ያሳስበዋል። (ኢሳ. 48:17, 18) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለእኛ መንፈሳዊ ደኅንነት እንደሚያስብ ካሳየባቸው መንገዶች አንዱ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም እንዲኖር ዝግጅት ማድረጉ ነው።
3. የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ዓላማ ምንድን ነው?
3 የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ዓላማ ምንድን ነው? ከጥር 2009 አንስቶ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ በሚደረጉበት ምሽት መካሄድ ጀመረ። እንዲህ ያለ ማስተካከያ የተደረገበት አንደኛው ምክንያት ቤተሰቦች በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ የሚያደርጉበት ቋሚ የሆነ አንድ ምሽት በመመደብ መንፈሳዊነታቸውን እንዲያጠናክሩ አጋጣሚ ለመፍጠር ነው። እያንዳንዱ ቤተሰብ የሚቻል ከሆነ የቤተሰብ ጥናት ፕሮግራሙን ቀደም ሲል መጽሐፍ ጥናት ያደርግ ወደነበረበት ምሽት እንዲያዘዋውር ማበረታቻ ተሰጥቶ ነበር። በተጨማሪም ቤተሰቦች ለቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ሰፋ ያለ ጊዜ በመመደብ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እንዲያደርጉ እንዲሁም ለቤተሰቡ ይበልጥ በሚያስፈልገው ነገር ላይ ያተኮረ ጥናት እንዲያካሂዱ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።
4. ቤተሰቦች የአምልኮ ፕሮግራማቸውን በአንድ ሰዓት ብቻ መገደብ ይኖርባቸዋል? አብራራ።
4 በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ላይ ለመገኘት የምንለባብስበት፣ የምንጓዝበትና ሌሎችም ነገሮች የምናደርግበት ጊዜ ያስፈልገን ነበር። ብዙዎቻችን በዚህ የአንድ ሰዓት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ስብሰባው ከሚወስደው ሰዓት የበለጠ ጊዜ እናጠፋ ነበር። በስብሰባ ፕሮግራሞች ላይ ማስተካከያ መደረጉ በአሁኑ ጊዜ ከቤተሰባችን ጋር ሆነን ይሖዋን ማምለክ የምንችልበት አንድ ምሽት አስገኝቶልናል። በመሆኑም የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችንን በአንድ ሰዓት ብቻ መገደብ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ነገሮችና የእያንዳንዱን አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ጊዜውን እንደሁኔታው ማስተካከል ይገባናል።
5. ሙሉውን ጊዜ በቤተሰብ ውይይት ለማድረግ ልንጠቀምበት ይገባል? አብራራ።
5 ሙሉውን ጊዜ በቤተሰብ ውይይት ለማድረግ ልንጠቀምበት ይገባል? ባልና ሚስቶችም ሆኑ ልጆች ያላቸው ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት በሚያደርጉበት ጊዜ እርስ በርስ ይበረታታሉ። (ሮም 1:12) እንዲሁም ቤተሰቡ ይበልጥ ይቀራረባል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ማድረግ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ዓብይ ክፍል ሊሆን ይገባል። ይሁን እንጂ፣ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የተወሰነውን ጊዜ የግል ጥናት ለማድረግ ሊጠቀምበት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ቤተሰቡ አንድ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ እዚያው እንደተቀመጡ እያንዳንዳቸው በግላቸው ማጥናታቸውን መቀጠል ምናልባትም የጉባኤ ዝግጅታቸውን መጨረስ ወይም መጽሔቶችን ማንበብ ይችላሉ። አንዳንድ ቤተሰቦች በዚያ ምሽት ቴሌቪዥን ላለመክፈት ወስነዋል።
6. ውይይቱን እንዴት ማካሄድ ይቻላል?
6 ውይይቱ መካሄድ ያለበት እንዴት ነው? ውይይቱ ሁልጊዜ በጥያቄና መልስ መካሄድ አያስፈልገውም። ብዙ ቤተሰቦች የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ሞቅ ያለና አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ ሲሉ ፕሮግራማቸው በሳምንቱ መሃል የምናደርገው ስብሰባ ዓይነት ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ይጥራሉ። ውይይቱን በተለያዩ ክፍሎች በመከፋፈል ክፍሎቹ በተለያዩ መንገዶች እንዲቀርቡ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስን አብረው ሊያነቡ፣ የተወሰነውን የጉባኤ ስብሰባ ክፍል ሊዘጋጁ እንዲሁም ለአገልግሎት ልምምድ ሊያደርጉ ይችላሉ። በገጽ 6 ላይ አንዳንድ ተጨማሪ አማራጮች ቀርበዋል።
7. ወላጆች ምን ዓይነት መንፈስ እንዲሰፍን መጣር አለባቸው?
7 ወላጆች ምን ዓይነት መንፈስ እንዲሰፍን መጣር አለባቸው? ቤተሰባችሁ ከፕሮግራሙ ይበልጥ የሚጠቀመው ፍቅር ያለበትና ዘና ያለ መንፈስ ሲኖር ነው። የአየሩ ሁኔታ አመቺ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ጥናቱን ከቤት ውጪ ማድረግ ትችላላችሁ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ እረፍት ማድረግ ይቻላል። አንዳንድ ቤተሰቦች ከፕሮግራሙ በኋላ ሻይ ቡና በማለት ዘና ይላሉ። ወላጆች የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸውን ለወቀሳ ወይም ተግሣጽ ለመስጠት መጠቀማቸው ተገቢ ባይሆንም ይህን አጋጣሚ በቤተሰባቸው የሚታዩ አንዳንድ አዝማሚያዎችን ወይም ችግሮችን አንስቶ ለመወያየት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ይሁን እንጂ፣ አንድን ልጅ በወንድሞቹና በእህቶቹ ፊት ላለማሳፈር በቀላሉ እንዲሰማው ሊያደርጉ የሚችሉ የግል ጉዳዮችን በሳምንቱ ውስጥ በሌላ ጊዜ አንስቶ በግለሰብ ደረጃ ማነጋገሩ የተሻለ ነው። የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ድርቅ ያለና አሰልቺ ሊሆን አይገባውም፤ ከዚህ ይልቅ ደስተኛ የሆነውን አምላካችንን መንፈስ የሚያንጸባርቅ መሆን ይኖርበታል።—1 ጢሞ. 1:11
8, 9. የቤተሰብ ራሶች ምን ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?
8 የቤተሰቡ ራስ ምን ዓይነት ዝግጅት ማድረግ ይችላል? የቤተሰቡ ራስ በእያንዳንዱ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ላይ የሚጠናውን ነገር እንዲሁም የሚጠናበትን መንገድ አስቀድሞ በመወሰን ዝግጅት የሚያደርግ ከሆነ ቤተሰቡ ይበልጥ ይጠቀማል። (ምሳሌ 21:5) ባሎች ይህን በተመለከተ ሚስቶቻቸውን ማማከራቸው ጥሩ ይሆናል። (ምሳሌ 15:22) እናንተ የቤተሰብ ራሶች፣ አንዳንድ ጊዜ ልጆቻችሁም ሐሳብ እንዲሰጡ ለምን አታማክሯቸውም? እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ትኩረታቸውን ስለሚስቧቸውና ስለሚያሳስቧቸው ነገሮች ይበልጥ ማወቅ ትችላላችሁ።
9 የቤተሰቡ ራስ ዝግጅት ለማድረግ በየሳምንቱ ሰፊ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልገውም። ቤተሰቡ በየሳምንቱ አንዳንድ ቋሚ ፕሮግራሞችን ሊከተል ስለሚችል በየጊዜው ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ ፕሮግራም ለማዘጋጀት መጨነቅ አይኖርበትም። ቤተሰቡ የአምልኮ ፕሮግራሙን ካደረገ በኋላ በመንፈሳዊ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ማወቅ ስለሚቻል የቤተሰቡ ራስ ከእያንዳንዱ የቤተሰብ አምልኮ በኋላ ለቀጣዩ ሳምንት መዘጋጀቱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ የቤተሰብ ራሶች አጠር ያለ አጀንዳ ጽፈው ቤተሰቡ በቀላሉ ሊያየው በሚችልበት ቦታ ለምሳሌ ፍሪጅ ላይ ይለጥፋሉ። ይህም ቤተሰቡ ፕሮግራሙን በጉጉት እንዲጠብቅ ብሎም አስፈላጊ ከሆነ ዝግጅት ለማድረግ ጊዜ እንዲያገኝ ያስችለዋል።
10. ብቻቸውን የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች የቤተሰብ አምልኮ ምሽትን እንዴት ሊጠቀሙበት ይችላሉ?
10 የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት እኔ ብቻ ብሆንስ? ብቻቸውን የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች የቤተሰብ አምልኮን ምሽት የግል ጥናት ለማድረግ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ጥሩ የግል ጥናት ፕሮግራም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን፣ የጉባኤ ዝግጅትን እንዲሁም መጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶችን ማንበብን ይጨምራል። አንዳንድ አስፋፊዎች ከእነዚህ ነገሮች በተጨማሪ በተወሰኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምርምር ያደርጋሉ። አንዳንድ ጊዜም ሌላ አስፋፊ ወይም ቤተሰብ በጥናታቸው ላይ እንዲገኝ በመጋበዝ የሚያንጽ ውይይት ሊያደርጉ ይችላሉ።
11, 12. ቋሚ የሆነ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
11 ቋሚ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ምን ጥቅሞች አሉት? በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ የሙሉ ነፍስ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሁሉ ይበልጥ ወደ ይሖዋ መቅረብ ይችላሉ። በተጨማሪም አንድ ላይ ይሖዋን የሚያመልኩ ቤተሰቦች አንድነታቸው ይጠናከራል። አንድ ባልና ሚስት ያገኙትን በረከት አስመልክተው እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት የሌለብን አቅኚዎች ስንሆን የቤተሰብ አምልኮ የምናደርግበትን ምሽት የምንጠባበቀው በጉጉት ነው። እርስ በርስም ሆነ በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ጋር ይበልጥ እንደተቀራረብን ይሰማናል። የቤተሰብ አምልኮ በምናደርግበት ቀን ገና ጠዋት ስንነሳ እርስ በርሳችን ‘ዛሬ ማታ ምን አለን? የቤተሰብ አምልኮ!’ እንባባላለን።”
12 የቤተሰብ አምልኮ ዝግጅት መኖሩ በሥራ የተወጠሩ ቤተሰቦችንም ይጠቅማል። ብቻዋን ሁለት ልጆቿን የምታሳድግ የዘወትር አቅኚ የሆነች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ቀደም ሲል የቤተሰብ ጥናታችን ቋሚ አልነበረም። በጣም ይደክመኝ ስለነበር የማናደርግባቸው ጊዜያት ነበሩ። ጊዜዬን አብቃቅቼ ሁሉንም ነገር ማከናወን አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። ስለሆነም ይህን ደብዳቤ የጻፍኩላችሁ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራምን በተመለከተ በጣም እንደማመሰግናችሁ ለመግለጽ ነው። በአሁኑ ጊዜ ቋሚ የቤተሰብ ጥናት በማድረግ ረገድ ስለተሳካልን ብዙ ጥቅሞች አግኝተናል።”
13. ቤተሰባችሁ ከዚህ ዝግጅት የሚያገኘው ጥቅም በምን ላይ የተመካ ነው?
13 እንደ ሰንበት እረፍት ሁሉ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራምም ለቤተሰቦች ጥቅም የሚያስገኝ በሰማይ የሚኖረው አባታችን ስጦታ ነው። (ያዕ. 1:17) እስራኤላውያን ቤተሰቦች በመንፈሳዊ የሚያገኙት ጥቅም የሰንበት እረፍትን በሚጠቀሙበት መንገድ ላይ የተመካ ነበር። በተመሳሳይም ቤተሰባችን የሚያገኘው ጥቅም ለቤተሰብ አምልኮ የመደብነውን ምሽት በምንጠቀምበት መንገድ ላይ የተመካ ነው። (2 ቆሮ. 9:6፤ ገላ. 6:7, 8፤ ቆላ. 3:23, 24) ቤተሰባችሁ በዚህ ዝግጅት በሚገባ የሚጠቀም ከሆነ ልክ እንደ መዝሙራዊው “እኔ በበኩሌ ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል። . . . ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ” እንደሚል ጥርጥር የለውም።—መዝ. 73:28 NW
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ድርቅ ያለና አሰልቺ ሊሆን አይገባውም፤ ከዚህ ይልቅ ደስተኛ የሆነውን አምላካችንን መንፈስ የሚያንጸባርቅ መሆን ይኖርበታል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በቅርብ አስቀምጡት
በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ውስጥ ልታካትቷቸው የምትችሏቸው አንዳንድ ነገሮች
መጽሐፍ ቅዱስ፦
• ከሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ውስጥ የተወሰነውን አብራችሁ አንብቡ። አጻጻፉ የትረካ ይዘት ካለው አንድ ሰው ተራኪውን ሌሎች ደግሞ የተለያዩ ባለ ታሪኮችን ወክለው ማንበብ ይችላሉ።
• ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባቡ ውስጥ የተወሰነውን በድራማ መልክ አቅርቡት።
• እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎቹን አስቀድሞ በማንበብ አንድ ወይም ሁለት ጥያቄዎች አዘጋጅቶ እንዲመጣ አድርጉ። ከዚያም እያንዳንዱ ሰው ባመጣው ጥያቄ ላይ አብራችሁ ምርምር አድርጉ።
• በየሳምንቱ በአንድ ካርድ ላይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጽፋችሁ ጥቅሱን በቃላችሁ ለመያዝና ለማብራራት ጥረት አድርጉ። ካርዶቹን ካጠራቀማችሁ በኋላ ምን ያህል ጥቅሶችን በቃላችሁ እንደምታስታውሱ ለማወቅ በየሳምንቱ ተጠያየቁ።
• በድምፅ የተቀዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ከፍታችሁ መጽሐፍ ቅዱሳችሁን አውጥታችሁ ተከታተሉ።
የጉባኤ ስብሰባዎች፦
• የተወሰኑ የጉባኤ ስብሰባ ክፍሎችን አብራችሁ ተዘጋጁ።
• በቀጣዩ ሳምንት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚዘመሩ የመንግሥቱን መዝሙሮች ተለማመዱ።
• ከቤተሰቡ አባላት መካከል አንዱ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ ክፍል ካለው ወይም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ሠርቶ ማሳያ ካለው እንዴት ሊያቀርበው እንደሚችል ሐሳብ ተለዋወጡ፤ አሊያም በቤተሰቡ ፊት በማቅረብ እንዲለማመድ አድርጉ።
ለቤተሰቡ የሚያስፈልጉ ነገሮች፦
• የወጣቶች ጥያቄ ወይም ከታላቁ አስተማሪ ተማር በተባሉት መጽሐፎች ውስጥ አንድ ርዕስ መርጣችሁ ተወያዩ።
• በትምህርት ቤት ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ሁኔታዎች መልስ መስጠት የሚቻልበትን መንገድ ተለማመዱ።
• ወላጆች እንደ ልጆች፣ ልጆች ደግሞ እንደ ወላጆች በመሆን ልምምድ አድርጉ። ልጆች በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ምርምር አድርገው በመምጣት ለወላጆቻቸው ያስረዳሉ።
አገልግሎት፦
• ቅዳሜና እሁድ ለሚደረገው አገልግሎት መግቢያዎችን ተለማመዱ።
• የቤተሰቡ አባላት በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ወይም በእረፍት ጊዜ አገልግሎታቸውን ለማስፋት ምን ተጨባጭ ግብ ማውጣት እንደሚችሉ ውይይት አድርጉ።
• አገልግሎት ላይ ሊያጋጥሙ ለሚችሉ የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ስለሚቻልበት መንገድ ምርምር እንዲያደርግ ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ጥቂት ደቂቃዎች መድቡ፤ ከዚያም ልምምድ አድርጉ።
ተጨማሪ ሐሳቦች፦
• በቅርቡ ከደረሷችሁ መጽሔቶች ላይ አንድ ርዕስ አንብቡ።
• እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በቅርብ ከደረሷችሁ መጽሔቶች ውስጥ ደስ ያለውን ርዕስ አስቀድሞ አንብቦ እንዲመጣ በማድረግ ስላነበበው ነገር ሪፖርት እንዲያቀርብ አድርጉ።
• አልፎ አልፎ አንድ አስፋፊ ወይም አንድ ባልና ሚስት በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ እንዲገኙ ጋብዙ፤ ምናልባትም ቃለ ምልልስ ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ።
• ከቪዲዮዎቻችን መካከል አንዱን ተመልክታችሁ ውይይት አድርጉበት።
• “የወጣቶች ጥያቄ” ወይም “ቤተሰብ የሚወያይበት” በሚሉት የንቁ! መጽሔት አምዶች ላይ ውይይት አድርጉ።
• “ልጆቻችሁን አስተምሩ” ወይም “ለታዳጊ ወጣቶች” የሚሉትን የመጠበቂያ ግንብ አምዶች አንብባችሁ ውይይት አድርጉባቸው።
• በቅርብ ከወጣው የዓመት መጽሐፍ ወይም ባለፈው አውራጃ ስብሰባ ላይ ካገኘነው አዲስ ጽሑፍ ላይ የተወሰነው ክፍል አንብባችሁ ውይይት አድርጉበት።
• በአውራጃ፣ በልዩ ወይም በወረዳ ስብሰባ ላይ ከተካፈላችሁ በኋላ ዋና ዋና ነጥቦችን ከልሱ።
• የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በቀጥታ ከተመለከታችሁ በኋላ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምራችሁ ተወያዩ።
• አንድ ላይ ሆናችሁ አንድ ፕሮጀክት ሥሩ፤ ለምሳሌ ሞዴል፣ ካርታ ወይም ሰንጠረዥ ማዘጋጀት ትችላላችሁ።