መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት
አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ዮሐና የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር ሐና የምትባልን ሴት ቤቷ ሄዳ እያወያየቻት እንዳለች አድርገን እናስብ።
አምላክ እየደረሰብን ስላለው መከራና ሥቃይ ምን ይሰማዋል?
ዮሐና፦ ደህና ነሽ ሐና? በድጋሚ በመገናኘታችን ደስ ብሎኛል።
ሐና፦ እኔም ደስ ብሎኛል።
ዮሐና፦ ባለፈው ጊዜ አምላክ እየደረሰብን ስላለው መከራና ሥቃይ ምን እንደሚሰማው ተወያይተን ነበር።a ትዝ ይልሽ ከሆነ በተለይ እናትሽ የመኪና አደጋ ከደረሰባቸው በኋላ ይህ ጥያቄ በአእምሮሽ ይጉላላ እንደነበር ገልጸሽልኝ ነበር። ለመሆኑ እናትሽ እንዴት ናቸው?
ሐና፦ ምን እባክሽ፣ ብዙም ጤና የላትም። እርግጥ ዛሬ ሻል ብሏታል።
ዮሐና፦ አይዞሽ፣ እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ችሎ መኖር ቀላል አይደለም።
ሐና፦ እውነትሽን ነው። አንዳንድ ጊዜ እስከ መቼ እንዲህ እየተሠቃየች ትኖራለች ብዬ አስባለሁ።
ዮሐና፦ እንዲህ ቢሰማሽ አያስገርምም። የምታስታውሺ ከሆነ፣ ባለፈው ጊዜ በውይይታችን መደምደሚያ ላይ ‘አምላክ መከራንና ሥቃይን ማስወገድ የሚያስችል ኃይል እያለው እንዲህ ያላደረገው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ አንስቼልሽ ነበር።
ሐና፦ አዎ፣ አስታውሳለሁ።
ዮሐና፦ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ከማየታችን በፊት ባለፈው ጊዜ የተወያየንባቸውን አንዳንድ ነጥቦች እስቲ ላስታውስሽ።
ሐና፦ ጥሩ።
ዮሐና፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰ አንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋይም እንኳ ‘አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮበት እንደነበር ተመልክተናል። ይሁንና አምላክ ያን ታማኝ አገልጋይ ይህን ጥያቄ በማንሳቱ አልነቀፈውም ወይም ደግሞ እምነት እንደሚጎድለው አድርጎ አልተመለከተውም።
ሐና፦ ይህን ሐሳብ አላውቀውም ነበር።
ዮሐና፦ በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ መከራና ሥቃይ ሲደርስብን ሲመለከት እንደሚያዝን ተወያይተን ነበር። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሕዝቦቹ ሲጨነቁ ሲያይ እሱም ‘እንደተጨነቀ’ ይገልጻል።b አምላክ መከራና ሥቃይ ሲደርስብን ሲያይ እንደሚያዝን ማወቃችን አያጽናናም?
ሐና፦ አዎ፣ በጣም ያጽናናል እንጂ።
ዮሐና፦ በመጨረሻም ፈጣሪያችን ካለው ታላቅ ኃይል አንጻር ሲታይ በፈለገው ጊዜ ጣልቃ ሊገባና በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ ሊያስወግድ እንደሚል ማሰብ ምክንያታዊ እንደሆነ ተነጋግረን ነበር።
ሐና፦ እኔም እኮ ግራ የሚገባኝ ይህ ነው። አምላክ እየደረሰብን ያለውን መከራ ማስወገድ የሚያስችል ኃይል እያለው ይህ ሁሉ ችግር ሲደርስብን ለምን ዝም ብሎ ይመለከታል?
እውነተኛው ማን ነው?
ዮሐና፦ ለዚህ ጥያቄሽ መልስ ለማግኘት የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ይኸውም የዘፍጥረት መጽሐፍን እስቲ እናውጣ። ስለ አዳምና ሔዋን እንዲሁም እንዳይበሉ ስለተከለከሉት ፍሬ የሚገልጸውን ታሪክ ታውቂዋለሽ?
ሐና፦ አዎ፣ ይህን ታሪክ ሰንበት ትምህርት ቤት ተምሬዋለሁ። አምላክ ከአንድ ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ ከልክሏቸው ነበር፤ እነሱ ግን ከፍሬው በሉ።
ዮሐና፦ ትክክል ነሽ። አሁን አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንዲሠሩ ያደረጓቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ እስቲ እንመልከት። እነዚህ ነገሮች ‘ሥቃይና መከራ የሚደርስብን ለምንድን ነው?’ ከሚለው ጥያቄ መልስ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ከቁጥር 1 እስከ 5ን ልታነብቢው ትችያለሽ?
ሐና፦ እሺ። “እባብ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው የዱር አራዊት ሁሉ ተንኰለኛ ነበረ፤ ሴቲቱንም፣ ‘በእርግጥ እግዚአብሔር፣ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ” ብሎአልን?’ አላት። ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር “በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁ” ብሎአል።’ እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤ ‘መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው።’”
ዮሐና፦ አመሰግንሻለሁ። እስቲ በዚህ ሐሳብ ላይ ጥቂት እንወያይ። በመጀመሪያ ሔዋንን አንድ እባብ እንዳነጋገራት ልብ በይ። በእባብ አማካኝነት ሔዋንን ያነጋገራት ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተገልጿል።c ሰይጣን፣ አምላክ እንዳይበሉ የከለከላቸውን ዛፍ አስመልክቶ ለሔዋን ጥያቄ አቀረበላት። አዳምና ሔዋን ከዛፉ ፍሬ ቢበሉ የሚደርስባቸውን ቅጣት በተመለከተ አምላክ ምን እንዳለ ልብ ብለሻል?
ሐና፦ ትሞታላችሁ ብሏቸዋል።
ዮሐና፦ ትክክል ነሽ። ሰይጣን ቀጥሎ የተናገረው ነገር በአምላክ ላይ የተሰነዘረ ትልቅ ክስ ነው። “መሞት እንኳ አትሞቱም” እንዳላቸው ልብ በይ። ሰይጣን እንዲህ ሲል አምላክ ውሸታም እንደሆነ መናገሩ ነበር!
ሐና፦ ይህን ልብ ብየው አላውቅም ነበር።
ዮሐና፦ ሰይጣን፣ አምላክ ውሸታም እንደሆነ በመናገር የሰነዘረው ክስ ትክክል መሆን አለመሆኑ እንዲረጋገጥ ከተፈለገ ጊዜ ይጠይቃል። እንዲህ ያልኩሽ ለምን እንደሆነ ገብቶሻል?
ሐና፦ አይ፣ በደንብ አልገባኝም።
ዮሐና፦ ነጥቡ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልሽ አንድ ምሳሌ ልንገርሽ። እኔ ከአንቺ ይበልጥ ጠንካራ ነኝ በማለት ተፎካከርኩሽ እንበል። ማናችን ይበልጥ ጠንካራ እንደሆንን ማረጋገጥ የሚቻለው እንዴት ነው ትያለሽ?
ሐና፦ ምናልባት ሁለታችንም ጉልበታችንን የሚፈትን ነገር በማድረግ ማን ጠንካራ መሆኑን ማሳየት እንችል ይሆናል።
ዮሐና፦ እውነትሽን ነው። ምናልባትም አንድ ከባድ ዕቃ መርጠን ማናችን ማንሳት እንደምንችል መሞከር ሊሆን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ማን ጠንካራ ነው የሚለውን መለየት ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም።
ሐና፦ ምን ለማለት እንደፈለግሽ ገብቶኛል።
ዮሐና፦ ሆኖም ከአንቺ ይበልጥ ጠንካራ ነኝ ከማለት ይልቅ ከአንቺ ይበልጥ ሐቀኛ እንደሆንኩ አድርጌ ብናገርስ? ይህን ማረጋገጥ ይበልጥ አስቸጋሪ የሚሆን አይመስልሽም?
ሐና፦ ልክ ነሽ፣ አስቸጋሪ ይመስለኛል።
ዮሐና፦ ሐቀኝነት ልክ እንደ ጥንካሬ በቀላል ሙከራ ሊረጋገጥ የሚችል ነገር አይደለም።
ሐና፦ እውነትሽን ነው።
ዮሐና፦ ስለዚህ ሰዎች ከሁለታችን ማናችን ሐቀኛ እንደሆንን ማረጋገጥ የሚችሉት በቂ ጊዜ ተሰጥቷቸው አኗኗራችንን ማየት ከቻሉ ብቻ ነው።
ሐና፦ ይህ ምክንያታዊ ይመስላል።
ዮሐና፦ እስቲ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ያለውን ዘገባ መለስ ብለሽ ተመልከቺው። ታዲያ ሰይጣን ከአምላክ ይበልጥ ኃይል እንዳለው ነው የተናገረው?
ሐና፦ አይደለም።
ዮሐና፦ ያ ቢሆን ኖሮ አምላክ፣ ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑን በቀላሉ ማሳየት ይችል ነበር። ሆኖም ሰይጣን የተናገረው ከአምላክ ይልቅ እሱ ሐቀኛ እንደሆነ ነው። ሰይጣን ሔዋንን ‘አምላክ ዋሽቷችኋል፤ እኔ ግን እውነቱን እየነገርኩሽ ነው’ ያላት ያህል ነበር።
ሐና፦ በጣም ይገርማል።
ዮሐና፦ ጥበበኛ የሆነው አምላክ ይህ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ በቂ ጊዜ ፈቀደ። ማን ሐቀኛና ማን ውሸታም እንደሆነ በጊዜ ሂደት መታወቁ አይቀርም።
መልስ የሚያሻው ወሳኝ ጥያቄ
ሐና፦ ታዲያ ሔዋን ስትሞት አምላክ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑ ተረጋግጦ የለም?
ዮሐና፦ በተወሰነ ደረጃ ተረጋግጧል። ይሁንና ሰይጣን የሰነዘረው ክስ ይህ ብቻ አልነበረም። እስቲ ቁጥር 5ን እንደገና ተመልከቺው። እዚህ ላይ ሰይጣን ሔዋንን ምን ሌላ ተጨማሪ ነገር እንደነገራት ልብ ብለሻል?
ሐና፦ ከፍሬው ከበላች ዓይኖቿ እንደሚገለጡ ነግሯታል።
ዮሐና፦ ልክ ነሽ፤ እንዲያውም ‘መልካምና ክፉን በማወቅ እንደ አምላክ እንደሚሆኑ’ ነግሯታል። ስለዚህ ሰይጣን፣ አምላክ የሰው ልጆችን አንድ መልካም ነገር እንዳስቀረባቸው አድርጎ ተናግሯል።
ሐና፦ አሃ፣ አሁን ገባኝ።
ዮሐና፦ ይህም ቢሆን መልስ የሚያሻው ወሳኝ ጥያቄ ነው።
ሐና፦ ምን ማለትሽ ነው?
ዮሐና፦ ሰይጣን እንዲህ ብሎ ሲናገር ሔዋንን ማለትም የሰው ልጆችን አምላክ ከሚገዛቸው ይልቅ ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ የተሻለ ነው ማለቱ ነበር። ይሖዋ ይህ ጥያቄም ቢሆን በተሻለ ሁኔታ መልስ እንዲያገኝ ማድረግ የሚቻለው ሰይጣን የተናገረው ነገር ትክክል መሆን አለመሆኑ እንዲረጋገጥ ጊዜ በመፍቀድ እንደሆነ ያውቃል። ስለሆነም አምላክ፣ ሰይጣን ይህን ዓለም ለተወሰነ ጊዜ እንዲገዛ ፈቀደለት። ይህ ሁሉ መከራ እየደረሰብን ያለውም ለዚህ ነው፤ ይህን ዓለም እየገዛ ያለው አምላክ ሳይሆን ሰይጣን ነው።d ይሁንና አንድ የምሥራች አለ።
ሐና፦ ምን ይሆን ባክሽ?
ዮሐና፦ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በተመለከተ ሁለት አስደሳች እውነቶችን ይነግረናል። በመጀመሪያ ይሖዋ የሚደርስብን ሥቃይ ያሳስበዋል። ለምሳሌ በመዝሙር 31:7 ላይ የሚገኘውን ንጉሥ ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ ተመልከቺ። ዳዊት በሕይወት ዘመኑ የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ያጋጠሙት ቢሆንም ወደ አምላክ ምን ብሎ እንደጸለየ ልብ በይ። እባክሽ ጥቅሱን ልታነብቢው ትችያለሽ?
ሐና፦ እሺ። “በምሕረትህ ደስ እሰኛለሁ፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤ መከራዬን አይተሃልና፤ የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል” ይላል።
ዮሐና፦ ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ዳዊት መከራ ቢደርስበትም እንኳ ይሖዋ የሚደርስበትን ሥቃይ እንደሚመለከት ማወቁ አጽናንቶታል። አንቺስ፣ ይሖዋ ሁሉንም ነገር ሌላው ቀርቶ ሌሎች ሰዎች ሊረዱልን የማይችሉትን የስሜት ሥቃይ እንኳ እንደሚረዳልን ማወቅሽ አያጽናናሽም?
ሐና፦ እንዴታ!
ዮሐና፦ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አምላክ ለዘላለም እየተሠቃየን እንድንኖር አይፈቅድም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ክፉ የሆነውን የሰይጣንን አገዛዝ በቅርቡ ጠራርጎ እንደሚያጠፋው ይገልጻል። ከዚያም በአንቺም ሆነ በእናትሽ ላይ የደረሰውን ሥቃይ ጨምሮ ማንኛውንም መጥፎ ነገር ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። በሚቀጥለው ሳምንት መጥቼ አምላክ በቅርቡ ማንኛውንም ዓይነት መከራ እንደሚያስወግድ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ ብንወያይ ምን ይመስልሻል?e
ሐና፦ ደስ ይለኛል!
ግራ የሚያጋባህ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታቸው ማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር መወያየት ያስደስታቸዋል።
a በዚህ መጽሔት ሐምሌ 1, 2013 እትም ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት—አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው መከራ ያሳስበዋል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b ኢሳይያስ 63:9ን ተመልከት።
d ዮሐንስ 12:31ን እና 1 ዮሐንስ 5:19ን ተመልከት።
e ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት።