የጥናት ርዕስ 44
መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ወዳጅነታችሁን አጠናክሩ
“እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው።”—ምሳሌ 17:17
መዝሙር 101 በአንድነት አብሮ መሥራት
ማስተዋወቂያa
1-2. በ1 ጴጥሮስ 4:7, 8 መሠረት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚረዳን ምንድን ነው?
‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ማብቂያ ይበልጥ እየተቃረበ ሲሄድ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:1) ለምሳሌ ያህል፣ በምዕራብ አፍሪካ ባለች አንዲት አገር ውስጥ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ አገሪቱ በነውጥና በዓመፅ ታመሰች። በግጭቱ የተነሳ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከስድስት ወር ለሚበልጥ ጊዜ በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻሉም ነበር። ታዲያ ይህን ከባድ ሁኔታ እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምንድን ነው? አንዳንዶቹ፣ የተሻለ መረጋጋት ባለበት አካባቢ በሚኖሩ ወንድሞቻቸው ቤት አረፉ። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለ ሁኔታ ባጋጠመኝ ወቅት፣ የሚያስጠጉኝ ወዳጆች ያሉኝ በመሆኑ በጣም ተደስቼ ነበር። እርስ በርስ ተበረታተናል።”
2 ‘ታላቁ መከራ’ ሲጀምር፣ የሚወዱን ጥሩ ወዳጆች ካሉን እንደምንደሰት ጥያቄ የለውም። (ራእይ 7:14) በመሆኑም ከአሁኑ ወዳጅነታችንን ማጠናከራችን በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥሮስ 4:7, 8ን አንብብ።) በዚህ ረገድ ኤርምያስ ካጋጠመው ነገር ብዙ መማር እንችላለን፤ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት በነበረው ጊዜ ላይ የኤርምያስ ጓደኞች ሕይወቱን አትርፈውለታል።b ታዲያ የኤርምያስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
ከኤርምያስ ምሳሌ ተማሩ
3. (ሀ) ኤርምያስ ራሱን ከሌሎች እንዲያገልል ሊያደርጉ የሚችሉ ምን ሁኔታዎች አጋጥመውታል? (ለ) ኤርምያስ ጸሐፊው ለሆነው ለባሮክ ምን ነግሮታል? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
3 ኤርምያስ ቢያንስ ለ40 ዓመታት ያህል የኖረው ዓመፀኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ነው፤ ከእነዚህም መካከል ጎረቤቶቹ፣ ምናልባትም በትውልድ ከተማው በአናቶት ያሉ አንዳንድ ዘመዶቹ ይገኙበታል። (ኤር. 11:21፤ 12:6) ያም ቢሆን ኤርምያስ ራሱን ከሌሎች አላገለለም። እንዲያውም ታማኝ ጸሐፊው ለሆነው ለባሮክ ስሜቱን አውጥቶ ነግሮታል፤ እኛም ኤርምያስ ምን ተሰምቶት እንደነበር ማወቅ ችለናል። (ኤር. 8:21፤ 9:1፤ 20:14-18፤ 45:1) ባሮክ፣ ኤርምያስ ስለገጠሙት አስገራሚ ክንውኖች በሚጽፍበት ወቅት ሁለቱ ሰዎች አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት እየጨመረ እንደሄደ መገመት አያዳግትም።—ኤር. 20:1, 2፤ 26:7-11
4. ይሖዋ ኤርምያስን ምን እንዲያደርግ ነግሮታል? ይህ ሥራ በኤርምያስና በባሮክ መካከል ያለው ወዳጅነት እንዲጠናከር ያደረገው እንዴት ነው?
4 ኤርምያስ በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጣውን ጥፋት በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት እስራኤላውያንን በድፍረት ያስጠነቅቅ ነበር። (ኤር. 25:3) ይሖዋ፣ ሕዝቡ ንስሐ ለመግባት እንዲነሳሱ ሲል ማስጠንቀቂያዎቹን በጥቅልል ላይ እንዲጽፍ ለኤርምያስ ነገረው። (ኤር. 36:1-4) ይህ ሥራ የተወሰኑ ወራት ሳይፈጅ አልቀረም፤ ኤርምያስና ባሮክ አምላክ በሰጣቸው በዚህ ሥራ አብረው በሚካፈሉበት ወቅት እምነታቸውን የሚያጠናክሩ ውይይቶች አድርገው እንደሚሆን አያጠራጥርም።
5. ባሮክ ለኤርምያስ ጥሩ ወዳጅ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
5 የማስጠንቀቂያው መልእክት በጥቅልሉ ላይ ከተጻፈ በኋላ ኤርምያስ፣ መልእክቱን እንደሚያደርስ በመተማመን ባሮክን ላከው። (ኤር. 36:5, 6) ባሮክም ይህን አደገኛ ተልእኮ በድፍረት ተወጣ። ኤርምያስ፣ ባሮክ ወደ ቤተ መቅደሱ ግቢ ሄዶ የታዘዘውን ነገር እንዳደረገ ሲያውቅ በእሱ ምን ያህል እንደኮራ አስበው። (ኤር. 36:8-10) የይሁዳ መኳንንት ባሮክ ያደረገውን ሲሰሙ፣ ጥቅልሉን ለእነሱም ጮክ ብሎ እንዲያነብላቸው አዘዙት። (ኤር. 36:14, 15) መኳንንቱ የኤርምያስን መልእክት ለንጉሥ ኢዮዓቄም ለመናገር ወሰኑ። በመሆኑም በደግነት ባሮክን “ሂድ፣ አንተና ኤርምያስ ተደበቁ፤ ያላችሁበትንም ማንም ሰው አይወቅ” አሉት። (ኤር. 36:16-19) ይህ በእርግጥም ጠቃሚ ምክር ነበር!
6. ኤርምያስና ባሮክ ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው ምን አደረጉ?
6 ንጉሥ ኢዮዓቄም፣ ኤርምያስ የጻፈውን መልእክት ሲሰማ በጣም ከመናደዱ የተነሳ ጥቅልሉን አቃጠለው፤ ከዚያም ኤርምያስና ባሮክ እንዲታሰሩ ትእዛዝ አስተላለፈ። ኤርምያስ ግን በዚህ አልተሸበረም። ኤርምያስ ሌላ ጥቅልል ወስዶ ለባሮክ ሰጠው፤ ከዚያም ባሮክ፣ ኤርምያስ በቃል እያስጻፈው የይሖዋን መልእክት ይኸውም “የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓቄም በእሳት ባቃጠለው ጥቅልል ላይ የነበረውን ቃል ሁሉ” በጥቅልሉ ላይ አሰፈረ።—ኤር. 36:26-28, 32
7. ኤርምያስና ባሮክ አብረው መሥራታቸው ምን ጥቅም አስገኝቶላቸው ሊሆን ይችላል?
7 አስቸጋሪ ሁኔታን አብረው ያሳለፉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ጠንካራ ወዳጅነት ይኖራቸዋል። ከዚህ አንጻር ኤርምያስና ባሮክ፣ ክፉው ንጉሥ ኢዮዓቄም ያቃጠለውን ጥቅልል ለመተካት አብረው ሲሠሩ እርስ በርስ ይበልጥ እንደተዋወቁና ወዳጅነታቸው እንደተጠናከረ መገመት እንችላለን። እነዚህ ሁለት ታማኝ ሰዎች ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
የልባችሁን አውጥታችሁ ተነጋገሩ
8. የጠበቀ ወዳጅነት እንዳንመሠርት እንቅፋት የሚሆንብን ምን ሊሆን ይችላል? ሆኖም ወዳጆች ለማፍራት ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
8 ከዚህ ቀደም አንድ ሰው ስሜታችንን ጎድቶት ከነበረ የልባችንን አውጥተን ለሌሎች መናገር ከባድ ሊሆንብን ይችላል። (ምሳሌ 18:19, 24) በሌላ በኩል ደግሞ የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ጊዜውም ሆነ ጉልበቱ እንደሌለን ይሰማን ይሆናል። ያም ቢሆን የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የማይቻል ነገር እንደሆነ ልናስብ አይገባም። ወንድሞቻችን በመከራ ወቅት ከጎናችን እንዲሆኑ ከፈለግን በአሁኑ ጊዜ እነሱን ማመንን እንዲሁም ለእነሱ የልባችንን አውጥተን መናገርን መልመድ ያስፈልገናል። ይህ እውነተኛ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ነው።—1 ጴጥ. 1:22
9. (ሀ) ኢየሱስ ወዳጆቹን እንደሚተማመንባቸው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የልብን አውጥቶ መናገር ወዳጅነትን የሚያጠናክረው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።
9 ኢየሱስ ለወዳጆቹ ሐሳቡንና ስሜቱን በመናገር እንደሚተማመንባቸው አሳይቷል። (ዮሐ. 15:15) እኛም ስለሚያስደስቱን፣ ስለሚያሳስቡንና ስለሚያስከፉን ነገሮች ለወዳጆቻችን በመናገር የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። አንድ ሰው ሲያዋራህ በጥሞና አዳምጥ፤ ይህን ስታደርግ ከአመለካከታችሁ፣ ከስሜታችሁና ከግቦቻችሁ ጋር በተያያዘ ብዙ የምትመሳሰሉባቸው ነገሮች እንዳሉ ልታስተውል ትችላለህ። በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ሲንዲ የተባለችን እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሲንዲ፣ በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከምትገኝ ማሪ ሉዊዝ የተባለች አቅኚ ጋር ወዳጅነት መሠረተች። ሲንዲ እና ማሪ ሉዊዝ በየሳምንቱ ሐሙስ ጠዋት ላይ አብረው የሚያገለግሉ ሲሆን ስለተለያዩ ጉዳዮች የውስጣቸውን አውጥተው ያወራሉ። ሲንዲ “ትልቅ ቦታ ስለሚሰጣቸው ጉዳዮች ከወዳጆቼ ጋር ማውራት ያስደስተኛል፤ ምክንያቱም ይህን ማድረጋችን እነሱን ይበልጥ ለማወቅና ለመረዳት ያስችለኛል” ብላለች። ወዳጅነት የሚጠናከረው ሐሳባችንን እና ስሜታችንን አውጥተን በግልጽ የምንነጋገር ከሆነ ነው። አንተም ከሌሎች ጋር ስትጨዋወት እንደ ሲንዲ የልብህን አውጥተህ የምትናገር ከሆነ ከእነሱ ጋር ያለህ ወዳጅነት መጠናከሩ አይቀርም።—ምሳሌ 27:9
አብራችሁ ሥሩ
10. በምሳሌ 27:17 መሠረት ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አብረን መሥራታችን ምን ውጤት ይኖረዋል?
10 እንደ ኤርምያስና ባሮክ ሁሉ እኛም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አብረን ስንሠራ እንዲሁም ያሏቸውን ግሩም ባሕርያት ስንመለከት ከእነሱ መማራችንና ይበልጥ መቀራረባችን አይቀርም። (ምሳሌ 27:17ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ ከጓደኛህ ጋር አገልግሎት ላይ ሆናችሁ ጓደኛህ ለእምነቱ በድፍረት ጥብቅና ሲቆም ወይም ስለ ይሖዋ እና ስለ ዓላማዎቹ ከልቡ ሲናገር ስትመለከት ምን ይሰማሃል? ጓደኛህን ይበልጥ እንደምትወደው የታወቀ ነው።
11-12. አብሮ ማገልገል ወዳጅነታችንን ለማጠናከር እንደሚረዳን የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
11 አብሮ ማገልገል፣ ይበልጥ እንደሚያቀራርብ የሚያሳዩ ሁለት ተሞክሮዎችን እንመልከት። የ23 ዓመት ወጣት የሆነችው አደሊን፣ ካንዲስ የተባለችውን ጓደኛዋን ብዙም ወዳልተሰበከበት ክልል ሄደው እንዲያገለግሉ ጠየቀቻት። አደሊን እንዲህ ብላለች፦ “ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት እንዲቀጣጠልና ከአገልግሎታችን የምናገኘው ደስታ እንዲጨምር ፈልገን ነበር። ሁለታችንም በመንፈሳዊ የሚያነቃቃን ነገር አስፈልጎን ነበር።” ታዲያ አብረው በማገልገላቸው የተጠቀሙት እንዴት ነው? አደሊን እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ላይ ምን እንደተሰማን፣ ከሰዎች ጋር ካደረግነው ውይይት ትኩረታችንን የሳበው ምን እንደሆነ እንዲሁም በአገልግሎታችን ላይ የይሖዋን እጅ ያየነው እንዴት እንደሆነ እንወያይ ነበር። በምናደርገው ውይይት ሁለታችንም የምንደሰት ሲሆን ጭውውታችን ይበልጥ ለመተዋወቅም ረድቶናል።”
12 ሌይላ እና ማሪያን የተባሉ በፈረንሳይ የሚኖሩ ሁለት ያላገቡ እህቶች፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በባንጊ ለአምስት ሳምንት ለመስበክ ወደዚያ ሄዱ። ሌይላ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ማሪያን አንዳንድ ችግሮች ቢያጋጥሙንም በግልጽ መነጋገራችንና ከልብ መዋደዳችን ወዳጅነታችን እንዲጠናከር ረድቶናል። ማሪያን አዳዲስ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟት የምትወጣበትን መንገድ፣ ለአገሩ ሰዎች ያላትን ፍቅር እንዲሁም የአገልግሎት ቅንዓቷን ስመለከት ይበልጥ አደነቅኳት።” እነዚህን ጥቅሞች ለማግኘት ወደ ሌላ አገር መሄድ አያስፈልግህም። ከአንድ የእምነት ባልንጀራህ ጋር በጉባኤያችሁ ክልል ውስጥ ባገለገልክ ቁጥር ከግለሰቡ ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅና ወዳጅነታችሁን ለማጠናከር የሚያስችል አጋጣሚ ታገኛለህ።
መልካም ጎናቸው ላይ አተኩሩ፤ ይቅር ባይ ሁኑ
13. ከወዳጆቻችን ጋር አብረን ስንሠራ ምን እናስተውል ይሆናል?
13 ከወዳጆቻችን ጋር አብረን ስንሠራ መልካም ጎናቸውን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ ድክመታቸውንም ማስተዋላችን አይቀርም። ታዲያ ወዳጅነታችንን ጠብቀን ለመቀጠል የሚረዳን ምንድን ነው? እስቲ የኤርምያስን ምሳሌ እንደገና እንመልከት። ኤርምያስ የሌሎችን መልካም ጎን እንዲመለከትና ድክመታቸውን ችላ ብሎ እንዲያልፍ የረዳው ምንድን ነው?
14. ኤርምያስ ስለ ይሖዋ ምን ተገንዝቧል? ይህስ የረዳው እንዴት ነው?
14 ኤርምያስ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል፤ በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን የአንደኛና የሁለተኛ ነገሥት መጻሕፍት የጻፈው እሱ ሳይሆን አይቀርም። ኤርምያስ እነዚህን መጻሕፍት ሲጽፍ፣ ይሖዋ ፍጹማን ላልሆኑ የሰው ልጆች ምን ያህል ምሕረት እንደሚያሳይ ይበልጥ ተገንዝቦ መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ አክዓብ ከመጥፎ ድርጊቱ ንስሐ ስለገባ ይሖዋ በቤተሰቡ ላይ የሚመጣውን ጥፋት እንዳያይ አድርጎታል፤ ኤርምያስ ይህን ያውቅ ነበር። (1 ነገ. 21:27-29) በተመሳሳይም ምናሴ ከአክዓብ ይበልጥ ይሖዋን የሚያስቆጣ ድርጊት እንደፈጸመ ኤርምያስ ያውቅ ነበር። ይሁንና ምናሴ ንስሐ ስለገባ ይሖዋ ይቅር ብሎታል። (2 ነገ. 21:16, 17፤ 2 ዜና 33:10-13) እነዚህ ታሪኮች ኤርምያስም ከቅርብ ወዳጆቹ ጋር ባለው ግንኙነት እንደ አምላክ ታጋሽና ይቅር ባይ እንዲሆን አነሳስተውት መሆን አለበት።—መዝ. 103:8, 9
15. ባሮክ ትኩረቱ በተከፋፈለበት ወቅት ኤርምያስ እንደ ይሖዋ ትዕግሥት ያሳየው እንዴት ነው?
15 ባሮክ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ትኩረቱ በተከፋፈለበት ወቅት ኤርምያስ ያደረገውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ወዳጁ እንደማይስተካከል በማሰብ ቶሎ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ አምላክ የተናገረውን ደግነት የተንጸባረቀበት ግልጽ ምክር በማካፈል ባሮክን ረድቶታል። (ኤር. 45:1-5) ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?
16. ምሳሌ 17:9 እንደሚያሳየው ወዳጅነታችንን ጠብቀን ለማቆየት ምን ማድረግ ያስፈልገናል?
16 ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ፍጽምና መጠበቅ አንችልም። በመሆኑም ከሌሎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ከመሠረትን በኋላ ወዳጅነታችንን ጠብቀን ለማቆየት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። ወዳጆቻችን ስህተት ቢሠሩ በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርተን በደግነት ሆኖም በግልጽ ምክር መስጠት ሊያስፈልገን ይችላል። (መዝ. 141:5) የሚያስከፋን ነገር ካደረጉ ደግሞ ይቅር ልንላቸው ይገባል። አንዴ ይቅር ካልናቸው በኋላ በሌላ ጊዜ ጥፋታቸውን ላለማንሳት መጠንቀቅ ይኖርብናል። (ምሳሌ 17:9ን አንብብ።) በዚህ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ድክመት ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ ትኩረት ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! እንዲህ ማድረጋችን ወዳጅነታችንን ያጠናክረዋል፤ ደግሞም በታላቁ መከራ ወቅት የቅርብ ወዳጆች ያስፈልጉናል።
ታማኝ ፍቅር አሳዩ
17. ነቢዩ ኤርምያስ ለክፉ ቀን የሚደርስ እውነተኛ ወዳጅ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
17 ነቢዩ ኤርምያስ ለክፉ ቀን የሚደርስ እውነተኛ ወዳጅ መሆኑን አሳይቷል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ኤቤድሜሌክ የተባለው የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን ኤርምያስን በጭቃ ከተሞላ ጉድጓድ በማውጣት ከሞት አተረፈው፤ ኤቤድሜሌክ በዚህ ምክንያት መኳንንቱ ጉዳት እንዳያደርሱበት ፈርቶ ነበር። ኤርምያስ ይህን ሲያውቅ ወዳጁ ችግሩን በራሱ እንደሚወጣው ተስፋ በማድረግ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። በወቅቱ ኤርምያስ ታስሮ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ የላከውን የሚያጽናና መልእክት ለወዳጁ ለኤቤድሜሌክ በመንገር እሱን ለመርዳት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል።—ኤር. 38:7-13፤ 39:15-18
18. ምሳሌ 17:17 እንደሚለው ወዳጃችን ችግር ሲያጋጥመው ምን ማድረግ እንችላለን?
18 በዛሬው ጊዜ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች በተፈጥሮ ወይም በሰው ሠራሽ አደጋዎች የተነሳ ችግር ደርሶባቸዋል። እንዲህ ያሉ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት አንዳንዶቻችን እነዚህን ወንድሞቻችንን ቤታችን ማሳረፍ እንችል ይሆናል። ሌሎች ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጉ ይሆናል። ሁላችንም ልናደርገው የምንችለው ሌላ ነገር ደግሞ ይሖዋ፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንዲረዳቸው መጠየቅ ነው። በሌላ በኩል አንድ ወንድማችን ወይም አንዲት እህታችን ተስፋ እንደቆረጡ አስተውለን ይሆናል፤ ይሁንና ምን ማለት ወይም ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ይገባን ይሆናል። ሆኖም ሁላችንም እርዳታ ማበርከት የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ችግር ከገጠመው ወንድማችን ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንችላለን። ወንድማችን ሲናገር አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ማዳመጥ እንችላለን። የምንወደውን የሚያጽናና ጥቅስ ልንነግረውም እንችላለን። (ኢሳ. 50:4) ዋናው ነገር ወዳጆቻችን የእኛ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ወቅት ከጎናቸው መሆናችን ነው።—ምሳሌ 17:17ን አንብብ።
19. ከአሁኑ ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታችን ወደፊት የሚጠቅመን እንዴት ነው?
19 ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር ከአሁኑ ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታችንና ወዳጅነታችንን ጠብቀን ለማቆየት ጥረት ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ጠላቶቻችን ውሸትና የተሳሳተ መረጃ በመጠቀም እኛን ለመከፋፈል መሞከራቸው አይቀርም። በመካከላችን መተማመን እንዳይኖር ለማድረግ ይጥራሉ። ሆኖም የሚያደርጉት ጥረት ትርፉ ልፋት ብቻ ነው። በመካከላችን ያለውን ጠንካራ ፍቅር ማጥፋት አይችሉም። ምንም ቢያደርጉ ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ማናጋት አይችሉም። እንዲያውም ወዳጅነታችን እስከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ይዘልቃል!
መዝሙር 24 ኑ! ወደ ይሖዋ ተራራ
a መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ ሁላችንም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ማጠናከር ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ ኤርምያስ ከተወው ምሳሌ የምናገኘውን ትምህርት በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ወዳጅነታችንን ማጠናከራችን፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።
b በኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩት ክንውኖች የተመዘገቡት በጊዜ ቅደም ተከተል አይደለም።
c የሥዕሎቹ መግለጫ፦ ይህ ፎቶግራፍ ወደፊት ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ሊያጋጥም የሚችለውን ነገር የሚያሳይ ነው። የተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች ጣሪያ ሥር ተሸሽገዋል። በዚያ የመከራ ወቅት አብረው ስለሆኑ እርስ በርስ መበረታታት ችለዋል። ቀጥሎ ያሉት ሦስት ፎቶግራፎች፣ እነዚሁ ወንድሞችና እህቶች ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ጠንካራ ወዳጅነት እንደመሠረቱ ያሳያሉ።