-
የማይጠቅም ጓደኛንቁ!—2010 | ግንቦት
-
-
የማይጠቅም ጓደኛ
ወጣት ሳለህ የተዋወቅከው አንድ “ጓደኛ” አለህ። ይህ ጓደኛህ ትልቅ ሰው እንደሆንክ እንዲሰማህ ያደረገህ ከመሆኑም በላይ በሌሎች ዘንድም ተቀባይነት እንድታገኝ አስችሎሃል። ውጥረት በተሰማህ ቁጥር “ዘና” እንዲያደርግህ የምትሄደው ወደ እሱ ነው። በአብዛኛው ያለሱ መንቀሳቀስ አልሆንልህ እያለህ መጥቷል።
ከጊዜ በኋላ ግን ይህ “ጓደኛህ” መጥፎ ጠባይ እንዳለው ደረስክበት። ከእሱ ጋር መሆንህ ተገቢ በማይሆንባቸው ቦታዎች እንኳ ሳይቀር ሁልጊዜ አብሬህ ካልሆንኩ ይልሃል። ትልቅ ሰው እንደሆንክ እንዲሰማህ ያደረገህ ቢሆንም እንኳን ለዚህ ያበቃህ ጤንነትህን እየጎዳ ነው። ይህ ሁሉ እንዳይበቃው ከደሞዝህ የተወሰነውን ይሰርቅሃል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከእሱ ጋር ያለህን ጓደኝነት ለማቆም ብትሞክርም የሙጥኝ ብሎ ይዞሃል። በሌላ አባባል ጌታህ ሆኗል ማለት ነው። አሁን አሁን ከእሱ ጋር የተዋወቅክበትን ቀን መርገም ጀምረሃል።
አብዛኞቹ አጫሾች ከሲጋራ ጋር ያላቸው ዝምድና ይህን ይመስላል። ለ50 ዓመታት ያህል አጭሳ የነበረች ኧርሊን የተባለች አንዲት ሴት ሁኔታውን ስታስታውስ እንዲህ ብላለች፦ “ከሰው ጋር ከምሆን ይልቅ ከሲጋራ ጋር መሆን ይበልጥ ያረጋጋኝ ነበር። የረጅም ጊዜ ጓደኛዬ ብቻ ሳይሆን ያለሱ ጓደኛ እንደሌለኝ የሚሰማኝ ጊዜ ነበር።” ይሁን እንጂ ኧርሊን ኋላ ላይ እንደተገነዘበችው ሲጋራ የማይጠቅም ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ጨካኝም ነው። በእርግጥም ከአንድ ነገር በስተቀር በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ነገሮች በሙሉ በእሷ ሕይወት ውስጥ ተፈጽመዋል ማለት ይቻላል። ኧርሊን፣ ማጨስ አምላክ የሰጠንን አካል የሚበክል በመሆኑ በእሱ ዘንድ የተጠላ እንደሆነ ስታውቅ ይህን ልማዷን አቆመች።—2 ቆሮንቶስ 7:1
ፍራንክ የተባለ አንድ ሰውም አምላክን ለማስደሰት ሲል ማጨሱን ለማቆም ወሰነ። ማጨሱን ካቆመ ከአንድ ከሁለት ቀን በኋላ ግን በቤቱ ወለል ላይ በእንብርክክ እየሄደ በሳንቃዎቹ መካከል የተሾጎጠ የሲጋራ ቁራጭ መፈለግ ጀመረ። “ቁርጥ ያለ ውሳኔ ያደረግኩት በዚህ ጊዜ ነበር” በማለት ፍራንክ ተናግሯል። “በእጄና በእግሬ እየዳህኩ የሲጋራ ቁራጭ ለማግኘት በስንጥቆቹ መሃል የተጋገረውን አቧራ ስጭር ራሴን ታዘብኩት። ሁኔታዬ ስለዘገነነኝ ከዚያ በኋላ አንድም ሲጋራ አላጨስኩም።”
ሲጋራ ማጨስን ማቆም ይህን ያህል አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው? ተመራማሪዎች ለዚህ ምክንያት የሚሆኑ በርካታ ነገሮች እንዳሉ ደርሰውበታል፦ (1) የትንባሆ ምርቶች ከሕገ ወጥ ዕፆች ያላነሰ ሱስ ሊያሲዙ ይችላሉ። (2) ወደ ሳንባ የገባ ኒኮቲን በሰባት ሴኮንድ ውስጥ ወደ አንጎል ይደርሳል። (3) የሚያጨሱ ሰዎች በሚመመገቡበት፣ በሚጠጡበት፣ ከሌሎች ጋር በሚጨዋወቱበት፣ ጭንቀታቸውን በሚያስታግሱበትና በመሳሰሉት ጊዜያት ሁሉ ስለሚያጨሱ ሲጋራ ከዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።
ይሁን እንጂ ከኧርሊንና ከፍራንክ ሕይወት መመልከት እንደሚቻለው ከዚህ ጎጂ ሱስ መላቀቅ ይቻላል። የምታጨስ ብትሆንም ለማቆም የምትፈልግ ከሆነ ቀጥሎ ያሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማንበብህ ሕይወትህን በአዲስ መልክ ለመምራት ጥሩ ጅማሮ ሊሆንልህ ይችላል።
-
-
ጠንካራ ፍላጎት አዳብርንቁ!—2010 | ግንቦት
-
-
ጠንካራ ፍላጎት አዳብር
“ማጨስ በማቆም ረገድ ከተሳካላቸው ሰዎች ማየት እንደሚቻለው ሲጋራ ማጨስ ለማቆም የሚያስፈልገው ብቸኛውና ዋነኛው ባሕርይ የልብ ቁርጠኝነት ነው።” —“ስቶፕ ስሞኪንግ ናው!”
ነገሩን በአጭሩ ለማስቀመጥ፣ ማጨስ ለማቆም ከፈልግክ ቢያንስ ቢያንስ ጠንካራ ፍላጎት ሊኖርህ ይገባል። ታዲያ ጠንካራ ፍላጎት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ማጨስ ብታቆም ምን ያህል የተሻልክ ሰው ልትሆን እንደምትችል አስብ።
ከወጪ ትድናለህ። በቀን አንድ ፓኮ የማጨስ ልማድ ያለው ሰው በዓመት በሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣል። “ምን ያህል ገንዘብ ለትንባሆ እንደማጠፋ ተገንዝቤ አላውቅም ነበር።”—ግያኑ፣ ኔፓል
በሕይወትህ ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለህ። “መኖር የጀመርኩት ማጨስ ካቆምኩ በኋላ ነው ማለት እችላለሁ፤ ሕይወቴ ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ መጥቷል።” (ረጂነ፣ ደቡብ አፍሪካ) ሰዎች ማጨስ ሲያቆሙ ጣዕም የመለየትና የማሽተት ችሎታቸው በከፍተኛ ደረጃ ይሻሻላል፤ እንዲሁም የተሻለ አቅም የሚኖራቸው ሲሆን መልካቸውም እየተመለሰ ይመጣል።
ጤንነትህ ሊሻሻል ይችላል። “በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ማጨስ ሲያቆሙ ጤንነታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ፈጣን መሻሻል ያሳያል።”—የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል
በራስ የመተማመን ስሜትህ ከፍ ይላል። “ትንባሆ ጌታዬ እንዲሆን ስላልፈልግኩ ማጨስ አቆምኩ። በገዛ ሰውነቴ ላይ ጌታ መሆን እንዳለብኝ ተሰማኝ።”—ሄኒንግ፣ ዴንማርክ
ቤተሰቦችህና ወዳጆችህ ተጠቃሚ ይሆናሉ። “ማጨስ . . . በአካባቢህ የሚኖሩ ሰዎችን ጤንነትም ይጎዳል። . . . ከሚያጨሱ ሰዎች የሚወጣው የሲጋራ ጭስ በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ . . . የማያጨሱ ሰዎች በሳንባ ካንሰርና በልብ ሕመም እንዲሞቱ ምክንያት መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠዋል።”—የአሜሪካ የካንሰር ማኅበር
ፈጣሪህን ታስደስታለህ። ‘የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ሥጋን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።’ (2 ቆሮንቶስ 7:1) “ሰውነታችሁን . . . ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው . . . አድርጋችሁ [አቅርቡ]።”—ሮም 12:1
“አምላክ ሰውነትን የሚያረክሱ ነገሮችን እንደሚጠላ ስገነዘብ ማጨሴን ወዲያውኑ ለማቆም ወሰንኩ።”—ሲልቭያ፣ ስፔን
ይሁንና ከፍተኛ ፍላጎት ማዳበር በራሱ በአብዛኛው በቂ አይደለም። የቤተሰቦቻችንና የወዳጆቻችንን ጨምሮ የሌሎች ሰዎች እርዳታም ሊያስፈልገን ይችላል። ታዲያ እኛን ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ?
-
-
እርዳታ ፈልግንቁ!—2010 | ግንቦት
-
-
እርዳታ ፈልግ
“አንድ ሰው ብቸኛውን ቢያጠቃውም፣ ሁለት ከሆኑ ይመክቱታል።” —መክብብ 4:12
ጠላታችን ምንም ይሁን ምን የሌሎችን እርዳታ ካገኘን ያንን ጠላት የማሸነፍ አጋጣሚያችን ሰፊ ይሆናል። ስለዚህ የማጨስ ልማድህን ማሸነፍ ከፈለግህ የቤተሰቦችህንና የወዳጆችህን አሊያም በትዕግሥት ሊረዳህ ልባዊ ፍላጎት ያለው የማንኛውንም ሰው እርዳታ መሻትህ ብልህነት ነው።
የማጨስ ልማዳቸውን ያሸነፉ ሰዎች ችግርህን መረዳት ብቻ ሳይሆን የተሻለ ድጋፍ ሊሰጡህም ስለሚችሉ እንዲህ ዓይነት ግለሰቦችን ለማግኘት ጥረት አድርግ። በዴንማርክ የሚኖረው ቶርበን የተባለ አንድ ክርስቲያን “ሌሎች ያደረጉልኝ ድጋፍ በጣም ጠቅሞኛል” ብሏል። በሕንድ የሚኖረው ኤብረሃም ደግሞ “ቤተሰቦቼና ክርስቲያን ባልደረቦቼ ያሳዩኝ ልባዊ ፍቅር ማጨሴን እንዳቆም ረድቶኛል” ብሏል። ይሁን እንጂ ቤተሰቦችህና ወዳጆችህ የሚያደርጉልህ ድጋፍ እንኳ በቂ የማይሆንበት ጊዜ ይኖራል።
በግዋንዳስ የተባለ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ለ27 ዓመታት አጭሻለሁ፤ ይሁንና ማጨስ ለመተው የወሰንኩት መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ ስለሆኑ ልማዶች ምን እንደሚል ሳውቅ ነው። የማጨሰውን ሲጋራ መጠን በመቀነስ ቀስ በቀስ ለመተው ሞክሬ ነበር። ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቆምኩ። ከባለሙያ የምክር አገልግሎት ለማግኘትም ሞከርኩ። ይህ ሁሉ ግን የፈየደልኝ ነገር አልነበረም። ይሁንና አንድ ቀን ማታ የልቤን አውጥቼ ወደ ይሖዋ አምላክ በመጸለይ ማጨሴን እንዳቆም እንዲረዳኝ ለመንኩት። በመጨረሻም ተሳካልኝ!”
ሌላው አስፈላጊ ነገር ሊያጋጥሙ ለሚችሉ መሰናክሎች ራስህን ማዘጋጀት ነው። እነዚህ መሰናክሎች ምንድን ናቸው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መድኃኒት መጠቀም ይኖርብሃል?
እንደ ኒኮቲን ፕላስተር (በውስጡ ጥቂት ኒኮቲን የያዘ ቆዳ ላይ የሚለጠፍ ነገር ነው) ያሉ ማጨስ ለማቆም ያግዛሉ የሚባሉ መድኃኒቶች ብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚዛቅባቸው ሆነዋል። እንዲህ ያለውን ሕክምና ከመጀመርህ በፊት በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ አስብ፦
ጥቅሞቹ ምንድን ናቸው? ብዙዎቹ መድኃኒቶች፣ ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን በመቀነስ ማጨስ የማቆም አጋጣሚህ ሰፊ እንዲሆን ይረዳሉ ተብሎ ይነገርላቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ መድኃኒቶች ዘላቂ ውጤት የማስገኘታቸው ጉዳይ በአንዳንዶች ዘንድ ጥርጣሬ ፈጥሯል።
አደጋዎቹ ምንድን ናቸው? አንዳንዶቹ መድኃኒቶች እንደማቅለሽለሽ፣ የመንፈስ ጭንቀትና ራስን የማጥፋት ሐሳብ ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን የማስከተል አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም ለኒኮቲን ምትክ ተደርገው የሚሰጡ ሕክምናዎችን መውሰድ ኒኮቲኑን በሌላ መልክ ወደ ሰውነት ማስገባት መሆኑን መዘንጋት የለብህም፤ ኒኮቲኑ በምንም መልክ ይወሰድ ጉዳት ማስከተሉ ስለማይቀር አልሸሹም ዞር አሉ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህን መድኃኒቶች የሚወስድ ሰው አሁንም ከሱሱ አልተላቀቀም ማለት ይቻላል።
ምን አማራጮች አሉ? በአንድ ጥናት እንደታየው ማጨስ ማቆም ከቻሉ ሰዎች መካከል 88 በመቶ የሚሆኑት ማጨስ ያቆሙት ያለምንም መድኃኒት እርዳታ በአንድ ጊዜ ነው።
-
-
መሰናክሎቹን ለማለፍ ዝግጁ ሁንንቁ!—2010 | ግንቦት
-
-
መሰናክሎቹን ለማለፍ ዝግጁ ሁን
“አዲስ ለተወለደው ልጃችን ጤንነት ስል ማጨስ ለማቆም ወሰንኩ። በመሆኑም ‘ማጨስ ክልክል ነው’ የሚል ምልክት ቤታችን ውስጥ ለጠፍኩ። ልክ ከአንድ ሰዓት በኋላ የኒኮቲን ሱሴ ውስጤን እንደ ሱናሚ ሲያናውጠው ግን ሲጋራ ለኮስኩ።”—ዮሺሚትሱ፣ ጃፓን
የዮሺሚትሱ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ማጨስ የማቆም ሂደት የራሱ የሆኑ መሰናክሎች አሉት። ከዚህም በላይ ሱሱ አገርሽቶባቸው በመሰናክሉ ከወደቁት አጫሾች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ማጨሳቸውን መቀጠላቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ። ስለዚህ ማጨስ ለማቆም እየጣርክ ከሆነ የሚያጋጥሙህን መሰናክሎች ለማለፍ አስቀድመህ ብትዘጋጅ ስኬታማ የመሆን ዕድልህ ከፍተኛ ይሆናል። ለመሆኑ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙት መሰናክሎች የትኞቹ ናቸው?
የኒኮቲን ሱስ፦ ሱስህ በጣም የሚያይለው ሲጋራ ካቆምክ በኋላ ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ሲሆን ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ግን ቀስ በቀስ እየጠፋ ይመጣል። ቀደም ሲል ያጨስ የነበረ አንድ ሰው እንደተናገረው ከሆነ ሱሱ በሚቀሰቀስበት ወቅት “የማጨስ ፍላጎቱ እንደ ባሕር ሞገድ አልፎ አልፎ የሚመጣ እንጂ ፋታ የማይሰጥ አይደለም።” ይሁን እንጂ ከዓመታት በኋላ እንኳን የማጨስ ፍላጎት ድንገት ሊመጣብህ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ሲመጣብህ ቶሎ እጅህን አትስጥ። ለአምስት ለስድስት ደቂቃ ብትታገሥ አምሮቱ ማለፉ አይቀርም።
ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ችግሮች፦ ማጨስ የሚያቆሙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ንቁ ሆኖ መቆየት ወይም በአንድ ነገር ላይ ማተኮር አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፤ እንዲሁም በቀላሉ ክብደታቸው ሊጨምር ይችላል። በተጨማሪም የሕመም ስሜት ሊሰማቸው፣ ሊያስላቸው እንዲሁም ሰውነታቸውን ሊያሳክካቸውና ሊያልባቸው ይችላል። ከዚህም ባሻገር ስሜታቸው ሊለዋወጥ ይኸውም ትዕግሥት ሊያጡና ቁጠኞች ሊሆኑ አልፎ ተርፎም የመንፈስ ጭንቀት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡት አብዛኞቹ ችግሮች ከአራት እስከ ስድስት ባሉት ሳምንታት ውስጥ እየጠፉ ይሄዳሉ።
በዚህ ወሳኝ የሆነ ጊዜ ውስጥ ችግሮቹን እንድትቋቋም የሚረዱ አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፦
● ከወትሮ በተለየ ረዘም ላለ ሰዓት ለመተኛት ሞክር።
● ብዙ ውኃ ወይም ጭማቂ ጠጣ። ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦችን ተመገብ።
● መጠነኛ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ።
● በረጅሙ ተንፍስ፤ እንዲህ በምታደርግበት ጊዜም ንጹሕ አየር ሳንባህን ሲሞላው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ።
ሱስህን የሚቀሰቅሱ ነገሮች፦ የማጨስ ፍላጎትህ እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉት እነዚህ ነገሮች ከአንዳንድ ድርጊቶችና ስሜቶች ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ አንዳንድ ነገሮችን ዘና ብለህ እየጠጣህ ሲጋራ የማጨስ ልማድ ይኖርህ ይሆናል። እንግዲያው ሲጋራ ለማቆም የምትፈልግ ከሆነ እንዲህ ያለውን ዘና ብሎ የመጠጣት ልማድ ማቆም አለብህ። ይዋል ይደር እንጂ ዘና ብለህ መጠጣት የምትችልበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።
ይህ እንዳለ ሆኖ ኒኮቲኑ ከሰውነትህ ሙሉ በሙሉ ከወጣ በኋላም አእምሮህ ይህን ልማድ ለረጅም ጊዜ ሳይረሳው ሊቆይ ይችላል። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ቶርበን “ማጨስ ካቆምኩ አሥራ ዘጠኝ ዓመት ቢሆነኝም አሁንም በእረፍት ሰዓት ቡና ስጠጣ ለማጨስ እፈተናለሁ” በማለት ሁኔታውን ሳይሸሽግ ተናግሯል። በአጠቃላይ ሲታይ ግን በአእምሮ ላይ የተቀረጸው በማጨስና በአንዳንድ ድርጊቶች መካከል ያለው ቁርኝት እየተዳከመ ስለሚመጣ ተጽእኖ የማሳደር ኃይሉ መጥፋቱ አይቀርም።
ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው የተለየ ነው። ሰዎች የማጨስ ሱሳቸው በአብዛኛው የሚያገረሽባቸው በሚጠጡበት ወቅት በመሆኑ ማጨስ ለማቆም በምትሞክርበት ጊዜ ከአልኮልም ሆነ አልኮል ከሚጠጣባቸው ቦታዎች መራቅ ይኖርብህ ይሆናል። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው?
● ትንሽ አልኮል መጠጣት እንኳን በደም ውስጥ ያለው ኒኮቲን የሚፈጥረውን የእርካታ ስሜት ከፍ እንዲል ያደርጋል።
● በአብዛኛው ሰዎች ተሰባስበው በሚጠጡበት ጊዜ ማጨስ የተለመደ ድርጊት ነው።
● አልኮል የማመዛዘን ችሎታን የሚያዛባ ከመሆኑም በላይ ዓይን ያወጣ ድርጊት ወደ መፈጸም ይመራል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ወይን ጠጅ ማስተዋልን እንደሚወስድ’ መናገሩ የተገባ ነው።—ሆሴዕ 4:11, 12
አብረህ የምትውላቸው ሰዎች፦ መራጭ ሁን። ለምሳሌ ከሚያጨሱ ወይም እንድታጨስ ከሚገፋፉህ ሰዎች ጋር አላስፈላጊ ቅርርብ አትፍጠር። በተጨማሪም በማሾፍ ሊሆን ይችላል ማጨስ ለማቆም የምታደርገውን ጥረት ከሚያጣጥሉብህ ሰዎች ራቅ።
ስሜቶች፦ ሱሳቸው ካገረሸባቸው ሰዎች መካከል ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት በሱሱ ከመሸነፋቸው በፊት ውጥረት ውስጥ ገብተው ወይም ተበሳጭተው እንደነበረ አንድ ጥናት አመልክቷል። አንዳንድ ስሜቶች የማጨስ ፍላጎትህን ከቀሰቀሱብህ ውኃ በመጠጣት፣ ማስቲካ በማኘክ፣ የእግር ጉዞ በማድረግ ወይም በመሳሰሉት ነገሮች የማጨስ ስሜትህን ለመርሳት ጥረት አድርግ። ወደ አምላክ በመጸለይ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ገጾችን በማንበብ ወይም በመሳሰሉት መንገዶች አእምሮህን አዎንታዊ በሆኑ ሐሳቦች ለመሙላት ሞክር።—መዝሙር 19:14
ሰበብ አስባቦችን አስወግድ
● አንድ ጊዜ ብቻ ሳብ ባደርግስ?
እውነታው፦ አንድ ጊዜ ብቻ ሳብ ማድረግ እንኳ በአንጎልህ ውስጥ ከሚገኙት ኒኮቲን ተቀባይ ሴሎች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑትን ለሦስት ሰዓት ያህል ሊያረካ ይችላል። ታዲያ ይህ ምን ውጤት ያስከትላል? በአብዛኛው ሱሱ ሙሉ በሙሉ ያገረሻል።
● ማጨሴ የሚሰማኝን ውጥረት እንድቋቋም ይረዳኛል።
እውነታው፦ እንዲያውም ኒኮቲን በውጥረት ጊዜ የሚመነጩ ሆርሞኖችን መጠን እንደሚጨምር ጥናቶች አመልክተዋል። አንድ ሰው ማጨሱ የገጠመውን ውጥረት እንዳቃለለለት ሆኖ ይሰማው ይሆናል፤ ይሁንና በአብዛኛው እንዲህ እንዲሰማው የሚያደርገው ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡት ችግሮች ለጊዜው መወገዳቸው ሊሆን ይችላል።
● ለረጅም ዓመታት ስላጨስኩ ከአሁን በኋላ ማቆም የምችል አይመስለኝም።
እውነታው፦ አፍራሽ አመለካከት መያዝ ወኔ ይሰልባል። መጽሐፍ ቅዱስ “በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!” ይላል። (ምሳሌ 24:10) ስለዚህ አይሆንልኝም የሚል አስተሳሰብ እንዳይጠናወትህ ተጠንቀቅ። ማጨስ ለማቆም ልባዊ ፍላጎት ያለውና በዚህ መጽሔት ውስጥ የተገለጹትን የመሰሉ ጠቃሚ መመሪያዎችን ሥራ ላይ የሚያውል ማንኛውም ሰው ሊሳካለት ይችላል።
● ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ችግሮች መቋቋም አልችልም።
እውነታው፦ ማጨስ ከማቆም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን መቋቋም ከባድ እንደሆነ ባይካድም ችግሮቹ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ቀስ በቀስ እየጠፉ ይሄዳሉ። ስለዚህ አታወላውል! የማጨስ አምሮትህ ከወራት ወይም ከዓመታት በኋላ ቢቀሰቀስብህ እንኳን የደቂቃዎች ጉዳይ እንጂ ያልፋል፤ ብቻ ሲጋራ እንዳትለኩስ ተጠንቀቅ።
● የአእምሮ ሕመም አለብኝ።
እውነታው፦ እንደ መንፈስ ጭንቀት ወይም ስኪዞፍሬንያ ያለ የአእምሮ በሽታ ካለብህና ሕክምና በመከታተል ላይ ከሆንክ ዶክተርህ ማጨስ እንድታቆም እንዲረዳህ ጠይቀው። ሐኪምህ ከጎንህ ለመቆም ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም ማጨስ ማቆምህ በሕመምህ ወይም በምትወስዳቸው መድኃኒቶች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ከግምት በማስገባት በምትከታተለው ሕክምና ላይ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል።
● አገርሽቶብኝ ዳግመኛ ባጨስ እንደማይሳካልኝ በማሰብ ተስፋ እቆርጣለሁ።
እውነታው፦ ብዙዎች ማጨስ ለማቆም በሚሞክሩበት ጊዜ እንደሚያጋጥማቸው አንተም አንድ ዓይነት መሰናክል አጋጥሞህ ብታጨስ ሁኔታህ ተስፋ ቢስ ነው ማለት አይደለም። ከወደቅክበት በመነሳት ጉዞህን ቀጥል። ወደቅክ ማለት አልተሳካልህም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አልተሳካልህም የሚባለው እንደወደቅክ ስትቀር ነው። ስለዚህ ጥረት ማድረግህን አታቁም። በመጨረሻ ድል ማድረግህ አይቀርም!
ለ26 ዓመታት ያጨሱትና ካቆሙ ከ30 ዓመት በላይ የሆናቸውን የሮሙአልዶን ተሞክሮ እንመልከት። እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ለምን ያህል ጊዜ እንዳገረሸብኝ መቁጠር ያዳግተኛል። ሱሴ ባገረሸብኝ ቁጥር ተስፋ ቢስ እንደሆንኩ ስለሚሰማኝ በራሴ ክፉኛ አዝን ነበር። ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረኝ ለማድረግ ቁርጥ አቋም ከወሰድኩና በጥረቴ እንዲረዳኝ ደጋግሜ ከጸለይኩ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጌ ለመተው ቻልኩ።”
በዚህ ተከታታይ ርዕስ የመጨረሻው ክፍል ላይ ከሲጋራ ሱስ የተላቀቀ ደስተኛ ሰው እንድትሆን የሚያስችሉህን አንዳንድ ሐሳቦች እንመለከታለን።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በዚያም ሆነ በዚህ ገዳይ ነው
ትንባሆ በብዙ መንገዶች ጥቅም ላይ ይውላል። እንዲያውም አንዳንድ የትንባሆ ምርቶች ለጤና ይጠቅማሉ የሚባሉ ምግቦችና የዕፅዋት መድኃኒቶች በሚሸጡባቸው መደብሮች ውስጥ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ “ትንባሆ በምንም መልክ ይቅረብ ገዳይ ነው” በማለት የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። በትንባሆ አማካኝነት የሚመጡ ለምሳሌ የካንሰር፣ የልብና የደም ሥር በሽታዎች ሞት ሊያስከትሉ ይችላሉ። በተጨማሪም የሚያጨሱ ነፍሰ ጡር ሴቶች በፅንሱ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። የትንባሆ ውጤቶች ብዙ ጊዜ የሚዘጋጁት በምን መልክ ነው?
ቤት ውስጥ የሚዘጋጅ ሲጋራ፦ እነዚህ በእጅ የሚጠቀለሉ ትናንሽ ሲጋራዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ አገሮች ይጨሳሉ። በእስያ አገሮች ውስጥ ቢዲ በመባል የሚታወቁት እነዚህ ሲጋራዎች በእነዚህ አካባቢዎች በብዛት ጥቅም ላይ ይውላሉ። እንዲህ ያሉ ሲጋራዎች ከመደበኛው ሲጋራ ጋር ሲነጻጸር በጣም ብዙ ኒኮቲንና ካርቦን ሞኖክሳይድ እንዲሁም ታር የተባለ መርዛማ ንጥረ ነገር ወደ ሳንባ ያስገባሉ።
ሲጋር፦ ሲጋር የሚዘጋጀው ትንባሆውን በራሱ በትንባሆ ቅጠል ወይም ከትንባሆ በተሠራ ወረቀት በመጠቅለል ሲሆን ከመደበኛ ሲጋራ በተለየ በጣም ጥቅጥቅ ያለ ነው። የአሲድነት ባሕርይ ካለው ሲጋራ በተለየ መልኩ በትንሹ የአልካላይነት ባሕርይ ያላቸው ሲጋሮች ሳይለኮሱ እንኳን አፍ ላይ እንዳሉ ኒኮቲኑ ወደ ሰውነት ውስጥ ሊገባ ይችላል።
ክሪቴክ ወይም የቅርንፉድ ሲጋራ፦ በኢንዶኔዥያ በብዛት የተለመደው ይህ የትንባሆ ዓይነት 60 በመቶው ትንባሆ ሲሆን 40 በመቶው ደግሞ ቅርንፉድ ነው። እንዲህ ያለው ሲጋራ ከመደበኛው ሲጋራ የበለጠ ኒኮቲንና ካርቦን ሞኖክሳይድ እንዲሁም ታር የተባለ መርዛማ ንጥረ ነገር ወደ ሳንባ ያስገባል።
ፒፓ፦ ፒፓ ማጨስ የሚያስከትለው ጉዳት ሲጋራ ከማጨስ የሚተናነስ አይደለም። ምክንያቱም ሁለቱም ተመሳሳይ የሆኑ የካንሰር ሕመሞችንና ሌሎች በሽታዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ጭስ አልባ ትንባሆ፦ ይህ ትንባሆ ማኘክን ወይም ሱረት በአፍንጫ መሳብን ይጨምራል። በደቡብ ምሥራቅ እስያ የተለመደው ማጣፈጫ የገባበት ጉትከ ከጭስ አልባ ትንባሆ ይመደባል። ትንባሆው በአፍ ላይ እንዳለ ኒኮቲኑ ወደ ደም ሥር ይገባል። ጭስ አልባ ትንባሆ መጠቀምም ቢሆን ሌሎች የትንባሆ ዓይነቶችን ከማጨስ ባልተናነሰ ጎጂ ነው።
ጋያ እና ሺሻ፦ በእነዚህ መሣሪያዎች አማካኝነት ትንባሆው ወደ አፍ ከመግባቱ በፊት በውኃ ውስጥ ያልፋል። ይሁን እንጂ ይህ ሂደት ካንሰር አምጪ የሆኑትን ጨምሮ ወደ ሳንባ የሚገቡትን መርዛማ ንጥረ ነገሮች መጠን ላይቀንስ ይችላል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
አንድ ሰው ማጨሱን እንዲያቆም መርዳት
● አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። ከመነዝነዝና ከመጨቅጨቅ ይልቅ ማመስገን ብሎም መሸለምን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች አድናቆትህን መግለጽ የተሻለ ውጤት ያስገኛል። “አገረሸብህ እንዴ!” ከማለት ይልቅ “እንደገና ብትሞክር እንደሚሳካልህ እርግጠኛ ነኝ” ማለትህ ይበልጥ ይረዳዋል።
● ይቅር ባይ ሁን። ማጨሱን ለማቆም የሚሞክር ሰው ቢቆጣህ ወይም ቢበሳጭብህ ችለህ ለማለፍ የበኩልህን ጥረት አድርግ። “በጣም ከባድ እንደሚሆንብህ አውቃለሁ፤ ነገር ግን እንዲህ ያለ ጥረት በማድረግህ እኮራብሃለሁ” እንደሚሉ ያሉ ደግነት የሚንጸባረቅባቸውን አስተያየቶች ሰንዝር። “ከአንተ ጋር ሰላም የምንሆነው ስታጨስ ሳይሆን አይቀርም!” እንደሚሉ ያሉ አባባሎችን በምንም ዓይነት እንዳትናገር ተጠንቀቅ።
● እውነተኛ ወዳጅ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል። (ምሳሌ 17:17) እውነት ነው፣ ማጨስ ለማቆም በመጣጣር ላይ ለሚገኝ ሰው “ምንጊዜም” ይኸውም ሰዓቱ ምንም ይሁን ምን ወይም የግለሰቡ ስሜት ምንም ያህል ቢቀያየር ታጋሽና አፍቃሪ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል።
-
-
ማሸነፍ ትችላለህ!ንቁ!—2010 | ግንቦት
-
-
ማሸነፍ ትችላለህ!
አሁን ‘በርትተህ የምትሠራበት’ ጊዜ ላይ ደርሰናል። (1 ዜና መዋዕል 28:10) ስኬታማ የመሆን ዕድልህን ለማስፋት ምን የመጨረሻ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ?
ቀን ቁረጥ። የዩናይትድ ስቴትስ የጤና እና ሰብዓዊ አገልግሎት ቢሮ ከሰጠው ሐሳብ መመልከት እንደምንችለው ማጨስ ለማቆም ከቆረጥክ ይህን ውሳኔህን ባደረግህ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከሲጋራ በመራቅ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መጀመር አለብህ። እንዲህ ማድረግህ ሲጋራ የማቆም ፍላጎትህ ሳይቀዘቅዝ በውሳኔህ እንድትገፋ ይረዳሃል። ማጨስ የምታቆምበትን ዕለት በቀን መቁጠሪያህ ላይ ምልክት አድርግ። ከዚያም ቀኑን ለወዳጆችህ ንገራቸው፤ እንዲሁም ሁኔታዎችህ ቢለዋወጡም እንኳን ከዚህ ቀን ውልፍት አትበል።
ካርድ አዘጋጅ። ይህ ካርድ ከታች የተዘረዘሩትን መረጃዎች ጨምሮ ያለህን ጠንካራ ፍላጎት የሚያጠናክሩ ሌሎች ሐሳቦችን የያዘ ሊሆን ይችላል።
● ማጨስ ለማቆም ያሰብክበት ምክንያት
● ልትሸነፍ እንደሆነ በሚሰማህ ጊዜ የምትደውልላቸው ሰዎች ስልክ ቁጥር
● እንደ ገላትያ 5:22, 23 ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ጨምሮ ወደ ግብህ እንድትደርስ የሚረዱ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች
ማጨስ ለማቆም የሚረዳህን ካርድ ከእጅህ አትለየው፤ እንዲያውም በቀን ውስጥ ደጋግመህ አንብበው። ማጨስ ካቆምክ በኋላም ቢሆን ፍላጎቱ በሚቀሰቀስብህ ጊዜ ሁሉ ይህን ካርድ መለስ ብለህ ተመልከተው።
ከሱስህ ጋር የሚዛመዱ ልማዶችን በዘዴ ለማዛባት ሞክር። ማጨስ ለማቆም የወሰንክበት ቀን ከመድረሱ በፊት ከሱስህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ልማዶች ሆን ብለህ ለማዛባት ሞክር። ለምሳሌ ጠዋት ከመኝታ እንደተነሳህ የማጨስ ልማድ ካለህ ማጨስህን በአንድ ሰዓት አራዝመው። በምትመገብበት ወቅት ወይም ከምግብ በኋላ የማጨስ ልማድ ካለህ ደግሞ ከዚህ ልማድ ለመውጣት ጥረት አድርግ። እንዲሁም የሚያጨሱ ሰዎች ባሉበት አካባቢ አትገኝ። በተጨማሪም ብቻህን ስትሆን ድምፅህን ከፍ አድርገህ “አመሰግናለሁ፣ ማጨስ አቁሜያለሁ” ማለትን ተለማመድ። እንደነዚህ ያሉ እርምጃዎችን መውሰድህ ማጨስ ለምታቆምበት ቀን ከማዘጋጀት ያለፈ ፋይዳ የላቸውም። ከዚህም ባሻገር ከሲጋራ ሱስ የምትላቀቅበት ቀን ቅርብ መሆኑን እንድታስታውስ ይረዱሃል።
ተዘጋጅ። ማጨስ የምታቆምበት ቀን እየቀረበ ሲመጣ እንደ ካሮት፣ ማስቲካ፣ ኦቾሎኒና ቆሎ ያሉ ሲጋራን የሚተኩ ነገሮችን በብዛት ገዝተህ አዘጋጅ። ማጨስ የምታቆምበትን ቀን ለጓደኞችህና ለቤተሰቦችህ አስታውሳቸው፤ እንዲሁም በምን መንገድ ድጋፍ ሊያደርጉልህ እንደሚችሉ ንገራቸው። አንድ ቀን ሲቀረው ደግሞ መኮስተሪያዎችንና የሲጋራ መለኮሻዎችን እንዲሁም የሲጋራ ፍላጎትህን የሚቀሰቅሱ ሌሎች ነገሮችን አስወግድ፤ በተጨማሪም ቤትህ፣ መኪናህ ወይም ኪስህ ውስጥ አሊያም በሥራ ቦታህ የቀሩ ሲጋራዎች ካሉ አስወግድ። ሲጋራን ከመሳቢያ ውስጥ ሳብ አድርጎ ማውጣት ሄዶ ከመግዛት ወይም ሌላ ሰው እንዲሰጥህ ከመጠየቅ እንደሚቀል የታወቀ ነው! በተጨማሪም አምላክን እንዲረዳህ ሳታሰልስ ለምነው፤ በተለይ ለመጨረሻ ጊዜ ካጨስክ በኋላ ልባዊ ጸሎት ማቅረብህ በጣም አስፈላጊ ነው።—ሉቃስ 11:13
ይህ ነው የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎች የማይጠቅም ብሎም ጨካኝ ከነበረው ጓደኛቸው ማለትም ከሲጋራ ጋር ያላቸው ወዳጅነት እንዲያከትም አድርገዋል። አንተም እንደነሱ ማድረግ ትችላለህ። የተሻለ ጤና የሚኖርህ ከመሆኑም በላይ ከፊትህ ታላቅ ነፃነት ይጠብቅሃል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማጨስ ለማቆም የሚረዳህን ካርድ ከእጅህ አትለየው፤ እንዲያውም በቀን ውስጥ ደጋግመህ አንብበው
-