የይሖዋ ምሥክሮች ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት እንዴት ነው?
ለስብከቱ ሥራ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በዋነኝነት የምናገኘው የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ግለሰቦች በፈቃደኝነት ከሚያደርጉት መዋጮ ነው።a በመሰብሰቢያ ቦታዎቻችን የመዋጮ ሣጥኖች ይቀመጣሉ፤ መዋጮ ማድረግ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶች ደግሞ ስለ መዋጮ በሚገልጸው የድረ ገጻችን ክፍል ላይ ተዘርዝረዋል። በዚህ ገጽ ላይ የተለያዩ አማራጮች ስለቀረቡ አንድ ሰው እንደ ምርጫው ለዓለም አቀፉ ሥራ፣ ለጉባኤ ወጪዎች ወይም ለሁለቱም መዋጮ ማድረግ ይችላል።
የይሖዋ ምሥክሮች አሥራት እንዲያወጡ ወይም ከገቢያቸው ላይ የተወሰነ መጠን እንዲሰጡ አይጠየቁም። (2 ቆሮንቶስ 9:7) በስብሰባዎቻችን ላይ ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም ወይም የመግቢያ ክፍያ አንጠይቅም፤ ሃይማኖታዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚሾሙ ሰዎችም ለጥምቀት፣ ለቀብር፣ ለሠርግ ወይም ለሌሎች አገልግሎቶች ክፍያ አይጠይቁም። የኬክ ሽያጭ፣ ባዛር፣ የቢንጎ ጨዋታዎች፣ ካርኒቫሎች፣ የራት ፕሮግራሞች፣ ሎተሪ ወይም እነዚህን የመሳሰሉ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን አናካሂድም፤ ሰዎች ገንዘብ እንዲያዋጡልንም አንጠይቅም። መዋጮ ስላደረጉ ሰዎች የሚገልጽ መረጃ ለሌሎች ወይም በሕዝብ ፊት አይነገርም። (ማቴዎስ 6:2-4) በድረ ገጾቻችን ወይም በጽሑፎቻችን ላይ፣ ገቢ የሚያስገኙ ማስታወቂያዎች አይወጡም።
ለሁሉም ሰው ክፍት በሆኑት ስብሰባዎቻችን ላይ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ በየወሩ የሒሳብ ሪፖርት ያቀርባል። በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ በተገቢው መንገድ መያዙን ለማረጋገጥ የእያንዳንዱ የጉባኤ ሒሳብ በየጊዜው ይመረመራል።—2 ቆሮንቶስ 8:20, 21
መዋጮ ማድረግ የሚቻልባቸው መንገዶች
የመዋጮ ሣጥን፦ በስብሰባ አዳራሾች፣ በትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ወይም ስብሰባዎቻችን በሚካሄዱባቸው ሌሎች ቦታዎች ላይ የመዋጮ ሣጥኖች ይቀመጣሉ፤ በእነዚህ ሣጥኖች ውስጥ ገንዘብ ወይም ቼክ ማስገባት ትችላለህ።
በኢንተርኔት መዋጮ ማድረግ፦ በብዙ አገሮች ውስጥ “ለይሖዋ ምሥክሮች መዋጮ አድርግ” የሚለው ገጽ ላይ በመግባት በክሬዲት ካርድ፣ በዴቢት ካርድ፣ በባንክ ገንዘብ በማስተላለፍ ወይም ሌሎች የኤሌክትሮኒክ መንገዶችን በመጠቀም መዋጮ ማድረግ ይቻላል።b በየወሩ ለመዋጮ የሚሆን “የተወሰነ ገንዘብ” ለመስጠት የሚመርጡ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች፣ እነዚህን ዘዴዎች ተጠቅመው በየወሩ በቋሚነት መዋጮ እንዲላክ ማዘዝ ይችላሉ።—1 ቆሮንቶስ 16:2
በዕቅድ የሚደረግ ስጦታ፦ መዋጮ የሚደረግባቸው አንዳንድ መንገዶች ዕቅድ ማውጣት እና/ወይም የሕግ ባለሙያ ማማከር ይጠይቃሉ። በዚህ መንገድ ዕቅድ ማውጣትህ በምትኖርበት አገር ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የተሻለ ጥቅም ያለው አማራጭ እንድታገኝ ያስችልህ ይሆናል። በርካታ ግለሰቦች፣ በሕይወት እያሉ ወይም በሚሞቱበት ጊዜ በዕቅድ የሚደረጉ ስጦታዎችን መስጠት ስለሚችሉበት መንገድ የተሻለ ግንዛቤ በማግኘታቸው ተጠቅመዋል። አንተም በሚከተሉት መንገዶች መዋጮ ማድረግ ከፈለግህ፣ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በአካባቢህ ያለውን ቅርንጫፍ ቢሮ ማነጋገር ትችላለህ፦
የባንክ ሒሳብ
ኢንሹራንስ እና የጡረታ አበል
የማይንቀሳቀስ ንብረት
አክሲዮኖችና ቦንዶች
ኑዛዜዎችና አደራዎች
አንተ በምትኖርበት አካባቢ መዋጮ ማድረግ ስለሚቻልባቸው አማራጮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ለይሖዋ ምሥክሮች መዋጮ አድርግ” የሚለውን ገጽ ተመልከት።
a የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎችም ሥራችንን ለመደገፍ በደስታ መዋጮ ያደርጋሉ።
b ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች መዋጮ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።