የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንስ ተተክቷል?
ሳይንስ በሕይወትህ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
አንድ መዝገበ ቃላት እንደገለጸው ሳይንስ “አስተውሎ በማየት፣ በሙከራና የአንድን ነገር መጠን በመለካት ግዑዙን ጽንፈ ዓለም ሥርዓት ባለው መንገድ ለማወቅ የሚደረግ ጥናት” ነው። ይህን ሁሉ ማድረግ ደግሞ አዳጋች ከመሆኑም ሌላ ብዙውን ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ነው። የሳይንስ ሊቃውንት ለሳምንታት፣ ለወራት አልፎ ተርፎም ለዓመታት ሙከራዎችን ያደርጋሉ፤ ይመራመራሉ። አንዳንድ ጊዜ ልፋታቸው መና ሊቀር ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ ግን የሰው ልጆችን የሚጠቅሙ ሥራዎችን አከናውነዋል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።
አንድ የአውሮፓ ኩባንያ ጠንካራ ፕላስቲክንና ዘመናዊ ማጣሪያን በመጠቀም ሰዎች የተበከለ ውኃ በመጠጣት ምክንያት ከሚመጣ በሽታ እንዲጠበቁ የሚረዳ አንድ መሣሪያ ሠርቷል። እንደነዚህ ያሉ መሣሪያዎች በ2010 በሄይቲ የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥ በመሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ወቅት ጥቅም ላይ ውለዋል።
ከመሬት በላይ ደግሞ አቅጣጫ ለመጠቆም የሚረዳ የሳተላይቶች አውታር አለ፤ ይህም ግሎባል ፖዚሺኒንግ ሲስተም ተብሎ ይጠራል። ግሎባል ፖዚሺኒንግ ሲስተም መጀመሪያ የተሠራው ለወታደራዊ አገልግሎት ቢሆንም መኪና አሽከርካሪዎች፣ የአውሮፕላን አብራሪዎች፣ መርከበኞች አልፎ ተርፎም አዳኞችና ተራራ ወጪዎች የሚጓዙበትን አቅጣጫ ለማወቅ ይጠቀሙበታል። ግሎባል ፖዚሺኒንግ ሲስተምን ለፈለሰፉት የሳይንስ ሊቃውንት ምስጋና ይግባቸውና የምትፈልግበት ቦታ በቀላሉ መድረስ ትችላለህ።
ሞባይል ስልክ፣ ኮምፒውተር ወይም ኢንተርኔት ትጠቀማለህ? ዘመናዊ ሕክምና ጤንነትህ እንዲሻሻል ወይም ከነበረብህ በሽታ እንድትድን አድርጓል? በአውሮፕላን ትጓዛለህ? እንዲህ ከሆነ ሳይንስ ለሰው ዘር ካበረከታቸው ነገሮች በአንዳንዶቹ እየተጠቀምክ ነው ማለት ነው። እንግዲያው ሳይንስ በሕይወትህ ላይ በብዙ መንገዶች ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ሊባል ይችላል።
ሳይንስ ያሉበት የአቅም ገደቦች
በዘመናችን ያሉ የሳይንስ ሊቃውንት የእውቀት አድማሳቸውን ለማስፋት ሲሉ በተፈጥሮ ላይ ጥልቅ ምርምር እያደረጉ ነው። የኑክሌር የፊዚክስ ሊቃውንት፣ የአተምን ውስጣዊ አሠራሮች በጥልቀት የሚመረምሩ ሲሆን የአስትሮፊዚክስ ጠበብት ደግሞ የጽንፈ ዓለምን አመጣጥ ለማወቅ በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተከናወኑትን ነገሮች ያጠናሉ። አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት በዓይን በማይታየውና ሊደረስበት በማይችለው ዓለም ላይ ይበልጥ ምርምር ባደረጉ መጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው አምላክ ቢኖር ኖሮ ሊያገኙት ይገባ እንደነበር ይናገራሉ።
አንዳንድ ስመ ጥር የሳይንስ ሊቃውንትና ፈላስፎች ከዚህም አልፈው ሄደዋል። እነዚህ ሰዎች፣ የሳይንሳዊ ጽሑፎች አዘጋጅ የሆኑት አሚር አክዜል “የአምላክን መኖር በመቃወም የቀረበ ሳይንሳዊ መከራከሪያ” በማለት የገለጹትን ሐሳብ ያራምዳሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዓለም የታወቁ አንድ የፊዚክስ ሊቅ “በጽንፈ ዓለም ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ የሚያበረክት አምላክ ለመኖሩ ማስረጃ ያልተገኘ መሆኑ እንዲህ ዓይነት አምላክ እንደሌለ በማያሻማ መልኩ ያረጋግጣል” በማለት ተናግረዋል። ሌሎች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አምላክ እንደሠራቸው የተገለጹት ነገሮች “አስማታዊ ጥበብ” እና “ከሰብዓዊ ችሎታ በላይ የሆኑ ማታለያዎች” እንደሆኑ ይናገራሉ።a
አሁን የሚነሳው ጥያቄ ግን ሳይንስ እንዲህ ያለ ድምዳሜ ላይ መድረስ የቻለው ስለ ተፈጥሮ ሁሉንም ነገር አውቆ ነው? የሚል ነው። የዚህ ጥያቄ መልስ በአጭሩ አይደለም የሚል ነው። ሳይንስ አስገራሚ እድገት እንዳስመዘገበ ባይካድም ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት አሁንም ገና ብዙ ያልታወቁና ምናልባትም ሊታወቁ የማይችሉ ነገሮች እንዳሉ ይገነዘባሉ። “እያንዳንዱን ነገር አበጥረን ማወቅ አንችልም” በማለት በተፈጥሮ ጥናት መስክ የፊዚክስ ሊቅና የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ስቲቨን ዋይንበርግ ተናግረዋል። የታላቋ ብሪታንያ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት የተከበሩት ፕሮፌሰር ማርቲን ሪስ “ሰዎች ፈጽሞ ሊረዷቸው የማይችሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ” በማለት ጽፈዋል። በጣም ትንሽ ከሆነችው ሴል አንስቶ እስከ ግዙፉ ጽንፈ ዓለም ድረስ ካሉት ፍጥረታት መካከል አብዛኞቹን ሳይንስ እስካሁን ድረስ ሊረዳቸው አለመቻሉ የተረጋገጠ ሐቅ ነው። የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት፦
የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ሕይወት ባላቸው ሴሎች ውስጥ የሚካሄዱትን ሂደቶች ሙሉ በሙሉ አልተረዱም። ሴሎች ኃይል የሚጠቀሙት፣ ፕሮቲን የሚያመርቱትና እየተባዙ የሚሄዱት እንዴት እንደሆነ ሳይንስ ገና ሙሉ በሙሉ መረዳት አልቻለም።
የስበት ኃይል በቀኑ ውስጥ በእያንዳንዷ ሴኮንድ በእኛ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሆኖም ይህ ለፊዚክስ ሊቃውንት ሚስጥር ነው። የስበት ኃይል፣ ወደ ላይ በምትዘልበት ጊዜ ወደ ታች የሚስብህ እንዴት እንደሆነ ወይም ጨረቃ ምህዋሯን ጠብቃ በመሬት ዙሪያ እንድትዞር የሚያደርጋት እንዴት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አያውቁም።
የኮስሞሎጂ ባለሙያዎች በግምት 95 በመቶ የሚሆነው የጽንፈ ዓለም ክፍል ለሳይንሳዊ ጥናት በሚያገለግሉ መሣሪያዎች የማይታይ እንደሆነና ምንነቱ ተለይቶ ሊታወቅ እንደማይችል ይናገራሉ። ይህን እንግዳ የሆነ የጽንፈ ዓለም ክፍል፣ ሚስጥራዊ ቁስ አካል እና ሚስጥራዊ ኃይል በማለት ለሁለት ይከፍሉታል። የእነዚህ ነገሮች ምንነት አይታወቅም።
የሳይንስ ሊቃውንትን የሚያስገርሙ ሌሎች የማይታወቁ ነገሮችም አሉ። ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ? አንድ ታዋቂ የሳይንስ ጸሐፊ “ከምናውቀው ነገር ይልቅ የማናውቀው ነገር በጣም ይበልጣል። ሳይንስ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት እንድንዋጥ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ አእምሯችንን በማስፋት ይበልጥ ምርምር ለማድረግ የሚያነሳሳ እንደሆነ ይሰማኛል” በማለት ጽፈዋል።
በመሆኑም ሳይንስ መጽሐፍ ቅዱስን ይተካ ይሆን እንዲሁም በአምላክ ማመንን ያስቀር ይሆን ብለህ የምታስብ ከሆነ የሚከተለውን ነጥብ ተመልከት፦ ጥሩ ችሎታ ያላቸው የሳይንስ ሊቃውንት ዘመናዊ በሆኑት መሣሪያዎቻቸው በመታገዝ ስለ ተፈጥሮ ማወቅ የቻሉት ነገር በጣም ውስን ከሆነ ሳይንስ ተመራምሮ ሊደርስበት ያልቻለውን ነገር የለም ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው? ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ከዚህ ነጥብ ጋር በመስማማት ስለ ሥነ ፈለክ ጥናት አጀማመርና እድገት ረጅም ሐሳብ ካቀረበ በኋላ “የሥነ ፈለክ ጥናት ከተጀመረ 4,000 ዓመት ገደማ ቢያልፍም ጽንፈ ዓለም የጥንቶቹን ባቢሎናውያን ግራ ያጋባ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ግራ እያጋባ ነው” በማለት ደምድሟል።
ሁሉም ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ የራሱን ውሳኔ የማድረግ መብት አለው፤ የይሖዋ ምሥክሮችም የእያንዳንዱን ሰው መብት ያከብራሉ። “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። (ፊልጵስዩስ 4:5) በመሆኑም ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርስ የሚስማሙትና የሚደጋገፉት እንዴት እንደሆነ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።
a አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የማይቀበሉት፣ ምድር የጽንፈ ዓለም እምብርት ናት የሚለውንና አምላክ ዓለምን የፈጠረው ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ ነው የሚለውን በመሳሰሉት ቤተ ክርስቲያን በምታስተምራቸው ትምህርቶች ምክንያት ነው።—“መጽሐፍ ቅዱስ እና የተረጋገጡ ሳይንሳዊ እውነቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።