የጥናት ርዕስ 46
ይሖዋ ምድርን ገነት እንደሚያደርግ ዋስትና የሰጠው እንዴት ነው?
“በምድር ላይ በረከትን የሚሻ ሁሉ በእውነት አምላክ ይባረካል።”—ኢሳ. 65:16
መዝሙር 3 ኃይላችን፣ ተስፋችን፣ ትምክህታችን
ማስተዋወቂያa
1. ኢሳይያስ ለእስራኤላውያን ወገኖቹ የተናገረው መልእክት ምን ነበር?
ነቢዩ ኢሳይያስ ይሖዋን ‘የእውነት አምላክ’ በማለት ጠርቶታል። “እውነት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ “አሜን” ማለት ነው። (ኢሳ. 65:16 ግርጌ) “አሜን” ማለት ደግሞ “ይሁን” ወይም “በእርግጥ” ማለት ነው። “አሜን” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከይሖዋ ወይም ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ሲሠራበት አንድ ነገር እውነት ስለመሆኑ ዋስትና ይሰጣል። በመሆኑም ኢሳይያስ ለእስራኤላውያን ወገኖቹ የተናገረው መልእክት ግልጽ ነበር፦ ይሖዋ የሚናገረው ትንቢት ምንጊዜም እምነት የሚጣልበት ነው። ይሖዋ የገባቸውን ቃሎች በሙሉ በመፈጸም ይህን እውነታ አረጋግጧል።
2. ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በገባልን ቃል ላይ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው? የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?
2 ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ በገባው ቃል ላይስ ተመሳሳይ እምነት መጣል እንችላለን? ከኢሳይያስ ዘመን ከ800 ዓመታት ገደማ በኋላ ጳውሎስ አምላክ በገባው ቃል ላይ ምንጊዜም እምነት መጣል የምንችለው ለምን እንደሆነ አብራርቷል። ‘አምላክ ሊዋሽ እንደማይችል’ ተናግሯል። (ዕብ. 6:18) የማንጎ ዛፍ ብርቱካን ሊያፈራ እንደማይችል ሁሉ የእውነት ምንጭ የሆነው ይሖዋ ውሸት መናገር አይችልም። በመሆኑም ይሖዋ በሚናገረው ነገር ሁሉ ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት መጣል እንችላለን፤ ይህም ስለ ወደፊቱ ጊዜ የገባልንን ቃል ይጨምራል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ ይሖዋ ወደፊት ምን እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል? ይህ ቃል በእርግጥ እንደሚፈጸም ዋስትና የሰጠንስ እንዴት ነው?
ይሖዋ ምን ቃል ገብቶልናል?
3. (ሀ) የአምላክ አገልጋዮች የትኛውን ተስፋ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል? (ራእይ 21:3, 4) (ለ) አንዳንድ ሰዎች ይህን ተስፋ ስንነግራቸው ምን ምላሽ ይሰጣሉ?
3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንመለከተው፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱት ተስፋ ነው። (ራእይ 21:3, 4ን አንብብ።) ይሖዋ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” በማለት ቃል ገብቶልናል። ብዙዎቻችን ለሌሎች በምንመሠክርበት ጊዜ በገነት ውስጥ ስለሚኖረን ሕይወት የሚገልጸውን ይህን የሚያበረታታ ጥቅስ እንጠቀምበታለን። አንዳንድ ሰዎች ይህን ተስፋ ስንነግራቸው ምን ምላሽ ይሰጣሉ? “ይህማ የሕልም እንጀራ ነው” ይሉ ይሆናል።
4. (ሀ) ይሖዋ የትኛውን ነገር አስቀድሞ ያውቅ ነበር? (ለ) ይሖዋ ተስፋ ከመስጠት ባለፈ ምን አድርጎልናል?
4 ይሖዋ ሐዋርያው ዮሐንስን በመንፈሱ በመምራት ስለ ገነት የሚናገረውን ይህን ተስፋ እንዲጽፍ ባደረገበት ወቅት በዘመናችንም የመንግሥቱን መልእክት በምንሰብክበት ጊዜ ይህን ተስፋ ለሌሎች እንደምንናገር ያውቅ ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ፣ ብዙ ሰዎች “አዳዲስ ነገሮች” እንደሚመጡ የሚገልጸውን ይህን ተስፋ ማመን ሊከብዳቸው እንደሚችል አስቀድሞ ያውቃል። (ኢሳ. 42:9፤ 60:2፤ 2 ቆሮ. 4:3, 4) ታዲያ ሌሎች ሰዎች በራእይ 21:3, 4 ላይ የተጠቀሱት በረከቶች እውን እንደሚሆኑ እንዲተማመኑ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? እኛስ በዚህ ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ይህን የሚያጽናና ተስፋ ከመስጠት ባለፈ በዚህ ተስፋ ላይ እምነት እንድንጥል የሚያነሳሱ አሳማኝ ምክንያቶችን ተናግሯል። እነዚህ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?
ይሖዋ ቃሉ እንደሚፈጸም ዋስትና ሰጥቶናል
5. ይሖዋ ስለ ገነት የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም የሚያረጋግጡ ምክንያቶችን በየትኛው ጥቅስ ላይ ማግኘት እንችላለን? ጥቅሱ ምን ይላል?
5 ይሖዋ ስለ ገነት የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም የሚያረጋግጡ ምክንያቶችን በዚህ ምዕራፍ ቀጣይ ቁጥሮች ላይ ማግኘት እንችላለን። እንዲህ ይላል፦ “በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ‘እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ’ አለ። ደግሞም ‘እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት ስለሆኑ ጻፍ’ አለኝ። እንዲህም አለኝ፦ ‘እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል! እኔ አልፋና ኦሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነኝ።’”—ራእይ 21:5, 6ሀ
6. በራእይ 21:5, 6 ላይ የሚገኘው ሐሳብ አምላክ በገባው ቃል ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን እንዴት ነው?
6 እነዚህ ቁጥሮች፣ አምላክ በገባው ቃል ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክሩልን እንዴት ነው? ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለው መጽሐፍ ይህን ጥቅስ አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “እነዚህ የወደፊት በረከቶች መፈጸማቸው እንደማይቀር ይሖዋ ራሱ የማረጋገጫ ፊርማ እንደፈረመ ወይም ዋስትና እንደሰጠ ያህል ነው።”b በራእይ 21:3, 4 ላይ አምላክ የገባውን ቃል እናገኛለን። ከዚያም በቁጥር 5 እና 6 ላይ ይሖዋ የዚህን ቃል እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ፊርማ ወይም ዋስትና ሰጥቶናል ሊባል ይችላል። ይሖዋ ይህን ዋስትና ለመስጠት የተጠቀመባቸውን ቃላት እስቲ በቅርበት እንመርምር።
7. ቁጥር 5 ሲጀምር ምን ይላል? ይህስ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?
7 ቁጥር 5 ሲጀምር፣ ይህን ሐሳብ የተናገረው ‘በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው’ እንደሆነ ይገልጻል። (ራእይ 21:5ሀ) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ይሖዋ ራሱ በቀጥታ የተናገረባቸው ጊዜያት ሦስት ብቻ ናቸው፤ ከእነዚህ አንዱ ይሄኛው ነው። ስለዚህ ይህን ዋስትና የሰጠው ኃያል የሆነ መልአክ፣ ሌላው ቀርቶ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ እንኳ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ራሱ ነው። ይህም ቀጣዩ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት እንደሆነ ያሳያል። ምክንያቱም ይሖዋ ‘ሊዋሽ አይችልም።’ (ቲቶ 1:2) ስለዚህ በራእይ 21:5, 6 ላይ በሚገኙት ቃላት ላይ ሙሉ እምነት መጣል እንችላለን።
“እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ”
8. ይሖዋ ቃሉ መፈጸሙ የተረጋገጠ እንደሆነ ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 46:10)
8 ከዚህ በመቀጠል “እነሆ” የሚለውን ቃል እንመልከት። (ራእይ 21:5) “እነሆ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይገኛል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው፣ ይህ ቃል “አንባቢው ቀጣዩን ሐሳብ ልብ እንዲል የሚያበረታታ ነው።” እዚህ ጥቅስ ላይ “እነሆ” ካለ በኋላ ምን ይላል? አምላክ “ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” ብሏል። እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ አገላለጽ በመከናወን ላይ ያለን ነገር ያመለክታል። ይሖዋ እዚህ ጥቅስ ላይ እየተናገረ ያለው ወደፊት ስለሚከናወኑ ነገሮች ቢሆንም ቃሉ መፈጸሙ የተረጋገጠ ከመሆኑ የተነሳ እየተፈጸመ እንዳለ አድርጎ ገልጾታል።—ኢሳይያስ 46:10ን አንብብ።
9. (ሀ) “ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” የሚለው ዓረፍተ ነገር ይሖዋ የሚያደርጋቸውን የትኞቹን ሁለት ነገሮች ያመለክታል? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ያሉት “ሰማይ” እና “ምድር” ምን ይሆናሉ?
9 በራእይ 21:5 ላይ የሚገኘውን ቀጣዩን ዓረፍተ ነገር ልብ ብለን እንመልከት፤ “ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” ይላል። በራእይ 21 ላይ ይህ አገላለጽ ይሖዋ የሚያደርጋቸውን ሁለት ነገሮች ያመለክታል፤ እነሱም መተካት እና ማደስ ናቸው። በመጀመሪያ፣ ይሖዋ የሚተካው የትኞቹን ነገሮች ነው? ራእይ 21:1 “የቀድሞው ሰማይና የቀድሞው ምድር አልፈዋል” ይላል። “የቀድሞው ሰማይ” የሚለው አገላለጽ በሰይጣንና በአጋንንቱ ተጽዕኖ ሥር ያሉትን መንግሥታት ያመለክታል። (ማቴ. 4:8, 9፤ 1 ዮሐ. 5:19) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ምድር” የሚለው ቃል የምድርን ነዋሪዎች ሊያመለክት ይችላል። (ዘፍ. 11:1፤ መዝ. 96:1) በመሆኑም “የቀድሞው ምድር” የሚለው አገላለጽ በዛሬው ጊዜ ያሉትን ክፉ ሰዎች ያመለክታል። ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ሰማይና ምድር ከመጠገን ይልቅ ሙሉ በሙሉ አጥፍቶ ይተካቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ያሉትን “ሰማይ” እና “ምድር” ‘በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር’ ማለትም በአዲስ መንግሥትና በአዲስ ሰብዓዊ ማኅበረሰብ ይተካቸዋል።
10. ይሖዋ አዲስ የሚያደርገው የትኞቹን ነገሮች ነው?
10 በራእይ 21:5 ላይ ይሖዋ አዲስ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በተመለከተ ምን እንዳለ እናነባለን። ይሖዋ “አዳዲስ ነገሮችን እፈጥራለሁ” እንዳላለ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ “ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” ብሏል። ይሖዋ ምድርንና የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ደረጃ በማድረስ አዲስ ያደርጋቸዋል። ኢሳይያስ በትንቢት እንደተናገረው መላዋ ምድር እንደ ኤደን ያለች ውብ ገነት ትሆናለች። እኛም በግለሰብ ደረጃ እንታደሳለን። አንካሶች፣ ዓይነ ስውራንና መስማት የተሳናቸው ሰዎች ይፈወሳሉ፤ ሙታን እንኳ ሕያው ይሆናሉ።—ኢሳ. 25:8፤ 35:1-7
‘እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት ናቸው፤ እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል!’
11. ይሖዋ ዮሐንስን ምን በማለት አዘዘው? ምክንያቱንስ የገለጸው እንዴት ነው?
11 አምላክ የሰጠው ዋስትና ሌላስ ምን ያካትታል? ይሖዋ ዮሐንስን “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት ስለሆኑ ጻፍ” ብሎታል። (ራእይ 21:5) ይሖዋ “ጻፍ” የሚል ትእዛዝ በመስጠት ብቻ አልተወሰነም። ምክንያቱንም ነግሮታል። “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት [ናቸው]” ብሏል፤ ይህም አምላክ የተናገራቸው ቃላት እምነት የሚጣልባቸውና ትክክለኛ እንደሆኑ ያመለክታል። ዮሐንስ “ጻፍ” የሚለውን ትእዛዝ በመፈጸሙ አመስጋኞች ነን። አምላክ ስለ ገነት የሰጠውን ተስፋ ማንበብና ስለሚጠብቁን አስደሳች በረከቶች ማሰላሰል የቻልነው ለዚህ ነው።
12. ይሖዋ “እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል” ማለቱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
12 ከዚያስ አምላክ ምን አለ? “እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል!” (ራእይ 21:6) እዚህ ላይ ይሖዋ፣ ከገነት ተስፋ ጋር በተያያዘ የተጠቀሱት ነገሮች በሙሉ እንደተፈጸሙ አድርጎ ተናግሯል። ደግሞም እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ ዓላማውን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም። ቀጥሎም ይሖዋ፣ የገባው ቃል እንደሚፈጸም የሚያረጋግጥ ሌላ አስተማማኝ ዋስትና ሰጥቷል። ይህ ዋስትና ምንድን ነው?
“እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ”
13. ይሖዋ “እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ” ያለው ለምንድን ነው?
13 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ ዮሐንስ ባየው ራእይ ላይ ይሖዋ ራሱ የተናገረባቸው ሦስት አጋጣሚዎች አሉ። (ራእይ 1:8፤ 21:5, 6፤ 22:13) በሦስቱም ጊዜያት ይሖዋ “እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ” ብሏል። “አልፋ” የግሪክኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ፊደል፣ “ኦሜጋ” ደግሞ የመጨረሻው ፊደል ነው። ይሖዋ “እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ” ማለቱ አንድ ነገር ከጀመረ በተሳካ ሁኔታ ዳር እንደሚያደርሰው ያመለክታል።
14. (ሀ) ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ “አልፋ” ካለባቸው ጊዜያት አንዱ የቱ ነው? “ኦሜጋ” የሚለውስ መቼ ነው? (ለ) በዘፍጥረት 2:1-3 ላይ ምን ዋስትና እናገኛለን?
14 ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ለሰዎችና ለምድር ያለውን ዓላማ ገልጿል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ ‘ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም።’” (ዘፍ. 1:28) በዚህ ወቅት ይሖዋ “አልፋ” እንዳለ ሊቆጠር ይችላል። ፍጹምና ታዛዥ የሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ምድርን የሚሞሉበትና ገነት የሚያደርጉበት ጊዜ እንደሚመጣ በግልጽ ተናግሯል። ወደፊት ይህ ዓላማው ሲፈጸም ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ “ኦሜጋ” ይላል። ይሖዋ “ሰማያትንና ምድርን እንዲሁም በውስጣቸው ያለውን ነገር ሁሉ” የመፍጠሩን ሥራ ሲያጠናቅቅ አንድ ዋስትና ሰጥቷል። ይህ ዋስትና ዘፍጥረት 2:1-3 ላይ ይገኛል። (ጥቅሱን አንብብ።) ይሖዋ ሰባተኛውን ቀን ለራሱ ቀደሰው። ይህ ምን ማለት ነው? ይሖዋ ለሰዎችና ለምድር ያወጣው ዓላማ በእርግጥ እንደሚፈጸም ዋስትና መስጠቱ ነው። በሰባተኛው ቀን መጨረሻ ላይ ዓላማው ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል።
15. አምላክ ለሰው ልጆች ያወጣውን ዓላማ ሰይጣን ያከሸፈው ሊመስል የሚችለው ለምንድን ነው?
15 አዳምና ሔዋን ካመፁ በኋላ ኃጢአተኞች ሆኑ፤ ኃጢአትንና ሞትንም ለዘሮቻቸው አወረሱ። (ሮም 5:12) በመሆኑም አምላክ፣ ምድር ፍጹምና ታዛዥ በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ያወጣውን ዓላማ ሰይጣን ያከሸፈው ሊመስል ይችላል። ሰይጣን፣ ይሖዋ መቼም “ኦሜጋ” ማለት እንዳይችል ያደረገው ይመስል ነበር። ሰይጣን፣ ይሖዋ ከዚያ በኋላ ብዙ አማራጭ እንደሌለው አስቦ ሊሆን ይችላል። አንደኛው አማራጭ አዳምንና ሔዋንን ማጥፋትና ለሰዎች ያለውን ዓላማ የሚያስፈጽሙ ሌሎች ፍጹም ባልና ሚስት መፍጠር ነበር። ሆኖም አምላክ ይህን ቢያደርግ ኖሮ ዲያብሎስ እሱን “ውሸታም ነው” ብሎ ይከሰው ነበር። ለምን? ምክንያቱም በዘፍጥረት 1:28 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን፣ ምድር በእነሱ ዘሮች እንደምትሞላ ነግሯቸዋል።
16. ሰይጣን፣ ይሖዋ ዓላማውን መፈጸም እንዳልቻለ በመግለጽ ሊከሰው የሚችለው ምን ቢሆን ነበር?
16 ሰይጣን፣ አምላክ ያለው ሌላው አማራጭ የትኛው እንደሆነ አስቦ ሊሆን ይችላል? ምናልባትም ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን መቼም ቢሆን ፍጽምና ደረጃ ላይ መድረስ የማይችሉ ልጆችን እንዲወልዱ ይፈቅድላቸዋል ብሎ አስቦ ይሆናል። (መክ. 7:20፤ ሮም 3:23) ይህ ቢሆን ኖሮ ዲያብሎስ፣ ይሖዋ ዓላማውን መፈጸም እንደማይችል በመግለጽ ይከሰው እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም። ለምን? ምክንያቱም ይህ አማራጭ፣ አምላክ ገነት የሆነችው ምድር ፍጹምና ታዛዥ በሆኑ የሰው ልጆች እንድትሞላ ያወጣውን ዓላማ ሊያሳካ አይችልም።
17. ሰይጣን እንዲሁም አዳምና ሔዋን ቢያምፁም ይሖዋ ለሁኔታው መፍትሔ የሰጠው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
17 ሰይጣን እንዲሁም አዳምና ሔዋን ቢያምፁም ይሖዋ ለሁኔታው መፍትሔ የሰጠበት መንገድ ሰይጣንን በጣም አስደንግጦት መሆን አለበት። (መዝ. 92:5) ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ በመፍቀድ ውሸታም አለመሆኑን አሳይቷል። በተጨማሪም ይሖዋ ምንም ነገር ዓላማውን ከመፈጸም ሊያግደው እንደማይችል አሳይቷል። ታዛዥ የሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮችን የሚያድን “ዘር” እንዲገኝ በማድረግ ዓላማውን ለማስፈጸም እርምጃ ወስዷል። (ዘፍ. 3:15፤ 22:18) ሰይጣን፣ ይሖዋ ያደረገውን የቤዛውን ዝግጅት ሲመለከት በጣም ደንግጦ መሆን አለበት! ለምን? ምክንያቱም ቤዛው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ዝግጅት ነው። (ማቴ. 20:28፤ ዮሐ. 3:16) ራስ ወዳድ የሆነው ሰይጣን ደግሞ እንዲህ ያለው ባሕርይ የለውም። ታዲያ የቤዛው ዝግጅት ምን ውጤት ያስገኛል? በሺህ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ፍጹምና ታዛዥ የሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ገነት የሆነችውን ምድር ይወርሳሉ፤ በዚህ መንገድ የይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማ ይፈጸማል። በዚያ ወቅት ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ “ኦሜጋ” ይላል።
ይሖዋ ስለ ገነት በሰጠው ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?
18. አምላክ የትኞቹን ሦስት ዋስትናዎች ሰጥቶናል? (“ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንድንጥል የሚያነሳሱን ሦስት ምክንያቶች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
18 እስካሁን ከተመለከትናቸው ነጥቦች አንጻር፣ አምላክ ገነትን አስመልክቶ የገባውን ቃል ለሚጠራጠሩ ሰዎች የትኞቹን ዋስትናዎች ልንነግራቸው እንችላለን? አንደኛ፣ ይህን ቃል የገባልን ይሖዋ ራሱ ነው። የራእይ መጽሐፍ “በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ‘እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ’ አለ” ይላል። እሱ ቃሉን ለመፈጸም የሚያስችል ጥበብ፣ ኃይልና ፍላጎት አለው። ሁለተኛ፣ ይህ ተስፋ መፈጸሙ የተረጋገጠ ከመሆኑ የተነሳ በይሖዋ ዓይን ያኔም እንደተፈጸመ ሊቆጠር ይችላል። ይሖዋ “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት [ናቸው]፤ እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል!” ያለው ለዚህ ነው። ሦስተኛ፣ ይሖዋ አንድ ነገር ከጀመረ በተሳካ ሁኔታ ዳር ያደርሰዋል። “እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ” የሚለው አገላለጽ ይህን ያረጋግጣል። ይሖዋ፣ ሰይጣን ውሸታም እንደሆነና ዓላማውን ከመፈጸም ሊያግደው እንደማይችል በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል።
19. አንድ ሰው አምላክ ገነትን አስመልክቶ የሰጠውን ተስፋ ቢጠራጠር ምን ማድረግ ትችላለህ?
19 አምላክ የሰጠውን ዋስትና በአገልግሎት ላይ ለምታገኛቸው ሰዎች በተናገርክ ቁጥር ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ያለህ እምነት እየተጠናከረ እንደሚሄድ አስታውስ። እንግዲያው ከዚህ በኋላ ራእይ 21:4 ላይ የሚገኘውን ስለ ገነት የሚገልጽ አስደሳች ተስፋ ለሌላ ሰው ስታነብ ግለሰቡ “ይህማ የሕልም እንጀራ ነው” ቢልህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ቁጥር 5ንና 6ን አንብበህ ለምን አታብራራለትም? ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ የራሱን ፊርማ በማስፈር ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም ዋስትና እንደሰጠን አሳየው።—ኢሳ. 65:16
መዝሙር 145 አምላክ የሰጠው የገነት ተስፋ
a በዚህ ርዕስ ላይ፣ ይሖዋ ምድርን ገነት እንደሚያደርግ የገባው ቃል በእርግጥ እንደሚፈጸም ዋስትና የሰጠን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ይህን ዋስትና በተመለከተ ለሌሎች በተናገርን ቁጥር ይሖዋ በገባው ቃል ላይ ያለንን እምነት እናጠናክራለን።