አምላክ በእርግጥ ለሴቶች ያስብላቸዋል?
“ጥንቱንም ኃጢአት ከሴት ተገኘች፤ ስለሷም ሁላችን እንሞታለን።”—መጽሐፈ ሲራክ፣ ሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.
“የዲያብሎስ መግቢያ በር አንቺ ነሽ፤ የተከለከለውን ፍሬ የቀጠፍሽ አንቺ ነሽ፤ መለኮታዊውን ሕግ መጀመሪያ የጣስሽ አንቺ ነሽ። . . . በአምላክ አምሳል የተፈጠረውን ወንድ በቀላሉ ያጠፋሽ አንቺ ነሽ።”—ተርቱሊያን፣ ኦን ዚ አፓረል ኦቭ ዊሜን፣ ሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም.
እነዚህ ጥንታዊ ጥቅሶች የተወሰዱት ከመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። ይሁንና በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን በደል ትክክል ለማስመሰል ለብዙ መቶ ዘመናት ሲሠራባቸው ቆይቷል። በዛሬው ጊዜም እንኳ ሳይቀር አንዳንድ ጽንፈኞች፣ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጭቆና ተገቢ እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ ሲሉ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን ይጠቅሳሉ፤ እነዚህ ሰዎች ለሰው ዘር ችግሮች ተጠያቂዎቹ ሴቶች እንደሆኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አምላክ፣ ሴቶችን የፈጠረው በወንዶች እንዲናቁና እንዲበደሉ ነበር? ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እስቲ እንመልከት።
አምላክ ሴቶችን ረግሟቸዋል?
አልረገማቸውም። አምላክ የረገመው ‘ዲያብሎስ ተብሎ የሚጠራውን የመጀመሪያውን እባብ’ እንጂ ሴቶችን አይደለም። (ራእይ 12:9፤ ዘፍጥረት 3:14) አምላክ፣ አዳም በሚስቱ ላይ “የበላይ” እንደሚሆን ሲናገር ወንዶች ሴቶችን እንዲጨቁኑ መፍቀዱ አልነበረም። (ዘፍጥረት 3:16) ከዚህ ይልቅ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ኃጢአት መሥራታቸው የሚያስከትለውን አሳዛኝ መዘዝ መተንበዩ ነበር።
በመሆኑም በሴቶች ላይ የሚደርሰው በደል የሰው ልጆች ኃጢአተኛ መሆናቸው ያስከተለው ውጤት እንጂ የአምላክ ፈቃድ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለመጀመሪያው ኃጢአት ስርየት እንዲገኝ ሲባል ሴቶች በወንዶች መጨቆን እንዳለባቸው አይገልጽም።—ሮም 5:12
አምላክ ሴትን የፈጠራት የወንድ የበታች አድርጎ ነው?
አይደለም። ዘፍጥረት 1:27 “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” በማለት ይናገራል። በመሆኑም ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ሲፈጠሩ የአምላክን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ ተሰጥቷቸዋል። አዳምና ሔዋን በስሜትም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ የተለያዩ ቢሆኑም ሁለቱም አንድ ዓይነት መመሪያ የተሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ በፈጣሪያቸው ፊት እኩል መብት ነበራቸው።—ዘፍጥረት 1:28-31
ሔዋን ከመፈጠሯ በፊት አምላክ ለአዳም “የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” ብሎ ነበር። (ዘፍጥረት 2:18) “ረዳት” ወይም “ማሟያ” የሚለው ቃል ሴቲቱ ከወንዱ ታንስ እንደነበር የሚያመለክት ነው? አይደለም፤ ምክንያቱም ይህ የዕብራይስጥ ቃል “አቻ” ወይም ለወንዱ “ተመጣጣኝ የሆነ ረዳት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። የቀዶ ጥገና ሐኪምና ማደንዘዣ የሚሰጥ ባለሙያ በቀዶ ጥገና ወቅት አንዱ የሌላው ረዳት በመሆን ስለሚያከናውኑት የሥራ ድርሻ አስብ። አንዱ የሌላውን ወገን እገዛ ሳያገኝ ብቻውን ሥራውን ማከናወን ይችላል? እንዲህ ማድረጉ አስቸጋሪ ይሆናል። ቀዶ ጥገናውን የሚያከናውነው የቀዶ ሕክምና ባለሙያው ቢሆንም የእሱ የሥራ ድርሻ ማደንዘዣ ከሚሰጠው ባለሙያ ይበልጥ አስፈላጊ ነው ማለት ነው? እንዲህ ማለት ያስቸግራል። በተመሳሳይም አምላክ ወንድና ሴትን የፈጠረው ተባብረው በመሥራት አንዳቸው ለሌላው አጋር እንዲሆኑ እንጂ እርስ በርስ እንዲፎካከሩ አይደለም።—ዘፍጥረት 2:24
አምላክ ለሴቶች እንደሚያስብላቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?
አምላክ ፍጹም ያልሆኑ ኃጢአተኛ ወንዶች ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስቀድሞ ስላወቀ ለሴቶች ጥበቃ ለማድረግ እንደሚፈልግ ገና ከጅምሩ አሳይቷል። ሎር ኤናርድ የተባሉት ደራሲ ላ ቢብል ኡ ፌሚና (መጽሐፍ ቅዱስ በእንስቷ ዓይን) በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ በ16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ሥራ ላይ ስለዋለው የሙሴ ሕግ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “የሕጉ ቃል ኪዳን ከሴት ጋር የተያያዘ ሐሳብ በሚናገርባቸው ቦታዎች ላይ በአብዛኛው የሚያወሳው መብቷን ስለማስከበር ነው።”
ለምሳሌ ያህል፣ ሕጉ አባትም ሆነ እናት እንዲከበሩ ያዛል። (ዘፀአት 20:12፤ 21:15, 17) በተጨማሪም በዚህ ሕግ ላይ ሕዝቡ ለነፍሰ ጡር ሴቶች ተገቢውን አሳቢነት ሊያሳዩ እንደሚገባ ታዝዘው ነበር። (ዘፀአት 21:22) አምላክ ያወጣቸው እነዚህ ሕጎች በዛሬው ጊዜም እንኳ የላቁ እንደሆኑ መመልከት ይቻላል፤ በዘመናችን በብዙ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ አንዳንድ ሴቶች ሕጋዊ መብቶቻቸው እንደማይጠበቁላቸው ስንመለከት የሙሴ ሕግ ለሴቶች ከፍተኛ ጥበቃ የሚያደርግ እንደነበረ መረዳት እንችላለን። ይሁን እንጂ አምላክ ለሴቶች እንደሚያስብላቸው የሚያሳዩት ሕጎች እነዚህ ብቻ አይደሉም።
አምላክ ለሴቶች ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ሕግ
ይሖዋ አምላክ ለእስራኤል ብሔር የሰጠው ሕግ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች በአካላዊ፣ በሥነ ምግባራዊና በመንፈሳዊ ሁኔታ የላቀ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። ብሔሩ ሕጉን ሰምቶ ቢታዘዝ “በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ” ከፍ ያለ ይሆን ነበር። (ዘዳግም 28:1, 2) ታዲያ በሕጉ መሠረት ሴቶች ምን ቦታ ነበራቸው? ቀጥሎ የቀረቡትን ነጥቦች ተመልከት፦
1. ነፃነት፦ በጥንት ዘመን እስራኤላውያን ሴቶች፣ በሌሎች በርካታ ብሔራት ውስጥ ከነበሩ ሴቶች በተለየ መልኩ ከፍተኛ ነፃነት ነበራቸው። የቤተሰቡ ራስ ባልየው ቢሆንም የባሏን ሙሉ አመኔታ ያተረፈች ሚስት “ራሷ አስባ የዕርሻ መሬት [መግዛት]” እንዲሁም ‘ወይን መትከል’ ትችል ነበር። መፍተልና መሸመን የምትችል ከሆነ ደግሞ የራሷን ንግድ እንኳ የማካሄድ መብት ነበራት። (ምሳሌ 31:11, 16-19) በሙሴ ሕግ ሥር ሴቶች የሚታዩት የራሳቸው መብት እንዳላቸው ግለሰቦች እንጂ የወንድ ጥገኛ እንደሆኑ ተደርገው አልነበረም።
በተጨማሪም በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ሴቶች በግለሰብ ደረጃ ከአምላክ ጋር ዝምድና የመመሥረት ነፃነት ነበራቸው። ሐና የተባለችው እስራኤላዊት ስለ ግል ጉዳይዋ ወደ አምላክ እንደጸለየችና ለማንም ሳትናገር ስእለት እንደተሳለች መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ሳሙኤል 1:11, 24-28) የሱነም ከተማ ነዋሪ የሆነች አንዲት ሴት፣ በሰንበት ቀናት ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ የመሄድ ልማድ ነበራት። (2 ነገሥት 4:22-25) እንደ ዲቦራና ሕልዳና ያሉትን ሴቶች ደግሞ አምላክ የእሱ ወኪሎች እንዲሆኑ ተጠቅሞባቸዋል። ትልቅ ቦታ የነበራቸው ወንዶችና ካህናትም ጭምር ከእነዚህ ሴቶች ምክር የጠየቁ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።—መሳፍንት 4:4-8፤ 2 ነገሥት 22:14-16, 20
2. የትምህርት ዕድል፦ ሴቶች በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉ እንደመሆናቸው መጠን የሙሴ ሕግ ሲነበብ እንዲያዳምጡ ተጋብዘዋል፤ ይህም የመማር አጋጣሚ አስገኝቶላቸዋል። (ዘዳግም 31:12፤ ነህምያ 8:2, 8) ከዚህም ሌላ ሕዝቡ ከሚያቀርበው አምልኮ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ሥልጠና ይሰጣቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሴቶች በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ‘አገልግሎት’ ይሰጡ፣ ሌሎች ደግሞ ወንዶችንና ሴቶችን ባቀፈ የመዘምራን ቡድን ውስጥ ያገለግሉ ነበር።—ዘፀአት 38:8፤ 1 ዜና መዋዕል 25:5, 6
ብዙ ሴቶች አትራፊ ንግድ ለማካሄድ የሚያስፈልገው እውቀትና ችሎታ ነበራቸው። (ምሳሌ 31:24) በዚያ ዘመን በነበሩ ሌሎች ብሔራት፣ ወንዶች ልጆችን ማስተማር የሚችሉት አባቶች ብቻ ቢሆኑም እስራኤላውያን እናቶች ወንዶች ልጆቻቸውን ለአካለ መጠን እስኪደርሱ ድረስ ያስተምሯቸው ነበር። (ምሳሌ 31:1) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ሴቶች የተማሩ ነበሩ።
3. አክብሮት፦ በአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚል ግልጽ ሕግ ነበር። (ዘፀአት 20:12) ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በጻፈው ምሳሌ ላይ “ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ምክር አድምጥ፤ የእናትህንም ትምህርት አትተው” የሚል ሐሳብ እናገኛለን።—ምሳሌ 1:8
ሕጉ በተቃራኒ ፆታዎች መካከል ሊኖር ስለሚገባው ምግባር ዝርዝር ደንቦችን የያዘ ሲሆን እነዚህ ደንቦች ወንዶች፣ ሴቶችን በአክብሮት እንዲይዟቸው ያዝዛሉ። (ዘሌዋውያን 18:6, 9፤ ዘዳግም 22:25, 26) አንድ ጥሩ ባል የሚስቱን የአቅም ገደብ ከግምት ማስገባት ነበረበት።—ዘሌዋውያን 18:19
4. ጥበቃ ማግኘት፦ ይሖዋ “ለድኻ አደጉ አባት፣ ለባልቴቲቱም ተሟጋች” እንደሆነ በቃሉ ውስጥ ገልጿል። በሌላ አነጋገር መብታቸውን የሚያስጠብቅላቸው አባት ወይም ባል ለሌላቸው ሁሉ ጥብቅና ይቆምላቸው ነበር። (መዝሙር 68:5፤ ዘዳግም 10:17, 18) ለምሳሌ፣ ነቢይ የነበረ ባሏን በሞት ያጣች አንዲት ሴት፣ አበዳሪዋ በደል ባደረሰባት ወቅት ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ ተአምር በመሥራት ከችግሯ እንድትላቀቅ ያደረጋት ሲሆን ይህም ክብሯ እንዲጠበቅ አድርጓል።—2 ነገሥት 4:1-7
እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ሰለጰዓድ የተባለ አንድ አባወራ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ሞተ። በመሆኑም አምስት ሴቶች ልጆቹ በተስፋይቱ ምድር ውስጥ “ርስት” እንዲሰጣቸው ሙሴን ጠየቁት። በዚህ ወቅት ይሖዋ የሰለጰዓድ ልጆች ለጥያቄያቸው ፍትሐዊ ምላሽ እንዲያገኙ ሙሴን አዝዞታል፤ “በአባታቸው ዘመዶች መካከል ድርሻቸውን ርስት አድርገህ ልትሰጣቸው ስለሚገባ የአባታቸውን ድርሻ ለእነርሱ አስተላልፍላቸው” ብሎታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስራኤላውያን ሴቶች ከአባታቸው ርስት መቀበልና ለዘሮቻቸው ማስተላለፍ ተፈቀደላቸው።—ዘኍልቍ 27:1-8
አምላክ ለሴቶች ያለውን አመለካከት አዛብቶ ማቅረብ
በሙሴ ሕግ ሥር ሴቶች የተከበረ ቦታ የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ መብታቸው ይጠበቅላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ከአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ወዲህ፣ ሴቶች ዝቅ ተደርገው ይታዩ የነበረበት የግሪክ ባሕል በአይሁድ እምነት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀመረ።—“ስለ ሴቶች የተዛባ አመለካከት የተንጸባረቀባቸው የጥንት ጽሑፎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ለምሳሌ ያህል፣ ግሪካዊው ገጣሚ ሂሲየድ (ስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.) የሰው ልጆች ችግሮች በሙሉ የመጡት በሴቶች ምክንያት እንደሆነ ገልጾ ነበር። ቲኦገኒ በተሰኘ ጽሑፉ ላይ ስለ ሴቶች ሲገልጽ “ሟች በሆኑ ወንዶች ላይ መከራ ለማምጣት በመካከላቸው ተሰግስገው የሚኖሩ አደገኛ የሴቶች ዘር” በማለት ተናግሯል። ይህ አስተሳሰብ በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መጀመሪያ ላይ በአይሁድ እምነት ውስጥ ተቀባይነት እያገኘ መጣ። ከሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ወዲህ የተዘጋጀው የአይሁድ ታልሙድ ለወንዶች እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፦ “ከሴቶች ጋር አትነጋገር፤ ምክንያቱም ይህ ውሎ አድሮ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናህን ያሳጣሃል።”
በአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ የነበረው እንዲህ ያለው ሴቶችን በጥርጣሬ ዓይን የመመልከት ዝንባሌ ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ሴቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ ባላቸው ሚና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። በኢየሱስ ዘመን ሴቶች ወደ ቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ መግባት የሚችሉት እስከ ሴቶች አደባባይ ብቻ ነበር። የሃይማኖት ትምህርት የሚሰጠው ለወንዶች ብቻ ሲሆን በምኩራብ ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ተገልለው ለብቻቸው እንዲቀመጡ ይደረግ የነበረ ይመስላል። አንድ የአይሁድ ረቢ “ለሴት ልጁ ቶራን [የሙሴን ሕግ] የሚያስተምር ሰው ብልግና እያስተማራት ነው” ብሎ እንደተናገረ ታልሙድ ላይ ተጠቅሷል። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ አምላክ ለሴቶች ያለውን አመለካከት አዛብተው በማቅረባቸው ብዙ ወንዶች ሴቶችን እንዲንቁ አድርገዋል።
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ፣ በወግ ላይ የተመሠረተው እንዲህ ያለው ጭፍን ጥላቻ በባሕሉ ውስጥ ሥር ሰዶ እንደነበር አስተውሏል። (ማቴዎስ 15:6, 9፤ 26:7-11) ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ባሕል ኢየሱስ ሴቶችን በሚይዝበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር? ኢየሱስ በዚህ ረገድ ከነበረው አመለካከትና ካደረጋቸው ነገሮች ምን ልንማር እንችላለን? እውነተኛ ክርስትና ለሴቶች እፎይታ አምጥቷል? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።