“ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው”
“እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።”—ዘፍጥረት 1:27
1. እውነት ለክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች በረከት ሆኖላቸዋል ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
ከይሖዋ ሕዝቦች አንዱ መሆንና በሕይወታቸው ውስጥ አምላክን ለማፍቀርና ለመታዘዝ ቅድሚያ ከሚሰጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ጋር ለመተባበርና ለመወዳጀት መቻል ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነው! በተጨማሪም እውነት ይሖዋ አምላክን ከማያስደስቱ ዝንባሌዎችና ድርጊቶች እንድንላቀቅ ከማድረጉም በላይ በክርስቲያናዊ አኗኗር እንዴት መመላለስ እንደሚገባን ያስተምረናል። (ዮሐንስ 8:32፤ ቆላስይስ 3:8-10) ለምሳሌ ያህል፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች ወንዶች ወንድነታቸውን፣ ሴቶች ደግሞ ሴትነታቸውን ስለሚያሳዩባቸው መንገዶች የተለያየ ባሕል ወይም አስተሳሰብ አላቸው። ይህ የሆነው ወንዶች የወንድነት ባሕርይ፣ ሴቶች ደግሞ የሴትነት ባሕርይ ኖሯቸው ስለ ተፈጠሩ ነው? ወይስ ግንዛቤ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች ጉዳዮች አሉ?
2. (ሀ) ስለ ወንድነትና ሴትነት ያለንን አመለካከት የሚወስነው ምን መሆን ይኖርበታል? (ለ) ጾታን አስመልክቶ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
2 እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት የባሕል ወይም የወግ ወይም ደግሞ የግል አመለካከት ይኑራቸው መገዛት የሚገባቸው የአምላክ ቃል ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ማቴዎስ 15:1-9) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወንድነትና ስለ ሴትነት ባሕርያት ዝርዝር መግለጫ እንደማይሰጥ ይታወቃል። ከዚህ ይልቅ በተለያዩ ባሕሎች እንደምናየው እነዚህ ባሕርያት በተለያዩ መንገዶች መንጸባረቅ የሚችሉበትን ነፃነት ይሰጣል። ወንዶችና ሴቶች አምላክ በፈጠራቸው ሁኔታ ለመኖር ከፈለጉ ወንዶች የወንድነት ባሕርይ፣ ሴቶች ደግሞ የሴትነት ባሕርይ ማሳየት ይኖርባቸዋል። ለምን? ወንድና ሴት በአካል አንዱ የሌላው ማሟያ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በወንድነትና በሴትነት ባሕርያትም ረገድ አንዳቸው የሌላው ማሟያ እንዲሆኑ ተደርገው የተፈጠሩ ናቸው። (ዘፍጥረት 2:18, 23, 24፤ ማቴዎስ 19:4, 5) ሆኖም ጾታን አስመልክቶ ያለው አመለካከት የተጣመመ ወይም የተዛባ ሆኗል። ወንድነትን አስገድዶ ከመግዛት፣ ከኃይለኛነት ወይም ከትምክህተኝነት ጋር የሚያመሳስሉ ብዙዎች ናቸው። በአንዳንድ ባሕሎች አንድ ወንድ በሰው ፊትም ሆነ ለብቻው ቢያለቅስ አሳፋሪ ወይም ያልተለመደ ነገር እንደሆነ ይቆጠራል። ሆኖም ‘ኢየሱስ’ በአልዓዛር መቃብር አጠገብ በሕዝብ መካከል ቆሞ ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:35) ፍጹም የሆነ የወንድነት ባሕርይ የነበረው ኢየሱስ ማልቀስ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሆኖ አልታየውም። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ስለ ሴትነት ባሕርይ ሚዛኑን ያልጠበቀ አመለካከት አላቸው። ሴትነት አካላዊና ወሲባዊ ማራኪነት ብቻ የሚመስላቸው አሉ።
እውነተኛ ወንድነትና እውነተኛ ሴትነት
3. ወንዶችና ሴቶች የሚለያዩት በምንድን ነው?
3 እውነተኛ ወንድነት ምንድን ነው? እውነተኛ ሴትነትስ? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል:- “አብዛኞቹ ወንዶችና ሴቶች በአካላዊ አፈጣጠራቸው ብቻ ሳይሆን በጠባያቸውና በስሜታቸውም ይለያያሉ። ከእነዚህ ልዩነቶች አንዳንዶቹ በዘር ውርስ የሚወሰኑ ናቸው። . . . ብዙዎቹ ከአካላዊ አፈጣጠር የተለዩ የባሕርይ ልዩነቶች ግን እያንዳንዱ ግለሰብ የወንዶችና የሴቶች የሥራ ድርሻ ናቸው ብሎ በሚማራቸው ነገሮች ላይ የተመሠረቱ ይመስላሉ። ሰዎች ወንድ ወይም ሴት ሆነው ይፈጠራሉ፣ ወንድነትን ወይም ሴትነትን ግን ከሌሎች ይማራሉ።” የዘር ውርሳችን ለብዙ ነገሮች ምክንያት ቢሆንም ትክክለኛ የሆነ የወንድነት ወይም የሴትነት ባሕርይ ማዳበራችን አምላክ ከእኛ የሚፈልጋቸውን ነገሮች በመማራችንና እያንዳንዳችን በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ሰጥተን ለመከታተልና ለማከናወን በምንመርጠው ነገር ላይ የተመካ ነው።
4. መጽሐፍ ቅዱስ የወንድንና የሴትን የሥራ ድርሻ በተመለከተ ምን ይላል?
4 የአዳም የሥራ ድርሻ ሚስቱንና ልጆቹን በራስነት ማስተዳደር እንደነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይገልጻል። በተጨማሪም ምድርን በመሙላትና የምድርን ፍጥረታት በሙሉ በመግዛት አምላክ ከወሰነለት ፈቃድ ጋር ተስማምቶ መኖር ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) በቤተሰብ ውስጥ ለሔዋን የተሰጣት የሴትነት ሚና ደግሞ ‘ረዳትነት፣’ የአዳም ማሟያ መሆን፣ ለአዳም ራስነት መገዛትና አምላክ ለእነርሱ ያወጣውን ዓላማ በመፈጸም ረገድ ከአዳም ጋር መተባበር ነበር።— ዘፍጥረት 2:18፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3
5. በወንድና በሴት መካከል ያለው ግንኙነት የተበላሸው እንዴት ነው?
5 ይሁን እንጂ አዳም የተሰጠውን ኃላፊነት አልተወጣም። እንዲሁም ሔዋን ሴትነትዋን አዳም አምላክን ባለመታዘዝ እንዲተባበራት ለማድረግና ለማታለያነት ተጠቀመችበት። (ዘፍጥረት 3:6) አዳምም ስህተት እንደሆነ የሚያውቀውን ነገር በማድረግ እውነተኛ የወንድነት ባሕርይ ሳያሳይ ቀረ። አባቱና ፈጣሪው የሆነው የተናገረውን ከመታዘዝ ይልቅ የተታለለች ሚስቱን ለመከተል መምረጡ ደካማነት ነበር። (ዘፍጥረት 2:16, 17) ወዲያው የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አምላክ አስቀድሞ የተናገረውን የዓመፅ ውጤት መቅመስ ጀመሩ። ቀደም ሲል ስለ ሚስቱ ሞቅ ባለ የፍቅር ስሜትና በግጥም የተናገረው አዳም አሁን በቀዘቀዘ ስሜት ‘የሰጠኸኝ ሴት’ ሲል ጠራት። አለፍጽምናው የወንድነት ባሕርይው እንዲበላሽና አቅጣጫውን እንዲስት ስላደረገው ‘ሚስቱን መግዛት’ ጀመረ። ሔዋን ደግሞ “ፈቃድዋ ወደ ባልዋ” ሆነ፤ ወይም ሚዛኑን ባልጠበቀና ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ምኞትዋ ወደ ባልዋ ሆነ።— ዘፍጥረት 3:12, 16
6, 7. (ሀ) ከጥፋት ውኃ በፊት የወንድነት ባሕርይ እየተበላሸ የመጣው እንዴት ነው? (ለ) ከጥፋት ውኃ በፊት ከነበረው ሁኔታ ምን ልንማር እንችላለን?
6 ከጥፋት ውኃ ቀደም ብሎ የወንድነትንና የሴትነትን ባሕርይ አለአግባብ መጠቀም ግልጽ ሆኖ ታይቷል። በሰማይ የነበራቸውን ቦታ የተዉ መላእክት ከሴቶች ጋር ሩካቤ ሥጋ ለመፈጸም ሰብዓዊ አካል ለበሱ። (ዘፍጥረት 6:1, 2) ከተፈጥሮ ውጭ ከሆነው ከዚህ ተራክቦ የተወለዱት ወንዶች ብቻ እንደነበሩ ታሪኩ ይገልጻል። በተጨማሪም የተወለዱት ልጆች መራባት የማይችሉ ዲቃሎች እንደነበሩ ይታመናል። ሰዎችን አንስተው የሚያፈርጡ በመሆናቸው ኃያላን፣ ኔፍሊም ወይም የሚዘርሩ የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። (ዘፍጥረት 6:4 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) በእርግጥ ኃይለኞች፣ እብሪተኞች፣ ለሌሎች ምንም ዓይነት ርህራሄ የማያሳዩ ነበሩ።
7 አካላዊ ቁንጅና፣ የሰውነት ቅርጽ፣ ግዝፈት ወይም ኃይል በራሱ ተቀባይነት ያለው ወንድነት ወይም ሴትነት እንደማያስገኝ ግልጽ ነው። ሥጋ የለበሱት መላእክት ቆንጆዎች እንደነበሩ ይገመታል። ኔፍሊሞች ደግሞ የፈረጠመ ጡንቻና ግዙፍ ሰውነት ያላቸው ቢሆኑም የአእምሮ ዝንባሌያቸው የተጣመመ ነበር። ዓመፀኞቹ መላእክትና ልጆቻቸው ምድርን በጾታ ብልግናና በዓመፅ ሞልተው ነበር። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ያን ዓለም አጠፋው። (ዘፍጥረት 6:5-7) ይሁን እንጂ ጎርፉ የአጋንንትን ተጽእኖ አላጠፋም፤ እንዲሁም የአዳም ኃጢአት ያስከተላቸውን ውጤቶች አላስወገደም። ከጥፋት ውኃ በኋላም ተገቢ ያልሆነ የወንድነትና የሴትነት ባሕርይ እንደገና ተስፋፍቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ትምህርት ልናገኝባቸው የሚችሉ ጥሩና መጥፎ ምሳሌዎች ተጠቅሰዋል።
8. ዮሴፍ ምን ትክክለኛ የሆነ የወንድነት ምሳሌ ትቷል?
8 ስለ ዮሴፍና ስለ ጶጢፋር ሚስት የሚገልጸው ታሪክ ትክክለኛ የሆነ የወንድነት ባሕርይ ዓለማዊ የሆነን የሴትነት ባሕርይ እንዴት እንደተቋቋመ የሚያሳይ ከፍተኛ ማነጻጸሪያ ነው። የጶጢፋር ሚስት መልከ ቀና የነበረውን ዮሴፍን በጣም ስለወደደችው ልታስተው ሞከረች። በዚያ ዘመን ምንዝር ወይም ዝሙት መፈጸምን የሚከለክል በጽሑፍ የሠፈረ መለኮታዊ ሕግ አልነበረም። ይሁን እንጂ ዮሴፍ ከዚህች ምግባረ ብልሹ ሴት በመሸሽ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የወንድነት ባሕርይ ያሳየ እውነተኛ የአምላክ ሰው መሆኑን አስመስክሯል።— ዘፍጥረት 39:7-9, 12
9, 10. (ሀ) ንግሥት አስጢን የሴትነት ባሕርይዋን አለአግባብ የተጠቀመችበት እንዴት ነበር? (ለ) አስቴር የሴትነት ባሕርይን በሚመለከት ምን ጥሩ ምሳሌ ትታልናለች?
9 አስቴርና ንግሥት አስጢን ለሴቶች ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ተጻራሪ ጠባይ አሳይተዋል። አስጢን በጣም ቆንጆ ስለሆንኩ ንጉሥ አርጤክስስ ምን ጊዜም ለእኔ ፈቃድ መሸነፉ አይቀርም ብላ አስባ ይሆናል። ይሁን እንጂ ቁንጅናዋ በዘመናችን የሚሸጡ የቆዳ ቅባቶች ከሚሰጡት ውጪያዊ ውበት ያልተሻለ ነበር። ባልዋ የሆነውን ንጉሡን ባለመታዘዝዋ ትህትናና የሴትነት ባሕርይ የጎደላት ሆና ተገኝታለች። ንጉሡም እርስዋን ትቶ ይሖዋን የምትፈራና እውነተኛ የሴትነት ባሕርይ ያላት ሴት ንግሥት እንድትሆን መረጠ።— አስቴር 1:10-12፤ 2:15-17
10 አስቴር ለክርስቲያን ሴቶች ግሩም ምሳሌ ትሆናለች። “የተዋበችና መልከ መልካም” የነበረች ቢሆንም ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የነበራት ‘የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለው የማይጠፋው የተሰወረ የልብ ሰው’ ነበር። (አስቴር 2:7፤ 1 ጴጥሮስ 3:4) ውጪያዊ ጌጥ ከሁሉ ይበልጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር ሆኖ አልታያትም። አስቴር የወገኖችዋ ሕይወት አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ እንኳ ለባልዋ ለአርጤክስስ ታዛዥ በመሆን ዘዴኛነትና ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይታለች። አስቴር ዝም ማለት የተሻለ በሚሆንበት ጊዜ ዝም ትል ነበር፤ አስፈላጊና ተገቢ ሲሆን ደግሞ በድፍረት ትናገር ነበር። (አስቴር 2:10፤ 7:3-6) የጎለመሰ ሰው የነበረው የአጎትዋ ልጅ መርዶክዮስ የሰጣትን ምክር ተከትላለች። (አስቴር 4:12-16) ለወገኖቿ ፍቅርና ታማኝነት አሳይታለች።
ውጫዊ መልክ
11. ውጫዊ መልክን በሚመለከት በአእምሯችን መያዝ የሚኖርብን ነገር ምንድን ነው?
11 ትክክለኛ የሴትነት ባሕርይ ለማግኘት ቁልፉ ምንድን ነው? አንዲት እናት እንዲህ በማለት ገልጻለች። “ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች።” (ምሳሌ 31:30) ስለዚህ ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየት የግድ አስፈላጊ ነው። እንዲሁም ፍቅራዊ ደግነት፣ አስደሳች ጠባይ ማሳየት፣ አቅምንና ቦታን ማወቅና በአንደበት አጠቃቀም ረገድ የዋህ መሆን ከአካላዊ ውበት ይልቅ ለሴትነት የበለጠ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።— ምሳሌ 31:26
12, 13. (ሀ) የሚያሳዝነው የብዙ ሰዎች ንግግር ምን ዓይነት ነው? (ለ) የምሳሌ 11:22 ትርጉም ምንድን ነው?
12 የሚያሳዝነው ግን ብዙ ወንዶችና ሴቶች አፋቸውን በጥበብ የማይከፍቱና ፍቅራዊ ደግነት የሚንጸባረቅበት አነጋገር የሌላቸው ናቸው። ንግግራቸው ሽሙጥ፣ ስድብ፣ ብልግና የሞላበትና አሳቢነት የጎደለው ነው። አንዳንድ ወንዶች የብልግና ንግግር የወንድነት ምልክት ነው ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ አንዲት ሴት ቆንጆ ብትሆንና ነገር ግን አስተዋይነት የጎደላት፣ አሽሟጣጭ፣ ተጨቃጫቂ ወይም እብሪተኛ ብትሆን በእርግጥ ቆንጆና የሴትነት ባሕርይ ያላት ናት ልትባል ትችላለችን? “የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደሆነ፣ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት።”— ምሳሌ 11:22
13 ቁንጅና ንጹሕ ካልሆነ አነጋገር፣ ከአሽሟጣጭነት ወይም አስተዋይነት ከጎደለው ጠባይ ጋር ሲሆን ሴትዬዋ ካላት ውጪያዊ ቁመና ጋር የማይጣጣም ይሆናል። እንዲያውም ይህ ዓይነቱ አምላካዊ ያልሆነ ጠባይ አካላዊ ቁንጅና ያላትን ሴት አስቀያሚ ሆና እንድትታይ ሊያደርጋት ይችላል። አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ቁጡ፣ ተሳዳቢ ወይም ጯሂ ቢሆን ወይም ብትሆን እንዲህ ያለው መጥፎ ጠባይ በመልካቸው ቁንጅና ሊሸፈን እንደማይችል ማስተዋል አያቅተንም። ክርስቲያኖች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተ አነጋገርና ጠባይ በአምላክና በሰዎች ዓይን ውብ ሆነው መታየት ይችላሉ፣ ይኖርባቸዋልም።— ኤፌሶን 4:31
14. አንደኛ ጴጥሮስ 3:3-5 የሚያበረታታው ምን ዓይነት አለባበስና አጋጌጥን ነው?
14 እውነተኛ ሴትነትና እውነተኛ ወንድነት በመንፈሳዊ ባሕርያት ላይ የተመኩ ቢሆኑም የምንለብሰውን ልብስና አለባበሳችንን ጨምሮ አካላዊ ቁመናችን ስለ እኛ የሚናገረው ነገር አለው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያን ሴቶችን “ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና” በማለት የመከረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የአለባበስና የአጋጌጥ ፈሊጥ አስታውሶ እንደነበረ አያጠራጥርም።—1 ጴጥሮስ 3:3-5
15. ክርስቲያን ሴቶች በአለባበሳቸው ምንን ለማንጸባረቅ መጣር ይኖርባቸዋል?
15 በአንደኛ ጢሞቴዎስ 2:9, 10 (NW) ላይ ጳውሎስ የሴቶችን አለባበስ አስመልክቶ የተናገረውን እናገኛለን:- “ሴቶች ከልከኝነትና ከጤናማ አእምሮ ጋር ራሳቸውን በሚገባ በተዘጋጀ ልብስ እንዲያስጌጡ እፈልጋለሁ። . . . አምላክን በፍርሐት እናመልካለን ለሚሉ ሴቶች እንደሚገባ በመልካም ሥራ ያጊጡ።” እዚህ ላይ ልከኛ መሆን አስፈላጊ መሆኑንና ጤናማ አእምሮ ያላቸው መሆኑን በሚያንጸባርቅ ሁኔታ ንጹሕና በሚገባ የተዘጋጀ ልብስ መልበስ አስፈላጊ መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል።
16, 17. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ወንዶችና ሴቶች አለባበሳቸው ማራኪ ያልሆነው እንዴት ነው? (ለ) ዘዳግም 22:5 ከሚሰጠው ምክር ምን ብለን መደምደም ይኖርብናል?
16 አንድ ወንድ ወይም አንዲ ሴት፣ አንድ ወጣት ልጅ ወይም አንዲት ልጃገረድ ወሲባዊ ስሜት የሚቀሰቅስ ጠባይ ቢያሳዩ ወይም እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚቀሰቅስ ልብስ ቢለብሱ እውነተኛ የወንድነት ወይም የሴትነት ባሕርያቸው ጎልቶ አይታይም። አምላክንም አያስከብርም። በዓለም ያሉ ብዙ ሰዎች ወንድነትን ወይም ሴትነትን አጋንኖ የሚያሳይ ልብስ ይለብሳሉ። ሌሎች ደግሞ በሁለቱ ጾታዎች መካከል ያለው ልዩነት ፈጽሞ እንዳይታይ የሚያደርግ አለባበስ ይከተላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ያለውን አመለካከት ግልጽ አድርጎ በማስቀመጡ እኛ ክርስቲያኖች ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይሖዋ ለጥንት እስራኤላውያን እንዲህ ብሎ ነበር:- “ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፣ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ። ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና።”— ዘዳግም 22:5
17 መጠበቂያ ግንብ በ16-109 እትሙ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ያብራራውን መለስ ብላችሁ ብትመለከቱ ልትጠቀሙ ትችላላችሁ። ገጽ 17 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ጉዳዩ አንዱ ዓይነት ስታይል ከመጠን ያለፈ ፋሽን የተከተለ መሆኑ ሳይሆን አምላክን አገለግላለሁ ለሚለው ሰው ተገቢ መሆኑ ነው። (ሮሜ 12:2፤ 2 ቆሮንቶስ 6:3) ከመጠን በላይ ግድየለሽነት የሚታይባቸው ወይም ሰውነት ላይ የሚጣበቁ ጠባብ ልብሶች የሰዎችን ትኩረት ከመልእክታችን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊወስዱ ይችላሉ። ወንዶችን ሴት፣ ሴቶችን ደግሞ ወንድ የሚያስመስሉ የአለባበስ ስታይሎች በእርግጥም ከሥርዓት ውጭ ናቸው። (ከዘዳግም 22:5 ጋር አወዳድር።) እርግጥ ነው፣ የአካባቢው የአለባበስ ልማድ በአየሩ ጠባይ፣ ለሥራ በማስፈለጉ ምክንያትና በመሳሰሉት ሊለዋወጥ ይችላል። በዚህ ምክንያት የክርስቲያን ጉባኤ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበሩን የሚሸፍኑ የማይሻሩና የማይለዋወጡ ሕጎችን አያዘጋጅም።”
18. አለባበስንና አበጣጠርን በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክርን በተግባር ላይ ለማዋል ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብናል?
18 እንዴት ያለ ሚዛናዊና ተገቢ ምክር ነው! ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች በይሖዋና በክርስቲያን ጉባኤ ላይ ምን ትርጉም እንደሚሰጥ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ይህ ዓለም በአለባበስና በአጋጌጥ ረገድ የሚያስፋፋውን ነገር ሁሉ በጭፍን ይከተላሉ። ሁላችንም በዓለም አስተሳሰብ ተነክተን እንደሆነ ለማየት ራሳችንን ብንመረምር ጥሩ ነው። አለበለዚያም ሰዎች ወደሚያከብሯቸውና ተሞክሮ ወዳላቸው ወንድም ወይም እህት ጠጋ ብለን በአለባበሳችንና በአጋጌጣችን ረገድ ማስተካከል የሚኖርብን ነገር እንዳለ እንዲነግሩን ልንጠይቅ እንችላለን። ከዚያም የተሰጠንን ምክር በጥሞና እናስብበት።
ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች —እውነተኛ ወንዶችና ሴቶች
19. ልንዋጋው የሚያስፈልገን ምን ዓይነት የማይፈለግ ተጽእኖ ነው?
19 የዚህ ዓለም አምላክ ሰይጣን ነው። እርሱም በሰዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ጾታን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሚታየው መዘበራረቅ ማስተዋል ይቻላል። ይህ ዝብርቅ በአለባበስ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። (2 ቆሮንቶስ 4:4) በአንዳንድ አገሮች ብዙ ሴቶች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ በማለት ራስነትን በተመለከተ ከወንዶች ጋር ይፎካከራሉ። በሌላው በኩል ደግሞ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ወንዶች ልክ እንደ አዳም የራስነት ኃላፊነታቸውን እርግፍ አድርገው ትተዋል። እንዲያውም ጾታቸው የሚጠይቅባቸውን ባሕርይ ለመለወጥ የሚሞክሩ አሉ። (ሮሜ 1:26, 27) መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሌላ ዓይነት አማራጭ አኗኗር እንዳለ አይገልጽም። ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት ስለማንነታቸው ወይም ስለ ወንድነት ወይም ስለ ሴትነት ባሕርያቸው ግራ ተጋብተው የነበሩ ካሉ አምላክ ለወንዶችና ለሴቶች ከወሰነው የአኗኗር ደንብ ጋር ተስማምተው ቢኖሩ ዘላለማዊ ጥቅም ያስገኝላቸዋል። ሰብዓዊ ፍጽምና የሚያገኙ የሰው ልጆች በሙሉ በአድናቆት የሚቀበሉት ይህን አምላክ የወሰነውን ደንብ ነው።
20. ገላትያ 5:22, 23 ስለ ወንድነትና ስለ ሴትነት ያለንን አመለካከት እንዴት ሊነካው ይገባል?
20 ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች የአምላክን መንፈስ ፍሬ የሆኑትን ማለትም ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ደግነትን፣ ጥሩነትን፣ እምነትን፣ የዋህነትን እንዲሁም ራስን መግዛት ማዳበርና ማሳየት እንደሚኖርባቸው ቅዱሳን ጽሑፎች ያመለክታሉ። (ገላትያ 5:22, 23) አምላክ ታላቅ በሆነው ጥበቡ አማካኝነት እነዚህን ባሕርያት እንዲያዳብሩ በማድረግ ወንዶች የወንድነት ባሕርያትን፣ ሴቶች ደግሞ የሴትነት ባሕርያትን እንዲያበለጽጉ ችሎታ ሰጥቷል። የመንፈስ ፍሬዎችን የሚያፈራ ወንድ ማክበር ወይም የመንፈስ ፍሬዎችን የምታፈራ ሴት መውደድ አስቸጋሪ አይሆንም።
21, 22. (ሀ) አኗኗርን በሚመለከት ኢየሱስ ምን ዓይነት ምሳሌ ትቶልናል? (ለ) ኢየሱስ ወንድነቱን ያሳየው እንዴት ነበር?
21 በምድር ላይ ከኖሩ ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሁሉም ክርስቲያኖች የእሱን የአኗኗር መንገድ መከተል ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:21-23) ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልክ እንደ ኢየሱስ ለአምላክ ታማኝ መሆናቸውንና ለቃሉም ታዛዥ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ አስደናቂ የሆኑትን የፍቅር፣ የርህራሄና የምህረት ባሕርያት አሳይቷል። እኛም እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን ለማረጋገጥ እርሱን እንድንመስል ይጠበቅብናል።— ዮሐንስ 13:35
22 ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ወንድ ነበረ። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሕይወት ታሪኩን በምናነብበት ጊዜም የወንድነት ባሕርዮቹን በግልጽ መመልከት እንችላለን። አግብቶ ባያውቅም ከሴቶች ጋር ሚዛኑን የጠበቀ ባልንጀርነት እንደነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። (ሉቃስ 10:38, 39) ከወንዶችም ሆነ ከሴቶች ጋር የነበረው ግንኙነት ንጹሕና የተከበረ ነበር። እርሱ ፍጹም የሆነ የወንድነት አርዓያ ነው። ማንም ወንድ፣ ወይም ሴት ወይም ዓመፀኛ መልአክ ከአምላካዊ ወንድነት ባሕሪውና ለይሖዋ ካለው ታማኝነት ንቅንቅ እንዲያደርገው አልፈቀደም። ኃላፊነቶቹን ለመቀበል ምንም አላመነታም። እንዲሁም ሳያጉረመርም ኃላፊነቱን ተወጥቷል።— ማቴዎስ 26:39
23. ሁለቱም ጾታዎች ያላቸውን ድርሻ በሚመለከት እውነተኛ ክርስቲያኖች ለየት ባለ መንገድ የተባረኩት እንዴት ነው?
23 ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ለመቆጠር መቻልና በሕይወታቸው ውስጥ ይሖዋ አምላክን ለመውደድና ለመታዘዝ ቅድሚያ ከሚሰጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ወጣቶች ጋር ለመወዳጀት መቻል ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነው! የአምላክን ቃል መታዘዝ ነፃነት አያሳጣም። ከዚህ ይልቅ ሁለቱ ጾታዎች ያላቸውን ውበት፣ ዓላማና በግልጽ ተለይቶ የሚታወቅ የሥራ ድርሻ ከሚያዋርደው ከዚህ ዓለም ነፃ እንወጣለን። ወንዶችም ሆንን ሴቶች አምላክ የሰጠንን ቦታና ሚና ከመፈጸም የሚገኘውን እውነተኛ ደስታ ለመቅመስ እንችላለን። አዎን፣ ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ለኛ ሲል ስላዘጋጃቸው ፍቅራዊ ዝግጅቶች ሁሉና ወንድና ሴት አድርጎ ስለ ፈጠረን ምንኛ ልናመሰግነው ይገባል!
ምን ብለህ ትመልሳለህ
◻ መጽሐፍ ቅዱስ የወንዶችንና የሴቶችን ትክክለኛ የሥራ ድርሻ እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?
◻ ከጥፋት ውኃ በፊት የወንድነት ባሕርይ የተበላሸው እንዴት ነው? በጊዜያችን ወንድነትንና ሴትነትን በሚመለከት ምን የተዛባ አመለካከት አለ?
◻ ልንከተለው የምንፈልገው መጽሐፍ ቅዱስ አካላዊ አቋምን አስመልክቶ የሚሰጠው ምን ምክር አለ?
◻ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች እውነተኛ ወንዶችና ሴቶች መሆናቸውን ሊያረጋግጡ የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምንም እንኳን አስቴር ቆንጆ የነበረች ቢሆንም የምትታወሰው በተለይ በልከኝነቷ፣ በጨዋነቷና በመልካም ባሕርይዋ ነው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለውስጣዊ ውበት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለአበጣጠር ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ