ሴቶች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያላቸው የሥራ ድርሻ
“እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።”—ዘፍጥረት 2:23
1, 2. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶችን እንዴት ይመለከታል ብለው ያስባሉ? (ለ) ይሁን እንጂ ያልተዛባ ፍርድ ለመስጠት ከምን ነገር ጋር ማነጻጸር ተገቢ ይሆናል? አንድ መጽሐፍ ስለዚህ ጉዳይ ምን ብሎአል?
ቅዱሳን ጽሑፎች ለሴቶች ያላቸው አመለካከት እንዴት ያለ ነው? በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ አስተያየት ይሰነዘራል። አንድ ስለዚህ ጉዳይ በቅርብ ጊዜ የተጻፈ መጽሐፍ “በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ለሴቶች ዝቅተኛ ቦታ ሰጥቶአል የሚል አስተሳሰብ አለ” ይላል። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በግሪክኛውም ሆነ በዕብራይስጥ ክፍሉ ውስጥ በሴቶች ላይ ይከፋባቸዋል ይላሉ። ይህ እውነት ነውን?
2 ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት እንድንችል በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ይኖሩ የነበሩ ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎች ሴቶቻቸውን እንዴት ይይዙ እንደነበረ መመርመር ተገቢ ይሆናል። የሴት ወላጅ አምላክ አምልኮ በነበራቸው የጥንት ሥልጣኔዎች ሴቶች የመራባት ምልክት እንደሆኑ ተደርገው ይከበሩ ነበር። በባቢሎንና በግብጽ ትልቅ ከበሬታ ይሰጣቸው የነበረ ይመስላል። በሌሎች አገሮች ግን እምብዛም ክብር አይሰጣቸውም ነበር። በጥንትዋ አሶር አንድ ወንድ ሚስቱን እንደፈለገ ሊያባርር ወይም ታማኝ ሆና ካላገኛት ሊገድላት ይችል ነበር። ከቤት ውጭ ስትሆን ደግሞ ፊትዋን መሸፋፈን ነበረባት። በግሪክና በሮም ትምህርትና መጠነኛ ነጻነት ለማግኘት የሚፈቀድላቸው በጣም ሀብታም የሆኑ የቤተ መንግሥት ሴቶች ወይም ባለ ከፍተኛ ማዕረግ ዝሙት አዳሪዎች ነበሩ። ስለዚህ በአዲስ ኪዳን መንፈሣዊ ትምህርት ኢንተርናሽናል መዝገበ ቃላትa ላይ “ሴት [በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ] በቀሩት የምሥራቅ አገሮች ከሚታየው ሁኔታ በተለየ መንገድ እንደ ሰውና የወንድ ባልንጀራ እንደሆነች ትቆጠር ነበር” የሚል ቃል ማንበባችን በጣም የሚያስደስት ነው። ይህ ቁም ነገር በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መደምደሚያ መጽሐፍ ላይ በሚገባ ተገልጾአል። በዚህ መጽሐፍ ነቢዩ ለአንድ ወንድ ሚስቱ “ባልንጀራው” እንደሆነች ከገለጸ በኋላ “ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል” ብሎአል።—ሚልክያስ 2:14, 15
የወንድ አምሳያ ሆና ተፈጠረች
3 እና የግርጌ ማስታወሻ (ሀ) ይሖዋ አዳምን ከፈጠረው በኋላ ምን ሥራ ሰጠው? (ለ) በዚህ ጊዜ ገና ሚስት ባያገኝም ሔዋን ከመፈጠርዋ በፊት ሁኔታው እንዴት ነበር? “የኋለኛው አዳም” ኢየሱስስ?
3 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይሖዋ አዳምን “ከምድር አፈር” ከፈጠረው በኋላ ምድሪቱን እንዲያርስና እንዲኮተኩት በኤደን ገነት አስቀመጠው። በተጨማሪም ይሖዋ የምድርን አራዊትና አእዋፍ እንዲያጠናና ስም እንዲያወጣላቸው ወደ አዳም አመጣቸው። አዳም ይህን ሥራ ለመፈጸም የፈጀበት ጊዜ ምንም ያህል ይሁን በዚያ ወቅት ሁሉ ብቻውን ነበር። እስከዚህ ጊዜ ድረስ አዳም ከይሖዋ ለተቀበለው ሥራ ሁሉ ብቁ፣ ፍጹምና ምንም አይነት ጉድለት ያልነበረው ሰው ነበር።b እርሱ የተሟላ ይሆን ዘንድ “ረዳት” አልነበረችውም።—ዘፍጥረት 2:7, 15, 19, 20
4, 5. (ሀ) አዳም ብቻውን መኖሩ መልካም ባልሆነ ጊዜ ይሖዋ ምን አደረገ? (ለ) ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ምን የረዥም ዘመን ሥራ ሰጣቸው? ይህስ ከሁለቱም ምን ነገር ይፈልግባቸዋል?
4 ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ይሖዋ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም” አለና ከፊቱ በሚጠብቀው ሥራ የምትካፈል ባልንጀራ ሊፈጥርለት ጀመረ። አዳምን አደንዝዞ አስተኛውና ከጎድን አጥንቶቹ አንዱን አውጥቶ ሴትን ፈጠረለት። ‘የአዳም አጥንት አጥንትዋ፤ ሥጋውም ሥጋዋ’ሆነ። አሁን አዳም “ረዳት” ወይም “ማሟያ” ወይም አምሳያ አገኘ። “እግዚአብሔርም ባረካቸው እንዲህም አላቸው፣ ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት። ግዙአትም፣ የባሕርን አሶችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።”—ዘፍጥረት 1:25, 28፤ 2:18, 21-23
5 ይህ ሥራ ለወንዱና ለሴቲቱ በጋራ የተሰጠ ሥራ መሆኑን አስተውሉ። የሁለቱ ህብረት ምድርን በመሙላት ብቻ የተወሰነ አይሆንም። ምድርን መግዛትንና የበታቾቻቸው የሆኑትን ፍጥረታት በሙሉ በተገቢ ሁኔታ ማስተዳደርን ይጨምራል። ይህም የአእምሮ ችሎታና መንፈሳዊ ባሕርያትን ይፈልግባቸው ነበር። ወንዱና ሴቲቱም ይህንን ችሎታና ባሕርይ ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ለማዳበርና ለማሳደግ የሚያስችል አቅምና ችሎታ ነበራቸው።
ለተፈጥሮዋ የሚስማማ የሴት የሥራ ድርሻ
6. (ሀ) ስለወንድና ስለሴት የአቅም መለያየት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ነገር ያመለክታል? (ለ) ሴቶች የይሖዋን ዝግጅት ለመቀበል እንዲችሉ ምን ምክንያቶችን እያስታወሱ ቢያስቡ ጥሩ ነው?
6 በተጨማሪም ምድርን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ አካላዊ ጉልበት እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። ይሖዋ ዳርቻ የሌለው ጥበብ ያለው አምላክ እንደመሆኑ በመጀመሪያ አዳምን በኋላም ሔዋንን ፈጠረ። “ለወንድ” ሲባል “ከወንድ” ተፈጠረች። በግልጽ እንደሚታየውም ከወንድ ያነሰ አቅም እንዲኖራት ተደረገ። (1 ጢሞቴዎስ 2:13፤ 1 ቆሮንቶስ 11:8, 9፤ ከ1 ጴጥሮስ 3:7 ጋር አወዳድር) ይህን ሐቅ ብዙ የሴቶች መብት ተከራካሪዎችና አንዳንድ ሌሎች ሴቶች መቀበል ያስቸገራቸው ይመስላል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ለምን እንደዚህ እንዳደረገ ለመረዳት ቢሞክሩና አምላክ የመደበላቸውን የሥራ ድርሻ ቢቀበሉ ይበልጥ ደስተኞች ይሆኑ ነበር። ስለ አምላክ ዝግጅት ቅር የሚሰኙ ሰዎች እንደ አሞራ ጉልበተኛ ባለመሆንዋ አኩርፋ ከጎጆዋ ወጥታ በተሰጣት ልዩ የመዘመር ችሎታ አምላክዋን ለማመስገን እምቢተኛ የሆነችን ድንቢጥ ይመስላሉ።
7. አዳም በሔዋንና በሚወለዱላቸው ልጆች ላይ ጥሩ የራስነት ሥልጣን ለማሳየት የሚያስችል ሁኔታ የነበረው ለምንድንነው? ይሁን እንጂ ይህ ሔዋንን የሚጎዳት ነበርን?
7 ሔዋን ከመፈጠርዋ በፊት አዳም ብዙ የኑሮ ተሞክሮ አግኝቶ እንደነበረ አይጠረጠርም። በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ ብዙ መመሪያዎችን ሰጥቶት ነበር። አዳም እነዚህን መመሪያዎች ለሚስቱ በማስተላለፍ የአምላክ ቃል አቀባይ መሆን ነበረበት። አምልኮትንና የሥራ ድርሻቸውን ለመፈጸም የሚያስችሏቸውን አምላካዊ እንቅስቃሴዎች በሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ አዳም ግንባር ቀደም መሆኑ ምክንያታዊ ነበር። ልጆች በሚወለዱበት ጊዜ ደግሞ የቤተሰቡ ራስ ይሆናል። ይሁን እንጂ የእርሱ ራስነት ሚስቱን የሚጎዳ አይሆንም። እንዲያውም አምላክ የሰጣትን ሥልጣን በልጆችዋ ላይ በምትጠቀምበት ጊዜ የሚደግፋትና የሚረዳት ስለሚኖር የሚጠቅማት ይሆናል።
8. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን መለኰታዊ የደረጃዎች ቅደም ተከተል ተገልጾአል?
8 በአምላክ የደረጃ ቅደም ተከተል መሰረት አዳም ተጠያቂነቱ ለይሖዋ ይሆናል። ሔዋን በአዳም ራስነት ሥር ስትተዳደር፣ ልጆቻቸው በወላጆቻቸው አመራር ሥር ይኖራሉ። እንስሳት ደግሞ ለሰው ልጆች ይገዛሉ። ወንድና ሴት የየራሳቸው የሥራ ድርሻ ሲኖራቸው ሁለቱም ደስተኛና ፍሬያማ ሕይወት ሊኖሩ ይችላሉ። በዚህ መንገድ ‘ሁሉ ነገር በአገባብና በሥርዓት ሊፈጸም እንደሚችል’ ሆኖ ተዘጋጀ።—1 ቆሮንቶስ 11:3፤ 14:33, 40 አዓት የግርጌ ማስታወሻ
ኃጢአት የሴቲቱን የሥራ ድርሻ ቅርጹን ለወጠው
9, 10. በኃጢአት መውደቃቸው በወንዱና በሴቲቱ ላይ ምን ውጤት አስከትሎአል? ይህስ በሴቲቱ ላይ ምን አምጥቶባታል?
9 ኃጢአትና አለፍጽምና ወደ መጀመሪያዋ ገነት ሰርጎ መግባቱ ይህንን ሥርዓታማ ዝግጅት አበላሸው። (ሮሜ 7:14-20) በአመጸኛው ወንድና ለመታዘዝ እምቢተኛ በሆነችው ሚስቱ ላይ መከራና ችግር አመጣባቸው። (ዘፍጥረት 3:16-19) ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ራስ ወዳድ የሆኑ ብዙ ወንዶች ተገቢውን የራስነት ሥልጣናቸው ለብዙ ዘመናት አለአግባብ ተጠቀሙበትና በሴቶች ላይ ብዙ ችግር አደረሱ።
10 ይሖዋም በተለይ ይህንን የኃጢአት ውጤት አስቀድሞ በመመልከት ለሔዋን “ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” አላት። (ዘፍጥረት 3:16) ይህ የጭቆና ገዥነት ከትክክለኛው የራስነት አስተዳደር የተለየ ነው። ይህም የወንድን የኃጢአተኝነት ሁኔታ ያንጸባርቃል፤ የሴትንም አለፍጽምና ያንጸባርቃል ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ሴቶች የባሎቻቸውን ሥልጣን ለመቀማት ሲሞክሩ ብዙ ስቃይ ደርሶባቸዋል።
11. ሴቶችን በተመለከተ ምን እውነተኛ ሁኔታ አለ? አንድ ጸሐፊ በጥንቶቹ አባቶች ዘመን ይኖሩ ስለነበሩ ሴቶች ምን ብሎአል?
11 ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሲሠራባቸው ብዙ ሴቶች ደስታና እርካታ አግኝተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተጠቀሱት የጥንቶቹ አባቶች ዘመን እንኳን ሳይቀር ይህ አባባል ሠርቷል። ሎር አይናርድ የተባሉ ፀሐፊ መጽሐፍ ቅዱስ በሴቴ ጾታ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ስለዚህ ዘመን እንዲህ ብለዋል፦ “በእነዚህ ትረካዎች ላይ ጐልቶ የሚታየው ነገር ሴቶች የነበራቸው ከፍተኛ የሥራ ድርሻ፣ በአበው ፊት የነበራቸው ከበሬታ፣ አዲስ ሐሳብ አመንጭተው ለመናገር የነበራቸው ድፍረት፣ በነጻነት አየር ውስጥ መኖራቸው ነው።”
በሙሴ ሕግ ሥር የነበሩ ሴቶች
12, 13. (ሀ) በሙሴ ሕግ ሥር የሴቶች ደረጃ ምን ነበር? (ለ) በሙሴ ሕግ ሥር ሴቶች በመንፈሳዊነታቸው ረገድ ምን ሁኔታ ነበራቸው?
12 አምላክ በሙሴ በኩል በሰጠው ሕግ መሰረት ሚስቶች እንደ ውድ ነገር ተቆጥረው በእንክብካቤ መያዝ ነበረባቸው። (ዘዳግም 13:6) በሩካቤ ሥጋ ጉዳዮችም የሚስቶች ክብር መጠበቅ ይገባው ነበር። ማንኛዋም ሴት በሩካቤ ሥጋ መደፈር አትችልም። (ዘሌዋውያን 18:8-19) ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ዝሙት ቢፈጽሙ ወይም ከቅርብ ዘመዳቸው ጋር ወይም ከእንስሳት ጋር ሩካቤ ሥጋ ቢፈጽሙ በሕጉ ፊት እኩል ተጠያቂነት ነበራቸው። (ዘሌዋውያን 18:6, 23፤ 20:10-12) አምስተኛው ትዕዛዝ ደግሞ አባትም ሆነ እናት በእኩልነት ደረጃ እንዲከበሩ ያዝዛል።—ዘጸአት 20:12
13 ከሁሉ በላይ ደግሞ ሴቶች መንፈሳዊነታቸውን እንዲያሳድጉና እንዲያዳብሩ የተሟላ እድል ተሰጥቷቸው ነበር። የሕጉ መጽሐፍ ሲነበብ ሰምተው ሊጠቀሙ ይችሉ ነበር። (ኢያሱ 8:35፤ ነህምያ 8:2, 3) በሃይማኖታዊ በዓሎች ላይ እንዲገኙ ይፈለግባቸው ነበር። (ዘዳግም 12:12, 18፤ 16:11, 14) ሳምንታዊውን ሰንበት በማክበሩ ላይ ተካፋይ ነበሩ፤ የናዝራዊነት ስእለት ሊሳሉ ይችሉ ነበር። (ዘጸአት 20:8፤ ዘኁልቅ 6:2) ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና ነበራቸው። በየግላቸውም ወደ እርሱ መጸለይ ይችሉ ነበር።—1 ሳሙኤል 1:10
14. አንድ ካቶሊካዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ ስለ ዕብራውያን ሴቶች ምን ብሎአል? ሴቶች በሙሴ ሕግ ውስጥ ስለነበራቸው የሥራ ድርሻ ምን ሊባል ይችላል?
14 ካቶሊካዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ የሆኑት ሮላንድ ደ ቮ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል፦ “በቤት ውስጥ ያለው ከባድ ሥራ ሁሉ በሴቲቱ ትከሻ ላይ ወድቆ ነበር። ለከብቶች አስፈላጊው እንክብካቤ መደረጉን ትከታተላለች፣ በእርሻ ቦታ ትሰራለች፣ ምግብ ታዘጋጃለች፤ ትፈትላለች። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የሥራ ጭነት ዝቅተኛ ደረጃ የሚያሰጣት ሳይሆን የሚያስከብራት ነበር። . . . ስለ ቤተሰብ ሕይወት የሚገልጹት ጥቂት አንቀጾች አንዲት እስራኤላዊት ሚስት በባልዋ ትወደድና ትደመጥ እንዲሁም እንደ እኩያው ተደርጋ ትታይ እንደነበረ ያመለክታሉ። . . . አጠቃላዩ ሁኔታ እንደዚህ እንደነበረ አያጠራጥርም። በዘፍጥረት ውስጥ የተቀረጸውን ትምህርት በታማኝነት የሚያንጸባርቅ አኗኗር ነበር። አምላክ በዘፍጥረት ውስጥ ሴት የወንድ ረዳት ባልንጀራ እንድትሆን እንደፈጠራትና ወንዱም ከእርስዋ ጋር መጣበቅ እንደሚኖርበት ይገልጻል። (ዘፍጥረት 2:18, 24) የመጨረሻው የምሳሌ መጽሐፍ ደግሞ ለጥሩ ሚስት የሚቀርበውን የውዳሴ መዝሙር ይገልጽልናል። ልጆችዋ ይባርኩአታል፣ ባልዋም ይኮራባታል። (ምሳሌ 31:10-31)” (የጥንትዋ እስራኤል አኗኗርና ድርጅቶች) እስራኤላውያን ሕጉን ይከተሉ በነበረበት ጊዜ ሁሉ በሴቶች ላይ በደል ይፈጸም እንዳልነበረ አያጠያይቅም።
ጐልተው የሚታዩ ሴቶች
15. (ሀ) የሣራ ጠባይ በወንድና በሴት መካከል ሊኖር ለሚችለው ትክክለኛ ግንኙነት ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው? (ለ) የረዓብ ሁኔታ ሊጠቀስ የሚገባው ለምንድን ነው?
15 የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጐልተው የሚታዩ ሴት የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች እንደነበሩ የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎችን ይጠቅሱልናል። ሣራ አንዲት አምላክን የምትፈራ ሴት ለባልዋ ተገዥ እየሆነች እንዴት ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ ልትረዳው እንደምትችል ለማስረዳት ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች። (ዘፍጥረት 21:9-13፤ 1 ጴጥሮስ 3:5, 6) የረዓብም ምሳሌነት ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ይሖዋ በዘር ያዳላል፣ ሴቶችንም ይበድላል የሚለው ክስ ሐሰት መሆኑን ያረጋግጣል። ረዓብ እስራኤላዊት ያልሆነች ጋለሞታ ነበረች። ይሖዋ አምላኪው እንድትሆን ከመቀበሉም በላይ አኗኗርዋን መለወጥን በሚጨምረው በሥራ በተገለጸው ከፍተኛ እምነትዋ ምክንያት እንደ ጻድቅ ቆጥሯታል። ከዚህም በተጨማሪ የመሢሑ ቅድመ አያት የመሆን መብት ሰጥቶአታል።—ማቴዎስ 1:1, 5፤ ዕብራውያን 11:31፤ ያዕቆብ 2:25
16. የአቢጋኤል ምሳሌ ምን ነገር ያስረዳናል? የወሰደችው እርምጃ ትክክል የሆነው ለምንድንነው?
16 አንዲት ሚስት ባልዋን በጭፍን እንድትታዘዝ ይሖዋ የማይፈልግባት መሆኑን ከአቢጋኤል ታሪክ ለመረዳት እንችላለን። የአቢጋኤል ባል ብዙ በጎችና ፍየሎች የነበሩት ሀብታም ሰው ነበር። ነገር ግን “ባለጌ ነበረ፣ ግብሩም ክፉ ነበረ።” አቢጋኤል ከባልዋ ጋር በክፉ አድራጎቱ ለመተባበር ፈቃደኛ አልሆነችም። አስተዋይነትዋን፣ ቀና አስተሳሰብዋን፣ ትህትናዋንና ፈጣንነቷን የሚያሳይ እርምጃ በመውሰዷ በቤትዋ ላይ ከባድ ችግር ሊያስከትል ይችል የነበረውን ሁኔታ አስወገደች። ይሖዋም ለዚህ አድራጎትዋ አብዝቶ ባረካት።—1 ሳሙኤል 25:2-42
17. (ሀ) አንዳንድ እስራኤላውያን ሴቶች ምን የላቀ መብት አግኝተዋል? (ለ) በሚርያም ላይ የታየው ሁኔታ የአገልግሎት መብት ላገኙ ክርስቲያን ሴቶች እንዴት ያለ ትምህርት ሊሰጣቸው ይችላል?
17 አንዳንድ ሴቶች ደግሞ ነቢያት ነበሩ። ከእነዚህም አንዷ በመሳፍንት ዘመን ትኖር የነበረችው ዲቦራ ነች። (መሳፍንት ምዕራፍ 4 እና 5) የኢየሩሳሌም መጥፊያ በደረሰበት ጊዜ ህልዳና በይሁዳ ምድር ነቢይት ነበረች። (2 ነገሥት 22:14-20) ሚርያምም መጠቀስ የሚገባት ሴት ነች። በይሖዋ የተላከች ነቢይት እንደሆነች ቢነገርም ይህ መብትዋ አንድ ወቅት ላይ አስታብዮአት ነበር። ይሖዋ ለታናሽ ወንድምዋ ለሙሴ እስራኤላውያንን እንዲመራ ሰጥቶት የነበረውን መብት መቀበል ተሳናት። በዚህ አድራጎትዋ ተጸጽታ ይቅርታ ብታገኝም እንኳን ተገቢውን ቅጣት አግኝታበታለች።—ዘጸአት 15:20, 21፤ ዘኁልቅ 12:1-15፤ ሚክያስ 6:4
የይሁዲነት ሃይማኖት ከመጣ በኋላ የሴቶች ሁኔታ
18, 19. በይሁዲነት ሃይማኖት ሴቶች እንዴት ያለ ደረጃ ነበራቸው? ይህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ?
18 ቀደም ስንል እንደተመለከትነው የሙሴ ሕግ የሴቶችን መብት ያስጠብቅና በትክክል ሲሠራበት ሴቶች የሚያረካ ሕይወት እንዲኖሩ ያስችል ነበር። ይሁን እንጂ ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ፣ በተለይም ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከጠፋች በኋላ በተጻፈው የይሖዋ ሕግ ላይ ሳይሆን ይበልጡን በአፈ ታሪክና በወግ ላይ የተመሰረተ የይሁዲነት ሃይማኖት መስፋፋት ጀመረ። ከአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ወዲህ የአይሁድ እምነት ብዙ የግሪክ ፍልስፍናዎችን ወረሰ። የግሪክ ፈላስፎች በአብዛኛው ለሴቶች መብት ትኩረት አይሰጡም ነበር። በዚህም ምክንያት በአይሁድ የይሁዲነት ሃይማኖት ከመጣ በኋላ ሴቶች የነበራቸው ደረጃና ከበሬታ ዝቅ እያለ ሄደ። ከሶስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ጀምሮ በአይሁዳውያን ምኩራብ ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ተለያይተው መቀመጥ ጀመሩ። ሴቶች የሕጉን መጽሐፍ እንዳያነቡ መከልከል ጀመሩ። ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ጁዳይካ ሳይሸሽግ እንደገለጸው “በዚህ ምክንያት የተማሩ ሴቶች ቁጥር በጣም አነስተኛ ሆነ።” ትምህርት መስጠት ለወንድ ልጆች ብቻ የተወሰነ ሆነ።
19 ጄ ጀርምያስ ኢየሩሳሌም በኢየሱስ ዘመን በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል፦ “‘ሴቶች፣ (አሕዛብ) ባሮችና ሕጻናት’ የሚለው የተለመደ አነጋገር በሃይማኖታዊ ሕግ ውስጥ ሴቶች በአጠቃላይ የነበራቸውን ደረጃ ያሳያል። . . . በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ ስለ ሴቶች ይሰነዘሩ የነበሩ አስጸያፊ አስተያየቶችን መጨመር ይቻላል። . . . ስለዚህ በኢየሱስ ዘመን የነበረው የይሁዲነት ሃይማኖት ስለሴቶች በጣም ዝቅተኛ የሆነ አስተያየት እንደነበረው መገንዘብ እንችላለን።”
መሲሑን ይጠብቁ የነበሩ ታማኝ ሴቶች
20, 21. (ሀ) አይሁዳውያን የሃይማኖት መሪዎች ሴቶችን አቃልለው የሚመለከቱ ቢሆንም መሲሑ የሚመጣበት ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ እንዴት ያሉ ሴቶች ተገኝተዋል? (ለ) ኤልሳቤጥና ማርያም በከፍተኛ ሁኔታ ለአምላክ ያደሩ ሴቶች እንደነበሩ እንዴት ለማወቅ እንችላለን?
20 የአይሁድ መምህራን ‘ስለ ወጋቸው የአምላክን ቃል ከንቱ’ ካደረጉባቸው መንገዶች አንዱ ይህ ሴቶችን የማዋረድና የማቃለል ዝንባሌ ነበር። (ማርቆስ 7:13) ይሁን እንጂ ይህን የመሰለ ሴቶችን የማንቋሸሽ ዝንባሌ ቢኖርም የመሲሑ መምጫ ሲደርስ አምላክን የሚፈሩ አንዳንድ ሴቶች ነቅተው ይጠብቁ ነበር። ከእነዚህም አንዷ የሌዋዊው ካህን የዘካርያስ ሚስት ኤልሳቤጥ ነበረች። ኤልሳቤጥና ባልዋ “[በይሖዋ (አዓት)] ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ።” (ሉቃስ 1:5, 6) ኤልሳቤጥ ለዚህ አድራጎትዋ ከይሖዋ ዘንድ በረከት አግኝታበታለች። መካንና በዕድሜ የገፋች ሴት ብትሆንም የአጥማቂው ዮሐንስ እናት ልትሆን ችላለች።—ሉቃስ 1:7, 13
21 ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ግፊት በዘመንዋ ትኖር ለነበረችው ማርያም የተባለች አምላክን የምትፈራ ዘመድዋ የጠለቀ ፍቅር እንዳላት አሳየች። 3 ከዘአበ ሊፈጸም በተቃረበበት ጊዜ መልአኩ ገብርኤል በተአምር ሕጻን እንደምትጸንስ ሲያበስራት “እጅግ የታደልሽ ሆይ፣ ይሖዋ ከአንቺ ጋር ነው” ብሎአታል። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ማርያም ኤልሳቤጥን ልትጠይቃት ሄደችና ኤልሳቤጥ እርስዋንም ሆነ ያረገዘችውን ሕጻን ባረከች። ኢየሱስ ገና ሳይወለድ “ጌታ” ብላ ጠራችው። በዚህ ጊዜ ማርያም ለአምላክ ያደረች ሴት እንደነበረች የሚመሰክርላት የውዳሴ ቃል ተናግራለች።—ሉቃስ 1:28, 31, 36-55
22. ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ መሲሑን ከሚጠባበቁት አምላክን የሚፈሩ ሴቶች መካከል አንዷ ሆና የተገኘችው ማን ነች?
22 ኢየሱስ ከተወለደና ማርያም በይሖዋ ፊት ልታቀርበው ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ካመጣችው በኋላ ሐና የተባለች አረጋዊት ነቢይት ደስታዋን ገልጻለች። ለይሖዋ የውዳሴና የምሥጋና ቃል ካሰማች በኋላ የመሲሑን መምጣት በጉጉት ይጠባበቁ ለነበሩ ሰዎች ሁሉ ስለ ኢየሱስ ተናገረች።—ሉቃስ 2:36-38
23. ሐዋርያው ጴጥሮስ ከክርስትና በፊት ስለነበሩ ታማኝ ሴቶች ምን ተናግሮአል? በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት የትኞቹ ጥያቄዎች ይመረመራሉ?
23 ስለዚህ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን የሚጀምርበት ጊዜ እየተቃረበ በመጣበት ጊዜ “በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉ ቅዱሳን ሴቶች” ነበሩ። (1 ጴጥሮስ 3:5) ከእነዚህም ሴቶች አንዳንዶቹ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ሆነዋል። ኢየሱስ እነዚህን ሴቶች እንዴት ይመለከታቸው ነበር? ዛሬስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የሥራ ድርሻ በደስታ ተቀብለው የሚኖሩ ሴቶች ይኖሩ ይሆንን? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ይመረምራሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ጥራዝ 3፣ ገጽ 1055
b “የኋለኛው አዳም” ኢየሱስ ክርስቶስም ሰብዓዊ ሚስት ያልነበረው ቢሆንም ፍጹምና ሙሉ ሰው ነበር።—1 ቆሮንቶስ 15:45
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ የእስራኤላውያን ሴቶች የሚያዙበት ሁኔታ በሌሎች አገሮች ከነበረው የሴቶች አያያዝ በጣም የሚለየው እንዴት ነው?
◻ አዳምና ሔዋን የነበራቸው ደረጃ እንዴት ያለ ነበር? ለምንስ?
◻ በሙሴ ሕግ ሥር ሴቶች ምን ደረጃ ነበራቸው? መንፈሳዊ ጉዳት ይደርስባቸው ነበርን?
◻ በዕብራውያን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ጐልተው ከሚታዩት ሴቶች አኗኗር ምን ትምህርት ሊገኝ ይችላል?
◻ የይሁዲነት ሃይማኖት አመለካከት እንደዚያ ሆኖ እያለ ምን የጥሩ እምነት ምሳሌዎች ታይተዋል?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ይሖዋን የምትፈራ ሴት”
“10 ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቍ እጅግ ይበልጣል። 11 የባልዋ ልብ ይታመንባታል፣ ምርኮም አይጐድልበትም። 12 ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች፣ ክፉም አታደርግም። 13 የበግ ጠጉርና የተልባ እግር ትፈልጋለች፣ በእጆችዋም ደስ ብሎአት ትሠራለች። 14 እርስዋ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፤ ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች። 15 ገና ሌሊት ሳለ ትነሣለች ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን፣ ለገረዶችዋም ተግባራቸውን ትሰጣለች። 16 እርሻንም ተመልክታ ትገዛለች፤ ከእጅዋም ፍሬ ወይን ትተክላለች። 17 ወገብዋን በኃይል ትታጠቃለች፣ ክንድዋንም ታበረታለች። 18 ንግድዋ መልካም እንደ ሆነ ትመለከታለች፤ መብራትዋ በሌሊት አይጠፋም። 19 እጅዋን ወደ አመልማሎ ትዘረጋለች፣ ጣቶችዋም እንዝርትን ይይዛሉ። 20 እጅዋን ወደ ድሀ ትዘረጋለች፣ ወደ ችግረኛም እጅዋን ትሰድዳለች። 21 ለቤትዋ ሰዎች ከበረዶ ብርድ የተነሣ አትፈራም፣ የቤትዋ ሰዎች ሁሉ እጥፍ ድርብ የለበሱ ናቸውና። 22 ለራስዋም ግብረ መርፌ ስጋጃ ትሠራለች፤ ጥሩ በፍታና ቀይ ግምጃ ትለብሳለች። 23 ባልዋ በአገር ሽማግሌዎች መካከል በሸንጎ በተቀመጠ ጊዜ በበር የታወቀ ይሆናል። 24 የበፍታ ቀሚስ እየሠራች ትሸጣለች፣ ለነጋዴም ድግ ትሸጣለች። 25 ብርታትና ከበሬታ ልብስዋ ነው፤ በኋላም ዘመን ላይ ትስቃለች። 26 አፍዋን በጥበብ ትከፍታለች፤ የርኅራኄም ሕግ በምላስዋ አለ። 27 የቤትዋን ሰዎች አካሄድ በደኅና ትመለከታለች፣ የሀኬትንም እንጀራ አትበላም። 28 ልጆችዋ ይነሣሉ፣ ምስጋናዋንም ይናገራሉ፤ ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል። 29 መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፣ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ። 30 ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ [ይሖዋን (አዓት)] የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። 31 ከእጅዋ ፍሬ ስጡአት፣ ሥራዎችዋም በሸንጎ ያመስግኑአት።—ምሳሌ 31:10-31
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቤተሰብ ኑሮ ውስጥ ሴት ክቡር ቦታ ነበራት