በእምነታቸው ምሰሏቸው
“ቢሞትም እንኳ . . . አሁንም ይናገራል”
አቤል ኮረብታው ላይ ተረጋግተው የሚግጡትን በጎቹን እየተመለከተ ነው። በጎቹ ካሉበት ወደ ማዶ አሻግሮ ሲመለከት ደግሞ አንድ የሚያብረቀርቅ ነገር በርቀት ይታየዋል። እዚያ ቦታ ላይ ያለችው ሁልጊዜ የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ ማንም ወደ ኤደን ገነት እንዳይገባ የምታግድ መሆኗን አቤል ያውቃል። ወላጆቹ በአንድ ወቅት በኤደን ገነት ይኖሩ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው ወደዚህ ቦታ መግባት አይችሉም። አቤል ዓይኖቹን ከዚያ መለስ በማድረግ ቀና ብሎ ሰማይ ሰማዩን እያየ ስለ ፈጣሪው ማሰብ ጀመረ፤ ወደ ላይ አንጋጥጦ በሚያሰላስልበት ወቅት አመሻሹ ላይ ያለው ነፋሻማ አየር ፀጉሩን ሲያመሳቅለው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። በሰው ልጆችና በአምላክ መካከል የተፈጠረው ክፍተት ይጠገን ይሆን? አቤል ከዚህ ይበልጥ የሚመኘው ነገር የለም።
በዛሬው ጊዜ አቤል እያናገረህ ነው፤ ድምፁ ይሰማሃል? ይህ ፈጽሞ የማይመስል ነገር እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ‘የአዳም ሁለተኛ ልጅ የሆነው አቤል ከሞተ ዘመናት ተቆጥረው የለ እንዴ?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። አካሉ ከአፈር ከተቀላቀለ ወደ 6,000 የሚጠጉ ዓመታት በማለፋቸው አፅሙን እንኳ ማግኘት አይቻልም። በዚያ ላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን . . . ምንም አያውቁም” ይላል። (መክብብ 9:5, 10) ከዚህም ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኝ አቤል የተናገረው አንድም ነገር የለም። ታዲያ አቤል እንዴት ሊያናግረን ይችላል?
ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ስለ አቤል ሲናገር “ቢሞትም እንኳ በእምነቱ አማካኝነት አሁንም ይናገራል” ብሏል። (ዕብራውያን 11:4) ግሩም የሆነውን ይህን ባሕርይ ይኸውም እምነትን ያዳበረው የመጀመሪያው ሰው አቤል ነው። አቤል እጅግ ታላቅ እምነት በማሳየት ሕያው ምሳሌ ትቶልናል፤ የእሱን አርዓያ ዛሬም ልንከተል እንችላለን። ከእሱ እምነት ትምህርት የምንወስድና ምሳሌውን የምንከተል ከሆነ ስለ አቤል የሚገልጸው ዘገባ ልክ ድምፁን የምንሰማው ያህል ሊያናግረን ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አቤል ብዙ ባይናገርም ስለ እሱና ስለ እምነቱ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? እስቲ ታሪኩን እያየን እንሂድ።
የሰው ልጆች የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተበት ወቅት
አቤል የተወለደው በሰው ልጆች ታሪክ መባቻ ላይ ነው። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ፣ አቤልን “ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ” ጋር አያይዞ ጠቅሶታል። (ሉቃስ 11:50, 51) ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ዓለም፣ በቤዛው አማካኝነት ከኃጢአት ነፃ የመውጣት ተስፋ ያላቸው የሰው ልጆችን የሚያመለክት መሆን አለበት። አቤል በምድር ላይ ወደ ሕልውና ከመጡት ሰዎች አራተኛው ቢሆንም ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ከኃጢአት ነፃ መውጣት እንደሚችል አድርጎ የተመለከተው የመጀመሪያው ሰው እሱ ይመስላል።a አቤል ልጅ በነበረበት ወቅት በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት የሚችል ሰው እንዳልነበረ ግልጽ ነው።
የሰው ልጆች ታሪክ ሀ ብሎ መጀመሩ ቢሆንም እንኳ የሰው ዘር ቤተሰብ የሐዘን ድባብ አጥልቶበት ነበር። የአቤል ወላጆች የሆኑት አዳምና ሔዋን ውብ ቁመናና ብሩሕ አእምሮ ያላቸው ሰዎች እንደሚሆኑ ግልጽ ነው። ይሁንና በሕይወታቸው ውስጥ ከባድ ስህተት እንደፈጸሙ ያውቁ ነበር። በአንድ ወቅት ፍጹማን የነበሩ ከመሆኑም ሌላ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ተዘርግቶላቸው ነበር። በይሖዋ አምላክ ላይ ሲያምፁ ግን መኖሪያቸው ከነበረችው ከኤደን ገነት ተባረሩ። አዳምና ሔዋን ከማንኛውም ነገር ሌላው ቀርቶ ከአብራካቸው ከሚወጡት ልጆች እንኳ በላይ የራሳቸውን ፍላጎት በማስቀደማቸው ፍጽምና እና ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ አጡ።—ዘፍጥረት 2:15 እስከ 3:24
አዳምና ሔዋን ከገነት ውጭ እንዲኖሩ ስለተፈረደባቸው ሕይወት ከብዷቸው ነበር። ይሁንና የመጀመሪያ ልጃቸውን ሲወልዱ ስሙን ቃየን አሉት፤ ቃየን ማለት “አንድ ነገር ማፍራት” ማለት ሲሆን ሔዋን ቃየንን ስትወልድ “በእግዚአብሔር ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” ብላ ነበር። ሔዋን ይህን ስትናገር ይሖዋ በገነት ውስጥ የገባውን ቃል አስባ ሊሆን ይችላል፤ ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋንን ወደ ጥፋት የመራቸውን ክፉ አካል የሚያጠፋ ‘ዘር’ ስለምታስገኝ ሴት ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 3:15፤ 4:1) ሔዋን፣ በትንቢቱ ላይ የተጠቀሰችው ሴት እሷ እንደሆነችና ተስፋ የተሰጠበት ‘ዘር’ ደግሞ ቃየን እንደሆነ አስባ ይሆን?
ከሆነ በጣም ተሳስታለች። እሷና አዳም፣ ቃየንን ሲያሳድጉ እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን ነግረውት ከሆነ ይህ፣ ልጃቸው ፍጽምና የጎደለው መሆኑ ከሚያሳድርበት ተጽዕኖ ጋር ተዳምሮ ትዕቢተኛ እንዲሆን አድርጎት መሆን አለበት። ከጊዜ በኋላ ሔዋን ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ይሁንና ከእሱ ጋር በተያያዘ ለቃየን እንደተናገረችው ያለ የኩራት ሐሳብ አልተናገረችም። ሁለተኛ ልጃቸውን አቤል ብለው የሰየሙት ሲሆን ትርጉሙም “ተን” ወይም “ባዶ” ማለት ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 4:2) ልጃቸውን እንዲህ ብለው መሰየማቸው የቃየንን ያህል ከአቤል ትልቅ ነገር እንደማይጠብቁ የሚጠቁም ይሆን? በእርግጠኝነት መናገር አንችልም።
ያም ሆነ ይህ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ወላጆች ከመጀመሪያዎቹ ወላጆች ብዙ ሊማሩ የሚችሉት ነገር አለ። እናንት ወላጆች፣ የምትናገሩት ወይም የምታደርጉት ነገር ልጆቻችሁ ኩራተኞች፣ ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት የሚመኙ ወይም ራስ ወዳዶች እንዲሆኑ የሚያነሳሳ ነው? ወይስ ይሖዋ አምላክን እንዲወዱና ከእሱ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ታሠለጥኗቸዋላችሁ? የሚያሳዝነው ነገር የመጀመሪያዎቹ ወላጆች ይህን ኃላፊነታቸውን አልተወጡም። ያም ቢሆን ግን ልጃቸው የእነሱን አካሄድ አልተከተለም።
አቤል እምነት ማዳበር የቻለው እንዴት ነው?
ሁለቱ ወንዶች ልጆች እያደጉ ሲሄዱ አዳም፣ ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማቅረብ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ሳያሠለጥናቸው አልቀረም። ቃየን ገበሬ ሲሆን አቤል ደግሞ በግ ጠባቂ ሆነ።
አቤል ግን ከዚህ ሥራው የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር አድርጓል። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ የጠቀሰውን ግሩም ባሕርይ ይኸውም እምነትን በጊዜ ሂደት አዳብሯል። እስቲ አስበው። ለአቤል ጥሩ ምሳሌ ሊሆንለት የሚችል ሰው አልነበረም። ታዲያ በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት ማዳበር የቻለው እንዴት ነው? አቤል ጠንካራ እምነት እንዲያዳብር መሠረት ሊሆኑለት የሚችሉ ሦስት ነገሮችን እንመልከት።
የይሖዋ የፍጥረት ሥራ፦
እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ምድሪቱን ስለረገማት እሾኽና አሜከላ ታበቅል ነበር፤ ይህም ለግብርናው ሥራ እንቅፋት መፍጠሩ አልቀረም። ያም ቢሆን ምድር ለአቤል ቤተሰብ የሚያስፈልገውን አትረፍርፋ ትሰጣቸው ነበር። ከዚህም ሌላ አእዋፍንና ዓሦችን ጨምሮ እንስሳት፣ ተራሮች፣ ሐይቆች፣ ወንዞችና ባሕሮች እንዲሁም ሰማያት፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ እና ከዋክብት አልተረገሙም። አቤል ዓይኑ በሚያርፍበት ቦታ ሁሉ፣ ነገሮችን በሙሉ የፈጠረውን የይሖዋ አምላክን ጥልቅ ፍቅር፣ ጥበብና ለጋስነት መመልከት ይችል ነበር። (ሮም 1:20) በእነዚህ የፍጥረት ሥራዎች ላይ በአድናቆት ማሰላሰሉ እምነቱ እንዲጠናከር አስተዋጽኦ አድርጓል።
አቤል ጊዜ ወስዶ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያሰላስል እንደነበረ ጥርጥር የለውም። አቤል መንጋውን ሲንከባከብ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አንድ እረኛ ሥራውን ለማከናወን ብዙ መጓዝ ነበረበት። ለእነዚህ ገራም ፍጥረታት ለምለም ሣር፣ ምርጥ የውኃ ጉድጓድ እንዲሁም ከሁሉ የተሻለ መጠለያ ያለው ማረፊያ ቦታ ለማግኘት ሲል ኮረብቶችን እየወጣና እየወረደ፣ ሸለቆዎችን እያቋረጠና ወንዞችን እየተሻገረ ይጓዝ ነበር። ከአምላክ ፍጥረታት ሁሉ በጎች በቀላሉ ሊጠቁ ስለሚችሉ የሰው ልጅ እንዲመራቸውና ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ታስበው የተፈጠሩ ይመስላሉ። አቤል፣ እሱም ቢሆን ከማንኛውም ሰው በላይ ጥበበኛና ኃያል ከሆነ አካል አመራር፣ ጥበቃና እንክብካቤ ማግኘት እንደሚያስፈልገው አስተውሎ ይሆን? አቤል በዚህ ረገድ ስሜቱን በጸሎት ይገልጽ እንደነበረና ይህም እምነቱን እንዳጠናከረለት ጥርጥር የለውም።
አቤል የፍጥረት ሥራዎችን መመልከቱ አፍቃሪ በሆነው ፈጣሪው ላይ እምነት ለማዳበር ጠንካራ መሠረት ሆኖለታል
ይሖዋ የተናገራቸው ነገሮች፦
አዳምና ሔዋን ከኤደን ገነት እንዲባረሩ ያደረጓቸውን ሁኔታዎች ለልጆቻቸው ሳይተርኩላቸው አይቀሩም። በመሆኑም አቤል የሚያሰላስልባቸው በርካታ ነገሮች ነበሩ።
ይሖዋ ምድሪቱ የተረገመች እንደምትሆን ተናግሮ ነበር። አቤል በምድሪቱ ላይ የበቀለውን እሾኽና አሜከላ ሲመለከት አምላክ የተናገረው ነገር እንደተፈጸመ በግልጽ ማየት ችሏል። ይሖዋ፣ ሔዋን በእርግዝናዋና ልጆች በምትወልድበት ወቅት ሥቃይ እንደሚኖራትም አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። አቤል ታናናሾቹ ሲወለዱ የዚህን ቃል ፍጻሜ ተመልክቶ መሆን አለበት። ሔዋን የባሏን ፍቅርና ትኩረት ከሚገባው በላይ እንደምትፈልግና እሱም የበላይዋ እንደሚሆን ይሖዋ ተናግሮ ነበር። አቤል ይህንን አሳዛኝ እውነታ በገዛ ዓይኑ ተመልክቷል። አቤል፣ ይሖዋ የተናገረው ሁሉ መፈጸሙ እንደማይቀር ማስተዋል ይችል ነበር። በመሆኑም አቤል፣ በኤደን የተፈጸመው ኃጢአት ያስከተላቸውን ጉዳቶች የሚያስተካክል ‘ዘር’ እንደሚመጣ አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት ለመጣል የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበረው።—ዘፍጥረት 3:15-19
የይሖዋ አገልጋዮች፦
በወቅቱ ከነበሩት የሰው ልጆች መካከል ለአቤል ጥሩ ምሳሌ ሊሆነው የሚችል ሰው አልነበረም፤ ይሁንና በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የነበሩት የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት የሰው ልጆች ብቻ አይደሉም። አዳምና ሔዋን ከኤደን ሲባረሩ ይሖዋ እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው ወደ ገነት መግባት እንዳይችሉ አገዳቸው። ይሖዋ የኤደንን መግቢያ እንዲጠብቁ ኪሩቤል የተባሉ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው መላእክትን ዘብ አቁሞ ነበር፤ በተጨማሪም በኤደን መግቢያ ላይ ያለማቋረጥ የሚገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ ነበር።—ዘፍጥረት 3:24
አቤል ልጅ እያለ እነዚያን መላእክት ሲመለከት ምን እንደሚሰማው አስብ። ኪሩቤል የሰው አካል ለብሰው ስለነበር ምን ያህል ኃያል እንደሆኑ አቤል ከቁመናቸው ማስተዋል ይችል ነበር። በእሳት እየተንቦገቦገ ያለማቋረጥ በሚገለባበጠው ‘ሰይፍም’ ተደምሞ መሆን አለበት። አቤል ልጅ እያለ መላእክቱ ሥራቸው ሰልችቷቸው የተመደቡበትን ቦታ ትተው ሲዘናጉ ተመልክቶ ይሆን? በፍጹም። እነዚህ ማሰብ የሚችሉ ኃያላን ፍጥረታት ቀንና ሌሊት፣ ዓመታት እንዲሁም ዘመናት ቢያልፉም ከቦታቸው ንቅንቅ አላሉም። በመሆኑም አቤል ይሖዋ አምላክ ጻድቅና ታማኝ የሆኑ አገልጋዮች እንዳሉት መገንዘብ ይችል ነበር። የእሱ ቤተሰብ ለይሖዋ ታማኝና ታዛዥ ባይሆኑም መላእክቱ እነዚህ ባሕርያት እንዳሏቸው ማየት ችሏል። የኪሩቤል ምሳሌነት የአቤልን እምነት እንዳጠናከረለት ጥርጥር የለውም።
አቤል፣ በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ በተንጸባረቁት የአምላክ ባሕርያት፣ በተናገራቸው ነገሮች ፍጻሜ እንዲሁም አገልጋዮቹ በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰሉ እምነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጠናከር አድርጓል። በእርግጥም አቤል በተወው ምሳሌ አማካኝነት ዛሬም ይናገራል ማለት ይቻላል። በተለይም ወጣቶች፣ የቤተሰባቸው አባላት ምንም አደረጉ ምን በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት ማሳደር እንደሚችሉ ከአቤል ምሳሌ መገንዘባቸው ያበረታታቸዋል። አስደናቂ የሆኑ የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች፣ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም በእምነታቸው ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ሰዎች ስላሉ በዛሬው ጊዜም እምነት ለማዳበር የሚያስችል በቂ መሠረት አለን።
የአቤል መሥዋዕት የበለጠ የሆነው ለምንድን ነው?
አቤል በይሖዋ ላይ ያለው እምነት እያደገ ሲሄድ እምነቱን በተግባር ማሳየት ፈለገ። ይሁንና አንድ ተራ ሰው ለጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ምን መስጠት ይችላል? አምላክ የሰው ልጆች የሚያቀርቡት ስጦታ ወይም የእነሱ እርዳታ እንደማያስፈልገው ጥያቄ የለውም። ውሎ አድሮ አቤል ትልቅ ትርጉም ያለው አንድ እውነታ ተገነዘበ፦ በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ተነሳስቶ፣ ካለው ነገር ምርጡን ለይሖዋ እስካቀረበ ድረስ በሰማይ የሚገኘው አፍቃሪ አባቱ በስጦታው ይደሰታል።
በመሆኑም አቤል ከመንጋው መካከል በጎችን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ወሰነ። ምርጥ የሆኑትንና መጀመሪያ የተወለዱትን ከወሰደ በኋላ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ያሰበውን ሥጋ ለአምላክ አቀረበ። ቃየንም በበኩሉ የአምላክን በረከትና ሞገስ ማግኘት ስለፈለገ ካመረተው እህል መሥዋዕት ለማቅረብ ወሰነ። የልቡ ዝንባሌ ግን እንደ አቤል አልነበረም። ሁለቱ ወንድማማቾች መሥዋዕታቸውን ባቀረቡበት ወቅት የተፈጸመው ነገር የተለያየ የልብ ዝንባሌ እንዳላቸው በግልጽ አሳይቷል።
ሁለቱም የአዳም ልጆች መሥዋዕታቸውን ለማቅረብ መሠዊያ ሠርተው እንዲሁም እሳት አንድደው ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም መሠዊያቸውን የሠሩት በወቅቱ በምድር ላይ ይሖዋን የሚወክሉት ብቸኛ ፍጥረታት ማለትም መላእክት ካሉበት ብዙም ሳይርቁ ሊሆን ይችላል። ይሖዋም ያደረጉትን ጥረት ተመልክቷል። ጥቅሱ “እግዚአብሔርም በአቤልና በመሥዋዕቱ ደስ አለው” ይላል። (ዘፍጥረት 4:4 የ1980 ትርጉም) አምላክ በመሥዋዕቱ መደሰቱን እንዴት እንዳሳየ ዘገባው አይናገርም። ይሁንና የአቤል መሥዋዕት ተቀባይነት ያገኘው ለምንድን ነው?
አምላክን ያስደሰተው አቤል ያቀረበው መሥዋዕት ዓይነት ነው? አቤል ሕይወት ያለው ነገር ያቀረበ ሲሆን ውድ የሆነውን ደም ለይሖዋ አፍስሷል። አቤል እንዲህ ዓይነቱ መሥዋዕት ወደፊት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ተደርጎ እንደሚታይ ተገንዝቦ ይሆን? አቤል ከሞተ ከበርካታ ዘመናት በኋላ አምላክ እንከን የሌለበትን በግ መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ ሕዝቡን አዝዞ ነበር፤ ይህንንም ያደረገው “የአምላክ በግ” ተብሎ የተጠራውና ፍጹም ሰው የሆነው ልጁ ኃጢአት የሌለበትን ደሙን እንደሚያፈስስ ለማመልከት ነበር። (ዮሐንስ 1:29፤ ዘፀአት 12:5-7) ይሁንና አቤል ይህን ሁሉ ማወቅ ወይም መረዳት የሚችልበት መንገድ የነበረ አይመስልም።
በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር አቤል ካለው ነገር ምርጡን ማቅረቡን ነው። ይሖዋ የተደሰተው በመሥዋዕቱ ብቻ ሳይሆን በአቤልም ጭምር ነው። አቤል መሥዋዕቱን እንዲያቀርብ ያነሳሳው ለይሖዋ ያለው ፍቅርና በእሱ ላይ ያለው እምነት ነው።
ከቃየን ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው የተለየ ነበር። ይሖዋ “በቃየንና በመሥዋዕቱ . . . አልተደሰተም።” (ዘፍጥረት 4:5) ይሖዋ በቃየን መሥዋዕት ያልተደሰተው ያቀረበው መሥዋዕት በራሱ የተሳሳተ በመሆኑ አይደለም፤ ምክንያቱም አምላክ ከጊዜ በኋላ በሰጠው ሕግ ላይ ሕዝቡ የምድርን ፍሬ መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ ፈቅዷል። (ዘሌዋውያን 6:14, 15) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቃየን ሲናገር ‘ሥራው ክፉ እንደነበረ’ ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 3:12) በዛሬው ጊዜ እንዳሉ ብዙ ሰዎች ሁሉ ቃየንም ለአምላክ ያደረ መስሎ መታየቱ ብቻውን በቂ እንደሆነ ሳያስብ አልቀረም። ብዙም ሳይቆይ ግን ቃየን በይሖዋ ላይ እውነተኛ እምነት እንደሌለውና አምላክን ከልቡ እንደማይወደው በድርጊቱ ግልጽ ሆነ።
ቃየን፣ የአምላክን ሞገስ እንዳላገኘ ሲመለከት ከአቤል ምሳሌ ለመማር ሞክሮ ይሆን? በፍጹም። እንዲያውም ወንድሙን አጥብቆ ጠላው። ይሖዋ የቃየንን የልብ ሁኔታ ስላስተዋለ በትዕግሥት ሊረዳው ሞከረ። አካሄዱ ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸም እንደሚመራው ቃየንን አስጠነቀቀው፤ አካሄዱን ካስተካከለ ደግሞ ‘ተቀባይነት እንደሚያገኝ’ ተስፋ ሰጠው።—ዘፍጥረት 4:6, 7
ቃየን ግን አምላክ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ነገሬ አላለም። ከዚህ ይልቅ ክፉ ነገር ያደርግብኛል ብሎ ፈጽሞ ያልጠረጠረውን ታናሽ ወንድሙን አብሮት ወደ ሜዳ እንዲወጣ ጠየቀው። በዚያም ወንድሙን አቤልን መትቶ ገደለው። (ዘፍጥረት 4:8) በመሆኑም አቤል በእምነቱ ምክንያት ስደት የደረሰበት የመጀመሪያው ሰማዕት ነው ማለት እንችላለን። የአቤል ሕይወት ቢያልፍም ታሪኩ ግን በዚህ አላበቃም።
በምሳሌያዊ አነጋገር የአቤል ደም ፍትሕ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጮዃል። አምላክም ክፉው ቃየን ለፈጸመው ወንጀል ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ በማድረግ ፍትሕ እንዲፈጸም አድርጓል። (ዘፍጥረት 4:9-12) አቤል እምነት በማሳየት የተወው ግሩም ምሳሌ ዛሬም ድረስ እየተናገረ ያለ ያህል ነው። በወቅቱ ሰዎች ከሚኖሩበት ዕድሜ አንጻር የአቤል ሕይወት በአጭሩ ቢቀጭም ሕይወቱን በሚገባ ተጠቅሞበታል ማለት ይቻላል። ሕይወቱን በሙሉ፣ በሰማይ ያለው አባቱ ይሖዋ እንደሚወደውና የእሱ ሞገስ እንዳልተለየው ያውቅ ነበር። (ዕብራውያን 11:4) በማስታወስ ችሎታው ተወዳዳሪ የሌለው ይሖዋ እንደማይረሳው እንዲያውም ገነት በሆነችው ምድር ላይ ከሞት እንደሚያስነሳው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐንስ 5:28, 29) አቤል ከሞት ሲነሳ በዚያ ትኖር ይሆን? አቤል ሲናገር ለማዳመጥና ያሳየውን ታላቅ እምነት ለመምሰል ቁርጥ ውሳኔ ካደረግህ በዚያ ጊዜ መኖር ትችላለህ።
a ‘ዓለም ሲመሠረት’ የሚለው አገላለጽ ዘር መተካትን ይኸውም ልጆች መውለድን ያመለክታል፤ በመሆኑም ይህ አገላለጽ መጀመሪያ ከተወለደው የሰው ልጅ ጋር የተያያዘ መሆን አለበት። ታዲያ ኢየሱስ የአዳምና የሔዋን የመጀመሪያ ልጅ የሆነውን ቃየንን ሳይሆን አቤልን ‘ከዓለም መመሥረት’ ጋር አያይዞ የጠቀሰው ለምንድን ነው? ከሁኔታዎች መመልከት እንደሚቻለው ቃየን ያደረጋቸው ውሳኔዎችና አካሄዱ በይሖዋ አምላክ ላይ ሆን ብሎ ከማመፅ አይተናነስም። በመሆኑም እንደ ወላጆቹ ሁሉ ቃየንም ቤዛ እና ትንሣኤ የሚያገኝ አይመስልም።