ስሞች ያላቸው ትርጉም
በኢትዮጵያ የምትኖር አንዲት ሴት ወንድ ልጅ ተገላገለች። ሆኖም ልጁ እንደማይንቀሳቀስ ስታይ ደስታዋ በሐዘን ተተካ። ከዚያም ሴት አያቱ ሕፃኑን ለማጠብ ሲወስዱት ድንገት መንቀሳቀስ፣ መተንፈስና ማልቀስ ጀመረ! የሕፃኑ አባት ስም “ታምር” ነው። ወላጆቹ ለልጁ ያወጡለት ስም ከአባቱ ስም ጋር አንድ ላይ ሲነበብ ተሠራ ታምር የሚል ሆነ።
ብሩንዲ ውስጥ አንድ ወጣት ሊገድሉት ከሚፈልጉ ወታደሮች ለማምለጥ በመሸሽ ላይ ነው። ጥሻ ውስጥ ተደብቆ ሳለ፣ አምላክ ካዳነው ለበኩር ልጁ “ማኒራኪዛ” የሚል ስም እንደሚያወጣለት ቃል ገባ፤ ስሙም “አምላክ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ሰው በሕይወት በመትረፉ አመስጋኝ መሆኑን ለመግለጽ ከአምስት ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ልጁን ሲወልድ ማኒራኪዛ አለው።
ለልጆች ትርጉም ያለው ስም ማውጣት በአንዳንድ አገሮች ያልተለመደ ነገር ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ይህ ልማድ የቆየ ታሪክ አለው። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትርጉም አዘል ስሞች ይገኛሉ። የተለያዩ ግለሰቦች የሚጠሩባቸው ስሞች ምን ትርጉም እንዳላቸው መረዳት ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ የምታገኘውን ጥቅም ያሳድግልሃል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ትርጉም አዘል ስሞች
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጀመሪያ አካባቢ ተጠቅሰው ከሚገኙ ስሞች መካከል ሴት የሚለው ይገኛል፤ ትርጉሙም “ምትክ ሰጠ” ማለት ነው። የሴት እናት የሆነችው ሔዋን ይህን ስም ያወጣችበትን ምክንያት ስትገልጽ “ቃየን በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር ምትክ ሰጠኝ” ብላለች። (ዘፍጥረት 4:25) በሴት የትውልድ መስመር የመጣው ላሜሕ ለልጁ ኖኅ የሚል ስም ያወጣለት ሲሆን ትርጉሙም “እረፍት” ወይም “መጽናናት” ማለት ነው። ላሜሕ ለልጁ ይህን ስም ያወጣለት “እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከልፋታችንና ከጕልበታችን ድካም ያሳርፈናል” በሚል ምክንያት እንደሆነ ገልጿል።—ዘፍጥረት 5:29
አምላክ ራሱ ትንቢታዊ መልእክት እንዲኖረው ሲል የአንዳንድ አገልጋዮቹን ስም ቀይሯል። ለአብነት ያህል፣ “አባት ተከበረ” የሚል ትርጉም ያለው የአብራም ስም ተቀይሮ አብርሃም (“የብዙ ሕዝቦች አባት” ማለት ነው) ተብሎ እንዲጠራ አድርጓል። አብርሃም ከስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ የብዙ ሕዝቦች አባት ሆኗል። (ዘፍጥረት 17:5, 6) የአብርሃም ሚስት የሆነችውን የሦራንም ስም እንመልከት። የስሟ ትርጉም “ተፎካካሪ” ማለት እንደሆነ ይገመታል። አምላክ፣ የነገሥታት ቅድመ አያት እንደምትሆን በማመልከት “ልዕልት” የሚል ትርጉም ያለው “ሣራ” የሚል ስም ሲሰጣት ምንኛ ተደስታ ይሆን።—ዘፍጥረት 17:15, 16
በተጨማሪም አምላክ ራሱ በቀጥታ ስም ያወጣላቸው አንዳንድ ልጆች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ለአብርሃምና ለሣራ ልጃቸውን ይስሐቅ ብለው እንዲጠሩት የነገራቸው ሲሆን ትርጉሙም “ሳቅ” ማለት ነው። ይህ ስም እነዚህ ታማኝ ባልና ሚስት በስተርጅናቸው ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ ሲነገራቸው የተሰማቸውን ስሜት ምንጊዜም ያስታውሳቸዋል። ይስሐቅ አድጎ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ከሆነም በኋላ እንኳ አብርሃምና ሣራ ከዚህ ተወዳጅ ልጃቸው ጋር አብረው ጊዜ ሲያሳልፉ ከስሙ ጋር የተያያዙ ነገሮችን እያስታወሱ ፈገግ ማለታቸው አይቀርም።—ዘፍጥረት 17:17, 19፤ 18:12, 15፤ 21:6
የይስሐቅ ምራት የሆነችው ራሔል ለመጨረሻ ልጇ ያወጣችለት ስም በወቅቱ ካጋጠማት ለየት ያለ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነበር። ራሔል ሞት አፋፍ ላይ በነበረችበት ጊዜ ልጁን ቤንኦኒ ብላ የጠራችው ሲሆን ትርጉሙም “የሐዘኔ ልጅ” ማለት ነው። በእሷ ሞት በሐዘን ላይ የነበረው ባለቤቷ ያዕቆብ የልጁን ስም ትንሽ ለወጥ በማድረግ ብንያም አለው፤ ትርጉሙ “የቀኝ እጄ ልጅ” ማለት ነው። ይህ ስም መወደድን ብቻ ሳይሆን የድጋፍ ምንጭ መሆንንም ያመለክታል።—ዘፍጥረት 35:16-19፤ 44:20
ከአንድ ሰው መልክና ቁመና አንጻር ስም የሚሰጥበት ጊዜም አለ። ለምሳሌ፣ ይስሐቅና ርብቃ ልጃቸው ሲወለድ ሰውነቱ ጥቅጥቅ ባለ ቀይ ፀጉር የተሸፈነ ስለነበር ኤሳው የሚል ስም አወጡለት። ለምን? ምክንያቱም ስሙ በዕብራይስጥ “ፀጉራም” ማለት ነው። (ዘፍጥረት 25:25) በሩት መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው ኑኃሚን ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሯት። የአንደኛው ስም መሐሎን ሲሆን ትርጉሙም “ታማሚ፣ ልፍስፍስ” ማለት ነው። ሌላኛው ደግሞ “ደካማ” የሚል ትርጉም ያለው ኬሌዎን የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር። ምንም እንኳ ስም የወጣላቸው ሲወለዱ ይሁን ወይም ከጊዜ በኋላ የተገለጸ ነገር ባይኖርም እነዚህ ሁለት ወጣቶች በለጋ እድሜያቸው ከመሞታቸው አንጻር ሲታይ ስሞቹ ተስማሚ ነበሩ ሊባል ይችላል።—ሩት 1:5
ሌላው በሰፊው ይሠራበት የነበረው ልማድ ደግሞ ስሞችን መቀየር ወይም በስሞች ላይ ማስተካከያ ማድረግ ነው። ባሏንና ልጆቿን በሞት ካጣች በኋላ ለድህነት የተዳረገችው ኑኃሚን (“ደስታዬ” ማለት ነው) ወደ ቤተልሔም ስትመለስ በስሟ መጠራት እንደማትፈልግ ተናግራለች። “ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ማራ [“መራራ” ማለት ነው] በሉኝ እንጂ ኑኃሚን አትበሉኝ” ስትል አጥብቃ ተናግራለች።—ሩት 1:20, 21 የ1954 ትርጉም
በተጨማሪም ከአንድ ጉልህ ክንውን ጋር አያይዞ ለልጆች ስም የማውጣት ልማድ ነበር። ለምሳሌ፣ የነቢዩ ሐጌ ስም “በበዓል ቀን የተወለደ” የሚል ትርጉም አለው።a
በክርስትና ዘመን የነበሩ ትርጉም አዘል ስሞች
የኢየሱስ ስም ከፍተኛ ትንቢታዊ ትርጉም አለው። ከመወለዱ በፊት ወላጆቹ ‘ስሙን ኢየሱስ ብለው እንዲጠሩት’ መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። ስሙ “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ስም የተሰጠው በምን ምክንያት ነው? ዮሴፍን ያነጋገረው መልአክ “ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 1:21) ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባ በስሙ ላይ “መሲሕ” የሚል የዕብራይስጥ የማዕረግ መጠሪያ ተጨመረለት። ይህ የማዕረግ ስም በግሪክኛ “ክርስቶስ” ማለት ነው። ሁለቱም ቃላት “የተቀባው” የሚል ትርጉም አላቸው።—ማቴዎስ 2:4
ኢየሱስ ለአንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ ማንነታቸውን የሚገልጹ ስሞች አውጥቶላቸዋል። ለአብነት ያህል፣ ለስምዖን በሴማዊ ቋንቋ ኬፋ የሚል ስም አውጥቶለት የነበረ ሲሆን ትርጓሜውም “ዐለት” ማለት ነው። ኬፋ የሚለው ስም በግሪክኛ “ጴጥሮስ” ማለት ሲሆን ስምዖን በሰፊው የሚታወቀውም በዚህ ስም ነው። (ዮሐንስ 1:42) ኢየሱስ ቀናተኛ የሆኑትን ወንድማማቾች ያዕቆብና ዮሐንስን “ቦአኔርጌስ” ማለትም “የነጎድጓድ ልጆች” ብሎ ጠርቷቸዋል።—ማርቆስ 3:16, 17
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ይህን ልማድ በመከተል ለሰዎች ተስማሚ የሆኑ ቅጽል ስሞችን ያወጡ ነበር። ሐዋርያት በርናባስ (“የመጽናናት ልጅ” ማለት ነው) የሚል ስም ያወጡለት ደቀ መዝሙሩ ዮሴፍ በዚህ ረገድ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። በርናባስ ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ስጦታዎችን በመስጠት ለብዙዎች የመጽናኛ ምንጭ በመሆኑ ከስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል።—የሐዋርያት ሥራ 4:34-37፤ 9:27፤ 15:25, 26
የምታተርፈው ስም ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል
ስንወለድ የሚወጣልንን ስም የምንመርጠው እኛ አይደለንም። ይሁን እንጂ በሌሎች ዘንድ የምናተርፈው ስም ሙሉ በሙሉ በእኛ ላይ የተመካ ነው። (ምሳሌ 20:11) ለምን እንዲህ እያልክ ራስህን አትጠይቅም፦ ‘ኢየሱስ ወይም ሐዋርያት አጋጣሚ ቢያገኙ ኖሮ ምን ስም ያወጡልኝ ነበር? የእኔን ባሕርይ ወይም ማንነት ለመግለጽ ተስማሚ የሚሆነው ምን ዓይነት ስም ነው?’
እነዚህ ጥያቄዎች በቁም ነገር ሊታሰብባቸው ይገባል። ለምን? ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “መልካም ስም ከብዙ ብልጽግና ይመረጣል” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 22:1) በምንኖርበት አካባቢ ጥሩ ስም ወይም ዝና ካተረፍን በእርግጥም ትልቅ ሀብት አግኝተናል ማለት ነው። ከዚህ ይበልጥ ደግሞ በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ማትረፋችን ዘላቂ ሀብት ያስገኝልናል። እንዴት? አምላክ እሱን የሚፈሩትን ሰዎች ስም ‘በመታሰቢያ መጽሐፉ’ ውስጥ እንደሚጽፍና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል።—ሚልክያስ 3:16፤ ራእይ 3:5፤ 20:12-15
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በአፍሪካ ውስጥ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች እነሱ በተወለዱበት ወቅት ከተደረጉ ትልልቅ ስብሰባዎች ርዕስ ጋር የተያያዘ ስም አላቸው።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የእኔን ማንነት ለመግለጽ ተስማሚ የሚሆነው ምን ዓይነት ስም ነው?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
አማኑኤል ማን ነበር?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ስሞች ትንቢታዊ ትርጉም የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ግለሰቦቹ የሚያከናውኑትንም ሥራ ይገልጻሉ። ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ በመመራት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” (ኢሳይያስ 7:14) ይህ ስም “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” የሚል ትርጉም አለው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ይህ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው ከእስራኤል ነገሥታት ወይም ከኢሳይያስ ወንዶች ልጆች በአንዱ ላይ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና የወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ የኢሳይያስ ትንቢት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያገኘው በኢየሱስ ላይ እንደሆነ ገልጿል።—ማቴዎስ 1:22, 23
አንዳንዶች፣ አማኑኤል የሚለው ስም ለኢየሱስ በመሰጠቱ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ ያስተምራል ይላሉ። ይሁን እንጂ በዚህ አካሄድ፣ ኢዮብን ያጽናናውና ያረመው ወጣቱ ኤሊሁ አምላክ ነበር ማለት ነው። ለምን? ምክንያቱም የስሙ ትርጉም “እሱ አምላኬ ነው” ማለት ነው።
ኢየሱስ መቼም ቢሆን አምላክ ነኝ ብሎ አያውቅም። (ዮሐንስ 14:28፤ ፊልጵስዩስ 2:5, 6) ይሁንና የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀ ከመሆኑም ሌላ አምላክ መሲሑን በተመለከተ የሰጣቸውን ተስፋዎች በሙሉ ፈጽሟል። (ዮሐንስ 14:9፤ 2 ቆሮንቶስ 1:20) አማኑኤል የሚለው ስም ለኢየሱስ መሰጠቱ አምላክ ከአገልጋዮቹ ጋር መሆኑን የሚያሳይ ከመሆኑም በተጨማሪ ይህ የዳዊት ልጅ መሲሐዊ ዘር በመሆን የሚጫወተውን ሚናም በሚገባ ይገልጻል።
[ሥዕል]
አማኑኤል “አምላክ ከእኛ ጋር ነው”
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ከሁሉ የላቀ ትርጉም ያለው ስም
የአምላክ የግል ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኛል። ይህ ስም በአራት የዕብራይስጥ ፊደላት (יהוה) የሚወከል ሲሆን በአማርኛ “ይሖዋ” የሚለው አጠራር የተለመደ ነው። ስሙ ምን ትርጉም ይዟል? ሙሴ የአምላክን ስም ለማወቅ በጠየቀበት ጊዜ ይሖዋ “መሆን የምፈልገውን ሁሉ እሆናለሁ” የሚል መልስ ሰጥቶታል። (ዘፀአት 3:14፣ በጆሴፍ ብራያንት ሮተርሃም የተዘጋጀው ዚ ኤምፈሳይዝድ ባይብል) በመሆኑም የአምላክ የግል ስም እሱ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሆን ዋስትና ይሰጣል። (ኢሳይያስ 55:8-11) አምላክ አንድ ተስፋ ከሰጠ ሕይወታችንን ከተስፋው ጋር በሚስማማ መንገድ መምራት እንችላለን። እንዲህ የምናደርገው ለምንድን ነው? ይሖዋ የሚለው ስም ምን ትርጉም እንዳለው ስለምንገነዘብ ነው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብርሃም “የብዙ ሕዝቦች አባት”
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሣራ “ልዕልት”