አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች በእምነት እየተጠባበቁ መኖር
“እኔ አምላክ ነኝና፣ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ።”—ኢሳይያስ 46:9, 10
1, 2. አምላክ በምድር ጉዳዮች ውስጥ እጁን ጣልቃ ማስገባቱን በሚመለከት ምን የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ?
አምላክ በምድር ጉዳይ እጁን ጣልቃ የሚያስገባው እስከ ምን ድረስ ነው? ሰዎች ያላቸው አስተያየት የተለያየ ነው። በአንድ በኩል ጨርሶ እጁን ጣልቃ አያስገባም የሚል አመለካከት አለ። አንዴ ነገሮችን ፈጥሮ መስመር ካስያዘ በኋላ ዳግም እጁን ለማስገባት አንድም ፈቃደኛ አይደለም አሊያም ደግሞ አይችልም። እንደዚህ አባባል ከሆነ አምላክ፣ ልጁን አዲስ ብስክሌት ላይ አመቻችቶ አስቀምጦ ገፋ በማድረግ መንገድ ካስጀመረ በኋላ ፊቱን አዙሮ የራሱን መንገድ ከቀጠለ አባት ጋር ይመሳሰላል። ከዚያ በኋላ ልጁ ብቻውን ነው። ሊወድቅም ላይወድቅም ይችላል። ምንም ይሁን ምን ከዚህ በኋላ አባትየው ሊያደርገው የሚችለው ነገር የለም።
2 ሌላው አመለካከት ደግሞ አምላክ እያንዳንዱን የሕይወታችንን ዘርፍ በቀጥታ ይቆጣጠራል፤ በፍጥረት ሥራዎቹ መካከል የሚከናወነው እያንዳንዱ ነገርም የእርሱ እጅ አለበት የሚል ነው። ይሁን እንጂ ይህ አባባል እውነት ከሆነ ለመልካም ነገሮች ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ እያሰቃዩት ላሉት ወንጀሎችና አሳዛኝ ነገሮችም ጭምር መንስኤው አምላክ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ የሚደርሱ ሰዎች ይኖራሉ። ስለ አምላክ አሠራር ትክክለኛውን ነገር ማወቃችን ከእርሱ ምን መጠበቅ እንዳለብን እንድናውቅ ይረዳናል። በተጨማሪም የማይጠረጠረውን የአምላክ ተስፋዎች ፍጻሜ በሚመለከት ያለንን እምነት ያጠነክርልናል።—ዕብራውያን 11:1
3. (ሀ) ይሖዋ የዓላማ አምላክ መሆኑን እንዴት እናውቃለን? (ለ) ይሖዋ ዓላማውን ‘መልክ እንደሚያስይዝና’ ‘እንደሚያስተካክል’ ተደርጎ የተገለጸው ለምንድን ነው?
3 አምላክ በሰዎች ጉዳይ ውስጥ እጁን ጣልቃ ያስገባል ወይስ አያስገባም ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይሖዋ የዓላማ አምላክ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህም በስሙ ላይ በግልጽ ተንጸባርቋል። “ይሖዋ” ማለት “እንዲሆን የሚያደርግ” ማለት ነው። ይሖዋ ደረጃ በደረጃ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ራሱን የሰጠው የተስፋ ቃል አስፈጻሚ ያደርጋል። ከዚህም የተነሣ ይሖዋ ወደፊት የሚከናወኑትን ነገሮች በተመለከተ ያለውን ዓላማ ‘መልክ እንደሚያስይዝ’ ወይም ‘እንደሚያስተካክል’ ተደርጎ ተገልጿል። (2 ነገሥት 19:25 NW፤ 46:11 NW) እነዚህ አገላለጾች ያስታር ከተባለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኙ ሲሆን ይህ ቃል ደግሞ “ሸክላ ሠሪ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል ጋር ተዛማጅነት አለው። (ኤርምያስ 18:4) አንድ የተዋጣለት ሸክላ ሠሪ ጥፍጥፉን ጭቃ ያማረ ዕቃ አድርጎ ቅርጽ እንደሚያስይዘው ሁሉ ይሖዋም ፈቃዱን ለመፈጸም ሲል ነገሮችን መልክ ማስያዝ ወይም እንደሚፈልገው አድርጎ ማስተካከል ይችላል።—ኤፌሶን 1:11
4. አምላክ ምድርን ለሰው ልጆች መኖሪያነት ያዘጋጃት እንዴት ነበር?
4 ለምሳሌ ያህል አምላክ፣ ምድራችን ውበት የተላበሰችና ታዛዥ የሆኑ ፍጹማን የሰው ልጆች የሚኖሩባት ቦታ እንድትሆን ዓላማ ነበረው። (ኢሳይያስ 45:18) ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ለእነርሱ ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጓል። የዘፍጥረት መጽሐፍ የመክፈቻ ምዕራፎች ይሖዋ ቀንና ሌሊትን እንዲሁም የብስና ባሕርን እንዴት እንዳዋቀረ ይገልጻሉ። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ዕጽዋትንና እንስሳትን ፈጠረ። ምድርን ለሰው ልጆች መኖሪያነት ለማዘጋጀት የተከናወነው ይህ ሥራ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት የፈጀ ነበር። ፕሮጄክቱ በተሳካ መንገድ ተጠናቀቀ። የመጀመሪያዎቹም ወንድና ሴት በኤደን ማለትም ደስ እያላቸው እንዲኖሩ ታስቦ በተዘጋጀላቸው ይህ ቀረው በማይባል አስደሳች ገነት ውስጥ መኖር ጀመሩ። (ዘፍጥረት 1:31) በዚህ መንገድ ይሖዋ ታላቁን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ሲል ሥራውን ደረጃ በደረጃ በማከናወን በምድር ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ እጁን ጣልቃ አስገብቶ ነበር። የሰው ዘር ቤተሰብ ቁጥሩ እየጨመረ ሲመጣ አምላክ በምድር ጉዳይ እጁን ጣልቃ ማስገባቱን አቁሟልን?
ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ገደብ አለው
5, 6. አምላክ ከሰዎች ጋር ለሚያደርገው ግንኙነት ገደብ ያበጀለት ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ እያንዳንዱን የሰው ልጆች እንቅስቃሴ መምራትና መቆጣጠር የሚችል ቢሆንም እንደዚያ ግን አያደርግም። ይህን የማያደርግበት ምክንያት አለው። አንደኛው ምክንያት ሰዎች በአምላክ ምሳሌ የተፈጠሩ ነፃ ምርጫ ያላቸው ፍጥረታት መሆናቸው ነው። ይሖዋ የእርሱን ትእዛዛት እንድናከብር አያስገድደንም። ወይም እንደ ሮቦት አድርጎ አልፈጠረንም። (ዘዳግም 30:19, 20፤ ኢያሱ 24:15) አምላክ ለምናደርገው ነገር በኃላፊነት የሚጠይቀን ቢሆንም በፍቅር ተገፋፍቶ ሕይወታችንን እንዴት እንደምንጠቀምበት የመወሰን ሰፊ ነፃነት ሰጥቶናል።—ሮሜ 14:12፤ ዕብራውያን 4:13
6 አምላክ እያንዳንዱን ነገር የማይቆጣጠርበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ሰይጣን በኤደን ካስነሣው ክርክር ጋር የሚዛመድ ነው። ሰይጣን የአምላክን ሉዓላዊነት ተገዳድሯል። ሔዋን ራስዋን በራስዋ ማስተዳደር የምትችል አስመስሎ አንድ ምርጫ አቅርቦላት ነበር። እርሷም ሆነች ባሏ አዳም ይህን ምርጫ ተቀበሉ። (ዘፍጥረት 3:1-6) በምላሹም አምላክ የሰይጣን ግድድር ትክክል መሆን አለመሆኑ እንዲታይ የሰው ልጅ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር የተወሰነ ጊዜ ፈቅዷል። ከዚህ የተነሣ ዛሬ የሰው ልጅ ለሚፈጽማቸው መጥፎ ነገሮች አምላክ ሊወቀስ አይችልም። ሙሴ ዓመፀኛ የነበሩ ሰዎችን በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም [የአምላክ ልጆች] አይደሉም። ነውርም አለባቸው [“ችግሩ ከእነርሱ ነው፣” NW]።”—ዘዳግም 32:5
7. ይሖዋ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
7 ይሁን እንጂ ይሖዋ ነፃ ምርጫ እንዲኖረን ማድረጉና የሰው ልጅ ራሱን በራሱ አስተዳድሮ ውጤቱን እንዲያየው መፍቀዱ የምድርን ጉዳይ እርግፍ አድርጎ ትቶታል ማለት አይደለም። እንደዚያ ከሆነ ዓላማውን ያስፈጽማል የሚል ተስፋ ሊኖረን አይችልም። አዳምና ሔዋን በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ቢያምጹም ይሖዋ ለምድርና ለሰው ዘር ያለውን ፍቅራዊ ዓላማ አልለወጠም። ምድርን ፍጹም፣ ታዛዥና ደስተኛ በሆኑ ሰዎች የተሞላች ገነት እንደሚያደርጋት ምንም አያጠራጥርም። (ሉቃስ 23:42, 43) ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ ይህንን ግቡን ዳር ለማድረስ እንዴት ደረጃ በደረጃ ሲሠራ እንደቆየ ይገልጻል።
አምላክ ፈቃዱን ለመፈጸም እርምጃ ይወስዳል
8. እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር ማስገባት ምን ነገሮችን ይጠይቅ ነበር?
8 አምላክ ከእስራኤል ብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት ዓላማውን የሚፈጽም መሆኑን የሚያረጋግጥ ነበር። ለምሳሌ ያህል ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብጽ ነፃ አውጥቶ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ተስፋይቱ ምድር እንደሚያስገባቸው ይሖዋ ማረጋገጫ ሰጥቶት ነበር። (ዘጸአት 3:8) ይህ ትልቅ ግምት የሚሰጠውና እምነት የሚገነባ ማረጋገጫ ነበር። ይህም ተባባሪዎቻቸውን ጨምሮ ወደ ሦስት ሚልዮን የሚጠጉትን እስራኤላውያን አልለቃቸውም ብሎ ይሟገት ከነበረው ኃያል ብሔር እጅ ነፃ ማውጣት ማለት ነበር። (ዘጸአት 3:19) ከዚያ ወጥተው የሚገቡበትም ምድር ቢሆን የእነርሱን መምጣት በሚቃወሙ ኃያላን ብሔራት የተያዘ ነበር። (ዘዳግም 7:1) በዚህ መካከል ያለው ቦታ ደግሞ ምድረ በዳ ሲሆን እስራኤላውያን ምግብና ውኃ ያስፈልጋቸው ነበር። እነዚህ ሁኔታዎች ይሖዋ ታላቅ ክንዱንና አምላክነቱን እንዲያሳይ አስችለውታል።—ዘሌዋውያን 25:38
9, 10. (ሀ) ኢያሱ አምላክ የሚሰጠው የተስፋ ቃል አስተማማኝ መሆኑን ሊመሠክር የቻለው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ በእርሱ ለሚታመኑት ዋጋቸውን እንደሚሰጥ ማመናችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
9 አምላክ ኃያል ክንዱን ያሳየባቸውን ተከታታይ እርምጃዎች በመውሰድ እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር ነፃ አውጥቷቸዋል። በመጀመሪያ አሥር አውዳሚ መቅሰፍቶችን በግብጽ ብሔር ላይ አወረደ። ከዚያም ቀይ ባሕርን በመክፈል እስራኤላውያን እንዲያልፉና ያሳድዳቸው የነበረው የግብጻውያን ሠራዊት እንዲጠፋ አደረገ። (መዝሙር 78:12, 13, 43-51) በዚህ ብቻ ሳያበቃ እስራኤላውያን በበረሃ በቆዩባቸው 40 ዓመታት ሁሉ መና በመመገብ፣ ውኃ በመስጠት አልፎ ተርፎም ልብሳቸው እንዳያረጅና እግራቸው እንዳያብጥ በማድረግ ተንከባክቧቸዋል። (ዘዳግም 8:3, 4) እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡም በኋላ ይሖዋ በጠላቶቻቸው ላይ ድል እንዲቀዳጁ አስችሏቸዋል። በአምላክ ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት የነበረው ኢያሱ ለዚህ ሁሉ ነገር የዓይን ምሥክር ነበር። በመሆኑም በዘመኑ ለነበሩት ሽማግሌዎች እንዲህ ማለት ችሎ ነበር:- “እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁም ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል።”—ኢያሱ 23:14
10 ልክ እንደ ጥንቱ ኢያሱ ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖችም አምላክ ለሚያገለግሉት ሰዎች ሲል እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ እንደሆነና አቅሙም እንዳለው ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ናቸው። ይህ የጸና ትምክህት ለእምነታችን ወሳኝ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር . . . [ለሚፈልጉት] ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።”—ዕብራውያን 11:6
አምላክ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ያውቃል
11. አምላክ ዓላማውን ከዳር እንዲያደርስ የሚረዱት ነገሮች ምንድን ናቸው?
11 እስካሁን ድረስ እንደተመለከትነው አምላክ ነፃ ምርጫ እንዲኖረንና ሰዎችም ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ቢፈቅድም ዓላማውን ለመፈጸም ሲል እርምጃ ለመውሰድ ኃይሉም ፈቃደኛነቱም አለው። ይሁንና የአምላክ ዓላማዎች የማይቀር ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሌላም ነገር አለ። ይሖዋ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ ማወቅ ይችላል። (ኢሳይያስ 42:9) አምላክ በነቢዩ አማካኝነት እንዲህ ብሏል:- “እኔ አምላክ ነኝና፣ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴን ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ።” (ኢሳይያስ 46:9, 10) አንድ ጥሩ ተሞክሮ ያለው ገበሬ ዘሩን መቼና የት መዝራት እንዳለበት ያውቃል። ይሁንና የመጨረሻው ውጤት ምን እንደሚሆን በእርግጠኛነት መናገር አይቻል ይሆናል። ይሁን እንጂ ‘የዘላለሙም ንጉሥ’ ዓላማውን ለመፈጸም መቼና የት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አስቀድሞ በትክክል ለመወሰን የሚያስችል ትክክለኛ እውቀት አለው።—1 ጢሞቴዎስ 1:17 የ1980 ትርጉም
12. ይሖዋ በኖኅ ዘመን ወደፊት ስለሚሆነው ነገር የማወቅ ችሎታውን የተጠቀመበት በምን መንገድ ነው?
12 አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ነገር የማወቅ ችሎታውን በኖኅ ዘመን እንዴት እንደተጠቀመበት ተመልከት። አምላክ በወቅቱ በምድር ላይ እጅግ ተስፋፍቶ ከነበረው ክፋት የተነሣ የማይታዘዙትን የሰው ልጆች ለማጥፋት ወሰነ። ይህንንም የሚያደርግበትን ጊዜ በመወሰን 120 ዓመታት መደበ። (ዘፍጥረት 6:3) ይሖዋ ይህንን ጊዜ ሲወስን ግምት ውስጥ ያስገባው የክፉዎችን መጥፋት ብቻ አልነበረም። ይህንን በማንኛውም ጊዜ ሊያደርገው ይችል ነበር። የይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ ጻድቃን ሕይወታቸውን ማትረፍ የሚችሉበትንም ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችል ነበር። (ከዘፍጥረት 5:29 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ ጥበበኛ በመሆኑ ይህን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚያስችለውን ሥራ መቼ እንደሚያስጀምርም አስቀድሞ ያውቅ ነበር። ለኖኅ አስፈላጊውን ዝርዝር መረጃ ሰጠው። ኖኅ ‘ቤተ ሰዎቹን ለማዳን’ መርከብ መሥራት የነበረበት ሲሆን ክፉዎች ግን በምድር አቀፉ ጎርፍ አማካኝነት ጥፋት ይጠብቃቸው ነበር።—ዕብራውያን 11:7፤ ዘፍጥረት 6:13, 14, 18, 19
እጅግ ግዙፍ የሆነ የግንባታ ፕሮጄክት
13, 14. የመርከብ ግንባታው ፈታኝ ሥራ የነበረው ለምንድን ነው?
13 እስቲ ራስህን በኖኅ ቦታ አስቀምጥና ስለተሰጠው ሥራ አስብ። ኖኅ የአምላክ ሰው ስለነበር ይሖዋ አምላካዊ ያልሆኑትን ሰዎች ሊያጠፋ እንደሚችል ያውቅ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ከመሆኑ በፊት እምነት የሚጠይቅ አንድ ሥራ መሠራት ነበረበት። የመርከብ ግንባታው እጅግ ግዙፍ ፕሮጄክት ነበር። አምላክ የመርከቡ ልክ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ነግሮታል። ይህ መርከብ ዛሬ ካሉት ዘመናዊ የስፖርት ሜዳዎች የሚረዝም ሲሆን እስከ አምስት ፎቅ የሚደርስ ከፍታ ይኖረዋል። (ዘፍጥረት 6:15) ይህን መርከብ የሚሠሩት ደግሞ ተሞክሮ የሌላቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው። ዛሬ ያሉት የተራቀቁ መሣሪያዎችና ዕቃዎች አልነበሯቸውም። ከዚህም በላይ ኖኅ እንደ ይሖዋ ወደፊት የሚሆነውን ነገር የማወቅ ችሎታ ስላልነበረው ከዓመታት በኋላ የግንባታ ፕሮጄክቱን የሚያግዙ ወይም የሚያደናቅፉ ምን ነገሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ የሚያውቅበት ምንም መንገድ አልነበረም። በኖኅ አእምሮ ውስጥ የሚጉላሉ ብዙ ጥያቄዎች እንደነበሩ ምንም አያጠራጥርም። የግንባታው ዕቃዎች የሚሰባሰቡት እንዴት ነው? እንስሳቱንስ የሚያሰባስበው እንዴት ነው? ምን ዓይነት ምግብ ነው የሚያስፈልገው? ደግሞስ ምን ያህል? አስቀድሞ የተነገረው የውኃ ጥፋት የሚመጣበት ትክክለኛ ጊዜ መቼ ይሆን?
14 ከዚህም በተጨማሪ ማኅበራዊ ጉዳዮችም ነበሩ። ክፋት በዝቷል። ከክፉዎቹ መላእክትና ከሴቶች የተዳቀሉት ግዙፍ ኔፍሊሞች ምድርን በዓመፅ ሞልተዋት ነበር። (ዘፍጥረት 6:1-4, 13) ከዚህም በላይ የመርከብ ግንባታ በምሥጢር ሊካሄድ የሚችል ነገር አይደለም። ሰዎቹ ኖኅ ምን እየሠራ ነው ብለው መገረማቸው አይቀርም፤ እርሱም ይነግራቸዋል። (2 ጴጥሮስ 2:5) ሥራውን ይደግፉለታል ብሎ መጠበቅ ይቻላልን? በፍጹም! ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የታመነው ሔኖክ ክፉዎች እንደሚጠፉ ተናግሮ ነበር። መልእክቱ በሰዎቹ ዘንድ ተወዳጅ ስላልነበረ አምላክ ጠላቶቹ እንዳይገድሉት ሲል ‘ወስዶታል’ በሌላ አባባል ሕይወቱን አሳጥሮለታል። (ዘፍጥረት 5:24፤ ዕብራውያን 11:5፤ ይሁዳ 14, 15) ኖኅም ለሰዎቹ ጆሮ የማይጥመውን መልእክት ማወጅ ብቻ ሳይሆን መርከብም መገንባት ነበረበት። የመርከቡ ግንባታ የኖኅን ታማኝነት በዘመኑ ለነበረው ክፉ ትውልድ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነበር!
15. ኖኅ ሥራውን ከዳር ማድረስ እንደሚችል ትምክህት የነበረው ከምን የተነሣ ነው?
15 ኖኅ ፕሮጄክቱ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ድጋፍና በረከት እንደነበረው እርግጠኛ ነበር። ደግሞስ ሥራውን የሰጠው ይሖዋ ራሱ አልነበረምን? ኖኅና ቤተሰቡ ተሠርቶ በተጠናቀቀው መርከብ ውስጥ እንደሚገቡና ከምድር አቀፉ የጥፋት ውኃ እንደሚድኑ ይሖዋ ማረጋገጫ ሰጥቶት ነበር። አምላክ የዚህን ጉዳይ አስተማማኝነት አስረግጦ ነግሮታል። (ዘፍጥረት 6:18, 19) ይሖዋ ይህንን ሥራ ሲሰጠው የሚያስከትለውን ኃላፊነት ሁሉ አስቀድሞ አስቦበትና አመዛዝኖ እንደሰጠው ኖኅ እንደተገነዘበ እሙን ነው። ከዚህም ሌላ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ይሖዋ እርሱን ለመርዳት አቅም እንደማያንሰው እርግጠኛ ነበር። በመሆኑም ኖኅ የነበረው እምነት ለሥራ አንቀሳቅሶታል። ከአብራኩ የተገኘው አብርሃም እንዳደረገው ሁሉ ኖኅም ‘አምላክ የሰጠውን ተስፋ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ ተረድቶ’ ነበር።—ሮሜ 4:20, 21
16. የመርከቡ ግንባታ እየተገባደደ ሲሄድ የኖኅ እምነት የተጠናከረው እንዴት ነው?
16 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱና መርከቡም መልክ እየያዘ ሲመጣ የኖኅ እምነት ተጠናክሮ ነበር። የገጠሙት የግንባታና የሎጂስቲክ ችግሮች መፍትሔ አግኝተዋል። የደረሱበትን ፈተናዎች ተወጥቷቸዋል። ምንም ዓይነት ተቃውሞ ሥራውን ሊገታው አልቻለም። የኖኅም ቤተሰብ የይሖዋን ድጋፍና ጥበቃ አግኝቷል። ኖኅ በቆራጥነት ወደ ፊት ሲገፋ ‘የእምነቱ መፈተን ጽናትን አፍርቶለታል።’ (ያዕቆብ 1:2-4 NW) በመጨረሻ መርከቡ ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ የውኃ መጥለቅለቁ ጀመረ። ኖኅና ቤተሰቡም ከጥፋቱ ተረፉ። ኖኅ ከጊዜ በኋላ ኢያሱ እንደተናገረው የአምላክ ቃል ፍጻሜውን ሲያገኝ ተመልክቷል። ኖኅ ያሳየው እምነት ተክሷል።
ሥራውን የሚደግፈው ይሖዋ ነው
17. እኛ ያለንበት ዘመን ከኖኅ ዘመን ጋር የሚመሳሰለው በምን መንገድ ነው?
17 ኢየሱስ የእኛ ዘመን ከኖኅ ዘመን ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ተንብዮአል። ዛሬም አምላክ ክፉዎችን ዳግም ለማጥፋት ከመወሰኑም ሌላ ይህንን የሚያደርግበትን ጊዜ ቀጥሯል። (ማቴዎስ 24:36-39) እንዲሁም ጻድቃን የሚተርፉበትን ዝግጅት አድርጓል። ኖኅ መርከብ መገንባት የነበረበት ቢሆንም ዛሬ ያሉት የአምላክ አገልጋዮች የሚጠበቅባቸው የአምላክን ዓላማ ማወጅ፣ ቃሉን ማስተማርና ደቀ መዛሙርት ማድረግ ነው።—ማቴዎስ 28:19
18, 19. የምሥራቹ ስብከት ሥራ የይሖዋ ድጋፍ እንዳለው እንዴት እናውቃለን?
18 ኖኅ የይሖዋን ድጋፍና እርዳታ ባያገኝ ኖሮ መርከቡን መገንባት ባልቻለ ነበር። (ከመዝሙር 127:1 ጋር አወዳድር።) በተመሳሳይም የይሖዋ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ እውነተኛው ክርስትና እየጎለበተ መሄድ ይቅርና ጨርሶ በጠፋ ነበር። ትልቅ ተሰሚነት የነበረው ፈሪሳዊና የሕግ አስተማሪ ገማልያል በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይህንን ሐቅ ተገንዝቦ ነበር። የአይሁዳውያን ሳንሄድሪን ሸንጎ ሐዋርያቱን ሊገድላቸው ባሰበ ጊዜ ሸንጎውን እንዲህ ሲል አሳስቧል:- “ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፣ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ።”—ሥራ 5:38, 39
19 በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ሆነ ዛሬ የተከናወነው የስብከት ሥራ ውጤታማ መሆኑ ሥራው የአምላክ እንጂ የሰው እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ነው። የሚቀጥለው ርዕስ ይህ ሥራ ይህን በሚያክል ስፋት ስኬታማ በሆነ መንገድ እንዲከናወን እገዛ ያደረጉት አስገራሚ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ ይዳስሳል።
ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጡ!
20. በስብከቱ ሥራችን እነማን ይደግፉናል?
20 ምንም እንኳ ዛሬ የምንኖረው ‘አስጨናቂ በሆነ ዘመን’ ውስጥ ቢሆንም ከይሖዋ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ምንም ነገር እንደሌለ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አምላክ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት የቀጠረው ጊዜ ከመድረሱ በፊት አገልጋዮቹ የምሥራቹን የመስበክ ሥራቸውን ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና ሲሉ ይደግፋቸዋል፤ ያጸናቸውማል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ማቴዎስ 24:14) ይሖዋ ‘ከእርሱ ጋር አብረን እንድንሠራ’ ጋብዞናል። (1 ቆሮንቶስ 3:9) ክርስቶስ ኢየሱስ በዚህ ሥራ እንደሚደግፈንና የመላእክትንም ድጋፍና መመሪያ እንደምናገኝ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል።—ማቴዎስ 28:20፤ ራእይ 14:6
21. ስለ ምን ነገር ያለንን የጸና እምነት ፈጽሞ ልናጠፋ አይገባንም?
21 ኖኅና ቤተሰቡ በይሖዋ የተስፋ ቃል ላይ እምነት እንዳላቸው በማሳየታቸው ከውኃው መጥለቅለቅ በሕይወት ሊተርፉ ችለዋል። ዛሬም ተመሳሳይ እምነት የሚያሳዩ ሰዎች ከመጪው ‘ታላቅ መከራ’ ይተርፋሉ። (ራእይ 7:14) ዛሬ የምንኖረው በእርግጥም በጣም በሚያስደስት ወቅት ላይ ነው። ከፊታችን ወሳኝ ክንውኖች ይጠብቁናል! በቅርቡ አምላክ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ለማምጣት እርምጃ ይወስዳል። (2 ጴጥሮስ 3:13) አምላክ የተናገረውን ነገር ሁሉ ሊያደርገው እንደሚችል ያላችሁን ጽኑ እምነት ፈጽሞ አታጥፉ።—ሮሜ 4:21
የክለሳ ነጥቦች
◻ ይሖዋ እያንዳንዱን የሰው ልጅ እንቅስቃሴ የማይቆጣጠረው ለምንድን ነው?
◻ ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ያለው ችሎታ ለእስራኤል ሕዝብ ባደረገው ነገር በግልጽ የታየው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ያለው ችሎታ በኖኅ ዘመን የተገለጠው እንዴት ነው?
◻ በአምላክ የተስፋ ቃል ላይ ምን ትምክህት ሊኖረን ይችላል?