ምዕራፍ 10
ክፉ መናፍስት ኃይለኞች ናቸው
1. ብዙ ሰዎች ከሙታን ጋር ለመነጋገር እንደሚችሉ አድርገው የሚያምኑት ለምንድን ነው?
ብዙ ጊዜ ሰዎች ከሙታን ጋር ተነጋገርን ይላሉ። ታዋቂ የነበሩት ሟቹ የኤፒስኮፓል ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ጄምስ ኤ ፓይክ ከሞተው ልጃቸው ከጂም ጋር እንደተነጋገሩ ገልጸዋል። ፓይክ በተናገሩት መሠረት ወንድ ልጃቸው እንደሚከተለው በማለት ነግሯቸዋል:- “ብዙ ሰዎች በዙሪያዬ ከብበውኛል፤ እጆችም ወደ ላይ ብድግ አድርገው አንሥተውኛል። . . . ይህንን ነገር እስከማሳውቅህ ድረስ በጣም አዝኜ ነበር።”
2. (ሀ) ማንም ሰው ከሙታን ጋር ለመነጋገር የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) ስለዚህ ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?
2 እንደነዚህ ያሉት አጋጣሚዎች በጣም የተለመዱ በመሆናቸው ብዙ ሰዎች በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ካለ ከአንድ አካል ጋር እንደተነጋገሩ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ከሙታን ጋር አልተነጋገሩም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም ” ብሎ በግልጽ ይናገራል። (መክብብ 9:5) ከመንፈሳዊው ዓለም የሚናገሩት ሙታን ካልሆኑ ታዲያ ተናጋሪዎቹ እነማን ናቸው? የሞቱትን ሰዎች መስለው የሚናገሩት እነማን ናቸው?
3. (ሀ) የሞቱትን ሰዎች አስመስለው የሚቀርቡት እነማን ናቸው? ለምንስ? (ለ) ብዙውን ጊዜ ክፉ መናፍስት አንዳንድ ነገሮችን የሚያሳውቁት ለእነማን ነው?
3 ክፉ መናፍስት ናቸው። እነዚህ መናፍስት ወይም አጋንንት በአምላክ ላይ በተነሣው ዐመፅ ከሰይጣን ጋር የተባበሩ መላእክት ናቸው። ታዲያ የሞቱት ሰዎች እንደሆኑ አስመስለው የሚቀርቡት ለምንድን ነው? ሙታን አሁንም በሕይወት አሉ የሚለውን ሐሳብ ለማስፋፋት ነው። በተጨማሪም ክፉ መናፍስት ሞት ማለት ወደ ሌላ ዓይነት ሕይወት መለወጥ ማለት ነው የሚለውን ውሸት ብዙ ሰዎች እንዲያምኑ አድርገዋቸዋል። ይህንን ውሸት ለማስፋፋት ክፉ መናፍስት ለመናፍስት ጠሪዎች፣ ለምዋርተኞችና ለአስማተኞች ከሞቱት ሰዎች ብቻ እንደመጣ የሚመስል ልዩ እውቀት ይሰጧቸዋል።
ሟቹን ሳሙኤልን መስሎ መቅረብ
4. (ሀ) ንጉሥ ሳኦል ርዳታ ለማግኘት የተጨነቀው ለምንድን ነው? (ለ) መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን በሚመለከት የአምላክ ሕግ ምን ይል ነበር?
4 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሞቶ የነበረውን የአምላክ ነቢይ ሳሙኤልን መስሎ ስለቀረበ ክፉ መንፈስ የተገለጸ አንድ ምሳሌ አለ። ይህ የሆነው በንጉሥ ሳኦል 40ኛ የግዛት ዘመን ላይ ነበር። ኃያል የሆነ የፍልስጥኤም ሠራዊት በሳኦል የእስራኤል ሠራዊት ላይ ስለመጣ ሳኦል በጣም ፈርቶ ነበር። ሳኦል “ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ፤ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጓቸው” የሚለውን የአምላክን ሕግ ያውቅ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:31) ሆኖም ከጊዜ በኋላ ሳኦል ከይሖዋ ዘወር አለ። ስለዚህም በወቅቱ በሕይወት የነበረው ሳሙኤል ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርሱን ለማየት እምቢ አለ። (1 ሳሙኤል 15:35) አሁን በዚህ የችግር ወቅት ላይ ንጉሥ ሳኦል ይሖዋ እንዲረዳው ያቀረበውን ልመና ስላልሰማለት ምን እንደሚያደርግ ግራ ገብቶታል።
5. (ሀ) ሳኦል ርዳታ ለማግኘት ወዴት ሄደ? (ለ) መናፍስት ጠሪዋ ምን ለማድረግ ቻለች?
5 ሳኦል ምን ሊመጣ እንዳለ ለማወቅ በጣም ስለጓጓ በዓይንዶር ወደምትገኝ መናፍስት ጠሪ ሄደ። እርስዋም ልታየው የምትችለውን የአንድ ሰው ቅርጽ ለማምጣት ቻለች። ስለ ሰውየው ቅርጽ በሰጠችው መግለጫ መሠረት ሳኦል ‘ይህ ሳሙኤል ነው’ የሚል ግንዛቤ ወሰደ። በዚህ ጊዜ ሳሙኤልን መስሎ የቀረበው መንፈሳዊው አካል:- “ለምን አወክኸኝ? ለምንስ አስነሣኸኝ?” ብሎ ተናገረ። ሳኦልም “ፍልስጥኤማውያን ይወጉኛልና እጅግ ተጨንቄአለሁ” ብሎ መለሰለት። መንፈሳዊው አካልም:- “[ይሖዋ (አዓት)] ከራቀህ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ?” አለው። ከዚያ በኋላ የሞተውን ሳሙኤልን መስሎ የቀረበው መንፈሳዊ አካል ከፍልስጥኤማውያን ጋር በሚያደርገው ውጊያ እንደሚገደል ለሳኦል ነገረው።— 1 ሳሙኤል 28:3-19
6. ከሳኦል ጋር የተነጋገረው ሳሙኤል ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?
6 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መናፍስት ጠሪዋ ግንኙነት ያደረገችው ከሳሙኤል ጋር አልነበረም። ሳሙኤል ሞቶ ነበር፤ አንድ ሰው ሲሞት “ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜም [አሳቡ (አዓት)] ሁሉ ይጠፋል።” (መዝሙር 146:4) በጉዳዩ ላይ ትንሽ ምርምር ማድረጉ በዚያን ጊዜ የተሰማው ድምፅ በእርግጥ ሞቶ የነበረው የሳሙኤል ድምፅ እንዳልነበረ የበለጠ ያሳያል። ሳሙኤል የአምላክ ነቢይ ነበር። በመሆኑም መናፍስት ጠሪዎችን ይቃወም ነበር። አስቀድመን እንደተመለከትነውም በሕይወት በነበረበት ጊዜ ታዛዥ ካልነበረው ከሳኦል ጋር ዳግመኛ ለመነጋገር እምቢ ብሎ ነበር። ታዲያ በሕይወት ቢኖር ኖሮ አንዲት መናፍስት ጠሪ ሳሙኤልን ከሳኦል ጋር ለማገናኘት ዝግጅት ብታደርግ እሺ ይላት ነበርን? በተጨማሪም ይሖዋ ለሳኦል ምንም ዓይነት መመሪያ ለመስጠት እምቢ ማለቱን አስብ። አንዲት መናፍስት ጠሪ በሞተው በሳሙኤል በኩል ለሳኦል አንድ መልእክት እንዲሰጥ ይሖዋን ልታስገድደው ትችላለችን? ሕያዋን የሆኑት ከሞቱት ዘመዶቻቸው ጋር በእውነት ለመነጋገር የሚችሉ ቢሆን ኖሮ የፍቅር አምላክ ወደ መናፍስት ጠሪ በመሄዳቸው ‘ረክሳችኋል’ አይላቸውም ነበር።
7. አምላክ ሕዝቡን ከክፉ መናፍስት ለመጠበቅ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጠ?
7 እንደ እውነቱ ከሆነ ክፉ መናፍስት ሰዎችን ለመጉዳት ታጥቀው ተነሥተዋል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ አገልጋዮቹን ለመጠበቅ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣል። የሚከተለውን ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ አንብብ። ጥቅሱ አጋንንት ሰዎችን ለማሳሳት ስለሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ሐሳብ ይሰጥሃል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ምዋርተኛም፥ ሞራ ገላጭም፥ አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቁልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም (ሙታንን የሚጠይቅ ) በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንን የሚያደርግ ሁሉ [በይሖዋ (አዓት)] ፊት የተጠላ ነው።” (ዘዳግም 18:10-12) በዛሬው ጊዜ ክፉ መናፍስት ሰዎችን ለመጉዳት ምን እያደረጉ እንዳሉና ራሳችንን ከእነርሱ እንዴት መጠበቅ እንደምንችል ለማወቅ መፈለግ ይገባናል። ሆኖም ስለዚህ ነገር ከመማራችን በፊት ክፉ መናፍስት መቼና እንዴት ክፉ መሆን እንደጀመሩ እንመርምር።
በኋላ ክፉ መናፍስት የሆኑት መላእክት
8. (ሀ) ሰይጣን እነማንንም ጭምር በአምላክ ላይ አሳመፀ? (ለ) እነርሱስ በሰማይ የነበራቸውን ሥራ ከተዉ በኋላ ወዴት ሄዱ?
8 መልአክ የነበረ አንድ ፍጡር በኤደን ገነት ውስጥ ለሔዋን ውሸት በመናገር ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የሚጠራ ክፉ መንፈስ አደረገ። ከዚያ በኋላ ሌሎችንም መላእክት በአምላክ ላይ ለማሳመፅ መሞከር ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ተሳካለት። አንዳንድ መላእክት አምላክ በሰማይ እንዲሠሩት የሰጣቸውን ሥራ አቆሙና ወደ ምድር በመውረድ ልክ እንደ ሰዎች ሥጋዊ አካል ለበሱ። ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር ይሁዳ “መኖሪያቸውን የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት” ብሎ በጠቀሰ ጊዜ ስለ እነርሱ ጽፏል። (ይሁዳ 6) ወደ ምድር የመጡት ለምን ነበር? በሰማይ የነበራቸውን ጥሩ ቦታ እንዲተዉ ለማድረግ ሰይጣን በውስጣቸው ምን የተሳሳተ ምኞት አሳደረባቸው?
9. (ሀ) መላእክት ለምን ወደ ምድር መጡ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስስ እነርሱ ያደረጉት ነገር ስሕተት እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው?
9 መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ” ብሎ በመናገር መልሱን ይነግረናል። (ዘፍጥረት 6:2) አዎን፤ መላእክት ሥጋዊ አካል ለበሱና ከቆንጆ ሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት ለማድረግ ወደ ምድር መጡ። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለው የጾታ ግንኙነት ለመላእክት ስሕተት ነበር። ይህ ያለ መታዘዝ ድርጊት ነበር። እነርሱ የፈጸሙት ነገር የሰዶምና የጐሞራ ሰዎች የፈጸሙትን የወንድ ከወንድ ግንኙነት ያህል መጥፎ ድርጊት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክተናል። (ይሁዳ 6, 7) ይህስ ምን አስከተለ?
10, 11. (ሀ) መላእክቱ ምን ዓይነት ልጆችን ወለዱ? (ለ) የጥፋቱ ውኃ ሲመጣ ግዙፎቹ ልጆቻቸው ምን ሆኑ? (ሐ) በጥፋቱ ውኃ ጊዜ መላእክቱ ምን ሆኑ?
10 ለእነዚህ መላእክትና ለሚስቶቻቸው ሕፃናት ተወለዱላቸው። ይሁን እንጂ ልጆቹ የተለዩ ዓይነት ነበሩ። ግዙፎች ፤ አዎን ክፉ የሆኑ ግዙፍ ፍጡሮች እስከሚሆኑ ድረስ እያደጉ ሄዱ። መጽሐፍ ቅዱስ እነርሱን “በድሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን” ብሎ ይጠራቸዋል። እነዚህ ግዙፍ ፍጡራን ሰው ሁሉ እንደ እነርሱ ክፉ እንዲሆን ለማስገደድ ይሞክሩ ነበር። ከዚህም የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ “የሰውም ክፋት በምድር ላይ . . . በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ” ሆነ ሲል ይገልጻል። (ዘፍጥረት 6:4, 5) በዚህም ምክንያት ይሖዋ የጥፋት ውኃ አመጣ። ግዙፎቹ ፍጡራን ወይም “ኔፊሊሞች” እና ክፉ የሆኑት ሰዎች ሁሉ ሰጥመው ጠፉ። ወደ ምድር መጥተው የነበሩት መላእክትስ ምን ሆኑ?
11 እነርሱ አልሰጠሙም። ሥጋዊ አካላቸውን ጣሉና መንፈሳዊ አካል በመሆን ወደ ሰማይ ተመለሱ። ሆኖም እንደገና የአምላክ ቅዱሳን መላእክት ድርጅት ክፍል እንዲሆኑ አልተፈቀደላቸውም። በዚያ ፋንታ ግን መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ (እንጦሮጦስ) ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ” እንደ ሰጣቸው ይናገራል።— 2 ጴጥሮስ 2:4
12. (ሀ) ክፉዎቹ መላእክት ወደ ሰማይ ሲመለሱ ምን ደረሰባቸው? (ለ) እንደገና የሰው አካል ሊለብሱ የማይችሉት ለምንድን ነው? (ሐ) ስለዚህ አሁን ምን እያደረጉ ነው?
12 እነዚህ ክፉ መላእክት ቃል በቃል እንጦሮጦስ ተብሎ ወደሚጠራ ቦታ አልተጣሉም። ከዚህ ይልቅ በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ በተሳሳተ መንገድ “ሲኦል” (“ገሃነም”) ተብሎ የተተረጎመው እንጦሮጦስ የእነዚህን መላእክት ዝቅ መደረግ ወይም የመዋረድ ሁኔታን ያመለክታል። የአምላክ ድርጅት የሚያገኘው መንፈሳዊ ብርሃን ተቋርጦባቸዋል፤ የሚጠብቃቸውም ዘላለማዊ ጥፋት ብቻ ነው። (ያዕቆብ 2:19፤ ይሁዳ 6) ከጥፋት ውኃ ወዲህ እነዚህ አጋንንታዊ መላእክት ሥጋዊ አካል እንዲለብሱ አምላክ አልፈቀደላቸውም። ስለዚህ ከተፈጥሮአቸው ውጭ የሆነውን የጾታ ምኞታቸውን በቀጥታ ለማርካት አይችሉም። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በወንዶችና በሴቶች ላይ አደገኛ የሆነ ግፊት ሊያደርጉ ይችላሉ። እንዲያውም በእነዚህ አጋንንት እርዳታ ሰይጣን ‘ጠቅላላውን ዓለም እያሳተ ነው።’ (ራእይ 12:9) በዛሬው ጊዜ የጾታ ወንጀሎች፣ ዓመፅና ሌሎች መጥፎ ድርጊቶች በጣም መጨመራቸው እነርሱ እንዳያሳስቱን ራሳችንን መጠበቅ እንደሚያስፈልገን ያሳያል።
ክፉ መናፍስት እንዴት እንደሚያስቱ
13. (ሀ) ክፉ መናፍስት የሚያስቱት እንዴት ነው? (ለ) መናፍስትነት ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስስ ስለ እርሱ ምን ይላል?
13 ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” እንደመሆኑ መጠን፣ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች እንዳይታዩአቸው በዓለማውያን መንግሥታትና በሐሰት ሃይማኖት አማካኝነት እንዳሳወራቸው ቀደም ብለን ተምረናል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ክፉ መናፍስት ወንዶችንና ሴቶችን የሚያስቱበት ሌላው ትልቅ መንገድ መናፍስትነት ነው። መናፍስትነት ምንድን ነው? ከክፉ መንፈሳዊ አካሎች ጋር በቀጥታ ወይም በሰብዓዊ አገናኝ አማካኝነት ግንኙነት ማድረግ ማለት ነው። መናፍስትነት አንድን ሰው በአጋንንት ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ከመናፍስትነት ጋር ግንኙነት ካለው ከማንኛውም ድርጊት እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል።— ገላትያ 5:19-21፤ ራእይ 21:8
14. (ሀ) ምዋርት ምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እርሱ ምን ይላል?
14 በጣም ከተለመዱት የመናፍስትነት ሥራዎች አንዱ ምዋርት ነው። ምዋርት በማይታዩ መንፈሳዊ አካላት ርዳታ ስለ ወደፊቱ ወይም ስለ አንድ ያልታወቀ ነገር ለማወቅ የሚደረግ ሙከራ ነው። ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር ሉቃስ:- “የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶቿም እየጠነቆለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን” ሲል የጻፈው ቃል ይህንን ያሳያል። ሐዋርያው ጳውሎስ ልጅቷን ከዚህ ክፉ መንፈስ እጅ ሊያላቅቃት ችሏል። ከዚያ በኋላ ስለ ወደፊቱ ለመተንበይ አልቻለችም።— ሥራ 16:16-19
15. (ሀ) ከመናፍስትነት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) እንደነዚህ ባሉ ነገሮች መሳተፉ ለምን አደገኛ ነው?
15 ብዙ ሰዎች ምሥጢራዊና እንግዳ ነገር በመሆኑ ለመናፍስትነት ጉጉት ያድርባቸዋል። ስለዚህም በጥንቆላ፣ በዛር፣ በድግምት፣ በአስማት፣ በኮከብ ቆጠራ፣ በአውደ ነገሥት፣ ወይም ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ግንኙነት ባለው በሌላ ነገር ይሳተፋሉ። ስለ እነዚህ ነገሮች መጻሕፍትን ያነባሉ፤ ወይም ፊልሞችን ያያሉ፤ ወይም ስለ እነዚህ የተዘጋጀውን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ይከታተሉ ይሆናል። እንዲሁም ከመናፍስት ጋር አገናኝ የሆነ ሰው ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ግንኙነት ወደሚያደርግበት ስብሰባ ይሄዱ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል ለሚፈልገው ሰው ጥበብ አይደለም። አደገኛም ነው። አሁንም ቢሆን ወደ ችግር ሊመራው ይችላል። በተጨማሪም አምላክ መናፍስታዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙትን ይፈርድባቸዋል፤ ከራሱም ያርቃቸዋል።— ራእይ 22:15
16. ክርስቲያኖች ከክፉ መናፍስት ጋር ውጊያ እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?
16 አንድ ሰው ከመናፍስትነት ለመራቅ የተቻለውን ሁሉ ቢጥርም የክፉ መናፍስት ጥቃት ሊደርስበት ይችል ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስ የዲያብሎስን ድምፅ እንደሰማ አስታውስ። የአምላክን ሕግ እንዲያፈርስ ተናግሮታል። (ማቴዎስ 4:8, 9) ሌሎች የአምላክ አገልጋዮችም እንደዚህ ያለ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “መጋደላችን . . . በሰማያዊ ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው” ብሏል። ይህም እያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ ይህንን ‘ለመቋቋም እንዲችል ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ዕቃ ማንሣት’ ይኖርበታል ማለት ነው።— ኤፌሶን 6:11-13
የክፉ መናፍስትን ጥቃት መቋቋም
17. ከመንፈሳዊው ዓለም አንድ “ድምፅ” ቢያነጋግርህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
17 ከመንፈሳዊው ዓለም አንድ “ድምፅ” ቢያነጋግርህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የሰማኸውስ “ድምፅ” የአንድ የሞተ ዘመድህ ወይም የጥሩ መንፈስ ድምፅ ቢመስል ምን ታደርጋለህ? ኢየሱስ “የአጋንንት አለቃ” ባነጋገረው ጊዜ ምን አደረገ? (ማቴዎስ 9:34) “ሂድ አንተ ሰይጣን!” አለው። (ማቴዎስ 4:10) አንተም እንደዚያ ልታደርግ ትችላለህ። እንዲሁም እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ልትጮኽ ትችላለህ። በአምላክ ስም በመጠቀም ጮክ ብለህ ጸልይ። እርሱ ከክፉ መናፍስት ሁሉ ይበልጥ ኃያል መሆኑን አስታውስ። ይህንን የጥበብ መንገድ ተከተል። ከመንፈሳዊው ዓለም የሚመጡትን እንደነዚህ ያሉትን ድምፆች አታዳምጥ። (ምሳሌ 18:10፤ ያዕቆብ 4:7) እንደዚህ ሲባል ግን “ድምፅ” የሚሰማ ሰው ሁሉ አጋንንቶች አነጋገሩት ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በአንድ ዓይነት አካላዊ ወይም አእምሮአዊ ሕመም ምክንያት እንደዚህ ዓይነት ድምፅ ሊሰሙ ይችላሉ።
18. አንድ ሰው ከመናፍስትነት ለመላቀቅ ከፈለገ በድሮ ጊዜ የነበሩት የኤፌሶን ክርስቲያኖች ያሳዩትን የትኛውን ምሳሌ ቢከተል ጥሩ ነው?
18 ምናልባት በአንድ ዓይነት የመናፍስትነት ድርጊት ስትሳተፍ ቆይተህ፣ አሁን ከዚህ ለመላቀቅ ትፈልግ ይሆናል። ምን ልታደርግ ትችላለህ? በኤፌሶን የነበሩትን የጥንት ክርስቲያኖች ምሳሌ አስብ። ሐዋርያው ጳውሎስ የሰበከላቸውን “የይሖዋን ቃል” ከተቀበሉ በኋላ ስላደረጉት ነገር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ከአስማተኞችም ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት።” እነዚህ መጻሕፍት ዋጋቸው 50, 000 ጥሬ ብር ነበር።” (ሥራ 19:19, 20) በቀጥታ ከመናፍስትነት ጋር ግንኙነት ያላቸው ዕቃዎች ካሉህ ምንም ያህል ውድ ቢሆኑም እነዚህን በኤፌሶን የነበሩ የክርስቶስ ተከታዮች በመምሰል ኰተቶቹን ማጥፋቱ የጥበብ መንገድ ነው።
19. (ሀ) በመናፍስትነት ድርጊት የሚሳተፉ አብዛኞቹ ሰዎች ምን የማያውቁት ነገር አለ? (ለ) በምድር ላይ በደስታ ለዘላለም መኖር ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
19 በአሁኑ ጊዜ አዲስና ምሥጢራዊ ስለሆኑ ነገሮች ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ስላለ በመናፍስትነት ድርጊቶች የሚጠመዱ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ሄዷል። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ካሉት መካከል አብዛኞቹ ከክፉ መናፍስት ጋር ግንኙነት እያደረጉ እንዳሉ አያውቁም። ይህ ነገር ምንም ጉዳት የማያመጣ ጨዋታ አይደለም። ክፉ መናፍስት ለማሰቃየትና ለመጉዳት ኃይል አላቸው። ጨካኞች ናቸው። ክርስቶስ እነርሱን በዘላለም ጥፋት ከማሰሩ በፊትም ሰዎችን በክፉ ኃይላቸው ስር ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ ይጥራሉ። (ማቴዎስ 8:28, 29) እንግዲያው ክፋት ሁሉ ከጠፋ በኋላ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ለመኖር የምትፈልግ ከሆነ ከየትኛውም ዓይነት የመናፍስትነት ድርጊት በመራቅ ከአጋንንት ኃይል ነፃ መሆን ያስፈልግሃል።
[በገጽ 91 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአይንዶር የነበረችው መናፍስት ጠሪ ግንኙነት ያደረገችው ከማን ጋር ነው?
[በገጽ 92, 93 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
መላእክት የሆኑት የአምላክ ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ተመለከቱ
[በገጽ 94 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሥጋ የለበሱት መላእክት በውኃው ሰጥመው አልጠፉም። ሥጋዊ አካላቸውን ጣሉና ወደ ሰማይ ተመለሱ
[በገጽ 97 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከማንኛውም ዓይነት የመናፍስትነት ድርጊት ራቁ’ ሲል ያስጠነቅቀናል
[በገጽ 98 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኤፌሶን ውስጥ ወደ ክርስትና እምነት የገቡ ሰዎች የመናፍስትነት መጻሕፍታቸውን በእሳት አቃጠሉ። በዚህም ዛሬ ለምንገኘው ጥሩ ምሳሌ ሆነዋል።