‘ከክርስቶስ ጋር በአንድነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ’
“እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ [“ከእርሱ ጋር በአንድነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ፣” NW]።”—ቆላስይስ 2:6
1, 2. (ሀ) ሄኖክ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ያሳለፈውን ሕይወት መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) ቆላስይስ 2:6, 7 እንደሚያመለክተው ይሖዋ ከእርሱ ጋር እንድንመላለስ የረዳን እንዴት ነው?
አንድ ትንሽ ልጅ ከአባቱ ጋር በእግሩ ሲሄድ ተመልክተሃልን? ትንሹ ልጅ ፊቱ በአድናቆት ፈክቶ እያንዳንዱን የአባቱን እንቅስቃሴ ይኮርጃል። አባትየውም በፍቅርና በደስታ አብሮት እንዲራመድ ይረዳዋል። ይሖዋ እርሱን በታማኝነት የሚያገለግሉት ሰዎችን ሕይወት በተመሳሳይ መንገድ መግለጹ ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል የአምላክ ቃል ታማኝ የነበረው ሄኖክ ‘አካሄዱን ከእውነተኛው አምላክ ጋር አደረገ’ በማለት ይገልጻል።—ዘፍጥረት 5:24፤ 6:9
2 አንድ አሳቢ የሆነ አባት ልጁ አብሮት በእግሩ እንዲሄድ እንደሚረዳው ሁሉ ይሖዋም ከሁሉ የተሻለውን እርዳታ ሰጥቶናል። አንድያ ልጁን ወደ ምድር ልኮታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በሕይወት በነበረበት ጊዜ በእያንዳንዱ እርምጃው ሰማያዊ አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐንስ 14:9, 10፤ ዕብራውያን 1:3) ስለዚህ ከአምላክ ጋር ለመመላለስ ከኢየሱስ ጋር መመላለስ ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፣ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፣ ምስጋናም ይብዛላችሁ [“በብዙ አመስግኑ፣” የ1980 ትርጉም]” ሲል ጽፏል።—ቆላስይስ 2:6, 7
3. በቆላስይስ 2:6, 7 መሠረት ከክርስቶስ ጋር በአንድነት መመላለስ ማለት መጠመቅ ማለት ብቻ አይደለም ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
3 ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከክርስቶስ ጋር በአንድነት ለመራመድና ፍጹም የሆነ ዱካውን ለመከተል ስለሚፈልጉ ይጠመቃሉ። (ሉቃስ 3:21፤ ዕብራውያን 10:7-9) በ1997 ብቻ በዓለም ዙሪያ ከ375,000 የሚበልጡ ሰዎች ይህን ወሳኝ እርምጃ ወስደዋል። ይህ ደግሞ በአማካይ በየቀኑ ከ1,000 የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀዋል ማለት ነው። ይህ እድገት እጅግ የሚያስደንቅ ነው! ይሁን እንጂ በቆላስይስ 2:6, 7 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት እንደሚያሳዩት ከክርስቶስ ጋር በአንድነት መመላለስ ማለት መጠመቅ ማለት ብቻ አይደለም። “ተመላለሱ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል መቋረጥ የሌለበትን፣ ቀጣይነት ያለውን ድርጊት ያመለክታል። ከዚህም በላይ ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር በአንድነት መመላለስ አራት ነገሮችን ማለትም በክርስቶስ ሥር መስደድን፣ በእርሱ መታነጽን፣ በእምነት መጽናትንና አብዝቶ ማመስገንን የሚያካትት መሆኑን ጨምሮ ገልጿል። እያንዳንዱን ሐረግ በመመርመር ከክርስቶስ ጋር በአንድነት ለመመላለስ እንዴት ሊረዳን እንደሚችል እንመልከት።
‘በክርስቶስ ሥር ሰዳችኋልን’?
4. ‘በክርስቶስ ሥር መስደድ’ ማለት ምን ማለት ነው?
4 በመጀመሪያ ጳውሎስ ‘በክርስቶስ ሥር መስደድ’ እንዳለብን ጽፏል። (ከማቴዎስ 13:20, 21 ጋር አወዳድር።) አንድ ሰው በክርስቶስ ሥር ለመስደድ ምን ማድረግ ይችላል? የአንድ ተክል ሥሮች ከእይታ የተሰወሩ ቢሆኑም ተክሉን ቀጥ አድርገው ስለሚያቆሙትና አስፈላጊውን ምግብ ስለሚያቀብሉት ለተክሉ ሕልውና ወሳኝ ነገሮች ናቸው። በተመሳሳይም የክርስቶስ ትምህርትና የተወልን ምሳሌ በመጀመሪያ በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ ተተክለው ውስጣዊ ለውጥ ያመጡልናል። በመንፈሳዊ እንድናድግና እንድንጠነክር ይረዱናል። አስተሳሰባችን፣ ድርጊታችንና ውሳኔያችን በእነዚህ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ሕይወታችንን ለይሖዋ ለመወሰን እንገፋፋለን።—1 ጴጥሮስ 2:21
5. ለመንፈሳዊ ምግቦች ‘ጉጉት’ እንዲያድርብን ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ ከአምላክ የሚገኘውን እውቀት ይወድ ነበር። ከምግብ ጋር ሳይቀር አመሳስሎታል። (ማቴዎስ 4:4) እንዲያውም በተራራ ስብከቱ ላይ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙ ስምንት የተለያዩ መጻሕፍት 21 ጊዜ ጠቅሷል። የእሱን ምሳሌ ለመከተል ሐዋርያው ጴጥሮስ “አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት” መንፈሳዊ ምግብን “ተመኙ” ሲል የሰጠውን ምክር በጥብቅ መከተል አለብን። (1 ጴጥሮስ 2:2) አንድ አዲስ የተወለደ ሕፃን ምግብ በሚፈልግበት ጊዜ ፍላጎቱን ከማሳወቅ ወደ ኋላ አይልም። በአሁኑ ጊዜ እኛም ለመንፈሳዊ ምግብ ተመሳሳይ ፍላጎት ከሌለን እንዲህ ያለውን ምኞት ‘እንድናዳብር’ የጴጥሮስ ቃላት ያበረታቱናል። እንዴት? በመዝሙር 34:8 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው “እግዚአብሔር ቸር [“ጥሩ፣” NW] እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ሊረዳን ይችላል። ምናልባትም በየቀኑ የተወሰነ ክፍል በማንበብ የይሖዋን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ‘የምንቀምስ’ ከሆነ በመንፈሳዊ የሚገነባና ጥሩ መሆኑን ልንገነዘብ እንችላለን። ውሎ አድሮ ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለን ጉጉት ያድጋል።
6. ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
6 ይሁን እንጂ የበላነው ምግብ ሰውነታችን ውስጥ በደንብ መፈጨት አለበት። ስለዚህ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ያስፈልገናል። (መዝሙር 77:11, 12) ለምሳሌ ያህል እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተሰኘውን መጽሐፍ ስናነብ ቆም እያልን ራሳችንን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ብንጠይቅ ከእያንዳንዱ ምዕራፍ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን እንችላለን:- ‘በዚህ ታሪክ ላይ የማየው የትኛውን የክርስቶስ ባሕርይ ነው? እኔም ይህን ባሕርይ በሕይወቴ ላንጸባርቅ የምችለው እንዴት ነው?’ በዚህ መልኩ ማሰላሰል የተማርነውን ነገር በተግባር ለማዋል ያስችለናል። ከዚያም ውሳኔ ማድረግን የሚጠይቅ ጉዳይ ሲያጋጥመን ኢየሱስ ቢሆን ኖሮ ምን ያደርግ እንደነበር ራሳችንን እንጠይቃለን። በዚህ መሠረት ውሳኔ የምናደርግ ከሆነ በክርስቶስ ሥር የሰደድን መሆናችንን እናረጋግጣለን።
7. ስለ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ያለን አመለካከት ምን መሆን አለበት?
7 በተጨማሪም ጳውሎስ “ጠንካራ ምግብ” ማለትም የአምላክን ቃል ጥልቅ እውነቶች እንድንመገብ አጥብቆ መክሯል። (ዕብራውያን 5:14) በዚህ ረገድ የመጀመሪያው ግባችን መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብቦ መጨረስ ሊሆን ይችላል። ከዚያም የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕትን፣ ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር የገባውን የተለያዩ ቃል ኪዳኖች ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ትንቢታዊ መልእክቶችን የመሳሰሉ የተወሰኑ የጥናት ርዕሶች አሉ። ይህን የመሰለውን ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብና ለመፍጨት የሚረዱን በርካታ ጽሑፎች አሉ። እንዲህ ያለውን እውቀት የምንወስደው ለምንድን ነው? ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማጎልበትና ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ እንጂ ጉራችንን ለመንዛት መሆን የለበትም። (1 ቆሮንቶስ 8:1፤ ያዕቆብ 4:8) ይህንን እውቀት በጉጉት የምንመገብ፣ በተግባር የምንተረጉምና ሌሎችን ለመርዳት የምንጠቀምበት ከሆነ ክርስቶስን በእርግጥ እየመሰልነው ነው። ይህ በትክክል በእርሱ ሥር እንድንሰድ ይረዳናል።
‘በክርስቶስ እየታነጻችሁ ነው?’
8. ‘በክርስቶስ ላይ መታነጽ’ ማለት ምን ማለት ነው?
8 ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር በአንድነት የመመላለስን ተከታይ ዘርፍ ለመግለጽ ስለ ተክል ይናገር የነበረውን ምሳሌ አቁሞ ወዲያው ስለ ሕንፃ መናገር ጀመረ። በመገንባት ላይ ስላለ አንድ ሕንፃ ስናስብ ስለ መሠረቱ ብቻ ሳይሆን ከብዙ ድካም በኋላ ከፍ ብሎ በመውጣት ለእይታ ግልጽ ስለሚሆነው የሕንፃው መዋቅር እናስባለን። በተመሳሳይም የክርስቶስን ዓይነት ባሕርያትና ልማዶች ለማዳበር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ‘የምታደርገውን መሻሻል ሰዎች ሁሉ ይዩት’ ብሎ የጻፈለት መሆኑ እንዲህ ዓይነቱ ጥረት በሌሎች ዘንድ መታየቱ እንደማይቀር ያሳያል። (1 ጢሞቴዎስ 4:15፤ ማቴዎስ 5:16) ሊገነቡን የሚችሉ አንዳንድ ክርስቲያናዊ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?
9. (ሀ) በአገልግሎታችን ክርስቶስን ለመኮረጅ እንድንችል የትኞቹን ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ግቦች ልናወጣ እንችላለን? (ለ) ይሖዋ በአገልገሎታችን እንድንደሰት እንደሚፈልግ እንዴት ልናውቅ እንችላለን?
9 ኢየሱስ ምሥራቹን የመስበክና የማስተማር ሥራ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በድፍረትና ውጤታማ በሆነ መንገድ በመመሥከር ፍጹም የሆነ ምሳሌ ትቶልናል። እርግጥ ነው ልክ እንደ እሱ ጥሩ በሆነ መንገድ አንሠራውም። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚከተለውን ግብ በፊታችን አስቀምጦልናል:- “ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፣ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 3:15) ‘መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ’ እንደሆናችሁ ካልተሰማችሁ ተስፋ አትቁረጡ። ቀስ በቀስ ወደዚህ ደረጃ የሚያደርሷችሁን ምክንያታዊ ግቦች አውጡ። አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ አቀራረባችሁን እንድትለዋውጡና አንድ ወይም ሁለት ጥቅስ አውጥታችሁ እንድታነቡ ሊረዳችሁ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በብዛት ለማበርከት፣ ብዙ ተመላልሶ መጠይቆችን ለማድረግ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ግብ ልታወጡ ትችላላችሁ። በዋነኛነት ሊያሳስበን የሚገባው ጉዳይ የምንመልሰው ሰዓት፣ የምናበረክተው ጽሑፍ ወይም የጥናቶቻችን ብዛት ብቻ ሳይሆን ጥራቱም ነው። ምክንያታዊ ግቦችን በማውጣት እነርሱ ላይ ለመድረስ መጣራችን ራሳችንን ለአገልግሎቱ በመስጠታችን እንድንደሰት ያስችለናል። ይሖዋ የሚፈልገው ‘በደስታ’ እንድናገለግለው ነው።—መዝሙር 100:2፤ ከ2 ቆሮንቶስ 9:7 ጋር አወዳድር።
10. ልንፈጽማቸው የሚገቡ አንዳንድ ክርስቲያናዊ ተግባራት ምንድን ናቸው? እነዚህስ የሚረዱን እንዴት ነው?
10 በክርስቶስ ላይ የሚገነቡን በጉባኤ ውስጥ የምናከናውናቸው ተግባራትም አሉ። ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆነው ነገር የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት የሆነውን ፍቅር አንዳችን ለሌላው ማሳየት ነው። (ዮሐንስ 13:34, 35) ጥናቶች በነበርንበት ጊዜ ከአስጠኚያችን ጋር ይበልጥ መቀራረባችን ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ አሁን በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ወንድሞች ጋር በመተዋወቅ ጳውሎስ “ተስፋፉ” ሲል የሰጠውን ምክር ልንከተል እንችላለን? (2 ቆሮንቶስ 6:13) ሽማግሌዎች ጭምር ፍቅራችንና አድናቆታችን ሊቸራቸው ይገባል። ከእነርሱ ጋር በመተባበር፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክራቸውን በመሻትና በሥራ ላይ በማዋል ድካማቸውን ልናቀልላቸው እንችላለን። (ዕብራውያን 13:17) የዚያኑ ያህል ደግሞ ይህ በክርስቶስ ላይ ለመገንባት ለምናደርገው ጥረት አስተዋጽኦ ያደርጋል።
11. ስለ ጥምቀት ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ምንድን ነው?
11 በምንጠመቅበት ወቅት በጣም ደስ ይለናል! ሆኖም ከዚያ በኋላ በሕይወታችን ውስጥ ምንም ችግር አይገጥመንም ማለት አይደለም። በክርስቶስ ላይ መገንባታችን በአብዛኛው የተመካው ‘በደረስንበት የእድገት ደረጃ በዚያው መመላለሳችንን በመቀጠላችን ላይ ነው።’ (ፊልጵስዩስ 3:16) ይህ ማለት አሰልቺ የሆነ ሕይወት መምራት ማለት አይደለም። በቀላል አነጋገር ቀጥ ባለ መስመር ላይ ወደፊት መራመድ ማለት ነው። በሌላ አባባል ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶችን ማዳበር እንዲሁም ቀናትና ዓመታት ባለፉ ቁጥር ልማዶቹን ጠብቆ መቆየት ማለት ነው። “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” የሚሉትን ቃላት አስታውሱ።—ማቴዎስ 24:13
‘በእምነት ጸንታችኋል?’
12. ‘በእምነት መጽናት’ ማለት ምን ማለት ነው?
12 ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር በአንድነት ስለ መመላለሳችን ለመግለጽ በተጠቀመበት ሦስተኛ ሐረግ ላይ ‘በእምነት የጸናን’ እንድንሆን አጥብቆ መክሯል። ጳውሎስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል “እውነት መሆኑን ማረጋገጥ፣ ዋስትና መስጠትና ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዳይሻር ማድረግ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ስለሚችል አንድ ትርጉም “እምነታችን እውነት መሆኑን እርግጠኛ መሆን” በማለት አስቀምጦታል። በእውቀት ስናድግ በይሖዋ አምላክ ላይ ያለን እምነት ጽኑ መሠረት ያለውና ሕጋዊ ለመሆኑ ተጨማሪ ምክንያቶችን እናገኛለን። ከዚህም የተነሣ ይበልጥ ጽኑ እንሆናለን። የሰይጣን ዓለም በቀላሉ እንድንዋዥቅ ሊያደርገን አይችልም። ይህ ደግሞ ጳውሎስ ‘ወደ ጉልምስና እንድንገፋ’ የሰጠውን ምክር ያስታውሰናል። (ዕብራውያን 6:1) ጉልምስናና ጽኑ አቋም እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው።
13, 14. (ሀ) የመጀመሪያው መቶ ዘመን የቆላስይስ ክርስቲያኖች በነበራቸው ጽኑ አቋም ላይ አንዣበው የነበሩትን የትኞቹን አደጋዎች ተቋቁመዋል? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስን ምን ነገር አሳስቦት መሆን አለበት?
13 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የቆላስይስ ክርስቲያኖች በነበራቸው ጽኑ አቋም ላይ አንዣበው የነበሩትን አደጋዎች ተቋቁመዋል። ጳውሎስ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ” ሲል አስጠንቅቋል። (ቆላስይስ 2:8) ጳውሎስ ‘የአምላክ ፍቅር ልጅ መንግሥት’ ተገዥዎች የሆኑትን የቆላስይስ ሰዎች በረከት ካገኙበት መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲወሰዱ ወይም እንዲወጡ አልፈለገም ነበር። (ቆላስይስ 1:13) ሊታለሉ የሚችሉት በምን ነበር? ጳውሎስ ‘ፍልስፍና’ በማለት የጠቀሰ ሲሆን ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው በዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው። ጳውሎስ እንደ ፕላቶና ሶቅራጥስ ስላሉት የግሪክ ፈላስፎች መናገሩ ነበርን? በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ለእውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያሰጉ ቢሆኑም በዚያ ዘመን ‘ፍልስፍና’ የሚለው ቃል ሰፊ ትርጉም ነበረው። ቃሉ በአጠቃላይ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ (ሃይማኖታዊም ሊሆን ይችላል) ያላቸውን ቡድኖችና ግለሰቦች ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል እንደ ጆሴፈስና ፊሎ ያሉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያን ሃይማኖታቸውን ፍልስፍና ብለው ይጠሩ ነበር፤ ይህንንም የሚያደርጉት ይበልጥ ተወዳጅ እንዲሆን በማሰብ ሊሆን ይችላል።
14 ጳውሎስን ያሳሰቡት አንዳንድ ፍልስፍናዎች ሃይማኖት ነክ ሳይሆኑ አይቀሩም። ቆየት ብሎ ለቆላስይስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ በዚያው ምዕራፍ ላይ “አትያዝ፣ አትቅመስ፣ አትንካ” ብለው በማስተማር በክርስቶስ ሞት የተቋረጠውን የሙሴን ሕግ በተዘዋዋሪ መንገድ ስለሚጠቅሱ ሰዎች ተናግሯል። (ሮሜ 10:4) ከእነዚህ አረማዊ ፍልስፍናዎች በተጨማሪ የጉባኤውን መንፈሳዊነት አደጋ ላይ የጣሉ ሌሎች ተጽእኖዎች ነበሩ። (ቆላስይስ 2:20-22) ጳውሎስ ‘ዓለማዊ የመጀመሪያ ትምህርት’ ክፍል ከሆነው ፍልስፍና የመራቅን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። እንዲህ ያለው የሐሰት ትምህርት ምንጩ ሰው ነው።
15. ዘወትር በሚያጋጥመን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አስተሳሰብ እንዳንወሰድ ምን ልናደርግ እንችላለን?
15 በአምላክ ቃል ላይ ጠንካራ መሠረት የሌላቸውን ሰብዓዊ ሐሳቦችና አመለካከቶች ማራመድ በክርስቲያናዊ ጽኑ አቋም ላይ አደጋ ይፈጥራል። እኛ ዛሬ ከእንዲህ ዓይነቱ አደጋ ለመራቅ ጠንቃቃ መሆን ይገባናል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ወዳጆች ሆይ፣ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፣ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ዮሐንስ 4:1) ስለዚህ አብራችሁት የምትማሩት ልጅ የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃዎች ጠብቆ መኖር ኋላ ቀርነት ነው በማለት ሊያሳምናችሁ ቢሞክር ወይም ጎረቤታችሁ ቁሳዊ ነገሮችን እንድታሳድዱ ግፊት ቢያደርግባችሁ ወይም የሥራ ባልደረባችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናችሁን እንድትጥሱ ሆን ብሎ ቢጫናችሁ ወይም ደግሞ አንድ የእምነት ወንድማችሁ በራሱ አመለካከት ላይ ተንተርሶ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ወንድሞች ቢተችና ቢያንቋሽሽ የተናገረውን ሁሉ ዝም ብላችሁ አትቀበሉ። ከአምላክ ቃል ጋር የማይስማማውን ሁሉ ለይታችሁ አውጡ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ጽኑ አቋማችንን ጠብቀን ከክርስቶስ ጋር በአንድነት መመላለስ እንችላለን።
“በብዙ አመስግኑ”
16. ከክርስቶስ ጋር በአንድነት የመመላለስ አራተኛው ዘርፍ ምንድን ነው? የትኞቹንስ ጥያቄዎች ልንጠይቅ እንችላለን?
16 ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር በአንድነት የመመላለስን አራተኛ ዘርፍ ሲጠቅስ “በብዙ አመስግኑ” ብሏል። (ቆላስይስ 2:7 የ1980 ትርጉም) “በብዙ” ተብሎ የተተረጎመው ኦቨርፍሎው የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ሞልቶ የሚፈስን ወንዝ ሊያስታውሰን ይችላል። ይህ ደግሞ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን አመስጋኝነታችን ቀጣይ ወይም ልማዳዊ ነገር መሆን እንዳለበት ያሳስበናል። እያንዳንዳችን ‘አመስጋኝ ነኝን?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።
17. (ሀ) በኃዘን ወይም በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ሁላችንም አመስጋኝነታችንን ልንገልጽባቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች አሉ ልንል የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) በውስጥህ የአመስጋኝነት ስሜት የሚያሳድሩብህ የይሖዋ ስጦታዎች ምንድን ናቸው?
17 ሁላችንም ለይሖዋ በየቀኑ የተትረፈረፈ ምስጋና የምናቀርብበት በቂ ምክንያት እንዳለን የተረጋገጠ ነው። ሌላው ቀርቶ በኃዘን ወይም በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ እፎይ እንድንል የሚያደርጉን አንዳንድ ቀላል ነገሮች ይኖራሉ። አንድ ወዳጃችን ችግራችንን ተረድቶ አዘኔታ ያሳየን ይሆናል። አንድ የምንወደው ሰው አይዞህ በርታ በሚል ስሜት ትከሻችንን መታ መታ ያደርገን ይሆናል። ጥሩ እንቅልፍ ተኝተን ስናድር ኃይላችን ታድሶ እንነሳለን። ጥሩ ምግብ የሚሞረሙርን ረሃብ ያስወግዳል። የአእዋፍ ዝማሬ፣ የሕፃን ልጅ ሳቅ፣ ጥርት ያለ ሰማይ፣ መንፈስን የሚያድስ ነፋሻ አየር የመሳሰሉት ሌሎች በርካታ ነገሮች በአንድ ቀን ብቻ እንኳ የምንደሰትባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ የመሳሰሉት ስጦታዎች እንደ ቀላል ነገር ሊታዩ ይችላሉ። ስለነዚህ ነገሮች ሁሉ አመሰግናለሁ ማለት አይገባንም? እነዚህ ነገሮች በሙሉ ‘የበጎ ስጦታና የፍጹም በረከት ሁሉ’ ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ የተገኙ ናቸው። (ያዕቆብ 1:17) ይሖዋ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች የሚያስንቁ ስጦታዎችንም ሰጥቶናል። ለምሳሌ ያህል ሕይወትን የመሰለ ድንቅ ስጦታ ሰጥቶናል። (መዝሙር 36:9) ከዚህም በላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ከፍቶልናል። ይህንን ስጦታ ለመስጠት ሲል ደግሞ ይሖዋ ‘የሚወደውን’ አንድያ ልጁን በመላክ ከሁሉ የላቀ መሥዋዕት እንዲሆን አድርጎታል።—ምሳሌ 8:30 NW፤ ዮሐንስ 3:16
18. ለይሖዋ አመስጋኞች መሆናችንን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
18 በመሆኑም “እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ምንኛ ትክክል ናቸው። (መዝሙር 92:1) ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ጳውሎስ በተሰሎንቄ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን “በሁሉ አመስግኑ” በማለት አሳስቧቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:18፤ ኤፌሶን 5:20፤ ቆላስይስ 3:15) እያንዳንዳችን ይበልጥ አመስጋኞች ለመሆን ቆርጠን ልንነሳ እንችላለን። ጸሎታችን ስለሚያስፈልጉን ነገሮች አምላክን መለመን ብቻ መሆን የለበትም። በጸሎታችን አንዳንድ የምንፈልጋቸውን ነገሮች መጠየቅ ምንም ስህተት የለውም። ይሁን እንጂ የሚፈልገው ነገር ሲኖር ብቻ የሚያነጋግራችሁ ጓደኛ ቢኖራችሁ ምን እንደሚሰማችሁ እስቲ አስቡት! ስለዚህ ይሖዋን ለማመስገንና ለማወደስ ስትሉ ብቻ ለምን አትጸልዩም? ይህን ምስጋና ቢስ ዓለም ከላይ ሆኖ ሲመለከት እንዲህ ያሉ ጸሎቶች ምን ያህል ያስደስቱት ይሆን! የእነዚህ ጸሎቶች ሁለተኛው ጥቅም ደግሞ የሕይወትን መልካም ጎኖች እንድንመለከትና ምን ያህል የተባረክን መሆናችንን እንድናስተውል ይረዱናል።
19. ጳውሎስ በቆላስይስ 2:6, 7 ላይ የተጠቀመበት አነጋገር ሁላችንም ከክርስቶስ ጋር በአንድነት መመላለሳችንን እንድንቀጥል የሚያሳስበን እንዴት ነው?
19 በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኝ በአንድ ምንባብ ላይ ብቻ በጥበብ የተሞላ መመሪያ የሚገኝ መሆኑ አያስገርምም? ጳውሎስ እያንዳንዳችን ከክርስቶስ ጋር በአንድነት መመላለሳችንን እንድንቀጥል የሰጠውን ምክር ልብ ልንለው ይገባል። ‘በክርስቶስ ሥር መስደድ፣’ ‘በእርሱ ላይ መታነጽ፣’ ‘በእምነት መጽናትና’ ‘የተትረፈረፈ ምስጋና ማቅረብ’ ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን። እንዲህ ያለው ምክር በተለይ ለአዲስ ተጠማቂዎች አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ምክሩ ለሁላችንም ይሠራል። አንድ ዋና ሥር እንዴት ወደ ታች እየጠለቀ እንደሚሄድና አንድ ሕንፃ ደግሞ ቁመቱ እንዴት ወደ ላይ እንደሚጨምር አስቡ። ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር መመላለስ ማቆሚያ የለውም። እድገት ለማድረግ ሰፊ አጋጣሚ አለ። ይሖዋ ከእርሱና ከውድ ልጁ ጋር ያለማቋረጥ እንድንመላለስ ስለሚፈልግ ይረዳናል እንዲሁም ይባርከናል።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ከክርስቶስ ጋር በአንድነት መመላለስ ምንን ይጨምራል?
◻ ‘በክርስቶስ ሥር መስደድ’ ማለት ምን ማለት ነው?
◻ ‘በክርስቶስ ላይ መታነጽ’ ማለት ምን ማለት ነው?
◻ ‘በእምነት መጽናት’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ‘የተትረፈረፈ ምስጋና’ የምናቀርበው በየትኞቹ ምክንያቶች ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዛፉ ሥሮች ላይታዩ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ ለዛፉ ምግብ ያቀብላሉ እንዲሁም ቀጥ አድርገው ያቆሙታል