ምዕራፍ 06
ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተገኙት እንዴት ነው?
“የሕይወት ምንጭ [ከአምላክ] ዘንድ ነው።” (መዝሙር 36:9) በዚህ ሐሳብ ትስማማለህ? አንዳንድ ሰዎች ሕይወት የተገኘው በድንገት በተከሰቱ ሁኔታዎች እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህ እውነት ከሆነ በሕይወት ልንኖር የቻልነው በአጋጣሚ ነው ማለት ነው። ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠረው ይሖዋ አምላክ ከሆነ ግን እንዲህ ያደረገበት ዓላማ ይኖራል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይመስልህም?a መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት ስለተገኘበት መንገድ ምን እንደሚልና ይህ ሐሳብ አሳማኝ የሆነበትን ምክንያት ተመልከት።
1. ሰማያትና ምድር የተገኙት እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። (ዘፍጥረት 1:1) አብዛኞቹ ሳይንቲስቶች ሰማያትና ምድር መጀመሪያ እንዳላቸው ይስማማሉ። አምላክ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረው እንዴት ነው? ‘ኃይሉን’ ማለትም ቅዱስ መንፈሱን በመጠቀም ኅብረ ከዋክብትን፣ ከዋክብትንና ፕላኔቶችን ጨምሮ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ፈጥሯል።—ዘፍጥረት 1:2
2. አምላክ ምድርን የፈጠረው ለምንድን ነው?
ይሖዋ “ምድርን . . . መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ [አልፈጠራትም]።” (ኢሳይያስ 45:18) ፕላኔታችንን የሰው ልጆች ለዘላለም መኖር የሚችሉባት ምቹ መኖሪያ እንድትሆን አድርጎ አዘጋጅቷታል። (ኢሳይያስ 40:28ን እና 42:5ን አንብብ።) በሳይንስ እንደተረጋገጠው ምድር ከሌሎች ፕላኔቶች የተለየች ናት። የሰው ልጆች በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሙሉ አሟልቶ የያዘ ሌላ ፕላኔት እስካሁን አልተገኘም።
3. የሰው ልጆችን ከእንስሳት የሚለያቸው ምንድን ነው?
ይሖዋ ምድርን ከፈጠረ በኋላ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ፈጥሯል። በመጀመሪያ ምድር በእንስሳትና በዕፀዋት እንድትሞላ አደረገ። ከዚያም “አምላክ . . . ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው።” (ዘፍጥረት 1:27ን አንብብ።) የሰው ልጆችን ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? የተፈጠርነው በአምላክ መልክ ስለሆነ እንደ ፍቅርና ፍትሕ ያሉ ባሕርያቱን ማንጸባረቅ እንችላለን። በተጨማሪም አምላክ የፈጠረን ቋንቋ የመማር፣ ውብ ነገሮችን የማድነቅና በሙዚቃ የመደሰት ችሎታ እንዲኖረን አድርጎ ነው። እንዲሁም ከእንስሳት በተለየ መልኩ እኛ ፈጣሪያችንን ማምለክ እንችላለን።
ጠለቅ ያለ ጥናት
ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠረ ንድፍ አውጪ እንዳለና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚናገረው ሐሳብ አሳማኝ እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እንመረምራለን። የሰው ልጆች የሚያንጸባርቋቸው ባሕርያት ስለ አምላክ ምን እንደሚያስተምሩን እንመለከታለን።
4. ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠረ ንድፍ አውጪ አለ
ሰዎች ፍጥረታትን ኮርጀው አንድ ነገር ሲሠሩ የባለቤትነት መብት ይሰጣቸዋል። ታዲያ ለዋናው ንድፍ የባለቤትነት መብት የሚገባው ማን ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ሰዎች ከተፈጥሮ ኮርጀው ያወጧቸው አንዳንድ ንድፎች የትኞቹ ናቸው?
አንድን ቤት ለመሥራት ንድፍ የሚያወጣና የሚገነባ ሰው ያስፈልጋል። ታዲያ በተፈጥሮ ላይ የምናያቸውን ነገሮች ንድፍ ያወጣውና የሠራው ማን ነው? ዕብራውያን 3:4ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በተፈጥሮ ላይ ከምታያቸው ነገሮች አንተን ይበልጥ የሚማርክህ የትኛው ነው?
ሰማያትንና ምድርን እንዲሁም በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች በሙሉ የፈጠረ ንድፍ አውጪ አለ ብሎ ማመን ምክንያታዊ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
ይህን ታውቅ ነበር?
jw.org ላይ “ንድፍ አውጪ አለው?” እና “ስለ ሕይወት አመጣጥ የተሰጡ አስተያየቶች” በሚሉት ተከታታይ ርዕሶች ሥር ስለዚህ ጉዳይ የሚያብራሩ ርዕሶችንና ቪዲዮዎችን ማግኘት ትችላለህ።
“እያንዳንዱ ቤት ሠሪ እንዳለው የታወቀ ነው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው”
5. ስለ ፍጥረት የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አሳማኝ ነው
መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ ምድርና በላይዋ ላይ ያለው ሕይወት ስለተገኙበት መንገድ ይገልጻል። ይህ ዘገባ እምነት የሚጣልበት ነው ወይስ አፈ ታሪክ? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
መጽሐፍ ቅዱስ ምድርና በላይዋ ላይ ያሉት ፍጥረታት ቃል በቃል በስድስት ቀናት ውስጥ እንደተፈጠሩ ያስተምራል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ስለ ፍጥረት የሚገልጸው ዘገባ አሳማኝና ምክንያታዊ እንደሆነ ይሰማሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
ዘፍጥረት 1:1ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ሳይንቲስቶች ሰማያትና ምድር መጀመሪያ እንዳላቸው ይናገራሉ። እነሱ የደረሱበት ድምዳሜ አሁን ካነበብነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ጋር የሚስማማው እንዴት ነው?
አንዳንድ ሰዎች አምላክ ሕይወትን የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሞ ሊሆን እንደሚችል ያስባሉ። ዘፍጥረት 1:21, 25, 27ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ውስብስብ ያልሆኑ ሴሎችን ከፈጠረ በኋላ እነዚህ ሴሎች በዝግመተ ለውጥ ዓሣዎችን፣ አጥቢ እንስሳትንና ሰዎችን እንዲያስገኙ እንዳደረገ ያስተምራል? ወይስ ሁሉንም ፍጥረታት የፈጠረው “እንደየወገናቸው” ነው?b
6. የሰው ልጆች አምላክ ከፈጠራቸው ሌሎች ፍጥረታት ይለያሉ
ሰዎችንም ሆነ እንስሳትን የፈጠረው አምላክ ነው፤ ሆኖም ሰዎች ከእንስሳት የተለዩ ናቸው። ዘፍጥረት 1:26ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
የተፈጠርነው በአምላክ መልክ ነው፤ ከዚህ አንጻር ፍቅርና ርኅራኄ የማሳየት ችሎታ ያለን መሆኑ ስለ አምላክ ባሕርይ ምን ይጠቁመናል?
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ስለ ፍጥረት የሚገልጸው ዘገባ አፈ ታሪክ ነው።”
አንተስ ምን ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
ማጠቃለያ
ሰማያትንና ምድርንም ሆነ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ የፈጠረው ይሖዋ ነው።
ክለሳ
መጽሐፍ ቅዱስ ሰማያትና ምድር ስለተገኙበት መንገድ ምን ያስተምራል?
አምላክ ውስብስብ ያልሆኑ ሴሎችን ከፈጠረ በኋላ እነዚህ ሴሎች በዝግመተ ለውጥ የተለያዩ ሕያዋን ነገሮችን እንዲያስገኙ አድርጓል? ወይስ ሁሉንም ፍጥረታት በቀጥታ ፈጥሯል?
የሰው ልጆችን ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
ምርምር አድርግ
በተፈጥሮ ላይ ስለሚታየው አስደናቂ ንድፍ ይበልጥ ለማወቅ ሞክር።
ወላጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው የፍጥረት ዘገባ ለልጆቻቸው ማስረዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ተመልከት።
‘ዝግመተ ለውጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል?’ የሚለውን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ሞክር።
“አምላክ የተለያዩ ፍጥረታትን ወደ ሕልውና ለማምጣት በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሟል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)
ከቅሪተ አካላት የተገኙ ማስረጃዎች ወይም ሳይንሳዊ ምርምሮች የሚያረጋግጡት ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ ነው ወይስ እንዲሁ በአጋጣሚ? በዚህ ጉዳይ ላይ ምርምር አድርግ።
b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እንደየወገናቸው” የሚለው አገላለጽ የተለያዩ ሕያዋን ፍጥረታትን ያቀፈን ሰፊ ቡድን ያመለክታል።