መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ
“ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።”—ገላትያ 6:9
1, 2. (ሀ) አምላክን ለማገልገል ጽናት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አብርሃም ጽናትን ያሳየው እንዴት ነው? እንዲጸና የረዳውስ ምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ያስደስተናል። የደቀ መዛሙርትነትን ‘ቀንበር’ በመሸከምም እረፍት እናገኛለን። (ማቴዎስ 11:29) ከክርስቶስ ጋርም ቢሆን ይሖዋን ማገልገል ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋል” በማለት አጥብቆ ባሳሰበ ጊዜ ይህን ጉዳይ ግልጽ አድርጎታል። (ዕብራውያን 10:36) አምላክን ማገልገል ፈታኝ ሊሆን ስለሚችል መጽናት አስፈላጊ ነው።
2 አብርሃም ያሳለፈው ሕይወት ለዚህ እውነት ምሥክር ይሆናል። ለበርካታ ጊዜያት አስቸጋሪ ምርጫዎችና የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ገጥመውታል። ተመችቶት ይኖርባት የነበረችውን ዑርን ለቅቆ እንዲወጣ የተሰጠው ትእዛዝ የመጀመሪያ ብቻ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ረሃብ፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጥላቻ፣ ሚስቱን የማጣት አደጋ፣ ከአንዳንድ ዘመዶች ጥላቻና ከባድ ጦርነት ገጥሞታል። የበለጡ ፈተናዎች ገና ይጠብቁት ነበር። ይሁን እንጂ አብርሃም መልካም ሥራን ከመሥራት ፈጽሞ ወደኋላ አላለም። እንደ እኛ የተሟላ የአምላክ ቃል ያልነበረው ሰው መሆኑ ሁኔታውን ይበልጥ አስገራሚ ያደርገዋል። አምላክ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ” በማለት የተናገረውን የመጀመሪያ ትንቢት ያውቅ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘፍጥረት 3:15) ዘሩ የሚመጣው በእርሱም በኩል ስለነበር ይህ ራሱ የሰይጣን የጥላቻ ዒላማ እንደሚያደርገው የታወቀ ነው። አብርሃም ይህን ሁኔታ ማወቁ የሚደርስበትን ፈተና በደስታ መቋቋም እንዲችል እንደረዳው የታወቀ ነው።
3. (ሀ) በጊዜያችን ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ፈተና ይደርስብናል ብለው መጠበቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ገላትያ 6:9 ምን ማበረታቻ ይሰጠናል?
3 በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችም ፈተና እንደሚደርስባቸው ሊጠብቁ ይገባል። (1 ጴጥሮስ 1:6, 7) ደግሞም ሰይጣን በቅቡዓን ላይ ‘ጦርነት ማወጁን’ ራእይ 12:17 ያስታውቀናል። ‘ሌሎች በጎችም’ ከቅቡዓኑ ጋር ተባብረው የሚሠሩ በመሆናቸው እነርሱም የሰይጣን ቁጣ ዒላማ ሆነዋል። (ዮሐንስ 10:16) ክርስቲያኖች በሕዝባዊ አገልግሎታቸው ወቅት ከሚደርስባቸው ተቃውሞ በተጨማሪ በግል ሕይወታቸውም ፈታኝ የሆኑ ተጽዕኖዎች ሊደርሱባቸው ይችላሉ። ጳውሎስ “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” በማለት በጥብቅ ይመክረናል። (ገላትያ 6:9) አዎን፣ ሰይጣን እምነታችንን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳ ቢሆንም ጠንካራ እምነት በመያዝ ጸንተን ልንቃወመው ይገባናል። (1 ጴጥሮስ 5:8, 9) በታማኝነት መጽናታችን ምን ዋጋ ያስገኝልናል? ያዕቆብ 1:2, 3 “ወንድሞቼ ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቊጠሩት” በማለት ይገልጻል።
ቀጥተኛ ጥቃት
4. ሰይጣን የአምላክን አገልጋዮች ጽኑ አቋም ለማስለወጥ ቀጥተኛ ጥቃትን እንደ መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመው እንዴት ነው?
4 የአብርሃም ሕይወት በዛሬ ጊዜ ያለ አንድ ክርስቲያን ሊያጋጥሙት የሚችሉትን “ልዩ ልዩ ፈተናዎች” ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ ነው። ለምሳሌ ያህል ከሰናዖር ምድር የመጡ ወራሪዎች ለሰነዘሩበት ጥቃት ምላሽ መስጠት አስፈልጎት ነበር። (ዘፍጥረት 14:11-16) ሰይጣን ስደት በማድረስ ቀጥተኛ ጥቃት መሰንዘሩን መቀጠሉ ምንም አያስደንቅም። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በደርዘን የሚቆጠሩ አገሮች በይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ የማስተማር ሥራ ላይ መንግሥታዊ እገዳ ጥለዋል። የ2001 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ በአንጎላ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በጠላቶቻቸው እጅ የተፈጸመባቸውን የኃይል ድርጊት ይዘረዝራል። እንደነዚህ ባሉ አገሮች የሚገኙ ወንድሞቻችን በይሖዋ ላይ በመታመን ከአቋማቸው ፍንክች ሳይሉ ቆመዋል! ዓመፅን ወይም ሁከትን እንደ መፍትሔ አድርገው ከመመልከት ይልቅ በስብከቱ ሥራ በጥበብ መካፈላቸውን በመቀጠል ምላሽ ሰጥተዋል።—ማቴዎስ 24:14
5. ክርስቲያን ወጣቶች ትምህርት ቤት ስደት ሊደርስባቸው የሚችለው እንዴት ነው?
5 ይሁን እንጂ ስደት ሁልጊዜ ከኃይል ድርጊት ጋር ተያይዞ ይመጣል ማለት አይደለም። በመጨረሻ አብርሃም እስማኤል እና ይስሐቅ የተባሉ ሁለት ወንዶች ልጆችን በማግኘት ተባርኳል። በአንድ ወቅት እስማኤል በይስሐቅ ላይ ‘እንደሳቀበት’ በዘፍጥረት 21:8-12 ላይ እናነባለን። ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እስማኤል ይስሐቅን እንዳሳደደው መግለጹ ጉዳዩ እንዲያው የልጆች ጨዋታ ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል! (ገላትያ 4:29) እንግዲያው የትምህርት ቤት ጓደኞች ፌዝና ተቃዋሚዎች የሚሰነዝሩት ስድብ ስደት እንደሆነ ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል። ራየን የተባለ አንድ ወጣት ክርስቲያን፣ የክፍል ተማሪዎቹ ያደርሱበት የነበረውን ሥቃይ በማስታወስ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከስድባቸው ብዛት 15 ደቂቃ የሚፈጀው ከቤት ወደ ትምህርት ቤት የማደርገው የአውቶቡስ ጉዞ የአንድ ሰዓት መንገድ ይመስለኝ ነበር። የወረቀት አግራፍ በሲጋራ መለኮሻ አግለው አቃጥለውኛል።” ይህ ሁሉ ግፍ ይደርስበት የነበረው ለምንድን ነው? “ያገኘሁት ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና በትምህርት ቤት ካሉ ሌሎች ወጣቶች የተለየሁ አድርጎኝ ስለነበር ነው” ብሏል። የሆነ ሆኖ ራየን ወላጆቹ ባደረጉለት ድጋፍ በታማኝት መጽናት ችሏል። እናንት ወጣቶች፣ እኩዮቻችሁ በሚሰነዝሩባችሁ የስድብ ቃላት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሰምቷችሁ ይሆን? ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጡ! በታማኝነት ከጸናችሁ “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ” በማለት ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት በእናንተ ላይ ሲፈጸሙ ትመለከታላችሁ።—ማቴዎስ 5:11
በዕለት ተዕለት ጭንቀቶች
6. ዛሬ በክርስቲያኖች መካከል ያለውን መልካም ዝምድና ሊያሻክሩ የሚችሉ ምን ነገሮች አሉ?
6 በዛሬ ጊዜ ከሚያጋጥሙን አብዛኞቹ ፈተናዎች መካከል የዕለት ተዕለት የተለመዱ ጭንቀቶች ይገኙበታል። አብርሃምም በእርሱና በወንድሙ ልጅ በሎጥ እረኞች መካከል የተነሳውን አለመግባባት መፍታት አስፈልጎታል። (ዘፍጥረት 13:5-7) በተመሳሳይ ዛሬም የባሕርይ አለመጣጣምና ጥቃቅን የቅናት ስሜቶች እርስ በርስ ያለንን ዝምድና ሊያሻክሩብን ከዚያም አልፎ የጉባኤውን ሰላም አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ። “ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና።” (ያዕቆብ 3:16) እኛም ልክ እንደ አብርሃም ተስፋ ሳንቆርጥ ኩራት ሰላማችንን እንዲያደፈርስብን አለመፍቀዳችንና የሌሎችን ጥቅም ማስቀደማችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—1 ቆሮንቶስ 13:5፤ ያዕቆብ 3:17
7. (ሀ) አንድ ግለሰብ የእምነት ባልደረባው ቢጎዳው ምን ማድረግ ይኖርበታል? (ለ) ከሌሎች ጋር ያለንን ዝምድና በመጠበቅ ረገድ አብርሃም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?
7 አንድ የእምነት ባልደረባችን እንደ ጎዳን በሚሰማን ጊዜ ሰላምን ጠብቆ መኖሩ ሊከብደን ይችላል። ምሳሌ 12:18 “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ [“ሳያስብ የሚናገር፣” NW ] ሰው አለ፤ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው” በማለት ይናገራል። በቅንነት የተነገሩ ቢሆንም እንኳ ‘ሳይታሰብ የሚሰነዘሩ ቃላት’ ከባድ የስሜት ቁስል ሊያስከትሉ ይችላሉ። ስማችን እንደጠፋ ወይም በመጥፎ እንደታማን በሚሰማን ጊዜ ደግሞ ቁስሉ የበለጠ ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 6:6, 7) ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን የደረሰበት የስሜት ጉዳት ተስፋ እንዲያስቆርጠው ሊፈቅድለት አይገባም! እንዲህ ያለ ነገር ገጥሞህ ከሆነ ያስቀየመህን ሰው በደግነት በማነጋገር ችግሩን ለመፍታት እርምጃ ውሰድ። (ማቴዎስ 5:23, 24፤ ኤፌሶን 4:26) ግለሰቡን ይቅር የማለት ዝንባሌ ይኑርህ። (ቆላስይስ 3:13) ቅሬታን በመተው የእኛም ስሜት ሆነ ከወንድማችን ጋር ያለን ዝምድና እንዲጠገን ማድረግ እንችላለን። አብርሃም ቅር የሚያሰኝ ነገር ቢገጥመውም በሎጥ ላይ ቂም አልያዘም። እንዲያውም አብርሃም ሎጥንና ቤተሰቡን ለማዳን ፈጥኖ እርምጃ ወስዷል!—ዘፍጥረት 14:12-16
በራሳችን ላይ የምናመጣቸው መከራዎች
8. (ሀ) ክርስቲያኖች ‘በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ሊወጉ’ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) አብርሃም ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው?
8 እውነቱን ለመናገር አንዳንዶቹን ፈተናዎች የምናመጣው ራሳችን ነን። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቈፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ” በማለት ተከታዮቹን አዝዟቸዋል። (ማቴዎስ 6:19) ሆኖም አንዳንድ ወንድሞች ቁሳዊ ጥቅማቸውን ከመንግሥቱ ፍላጎቶች በማስቀደም ‘ራሳቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።’ (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) አብርሃም አምላክን ለማስደሰት ሲል ቁሳዊ ጥቅሞችን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። “ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፣ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፣ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።” (ዕብራውያን 11:9, 10) አብርሃም ወደፊት በምትመጣዋ “ከተማ” ወይም መለኮታዊ መስተዳድር ላይ እምነት ማሳደሩ በሃብት እንዳይታመን ረድቶታል። እኛም እንዲህ ብናደርግ ጥበብ አይሆንም?
9, 10. (ሀ) ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት መፈለግ ፈተና ሊያስከትል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ አንድ ወንድም ራሱን ከሌሎች ‘ያነሰ’ እንደሆነ በመቁጠር መመላለስ የሚችለው እንዴት ነው?
9 ሌላም ዘርፍ ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ጠንካራ መመሪያ ይሰጣል:- “አንዱ ምንም ሳይሆን ምንም የሆነ ቢመስለው ራሱን ያታልላልና።” (ገላትያ 6:3) በተጨማሪም “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ” ተብለን በጥብቅ ተመክረናል። (ፊልጵስዩስ 2:3) አንዳንዶች ይህን ምክር ሳይከተሉ በመቅረታቸው በራሳቸው ላይ ፈተና አምጥተዋል። “መልካምን ሥራ” ለመሥራት በመመኘት ሳይሆን ክብር ለማግኘት በመጓጓት በጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት ኃላፊነት ለማግኘት ተነስተው ሳይሳካላቸው ሲቀር ተስፋ ይቆርጣሉ እንዲሁም ቅር ይሰኛሉ።—1 ጢሞቴዎስ 3:1
10 ‘ማሰብ ከሚገባው አልፎ ባለማሰብ’ በኩል አብርሃም ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። (ሮሜ 12:3) መልከ ጼዴቅን ባገኘው ጊዜ አብርሃም በአምላክ ዘንድ ተወዳጅነትን ማትረፉ እርሱን እንደሚያስበልጠው አድርጎ አላሰበም። ከዚያ ይልቅ አሥራት በመስጠት መልከ ጼዴቅ እንደ ካህን የላቀ ቦታ እንዳለው አምኖ ተቀብሏል። (ዕብራውያን 7:4-7) በዛሬም ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከሁሉ ‘ያነሱ’ እንደሆኑ አድርገው ለመቁጠር እንዲሁም ሰዎች ትኩረት ሊሰጧቸው እንደሚገባ አድርገው ከማሰብ ለመቆጠብ ፈቃደኛ መሆን ይኖርባቸዋል። (ሉቃስ 9:48) በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች አንዳንድ መብቶችን ሳይሰጡህ እንደቀሩ ሆኖ በሚሰማህ ጊዜ በባሕርይ ወይም ነገሮችን በምታከናውንበት መንገድ ላይ ምን ዓይነት ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብህ ለማወቅ በሃቀኝነት ራስህን መርምር። አንዳንድ መብቶች ለምን አልተሰጡኝም ብለህ ከማማረር ይልቅ ባገኘኸው መብት ማለትም ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ በመርዳት መብትህ ሙሉ በሙሉ ተጠቀም። አዎን፣ ‘በጊዜው ከፍ እንዲያደርግህ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራስህን አዋርድ።’—1 ጴጥሮስ 5:6
ባልታዩት ነገሮች ማመን
11, 12. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች የጥድፊያ ስሜታቸውን የሚያጡት ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) አብርሃም ሕይወቱ በጠቅላላ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ በነበረው እምነት ዙሪያ እንዲያተኩር በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?
11 የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ የዘገየ መስሎ መታየቱ ፈተና ሊሆን ይችላል። በ2 ጴጥሮስ 3:11, 12 መሠረት ክርስቲያኖች ‘የይሖዋ ቀን መምጣት እየጠበቁና እያስቸኮሉ መኖር’ ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ ብዙ ክርስቲያኖች ይህን “ቀን” ለዓመታት አንዳንዶች ደግሞ ለአሥርተ ዓመታት ሲጠባበቁ ኖረዋል። በዚህም የተነሳ አንዳንዶች ተስፋ ቆርጠው የጥድፊያ ስሜታቸውን ሊያጡ ይችላሉ።
12 አሁንም የአብርሃምን ምሳሌ ተመልከት። አምላክ የሰጠው ተስፋዎች በሙሉ በእርሱ የሕይወት ዘመን ፍጻሜያቸውን ሊያገኙ የሚችሉበት ምንም ዓይነት አጋጣሚ ባይኖርም ሕይወቱ በጠቅላላ ያተኮረው በእነዚህ ተስፋዎች ላይ በነበረው እምነት ዙሪያ ነበር። እርግጥ ይስሐቅ ተወልዶ ትልቅ እስኪሆን ድረስ በሕይወት የመቆየት አጋጣሚ አግኝቷል። ሆኖም የአብርሃም ዘሮች “እንደ ሰማይ ከዋክብት” ወይም “በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ” እስኪሆኑ ድረስ ብዙ መቶ ዓመታት ያስፈልጉ ነበር። (ዘፍጥረት 22:17) ያም ሆኖ አብርሃም አላማረረም ወይም ተስፋ አልቆረጠም። በዚህም የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ አብርሃምንና ሌሎች የዕብራውያን አባቶችን በማስመልከት እንዲህ ብሏል:- “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፤ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ።”—ዕብራውያን 11:13
13. (ሀ) በዛሬ ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ‘መጻተኞች’ የሆኑት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ይህን የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜ የሚያመጣው ለምንድን ነው?
13 አብርሃም መላ ሕይወቱ ፍጻሜያቸው ገና “ሩቅ” በሆነው ተስፋዎች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ከቻለ እነዚህ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን ሊያገኙ በጣም ተቃርበው በሚገኙበት በዛሬው ጊዜ የምንኖረውማ አብልጠን እንዲህ ልናደርግ አይገባምን! የራስን ፍላጎት የማሳደድን አኗኗር በማስወገድ ልክ እንደ አብርሃም ራሳችንን በሰይጣን ሥርዓት ውስጥ “መጻተኞች” እንደሆንን አድርገን መቁጠር ይኖርብናል። ‘የነገር ሁሉ መጨረሻ’ ከመቅረቡም አልፎ አሁኑኑ ቢሆን ደስ እንደሚለን የታወቀ ነው። (1 ጴጥሮስ 4:7) ሥር በሰደደ በሽታ እንሠቃይ ይሆናል። ወይም ኑሮ ከብዶብን ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ መጨረሻውን የሚያመጣው እኛን ከችግር ለመገላገል ብቻ ሳይሆን ስሙን ለማስቀደስም እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። (ሕዝቅኤል 36:23፤ ማቴዎስ 6:9, 10) መጨረሻው የሚመጣው እኛ በምንፈልገው ጊዜ ሳይሆን ይሖዋ ዓላማዎቹን ለማስፈጸም ተስማሚ ሆኖ ባገኘው ጊዜ ነው።
14. አምላክ ትዕግሥት ማሳየቱ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችን የሚጠቅመው እንዴት ነው?
14 በተጨማሪም “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል” የሚለውን ቃል አስታውስ። (2 ጴጥሮስ 3:9) አምላክ ‘ስለ እናንተ’ ማለትም ለክርስቲያን ጉባኤ አባላት ሲል ‘እንደሚታገሥ’ አስታውስ። አንዳንዶቻችን ‘ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆነን በሰላም በእርሱ መገኘት’ እንችል ዘንድ አንዳንድ ለውጦችንና ማስተካከያዎችን ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:14) ታዲያ አምላክ እንዲህ ያለውን ትዕግሥት ስላሳየን አመስጋኝ ልንሆን አይገባንም?
እንቅፋቶች ቢኖሩም ደስተኛ መሆን
15. ኢየሱስ ፈተና ደርሶበት እያለ እንኳን ደስታውን ጠብቆ መኖር የቻለው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች እርሱን በመምሰል የሚጠቅሙት እንዴት ነው?
15 የአብርሃም ሕይወት በዛሬው ጊዜ ላሉት ክርስቲያኖች በርካታ ትምህርቶችን ይዟል። አብርሃም እምነትን ብቻ ሳይሆን ትዕግሥትን፣ ብልሃትን፣ ድፍረትንና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅርንም አሳይቷል። በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለይሖዋ አምልኮ የመጀመሪያውን ቦታ ሰጥቷል። ሆኖም ልንመስለው የሚገባን ከሁሉ የላቀው ምሳሌያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ፈጽሞ መርሳት የለብንም። ኢየሱስ በርካታ መከራዎችንና ፈተናዎችን የተቋቋመ ቢሆንም እንኳ በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ደስታውን ጠብቋል። ለምን? በፊቱ ያለውን ተስፋ ትኩር ብሎ ይመለከት ስለነበር ነው። (ዕብራውያን 12:1-3) በዚህም የተነሳ ጳውሎስ “የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ ይስጣችሁ” በማለት ጸልዮአል። (ሮሜ 15:5 NW ) ትክክለኛ አስተሳሰብ ካለን ሰይጣን በመንገዳችን ላይ ምንም ዓይነት እንቅፋቶችን ቢያስቀምጥ ደስታችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን።
16. ችግሮች ከአቅማችን በላይ እንደሆኑብን በሚሰማን ጊዜ ምን ልናደርግ እንችላለን?
16 ችግሮች ከአቅምህ በላይ እንደሆኑብህ በሚሰማህ ጊዜ ይሖዋ አብርሃምን እንደወደደው ሁሉ አንተንም እንደሚወድህ አስታውስ። አንተም እንዲሳካልህ ይፈልጋል። (ፊልጵስዩስ 1:6) “ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” በሚለው ቃል ላይ ሙሉ ትምክህት በማሳደር በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን። (1 ቆሮንቶስ 10:13) የአምላክን ቃል በየዕለቱ የማንበብ ልማድ አዳብር። (መዝሙር 1:2) መጽናት ትችል ዘንድ እንዲረዳህ ሳታቋርጥ ይሖዋን በጸሎት ጠይቅ። (ፊልጵስዩስ 4:6) እርሱ ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸዋል።’ (ሉቃስ 11:13) ይሖዋ አንተን በመንፈሳዊ ደግፎ ለማቆም ባደረጋቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን በመሳሰሉት ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቀም። እንዲሁም ከወንድማማች ማኅበር ድጋፍ ለማግኘት ጥረት አድርግ። (1 ጴጥሮስ 2:17 NW ) መጽናት ትችል ዘንድ የሚያስፈልግህን ማበረታቻ የምታገኘው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመሆኑ ከስብሰባዎች ፈጽሞ አትቅር። (ዕብራውያን 10:24, 25) ጽናትህ በአምላክ ዘንድ ሞገስ እንደሚያስገኝልህና የታማኝነት አቋምህ ልቡን ደስ እንደሚያሰኝ ባለህ የጸና እምነት ደስ ይበልህ!—ምሳሌ 27:11፤ ሮሜ 5:3-5
17. ክርስቲያኖች ተስፋ ቆርጠው እጅ የማይሰጡት ለምንድን ነው?
17 አምላክ አብርሃምን እንደ ‘ወዳጁ’ አድርጎ ወድዶታል። (ያዕቆብ 2:23) እንደዚያም ሆኖ የአብርሃም ሕይወት ፈተናዎችና መከራዎች ተፈራርቀውበታል። ስለዚህ ክርስቲያኖች በዚህ ክፉ ‘የመጨረሻ ቀን’ ውስጥ ከዚያ ያነሰ ነገር ሊጠብቁ አይችሉም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” በማለት ያስጠነቅቃል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) ስለዚህ ለተስፋ መቁረጥ እጅህን ከመስጠት ይልቅ የሚደርሱብን ተጽዕኖዎች የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ መቃረቡን የሚያረጋግጡ እንደሆኑ አስታውስ። ሆኖም ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ የሚጸና . . . እርሱ ይድናል” በማለት ያሳስበናል። (ማቴዎስ 24:13) ስለዚህ ‘መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክት!’ የአብርሃምን ምሳሌ በመከተል ‘በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል ከሚወርሱት’ ሰዎች መካከል ሁን።—ዕብራውያን 6:11, 12
አስተውለሃልን?
• በዛሬ ጊዜ ያሉት የይሖዋ ሕዝቦች ፈተናና መከራ ይደርስብናል ብለው መጠበቅ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
• ሰይጣን ቀጥተኛ ጥቃት የሚሰነዝረው በምን መንገዶች ሊሆን ይችላል?
• በክርስቲያኖች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ሊፈቱ የሚችሉት እንዴት ነው?
• ኩራትና ስለ ራስ ከልክ በላይ ማሰብ ፈተና ሊያስከትሉ የሚችሉት እንዴት ነው?
• ይሖዋ የገባቸውን ተስፋዎች ፍጻሜ በመጠባበቅ ረገድ አብርሃም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን በምን መንገድ ነው?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በርካታ ክርስቲያን ወጣቶች የእኩዮቻቸው መሣለቂያ በመሆን ስደት ይደርስባቸዋል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአብርሃም ዘመን አምላክ የገባቸው ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበት ጊዜ ገና ‘ሩቅ’ ቢሆንም አብርሃም ሕይወቱ በእነዚህ ተስፋዎች ዙሪያ እንዲያተኩር አድርጓል