‘ምድሪቱን ተመላለስባት’
“ምድሪቱን . . . በርዝመቷም፣ በስፋቷም ተመላለስባት።”—ዘፍጥረት 13:17
1. አምላክ ለአብርሃም ምን ለየት ያለ መመሪያ ሰጥቶት ነበር?
በመኪና ወደ ገጠር ወጣ በማለት አካባቢውን ማየት ያስደስትሃል? አንዳንዶች እንደ ስፖርት እንዲሆንላቸውና መልክዓ ምድሩን በደንብ እያዩ ለመደሰት ሲሉ በብስክሌት መጓዝ ይመርጣሉ። ሌሎች ደግሞ እያንዳንዱን ነገር እንደ ልብ ማየት ስለሚፈልጉ በእግራቸው መጓዝ ያስደስታቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለውን ጉዞ ማድረግ የሚቻለው እስከተወሰነ ርቀት ብቻ ነው። ሆኖም አምላክ “ምድሪቱን ስለምሰጥህ ተነሣ፤ በርዝመቷም፣ በስፋቷም ተመላለስባት” ባለው ጊዜ አብርሃም ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስብ!—ዘፍጥረት 13:17
2. አብርሃም ከግብፅ ወጥቶ ወዴት ተጓዘ?
2 እስቲ አምላክ ለአብርሃም ይህን መመሪያ ከመስጠቱ በፊት የነበሩትን አንዳንድ ሁኔታዎች እንመልከት። አብርሃም ከሚስቱና ከዘመዶቹ ጋር ለተወሰነ ጊዜ በግብፅ ተቀምጦ ነበር። በዘፍጥረት ምዕራፍ 13 ላይ የሚገኘው ዘገባ አብርሃም ከብቶቹን ይዞ ከግብፅ ወደ “ኔጌብ” እንደተጓዘ ይገልጻል። ከዚያም “ከኔጌብ ተነሥቶ እስከ ቤቴል ተጓዘ።” ከጊዜ በኋላ በአብርሃምና በወንድሙ ልጅ በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ ስለተፈጠረ ሁለቱ ከብቶቻቸውን ይዘው ወደ ተለያየ ሥፍራ መሄድ ግድ ሆነባቸው። በዚህ ጊዜ አብርሃም፣ ሎጥ የፈለገውን እንዲመርጥ አጋጣሚውን ሰጠው። ሎጥም “እንደ እግዚአብሔር ገነት” ለም የሆነውን “የዮርዳኖስ ረባዳ ሜዳ” የመረጠ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በሰዶም መኖር ጀመረ። አምላክ፣ አብርሃምን “ካለህበት ስፍራ ቀና ብለህ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት” አለው። አብርሃም ከፍታ ቦታ ላይ ይገኝ ከነበረው ከቤቴል ሆኖ የምድሪቱን የተለያዩ አካባቢዎች መቃኘት ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ብቻ በቂ ስላልሆነ ምድሪቱን በደንብ ማየት እንዲችል አምላክ ‘በምድሪቱ ተመላለስባት’ ሲል ግብዣ አቀረበለት።
3. አብርሃም የተጓዘባቸውን ቦታዎች በዓይነ ኅሊናችን መሳል አስቸጋሪ ሊሆንብን የሚችለው ለምንድን ነው?
3 አብርሃም በምድሪቱ ላይ የተመላለሰው ምንም ያህል ጊዜ ይሁን ኬብሮን ከመድረሱ በፊት ከማናችንም በተሻለ ሁኔታ ተስፋይቱን ምድር ያውቃት ነበር። እስቲ በዚህ ዘገባ ላይ ስለተጠቀሱት ማለትም ኔጌብ፣ ቤቴል፣ ዮርዳኖስ፣ ሰዶምና ኬብሮን ስለተባሉት ቦታዎች አስብ። እነዚህ ቦታዎች የት እንደሚገኙ በዓይነ ኅሊናህ መሳል ትችላለህ? ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ቦታዎች የመጎብኘት አጋጣሚ ያላቸው ጥቂቶች በመሆናቸው እንዲህ ማድረግ ለብዙዎች በጣም አስቸጋሪ ነው። ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ቦታዎች የማወቅ ብርቱ ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል። ለምን?
4, 5. (ሀ) ምሳሌ 18:15 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ቦታዎች ሊኖረን ከሚገባው እውቀትና ማስተዋል ጋር ምን ግንኙነት አለው? (ለ) ሶፎንያስ ምዕራፍ 2 ለምን ነገር እንደምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል?
4 የአምላክ ቃል “የአስተዋይ ልብ ዕውቀትን ይገበያል፤ የጠቢብም ጆሮ አጥብቆ ይሻታል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 18:15) አንድ ሰው ሊያውቃቸው የሚገቡ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች አሉ፤ ሆኖም ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ የሚገልጸው ትክክለኛ እውቀት ከሁሉም በላይ ቀዳሚውን ሥፍራ መያዝ ይኖርበታል። ይህ ትክክለኛ እውቀት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) እዚህ ላይ አስተዋይነትም እንደተጠቀሰ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ማስተዋል አንድን ነገር በጥልቀት የመመልከት እንዲሁም የጉዳዩ የተለያዩ ገጽታዎች እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት የማወቅና አጠቃላዩን ገጽታ የመረዳት ችሎታ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተጠቀሱ ቦታዎች ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት ለምናደርገው ጥረትም ይህ ችሎታ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎቻችን ግብፅ የት እንደምትገኝ እናውቃለን። ሆኖም አብርሃም ከግብፅ “ወደ ኔጌብ” ከዚያም ወደ ቤቴል በኋላም ወደ ኬብሮን እንደተጓዘ የሚገልጸውን ዘገባ ምን ያህል በትክክል እንረዳለን? እነዚህ ቦታዎች የት እንደሚገኙና በመካከላቸው ያለው ርቀት ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ ትችላለህ?
5 ወይም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራምህ ሶፎንያስ ምዕራፍ 2ን አንብበህ ይሆናል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተለያዩ ከተሞች፣ ሕዝቦችና አገሮች ስም ተዘርዝሯል። ጋዛ፣ አስቀሎና፣ አዛጦን፣ አቃሮን፣ ሰዶም፣ ነነዌ፣ ከነዓን፣ ሞዓብ፣ አሞንና አሦር ተጠቅሰዋል። በመለኮታዊ ትንቢት አፈጻጸም ረገድ ድርሻ ያላቸው ሰዎች የኖሩባቸውን እነዚህን ቦታዎች በዓይነ ኅሊናህ ለመሳል ሞክረህ ታውቃለህ? ለመሆኑ ይህን በማድረግ ረገድ ምን ያህል ተሳክቶልሃል?
6. አንዳንድ ክርስቲያኖች ካርታዎችን መመልከት ጠቃሚ ሆኖ ያገኙት ለምንድን ነው? (ሣጥኑን ተመልከት።)
6 በርካታ የአምላክ ቃል ተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ቦታዎችን የሚያሳዩ ካርታዎችን በማየትና በማገናዘብ በእጅጉ ተጠቅመዋል። ይህን የሚያደርጉት ካርታ ማየት ስለሚያስደስታቸው ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ካርታዎችን ማየት ስለ አምላክ ቃል ያላቸውን እውቀት እንደሚያሰፋላቸው ስለሚገነዘቡ ነው። ከዚህም በላይ ካርታዎችን መመልከት አዲስ ያገኙት እውቀት ቀደም ሲል ከነበራቸው ግንዛቤ ጋር ምን ዝምድና እንዳለው ይበልጥ እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል። በዚህ ረገድ አንዳንድ ምሳሌዎችን ማየታችን አንተም ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ በቃሉ ውስጥ ስለሰፈሩት ዘገባዎች የበለጠ ማስተዋል እንድታገኝ ይረዳሃል። (በገጽ 14 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)
በቦታዎች መካከል ስላለው ርቀት ማወቅ ግንዛቤ ያሰፋል
7, 8. (ሀ) ሳምሶን በጋዛ የፈጸመው አስገራሚ ነገር ምንድን ነው? (ለ) ስለ ሳምሶን ጥንካሬ ያለንን ግንዛቤ የሚያሳድግልን ስለምን ነገር ማወቃችን ነው? (ሐ) ስለ ሳምሶን የሚናገረውን ዘገባ በትክክል ማወቃችን ምን ጥቅም አለው?
7 በመሳፍንት 16:2 ላይ መስፍኑ ሳምሶን በጋዛ እንደነበረ እናነባለን። ጋዛ ዛሬም በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች በተደጋጋሚ ስለምትጠቀስ ሳምሶን በሜድትራኒያን የባሕር ዳርቻ በሚገኘው የፍልስጥኤም ምድር ውስጥ የት አካባቢ እንደነበረ መገመት እንችል ይሆናል። [11] እስቲ መሳፍንት 16:3 ምን እንደሚል ልብ በል፦ “ሳምሶን እዚያ የተኛው እስከ እኩለ ሌሊት ብቻ ነበር፤ ተነሥቶም የከተማዪቱን ቅጥር በር ከሁለት መቃኖቹ ጋር መወርወሪያውንና ማያያዣውን ጭምር በሙሉ ነቅሎ በትከሻው ላይ ካደረገ በኋላ፣ በኬብሮን ፊት ለፊት እስካለው ኰረብታ ጫፍ ድረስ ተሸክሞት ወጣ።”
8 እንደ ጋዛ ያለች ትልቅ ቅጥር ያላት ከተማ በሮቿና መቃኖቿ ምን ያህል ግዙፍና ከባድ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። በሩንና መቃኖቹን መሸከም ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን አስብ! ሳምሶን ግን ይህን ማድረግ ችሏል፤ ሆኖም ሳምሶን በሩንና መቃኖቹን ተሸክሞ የወሰዳቸው ወዴት ነው? የተጓዘበት አቅጣጫስ ምን የሚጠይቅ ነበር? ጋዛ በባሕር ወለል ላይ የምትገኝ ከተማ ስትሆን [15] በስተ ምሥራቅ ያለችው ኬብሮን ግን ከባሕር ወለል በላይ 900 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች። ስለዚህ እዚያ ለመድረስ ከፍተኛ አቀበት መውጣት ይጠይቃል። ‘በኬብሮን ፊት ለፊት ያለው ኮረብታ’ የት እንደሚገኝ በትክክል ባናውቅም ከተማይቱ ከጋዛ 60 ኪሎ ሜትር ርቃ ከፍታ ቦታ ላይ ትገኝ እንደነበር ይታወቃል! በሁለቱ ቦታዎች መካከል ያለውን ርቀት ማወቃችን ስለ ሳምሶን ጥንካሬ ያለንን ግንዛቤ ይጨምርልናል። አይደለም እንዴ? ሳምሶን እንዲህ ያለ ነገር እንዲያደርግ ያስቻለው ምን እንደነበረ አትዘንጋ፤ “የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል” ወርዶበት ነበር። (መሳፍንት 14:6, 19፤ 15:14) በዛሬው ጊዜ ያለነው ክርስቲያኖች የአምላክ መንፈስ እንደ ሳምሶን ያለ የተለየ አካላዊ ጥንካሬ ይሰጠናል ብለን አንጠብቅም። ይሁን እንጂ፣ ይህ የአምላክ መንፈስ ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ነገሮችን እንድናስተውልና መንፈሰ ጠንካራ እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 2:10-16፤ 13:8፤ ኤፌሶን 3:16፤ ቆላስይስ 1:9, 10) አዎን፣ ስለ ሳምሶን የሚናገረውን ዘገባ በትክክል መረዳታችን የአምላክ መንፈስ እኛንም እንደሚረዳን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።
9, 10. (ሀ) ጌዴዎን በምድያማውያን ላይ ድል የተቀዳጀው ምን በማድረግ ብቻ አይደለም? ምን ማድረግስ ጠይቆበታል? (ለ) ታሪኩ ስለተፈጸመበት መልክዓ ምድር ያለን እውቀት ይህ ዘገባ ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆንልን ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
9 ጌዴዎን በምድያማውያን ላይ ስለተቀዳጀው ድል የሚገልጸው ዘገባም በቦታዎች መካከል ያለውን ርቀት በትክክል ማወቅ የሚያስገኘውን ጥቅም የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ብዙ ሰዎች መስፍኑ ጌዴዎንና የመለመላቸው 300 ሰዎች ከተለያዩ ብሔራት የተውጣጣውን 135,000 ወራሪ ሠራዊት ድል እንዳደረጉ ያውቃሉ። [18] የጌዴዎን ሰዎች ቀንደ መለከት በመንፋትና ያቀጣጠሉት ችቦ እንዲታይ ማሰሮዎቻቸውን በመስበር “የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ” ብለው ጮኹ። የጠላት ሠራዊት ግራ ስለተጋባና ስለተደናገጠ እርስ በርሱ መጨፋጨፍ ጀመረ። (መሳፍንት 6:33፤ 7:1-22) የተከናወነው ነገር ይህ ብቻ ነበር? መሳፍንት ምዕራፍ 7ን እና 8ን ማንበባችንን ስንቀጥል ጌዴዎን ጠላቶቹን ማሳደዱን እንደገፋበት እንረዳለን። በዘገባው ላይ የተጠቀሱት አብዛኞቹ ቦታዎች የት እንደነበሩ ስለማይታወቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ካርታ ላይ አይገኙም። ቢሆንም የሚታወቁ ቦታዎችም ስለተጠቀሱ ጌዴዎን ጠላቶቹን ያሳደደበትን አቅጣጫ መረዳት እንችላለን።
10 ጌዴዎን በሕይወት የተረፈውን የጠላት ሠራዊት እስከ ቤት ሺጣ ከዚያም አልፎ በዮርዳኖስ አቅራቢያ እስከሚገኘው እስከ አቤላሞሖላ ድረስ አሳዷል። (መሳፍንት 7:22-25) ዘገባው “ጌዴዎንና ሦስት መቶዎቹ ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ምንም እንኳ ድካም ቢሰማቸውም ጠላቶቻቸውን ያሳድዱ ነበር” ይላል። እስራኤላውያኑ ዮርዳኖስን ከተሻገሩም በኋላ ጠላቶቻቸውን በደቡብ አቅጣጫ ያቦቅ አቅራቢያ እስከሚገኙት እስከ ሱኮትና ጵኒኤል ከዚያም እስከ ዮግብሃ (ዛሬ ይህ ቦታ በዮርዳኖስ፣ አማን አቅራቢያ ይገኛል) ኮረብታ ድረስ አሳደዋል። ጠላቶቻቸውን 80 ኪሎ ሜትር ድረስ እያሳደዱ ወግተዋል። ጌዴዎን ሁለት የምድያም ነገሥታትን ማርኮ በሰይፍ ስለት ከገደለ በኋላ ጦርነቱ መጀመሪያ ወደተቀሰቀሰባት ወደ መኖሪያ ከተማው ወደ ዖፍራ ተመለሰ። (መሳፍንት 8:4-12, 21-27) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጌዴዎን የተቀዳጀው ድል እንዲሁ ለጥቂት ደቂቃዎች መለከት በመንፋት፣ ችቦ በማብራትና በመጮኽ ብቻ የተገኘ አይደለም። ይህን በግልጽ መረዳታችን “ስለ ጌዴዎን [እና ስለ ሌሎች] . . . እንዳልተርክ ጊዜ የለኝም። . . . ከድካማቸው በረቱ፤ በጦርነት ኀያል ሆኑ” የሚለው ስለ እምነት ሰዎች የሚገልጸው ዘገባ ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆንልን እንደሚረዳን ማሰብ ትችላለህ። (ዕብራውያን 11:32-34) እኛ ክርስቲያኖችም አካላዊ ድካም ቢሰማንም እንኳ የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችንን መቀጠላችን አስፈላጊ አይደለም?—2 ቆሮንቶስ 4:1, 16፤ ገላትያ 6:9
ሰዎች ያላቸው ዝንባሌና የሚወስዱት እርምጃ
11. እስራኤላውያን ቃዴስ ከመድረሳቸው በፊትና በኋላ ያደረጉት ጉዞ ምን ይመስላል?
11 አንዳንዶች የተለያዩ ቦታዎች ያሉበትን ሥፍራ ለማወቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ካርታዎችን ይመለከቱ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ካርታ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ጭምር ግንዛቤ እንድናገኝ በማድረግ ረገድ የሚያበረክተው ድርሻ ሊኖር ይችላል ብለህ ታስባለህ? ከሲና ተራራ ወደ ተስፋይቱ ምድር ይጓዙ የነበሩትን እስራኤላውያን እስቲ እንመልከት። በጉዟቸው ላይ በአንዳንድ ቦታዎች የተወሰነ ቆይታ በማድረግ ቃዴስ (ወይም ቃዴስ በርኔ) ደረሱ። [9] ይህ ጉዞ 11 ቀን እንደፈጀ ዘዳግም 1:2 የሚጠቁም ሲሆን ርቀቱ ወደ 270 ኪሎ ሜትር ገደማ ይሆናል። ከዚያም ሙሴ ተስፋይቱን ምድር እንዲሰልሉ 12 ሰላዮችን ላከ። (ዘኍልቍ 10:12, 33፤ 11:34, 35፤ 12:16፤ 13:1-3, 25, 26) ሰላዮቹ በኔጌብ አድርገው ወደ ሰሜን አቅጣጫ በመጓዝ ምናልባትም በቤርሳቤህ በኩል አልፈው ኬብሮን የደረሱ ሲሆን ከዚያም እስከ ተስፋይቱ ምድር ሰሜናዊ ጫፍ ድረስ ዘለቁ። (ዘኍልቍ 13:21-24) እስራኤላውያን አሥሩ ሰላዮች የነገሯቸውን አፍራሽ ወሬ በማመናቸው ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ለመንከራተት ተገድደዋል። (ዘኍልቍ 14:1-34) ይህ ዘገባ እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ ስለነበራቸው እምነትና ትምክህት ምን ያስተምረናል?—ዘዳግም 1:19-33፤ መዝሙር 78:22, 32-43፤ ይሁዳ 5
12. እስራኤላውያን ስለነበራቸው እምነት ምን ብለን መደምደም እንችላለን? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
12 እስቲ ይህንን ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር እንመልከተው። እስራኤላውያን እምነት ኖሯቸው የኢያሱንና የካሌብን ምክር ሰምተው ቢሆን ኖሮ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ይህን ያህል ረጅም ርቀት መጓዝ ያስፈልጋቸው ነበር? ቃዴስ የምትገኘው ይስሐቅና ርብቃ ይኖሩባት ከነበረችው ከብኤርላሃይሮኢ 16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነበር። [7] ከዚያ ተነስቶ ተስፋይቱ ምድር ደቡባዊ ጫፍ ወደምትገኘው ቤርሳቤህ ለመድረስ ያለው ርቀት 95 ኪሎ ሜትር እንኳ አይሞላም። (ዘፍጥረት 24:62፤ 25:11፤ 2 ሳሙኤል 3:10) ከግብፅ ተነስተው ወደ ሲና ተራራ ከዚያ ደግሞ 270 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ቃዴስ ተጓዙ ማለት ተስፋይቱ ምድር ደፍ ላይ ደረሱ ማለት ነው። እኛም ብንሆን ይሖዋ በሰጠን ተስፋ መሠረት ገነት ወደምትሆነው ምድር ለመግባት ደፍ ላይ ደርሰናል። ታዲያ ከእስራኤላውያን ታሪክ ምን እንማራለን? ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዲህ ማንም የእነዚያን አለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ” የሚል ምክር በሰጠ ጊዜ የእስራኤላውያንን ሁኔታ ከዚህ ጋር አያይዞ ገልጾታል።—ዕብራውያን 3:16 እስከ 4:11
13, 14. (ሀ) ገባዖናውያን ወሳኝ የሆነ እርምጃ እንዲወስዱ ያደረጋቸው ምንድን ነው? (ለ) ገባዖናውያን ምን ዓይነት ዝንባሌ እንደነበራቸው የሚጠቁመን ምንድን ነው? እኛስ ከዚህ ምን መማር ይኖርብናል?
13 ስለ ገባዖናውያን የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ደግሞ እነዚህ ሰዎች ከእስራኤላውያን የተለየ አመለካከት እንደነበራቸው ይጠቁማል። አምላክ ፈቃዱን ከመፈጸም ወደኋላ እንደማይል ሙሉ እምነት ነበራቸው። እስራኤላውያን በኢያሱ መሪነት ዮርዳኖስን ተሻግረው አምላክ ለአብርሃም ቃል ወደገባለት ምድር ከገቡ በኋላ ቀጣዩ እርምጃ ከነዓናውያንን ከምድሪቱ ማባረር ነበር። (ዘዳግም 7:1-3) ይህም ገባዖናውያንን ይጨምር ነበር። እስራኤላውያን ኢያሪኮንና ጋይን ድል ካደረጉ በኋላ በጌልገላ አቅራቢያ ሰፈሩ። ገባዖናውያን እንደሌሎቹ ከነዓናውያን እንዳይጠፉ በመፍራት ጌልገላ ወደሚገኘው ወደ ኢያሱ ተወካዮች ላኩ። ከከነዓን ራቅ ብሎ ከሚገኝ አገር እንደመጡ በማስመሰል ከዕብራውያን ጋር የሰላም ስምምነት ለመዋዋል ጥያቄ አቀረቡ።
14 የገባዖናውያን ወኪሎች “እኛ ባሪያዎችህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ዝና ሰምተን፣ እጅግ ሩቅ ከሆነ አገር መጥተናል” በማለት አስረዱ። (ኢያሱ 9:3-9) ደግሞም ልብሳቸውና የያዙት ምግብ ሲታይ ከጌልገላ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኝ ቦታ ሳይሆን በእርግጥም ከሩቅ አገር የመጡ የሚያስመስል ነበር። [19] ኢያሱና የሕዝቡ አለቆች ምንም ስላልተጠራጠሩ ከገባዖናውያንና በአቅራቢያቸው ካሉት ሌሎች ከተሞች ጋር የሰላም ስምምነት ተዋዋሉ። ገባዖናውያን ይህን መላ የዘየዱት እንዳይጠፉ ስለፈሩ ብቻ ነው? በፍጹም፤ የእስራኤላውያንን አምላክ ሞገስ ለማግኘት ይፈልጉ እንደነበር ከሁኔታቸው መረዳት ይቻላል። ይሖዋም ገባዖናውያን ‘ለማኅበረሰቡና ለእግዚአብሔር መሠዊያ ዕንጨት ቈራጮችና ውሃ ቀጂዎች’ እንዲሆኑ ፈቀደላቸው። (ኢያሱ 9:11-27) ገባዖናውያንም ቢሆኑ በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ይህን ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ ለማከናወን ፈቃደኞች ሆነዋል። እንዲያውም ከባቢሎን ምርኮ ተመልሰው በቤተ መቅደሱ ግንባታ ከተካፈሉት ናታኒሞች መካከል አንዳንዶቹ ገባዖናውያን ሳይሆኑ አይቀሩም። (ዕዝራ 2:1, 2, 43-54፤ 8:20) እኛም ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት በመመሥረትና በእርሱ አገልግሎት ውስጥ ትሕትና የሚጠይቁ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቃደኛ በመሆን የእነርሱን ምሳሌ መኮረጅ እንችላለን።
የራሳችንን ጥቅም የምንሰዋ እንሁን
15. በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለተጠቀሱት ቦታዎች የማወቅ ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?
15 የመጽሐፍ ቅዱስ መልክዓ ምድር ኢየሱስና ሐዋርያው ጳውሎስ የተጓዙባቸውንና ያገለገሉባቸውን ቦታዎች ጨምሮ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱ ሌሎች ሥፍራዎችንም ያካትታል። (ማርቆስ 1:38፤ 7:24, 31፤ 10:1፤ ሉቃስ 8:1፤ 13:22፤ 2 ቆሮንቶስ 11:25, 26) ቀጥሎ ያሉትን ታሪኮች በማንበብ ጳውሎስ ያደረጋቸውን ጉዞዎች በዓይነ ኅሊናህ ለመሳል ሞክር።
16. በቤርያ የነበሩ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ አድናቆት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?
16 ጳውሎስ በሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት በዛሬው ጊዜ የግሪክ ግዛት ክፍል ወደሆነችው ፊልጵስዩስ ደረሰ። [33] (በካርታው ላይ በወይን ጠጅ ቀለም የተሰመረውን ተመልከት።) በዚህች ከተማ ውስጥ ሰፊ ምሥክርነት በመስጠቱ ምክንያት የታሰረ ሲሆን ሲለቀቅ ወደ ተሰሎንቄ ሄደ። (የሐዋርያት ሥራ 16:6 እስከ 17:1) እዚያም አይሁዶች ሁከት ስላስነሱበት የተሰሎንቄ ወንድሞች ጳውሎስ 65 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ቤርያ እንዲሄድ ለመኑት። በቤርያም አገልግሎቱን በተሳካ ሁኔታ አከናወነ፤ ሆኖም አይሁዳውያን እዚያ ድረስ በመሄድ የሕዝብ አመጽ አስነሱበት። በመሆኑም “ወንድሞች ጳውሎስን ቶሎ ብለው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሰደዱት። . . . የሸኙት ሰዎችም አቴና አደረሱት።” (የሐዋርያት ሥራ 17:5-15) ከዚህ እንደምንረዳው ወደ ክርስትና የተለወጡ አዳዲስ ወንድሞች ጳውሎስን 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እስከሚገኘው እስከ ኤጂያን ባሕር ድረስ በእግር ከሸኙት በኋላ በራሳቸው ወጪ መርከብ ተሳፍረው 500 ኪሎ ሜትር አብረውት የተጓዙ ይመስላል። እንዲህ ዓይነቱ ጉዞ አደገኛ ሊሆን ቢችልም እንኳ ወንድሞች አብረውት በመጓዝ የአምላክ ወኪል ከሆነው ከጳውሎስ ጋር መሆን መርጠዋል።
17. በሚሊጢንና በኤፌሶን መካከል ያለውን ርቀት ማወቃችን ምን እንድናደንቅ ያደርገናል?
17 ጳውሎስ በሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ሚሊጢን ወደብ ደረሰ። (በካርታው ላይ አረንጓዴውን መስመር ተመልከት።) እዚያም ሰዎችን ልኮ የኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎችን አስጠራ። በእነዚህ ቦታዎች መካከል ያለው ርቀት 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ይሆናል። እነዚህ ሽማግሌዎች ሥራቸውን ሁሉ ትተው ወደ ጳውሎስ ለመሄድ ሲነሱ በዓይነ ኅሊናህ ተመልከት። በጉዟቸው ላይ ከጳውሎስ ጋር ስለሚያደርጉት ስብሰባ እርስ በርስ ይጨዋወቱ እንደነበረ መገመት አያዳግትም። ስብሰባውን ካደረጉና የጳውሎስን ጸሎት ከሰሙ በኋላ “ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም አንገቱን ዐቅፈው ሳሙት።” ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ “እስከ መርከቡ ድረስ ሸኙት።” (የሐዋርያት ሥራ 20:14-38) ወደ ኤፌሶን የተመለሱት ከጳውሎስ ባገኙት ምክርና ሐሳብ ላይ እያሰላሰሉና እርስ በርስ እየተነጋገሩ ሊሆን ይችላል። እነዚህ የኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎች ከተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ምክርና ማበረታቻ ለማግኘት ያን ያህል ርቀት ለመጓዝ ፈቃደኛ መሆናቸው የሚያስደንቅ አይደለም? አንተስ ልትሠራበትና ልታሰላስልበት የምትችለው ምን ትምህርት አግኝተሃል?
ስለ ተስፋይቱ ምድርና ስለ ወደፊቱ ተስፋችን መማር
18. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ቦታዎችን በሚመለከት ምን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል?
18 እስከ አሁን ያየናቸው ምሳሌዎች አምላክ ለእስራኤላውያን ስለሰጣቸው ምድር ያለንን እውቀት ማስፋታችን ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነና በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በዚህች ምድር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ እንደሆኑ የሚያስገነዝቡ ናቸው። (ስለ ተስፋይቱ ምድር ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ ስለተጠቀሱ አጎራባች አገሮችም በመመርመር የእውቀት አድማሳችንን ማስፋት እንችላለን።) ስለ ተስፋይቱ ምድር ያለንን እውቀትና ማስተዋል ማስፋታችን እስራኤላውያን “ማርና ወተት ወደምታፈሰው” ምድር ለመግባት በዋነኝነት ምን ይጠበቅባቸው እንደነበር ሊያስገነዝበን ይገባል። እስራኤላውያን ወደዚያ ለመግባት ይሖዋን መፍራትና ትእዛዛቱን መጠበቅ ነበረባቸው።—ዘዳግም 6:1, 2፤ 27:3
19. ሁልጊዜ በትኩረት ልናሰላስልባቸው የሚገቡት ሁለት የገነት ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?
19 እኛም በተመሳሳይ ይሖዋን መፍራትና ከመንገዱ እንዳንወጣ መጠንቀቅ ይኖርብናል። እንዲህ በማድረግ ዛሬ እውነተኛ ክርስቲያኖች ያሉበት ዓለም አቀፍ የሆነው መንፈሳዊ ገነት ይበልጥ ውበት እንዲላበስ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። ይህ መንፈሳዊ ገነት ስላሉት የተለያዩ ገጽታዎችና በዚያ መኖር ስለሚያስገኘው በረከት ያለንን እውቀት በየጊዜው እያሰፋን መሄድ ያስፈልገናል። ወደፊት ደግሞ ከዚህ የበለጠ በረከት ይጠብቀናል። ኢያሱ እስራኤላውያንን ከዮርዳኖስ ባሻገር ወደሚገኘው ለምና አስደሳች ምድር እየመራ አስገብቷቸዋል። እኛም በቅርቡ ቃል በቃል ገነት ወደምትሆነው መልካም ምድር እንደምንገባ እርግጠኞች እንድንሆን የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን።
ታስታውሳለህ?
• በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተጠቀሱት ቦታዎች ያለንን እውቀትና ግንዛቤ የማስፋት ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?
• በዚህ ርዕስ ላይ ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ማብራሪያ ከተሰጠባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ የነበረህን ግንዛቤ ይበልጥ ያሰፋልህ የትኛው ነው?
• በአንዳንድ ታሪኮች ውስጥ የተጠቀሱትን ቦታዎች በተመለከተ የተሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ ምን ትምህርት እንድታገኝ ረድቶሃል?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
‘መልካሚቱን ምድር ተመልከት’
የይሖዋ ምሥክሮች በ2003/2004 ባደረጉት የአውራጃ ስብሳባ ላይ ‘መልካሚቱን ምድር ተመልከት ’ የተባለ አዲስ ብሮሹር በመውጣቱ በጣም ተደስተዋል። ይህ ብሮሹር ወደ 80 በሚጠጉ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ የተለያዩ ቦታዎችን በተለይ ደግሞ ተስፋይቱ ምድር በተለያዩ ዘመናት የነበራትን ገጽታ የሚያሳዩ ባለቀለም ካርታዎችንና ሰንጠረዦችን ይዟል።
ይህ የጥናት ርዕስ ከብሮሹሩ ላይ አንዳንድ ካርታዎችን የሚጠቅስ ሲሆን ካርታዎቹ የሚገኙበት ገጽ ጎላ ተደርጎ በቅንፍ ውስጥ ተጽፏል። ይህ አዲስ ብሮሹር ካለህ ስለ አምላክ ቃል ያለህን እውቀትና ማስተዋል ማስፋት እንድትችል ብሮሹሩ ስላሉት የተለያዩ ገጽታዎች በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርግ።
(1) አብዛኞቹ ካርታዎች በዚያ ላይ ስለሚገኙት ምልክቶች ተጨማሪ መግለጫ የሚሰጡ ሣጥኖች አሏቸው [18]። (2) ብዙዎቹ ካርታዎች በቦታዎች መካከል ያለውን ርቀት ለማስላት የሚያስችል ስኬል አላቸው [26]። (3) የሰሜንን አቅጣጫ የሚያሳየው ቀስት ሌሎች አቅጣጫዎችን እንድትለይ ይረዳሃል [19]። (4) ካርታዎቹ ባለ ቀለም መሆናቸው የአካባቢውን የመሬት አቀማመጥ ለመለየት ያስችላል [12]። (5) በካርታዎቹ ዙሪያ ያሉት ፊደላትና ቁጥሮች በካርታው ላይ የሰፈሩ ከተሞችን ወይም ሌሎች ቦታዎችን በቀላሉ ፈልጎ ለማግኘት ይረዳሉ [23]። (6) የቦታዎችን ስም በያዘው ማውጫ ላይ [ገጽ 34-35] የሚገኘው ደመቅ ተደርጎ የተጻፈው ቁጥር ገጹን የሚጠቁም ሲሆን ከጎኑ ያለው ፊደልና ቁጥር [ለምሳሌ E2] ቦታውን ፈልጎ ለማግኘት የሚረዳ ነው። ብሮሹሩን በዚህ መንገድ ከተጠቀምክበት የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትህንና ማስተዋልህን በማስፋት ረገድ በጣም ጠቃሚ መሣሪያ መሆኑን ትገነዘባለህ።
[በገጽ 16,17 ላይ የሚገኝ ግራፍ/ሰንጠረዥ/ካርታ]
ተፈጥሯዊ አካባቢዎችን የሚያሳይ ሰንጠረዥ
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
A. የታላቁ ባሕር ዳርቻ
B. የምዕራብ ዮርዳኖስ ሜዳማ አካባቢ
1. የአሴር ሜዳማ አካባቢ
2. የዶር የባሕር ጠረፍ አካባቢ
3. የሳሮን የግጦሽ ስፍራዎች
4. የፍልስጥኤም ሜዳ
5. መካከለኛው የምሥራቅ-ምዕራብ ሸለቆ
a. የመጊዶ ሜዳ
b. የኢይዝራኤል ሸለቆ
C. የምዕራብ ዮርዳኖስ ተራሮች
1. የገሊላ ኮረብታዎች
2. የቀርሜሎስ ኮረብታዎች
3. የሰማርያ ኮረብታዎች
4. ሼፌላህ (ቆላማው ምድር)
5. የይሁዳ ኮረብታማ አካባቢ
6. የይሁዳ ምድረ በዳ
7. ኔጌብ
8. የፋራን ምድረ በዳ
D. ዓረባ (ስምጥ ሸለቆ)
1. የሁላ ረባዳ ቦታ
2. የገሊላ ባሕር ክልል
3. የዮርዳኖስ ሸለቆ
4. የጨው ባሕር (ሙት ባሕር)
5. ዓረባ (የጨው ባሕር ደቡባዊ ክፍል)
E. የምሥራቅ ዮርዳኖስ ተራሮችና ሜዳዎች
1. ባሳን
2. ገለዓድ
3. አሞን እና ሞዓብ
4. የኤዶም ተራራ
F. የሊባኖስ ተራሮች
[ካርታ]
የአርሞንዔም ተራራ
ሞሬ
አቤላሞሖላ
ሱኮት
ዮግብሃ
ቤቴል
ጌልገላ
ገባዖን
ኢየሩሳሌም
ኬብሮን
ጋዛ
ቤርሳቤህ
ሰዶም?
ቃዴስ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ከነዓን
መጊዶ
ገለዓድ
ዶታይን
ሴኬም
ቤቴል (ሎዛ)
ጋይ
ኢየሩሳሌም (ሳሌም)
ቤተልሔም (ኤፍራታ)
መምሬ
ኬብሮን (መክፈላ)
ጌራራ
ቤርሳቤህ
ሰዶም?
ኔጌብ
ርኆቦት?
[ተራሮች]
ሞሪያ
[የውኃ አካላት]
የጨው ባሕር
[ወንዞች]
ዮርዳኖስ
[ሥዕል]
አብርሃም ምድሪቱን አቋርጦ ሄዷል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ጢሮአዳ
ሳሞትራቄ
ናጱሌ
ፊልጵስዩስ
አንፊጶል
ተሰሎንቄ
ቤርያ
አቴና
ቆሮንቶስ
ኤፌሶን
ሚሊጢን
ሩድ