የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 1—ዘፍጥረት
ጸሐፊው፦ ሙሴ
የተጻፈበት ቦታ፦ ምድረ በዳ
ተጽፎ ያለቀው፦ 1513 ከዘአበ
የሚሸፍነው ጊዜ፦ “በመጀመሪያ” እስከ 1657 ከዘአበ
መጽሐፉ ያሉት 50 አጫጭር ምዕራፎች ብቻ ነው። የመጀመሪያዎቹን አንድ ወይም ሁለት ገጾች ብቻ እንኳን ስታነብብ ስለ ሰው ልጅ የመጀመሪያ ታሪክ የሚገልጸውን ብቸኛውን ትክክለኛ ዘገባ እንዲሁም ሰው ፈጣሪው ከሆነው አምላክና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፍጥረታትን ከተሞላችው ምድር ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጽ ታሪክ ታገኛለህ! በተጨማሪም በእነዚህ ጥቂት ገጾች ውስጥ አምላክ ሰውን በምድር ላይ ስላስቀመጠበት ዓላማ ጥልቅ ማስተዋል ታገኛለህ። ማንበብህን ስትቀጥል ደግሞ ሰው ለምን እንደሚሞትና አሁን ለሚገኝበት የተመሰቃቀለ ሁኔታ የዳረገው ምን እንደሆነ ትገነዘባለህ። እንዲሁም ለእምነትና ለተስፋ ትክክለኛ መሠረት ስለ ሆነው ነገር አልፎ ተርፎም አምላክ የሰውን ልጅ ለማዳን እንደ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀምበትን የተስፋውን ዘር በሚመለከት የእውቀት ብርሃን ታገኛለህ። እነዚህን ሁሉ መረጃዎች የያዘው ግሩም መጽሐፍ ከ66ቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ የመጀመሪያ የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ ነው።
2 “ጀነሲስ”(ዘፍጥረት) “ምንጭ፣ ልደት” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ስሙ የተወሰደው ከግሪክኛው የሴፕቱጀንት ትርጉም ነው። በዕብራይስጥ ጽሑፎች ውስጥ የመጽሐፉ ስም ቤሬሺዝ፣ “በመጀመሪያ” (በግሪክኛ ኢነአርኬይ) ከሚለው የመጽሐፉ የመክፈቻ ቃል የተወሰደ ነው። ዘፍጥረት ከአምስቱ የኦሪት መጻሕፍት (ፔንታቱች-“አምስት ጥቅልሎች” ወይም “ባለ አምስት ጥቅል ጥራዝ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የተወሰደ የእንግሊዝኛ ቃል ነው) ውስጥ የመጀመሪያው ነው። ይህ በመጀመሪያ ላይ ቶራህ (ሕግ) ወይም ’የሙሴ ሕግ መጽሐፍ’ በመባል የሚታወቅ አንድ ወጥ መጽሐፍ እንደነበረና ከጊዜ በኋላ ግን ለአያያዝ እንዲያመች ሲባል በአምስት ጥቅሎች እንደ ተከፋፈለ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል።—ኢያሱ 23:6፤ ዕዝራ 6:18
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ይሖዋ አምላክ ነው፤ ሆኖም በመንፈሱ አነሳሽነት ሙሴ የዘፍጥረትን መጽሐፍ እንዲጽፍ አድርጓል። ሙሴ በዘፍጥረት ላይ የመዘገበውን መረጃ ያገኘው ከየት ነው? አንዳንዱ በመለኮታዊ ራእይ አማካኝነት በቀጥታ የተቀበለው ሊሆን ይችላል፤ ሌላው ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ አመራር በቃል የተላለፈለት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ሙሴ የቀድሞ አባቶቹ ጠብቀው ያቆዩአቸውን ስለ ሰው ልጅ መጀመሪያ የሚናገሩ ዘገባዎችን የያዙ እጅግ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሰነዶች አግኝቶ ሊሆን ይችላል።a
4 ሙሴ በመንፈስ አነሣሽነት መጽሐፉን ጽፎ ያጠናቀቀው በ1513 ከዘአበ በሲና ምድረ በዳ ሳይሆን አይቀርም። (2 ጢሞ. 3:16፤ ዮሐ. 5:39, 46, 47) ሙሴ በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጨረሻ ክፍል ላይ ሰፍሮ የሚገኘውን መረጃ ያገኘው ከየት ነው? ቅደመ አያቱ ሌዊ የዮሴፍ ግማሽ ወንድም ስለነበረ የራሱ ቤተሰብም እነዚህን ዝርዝር ጉዳዮች ጠንቅቆ ሊያውቅ ይችላል። ምናልባትም ሌዊ እስከ ሙሴ አባት እስከ እንበረም ዘመን ድረስ በሕይወት ሳይቆይ አይቀርም። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ መንፈስ ይህ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል በትክክል እንዲመዘገብ በማድረግ በኩል የሚጫወተው ሚና እንደሚኖር የተረጋገጠ ነው።—ዘጸ. 6:16, 18, 20፤ ዘኁ. 26:59
5 ዘፍጥረትን የጻፈው ማን ስለ መሆኑ ምንም ጥያቄ አይነሣም። የዘፍጥረትን መጽሐፍ አካትተው የያዙትን የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የሚጠቅሱ ’የሙሴ ሕግ መጽሐፍ’ የሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ መግለጫዎች ሙሴን ከተካው ከኢያሱ ዘመን በኋላ በብዛት ተጠቅሰው ይገኛሉ። እንዲያውም ከዚያ በኋላ በተጻፉት 27 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ ሙሴ 200 ለሚያክል ጊዜ ተጠቅሷል። ጸሐፊው ሙሴ መሆኑ በአይሁዳውያን ዘንድ አንዳችም ጥያቄ አስነስቶ አያውቅም። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ’የሕጉ’ ጸሐፊ ሙሴ መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜ የገለጹ ሲሆን ከሁሉ የሚበልጠው ማስረጃ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሙሴ የጻፈው ከይሖዋ ቀጥተኛ ትእዛዝ አግኝቶና በእርሱ መንፈስ አነሣሽነት ነው።—ዘጸ. 17:14፤ 34:27፤ ኢያሱ 8:31፤ ዳን. 9:13፤ ሉቃስ 24:27, 44
6 አንዳንድ ተጠራጣሪዎች ለመሆኑ ሙሴና ከእሱ በፊት የነበሩ ሰዎች መጻፍ ይችሉ ነበር? የመጻፍ ችሎታ የሰው ልጅ ከጊዜ በኃላ ያዳበረው ነገር አይደለምን? ብለው ጠይቀዋል። መጻፍ የተጀመረው በቀደምት የሰው ልጅ ታሪክ ምናልባትም በ2370 ከዘአበ ከመጣው የኖኅ የጥፋት ውኃ በፊት መሆኑ ግልጽ ነው። ሰው የመጻፍ ችሎታ ያዳበረው ቀደም ባለው ዘመን መሆኑን የሚያሳይ ምን ማረጋገጫ አለ? አርኪኦሎጂስቶች በቁፋሮ ያገኟቸው አንዳንድ የሸክላ ጽላቶች ከ2370 ከዘአበ የሚቀድም እድሜ እንዳላቸው ቢናገሩም እነዚህ ቀኖች ግምታዊ ናቸው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የከተማዎች ግንባታ፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች አጀማመርና የብረት መሣሪያዎች ሥራ ከጥፋት ውኃው ከረዥም ጊዜ በፊት የተጀመሩ መሆናቸውን በግልጽ እንደሚናገር ማስታወስ ይገባል። (ዘፍ. 4:17, 21, 22) ስለዚህ ሰዎች የአጻጻፍ ዘዴ ለማግኘት ብዙም አልተቸገሩም ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ይሆናል።
7 ዘፍጥረት በሌሎች ብዙ መንገዶችም በማስረጃ ከተረጋገጡ እውነታዎች ጋር አስገራሚ ስምምነት ያለው መሆኑ ተረጋግጧል። በሰብዓዊው ቤተሰብ የተለያዩ የዘር ግንዶች ውስጥ በአፈ ታሪክነት የሚወሱ ስለ ጥፋት ውኃና ከዚህ ጥፋት በሕይወት ስለተረፉ (አብዛኛውን ጊዜ በመርከብ አማካኝነት ስለ ዳኑ) ሰዎች የሚናገሩ ታሪኮች ቢኖሩም ስለ ጥፋት ውኃውና ስለ ተራፊዎቹ ትክክለኛ ዘገባ የሚያቀርበው የዘፍጥረት መጽሐፍ ብቻ ነው። በተጨማሪም የዘፍጥረት ዘገባ በሦስቱ የኖኅ ልጆች ማለትም በሴም፣ በካምና በያፌት የዘር ግንድነት የተገኙት የተለያዩ የሰው የዘር ወገኖች አሠፋፈር ጅምሩ ምን እንደሚመስል ይገልጻል።b በዩ ኤስ ኤ፣ ሚዙሪ በሚገኘው የዜኒያ ቲኦሎጂካል ሴሚነሪ የሚሠሩት ዶክተር ሜልቪን ጂ ካይል እንዲህ ብለዋል፦ “በሜሶጶጣሚያ ከሚገኝ አንድ ማዕከላዊ ቦታ በመነሣት ካማዊው የዘር ግንድ ወደ ደቡብ ምዕራብ፣ ያፌታዊው የዘር ግንድ ወደ ሰሜን ምዕራብ እንዲሁም ሴማዊው የዘር ቅርንጫፍ ’በሰናዖር ምድር’ አቅጣጫ ’ወደ ምሥራቅ’ መፍለሱ የማያከራክር ሐቅ ነው።”c
8 በተጨማሪም የዘፍጥረት መጽሐፍ እርስ በርሱ ያለው ስምምነትና ከተቀሩት በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም መሆኑ የመለኮታዊው ዘገባ ክፍል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። የመጽሐፉ ግልጽነት ጸሐፊው ይሖዋን የሚፈራና እውነትን የሚወድድ እንደነበረ እንዲሁም የብሔሩንም ሆነ በእስራኤል ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበራቸው ሰዎች የሠሯቸውን ኃጢአቶች ያለ ማመንታት መጻፉን ያሳያል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ ምዕራፍ ማብቂያ ላይ ተገልጾ እንደሚገኘው ትንቢቶቹ ያለአንዳች መዛነፍ ሙሉ በሙሉ በትክክል መፈጸማቸው የዘፍጥረት መጽሐፍ በይሖዋ አምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ በምሳሌነት የሚጠቀስ የላቀ መጽሐፍ መሆኑን ያረጋግጣሉ።—ዘፍ. 9:20-23፤ 37:18-35፤ ገላ. 3:8, 16
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
30 ዘፍጥረት በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል መጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን የይሖዋ አምላክን ክብራማ ዓላማዎች በማስተዋወቅ ረገድ ይህ ነው የማይባል ጥቅም አለው። ወደ ኋላ ላይ የሚገኙትን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ለማስተዋል የሚያስችል እንዴት ያለ ግሩም መሠረት ነው! ሰፊ በሆነው የዘገባ አድማሱ በኤደን ስለነበረው ጽድቅ የሰፈነበት ዓለም አጀማመርና ፍጻሜ፣ ስለ መጀመሪያው አምላካዊ ያልሆኑ ሰዎች ያሉበት ዓለም ማቆጥቆጥና አደገኛ በሆነ ሁኔታ መስፋፋት እንዲሁም በጊዜያችን ስለሚገኘው ክፉ ዓለም አጀማመር ይተርካል። የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ጭብጥ ተስፋ በተሰጠበት “ዘር” በሚመራው መንግሥት አማካኝነት የይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥ መሆኑን ይናገራል። ሰው የሚሞትበትን ምክንያት ይገልጻል። ከዘፍጥረት 3:15 ጀምሮ በዘሩ በሚተዳደረው መንግሥት ሥር ስለሚኖረው የአዲስ ዓለም ሕይወት ተስፋ ይናገራል። በተለይም ደግሞ ይህ አምላክ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር ስለነበረው ግንኙነት በሚናገረው ዘገባ ላይ በጉልህ ተንጸባርቋል። የሁሉም የሰው ልጆች ዋነኛ ዓላማ የጸና አቋማቸውን መጠበቃቸውና የይሖዋን ስም ማስቀደሳቸው እንደሆነ በመግለጽ ረገድም በጣም ጠቃሚ ነው።—ሮሜ 5:12, 18፤ ዕብ. 11:3-22, 39, 40፤ 12:1፤ ማቴ. 22:31, 32
31 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን እያንዳንዱን አበይት ክንውንና ጉልህ ሚና የነበረውን ሰው ይጠቅሳሉ። ከዚህም በላይ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በጠቅላላ እንደታየው በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገቡት ትንቢቶች ያለ አንዳች ስህተት ተፈጽመዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በአብርሃም ዘር ላይ የደረሰውን የ“አራት መቶ ዓመት” መከራ ሲሆን እስማኤል በይስሐቅ ላይ ባሾፈበት ጊዜ በ1913 ከዘአበ ጀምሮ እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡበት በ1513 ከዘአበ ተደምድሟል።d (ዘፍ. 15:13) ትልቅ ትርጉም ያዘሉ ሌሎች ብዙ ትንቢቶችና ፍጻሜያቸው በዚህ መጽሐፍ የእንግሊዝኛ ቅጂ ገጽ 18 ላይ በሚገኘው ሠንጠረዥ ላይ ተዘርዝረዋል። በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱት መለኮታዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች እምነትን በመገንባትና ማስተዋል በመጨመር በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው። የጥንት ነቢያት እንዲሁም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከዘፍጥረት መጽሐፍ ምንባቦች በተደጋጋሚ ይጠቅሱና ተግባራዊነታቸውን ያስረዱ ነበር። የእነርሱን ምሳሌ መከተላችን ተገቢ ነው፤ ለዚህም ሠንጠረዡን ማጥናታችን ሊረዳን ይችላል።
32 የዘፍጥረት መጽሐፍ ጋብቻን፣ ባልና ሚስት ሊኖራቸው የሚገባውን ተገቢ ግንኙነት እንዲሁም የራስነት መሠረታዊ ሥርዓትንና ለቤተሰብ ሥልጠና መስጠትን በሚመለከት አምላክ ያለውን ፈቃድና ዓላማ በግልጽ ያስቀምጣል። ኢየሱስ ራሱ የዘፍጥረት መጽሐፍን የመጀመሪያና ሁለተኛ ምዕራፎች እንደሚከተለው በማለት በአንድ ዓረፍተ ነገር አጠቃልሎ ገልጿቸዋል። “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፣ አለም፦ ‘ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፣ ሁለቱም አንድ ሥራ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን?“ (ማቴ. 19:4, 5፤ ዘፍ. 1:27፤ 2:24) የዘፍጥረት ዘገባ የሰብዓዊውን ቤተሰብ የዘር ሐረግ ዝርዝር ከማቅረብም በተጨማሪ ሰው በዚህ ምድር ላይ የኖረበትን ዘመን ለማስላት የሚያስችል ጠቃሚ የሆነ መረጃ ይሰጣል።—ዘፍ. ምዕ. 5, 7, 10, 11
33 በተጨማሪም በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰውን በእምነት አባቶች ይተዳደር ስለነበረው ማኅበረሰብ የሚናገረውን ታሪክ ማጥናት ለአንድ የቅዱሳን ጽሑፎች ተማሪ በጣም ጠቃሚ ነው። በእምነት አባቶች የሚተዳደረው ማኅበረሰብ ከኖኅ ዘመን አንስቶ ሕጉ በሲና ተራራ እስከ ተሰጠበት ጊዜ ድረስ በአምላክ ሕዝቦች ዘንድ የነበረው ቤተሰባዊ መስተዳድር ነው። በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ የተካተቱት ብዙዎቹ ዝርዝር ሐሳቦች ቀደም ሲል በእምነት አባቶች በሚተዳደረው ማኅበረሰብ ውስጥ ይተገበሩ ነበር። እንደ ማኅበረሰባዊ የደኅንነት ዋስትና (18:32)፣ ማኅበረሰባዊ ተጠያቂነት (19:15)፣ የይሙት በቃ ፍርድ እንዲሁም የደምና የሕይወት ቅድስና (9:4-6)፣ አምላክ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ለሚያደርጉ ሰዎች ያለው ጥላቻና (11:4-8) የመሳሰሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች በታሪክ ዘመናት በሙሉ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ሲንጸባረቁ ኖረዋል። ብዙ ሕግ ነክ ጉዳዮችና መግለጫዎች፣ በኢየሱስ ዘመን የተከናወኑትን ጨምሮ ከጊዜ በኋላ የተፈጸሙ ነገሮችን በግልጽ ለመረዳት ያስችላሉ። ሰዎችንና ንብረትን በሌላ ወገን ኃላፊነት ሥር እንዲውሉ ማድረግን ስለሚቆጣጠረውና (ዘፍ. 31:38, 39፤ 37:29-33፤ ዮሐ. 10:11, 15፤ 17:12፤ 18:9) የንብረት ዝውውር የሚካሄድበትን ተገቢ አሠራር (ዘፍ. 23:3-18) እንዲሁም የብኩርናን መብት የተቀበለ ሰው የሚያገኘውን ውርሻ ስለሚመለከተው (48:22) የእምነት አባቶች ሕግ ማወቃችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ማስተዋል ለማግኘት የግድ አስፈላጊ ነው። የእምነት አባቶች በሚያስተዳድሩት ማኅበረሰብ ውስጥ ይሠራባቸው የነበሩትና በሕጉ ውስጥ የተጨመሩት ሌሎች ልማዶች ደግሞ መሥዋዕት ማቅረብ፣ ግርዘት (በመጀመሪያ ለአብርሃም የተሰጠው)፣ ቃል ኪዳን መግባት፣ የዋርሳ ጋብቻ (38:8, 11, 26) እንዲሁም አንድን ጉዳይ በመሃላ ማረጋገጥን የመሳሰሉት ናቸው።—22:16፤ 24:3e
34 የመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ መጽሐፍ የሆነው ዘፍጥረት ጽኑ አቋም መያዝን፣ እምነትን፣ የታመኑ መሆንን፣ ታዛዥነትን፣ አክብሮትን፣ መልካም ምግባርንና ድፍረትን የሚመለከቱ በርካታ ትምህርቶች ይዟል። ጥቂት ምሳሌዎች እነሆ፦ ሄኖክ ክፉ ጠላቶች ቢኖሩትም አካሄዱን ከአምላክ ጋር ለማድረግ የነበረው እምነትና ድፍረት፤ ኖኅ ያሳየው ጽድቅ፣ እንከን የለሽነትና ፍጹም ታዛዥነት፤ የአብርሃም እምነት፣ ቆራጥነትና ጽናት፣ በቤተሰብ ራስነቱና የአምላክን ትእዛዛት ለልጆቹ አስተማሪ በመሆን በኩል ይሰማው የነበረው የኃላፊነት ስሜት፣ ለጋስነቱና ፍቅሩ፤ ሣራ ለባሏ ራስነት የነበራት ተገዢነትና ታታሪነቷ፤ የያዕቆብ ታጋሽነትና አምላክ ስለ ሰጠው ተስፋ ከልቡ ያስብ የነበረ መሆኑ፤ ዮሴፍ ለአባቱ የነበረው ታዛዥነት፣ ንጹህ የሥነ ምግባር አቋሙ፣ ድፍረቱ፣ በእስር ቤት የነበረው መልካም ጠባይ፣ ለበላይ ባለ ሥልጣናት የነበረው አክብሮት፣ በትሕትና አምላክን ከፍ ከፍ ማድረጉ እንዲሁም ወንድሞቹን በምሕረት ይቅር ማለቱና እነዚህ ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ስም ለመቀደስ የነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት አንዳንዶቹ ናቸው። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ ዮሴፍ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ባሉት 2,369 ዓመታት ውስጥ አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር በማድረግ የተመላለሱ ሰዎች እነዚህን በምሳሌነት የሚጠቀሱ ድንቅ ባህርያት በሕይወታቸው አንጸባርቀዋል።
35 በእርግጥም የዘፍጥረት መጽሐፍ በውስጡ ግሩም የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ታሪክ ስለያዘ እምነትን በማጎልበት ረገድ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እነዚህ ሰዎች የነበራቸው የተፈተነ እምነት አምላክ ወደ ሠራትና ወደ ፈጠራት ከተማ ማለትም የይሖዋን ታላቅ ስም በመቀደሱ ተግባር ተቀዳሚውን ቦታ በያዘው በተስፋው ዘር አማካኝነት ከረዥም ዘመን ጀምሮ ሲያዘጋጀው ወደቆየው ንጉሣዊ መስተዳድር ለመግባት እንዲጣጣሩ ረድቷቸዋል።—ዕብ. 11:8, 10, 16
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
c ቢብሊካል ሂስትሪ ኢን ዘ ላይት ኦቭ አርኪኦሎጂካል ዲስከቨሪ 1934፣ ዲ ኢ ሃርት-ዴቪስ ገጽ 5
e መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) 1952 ገጽ 432-45