የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ለይስሐቅ ሚስት መፈለግ
በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ የተቀመጠው አረጋዊ ሰው በጣም ደክሞታል። እሱና አገልጋዮቹ ከአሥር ግመሎቻቸው ጋር ከቤርሳቤህ ተነሥተው እስከ ሰሜናዊው መስጴጦምያ ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘዋል።a አሁን የሚፈልጉበት ቦታ ስለ ደረሱ ይህ በጣም የደከመው መንገደኛ የተሰጠውን አስቸጋሪ ተልእኮ እያሰላሰለ ነው። ይህ ሰው ማን ነበር? ይህን አስቸጋሪ ጉዞ ያደረገው ለምንድን ነው?
ሰውዬው በአብርሃም ‘ቤት ካሉት ሁሉ በዕድሜ የገፋው’ የአብርሃም አገልጋይ ነበር። (ዘፍጥረት 24:2) ምንም እንኳ የሰውዬው ስም በታሪኩ ውስጥ ባይገለጽም በአንድ ወቅት አብርሃም “በቤቴ የተወለደ ሰው ይወርሰኛል” ብሎ የተናገረለት ኤሊዔዘር እንደ ነበረ ግልጽ ነው። (ዘፍጥረት 15:2, 3) እርግጥ ይህ የሆነው አብርሃምና ሣራ ከመውለዳቸው በፊት ነው። አሁን ልጃቸው ይስሐቅ 40 ዓመቱ ሆኖታል፤ ኤሊዔዘር የአብርሃም ወራሽ ባይሆንም አሁንም ያገለግላቸዋል። ስለዚህ አብርሃም አንድ አስቸጋሪ ጥያቄ ሲያቀርብለት ጉዳዩን ለመፈጸም ተስማማ። ይህ ጥያቄ ምን ነበር?
አንድ አስቸጋሪ ተልእኮ
በአብርሃም ዘመን አንድ ጋብቻ ቤተሰቡን ብቻ ሳይሆን መላውን ነገድ ወይም ማኅበረሰብ ይነካ ነበር። ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ መምረጣቸው የተለመደ ነበር። ሆኖም አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ሚስት በሚፈልግበት ወቅት አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞታል። በአካባቢው ያሉ ከነዓናውያን ከሚከተሏቸው አምላካዊ ያልሆኑ መንገዶች አንፃር ሲታይ ከእነሱ መካከል ለትዳር የሚሆን ሰው መምረጥ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። (ዘዳግም 18:9-12) በተጨማሪም በዚያን ወቅት አንድ ሰው በራሱ ነገድ ውስጥ ያለውን ግለሰብ ማግባቱ የተለመደ ቢሆንም እንኳ የአብርሃም ዘመዶች የሚኖሩት በብዙ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው በሰሜናዊው መስጴጦምያ ነበር። ይሖዋ ‘ይህችንም ምድር እሰጥሃለሁ’ በማለት የከነዓን ምድርን እንደሚሰጠው ለአብርሃም ቃል ስለገባለት ይስሐቅ እዚያ ሄዶ እንዲቀመጥ ሊያደርግ አይችልም። (ዘፍጥረት 24:7) ስለዚህ አብርሃም ኤሊዔዘርን “ወደ አገሬና ወደ ተወላጆቼ ትሄዳለህ፣ ለልጄ ለይስሐቅም ሚስትን ትወስድለታለህ” አለው።— ዘፍጥረት 24:4
ኤሊዔዘር ከዚያ ረዥም ጉዞ በኋላ ስለ ተልእኮው እያሰላሰለ በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ አረፍ አለ። ብዙም ሳይቆይ ሴቶች ለማታ ውኃ ለመቅዳት ወደ ጉድጓዱ እንደሚመጡ ትዝ አለው። ስለዚህ ይሖዋን እንዲህ ሲል ለመነው:- “ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርሷም:- አንተ ጠጣ፣ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፣ እርስዋ ለባርያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።”— ዘፍጥረት 24:14
ገና እየጸለየ ሳለ ርብቃ የተባለች አንዲት የተዋበች ወጣት መጣች። ኤሊዔዘር “ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ” አላት። ርብቃ ውኃ ከሰጠችው በኋላ “ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉ እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ” አለችው። አንድ የተጠማ ግመል በአሥር ደቂቃ ውስጥ ብቻ 95 ሊትር ውኃ ሊጠጣ ስለሚችል ይህ ትልቅ ልግስና ነበር! የኤሊዔዘር ግመሎች ይህን ያህል ተጠምተው የነበሩም ይሁን አይሁን ርብቃ ልታደርገው ያሰበችው ነገር አድካሚ መሆኑን ሳታውቅ አትቀርም። “ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፣ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጉድጓዱ ሮጠች፣ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች።”— ዘፍጥረት 24:15-20
ኤሊዔዘር በጉዳዩ የይሖዋ አመራር እንዳለበት ስለ ተገነዘበ በዛሬው ገንዘብ ሲሰላ 1, 400 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ አንድ የወርቅ የአፍንጫ ቀለበትና ሁለት የወርቅ አምባሮች ለርብቃ ሰጣት። ርብቃ የአብርሃም ወንድም የናኮር የልጅ ልጅ እንደሆነች ስትነግረው ኤሊዔዘር ለአምላክ የምስጋና ጸሎት አቀረበ። “እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ” አለ። (ዘፍጥረት 24:22-27) ኤሊዔዘር ወደ ርብቃ ቤተሰብ ሄደ። ከዚያ በኋላ ርብቃ የይስሐቅ ሚስት ሆነች፤ በዚህ መንገድ የመሲሑ የኢየሱስ ቅድመ አያት የመሆን መብት አግኝታለች።
ለእኛ የሚሆን ትምህርት
ኤሊዔዘር ለይስሐቅ ፈሪሃ አምላክ ያላት የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ያደረገውን ጸሎት የታከለበት ጥረት ይሖዋ ባርኮለታል። ሆኖም የይስሐቅ ጋብቻ አምላክ በአብርሃም በኩል የተስፋውን ዘር ለማስገኘት ከነበረው ዓላማ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ እንደ ነበረ አስታውስ። ስለዚህ ይህ ታሪክ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት የጸለየ ሁሉ በተአምር ይሰጠዋል የሚል መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ሊያደርገን አይገባም። ሆኖም መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በጥብቅ ከተከተልን ይሖዋ በጋብቻም ሆነ በነጠላነት ሕይወት የሚመጡትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል።— 1 ቆሮንቶስ 7:8, 9, 28፤ ከፊልጵስዩስ 4:11-13 ጋር አወዳድር።
ኤሊዔዘር ነገሮችን በይሖዋ መንገድ ለማከናወን ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። እኛም ከይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምቶ መኖር ሁልጊዜ ቀላል ሆኖ ላናገኘው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል ለቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴያችን እንቅፋት የማይሆን ሥራ፣ ፈሪሃ አምላክ ያለው/ያላት የትዳር ጓደኛ፣ የሚያንጹ ባልንጀሮችና ወራዳ ያልሆነ መዝናኛ ማግኘት ሊያስቸግረን ይችላል። (ማቴዎስ 6:33፤ 1 ቆሮንቶስ 7:39፤ 15:33፤ ኤፌሶን 4:17-19) ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ያላቸውን አቋም የማያላሉ ሰዎችን ይሖዋ ይረዳቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚል ተስፋ ይሰጣል።— ምሳሌ 3:5, 6
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከግመሎች አማካይ ፍጥነት አንፃር ጉዞው ከ25 ቀናት በላይ ሳይፈጅ አይቀርም።