ሴቶች በጥንት የአምላክ አገልጋዮች ዘንድ የነበራቸው የተከበረ ቦታ
“ይሖዋ አምላክ ‘ሰው ብቻውን መኖሩን ይቀጥል ዘንድ መልካም አይደለም፤የተሟላ የምታደርገውን ረዳት እፈጥርለታለሁ ’ አለ።”—ዘፍጥረት 2:18 አዓት
1. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ሴቶች በጥንት ዘመን የነበራቸውን ሕይወት የገለጸው እንዴት ነው?
“በጥንት የሜዲትራንያን ባሕር አጎራባች አገሮችም ሆነ በቅርብ ምሥራቅ አገሮች ሴቶች በሠለጠነው የምዕራቡ ኅብረተሰብ ውስጥ የሚያገኙትን ዓይነት ነፃነት አያገኙም ነበር። በዚያን ወቅት ባሪያዎች ለጌታቸው እንዲሁም ልጆች ለአዋቂዎች የሚገዙትን ያህል ሴቶች ለወንዶች ይገዙ ነበር። . . . ወንዶች ልጆች ከሴቶች ልጆች ይልቅ ይወደዱ ነበር፤ ከዚህም በላይ አንዳንድ ጊዜ ሴት ሕፃናት ለሐሩርና ለቁር ተጋልጠው እንዲሞቱ ይደረግ ነበር።” አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በጥንት ዘመን የነበረውን የሴቶች ሕይወት የገለጸው በዚህ መንገድ ነበር።
2, 3. (ሀ) በአንድ ሪፖርት መሠረት በአሁኑ ወቅት ያለው የብዙ ሴቶች ሁኔታ ምንድን ነው? (ለ) ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?
2 ዛሬ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ያለው ሁኔታ ከዚህ የተሻለ አይደለም። በ1994 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ ያቀረበው ዓመታዊ ሪፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች እየደረሰባቸው ባለው ሁኔታ ላይ አተኩሮ ነበር። በኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ ይህን ሪፖርት አስመልክቶ ሲናገር “ከ193 አገሮች የተገኘው መረጃ ሴቶች በየቀኑ አድልዎ እንደሚደረግባቸው ይጠቁማል” ብሏል።
3 በመላው ዓለም ባሉ የይሖዋ ሕዝብ ጉባኤዎች መካከል ከተለያዩ ባህሎች የመጡ ብዙ ሴቶች ስለሚገኙ አንዳንድ ጥያቄዎች ይነሣሉ፦ ከላይ የተገለጸው አያያዝ አምላክ ለሴቶች በመጀመሪያ እንዲደረግላቸው ያሰበው ዓይነት አያያዝ ነውን? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት የይሖዋ አምላኪዎች ሴቶችን ይይዟቸው የነበረው እንዴት ነው? በአሁኑ ጊዜስ ሴቶች መያዝ ያለባቸው እንዴት ነው?
“ረዳት” እና “የተሟላ የምታደርገው”
4. የመጀመሪያው ሰው በኤደን ገነት ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ብቻውን ከኖረ በኋላ ይሖዋ ምን አለ? ከዚያ በኋላስ አምላክ ምን አደረገ?
4 አዳም በኤደን የአትክልት ቦታ ለተወሰነ ጊዜ ብቻውን ከኖረ በኋላ ይሖዋ “ሰው ብቻውን መኖሩን ይቀጥል ዘንድ መልካም አይደለም፤ የተሟላ የምታደርገውን ረዳት እፈጥርለታለሁ” አለ። (ዘፍጥረት 2:18 አዓት) አዳም ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም የፈጣሪን ዓላማ ለመፈጸም አንድ ሌላ ነገር ያስፈልግ ነበር። ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ሴትን ፈጥሮ የመጀመሪያውን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አከናወነ።—ዘፍጥረት 2:21–24
5. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ረዳት” ተብሎ የተተረጎመውን የዕብራይስጥ ቃል ብዙውን ጊዜ የተጠቀሙበት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የመጀመሪያይቱን ሴት ‘የተሟላ የምታደርገው’ ብሎ መጥራቱ ምን ያመለክታል?
5 “ረዳት” እና “የተሟላ የምታደርገውን” የሚሉት ቃላት አምላክ ለሴት የሰጣት ቦታ ዝቅተኛ እንደሆነ ያሳያሉን? በፍጹም አያሳዩም። ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች “ረዳት” ተብሎ የተተረጎመውን የዕብራይስጥ ስም (ኢዘር) አምላክን ለመግለጽ ተጠቅመውበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ “ረዳታችንና መጠጊያችን” ሆኗል። (መዝሙር 33:20፤ ዘጸአት 18:4፤ ዘዳግም 33:7) እንዲያውም በሆሴዕ 13:9 ላይ ይሖዋ ራሱን የእስራኤል ‘ረዳት’ በማለት ጠርቷል። “የተሟላ የምታደርገውን” ተብሎ የተተረጎመውን የዕብራይስጥ ቃል (ኔገድ) በተመለከተ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ሲያብራሩ “ሰውዬው የሚያስፈልገው እርዳታ በየቀኑ ለሚያከናውነው ሥራ የሚሰጥ እገዛ ወይም ልጅ መውለድ ብቻ ሳይሆን . . . አብሮ መሆን የሚያስገኘው የጋራ መደጋገፍ ነው” ብለዋል።
6. ሴት ከተፈጠረች በኋላ ምን ተብሎ ነበር? ለምንስ?
6 ስለዚህ ይሖዋ ሴትን “ረዳት” እና “የተሟላ የምታደርገውን” ብሎ ሲጠራ በምንም ዓይነት መንገድ ሴትን ዝቅ ማድረጉ አልነበረም። ሴት የራሷ የሆነ የተለየ አእምሯዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ አሠራር አላት። ወንድን የተሟላ ለማድረግ ተስማሚ የሆነች የምታረካ ተጓዳኝ ናት። የተለያዩ ቢሆኑም ሁለቱም ፈጣሪ ‘ምድርን ለመሙላት’ ላለው ዓላማ ያስፈልጋሉ። እግዚአብሔር ያደረገውን ሁሉ ተመልክቶ “እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” ያለው ሰውዬውም ሆነ ሴትየዋ ከተፈጠሩ በኋላ እንደ ነበረ ግልጽ ነው።—ዘፍጥረት 1:28, 31
7, 8. (ሀ) በኤደን ውስጥ ኃጢአት በመሠራቱ የሴቶች ቦታ የተነካው እንዴት ነው? (ለ) ዘፍጥረት 3:16 በይሖዋ አምላኪዎች መካከል መፈጸሙን በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?
7 ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ሰውዬውና ሴትየዋ የነበሩበት ሁኔታ ተለወጠ። በሠሩት ኃጢአት የተነሣ ይሖዋ በሁለቱም ላይ የፍርድ ብያኔ አስተላለፈ። ይሖዋ በኃጢአቷ ምክንያት እንዲመጣባት የፈቀደውን ነገር እሱ ራሱ እንዳደረገው ያህል “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ” በማለት ለሔዋን ነገራት። አክሎም “በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” አላት። (ዘፍጥረት 3:16) ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አያሌ ሚስቶች በባሎቻቸው ተጨቁነዋል፤ ብዙውን ጊዜም የጭካኔ ተግባር ተፈጽሞባቸዋል። አብዛኛውን ጊዜም ረዳቶችና የተሟላ የሚያደርጉ እንደሆኑ ተደርገው ከመታየት ይልቅ እንደ ባሪያዎች ተቆጥረዋል።
8 ታዲያ ዘፍጥረት 3:16 መፈጸሙ ሴቶች ለሆኑት የይሖዋ አምላኪዎች ምን ትርጉም ነበረው? ዝቅተኛና አነስተኛ ቦታ እንዳላቸው ተደርገው ይታዩ ነበርን? በጭራሽ አልነበረም! ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ባሉ አንዳንድ ኅብረተሰቦች ውስጥ ተቀባይነት የሌላቸው የሚመስሉ ባህሎችንና ልማዶችን ስለሚተርኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ምን ለማለት ያቻላል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ባህሎችን መረዳት
9. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩትን ሴቶች የሚመለከቱ ባህሎችን ስንመረምር በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡን ሦስት ነገሮች ምን ምን ናቸው?
9 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ሴቶችን በሚገባ ይይዟቸው ነበር። እርግጥ በዚያ ዘመን የነበሩትን ሴቶች የሚመለከቱ ባህሎችን ስንመረምር በርካታ ነገሮችን በአእምሯችን መያዛችን ይጠቅመናል። በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ በክፉ ወንዶች የራስ ወዳድነት ጭቆና የተነሣ ስለሚፈጠሩ መጥፎ ሁኔታዎች ሲናገር አምላክ ሴቶች እንዲህ ባለ ሁኔታ መያዛቸውን ይቀበላል ማለት አይደለም። በሁለተኛ ደረጃ ይሖዋ አገልጋዮቹ የነበሯቸውን አንዳንድ ባህሎች ለተወሰነ ጊዜ ቢፈቅድም ሴቶችን ለመጠበቅ ብሎ እነዚህን ልማዶች ተቆጣጥሯቸዋል። በሦስተኛ ደረጃ በዘመናዊ የአቋም መመዘኛዎች ተመርኩዘን የጥንት ባህሎችን እንዳንገመግም መጠንቀቅ አለብን። በአሁኑ ወቅት ለሚኖሩ ሰዎች የማያስደስቱ የሚመስሉ አንዳንድ ልማዶች በዚያ ወቅት የነበሩ ሴቶችን ዝቅ እንደተደረጉ እንዲሰማቸው ያደርጋሉ ማለት አይቻልም። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
10. ይሖዋ ከአንድ በላይ ማግባትን እንዴት ይመለከተው ነበር? አንድ ላንድ የሚለውን የመጀመሪያ ሥርዓት በጭራሽ እንዳልለወጠው የሚጠቁመው ምንድን ነው?
10 ከአንድ በላይ ማግባት፦a ይሖዋ በመጀመሪያ የነበረው ዓላማ አንድ ወንድ አንዲት ሚስት ብቻ እንድትኖረው ነበር። አምላክ ለአዳም የፈጠረለት አንዲት ሚስት ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 2:21, 22) በኤደን ዓመፅ ከተደረገ በኋላ የቃየል ዘር የሆነ ሰው ካንድ በላይ ማግባትን ጀመረ። ውሎ አድሮ እንደ ልማድ ሆነና በአንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ዘንድ ተቀባይነት አገኘ። (ዘፍጥረት 4:19፤ 16:1–3፤ 29:21–28) ይሖዋ የእስራኤል ሕዝብ ቁጥር እንዲጨምር ሲል ከአንድ በላይ ማግባትን ቢፈቅድም እንኳ ሚስቶችና ልጆች ጥበቃ እንዲያገኙ ይህን ልማድ በመቆጣጠር ለሴቶች ያለውን አሳቢነት አሳይቷል። (ዘጸአት 21:10, 11፤ ዘዳግም 21:15–17) ከዚህም በላይ ይሖዋ መጀመሪያ ያወጣውን አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት የሚል ሥርዓት አልለወጠውም። ‘ብዙ ተባዙ፣ ምድርን ሙሉአት’ የሚለውን ትእዛዝ በድጋሜ የታዘዙት ኖኅና ልጆቹ አንድ አንድ ሚስት ብቻ ነበራቸው። (ዘፍጥረት 7:7፤ 9:1፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) አምላክ ከእስራኤል ጋር የነበረውን ዝምድና በምሳሌ ሲያስረዳ ራሱን አንዲት ሚስት ብቻ ባለው ባል መስሏል። (ኢሳይያስ 54:1, 5) ከዚህም ሌላ ይሖዋ መጀመሪያ ያወጣውን አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት የሚል ሥርዓት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና አጽንቶታል፤ ይህ ሥርዓት በመጀመሪያው የክርስቲያን ጉባኤ ይሠራበት ነበር።—ማቴዎስ 19:4–8፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:2, 12
11. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ጥሎሽ የሚሰጠው ለምን ነበር? ይህስ ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ ነበርን?
11 ጥሎሽ መስጠት፦ አንሸንት ኢዝራኤል—ኢትስ ላይፍ ኤንድ ኢንስቲቲውሽንስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ይህ ለልጃገረዲቱ ቤተሰብ የተወሰነ ገንዘብ ወይም ለገንዘቡ ምትክ የሚሆን ነገር የመክፈል ግዴታ የእስራኤላውያንን ጋብቻ ሽያጭ እንደሚያስመስለው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ [ጥሎሽ] ልጅቷን በመስጠታቸው ምክንያት ለቤተሰቧ ካሳ እንዲሆን የሚከፈል ከልጅቷ ጋር የሚተካከል ዋጋ ተደርጎ መታየት የለበትም።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ስለዚህ ጥሎሽ የልጅቷ ቤተሰብ ያጡትን እሷ ትሰጣቸው የነበረውን አገልግሎት እንዲሁም ቤተሰቦቿ እሷን ለማሳደግ ሲሉ የደከሙትን ድካምና ያወጡትን ወጪ ለመካስ ያገለግል ነበር። እንግዲያውስ ጥሎሽ ልጅቷን ዝቅ ከማድረግ ይልቅ ለቤተሰቧ ታበረክት የነበረውን ጠቀሜታ ያረጋግጣል።—ዘፍጥረት 34:11, 12፤ ዘጸአት 22:16፤ ጥር 15, 1989 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 21–4 ተመልከት።
12. (ሀ) አንዳንድ ጊዜ የተጋቡ ወንዶችና ሴቶች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠሩት ምን ተብለው ነው? እነዚህ ቃላት ሴቶችን ቅር ያሰኙ ነበርን? (ለ) ይሖዋ በኤደን ውስጥ ስለ ተጠቀመባቸው ቃላት ምን ሊስተዋል ይገባል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
12 ባሎች “ባለቤት” መሆናቸው፦ በ1918 ከዘአበ በአብርሃምና በሣራ ሕይወት ውስጥ የተከሰተ አንድ ገጠመኝ በዘመናቸው ያገባ ወንድ እንደ “ባለቤት”፣ (በዕብራይስጥ በአል) እና ያገባች ሴት ደግሞ ‘ባለቤት ያላት’ (በዕብራይስጥ በኡላ) ተደርገው መታየታቸው የተለመደ እንደነበረ ያሳያል። (ዘፍጥረት 20:3 አዓት) እነዚህ ቃላት ከዚህ በኋላ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አልፎ አልፎ ቢገኙም ከክርስትና በፊት የነበሩ ሴቶች ቅር እንደተሰኙባቸው የሚጠቁም መረጃ የለም።b (ዘዳግም 22:22 አዓት) ሆኖም ሚስቶች እንደ ንብረት መቆጠር የለባቸውም። ንብረት ወይም ሀብት ይገዛል፣ ይሸጣል እንዲሁም ይወረሳል፤ ሚስት ግን እንዲህ አይደለችም። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት” ይላል።—ምሳሌ 19:14፤ ዘዳግም 21:14
የተከበረ ቦታ
13. ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ይሖዋ ያሳየውን ምሳሌ መከተላቸውና መታዘዛቸው ለሴቶች ምን ጥቅም አስገኝቶላቸው ነበር?
13 ታዲያ በቅድመ ክርስትና ዘመን በነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ዘንድ ሴቶች ምን ቦታ ነበራቸው? ለሴቶች የነበረው አመለካከትና አያያዝ ምን ይመስል ነበር? ጉዳዩን በቀላሉ ለመግለጽ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ይሖዋ ራሱ ያሳየውን ምሳሌ ሲከተሉና ሕጎቹን ሲታዘዙ ሴቶች ክብራቸው ተጠብቆና ብዙ መብቶችን እያገኙ ይኖሩ ነበር።
14, 15. ሴቶች በእስራኤል ውስጥ ይከበሩ እንደነበር የሚጠቁመው ምንድን ነው? ይሖዋ ወንዶች አምላኪዎቹ ሴቶችን እንዲያከብሩ መጠበቁ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
14 ሴቶች ይከበሩ ነበር። አምላክ ለእስራኤል የሰጠው ሕግ አባቶችም ሆኑ እናቶች እንዲከበሩ ያዛል። (ዘጸአት 20:12፤ 21:15, 17) ዘሌዋውያን 19:3 “ሰው ሁሉ እናቱንና አባቱን ይፍራ” ይላል። ቤርሳቤህ ወደ ልጅዋ ወደ ሰሎሞን በቀረበችበት ወቅት ንጉሡ በአክብሮት “ከተቀመጠበት ተነሥቶ እናቱን እጅ በመንሣት ተቀበላት።” (1 ነገሥት 2:19 የ1980 ትርጉም) ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ “አምላክ ለእስራኤል ያለውን ፍቅር ባል ለሚስቱ ካለው ፍቅር ጋር ትንቢታዊ በሆነ መንገድ በማነጻጸር ሊነገር የሚችለው ሴቶች በሚከበሩበት ኅብረተሰብ ውስጥ ብቻ ነው” ይላል።
15 ይሖዋ ራሱ ሴቶችን ስለሚያከብር ወንዶች አምላኪዎቹም ሴቶችን እንዲያከብሩ ይጠብቅባቸዋል። ይሖዋ ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች እንደ ምሳሌ አድርጎ በተጠቀመባቸውና ስሜቶቹን ከሴቶች ስሜቶች ጋር ባወዳደረባቸው ጥቅሶች ላይ ይህን የሚጠቁሙ ሐሳቦችን እናገኛለን። (ኢሳይያስ 42:14፤ 49:15፤ 66:13) ይህም ይሖዋ እንዴት እንደሚሰማው አንባብያን እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። ይሖዋ ለራሱ የተጠቀመበት “ምሕረት” ወይም “ርኅራሄ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ማኅፀን” ከሚለው ቃል ጋር በጣም የሚቀራረብ ከመሆኑም በላይ “የእናትነት ስሜት” ተብሎ ሊገለጽ መቻሉ ትኩረት የሚስብ ነው።—ዘጸአት 33:19፤ ኢሳይያስ 54:7
16. አምላካዊ አክብሮት ያላቸው ሴቶች ምክር ከፍተኛ ግምት ይሰጠው እንደነበር የሚጠቁሙት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?
16 አምላካዊ አክብሮት ያላቸው ሴቶች ምክር ከፍተኛ ግምት ይሰጠው ነበር። በአንድ ወቅት ፈሪሃ አምላክ የነበረው አብርሃም አምላካዊ አክብሮት የነበራት ሚስቱ የሰጠችውን ምክር ለመቀበል ሲያቅማማ ይሖዋ “የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ” በማለት አዞት ነበር። (ዘፍጥረት 21:10–12) ዔሳው ከኬጢ ሴቶች ያገባቸው ሚስቶች “የይስሐቅንና የርብቃን ልብ ያሳዝኑ ነበር።” ከጊዜ በኋላ ርብቃ ያዕቆብ ከኬጢ ሴቶች ሚስት ቢያገባ በጣም እንደምታዝን ለይስሐቅ ገለጸችለት። የይስሐቅ ምላሽ ምን ነበር? ዘገባው “ይስሐቅም ያዕቆብን ጠራው፣ ባረከውም፣ እንዲህ ብሎም አዘዘው፦ ከከንዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ” ይላል። አዎን፣ ርብቃ ቀጥተኛ ምክር ባታቀርብም እንኳ ባሏ ስሜቶቿን ግምት ውስጥ የሚያስገባ ውሳኔ አደረገ። (ዘፍጥረት 26:34, 35፤ 27:46፤ 28:1) ከዚህ በኋላም ንጉሥ ዳዊት የአቢግያን ልመና ስላዳመጠ ንጹሕ ደም ከማፍሰስ ሊርቅ ችሏል።—1 ሳሙኤል 25:32–35
17. ሴቶች በቤተሰብ ውስጥ መጠነኛ ሥልጣን እንደነበራቸው የሚጠቁመው ምንድን ነው?
17 ሴቶች በቤተሰባቸው ውስጥ መጠነኛ ሥልጣን ነበራቸው። ልጆች “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው” የሚል ጥብቅ ምክር ተሰጥቷቸው ነበር። (ምሳሌ 1:8) በምሳሌ ምዕራፍ 31 ላይ ያለው ስለ “ልባም ሴት” የሚናገረው መግለጫ ጠንክራ የምትሠራ ባለ ትዳር ሴት ቤቷን በሚገባ ከማስተዳደሯም በላይ ቋሚ ንብረቶችን ልትገዛ፣ እርሻ ልታቋቁም፣ አነስተኛ ንግድ ልታካሂድና ከአፏ በሚወጡት የጥበብ ቃላት የታወቀች ልትሆን እንደምትችል ይገልጻል። አንድን ሴት ከሁሉም በላይ የሚያስመሰግናት ይሖዋን መፍራቷ ነው። የዚህች ሴት ዋጋ ‘ከቀይ ዕንቁ እጅግ የሚበልጥ’ መሆኑ አያስደንቅም! ውድ የሆነው ቀይ ዕንቁ ለጌጣጌጦች መሥሪያነት በጣም ተፈላጊ ነው።—ምሳሌ 31:10–31
አምላክ ልዩ መብት ያደላቸው ሴቶች
18. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለአንዳንድ ሴቶች ልዩ መብት የታደላቸው በምን መንገዶች ነበር?
18 ይሖዋ ለሴቶች ያለው አመለካከት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለነበሩ አንዳንድ ሴቶች በለገሳቸው ልዩ መብት ታይቷል። መላእክት አጋርን፣ ሣራንና የማኑሄ ሚስትን ጎብኝተዋቸዋል፤ መለኮታዊ መመሪያም አስተላልፈውላቸዋል። (ዘፍጥረት 16:7–12፤ 18:9–15፤ መሳፍንት 13:2–5) በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ‘ሴቶች ያገለግሉ’ ነበር፤ በሰሎሞን ቤተ መንግሥት ውስጥም የሚዘፍኑ ሴት አዝማሪዎች ነበሩ።—ዘጸአት 38:8፤ 1 ሳሙኤል 2:22፤ መክብብ 2:8
19. አንዳንድ ጊዜ ሴቶች እሱን እንዲወክሉት ይሖዋ የተጠቀመባቸው በምን መንገድ ነው?
19 ይሖዋ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት እንድትወክለው ወይም መልእክቱን እንድታስተላልፍ በሴት ተጠቅሟል። ነቢይቱን ዲቦራን በተመለከተ “የእስራኤልም ልጆች ወደ እርስዋ ለፍርድ ይወጡ ነበር” የሚል እናነባለን። (መሳፍንት 4:5) እስራኤላውያን ኢያቢስ የተባለውን ከነዓናዊ ንጉሥ ድል ካደረጉ በኋላ ዲቦራ በእርግጥም ልዩ መብት አግኝታለች። በይሖዋ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው ታሪክ ክፍል የሆነውን የድል መዝሙር ቢያንስ በከፊል የደረሰችው እሷ እንደነበረች የተረጋገጠ ነው።c (መሳፍንት ምዕራፍ 5) ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ንጉሥ ኢዮስያስ ይሖዋን ለመጠየቅ ሲል ሊቀ ካህኑ ያለበትን ልዑካን ወደ ነቢይቱ ሕልዳና ላከ። ሕልዳና “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] እንዲህ ይላል” በማለት በሥልጣን መልስ ለመስጠት ችላለች። (2 ነገሥት 22:11–15) በዚያ ወቅት ንጉሡ መልእክተኞቹን ወደ ነቢይቱ እንዲሄዱ አዟቸዋል፤ ይህን ያደረገው ግን ከይሖዋ መመሪያ ለመቀበል ነበር።—ከሚልክያስ 2:7 ጋር አወዳድር።
20. ይሖዋ ለሴቶች ስሜትና ደኅንነት እንደሚያስብ የሚያሳዩ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
20 ይሖዋ ለሴቶች ደኅንነት ያለው አሳቢነት ለአንዳንድ ሴት አገልጋዮቹ ሲል ባደረጋቸው ነገሮች ታይቷል። የአብርሃም ውብ ሚስት የነበረችው ሣራ እንዳትደፈር ለመከላከል ሁለት ጊዜ ጣልቃ ገብቷል። (ዘፍጥረት 12:14–20፤ 20:1–7) ወንድ ልጅ እንድትወልድ ‘ማኅፀኗን በመክፈት’ ያዕቆብ የራሔልን ያህል ለማይወዳት ሚስቱ ለልያ አምላክ ሞገስ አሳይቷታል። (ዘፍጥረት 29:31, 32) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሁለት እስራኤላውያን አዋላጆች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በግብፅ ውስጥ ሊገደሉ የነበሩትን ዕብራውያን ወንዶች ልጆች ባዳኑበት ወቅት ይሖዋ በአድናቆት ተገፋፍቶ “ለእያንዳንዳቸው ቤተ ሰብ ሰጣቸው።” (ዘጸአት 1:17, 20, 21 የ1980 ትርጉም) የሐናን ልባዊ ጸሎትም ሰምቷል። (1 ሳሙኤል 1:10, 20) በተጨማሪም የአንድ ነቢይ ሚስት የነበረች መበለት ባለባት ዕዳ ፈንታ ልጆቿን ሊወስድባት የፈለገ አበዳሪ ሲያጋጥማት ይሖዋ አልተዋትም። አምላክ በፍቅር ተገፋፍቶ መበለቲቱ ዕዳዋን ለመክፈል እንድትችል ነቢዩ ኤልሳዕን የነበራት ዘይት እንዲትረፈረፍ እንዲያደርግ ረዳው። በዚህ መንገድ ክብሯን ለመጠበቅና ቤተሰቧን ለማዳን ቻለች።—ዘጸአት 22:22, 23፤ 2 ነገሥት 4:1–7
21. የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ሴቶች ያላቸውን ቦታ በተመለከተ ምን ሚዛናዊ መግለጫ ያቀርባሉ?
21 ስለዚህ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ሴቶችን ዝቅ አድርገን እንድንመለከታቸው ከማበረታታት ይልቅ በአምላክ ሕዝቦች መካካል ስለነበራቸው ቦታ ሚዛናዊ መግለጫ ያቀርቡልናል። ይሖዋ የሚያመልኩትን ሴቶች ዘፍጥረት 3:16 እንዳይፈጸምባቸው ባይጠብቃቸውም እሱ ያሳየውን ምሳሌ የተከተሉና ሕጎቹን የታዘዙ ወንዶች ሴቶችን በክብር ይዘዋ ቸዋል።
22. ኢየሱስ ምድር በነበረበት ወቅት የሴቶች ቦታ የተለወጠው እንዴት ነው? ምን ጥያቄዎች ተነሥተዋል?
22 የዕብራይስጥ ጽሑፎች ተጽፈው ካለቁ በኋላ ባሉት መቶ ዘመናት ሴቶች በአይሁዶች መካከል ያላቸው ቦታ ተለወጠ። ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ወቅት የረቢዎች ወጎች ሴቶች ሃይማኖታዊ መብቶችና ማኅበራዊ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው አገዷቸው። እነዚህ ወጎች ኢየሱስ ከሴቶች ጋር ባደረገው ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ አሳድረው ነበርን? በአሁኑ ወቅት ያሉት ክርስቲያን ሴቶች እንዴት ሊያዙ ይገባል? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሌጂየት መዝገበ ቃላት መሠረት “ፖሊጋሚ” የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል “ከሁለቱ ጾታዎች አንዱ በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ የትዳር ጓደኛ ሊኖረው የሚችልበትን ጋብቻ” ያመለክታል። የቃሉን ትርጉም በትክክል የሚገልጸው “ፖሊጀኒ” የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል “በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ሚስት ወይም ሴት የማግባት ሁኔታ ወይም ልማድ” የሚል ትርጉም አለው።
b በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያገቡ ወንዶችና ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ የተጠቀሱት “ባል” (በዕብራይስጥ ኢሻ) እና “ሚስት” (በዕብራይስጥ ኢሺሻህ) ተብለው ነው። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ በኤደን የተጠቀመባቸው ቃላት “ባለቤት” እና ‘ባለቤት ያላት’ የሚሉትን ሳይሆን ‘ባል’ እና ‘ሚስት’ የሚሉትን ቃላት ነው። (ዘፍጥረት 2:24፤ 3:16, 17) የሆሴዕ ትንቢት እስራኤላውያን ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ይሖዋን “ባሌ” እንጂ እንደ ድሮው “ባለቤቴ” ብለው እንደማይጠሩት ተንብዮ ነበር። ይህም “ባሌ” የሚለው ቃል “ባለቤቴ” ከሚለው ቃል የበለጠ የአሳቢነት ስሜትን እንደሚያሳይ ሊያመለክት ይችላል።—ሆሴዕ 2:18 አዓት
c በመሳፍንት 5:7 [አዓት] ላይ ዲቦራን ለማመልከት የገባው እኔ የሚለው ቃል አጠቃቀም ሊስተዋል ይገባል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ “ረዳት” እና ‘ወንድን የተሟላ የምታደርገው’ የሚሉት ቃላት አምላክ ለሴቶች ስለ ሰጣቸው ቦታ ምን ይጠቁማሉ?
◻ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ሴቶችን የሚመለከቱ ባህሎችን ስንመረምር በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ ሴቶች በጥንት የአምላክ አገልጋዮች ዘንድ የተከበረ ቦታ እንደ ነበራቸው የሚጠቁመው ምንድን ነው?
◻ ይሖዋ በቅድመ ክርስትና ዘመን ለነበሩ ሴቶች ልዩ መብት ያደላቸው በምን በምን መንገዶች ነበር?