ያዕቆብ ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍተኛ አድናቆት ነበረው
የያዕቆብ ሕይወት በችግርና በመከራ የተሞላ ነበር። በነፍስ ይፈልገው የነበረውን መንትያ ወንድሙን ሸሽቶ ተሰድዷል። የሚወዳት ልጃገረድ ልትዳርለት ሲገባ በመጀመሪያ ሌላ እንዲያገባ ተደርጓል። የኋላ ኋላም አራት ሚስቶች የኖሩት ሲሆን በዚህም ሳቢያ ሌሎች ብዙ ችግሮች ደርሰውበታል። (ዘፍጥረት 30:1-13) ለ20 ዓመታት ያህል ለሰው ተቀጥሮ ጉልበቱ ተበዝብዟል። ከአንድ መልአክ ጋር በመታገሉ ምክንያት ዘላቂ ጉዳት ደርሶበታል። ሴት ልጁ ተገድዳ ስትደፈር ወንዶች ልጆቹ በቁጣ ተነሳስተው እልቂት አስከትለዋል። የሚወዳት ሚስቱ ስትሞትና የሚወደው ልጁ ሲጠፋም አልቅሷል። በወቅቱ በተከሰተው ከባድ ረሀብ የተነሳ በስተርጅናው ለመሰደድ የተገደደ ሲሆን የሕይወቱ ዘመኖች “ጥቂትም ክፉም” እንደሆኑበት ተናግሯል። (ዘፍጥረት 47:9) ያዕቆብ ይህ ሁሉ መከራ ቢፈራረቅበትም መንፈሳዊና በአምላክ የሚተማመን ሰው ነበር። ይሁን እንጂ እምነቱን በአምላክ ላይ ለመጣል የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበረው? ከያዕቆብ ተሞክሮዎች ጥቂቶቹን በመመርመር ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
ከወንድሙ በጣም የተለየ ነበር
ከወንድሙ ጋር ለነበረው አለመግባባት ዋነኛው መንስኤ ያዕቆብ ለመንፈሳዊ ነገሮች ከፍ ያለ ቦታ ሲሰጥ ዔሳው ግን አቅልሎ መመልከቱ ነበር። ያዕቆብ ለአብርሃም ለተገባለት የተስፋ ቃል ኪዳን ትልቅ ቦታ ይሰጥ ስለነበር አምላክ ወራሽ እንዲሆን ለመረጠው ለዚህ ቤተሰብ እንክብካቤ ለማድረግ ራሱን አቅርቦ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ “ወደደው።” ያዕቆብ “ጭምት” ማለትም የላቀ የሥነ ምግባር ደረጃ ያለው ሰው ነበር። በተቃራኒው ዔሳው ለመንፈሳዊ ውርሻው እምብዛም ደንታ የሌለውና ይህንኑ ውርሻውን ለወንድሙ በማይረባ ነገር የሸጠ ሰው ነበር። ያዕቆብ አምላክ ለእሱ እንደሚገባው ያፀደቀለትን የብኩርና መብት ሲወስድና ለወንድሙ ታስቦ የነበረውን ምርቃት ሲቀበል ዔሳው በቀል በተሞላበት ቁጣ ነደደ። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ የሚወዳቸውን ቤተሰቦቹን ትቶ ለመሰደድ ተገደደ። በጉዞው ላይ ያጋጠመው ሁኔታ ግን የተደቆሰ መንፈሱን እንዳደሰለት ምንም ጥርጥር የለውም።—ሚልክያስ 1:2, 3፤ ዘፍጥረት 25:27–34፤ 27:1-45
አምላክ ለያዕቆብ መላእክት በሰማይና በምድር መካከል በቆመ መሰላል ወይም ደረጃ መሰል ነገር ላይ ሲወጡና ሲወርዱ በሕልም ካሳየው በኋላ እርሱንና ዘሩን እንደሚጠብቀው ነገረው። “የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ። እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፣ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና” አለው።—ዘፍጥረት 28:10-15
እንዴት የሚያጽናኑ ቃላት ናቸው! ይሖዋ ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጣቸው የተስፋ ቃል የያዕቆብን ቤተሰብ በመንፈሳዊ እንደሚያበለጽገው አረጋገጠለት። ያዕቆብ መላእክት የአምላክን ሞገስ ያገኙ ሰዎችን እንደሚያገለግሉ የተገነዘበ ሲሆን መለኮታዊ ጥበቃም እንደሚደረግለት ዋስትና ተሰጥቶታል። በመሆኑም በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልቶ ለይሖዋ ታማኝ እንደሚሆን ቃል ገባ።—ዘፍጥረት 28:16-22
ያዕቆብ የዔሳውን ውርሻ የወሰደው ያለአግባብ አልነበረም። እነዚህ ልጆች ገና ከመወለዳቸው በፊት ይሖዋ “ታላቁም ለትንሹ ይገዛል” ብሎ ነበር። (ዘፍጥረት 25:23) ነገር ግን ‘አምላክ መጀመሪያውኑ ያዕቆብ አስቀድሞ እንዲወለድ ቢያደርግ አይሻልም ነበር?’ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ይኖር ይሆናል። ይሁን እንጂ የተፈጸሙት ነገሮች አንድ አስፈላጊ እውነታ የሚያስተምሩ ናቸው። አምላክ በረከቱን የሚሰጠው መብታቸው እንደሆነ ለሚሰማቸው ሰዎች አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ለሚመርጣቸው ሰዎች ይገባናል የማይሉትን ደግነት ያሳያቸዋል። በዚህም የተነሳ የብኩርና መብቱ አድናቆት ከሌለው ከታላቅ ወንድሙ ተወስዶ ለያዕቆብ ተሰጠ። በተመሳሳይም አይሁዳውያን በብሔር ደረጃ የዔሳው ዓይነት ዝንባሌ በማሳየታቸው በመንፈሳዊ እስራኤል ተተክተዋል። (ሮሜ 9:6-16, 24) ዛሬም ቢሆን አንድ ሰው ፈሪሃ አምላክ ባለው ቤተሰብ ውስጥ ቢወለድም ምንም ጥረት ሳያደርግ በውርስ ብቻ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት አይችልም። መለኮታዊ በረከት ለማግኘት የሚሹ ሁሉ ለአምላክ ያደሩ ለመሆን የሚጥሩና ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ የሚሰጡ መሆን አለባቸው።
ላባ በደስታ ተቀበለው
ያዕቆብ ከዘመዶቹ መካከል ሚስት ፍለጋ መስጴጦሚያ ሲደርስ የአጎቱን የላባን ልጅ ራሔልን በውኃ ጉድጓድ አጠገብ አገኛትና የምትጠብቃቸው በጎች ውኃ እንዲጠጡ በጉድጓዱ ላይ የተገጠመውን ከባድ ድንጋይ አንከባለለላት።a ራሔል በፍጥነት ወደቤት ሄዳ የያዕቆብን መምጣት ስትናገር ላባ ሊገናኘው ፈጥኖ መጣ። ላባ ወላጆቹ ከአብርሃም ሎሌ የተቀበሉትን ዓይነት ሀብት አገኛለሁ ብሎ ጠብቆ ከነበረ ተበሳጭቶ መሆን አለበት። ምክንያቱም ያዕቆብ የመጣው ባዶ እጁን ነበር። ይሁን እንጂ ላባ ሊበዘብዘው የሚችል ታታሪ ሠራተኛ እንዳገኘ ተገንዝቦ ነበር።—ዘፍጥረት 28:1–5፤ 29:1-14
ያዕቆብ ታሪኩን ለላባ ነገረው። የብኩርና መብቱን ለማግኘት የተጠቀመበትን ዘዴ ይንገረው አይንገረው ግልጽ ባይሆንም ላባ “ነገሩንም ሁሉ” ከሰማ በኋላ “በእውነት አንተ አጥንቴ ሥጋዬም ነህ” አለው። ይህ ሐረግ ላባ አብሯቸው እንዲኖር ያዕቆብን እንደጋበዘው ወይም ጥበቃ እንዲያደርግለት የሥጋ ዝምድናው እንደሚያስገድደው መገንዘቡን ሊያመለክት እንደሚችል አንድ ምሑር ተናግረዋል። ያም ሆነ ይህ ላባ የእህቱን ልጅ እንዴት አድርጎ እንደሚበዘብዘው ወዲያውኑ ማሰብ ጀመረ።
ላባ በቀጣዮቹ 20 ዓመታት በእርሱና በያዕቆብ መካከል ብዙ ውዝግብ ያስነሳ አንድ ሐሳብ አቀረበ። “ወንድሜ ስለ ሆንህ በከንቱ ታገለግለኛለህን? ምንዳህ ምንድር ነው? ንገረኝ” አለው። ላባ ደግ አጎት መስሎ ቢቀርብም በመካከላቸው የነበረውን የሥጋ ዝምድና ወደ ሥራ ውል ቀየረው። ያዕቆብ ራሔልን አፍቅሯት ስለነበር “ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ” በማለት መለሰለት።—ዘፍጥረት 29:15-20
አንድ ወንድ ሚስት ሲያጭ ለሙሽሪቷ ቤተሰብ ጥሎሽ መስጠት ይጠበቅበት ነበር። ከጊዜ በኋላ የወጣው የሙሴ ሕግ ድንግል ልጃገረድን አባብሎ የደረሰባት ሰው 50 የብር ሰቅል ለአባቷ እንዲከፍል ይደነግግ ነበር። ጎርደን ዌንሃም የተባሉ ምሑር ይህ ገንዘብ “ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሎሽ” እንደነበረና አብዛኞቹ የጥሎሽ ክፍያዎች ግን “ከዚህ በጣም አነስተኛ” እንደነበሩ ያምናሉ። (ዘዳግም 22:28, 29) ያዕቆብ ገንዘብ መክፈል አይችልም ነበር። ስለዚህ ለላባ ያቀረበው ክፍያ የሰባት ዓመት አገልግሎት ነበር። ጎርደን ዌንሃም አክለው “በጥንት ባቢሎናውያን ዘመን ተራ ሠራተኞች በወር የሚከፈላቸው ደመወዝ ከግማሽ እስከ አንድ ሰቅል ብር ስለነበር (በሰባት ዓመት ውስጥ ከ42 እስከ 84 ሰቅል ማለት ነው) ያዕቆብ ራሔልን ለማግባት ለላባ ያቀረበለት ጥሎሽ ከፍተኛ ነበር” ብለዋል። ላባም ሐሳቡን የተቀበለው ሳያንገራግር ነበር።—ዘፍጥረት 29:19
ያዕቆብ ራሔልን በጣም ይወዳት ስለነበር ሰባቱ ዓመት “እንደ ጥቂት ቀን ሆነለት።” ሰባቱ ዓመታት ሲያልቁ ላባ ያታልለኛል ብሎ ቅንጣት ታክል ያልጠረጠረው ያዕቆብ በዓይነ እርግብ የተሸፈነች ሙሽራውን ወሰደ። በማግሥቱ ከራሔል ጋር ሳይሆን ከእህቷ ከልያ ጋር እንዳደረ ሲያውቅ ምን ያህል እንደደነገጠ መገመት አያዳግትም! ያዕቆብ “ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለገልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ?” ብሎ ላባን ጠየቀው። ላባም “በአገራችን ታላቂቱ ሳለች ታናሺቱን እንሰጥ ዘንድ ወግ አይደለም፤ ይህችንም ሳምንት ፈጽም፤ ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርስዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ” ሲል መለሰለት። (ዘፍጥረት 29:20-27) ምንም አማራጭ ያልነበረው ያዕቆብ ራሔልን ለማግባት የግድ የላባን ሐሳብ መቀበል ነበረበት።
ከመጀመሪያዎቹ ሰባት ዓመታት በተለየ መልኩ እነዚህኞቹ ሰባት ዓመታት መራራ ነበሩ። ያዕቆብ የላባን የጭካኔ ተንኮል እንዴት ችላ ብሎ ሊያልፈው ይችላል? ልያስ ብትሆን ከአባቷ ጋር ተባብራ ያደረገችበትን እንዴት ሊረሳው ይችላል? ላባ በዚህ ድርጊቱ የልያና የራሔል የወደፊት ሕይወት በብጥብጥ የተሞላ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ለእነርሱ ጭራሽ ደንታ እንደሌለው በግልጽ አሳይቷል። እሱ የሚያስበው ስለግል ጥቅሙ ብቻ ነበር። ልያ አከታትላ አራት ወንድ ልጆችን ስትወልድ ራሔል ግን መካን በመሆኗ በቅሬታዋ ላይ ቅናት ተጨመረባት። ከዚያም ራሔል ልጅ ለማግኘት ከነበራት ብርቱ ፍላጎት የተነሳ ገረዷን ለያዕቆብ ስትሰጥ ልያም በፉክክር እንዲሁ አደረገች። ይህም ያዕቆብን የአራት ሚስቶች ባልና የ12 ልጆች አባት ቢያደርገውም በቤተሰቡ ውስጥ ግን ደስታ አልነበረም። ያም ሆነ ይህ ይሖዋ ያዕቆብን ትልቅ ሕዝብ እያደረገው ነበር።—ዘፍጥረት 29:28 እስከ 30:24
ይሖዋ አበለጸገው
ያዕቆብ ብዙ መከራ ቢደርስበትም አምላክ ቃል በገባለት መሠረት ከእርሱ ጋር መሆኑን ያውቅ ነበር። ላባም ይህን ተገንዝቧል። ምክንያቱም ያዕቆብ ሲመጣ የነበሩት ጥቂት እንስሳት የእህቱ ልጅ ሲጠብቃቸው ግን በጣም እንደበዙ ተመልክቷል። ስለዚህ ያዕቆብን ለመስደድ ባለመፈለግ ለሚሰጠው ተጨማሪ አገልግሎት ምን እንዲከፈለው እንደሚሻ ጠየቀው። ያዕቆብ በላባ መንጋ ውስጥ የሚወለዱት ለየት ያለ ቀለም ያላቸው እንስሳት እንዲሰጡት ጠየቀ። በዚያ አካባቢ ባጠቃላይ ሲታይ የበጎች ቀለም ነጭ የነበረ ሲሆን ፍየሎች ደግሞ ጥቁር ወይም ጠቆር ያለ ቡናማ ቀለም ያላቸው እንደነበሩ ይነገራል። ዥንጉርጉር የሆኑትና ነቁጣ ያለባቸው እንስሳት ጥቂቶች ነበሩ። ስለዚህ ላባ ድርድሩ እንደቀናው በማሰብ የያዕቆብን ሐሳብ ሳያንገራግር ተቀብሎ ወዲያውኑ ዥንጉርጉር የሆኑትንና ነቁጣ ያለባቸውን እንስሳት ያዕቆብ ከሚጠብቃቸው እንስሳት ጋር እንዳይገናኙ ወደ ሩቅ ቦታ አዛወራቸው። የጥንት በግ ጠባቂዎች ብዙውን ጊዜ አዲስ ከሚወለዱት ግልገሎች ውስጥ 20 በመቶውን በደመወዝ መልክ ይወስዱ ነበር። ስለሆነም ላባ ለያዕቆብ የሚደርሰው 20 በመቶ እንኳን አይሞላም ብሎ አስቦ እንደነበር ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ተሳስቶ ነበር፣ ምክንያቱም ይሖዋ ከያዕቆብ ጋር ነበር።—ዘፍጥረት 30:25-36
ያዕቆብ በአምላክ እርዳታ የሚፈለገው ዓይነት ቀለም ያላቸው ጠንካራ እንስሳትን ለማርባት ቻለ። (ዘፍጥረት 30:37-42) ያዕቆብ እንስሳትን ስለ ማዳቀል የነበረው እውቀት ትክክል አልነበረም። ሆኖም ናሁም ሳርና የተባሉ አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል:- ‘ነጠብጣብ ባይኖርባቸውም ነጠብጣብ ቀለም የሚያስተላልፉ ጂኖች ያሏቸውን እንስሳት በተደጋጋሚ እርስ በርስ በማዋለድ ነጠብጣብ ቀለም ያላቸውን ግልገሎች ማግኘት እንደሚቻል በሳይንስ ተረጋግጧል። እንደነዚህ ያሉት እንስሳት ተለይተው የሚታወቁት በብርታታቸው ነው።’
ላባ ያዕቆብ ያገኘውን ውጤት ሲመለከት ነቁጣ፣ ዥንጉርጉር ወይም ሽመልመሌ ቀለም ያላቸውን እንስሳት እንዲወስድ የገባውን ውል ለመለወጥ ሞከረ። የራሱን ጥቅም በመፈለግ ምንም ያህል ውሉን ለመለዋወጥ ቢሞክርም ይሖዋ ያዕቆብን አበልጽጎታል። ላባ ውስጥ ውስጡን በንዴት ከመቃጠል በስተቀር ምንም ማድረግ አልቻለም። ያዕቆብ በራሱ ብልሃት ሳይሆን በይሖዋ እርዳታ በመታገዝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሀብት፣ የእንስሳት መንጎች፣ አገልጋዮች፣ ግመሎችና አህዮች አካበተ። ከጊዜ በኋላ ለራሔልና ለልያ “አባታችሁ ግን አታለለኝ፣ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉ ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም። . . . እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ” ብሏቸዋል። ይሖዋም ላባ ያደረገውን ሁሉ እንደተመለከተና ስለዚህ ጉዳይ መጨነቅ እንደማያስፈልገው በመግለጽ ያዕቆብን አጽናናው። “ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበትም ሥፍራ ተመለስ፣ በጎነትንም አደርግልሃለሁ” አለው።—ዘፍጥረት 31:1-13፤ 32:9
ያዕቆብ በመጨረሻ ከአታላዩ ላባ ተገላገለና ወደ ትውልድ ሥፍራው አመራ። ከዔሳው ጋር ከተለያዩ 20 ዓመታት ቢያልፉም ያዕቆብ አሁንም ይፈራው ነበር። በተለይ ዔሳው 400 ሰዎች አስከትሎ እንደሚመጣ ሲነገረው ይበልጡን ፈራ። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ምን ማድረግ ይችል ይሆን? ምንጊዜም በአምላክ የሚታመን መንፈሳዊ ሰው በመሆኑ በእምነት እርምጃ ወሰደ። ወደ ይሖዋ በመጸለይ ያደረገለት ቸርነት ሁሉ የማይገባው መሆኑን ገልጾ ቃል በገባለት መሠረት እርሱንና ቤተሰቡን ከዔሳው እጅ እንዲያድናቸው ለመነ።—ዘፍጥረት 32:2-12
ከዚህ በኋላ ያልጠበቀው ነገር አጋጠመው። አንድ የማያውቀው ሰው ሌሊቱን ሙሉ ሲታገለው አደረ። መልአክ ሆኖ የተገኘው ይህ ሰው የያዕቆብን የጭኑን ሹልዳ ነክቶ ከመገጣጠሚያው አወለቀው። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ መልአኩ ካልባረከው በቀር እንደማይለቀው ነገረው። ከጊዜ በኋላ ነቢዩ ሆሴዕ መልአኩ እንዲባርከው “አልቅሶም ለመነው” በማለት ጽፏል። (ሆሴዕ 12:2-4፤ ዘፍጥረት 32:24-29) ያዕቆብ ከዚያ በፊት መላእክት የተገለጡት ስለ አብርሃም ዘር ከተገባው ቃል ኪዳን አፈጻጸም ጋር በተያያዘ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ስለዚህ በብርቱ ትግል ታግሎ በረከቱን አገኘ። በዚህ ጊዜ አምላክ ስሙን እስራኤል ብሎ የለወጠለት ሲሆን ትርጉሙም “ከአምላክ ጋር የታገለ” ወይም “አምላክ ይታገላል” የሚል ነው።
አንተስ ለመታገል ፈቃደኛ ነህ?
ያዕቆብ መቋቋም የነበረበት ከመልአኩ ጋር መታገሉ ያስከተለበትን ጉዳትና ከዔሳው ጋር መገናኘት የሚጠይቅበትን ፈታኝ ሁኔታ ብቻ አልነበረም። ሆኖም እነዚህ ሁኔታዎች ያዕቆብ ምን ዓይነት ሰው እንደነበረ የሚያሳዩ ናቸው። ዔሳው ለብኩርና መብቱ ሲል ለትንሽ ጊዜ እንኳን ረሃቡን መታገስ ሲሳነው ያዕቆብ ግን በረከት ለማግኘት ዕድሜውን ሙሉ ታግሏል፤ እንዲያውም ከመልአክ ጋር ግብግብ እስከ መግጠም ደርሷል። አምላክ ቃል በገባለት መሠረት ያዕቆብ መለኮታዊ አመራርና ጥበቃ አግኝቶ የአንድ ታላቅ ሕዝብ አባትና የመሲሑ ቅድመ አያት ለመሆን ችሏል።—ማቴዎስ 1:2, 16
አንተስ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የሚፈለገውን ሁሉ ጥረት ለማድረግ ማለትም በምሳሌያዊ ሁኔታ ለመታገል ፈቃደኛ ነህ? በዛሬው ጊዜ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ለሚፈልጉ ሰዎች ሕይወት በብዙ ችግርና ተፈታታኝ ሁኔታዎች የተሞላ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ ትግል ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ያዕቆብ የተወልን ግሩም ምሳሌ እኛም ይሖዋ በፊታችን የዘረጋልንን ተስፋ አጥብቀን ለመያዝ ያለንን ቁርጠኝነት ያጠነክርልናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የያዕቆብ እናት ርብቃ የኤሊዔዘርን ግመሎች ያጠጣችበት ሁኔታ ከዚህ አጋጣሚ ጋር ይመሳሰላል። ያን ጊዜ ርብቃ እንግዳ መምጣቱን ለመንገር ወደቤት ሮጠች። ላባም እንግዳው ለእህቱ የሰጣትን የወርቅ አምባር ሲያይ ኤሊዔዘርን ለመቀበል ወጥቶ ነበር።—ዘፍጥረት 24:28-31, 53
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያዕቆብ በረከት ለማግኘት ዕድሜውን ሙሉ ታግሏል