ነፍስ ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ነፍስ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በዕብራይስጥ ነፈሽ ሲሆን በግሪክኛ ደግሞ ፕስኺ ነው። የዕብራይስጡ ቃል “የሚተነፍስ ፍጡር” የሚል ቀጥተኛ ፍቺ አለው፤ የግሪክኛው ቃል ደግሞ “ሕይወት ያለው ነገር” ማለት ነው።a ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ነፍስ ሕይወት ያላቸውን ፍጥረታት እንጂ በውስጣችን የሚገኝንና ስንሞት ከአካላችን ተለይቶ መኖሩን የሚቀጥል ነገርን አያመለክትም። የሰው ነፍስ ግለሰቡ ራሱ ማለት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቁመው እንዴት እንደሆነ እንመልከት፦
ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን በፈጠረበት ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። (ዘፍጥረት 2:7) መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው አዳም ነፍስ እንደተሰጠው ሳይሆን እሱ ራሱ ሕያው ነፍስ እንደሆነ ነው፤ በሌላ አባባል ሕይወት ያለው ሰው ሆነ ማለት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነፍስ እንደሚያደርጋቸው የተገለጹ ነገሮች አሉ፤ ከእነዚህም መካከል መሥራት፣ ለመብላት መጎምጀት፣ መብላት፣ ከጥም መርካትና ሕግ መታዘዝ ይገኙበታል። (ዘሌዋውያን 7:20፤ 23:30 NW፤ ዘዳግም 12:20 NW፤ ምሳሌ 25:25፤ ሮም 13:1) እነዚህ ነገሮች ሰው ሊያከናውናቸው የሚችላቸው ነገሮች ናቸው።
ነፍስ ትሞታለች?
አዎ፣ ነፍስ ልትሞት ትችላለች። ነፍስ እንደምትሞት የሚናገሩ በርካታ ጥቅሶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፦
“ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።”—ሕዝቅኤል 18:4, 20
በጥንቷ እስራኤል በጣም ከባድ ኃጢአት የሠራ ሰው ቅጣቱ ምን እንደሆነ ሲገልጽ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ነፍሱ ከወገኖቹ ተለይታ ትጥፋ’ ይላል። (ዘፀአት 12:15, 19 የ1954 ትርጉም፤ ዘሌዋውያን 7:20, 21, 27 NW፤ ዘሌዋውያን 19:8 NW) ይህም ግለሰቡ ‘በሞት እንደሚቀጣ’ የሚያመለክት ነው።—ዘፀአት 31:14
ሬሳ በሚለው ምትክ የዚህ ቃል ቀጥተኛ ትርጉም ይኸውም “የሞተ ነፍስ” የሚለው አገላለጽ የገባባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። (ዘሌዋውያን 21:11፤ ዘኍልቍ 6:6 NW) እርግጥ ነው፣ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ያለውን አገላለጽ የሚያስቀምጡት “የሞተ አካል” ወይም “የሞተ ሰው” ብለው ነው፤ ይሁን እንጂ ጥቅሶቹን መጀመሪያ በተጻፉበት ቋንቋ ብንመለከታቸው በእነዚህ ቦታዎች ላይ የገባው ቃል “ነፍስ” የሚል ትርጉም ያለው ነፈሽ የተባለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።
“ነፍስ” “ሕይወትን” ሊያመለክት ይችላል
“ነፍስ” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ሕይወት” የሚለውን ቃል ለማመልከት የተሠራበትም ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢዮብ 33:22 (የ1954 ትርጉም) ላይ “ሕይወት” የሚለውን ቃል ለማመልከት የገባው፣ “ነፍስ” የሚል ትርጉም ያለው ነፈሽ የተባለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። በተመሳሳይም ከአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መረዳት እንደምንችለው አንድ ሰው ነፍሱን ወይም ሕይወቱን ለሞት አሳልፎ ሊሰጥ ወይም ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል።—ዘፀአት 4:19፤ መሳፍንት 9:17 የ1954 ትርጉም፤ ፊልጵስዩስ 2:30
“ነፍስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በዚህ መንገድ የተሠራበት መሆኑ ‘ነፍስ እንደወጣች’ የሚናገሩ ጥቅሶች ምን ትርጉም እንዳላቸው እንድንረዳ ያስችሉናል። (ዘፍጥረት 35:18 የ1954 ትርጉም) ይህ ምሳሌያው አገላለጽ የግለሰቡ ሕይወት ማለፉን የሚጠቁም ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በዘፍጥረት 35:18 ላይ ያለውን ሐሳብ የሚያስቀምጡት “የመጨረሻዋን ትንፋሽ ተንፍሳ” በማለት ነው።—ጉድ ኒውስ ትራንስሌሽን፤ ኒው ጀሩሳሌም ባይብል
ነፍስ እንደማትሞት የሚገልጸው እምነት ከየት መጣ?
ነፍስ እንደማትሞት የሚያስተምሩ የክርስትና ሃይማኖቶች ትምህርታቸው የመነጨው ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን ከጥንት የግሪክ ፍልስፍና ነው። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነፍስ የተጠቀሰው ከእስትንፋስ ጋር ተያይዞ ነው፤ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ፣ ምድር ላይ የሚቀር ሥጋና ወደ ሰማይ ተለይታ የምትሄድ ነፍስ በማለት ሁለት የተለያዩ ነገሮች እንዳሉ የሚጠቁም ሐሳብ የትም ቦታ ላይ አናገኝም። ሥጋና ነፍስ ሁለት የተለያዩ ነገሮች እንደሆኑ የሚገልጸው የክርስትና ትምህርት የመነጨው ከጥንቷ ግሪክ ነው።”
አምላክ፣ የእሱን ትምህርቶች ከሰዎች ፍልስፍና ጋር መቀላቀልን አይደግፍም፤ ከእነዚህም መካከል ነፍስ እንደማትሞት የሚገልጸው ትምህርት ይገኝበታል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፦ “በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።”—ቆላስይስ 2:8
a The New Brown, Driver, and Briggs Hebrew and English Lexicon of the Old Testament ገጽ 659ን እንዲሁም Lexicon in Veteris Testamenti Libros ገጽ 627ን ተመልከት። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ነፈሽ ወይም ፕስኺ የሚሉትን ቃላት እንደ አገባባቸው “ነፍስ፣” “ሕይወት፣” “ሰው፣” “ፍጡር” ወይም “አካል” ብለው ተርጉመዋቸዋል።