በእምነታቸው ምሰሏቸው | ዮሴፍ
“ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ አድምጡኝ”
ዮሴፍ በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ ዓይኑ ይንከራተታል፤ የግመል ቅፍለታቸውን እየነዱ ከሚጓዙት ነጋዴዎች እጅ አምልጦ ቢሸሽ ደስ ባለው ነበር። በኬብሮን ያለው ቤቱ በማዶ ከሚታዩት ኮረብቶች ብዙም አይርቅም። ከሁሉ አብልጦ የሚወደው ልጁ የገጠመውን ዱብ ዕዳ ያላወቀው አባቱ ያዕቆብ ወደ ቤቱ ገብቶ አረፍ ብሏል። ልጁ ዮሴፍ ግን ወደ አባቱ መመለስ አይችልም፤ እንዲያውም እሱ እስከሚያውቀው ድረስ፣ የሚወደውን አረጋዊ አባቱን ፊት ዳግመኛ አያይም። ግመሎቻቸውን እየነዱ ወደ ደቡብ በሚወስደው የተለመደ መንገድ ላይ የሚጓዙት ነጋዴዎች ዮሴፍን በዓይነ ቁራኛ ይከታተሉታል። አሁን ዮሴፍ ንብረታቸው ነው፤ በመሆኑም ከዓይናቸው እንዲርቅ አይፈልጉም። ጥሩ መዓዛ እንዳለው ሙጫና ቅባት ሁሉ ይህ ልጅም በነጋዴዎቹ ዓይን፣ ሩቅ በምትገኘው ግብፅ ተሽጦ ትርፍ የሚያመጣላቸው ውድ ንብረት ነው።
በወቅቱ ዮሴፍ ዕድሜው ከ17 ዓመት ብዙም አይበልጥም። ዮሴፍ በስተ ምዕራብ ከታላቁ ባሕር ባሻገር እያሽቆለቆለች ያለችውን ጀንበር አሻግሮ እየተመለከተ እንዲህ በአንድ ጊዜ ሰማይ ምድሩ ጨለማ የሆነበትን ምክንያት ሲያስብ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። የገዛ ወንድሞቹ ሊገድሉት እንደነበረና በኋላም ለባርነት እንደሸጡት ማመን አዳጋች ነው። ይህን ሲያስብ በዓይኖቹ ግጥም ያለውን እንባ ለመቆጣጠር እየታገለ መሆን አለበት። ዮሴፍ ወደፊት ምን እንደሚያጋጥመውም ማወቅ አይችልም።
ዮሴፍ እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ የወደቀው እንዴት ነው? ደግሞስ የገዛ ቤተሰቡ ያገለሉትና በደል ያደረሱበት ይህ ወጣት ካሳየው እምነት ምን ልንማር እንችላለን?
ውጥንቅጡ የወጣ የቤተሰብ ሕይወት
ዮሴፍ የተወለደው በአንድ ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ ቤተሰቡ ግን ደስተኛና አንድነት ያለው አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ያዕቆብ ቤተሰብ የያዘው ዘገባ ከአንድ በላይ ማግባት የሚያስከትለውን መዘዝ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ አንድ ወንድ፣ አንዲት ሴት ብቻ እንዲያገባ ነበር፤ አምላክ በሕዝቦቹ መካከል ተስፋፍቶ የነበረውን ከአንድ በላይ የማግባት ልማድ ለረጅም ጊዜ እንዲቀጥል የፈቀደ ሲሆን የአምላክ ልጅ ሲመጣ ግን ተከታዮቹ አምላክ መጀመሪያ ያቋቋመውን ሥርዓት መከተል እንዳለባቸው አስተምሯል። (ማቴዎስ 19:4-6) ያዕቆብ ከአራት ሴቶች ይኸውም ልያና ራሔል ከተባሉ ሚስቶቹ እንዲሁም ዘለፋና ባላ ከተባሉት የሚስቶቹ አገልጋዮች ቢያንስ 14 ልጆችን ወልዷል። ያዕቆብ ከመጀመሪያውም የወደደው ውቧን ራሔልን ነበር። ተታልሎ ላገባት ለልያ (ለራሔል ታላቅ እህት) እንዲህ ዓይነት ስሜት አልነበረውም። በሁለቱ ሴቶች መካከል ከባድ ፉክክር የነበረ ሲሆን ይህ የቅናት ስሜት ወደ ልጆቻቸውም ተላልፏል።—ዘፍጥረት 29:16-35፤ 30:1, 8, 19, 20፤ 37:35
ራሔል ለረጅም ጊዜ መሃን ነበረች፤ በመጨረሻ ዮሴፍን ስትወልድ ያዕቆብ በስተርጅና ላገኘው ለዚህ ልጁ ልዩ ትኩረት ይሰጠው ጀመር። ለምሳሌ ያህል፣ ያዕቆብ ከወንድሙ ከዔሳው ጋር ለመገናኘት ባደረገው ጉዞ ላይ ራሔልና ትንሹ ዮሴፍ ከአደጋ እንዲርቁ ሲል በቡድን በቡድን ተከፋፍሎ ከሚሄደው ቤተሰቡ ሁሉ ኋላ እንዲሆኑ አድርጎ ነበር፤ ይህን ያደረገው ወንድሙ ዔሳው ሊገድለው ይፈልግ ስለነበረ ነው። ያ አስጨናቂ ቀን በዮሴፍ አእምሮ ላይ በማይፋቅ ሁኔታ ታትሞ መሆን አለበት። ዮሴፍ፣ አረጋዊ ቢሆንም ብርቱ የነበረው አባቱ የዚያን ዕለት ጠዋት ማነከስ የጀመረው ምን ሆኖ እንደሆነ ግራ ገብቶት እንደሚሆን መገመት ይቻላል። አባቱ ያነከሰበትን ምክንያት ሲያውቅ፣ ይኸውም ያዕቆብ በዚያን ዕለት ሌሊት ከአንድ ኃያል መልአክ ጋር ሲታገል ማደሩን ሲሰማ ምንኛ ተገርሞ ይሆን! ያዕቆብ ከኃያል መልአክ ጋር የታገለው ለምን ነበር? ያዕቆብ ከይሖዋ አምላክ በረከት ማግኘት ስለፈለገ ነው። በዚያን ጊዜ ያገኘው በረከት ስሙ መለወጡና እስራኤል መባሉ ነው። በእሱ ስም የሚጠራ አንድ ብሔር ይኖራል! (ዘፍጥረት 32:22-31) ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ፣ የእስራኤል ልጆች ይህን ብሔር የሚያስገኙ የነገድ አባቶች እንደሚሆኑ አወቀ!
ውሎ አድሮ፣ ዮሴፍ ከማንም በላይ የሚወዳት እናቱ በለጋ ሕይወቱ በሞት ስትለየው መራራ የሆነ ሐዘን ገጠመው። እናቱ የሞተችው ታናሽ ወንድሙን ብንያምን በምትወልድበት ጊዜ ነው። አባቱ በእሷ ሞት ጥልቅ ሐዘን ደርሶበታል። ያዕቆብ የዮሴፍን እንባ እያበሰ የያዕቆብ አያት የሆነው አብርሃም በአንድ ወቅት በተጽናናበት የትንሣኤ ተስፋ ልጁን ሲያጽናናው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ዮሴፍ፣ ይሖዋ አንድ ቀን እናቱን ወደ ሕይወት እንደሚመልስለት ሲሰማ ምንኛ ልቡ ተነክቶ ይሆን! ምናልባትም ዮሴፍ ደግ ለሆነው “የሕያዋን . . . አምላክ” ያለው ፍቅር ይበልጥ የጨመረው በዚህ ጊዜ ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 20:38፤ ዕብራውያን 11:17-19) ያዕቆብ ከሚስቱ ከራሔል ሞት በኋላ ከእሷ ለወለዳቸው ሁለት ወንዶች ልጆቹ ልዩ ፍቅር ነበረው።—ዘፍጥረት 35:18-20፤ 37:3፤ 44:27-29
ብዙ ልጆች እንዲህ ያለ የተለየ እንክብካቤ ሲደረግላቸው ይሞላቀቃሉ ወይም ይበላሻሉ፤ ዮሴፍ ግን ከወላጆቹ ብዙ ጥሩ ባሕርያትን የተማረ ሲሆን ጠንካራ እምነትም አዳብሯል፤ እንዲሁም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በሚገባ ያውቅ ነበር። ዮሴፍ በ17 ዓመቱ የበግ እረኛ ሆኖ ታላላቅ ወንድሞቹን ያግዝ ጀመር፤ በዚህ ጊዜ ወንድሞቹ ጥፋት ሲሠሩ ተመለከተ። ታዲያ በእነሱ ለመወደድ ሲል ጥፋታቸውን ለመደበቅ ተፈትኖ ይሆን? የተሰማው ምንም ሆነ ምን፣ ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል። ጉዳዩን ለአባቱ ነገረው። (ዘፍጥረት 37:2) ይህ ድፍረት የሚጠይቅ ተግባር ያዕቆብ ይህን ውድ ልጁን ይበልጥ ከፍ አድርጎ እንዲመለከተው አድርጎት ሊሆን ይችላል። ክርስቲያን ወጣቶች ሊያስቡበት የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ሌሎች ለምሳሌ ወንድሞችህና እህቶችህ ወይም ጓደኞችህ የፈጸሙትን ከባድ ኃጢአት ለመደበቅ በምትፈተንበት ጊዜ ጉዳዩን ጥፋተኛውን ሊረዱት ለሚችሉ ሰዎች በማሳወቅ የዮሴፍን አርዓያ መከተልህ ጥበብ ነው።—ዘሌዋውያን 5:1
ከዮሴፍ የቤተሰብ ሕይወትም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአንድ በላይ ባያገቡም የእንጀራ ወላጆችና የእንጀራ ልጆች ያሉባቸው ቤተሰቦች አሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ቤተሰቦች፣ አንዱን ከአንዱ ማበላለጥ ወይም ማዳላት የቤተሰብን አንድነት እንደሚሸረሽር ከያዕቆብ ቤተሰብ መማር ይችላሉ። እንዲህ ያለ ቤተሰብ ያላቸው ብልህ ወላጆች፣ የራሳቸውንም ሆነ የትዳር ጓደኛቸውን ልጆች እንደሚወዷቸው፣ ሁሉም ልጅ የራሱ የሆኑ ልዩ ስጦታዎች እንዳሉት እንዲሁም እያንዳንዱ ልጅ ለቤተሰቡ ደስታ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ልጆቹ እንዲሰማቸው ለማድረግ ይጥራሉ።—ሮም 2:11
ቅናት ሥር መስደድ ጀመረ
ያዕቆብ ለዮሴፍ ለየት ያለ ክብር ሰጥቶታል፤ ይህን ያደረገው ዮሴፍ ትክክል ከሆነው ነገር ጎን ለመቆም በድፍረት አቋም በመውሰዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለዮሴፍ አንድ ልዩ ልብስ አሠርቶለታል። (ዘፍጥረት 37:3) ብዙውን ጊዜ ይህ ልብስ በኅብረ ቀለማት ያጌጠ እንደሆነ ቢገለጽም እንዲህ ለማለት የሚያስችል በቂ ማስረጃ የለም። ይህ ልብስ ረጅምና በጣም የሚያምር ምናልባትም እጅጌ ሙሉና እስከ ቁርጭምጭሚት የሚደርስ ይሆናል። የመኳንንት ዘር ወይም መስፍን የሆነ ሰው የሚለብሰው ዓይነት ልብስ ሊሆን ይችላል።
ያዕቆብ ይህን ያደረገው በቅንነት እንደሆነ የተረጋገጠ ነው፤ ዮሴፍም ቢሆን አባቱ ለእሱ ያለውን አክብሮትና ፍቅር በሚያሳየው በዚህ ስጦታ ልቡ ተነክቶ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ይህ ልብስ ለዮሴፍ ገና ብዙ ጣጣ ያመጣበታል። አንደኛ ነገር፣ ዮሴፍ እረኛ እንደሆነ አስታውስ። ይህ ደግሞ የጉልበት ሥራ የሚጠይቅ ነው። እንዲህ ዓይነቱን የክብር ልብስ ለብሶ በረጃጅም ሣር መሃል እየጎተተው ሲሄድ፣ ቋጥኞች ላይ ሲወጣ ወይም በቁጥቋጦ ተተብትቦ የተያዘን የበግ ጠቦት ለማስለቀቅ ሲታገል ይታይህ። ይበልጥ የሚያሳስበው ግን ‘ያዕቆብ ከሌሎቹ አስበልጦ እንደሚወደው የሚያሳየው ይህ ልብስ ዮሴፍ ከወንድሞቹ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?’ የሚለው ጥያቄ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ “ወንድሞቹም፣ አባታቸው ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው መሆኑን ሲያዩ፣ ዮሴፍን ጠሉት፤ በቅን አንደበትም ሊያናግሩት አልቻሉም” በማለት መልሱን ይሰጠናል።a (ዘፍጥረት 37:4) የዮሴፍ ወንድሞች የቀኑበትን ምክንያት ለመረዳት አዳጋች ባይሆንም እንደ መርዝ አደገኛ በሆነው በዚህ ስሜት መሸነፋቸው ግን ሞኝነት ነበር። (ምሳሌ 14:30፤ 27:4) አንተስ ልታገኘው የምትፈልገው ትኩረት ወይም ክብር ለሌላ ሰው በመሰጠቱ ቅናት ቢጤ የተሰማህ ጊዜ አለ? የዮሴፍን ወንድሞች አስታውስ። ያደረባቸው ቅናት የኋላ ኋላ አምርረው የተጸጸቱበትን ድርጊት ወደመፈጸም መርቷቸዋል። የእነሱ ምሳሌ፣ “ደስ ከተሰኙ ሰዎች ጋር ደስ [መሰኘት]” የጥበብ አካሄድ መሆኑን ለክርስቲያኖች ትምህርት ይሰጣቸዋል።—ሮም 12:15
ዮሴፍ፣ ወንድሞቹ በጥላቻ ዓይን እንደሚመለከቱት ሳይገባው አልቀረም። ታዲያ ወንድሞቹ አጠገብ ሲሆን ያንን የሚያምር ልብሱን ደብቆት ይሆን? እንዲህ ለማድረግ ተፈትኖ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ያዕቆብ ልብሱን ለዮሴፍ የሰጠው እሱን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተውና እንደሚወድደው ለመግለጽ እንደሆነ አስታውስ። ዮሴፍ፣ የሚተማመንበትን አባቱን ማሳፈር ስላልፈለገ ልብሱን አዘውትሮ ይለብሰው ነበር። የእሱ ምሳሌነት ለእኛም ጠቃሚ ነው። በሰማይ ያለው አባታችን ፈጽሞ የማያዳላ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ለታማኝ አገልጋዮቹ ከሌሎች የተለየ ክብር ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም ከዚህ ብልሹና ሥነ ምግባር የጎደለው ዓለም የተለዩ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። እንደ ዮሴፍ ልዩ ልብስ ሁሉ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ምግባርም በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች የተለዩ ያደርጋቸዋል። መልካም ምግባራቸው አንዳንድ ጊዜ ሌሎች እንዲቀኑባቸውና እንዲጠሏቸው ያደርጋል። (1 ጴጥሮስ 4:4) ታዲያ አንድ ክርስቲያን የአምላክ አገልጋይ መሆኑን መደበቅ ይኖርበታል? ዮሴፍ ልብሱን እንዳልደበቀ ሁሉ አንድ ክርስቲያንም እውነተኛ ማንነቱን አይደብቅም።—ሉቃስ 11:33
የዮሴፍ ሕልሞች
ብዙም ሳይቆይ ዮሴፍ ሁለት እንግዳ ሕልሞች አለመ። በመጀመሪያው ሕልም ላይ ዮሴፍ፣ እሱና ወንድሞቹ ነዶዎች ሲያስሩ አየ። ይሁን እንጂ የእሱ ነዶ ቀጥ ብላ ስትቆም የወንድሞቹ ነዶዎች በእሱ ነዶ ዙሪያ ሆነው ሲሰግዱላት ተመለከተ። በሁለተኛው ሕልም ላይ ደግሞ ፀሐይ፣ ጨረቃና 11 ከዋክብት ለዮሴፍ ሰገዱለት። (ዘፍጥረት 37:6, 7, 9) ዮሴፍ ቁልጭ ባለ መንገድ ከታዩት ከእነዚህ እንግዳ ሕልሞች ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ ነበረበት?
ለዮሴፍ እንዲህ ዓይነት ሕልሞች ያሳየው ይሖዋ አምላክ ነበር። ሕልሞቹ ትንቢታዊ መልእክት ያዘሉ ሲሆኑ አምላክ ይህን መልእክት ዮሴፍ እንዲያስተላልፍ ፈልጓል። በአንድ በኩል ሲታይ ከዮሴፍ የሚጠበቀው ነገር፣ ከጊዜ በኋላ የተነሱ ነቢያት የአምላክን መልእክቶችና ፍርዶች ከሃዲ ለነበረው ሕዝቡ ሲያስተላልፉ ካደረጉት ነገር ጋር የሚመሳሰል ነው።
ዮሴፍ ወንድሞቹን “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ አድምጡኝ” በማለት በዘዴ ጠየቃቸው። ወንድሞቹ የሕልሙ ትርጉም ሲገባቸው ፈጽሞ አልተደሰቱም። “ለካስ በላያችን ለመንገሥ ታስባለህና! ለመሆኑ አንተ እኛን ልትገዛ!” አሉት። ዘገባው አክሎ “ስለ ሕልሙና ስለ ተናገረው ቃል ከፊት ይልቅ ጠሉት” ይላል። ዮሴፍ ሁለተኛውን ሕልም ለአባቱና ለወንድሞቹ ሲነግራቸው የሰጡት ምላሽ ከፊተኛው ብዙም የሚሻል አልነበረም። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አባቱ ‘ይህ ያየኸው ሕልም ምንድን ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም በፊትህ ወደ ምድር ተጐንብሰን በእርግጥ ልንሰግድልህ ነው?’ ሲል ገሠጸው።” ይሁን እንጂ ያዕቆብ ጉዳዩን በልቡ ይዞ ያሰላስለው ነበር። ይሖዋ በዚህ ልጅ በኩል መልእክት እያስተላለፈ ይሆን?—ዘፍጥረት 37:6, 8, 10, 11
ዮሴፍ ሰሚዎቹን የማያስደስት አልፎ ተርፎም ስደት የሚያስከትል ትንቢታዊ መልእክት እንዲያስተላልፍ የተጠየቀ የመጀመሪያውም ሆነ የመጨረሻው የይሖዋ አገልጋይ አይደለም። እንዲህ ዓይነት መልእክት እንዲያስተላልፉ ከተላኩት ሁሉ የሚበልጠው ኢየሱስ ሲሆን ለተከታዮቹ “እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል” በማለት ነግሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 15:20) በሁሉም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች ወጣቱ ዮሴፍ ካሳየው እምነትና ድፍረት ብዙ ነገር መማር ይችላሉ።
ጥላቻቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ያዕቆብ ወጣቱን ዮሴፍን ላከው። የያዕቆብ ትላልቅ ልጆች ከጥቂት ጊዜ በፊት ጠላቶች ባፈሩበት በስተ ሰሜን በሚገኘው በሴኬም አቅራቢያ መንጎቻቸውን እየጠበቁ ነበር። ያዕቆብ አባት እንደመሆኑ መጠን የልጆቹ ነገር ስላሳሰበው ደኅንነታቸውን እንዲያጣራ ዮሴፍን ላከው። ዮሴፍ ምን እንደተሰማው መገመት ትችላለህ? ወንድሞቹ ከምንጊዜውም የበለጠ እንደጠሉት አውቋል! አሁን አባታቸውን ወክሎ ወደ እነሱ ሲመጣ እንዴት ይቀበሉት ይሆን? ያም ሆነ ይህ ዮሴፍ አባቱን ታዝዞ ሄደ።—ዘፍጥረት 34:25-30፤ 37:12-14
ጉዞው በእግር አራት ወይም አምስት ቀናት ሊፈጅ የሚችል ረጅም መንገድ ነበር። ሴኬም የሚገኘው ከኬብሮን በስተ ሰሜን 80 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ነው። ይሁን እንጂ ዮሴፍ ሴኬም ሲደርስ ወንድሞቹ ከሴኬም በስተ ሰሜን 22 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ወደሚገኘው ወደ ዶታይን እንደሄዱ ሰማ። ዮሴፍ በመጨረሻ ዶታይን ሲደርስ ወንድሞቹ ከርቀት አዩት። በውስጣቸው የታመቀው ጥላቻ እሱን ሲያዩ ገንፍሎ ወጣ። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “እነርሱም እንዲህ ተባባሉ፤ ‘ያ ሕልም ዐላሚ መጣ፤ ኑ እንግደለውና ከጕድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም፣ “ክፉ አውሬ ነጥቆ በላው” እንላለን፤ እስቲ ሕልሞቹ ሲፈጸሙ እናያለን።’” ሮቤል ግን ዮሴፍን ከነሕይወቱ ጉድጓድ ውስጥ እንዲጥሉት ወንድሞቹን አሳመናቸው፤ እንዲህ ያደረገው በኋላ ላይ ተመልሶ ሊያወጣው አስቦ ነበር።—ዘፍጥረት 37:19-22
ወንድሞቹ የጠነሰሱለትን ሴራ ያልጠረጠረው ዮሴፍ በሰላም እንደሚቀበሉት በማሰብ ወደ እነሱ መጣ። ወንድሞቹ ግን ጥቃት ሰነዘሩበት! የለበሰውን ልዩ ልብስ ከገፈፉት በኋላ ወደ አንድ ደረቅ የውኃ ጉድጓድ እየጎተቱ ወስደው እዚያ ውስጥ ጣሉት! ዮሴፍ ድንጋጤው ሲለቀው እንደምንም ተንገዳግዶ በእግሩ ቆመ፤ ይሁን እንጂ የሚረዳው ሰው ሳይኖር ከጉድጓዱ መውጣት የማይቻል ነገር ነው። ወደ ላይ ሲመለከት ከሰማዩ ሌላ የሚታይ ነገር የለም፤ የወንድሞቹም ድምፅ እየራቀው ሄደ። እየጮኸ ቢማጸናቸውም እንዳልሰሙ ሆነው ጥለውት ሄዱ። ለዮሴፍ ልመና ጆሮ ዳባ በማለት ጨክነው በጉድጓዱ አቅራቢያ ምግባቸውን በሉ። ሮቤል በሌለበት ሰዓት ወንድሞቹ ዮሴፍን ሊገድሉት እንደገና አስበው ነበር፤ ይሁዳ ግን በመግደል ፋንታ በዚያ ለሚያልፉ ነጋዴዎች እንዲሸጡት አግባባቸው። ዶታይን የሚገኘው ወደ ግብፅ በሚወስደው የንግድ መንገድ አቅራቢያ ስለነበረ ብዙም ሳይቆይ እስማኤላውያንና ምድያማውያን ተጓዥ ነጋዴዎች ብቅ አሉ። ሮቤል ከሄደበት ከመመለሱ በፊት ጉዳዩ ተጠናቀቀ። ወንድማቸውን በ20 ሰቅል ለባርነት ሸጡት።b—ዘፍጥረት 37:23-28፤ 42:21
አሁን፣ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ ታሪኩን ስንጀምር የተነሳንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ዮሴፍ በስተ ደቡብ ወደ ግብፅ በሚወስደው መንገድ ላይ ሲጓዝ ሁሉን ነገር እንዳጣ ሳይሰማው አልቀረም። ሳይወድ በግድ ከቤተሰቡ ተነጠለ! ለዓመታት ስለ ቤተሰቡ ይኸውም ሮቤል ከሄደበት ተመልሶ ዮሴፍን ጉድጓዱ ውስጥ ሲያጣው ስለተሰማው ጭንቀት፣ ያዕቆብ የሚወደው ልጁ ዮሴፍ እንደሞተ ሲነገረው ስለተሰማው መሪር ሐዘን፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በሕይወት ስለነበረው ስለ አረጋዊው አያቱ ይስሐቅ እንዲሁም በጣም ስለሚናፍቀውና ስለሚወደው ታናሽ ወንድሙ ስለ ብንያም ምንም ነገር ማወቅ አይችልም። ይሁን እንጂ ዮሴፍ ሁሉንም ነገር አጥቷል ማለት ነው?—ዘፍጥረት 37:29-35
ዮሴፍ ወንድሞቹ ፈጽሞ ሊወስዱበት የማይችሉት አንድ ነገር አለው፤ ይኸውም እምነቱ ነው። ስለ አምላኩ ስለ ይሖዋ ብዙ ነገር ስለሚያውቅ እምነቱን ሊያጠፋበት የሚችል ምንም ነገር የለም፤ ከቤተሰቡ መራቁ፣ ወደ ግብፅ በግዞት ሲወሰድ በነበረው ረጅም ጉዞ ላይ ያጋጠመው መከራ ሌላው ቀርቶ ጲጥፋራ ለሚባል ግብፃዊ ባለጸጋ በባርነት መሸጡ ያስከተለበት ውርደትም እንኳ እምነቱን አላጠፋበትም። (ዘፍጥረት 37:36) እንዲህ ያሉት መከራዎች ቢደርሱበትም የዮሴፍ እምነትና ከአምላኩ ጋር ተቀራርቦ ለመኖር የነበረው ቆራጥ አቋም ይበልጥ ተጠናክረዋል። የዮሴፍ እምነት ለአምላኩ ለይሖዋና በችግር ላይ ለወደቀው ቤተሰቡ ይበልጥ ጠቃሚ እንዲሆን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ወደፊት በሚወጡ ርዕሶች ላይ እንመለከታለን። የዮሴፍን እምነት መኮረጃችን ምንኛ ጥበብ ነው!
a አንዳንድ ተመራማሪዎች የዮሴፍ ወንድሞች፣ ያዕቆብ ለዮሴፍ የሰጠውን ስጦታ የብኩርና መብትን ሊሰጠው ማሰቡን እንደሚያሳይ ማስረጃ አድርገው ተመልክተውታል የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ። ዮሴፍ፣ ያዕቆብ መጀመሪያ ሊያገባት አስቧት የነበረችውና አብልጦ የሚወዳት ሚስቱ የበኩር ልጅ መሆኑን ወንድሞቹ ያውቃሉ። ከዚህም ሌላ የያዕቆብ የበኩር ልጅ የሆነው ሮቤል ከአባቱ ቁባት ጋር በመተኛቱ አባቱን ያዋረደ ሲሆን በዚህም የብኩርና መብቱን አጥቷል።—ዘፍጥረት 35:22፤ 49:3, 4
b በዚህ ትንሽ የሚመስል ጉዳይም ጭምር የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክል መሆኑ ተረጋግጧል። በዚያ ዘመን የተጻፉ ሰነዶች በግብፅ አገር ባሪያዎች የሚሸጡበት የተለመደ ዋጋ 20 ሰቅል እንደነበረ ይገልጻሉ።