አለመግባባቶችን በመፍታት ሰላም ለመፍጠር ጥረት ታደርጋለህ?
ይሖዋ አምላክ፣ ክርስቲያኖች ሰላም ወዳድ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። በተጨማሪም በሕይወታቸው በሙሉ ሰላማዊ እንዲሆኑ ይፈልጋል። እያንዳንዳችን ሰላም ፈጣሪ መሆናችን በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል። ይህ ደግሞ ሰላማዊ ሕይወት መምራት የሚፈልጉ ሰዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ እንዲሳቡ ያደርጋል።
ለምሳሌ ያህል፣ በማዳጋስካር የሚኖር አንድ ጠንቋይ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለውን ሰላም ሲመለከት በጣም ተገረመ። ከዚያም ‘ወደፊት የአንድ ሃይማኖት አባል ከሆንኩ የምከተለው ይህን ሃይማኖት ነው’ በማለት አሰበ። ውሎ አድሮ መናፍስታዊ ድርጊቶች መፈጸሙን አቆመ፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር በሚስማማ መንገድ ጋብቻውን አስተካከለ፤ ከዚያም የሰላም አምላክ የሆነውን ይሖዋን ማምለክ ጀመረ።
በየዓመቱ ልክ እንደዚህ ግለሰብ ሰላምን አጥብቀው ሲፈልጉ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ይህን ሰላም ማግኘት ችለዋል። ይሁንና በጉባኤ ውስጥ “መራራ ቅናትና ጠበኝነት ካለ” በሰዎች መካከል ያለው ወዳጅነት ሊበላሽና ችግር ሊፈጠር እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ያዕ. 3:14-16) ደስ የሚለው ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መከላከልና በመካከላችን ያለው ሰላም እንዲጠናከር ማድረግ የምንችልበትንም መንገድ በተመለከተ ጠቃሚ ምክር ይሰጠናል። እነዚህ ምክሮች እንዴት ተግባራዊ መሆን እንደሚችሉ ለመረዳት በቅድሚያ የአንዳንድ ሰዎችን ተሞክሮ እንመልከት።
ችግሮቹና መፍትሔዎቻቸው
“አብሮኝ ከሚሠራ አንድ ወንድም ጋር መስማማት በጣም ከብዶኝ ነበር። አንድ ቀን ከዚህ ወንድም ጋር ስንጨቃጨቅ ሁለት ሰዎች አዩን።”—ክሪስ
“ከአንዲት እህት ጋር አዘውትረን እናገለግል ነበር፤ ነገር ግን በድንገት ከእኔ ጋር ማገልገል አቆመች። በኋላም ጨርሶ እኔን ማነጋገር ተወች። ለምን እንደዚያ እንዳደረገች ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም።”—ጃኔት
“ሦስት ሆነን አንድ ላይ በስልክ እያወራን ነበር። አንደኛው ሰው ‘ቻው’ ብሎን ስለነበር ስልኩን የዘጋው መስሎኝ ነበር። ከዚያም ይህን ግለሰብ በተመለከተ ለሌላኛው ሰው አንዳንድ ደስ የማይሉ ነገሮች ተናገርኩ፤ ግን ለካ ስልኩን አልዘጋውም ነበር።”—ማይክል
“በጉባኤያችን ውስጥ በሚገኙ ሁለት አቅኚዎች መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ እርስ በርስ ይጨቃጨቁ ነበር። የእነሱ ጭቅጭቅ ሌሎችን ቅር አሰኝቷል።”—ጋሪ
እዚህ ላይ የተጠቀሱት ችግሮች ያን ያህል ከባድ እንዳልሆኑ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም በባለጉዳዮቹ ላይ ዘላቂ የሆነ ስሜታዊና መንፈሳዊ ጉዳት ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። ደስ የሚለው ነገር፣ እዚህ ላይ የተጠቀሱት ወንድሞችና እህቶች በሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በመከተላቸው ዳግመኛ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ችለዋል። እነሱን የረዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች የትኞቹ ይመስሉሃል?
“በመንገድ ላይ እርስ በርስ እንዳትጣሉ።” (ዘፍ. 45:24) ዮሴፍ፣ ወንድሞቹ ወደ አባታቸው ተመልሰው በሚሄዱበት ወቅት ይህን ምክር ሰጥቷቸው ነበር። እንዴት ያለ ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር ነው! አንድ ሰው ስሜቱን የማይቆጣጠርና በቀላሉ የሚበሳጭ ከሆነ ሌሎችን ሊያስቆጣ ይችላል። ክሪስ፣ የኩራት ዝንባሌ እንዳለውና መመሪያ መቀበል እንደሚከብደው ተገነዘበ። ለውጥ ማድረግ ስለፈለገ ቅር ያሰኘውን ወንድም ይቅርታ ጠየቀ፤ ከዚያም ቁጣውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመረ። የሥራ ባልደረባው፣ ክሪስ ለመለወጥ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ሲያስተውል እሱም አንዳንድ ለውጦች ማድረግ ጀመረ። በአሁኑ ጊዜ ተስማምተው ይሖዋን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
“መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል።” (ምሳሌ 15:22) ጃኔት ይህን ምክር ተግባር ላይ ማዋል እንደሚያስፈልጋት ተገነዘበች። ስለዚህ ካኮረፈቻት እህት ጋር ‘ለመመካከር’ ወይም ለመነጋገር ወሰነች። በሚወያዩበት ወቅት ጃኔት፣ እህት ቅር ስለተሰኘችበት ነገር እንድትናገር በዘዴ አበረታታቻት። መጀመሪያ ላይ ውይይታቸው ውጥረት የሰፈነበት ነበር፤ በኋላ ላይ ግን ተረጋግተው ስለ ችግራቸው መወያየት የቻሉ ሲሆን በመካከላቸው የነበረው ውጥረትም እየቀለለ መጣ። ያቺ እህት አንድን ጉዳይ በተሳሳተ መንገድ ተረድታ እንደነበርና ጃኔት በጉዳዩ ውስጥ ጨርሶ እንደሌለችበት ተገነዘበች። በመሆኑም ይቅርታ ጠየቀች፤ በአሁኑ ጊዜ በአንድነት ይሖዋን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
“መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ።” (ማቴ. 5:23, 24) ኢየሱስ በተራራው ስብከት ላይ የሰጠውን ይህን ምክር ታስታውስ ይሆናል። ማይክል፣ የፈጸመው ድርጊት ምን ያህል አሳቢነትና ደግነት የጎደለው እንደሆነ ሲገነዘብ በጣም አዘነ። በመሆኑም ከዚያ ወንድም ጋር ዳግመኛ ሰላም ለመፍጠር ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። ወንድምን በአካል አግኝቶ በትሕትና ይቅርታ ጠየቀው። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ማይክል “ወንድሜ ከልቡ ይቅርታ አደረገልኝ” በማለት ተናግሯል። ሁለቱ ወንድሞች ወዳጅነታቸውን መልሰው ማደስ ችለዋል።
“አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።” (ቆላ. 3:12-14) ለረጅም ጊዜ በአቅኚነት ያገለገሉትን ሁለቱን እህቶች የረዳቸውስ ምንድን ነው? አንድ አሳቢ የጉባኤ ሽማግሌ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንዲያስቡባቸው አደረገ፦ ‘በሁለታችን አለመግባባት ምክንያት ሌሎች እንዲያዝኑ ማድረጋችን ተገቢ ነው? በእርግጥ እርስ በርሳችን እንዳንቻቻልና በሰላም ይሖዋን አብረን እንዳናገለግል የሚያደርግ ምክንያት አለን?’ እነዚህ እህቶች ሽማግሌው የሰጣቸውን ምክር ተቀብለው ተግባር ላይ አዋሉት። በአሁኑ ጊዜ በአንድነት ምሥራቹን በመስበክ ላይ ይገኛሉ።
ከላይ የተጠቀሰውን በቆላስይስ 3:12-14 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግህ አንድ ሰው በሚበድልህ ጊዜ ችግሩን ለመፍታት ይረዳሃል። ብዙ ሰዎች የትሕትና ባሕርይ በማንጸባረቅ የተፈጸመባቸውን በደል ይቅር ማለትና ማለፍ እንደሚቻል ተገንዝበዋል። ይሁንና በዚህ መልኩ በደሉን ይቅር ብለህ ማለፍ እንደማትችል ከተሰማህ በማቴዎስ 18:15 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግህ ሊረዳህ ይችላል። ኢየሱስ እዚህ ላይ የሰጠው ምክር አንድ ሰው በሌላው ሰው ላይ ከባድ በደል በሚፈጽምበት ጊዜ መወሰድ ስላለበት እርምጃ የሚገልጽ ነው። ሆኖም መሠረታዊ ሥርዓቱ በሌሎች ሁኔታዎችም ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ወንድምህን ወይም እህትህን ቀርበህ በደግነትና በትሕትና በማነጋገር ጉዳዩን ልትፈቱት ትችላላችሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች ምክሮችም ይዟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ብዙዎቹ ምክሮች “የመንፈስ ፍሬ” ማፍራትን ማለትም እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን ባሕርያት ማንጸባረቅን የሚጠይቁ ናቸው። (ገላ. 5:22, 23) የአንድ ማሽን ክፍሎች በተገቢው መንገድ እንዲሠሩ ዘይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ከሌሎች ጋር ሰላም ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት እንዲሳካም እነዚህን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ማንጸባረቅ ያስፈልጋል።
የተለያየ ባሕርይ ያላቸው ሰዎች መኖራቸው ለጉባኤው ውበት ይጨምራል
እያንዳንዳችን የተለያዩ ባሕርያት አሉን፤ በርካታ ነገሮችን የምናይበት መንገድም ሆነ ራሳችንን የምንገልጽበት መንገድ የተለያየ ነው። ይህ መሆኑ በመካከላችን ያለው ወዳጅነት አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ነገር ግን የባሕርይ ልዩነት መኖሩ ለግጭቶች መፈጠር ምክንያት ሊሆንም ይችላል። ለረጅም ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለ አንድ ወንድም ይህን ምሳሌ ሰጥቷል፦ “አንድ አይናፋር የሆነ ሰው በጣም ተጫዋች ከሆነ ሰው ጋር መሆን ሊከብደው ይችላል። በእነዚህ ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ቀላል ይመስል ይሆናል፤ ሆኖም በመካከላቸው ከባድ ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል።” እንዲህ ሲባል ታዲያ በጣም የተለያየ ባሕርይ ያላቸው ሰዎች እርስ በርስ ሊግባቡ አይችሉም ማለት ነው? እስቲ የሁለት ሐዋርያትን ምሳሌ እንመልከት። ጴጥሮስ ምን ዓይነት ሰው ነበር? ስለ ጴጥሮስ ስናስብ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ችኩልና የተሰማውን ከመናገር ወደኋላ የማይል ሰው ነው። ዮሐንስስ ምን ዓይነት ሰው ነበር? ስለ ዮሐንስ ስናስብ ደግሞ ወደ አእምሯችን የሚመጣው አፍቃሪ እንዲሁም በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ቁጥብ የሆነ ሰው ሊሆን ይችላል። እነዚህን ሐዋርያት በተመለከተ እንዲህ ያለ መደምደሚያ ላይ ልንደርስ የቻልነው ስለ እነሱ ከሚናገሩት ዘገባዎች በመነሳት ይሆናል። ሁለቱ ሐዋርያት የተለያየ ባሕርይ የነበራቸው ይመስላል። ሆኖም በሰላም አብረው ሠርተዋል። (ሥራ 8:14፤ ገላ. 2:9) ከዚህ ማየት እንደምንችለው በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የተለያየ ባሕርይ ያላቸው ክርስቲያኖችም በሰላም አብረው መሥራት ይችላሉ።
ምናልባት በጉባኤህ ውስጥ ያለ አንድ ወንድም አነጋገር ወይም ድርጊት ያበሳጭህ ይሆናል። ሆኖም ክርስቶስ ለዚያ ግለሰብ እንደሞተለት እንዲሁም ለግለሰቡ ፍቅር ማሳየት እንደሚጠበቅብህ ትገነዘባለህ። (ዮሐ. 13:34, 35፤ ሮም 5:6-8) በመሆኑም ከዚያ ግለሰብ ጋር በፍጹም ወዳጅ ልትሆን እንደማትችል ከመደምደም ይልቅ ራስህን እንዲህ እያልክ መጠየቅህ የተሻለ ይሆናል፦ ‘ይህ ወንድም ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በግልጽ የሚቃረን ነገር እየፈጸመ ነው? ሆን ብሎ እኔን ለማበሳጨት እየሞከረ ነው? ወይስ እንዲህ የተሰማኝ በመካከላችን የባሕርይ ልዩነት ስላለ ብቻ ነው? እሱ ካሉት ጥሩ ባሕርያት መካከል ማዳበር የምፈልገው የትኞቹን ነው?’
በተለይ የመጨረሻውን ጥያቄ መጠየቅህ በጣም አስፈላጊ ነው። ምናልባት አንተ ዝምተኛ ሆነህ ግለሰቡ ደግሞ ተጫዋች ሊሆን ይችላል፤ ከሆነ ግለሰቡ በአገልግሎት ላይ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር በቀላሉ ውይይት የሚጀምረው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። አብረኸው አገልግሎት በመውጣት ከእሱ አንዳንድ ነገሮችን መማር ትችል ይሆናል። ምናልባትም ግለሰቡ ከአንተ ይበልጥ ለጋስ ሊሆን ይችላል፤ ከሆነ ግለሰቡ በዕድሜ ለገፉ፣ ለታመሙ ወይም ለተቸገሩ ሰዎች ደግነት ሲያሳይ የሚያገኘውን ደስታ በመመልከት አንተም የእሱን ምሳሌ ለመከተል ለምን ጥረት አታደርግም? ዋናው ነጥብ፣ ከዚህ ወንድም ጋር የባሕርይ ልዩነት ቢኖራችሁም እንኳ አንዳችሁ ሌላው ባሉት መልካም ጎኖች ላይ ካተኮራችሁ እርስ በርስ ልትቀራረቡ ትችላላችሁ። እርግጥ እንዲህ ማድረጋችሁ የቅርብ ጓደኞች እንድትሆኑ አያስችላችሁ ይሆናል፤ ሆኖም መቀራረብ እንድትችሉና ለራሳችሁም ሆነ ለጉባኤው ሰላም አስተዋጽኦ ማበርከት እንድትችሉ ይረዳችኋል።
ኤዎድያንና ሲንጤኪ በጣም የተለያየ ባሕርይ የነበራቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ “በጌታ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው” መክሯቸዋል። (ፊልጵ. 4:2) አንተም የጳውሎስን ምክር ለመከተልና ሰላም ለማስፈን ጥረት ታደርጋለህ?
ግጭቶች ለረጅም ጊዜ እንዲቀጥሉ አትፍቀዱ
የሚያማምሩ አበቦች የሞሉበት የአትክልት ቦታ እንዲሁ ከተተወ አረም ሊወርሰው እንደሚችል ሁሉ እኛም ስለ ሌሎች የሚሰማንን መጥፎ ስሜት ከሥሩ ካልነቀልነው እየተባባሰ መሄዱ አይቀርም። አንድ ሰው ልቡ በምሬት ከተሞላ በጉባኤው መንፈስም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ለይሖዋና ለወንድሞቻችን ፍቅር ካለን የግል አለመግባባቶቻችን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለውን ሰላም እንዳያውኩ የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን።
ሰላም ለመፍጠር በማሰብ ግጭቶችን ወይም አለመግባባቶችን ለመፍታት ጥረት የምናደርግ ከሆነ በጣም ግሩም የሆነ ውጤት ልናገኝ እንችላለን። አንዲት የይሖዋ ምሥክር የገጠማትን ነገር እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “አንዲት እህት ልክ እንደ ሕፃን ልጅ እንደምትቆጥረኝ ይሰማኝ ነበር። ይህ ደግሞ በጣም ያበሳጨኝ ነበር። ከጊዜ ወደ ጊዜ ብስጭቴ እየጨመረ ስለመጣ እሷን ትሕትና በጎደለው መንገድ ማነጋገር ጀመርኩ። ‘እሷ የሚገባኝን አክብሮት እስካላሳየችኝ ድረስ እኔም ለእሷ አክብሮት አላሳያትም’ ብዬ አሰብኩ።”
በኋላ ላይ ግን ይህች እህት እሷ ራሷ ስላደረገቻቸው ነገሮች ማሰብ ጀመረች። እንዲህ ብላለች፦ “የራሴ ባሕርይ ችግር እንዳለው ማስተዋል ጀመርኩ፤ ከዚያም በራሴ በጣም አዘንኩ። አስተሳሰቤን ማስተካከል እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ከጸለይኩ በኋላ ለእህት ትንሽ ስጦታ ገዛሁ፤ እንዲሁም ላሳየሁት መጥፎ ባሕርይ ይቅርታ እንድታደርግልኝ የሚገልጽ ሐሳብ ካርድ ላይ ጽፌ ሰጠኋት። ከዚያም ሁለታችንም የተቃቀፍን ሲሆን ጉዳዩን ለመተው ተስማማን። ከዚያ በኋላ በመካከላችን ምንም ችግር ተፈጥሮ አያውቅም።”
ሰዎች ሰላም እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ይሁንና ብዙዎች ጥቃት እንደተሰነዘረባቸውና ክብራቸው እንደተነካ ሲሰማቸው ሰላም የሚያደፈርስ ነገር ማድረግ ይጀምራሉ። ይሖዋን በማያመልኩ ሰዎች ዘንድ ይህ የተለመደ ነገር ቢሆንም ይሖዋን በሚያመልኩ ሰዎች መካከል ግን ሰላምና አንድነት ሊሰፍን ይገባል። ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “ከተጠራችሁበት ጥሪ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በፍጹም ትሕትናና ገርነት፣ በትዕግሥት እንዲሁም እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ፤ አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።” (ኤፌ. 4:1-3) ይህ “የሰላም ማሰሪያ” በዋጋ ሊተመን የማይችል ነገር ነው። በመካከላችን የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ሁሉ በመፍታት ይህን “የሰላም ማሰሪያ” ለማጠናከር ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።