የጥናት ርዕስ 30
በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ ያለህን ቦታ ከፍ አድርገህ ተመልከት
“ከመላእክት በጥቂቱ አሳነስከው፤ የክብርና የግርማ ዘውድም ደፋህለት።”—መዝ. 8:5
መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት
ማስተዋወቂያa
1. አስደናቂ ስለሆኑት የይሖዋ ፍጥረታት ስናስብ ምን ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል?
ይሖዋ ስለፈጠረው ግዙፍ ጽንፈ ዓለም ስናስብ እንደ መዝሙራዊው ዳዊት ይሰማን ይሆናል፤ ዳዊት ወደ ይሖዋ ሲጸልይ እንዲህ ብሏል፦ “የጣቶችህን ሥራ ሰማያትን፣ አንተ የሠራሃቸውን ጨረቃንና ከዋክብትን ስመለከት፣ ታስበው ዘንድ ሟች ሰው ምንድን ነው? ትንከባከበውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?” (መዝ. 8:3, 4) እንደ ዳዊት ሁሉ እኛም፣ ከጽንፈ ዓለሙ ጋር ስንወዳደር ምን ያህል ትንሽ እንደሆንን ስናስብ ይሖዋ ትኩረት የሚሰጠን መሆኑ ራሱ ያስደንቀን ይሆናል። ሆኖም ከዚህ ቀጥለን እንደምንመለከተው ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለአዳምና ለሔዋን ትኩረት ከመስጠት ባለፈ የቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
2. ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ምድራዊ ልጆቹ ምን ዓላማ ነበረው?
2 አዳምና ሔዋን የይሖዋ የመጀመሪያዎቹ ምድራዊ ልጆች ነበሩ፤ ይሖዋ ደግሞ አፍቃሪ የሆነ ሰማያዊ አባታቸው ነበር። ይሖዋ እነዚህ ባልና ሚስት ጠቃሚ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ ይፈልግ ነበር። አምላክ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም።” (ዘፍ. 1:28) የአምላክ ዓላማ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱና ምድርን እንዲንከባከቡ ነበር። አዳምና ሔዋን ይሖዋን ቢታዘዙና የእሱን ዓላማ ቢፈጽሙ ኖሮ እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው ለዘላለም የአምላክ ቤተሰብ አባላት ሆነው መኖር ይችሉ ነበር።
3. አዳምና ሔዋን በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ የተከበረ ቦታ ተሰጥቷቸው ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
3 አዳምና ሔዋን በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ የተከበረ ቦታ ነበራቸው። ዳዊት በመዝሙር 8:5 ላይ ይሖዋ ሰውን ስለፈጠረበት መንገድ ሲናገር “ከመላእክት በጥቂቱ አሳነስከው፤ የክብርና የግርማ ዘውድም ደፋህለት” ብሏል። እርግጥ ነው፣ ሰዎች የመላእክትን ዓይነት ኃይል፣ የአእምሮ ብቃትም ሆነ ችሎታ አልተሰጣቸውም። (መዝ. 103:20) ያም ቢሆን ሰዎች ከእነዚህ ኃያል መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚያንሱት “በጥቂቱ” ብቻ ነው። ይህ የሚያስደንቅ አይደለም? በእርግጥም ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ግሩም ሕይወት ሰጥቷቸዋል።
4. አዳምና ሔዋን አለመታዘዛቸው ምን አስከተለ? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
4 የሚያሳዝነው፣ አዳምና ሔዋን በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ የነበራቸውን ቦታ አጡ። በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደምንመለከተው ይህ በዘሮቻቸው ላይም አስከፊ ውጤት አስከትሏል። ሆኖም የይሖዋ ዓላማ አልተለወጠም። ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ለዘላለም ልጆቹ እንዲሆኑ ይፈልጋል። እስቲ በመጀመሪያ ይሖዋ ያከበረን እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ከዚያም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት መሆን እንደምንፈልግ ለማሳየት ከአሁኑ ምን ማድረግ እንደምንችል እንመለከታለን። በመጨረሻም የይሖዋ ምድራዊ ልጆች ለዘላለም የሚያገኟቸውን በረከቶች እንመረምራለን።
ይሖዋ ሰዎችን ያከበራቸው እንዴት ነው?
5. አምላክ በራሱ መልክ ስለሠራን አመስጋኝ እንደሆንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5 ይሖዋ በራሱ መልክ በመሥራት አክብሮናል። (ዘፍ. 1:26, 27) የተፈጠርነው በአምላክ መልክ ስለሆነ የእሱን ግሩም ባሕርያት ማዳበርና ማንጸባረቅ እንችላለን፤ ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ፍቅር፣ ርኅራኄ፣ ታማኝነትና ጽድቅ ይገኙበታል። (መዝ. 86:15፤ 145:17) እንዲህ ያሉትን ባሕርያት ስናዳብር ይሖዋን እናከብረዋለን፤ እንዲሁም ለእሱ ያለንን አመስጋኝነት እናሳያለን። (1 ጴጥ. 1:14-16) የሰማዩን አባታችንን በሚያስደስት መንገድ ስንኖር ደስታና እርካታ እናገኛለን። ከዚህም ሌላ ይሖዋ በመልኩ ስለሠራን ከቤተሰቡ አባላት የሚጠብቃቸውን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንችላለን።
6. ይሖዋ ምድርን የፈጠረበት መንገድ ሰዎችን እንደሚያከብራቸው የሚያሳየው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ ልዩ መኖሪያ አዘጋጅቶልናል። ይሖዋ የመጀመሪያውን ሰው ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ምድርን ለሰው ልጆች ተስማሚ መኖሪያ እንድትሆን አድርጎ አዘጋጅቷታል። (ኢዮብ 38:4-6፤ ኤር. 10:12) ይሖዋ አሳቢና ለጋስ ስለሆነ የሚያስደስቱንን መልካም ነገሮች አትረፍርፎ ሰጥቶናል። (መዝ. 104:14, 15, 24) የፈጠራቸውን ነገሮች መለስ ብሎ ሲመለከት ሥራው “መልካም እንደሆነ” አይቷል። (ዘፍ. 1:10, 12, 31) ይሖዋ በምድር ላይ በፈጠራቸው አስደናቂ ነገሮች ሁሉ ላይ ለሰዎች “ሥልጣን” በመስጠት አክብሯቸዋል። (መዝ. 8:6) የአምላክ ዓላማ ፍጹም የሆኑ ሰዎች እነዚህን አስደናቂ ፍጥረታት እየተንከባከቡ ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ ነው። ለዚህ ግሩም ተስፋ ይሖዋን አዘውትረህ ታመሰግነዋለህ?
7. ኢያሱ 24:15 ሰዎች የመምረጥ ነፃነት እንዳላቸው የሚያመለክተው እንዴት ነው?
7 ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። በመሆኑም የምንሄድበትን የሕይወት ጎዳና መምረጥ እንችላለን። (ኢያሱ 24:15ን አንብብ።) አፍቃሪው አምላካችን እሱን ለማገልገል ስንመርጥ ይደሰታል። (መዝ. 84:11፤ ምሳሌ 27:11) በተጨማሪም የመምረጥ ነፃነታችንን ተጠቅመን ሌሎች በርካታ ጥሩ ውሳኔዎች ማድረግ እንችላለን። ኢየሱስ በዚህ ረገድ የተወውን ምሳሌ እንመልከት።
8. ኢየሱስ የመምረጥ ነፃነቱን ከተጠቀመባቸው መንገዶች አንዱ የትኛው ነው?
8 የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ቅድሚያ ለመስጠት መምረጥ እንችላለን። በአንድ ወቅት ኢየሱስና ሐዋርያቱ በጣም ስለደከማቸው እረፍት ለማግኘት ጸጥ ወዳለ ቦታ ሄዱ። ሆኖም ማረፍ አልቻሉም። ያሰቡት ቦታ ሲደርሱ በጣም ብዙ ሰዎች እየጠበቋቸው ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ከኢየሱስ ለመማር ጓጉተው ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ሰዎቹ ተከትለውት ስለመጡ አልተበሳጨባቸውም። ከዚህ ይልቅ አዘነላቸው። ስለዚህ ኢየሱስ ምን አደረገ? “ብዙ [ነገር] ያስተምራቸው ጀመር።” (ማር. 6:30-34) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ሌሎችን ለመርዳት ስንል ጊዜያችንንና ጉልበታችንን መሥዋዕት የምናደርግ ከሆነ የሰማዩን አባታችንን እናስከብራለን። (ማቴ. 5:14-16) በተጨማሪም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት መሆን እንደምንፈልግ እናሳያለን።
9. ይሖዋ ለሰዎች ምን ልዩ ስጦታ ሰጥቷቸዋል?
9 ይሖዋ ለሰዎች የመውለድ ችሎታ ሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ልጆቻቸው እሱን እንዲወዱትና እንዲያገለግሉት የማስተማር ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ወላጅ ከሆንክ ለዚህ ልዩ ስጦታ አድናቆት አለህ? ይሖዋ ለመላእክት ብዙ አስደናቂ ችሎታዎችን ቢሰጣቸውም ልጆች የመውለድ መብት አልሰጣቸውም። ስለዚህ ወላጆች፣ ልጆች የማሳደግ መብታቸውን ከፍ አድርገው ሊመለከቱት ይገባል። ወላጆች ቅዱስ አደራ፣ ማለትም ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” የማሳደግ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። (ኤፌ. 6:4፤ ዘዳ. 6:5-7፤ መዝ. 127:3) የይሖዋ ድርጅት ወላጆችን ለመርዳት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ብዙ መሣሪያዎችን አዘጋጅቷል፤ ከእነዚህም መካከል ጽሑፎች፣ ቪዲዮዎች፣ ሙዚቃዎችና ኢንተርኔት ላይ የወጡ ሌሎች ነገሮች ይገኙበታል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የሰማዩ አባታችንም ሆነ ልጁ ኢየሱስ ልጆችን ይወዷቸዋል። (ሉቃስ 18:15-17) ወላጆች በይሖዋ የሚተማመኑ እንዲሁም ውድ ልጆቻቸውን ተንከባክበው ለማሳደግ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉ ከሆነ ይሖዋ ይደሰታል። እንዲሁም እንዲህ የሚያደርጉ ወላጆች ልጆቻቸው ለዘላለም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት የመሆን አጋጣሚ እንዲከፈትላቸው ያደርጋሉ!
10-11. ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ምን አጋጣሚ ከፍቶልናል?
10 ይሖዋ የእሱ ቤተሰብ አባላት የመሆን አጋጣሚ መልሰን እንድናገኝ ሲል ውድ ልጁን ሰጥቶናል። በአንቀጽ 4 ላይ እንደተመለከትነው አዳምና ሔዋን በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ የነበራቸውን ቦታ አጥተዋል፤ ልጆቻቸውንም ይህን መብት አሳጥተዋቸዋል። (ሮም 5:12) አዳምና ሔዋን የአምላክን መመሪያ የጣሱት ሆን ብለው ነው፤ በመሆኑም ከእሱ ቤተሰብ መወገድ ይገባቸዋል። ይሁንና ልጆቻቸውስ? ይሖዋ ከእነሱ መካከል ታዛዥ የሆኑት፣ በእሱ ቤተሰብ ውስጥ እንዲታቀፉ በፍቅር ተነሳስቶ ዝግጅት አደረገ። ይህን ያደረገው በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት ነው። (ዮሐ. 3:16፤ ሮም 5:19) በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት አምላክ ታማኝነታቸውን የጠበቁ 144,000 ሰዎችን ልጆቹ አድርጎ ወስዷቸዋል።—ሮም 8:15-17፤ ራእይ 14:1
11 በተጨማሪም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ታማኝ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ በታዛዥነት እያደረጉ ነው። እነሱም በሺው ዓመት መጨረሻ ካለው ፈተና በኋላ የአምላክ ቤተሰብ አባላት የመሆን አጋጣሚ ያገኛሉ። (መዝ. 25:14፤ ሮም 8:20, 21) ይህ ተስፋ ስላላቸው አሁንም ቢሆን ፈጣሪያቸውን ይሖዋን “አባታችን” ብለው ይጠሩታል። (ማቴ. 6:9) ከሞት የሚነሱ ሰዎችም ይሖዋ ምን እንደሚጠብቅባቸው የመማር አጋጣሚ ያገኛሉ። ከዚያም የይሖዋን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑት ሰዎች የእሱ ቤተሰብ አባላት ይሆናሉ።
12. ከዚህ ቀጥሎ የትኛውን ጥያቄ እንመረምራለን?
12 እስካሁን እንደተመለከትነው ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ሰዎችን አክብሯቸዋል። ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ልጆቹ አድርጎ ወስዷቸዋል፤ ‘ለእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት ደግሞ በአዲሱ ዓለም ልጆቹ እንዲሆኑ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (ራእይ 7:9) ታዲያ ለዘላለም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት ሆነን መኖር እንደምንፈልግ ከአሁኑ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
የይሖዋ ቤተሰብ አባል መሆን እንደምትፈልግ አሳይ
13. የአምላክ ቤተሰብ አባላት ለመሆን ምን ማድረግ ይጠበቅብናል? (ማርቆስ 12:30)
13 በሙሉ ልብህ ይሖዋን በማገልገል ለእሱ ያለህን ፍቅር አሳይ። (ማርቆስ 12:30ን አንብብ።) ይሖዋ ብዙ ስጦታዎችን በደግነት ሰጥቶናል፤ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ስጦታዎቹ መካከል አንዱ ደግሞ እሱን የማምለክ መብታችን ነው። የይሖዋን ‘ትእዛዛት በመጠበቅ’ እሱን እንደምንወደው እናሳያለን። (1 ዮሐ. 5:3) ይሖዋ እንድንጠብቅ ከሚፈልጋቸው ትእዛዛት መካከል ኢየሱስ የሰጠው ትእዛዝ ይገኝበታል፤ ኢየሱስ ሰዎችን እያጠመቅን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ አዞናል። (ማቴ. 28:19) በተጨማሪም እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ትእዛዝ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 13:35) ይሖዋ ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች፣ በመላው ዓለም ያሉ አምላኪዎቹን ያቀፈው ቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ ይፈቅድላቸዋል።—መዝ. 15:1, 2
14. ለሌሎች ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ማቴዎስ 9:36-38፤ ሮም 12:10)
14 ለሌሎች ፍቅር አሳይ። ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ ፍቅር ያሳየን እኛ እሱን ከማወቃችን እንኳ በፊት ነው። (1 ዮሐ. 4:9, 10) ለሌሎች ፍቅር በማሳየት እሱን መምሰል እንችላለን። (ኤፌ. 5:1) ለሰዎች ፍቅር ማሳየት ከምንችልባቸው ወሳኝ መንገዶች አንዱ፣ ጊዜው ከማለፉ በፊት ስለ ይሖዋ እንዲማሩ መርዳት ነው። (ማቴዎስ 9:36-38ን አንብብ።) እንዲህ ስናደርግ የይሖዋ ቤተሰብ አባላት የመሆን አጋጣሚ እንከፍትላቸዋለን። አንድ ሰው ከተጠመቀ በኋላም ለእሱ ፍቅርና አክብሮት ማሳየታችንን መቀጠል አለብን። (1 ዮሐ. 4:20, 21) ይህ ምንን ይጨምራል? ለምሳሌ አንድን ነገር ለማድረግ ያነሳሳውን ውስጣዊ ዝንባሌ አንጠራጠርም። በሌላ አባባል፣ አንድን ነገር ያደረገው በክፋት ወይም በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ ነው ብለን አናስብም። ከዚህ ይልቅ ወንድማችን ከእኛ እንደሚበልጥ በማሰብ አክብሮት እናሳየዋለን።—ሮም 12:10ን አንብብ፤ ፊልጵ. 2:3
15. ምሕረትና ደግነት ማሳየት ያለብን ለእነማን ነው?
15 ለሁሉም ሰው ምሕረትና ደግነት አሳይ። ለዘላለም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት ሆነን መኖር ከፈለግን የአምላክን ቃል በሕይወታችን በሥራ ላይ ማዋል አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ጠላቶቻችንን ጨምሮ ለሁሉም ሰው ምሕረትና ደግነት ማሳየት እንዳለብን አስተምሯል። (ሉቃስ 6:32-36) ይህን ማድረግ አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ከሆነ በአስተሳሰባችንም ሆነ በምግባራችን ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይሖዋን ለመታዘዝና ኢየሱስን ለመምሰል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ለዘላለም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት ሆነን መኖር እንደምንፈልግ እናሳያለን።
16. የይሖዋን ቤተሰብ መልካም ስም ላለማጉደፍ መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?
16 የይሖዋን ቤተሰብ መልካም ስም ላለማጉደፍ ተጠንቀቅ። በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ ታናሽየው ልጅ የታላቅ ወንድሙን ምሳሌ ይከተላል። ታላቅየው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ የሚያውል ከሆነ ለታናሽ ወንድሙ ጥሩ ምሳሌ ይሆነዋል። ታላቅየው መጥፎ ድርጊት የሚፈጽም ከሆነ ግን ታናሽየውም የወንድሙን መጥፎ ምሳሌ ሊከተል ይችላል። በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በአንድ ወቅት ታማኝ የነበረ ክርስቲያን የክህደት አካሄድ መከተል ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት መምራት ቢጀምር ሌሎችም እሱን ተከትለው መጥፎ ድርጊት ለመፈጸም ሊፈተኑ ይችላሉ። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች የይሖዋን ቤተሰብ መልካም ስም ያጎድፋሉ። (1 ተሰ. 4:3-8) የሌሎችን መጥፎ ምሳሌ ከመከተል መቆጠብ ይኖርብናል፤ እንዲሁም ማንኛውም ነገር ከአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን እንዲያርቀን ልንፈቅድ አይገባም።
17. የትኛው አስተሳሰብ እንዳያድርብን መጠንቀቅ ይኖርብናል? ለምንስ?
17 በቁሳዊ ነገሮች ሳይሆን በይሖዋ ታመን። ይሖዋ ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱን ከፈለግንና በእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች ከተመራን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንደሚያሟላልን ቃል ገብቶልናል። (መዝ. 55:22፤ ማቴ. 6:33) ይሖዋ በገባልን ቃል የምንተማመን ከሆነ ይህ ዓለም የሚያቀርብልን ቁሳዊ ነገሮች ጥበቃ እንደሚሆኑልን ወይም ዘላቂ ደስታ እንደሚያስገኙልን አናስብም። እውነተኛ ሰላም ማግኘት የምንችለው የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን። (ፊልጵ. 4:6, 7) ብዙ ነገሮችን ለመግዛት አቅሙ ቢኖረንም እንኳ ‘እነዚህን ዕቃዎች ለመጠቀምም ሆነ ለመንከባከብ የሚያስፈልገው ጊዜና ጉልበት አለኝ ወይ’ የሚለውን ልናስብበት ይገባል። ለቁሳዊ ንብረቶቻችን ሚዛኑን የሳተ ፍቅር እያዳበርን ይሆን? አምላክ በቤተሰቡ ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንድናበረክት እንደሚጠብቅብን ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም ትኩረታችን እንዲከፋፈል ልንፈቅድ አይገባም። ቁሳዊ ንብረቶቹን በጣም ከመውደዱ የተነሳ ኢየሱስን ላለመከተል የመረጠውን ወጣት መምሰል አንፈልግም፤ ይህ ሰው ይሖዋን የማገልገልና የእሱ ልጅ የመሆን አጋጣሚ አምልጦታል።—ማር. 10:17-22
የይሖዋ ልጆች የሚያገኟቸው ዘላለማዊ በረከቶች
18. ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ምን ታላቅ ክብር ያገኛሉ? የትኞቹን ዘላለማዊ በረከቶችስ ያጣጥማሉ?
18 ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ከሁሉ የላቀውን ክብር፣ ማለትም ይሖዋን ለዘላለም የመውደድና የማምለክ መብት ያገኛሉ! ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ይሖዋ ውብ መኖሪያ አድርጎ ያዘጋጀላቸውን ምድርን መንከባከብ የሚያስገኘውን ደስታም ያጣጥማሉ። በቅርቡ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምድርም ሆነች በምድር ላይ ያሉት ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ አዲስ ይሆናሉ። አዳምና ሔዋን ከአምላክ ቤተሰብ ለመውጣት በመወሰናቸው ምክንያት የመጡትን ችግሮች በሙሉ ኢየሱስ ያስተካክላቸዋል። ይሖዋ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት ገነት በሆነች ምድር ላይ ፍጹም ጤናማ ሆነው ለዘላለም እንዲኖሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 23:42, 43) በምድር ላይ ያሉት የይሖዋ ቤተሰብ አባላት ወደ ፍጽምና ሲደርሱ ሁሉም ዳዊት የተናገረለትን ‘ክብርና ግርማ’ ይላበሳሉ።—መዝ. 8:5
19. በየትኞቹ ነገሮች ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል?
19 ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባል ከሆንክ ግሩም ተስፋ ተዘርግቶልሃል። አምላክ ይወድሃል፤ የቤተሰቡ አባል እንድትሆንም ይፈልጋል። እንግዲያው እሱን ለማስደሰት አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ። አምላክ በሰጠህ ተስፋዎች ላይ በየዕለቱ አሰላስል። የምንወደውን ሰማያዊ አባታችንን የማምለክና እሱን ለዘላለም የማወደስ መብትህን ከፍ አድርገህ ተመልከተው!
መዝሙር 107 መለኮታዊው የፍቅር መንገድ
a አንድ ቤተሰብ ደስተኛ እንዲሆን እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል የሚጠበቅበትን ነገር ማወቅ እንዲሁም ከሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ጋር መተባበር ይኖርበታል። አባትየው ቤተሰቡን በፍቅር ይመራል፤ እናትየዋ አባትየውን ትደግፈዋለች፤ ልጆቹ ደግሞ ወላጆቻቸውን ይታዘዛሉ። ከይሖዋ ቤተሰብ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አምላካችን ለእኛ ዓላማ አለው፤ ከዚህ ዓላማ ጋር ተባብረን የምንሠራ ከሆነ የይሖዋን አምላኪዎች ባቀፈው ቤተሰብ ውስጥ ለዘላለም መኖር እንችላለን።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ ይሖዋ ሰዎችን የፈጠራቸው በራሱ መልክ ነው፤ አንድ ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው እንዲሁም ለልጆቻቸው ፍቅርና ርኅራኄ በማሳየት የይሖዋን ባሕርያት ሲያንጸባርቁ። ባልና ሚስቱ ይሖዋን ይወዳሉ። ልጆች የመውለድ መብታቸውን ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱት ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱትና እንዲያገለግሉት በማስተማር አድናቆታቸውን ያሳያሉ። እነዚህ ወላጆች ይሖዋ ኢየሱስን ቤዛ አድርጎ የሰጠን ለምን እንደሆነ ቪዲዮ ተጠቅመው ለልጆቻቸው ያስረዳሉ። በተጨማሪም ወደፊት በሚመጣው ገነት ውስጥ ምድርንና እንስሳትን ለዘላለም እየተንከባከብን እንደምንኖር ያስተምሯቸዋል።