መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክን በምስሎች ተጠቅመን ማምለክ ይኖርብናል?
“ምስሎች ወደ አምላክ ይበልጥ እንድቀርብ ይረዱኛል ብዬ አስብ ነበር።”—ማክ
“ቤታችንን በሃይማኖታዊ ምስሎች የሞላነው ሲሆን ይህም አምላክን ያስደስተዋል ብለን እናስብ ነበር።”—ኸርታ
“ለአንዳንድ ምስሎች እንሰግድ ነበር። አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚሰማው ፈጽሞ አስበን አናውቅም።”—ሳንድራ
አንተስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል? ብዙ ሰዎች ሃይማኖታዊ ምስሎች አምላክን ለማምለክ ይረዱናል የሚል እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ ይህ አመለካከት ትክክል ነው? ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማዋል? የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እስቲ እንመልከት።
አምላክ ለሃይማኖታዊ ምስሎች ያለው አመለካከት
ሃይማኖታዊ ምስሎችና ጣዖታት፣ አምልኮ ወይም ክብር ሊሰጠው የሚገባውን አካል የሚወክሉ ነገሮች ናቸው። ከእነዚህም መካከል መስቀሎች፣ ሐውልቶች፣ ሥዕሎች አሊያም በሰማይ ወይም በምድር ላይ ያሉ እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ይገኙበታል።a ባንዲራዎችም አምልኮ ከሚሰጣቸው ነገሮች መካከል ሊካተቱ ይችላሉ።
ሰዎች እነዚህን ነገሮች ለአምልኮ መጠቀም ከጀመሩ ብዙ ሺህ ዓመታት አልፈዋል። አምላክ፣ በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት አዲስ ለተቋቋመው የእስራኤል ብሔር አሥርቱን ትእዛዛት ሲሰጥ ለሃይማኖታዊ ምስሎች ምን አመለካከት እንዳለው በግልጽ ተናግሯል። አምላክ እንዲህ ብሏል:- “በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] አምላክህ . . . ቀናተኛ አምላክ ነኝ።”—ዘፀአት 20:4, 5
አምላክ በሰጠው በዚህ ትእዛዝ ላይ የከለከላቸውን ሁለት ነገሮች ልብ በል። አንደኛ፣ ሕዝቡ ሃይማኖታዊ ምስሎችን እንዳይሠሩ አዟል። ሁለተኛ ደግሞ፣ ለምስሎቹ ‘መስገድ’ ወይም እነሱን ማምለክ እንደማይገባቸው ገልጿል። ፈጣሪያችን ሃይማኖታዊ ምስሎችን እንዳንሠራ የከለከለው ለምንድን ነው? የአምላክን ምስል የማንሠራበት አንዱ ምክንያት ‘እሱን ያየው ማንም ስለሌለ’ ነው። ይሖዋ መንፈስ ሲሆን የሚኖረውም በመንፈሳዊ ዓለም ነው። (ዮሐንስ 1:18፤ 4:24) ማናቸውንም ምስል የማንሠራበት ሌላው ምክንያት ደግሞ አምላክ “ቀናተኛ” ወይም እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ በመሆኑ ነው። አምላክ “ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም” ብሏል። (ኢሳይያስ 42:8) በዚህም ምክንያት ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ስህተት ነው። የእስራኤላውያን መሪ የነበረው አሮን ምስል በሠራ ጊዜ ይሖዋ በጣም አዝኗል።—ዘፀአት 32:4-10
ልንሰግድላቸው የማይገባው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ጣዖታትን አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም፣ ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም።” አክሎም ‘እነዚህን የሚያበጁ ሁሉ እንደ እነርሱ [ማለትም በድን] ይሆናሉ’ በማለት ያስጠነቅቃል!—መዝሙር 115:4-8
በተጨማሪም የጣዖት አምልኮ ኢፍትሐዊነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት ነው። እስቲ እንደሚከተለው ብለህ ራስህን ጠይቅ:- ‘በጣም ውድ የሆነ ስጦታ ለልጄ ብሰጠውና እኔን ማመስገን ትቶ ፈጽሞ የማያውቀውን ሰው ወይም በድን የሆነን ነገር ቢያመሰግን ምን ይሰማኛል?’ ይህ ጥያቄ ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን የሆነው አምላክ፣ ለእሱ የሚገባውን ምሥጋናና አምልኮ በድን የሆኑ ጣዖታትን ጨምሮ ለሌሎች ስትሰጥ ምን ሊሰማው እንደሚችል እንድትገነዘብ ይረዳሃል።—ራእይ 4:11
በሌላ በኩል አምላክ በራሱ አምሳል የፈጠራቸው የሰው ልጆች በድን የሆኑ ጣዖታትን ቢያመልኩ ምን ያህል አሳፋሪ ሊሆን እንደሚችል ገምት! (ዘፍጥረት 1:27) ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ያደረጉ አንዳንድ ሰዎችን አስመልክቶ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ጣቶቻቸው ላበጇቸው፣ ለእጆቻቸው ሥራ ይሰግዳሉ። ሰው ዝቅ ብሎአል፤ የሰው ልጅም ተዋርዶአል፤ ስለዚህ [ይሖዋ አምላክ] በደላቸውን ይቅር አትበል።”—ኢሳይያስ 2:8, 9
የሐሰት አምልኮን በአምላክ ዘንድ ይበልጥ አስጸያፊ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ ጣዖትን ማምለክ፣ የአምላክ ጠላቶች የሆኑትን አጋንንትን ማምለክ ማለት ስለሆነ ነው። ዘዳግም 32:17 እስራኤላውያን ይሖዋን ትተው ጣዖታትን ስላመለኩበት ወቅት ሲናገር “አምላክ ላልሆኑ አጋንንት . . . ሠዉ” ይላል።
የጥንቶቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ምስሎችን ያመልኩ አሊያም ለአምልኮ ይጠቀሙባቸው ነበር? በጭራሽ! የኢየሱስ ሐዋርያ የነበረው ዮሐንስ “ልጆች ሆይ፤ ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:21) ኧርሊ ቸርች ሂስትሪ ቱ ዘ ዴዝ ኦቭ ኮንስታንቲን የተባለው መጽሐፍ “የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት የምስልን አምልኮ ያህል የሚጸየፉት ነገር አልነበረም” በማለት ገልጿል።
ትክክለኛው አምልኮ
ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል።” (ዮሐንስ 4:23) አዎን፣ አምላክ ማንነቱን ማለትም የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች እንዲሁም የአቋም መሥፈርቶቹን ብሎም ለእኛ ያለውን ዓላማ እንድናውቅ ይፈልጋል። (ዮሐንስ 17:3) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲጻፍልን ያደረገውም ለዚህ ሲል ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በተጨማሪም አምላክ ‘ከእያንዳንዳችን የራቀ ስላልሆነ’ የሃይማኖታዊ ምስሎች እርዳታ ሳያስፈልገን በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ወደ እሱ መጸለይ እንችላለን።—የሐዋርያት ሥራ 17:27
ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሳንድራ እንዲህ ብላለች:- “ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሄድኩበት ጊዜ አንድም ምስል አላየሁም። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም የአምላክን ባሕርያትና የአቋም መሥፈርቶች እንዳውቅ ረዱኝ። በመሆኑም በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት በሚያስገኝ መንገድ መጸለይን ተማርኩ። አሁን ስለ ፈጣሪ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዳለኝና ወደ እሱ ይበልጥ እንደቀረብኩ ሆኖ ይሰማኛል።” አዎን፣ ሳንድራ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መንፈስን የሚያድሱና ነፃ የሚያወጡ መሆናቸውን ተገንዝባለች። (ዮሐንስ 8:32) አንተም ይህን መቅመስ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ መጽሔት፣ የሚያዝያ 2006 እትም ላይ የወጣውን “በእርግጥ ኢየሱስ የተሰቀለው በመስቀል ላይ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ይህን አስተውለኸዋል?
◼ ማንኛውንም ዓይነት ምስል ለአምልኮ መጠቀም የሌለብን ለምንድን ነው?—መዝሙር 115:4-8፤ 1 ዮሐንስ 5:21
◼ እውነተኛው አምላክ መመለክ ያለበት እንዴት ነው?—ዮሐንስ 4:24
◼ ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግህስ ምን ጥቅም ሊያስገኝልህ ይችላል?—ዮሐንስ 8:32፤ 17:3