ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ቃል “ዕለት ዕለት” መጠበቅ
“በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ የመከራውንም እንጨት ዕለት ዕለት ተሸክሞ ያለማቋረጥ ይከተለኝ።”—ሉቃስ 9:23 አዓት
1. ክርስቲያኖች ሆነን በምናከናውነው ሥራ ምን ያህል እንደተዋጣልን መመዘን የምንችልበት አንዱ መንገድ ምን ድን ነው?
“በእርግጥ ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ ለያዝነው ዓላማ ያዋልን ሰዎች ነበርንን?” 35ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዘዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ እንዳሉት ከሆነ የዚህ ጥያቄ መልስ በሥልጣን ኮርቻ ላይ ያሉትን ሰዎች ስኬታማነት ለመለካት የሚያስችል አንዱ መመዘኛ ነው። ይህ ጥያቄ ይበልጥ ጠለቅ ያለ ትርጉም ባለው መንገድ ክርስቲያን አገልጋዮች ሆነን በምንሠራው ሥራ ምን ያህል እንደተዋጣልን ለመመዘን ሊያገለግል ይችላል።
2. አንድ መዝገበ ቃላት “ራስን መወሰን” ለሚለው ቃል ምን ፍቺ ሰጥቶታል?
2 ይሁንና ሕይወትን ለአንድ ነገር ማዋል ወይም መወሰን ማለት ምን ማለት ነው? ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጂየት ዲክሽነሪ “ለአንድ መለኮታዊ አካል ወይም ለአንድ ቅዱስ ዓላማ ራስን ለማዋል የሚወሰድ እርምጃ ወይም ሃይማኖታዊ ሥርዓት”፤ “ለአንድ የተለየ ዓላማ ማደር ወይም ራስን ማዋል”፤ “የራስን ጥቅም በመሠዋት አቅም በሚፈቅደው ሁሉ ማገልገል” የሚሉ ፍቺዎች ሰጥቶታል። ጆን ኤ ፍ ኬኔዲ ቃሉን የተጠቀሙበት “የራስን ጥቅም በመሠዋት አቅም በሚፈቅደው ሁሉ ማገልገል” የሚለውን ሐሳብ ለማስተላለፍ ይመስላል። ለአንድ ክርስቲያን ራስን መወሰን ከዚህም የበለጠ ትርጉም አለው።
3. ራስን መወሰን ክርስቲያናዊ ትርጉሙ ምንድን ነው?
3 ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ የመከራውንም እንጨት ተሸክሞ ያለማቋረጥ ይከተለኝ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 16:24 አዓት) ራስን ለመለኮታዊ ዓላማ ማዋል ሲባል እሁድ እሁድ ወይም የሆነ የአምልኮ ቦታ በሚጎበኝበት ጊዜ ብቻ የሚከናወን የአምልኮ ሥርዓት ማለት አይደለም። የአንድን ሰው አኗኗር በሙሉ የሚያካትት ነው። ክርስቲያን መሆን ማለት ራስን በመካድ ኢየሱስ ክርስቶስ ያገለግለው የነበረውን አምላክ ይሖዋን ማገልገል ማለት ነው። በተጨማሪም አንድ ክርስቲያን የክርስቶስ ተከታይ በመሆኑ ምክንያት ሊደርስበት የሚችለውን ማንኛውንም መከራ በመቻል “የመከራውንም እንጨት” ይሸከማል።
ፍጹሙ ምሳሌ
4. የኢየሱስ ጥምቀት ምን ያመለክታል?
4 ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት ራስን ለይሖዋ መወሰን ምንን እንደሚጨምር በግልጽ አሳይቷል። “መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ” በማለት የተሰማውን ስሜት ገልጾታል። ከዚያም “እነሆ፣ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፣ አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ” ሲል አክሎ ተናግሯል። (ዕብራውያን 10:5–7) ራሱን ለአምላክ የወሰነ ሕዝብ አባል እንደ መሆኑ መጠን ሲወለድም ለአምላክ የተወሰነ ነበር። ያም ሆኖ ግን በምድራዊ አገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ማቅረቡን ለማመልከት ለጥምቀት ራሱን አቀረበ፤ ይህም ሕይወቱን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብንም ይጠይቅበት ነበር። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ክርስቲያኖች የይሖዋ ፈቃድ የሆነውን ማንኛውንም ነገር እንዲያደርጉ ምሳሌ ትቶላቸዋል።
5. ኢየሱስ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ምሳሌ የሚሆን አመለካከት ያሳየው እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በመጨረሻ መሥዋዕታዊ ሞት እንዲሞት ያደረገውን የሕይወት ጎዳና ተከትሏል። ሀብት የማካበት ወይም የተደላደለ ኑሮ የመኖር ፍላጎት አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ ኑሮው በጠቅላላ ያተኮረው በአገልግሎቱ ላይ ነበር። ደቀ መዛሙርቱን “መንግሥቱንና ጽድቁን አስቀድማችሁ መፈለጋችሁን አታቋርጡ” ሲል አጥብቆ መክሯቸዋል፤ እርሱ ራሱም እነዚህን ቃላት ሠርቶባቸዋል። (ማቴዎስ 6:33 አዓት) እንዲያውም አንድ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፣ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም።” (ማቴዎስ 8:20) ኢየሱስ የተከታዮቹን ገንዘብ ለመብላት ትምህርቶቹን እንደ መሣሪያ አድርጎ ሊጠቀምባቸው ይችል ነበር። አናጢ በመሆኑ ጥቂት ተጨማሪ ብር ለማግኘት አንድ ውብ የቤት ዕቃ ሠርቶ ለመሸጥ ሲል ለአገልግሎቱ ከሚያውለው ጊዜ ላይ የተወሰነ ጊዜ ዋጅቶ መጠቀም ይችል ነበር። ይሁን እንጂ የነበሩትን ሙያዎች ቁሳዊ ብልጽግና ለማግኘት አልተጠቀመባቸውም። ራሳችንን የወሰንን የአምላክ አገልጋዮች እንደ መሆናችን መጠን ለቁሳዊ ነገሮች ትክክለኛ አመለካከት በመያዝ ረገድ ኢየሱስን እየመሰልነው ነውን?—ማቴዎስ 6:24–34
6. የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት የምናደርግ ራሳችንን የወሰንን የአምላክ አገልጋዮች በመሆን ረገድ ኢየሱስን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ የራሱን ፍላጎቶች ለማሟላት አልጣረም፤ ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ለሚያቀርበው አገልግሎት ቅድሚያ ሰጥቷል። በሕዝብ ፊት ያከናውነው በነበረው የሦስት ዓመት ተኩል አገልግሎቱ ወቅት ያሳለፈው ሕይወት የራሱን ጥቅም መሥዋዕት ካደረገባቸው ጊዜያት አንዱ ነበር። ኢየሱስ በአንድ ወቅት ምግብ የሚቀምስበት ጊዜ እስኪያጣ ድረስ ቀኑን በሙሉ በሥራ ተጠምዶ ካሳለፈ በኋላ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም” የነበሩትን ሰዎች ለማስተማር ፈቃደኛ ሆኖ ነበር። (ማቴዎስ 9:36፤ ማርቆስ 6:31–34) ምንም እንኳ “መንገድ ከመሄድ ደክሞ” የነበረ ቢሆንም በሲካር ወደሚገኘው የያዕቆብ ጉድጓድ የመጣችውን ሳምራዊት ሴት ለማነጋገር ቅድሚያውን ወስዷል። (ዮሐንስ 4:6, 7, 13–15) ሁልጊዜ የሌሎችን ደህንነት ከእሱ ደህንነት ያስቀድም ነበር። (ዮሐንስ 11:5–15) አምላክንና ሌሎችን ለማገልገል በለጋስነት መንፈስ የራሳችንን ፍላጎቶች መሥዋዕት በማድረግ ኢየሱስን ልንመስለው እንችላለን። (ዮሐንስ 6:38) ከሚፈለግብን ነገር መካከል ጥቂቱን ብቻ ከማከናወን ይልቅ በእርግጥ አምላክን እንዴት ልናስደስተው እንደምንችል በማሰብ ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን እንኖራለን።
7. ሁልጊዜ ለይሖዋ ክብር በመስጠት ረገድ ኢየሱስን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ሰዎችን በመርዳት ትኩረትን ወደ እርሱ ለመሳብ አልሞከረም። የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ለአምላክ ወስኖ ነበር። ስለዚህ ለተከናወነው ማንኛውም ነገር የሚመጣው ክብር ሁሉ ለአባቱ ለይሖዋ እንዲሰጥ ያደርግ ነበር። አንድ አለቃ “ጥሩ” የሚለውን ቃል እንደ ማዕረግ ስም አድርጎ በመጠቀም “ጥሩ መምህር” ብሎ በጠራው ጊዜ ኢየሱስ “ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ጥሩ ማንም የለም” በማለት አርሞታል። (ሉቃስ 18:18, 19 አዓት ፤ ዮሐንስ 5:19, 30) ኢየሱስ እንዳደረገው ለእኛ ሳይሆን ለይሖዋ ክብር እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ ፈጣኖች ነንን?
8. (ሀ) ኢየሱስ ራሱን የወሰነ ሰው እንደመሆኑ መጠን ራሱን ከዓለም የለየው እንዴት ነው? (ለ) እኛ ልንመስለው የሚገባን እንዴት ነው?
8 ኢየሱስ ራሱን ለአምላክ በመወሰን በምድር ላይ ባሳለፈው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ ራሱን ለመለኮታዊ አገልግሎት ማዋሉን በግልጽ አሳይቷል። “ነውርና እድፍ እንደሌለው በግ” ራሱን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ራሱን ንጹሕ አድርጎ ጠብቋል። (1 ጴጥሮስ 1:19፤ ዕብራውያን 7:26) የሙሴን ሕግ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሙሉ ጠብቋል፤ በዚህም መንገድ ሕጉን ፈጽሟል። (ማቴዎስ 5:17፤ 2 ቆሮንቶስ 1:20) በሥነ ምግባር ደረጃ ካስተማረው ትምህርት ጋር በሚስማማ መንገድ ተመላልሷል። (ማቴዎስ 5:27, 28) መጥፎ ውስጣዊ ፍላጎቶች ነበሩት ብሎ በትክክል ሊወነጅለው የሚችል የለም። በእርግጥም ‘ዓመፅን ጠልቷል።’ (ዕብራውያን 1:9) የአምላክ ባሪያዎች እንደ መሆናችን መጠን አኗኗራችንና አልፎ ተርፎም ውስጣዊ ፍላጎቶቻችን በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሆነው እንዲገኙ በመጠበቅ ረገድ ኢየሱስን እንምሰለው።
የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች
9. ጳውሎስ የጠቀሰው ምን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ነው? ይህን ምሳሌ ልንመረምረው የሚገባን ለምንድን ነው?
9 ከኢየሱስ ምሳሌነት ተቃራኒ በሆነ መልኩ እስራኤላውያን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆኑናል። ሌላው ቀርቶ ይሖዋ ያለንን ሁሉ እናደርጋለን ብለው ከተናገሩ በኋላ እንኳ የእሱን ፈቃድ ሳያደርጉ ቀርተዋል። (ዳንኤል 9:11) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች በእስራኤላውያን ላይ ከደረሰው ሁኔታ ትምህርት እንዲቀስሙ አበረታቷቸዋል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ የጠቀሳቸውን አንዳንድ ክስተቶች እንመርምርና በጊዜያችን ያሉ ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ አገልጋዮች ምን እንቅፋቶችን ማስወገድ እንዳለባቸው እንመልከት።—1 ቆሮንቶስ 10:1–6, 11
10. (ሀ) እስራኤላውያን ‘ክፉ ነገር የተመኙት’ እንዴት ነበር? (ለ) እስራኤላውያን ለሁለተኛ ጊዜ ስለ ምግብ ባጉረመረሙ ጊዜ ይበልጥ ተጠያቂ የሆኑት ለምንድን ነው? ከዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌስ ምን ልንማር እንችላለን?
10 በመጀመሪያ ጳውሎስ “ክፉ ነገር . . . እንዳንመኝ” አስጠንቅቆናል። (1 ቆሮንቶስ 10:6) ይህ እስራኤላውያን ከመና በቀር የምንበላው የለንም ብለው ባጉረመረሙ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳችሁ ይሆናል። ይሖዋ ድርጭት ላከላቸው። ይህ ከመሆኑ ከአንድ ዓመት ገደማ አስቀድሞ ልክ እስራኤላውያን ራሳቸውን ለይሖዋ እንደወሰኑ ከማሳወቃቸው በፊት ተመሳሳይ የሆነ ነገር በሲና ምድረ በዳ ተከስቶ ነበር። (ዘጸአት 16:1–3, 12, 13) ይሁን እንጂ ሁኔታው ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት አልነበረም። ይሖዋ በመጀመሪያው ጊዜ ድርጭት ሲልክላቸው እስራኤላውያንን አጉረምርማችኋል በሚል ተጠያቂ አላደረጋቸውም። በዚህኛው ጊዜ ግን ሁኔታው የተለየ ነበር። “ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳያኝኩትም፣ የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት እጅግ መታ።” (ዘኁልቁ 11:4–6, 31–34) የተለወጠው ነገር ምን ነበር? ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሕዝብ እንደ መሆናቸው መጠን በዚህኛው ወቅት ላይ ላደረጉት ነገር ተጠያቂዎች ነበሩ። ምንም እንኳ ይሖዋ ያለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለው ቃል ቢገቡም ለይሖዋ ዝግጅቶች አድናቆት ማጣታቸው በይሖዋ ላይ እንዲያጉረመርሙ አድርጓቸዋል! በዛሬው ጊዜ ስላለው የይሖዋ ማዕድ ማጉረምረምም ተመሳሳይ ነው። አንዳንዶች ይሖዋ በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል የሚያዘጋጃቸውን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሳያደንቁ ቀርተዋል። (ማቴዎስ 24:45–47) ይሁን እንጂ ራሳችንን ስንወስን የገባነው ቃል ይሖዋ ያደረገልንን ነገር በአመስጋኝነት መንፈስ በአእምሯችን ውስጥ እንድናስቀምጥና ይሖዋ የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ እንድንቀበል ይጠይቅብናል።
11. (ሀ) እስራኤላውያን ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ በጣዖት አምልኮ የበከሉት እንዴት ነው? (ለ) በጣዖት አምልኮ ልንነካ የምንችለው እንዴት ነው?
11 በመቀጠል ጳውሎስ “ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ” ሲል አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 10:7) እዚህ ላይ ሐዋርያው የጠቀሰው እስራኤላውያን በሲና ተራራ ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረጉ ወዲያውኑ የተፈጸመውን የጥጃ አምልኮ እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ምናልባት ‘ራሴን የወሰንኩ የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆኔ መጠን ፈጽሞ በጣዖት አምልኮ አልሳተፍም’ ብለህ ትናገር ይሆናል። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ከነበሩበት ሁኔታ አንጻር ስናየው ይሖዋን ማምለካቸውን ባይተዉም አምላክ የሚጸየፈውን ነገር ይኸውም የጥጃ አምልኮ ማከናወን እንደ ጀመሩ ልብ በል። እንዲህ ዓይነቱ አምልኮ ምን ነገሮችን ያካተተ ነበር? ሕዝቡ በጥጃው ፊት መሥዋዕቶችን አቅርበዋል፤ ከዚያም “ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፣ ሊዘፍኑም ተነሡ።” (ዘጸአት 32:4–6) በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች ይሖዋን እናመልካልን ይሉ ይሆናል። ሆኖም ሕይወታቸው ያተኮረው በይሖዋ አምልኮ ላይ ሳይሆን በዚህ ዓለም የተለያዩ ነገሮች በመደሰት ላይ ሊሆን ይችላል፤ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አገልግሎት ደግሞ ለእነዚህ ነገሮች ከመደቡት ጊዜ ውጪ ባሉት አጋጣሚዎች ለማከናወን ይሞክሩ ይሆናል። እውነት ነው፣ ይህ ከወርቅ በተሠራ ጥጃ ፊት የመስገድን ያህል ከባድ ነገር ላይሆን ይችላል፤ በመሠረቱ ሲታይ ግን ብዙ ልዩነት ያለው አይደለም። አንድ ሰው የራሱን ፍላጎት እያመለከ ራሱን ለይሖዋ ሲወስን ከገባው ቃል ተስማምቶ ሊኖር ይችላል ማለት ዘበት ነው።—ፊልጵስዩስ 3:19
12. ከብዔልፌጎር ጋር በተያያዘ ሁኔታ በእስራኤላውያን ላይ ከደረሰው ነገር ራስን ስለ መካድ ምን እንማራለን?
12 ጳውሎስ ቀጥሎ በጠቀሰው የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ላይ አንድ የመዝናኛ ዓይነትም ተገልጿል። “ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ [“ሃያ ሦስት ሺ ሰዎች” የ1980 ትርጉም] እንደ ወደቁ አንሴስን።” (1 ቆሮንቶስ 10:8) እስራኤላውያን በሞዓብ ሴቶች በቀረበላቸው ሥነ ምግባር የጎደለው ደስታ ናውዘው በሰጢም ብዔልፌጎርን አመለኩ። (ዘኁልቁ 25:1–3, 9) የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችንን መካዳችን በሥነ ምግባር ንጹሕ እንድንሆን ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች መቀበልን ይጨምራል። (ማቴዎስ 5:27–30) በዚህ የሥነ ምግባር አቋም ባዘቀጠበት ዘመን ይሖዋ ጥሩና መጥፎ የሆነውን ለመወሰን ያለውን ሥልጣን በመቀበል ከሁሉም ዓይነት ሥነ ምግባር የጎደለው አድራጎት ራሳችንን መጠበቅ እንዳለብን ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል።—1 ቆሮንቶስ 6:9–11
13. የፊንሐስ ምሳሌ ራስን ለይሖዋ መወሰን ምንን እንደሚጨምር እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?
13 ምንም እንኳ ብዙዎች በሰጢም ተዘጋጅቶ በነበረው የዝሙት ወጥመድ ቢወድቁም አንዳንዶች በሕዝብ ደረጃ ራሳቸውን ለይሖዋ ሲወስኑ የገቡትን ቃል ጠብቀዋል። ከእነርሱ መካከል ፊንሐስ የነበረው ቅንዓት ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነው። ፊንሐስ አንድ እስራኤላዊ አለቃ አንዲት ምድያማዊት ሴት ይዞ ወደ ድንኳኑ ሲገባ ባየው ጊዜ ወዲያውኑ ጦር አንሥቶ ወጋቸው። ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቁጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም።” (ዘኁልቁ 25:11) ይሖዋን የሚቀናቀን ነገር እንዲኖር መፍቀድ አይገባም፤ ራስን መወሰን ማለት ይህ ነው። ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን የገባነው ቃል በልባችን ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ቦታ ሌላ ምንም ነገር እንዲወስደው መፍቀድ አንችልም። በተጨማሪም ለይሖዋ ያለን ቅንዓት ከባድ ነውርን እያየን ዝም እንድንል ሳይሆን ለሽማግሌዎች በመንገር የጉባኤውን ንጽሕና እንድንጠብቅ ይገፋፋናል።
14. (ሀ) እስራኤላውያን ይሖዋን የፈተኑት እንዴት ነው? (ለ) ራስን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ መወሰን ‘እንዳንዝል’ የሚረዳን እንዴት ነው?
14 ጳውሎስ “ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን” በማለት ሌላ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ጠቅሷል። (1 ቆሮንቶስ 10:9) ጳውሎስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው እስራኤላውያን ‘ከመንገዱ የተነሣ በደከሙ ጊዜ’ በአምላክ ላይ በማጉረምረም ሙሴን በተናገሩበት ወቅት ስለሆነው ሁኔታ ነው። (ዘኁልቁ 21:4) አንተም ይህንን ስሕተት ትሠራለህን? ራስህን ለይሖዋ ስትወስን አርማጌዶን ደፉ ላይ እንደደረሰ አድርገህ አስበህ ነበርን? የይሖዋ ትዕግሥት አንተ ከጠበቅከው ጊዜ በላይ ቆይቷልን? ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንነው ለተወሰነ ጊዜ ወይም እስከ አርማጌዶን ድረስ ብቻ እንዳልሆነ አስታውስ። ራሳችንን ስንወስን የገባነው ቃል ለዘላለም የሚቀጥል ነው። እንግዲያው “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።”—ገላትያ 6:9
15. (ሀ) እስራኤላውያን ያጉረመረሙት በማን ላይ ነበር? (ለ) ለይሖዋ ራሳችንን መወሰናችን ቲኦክራሲያዊ ሥልጣንን እንድናከብር የሚገፋፋን እንዴት ነው?
15 በመጨረሻም ጳውሎስ በተቀቡ የይሖዋ አገልጋዮች ላይ ‘እንዳናንጎራጉር’ አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 10:10) የከንዓንን ምድር እንዲሰልሉ ከተላኩት 12 ሰላዮች መካከል አሥሩ መጥፎ ሪፖርት ይዘው በተመለሱ ጊዜ እስራኤላውያን በኃይለ ቃል በመናገር በሙሴና በአሮን ላይ አጉረምርመዋል። እንዲያውም በሙሴ ምትክ አለቃ ሾመው ወደ ግብፅ ለመሄድ ተመካክረው ነበር። (ዘኁልቁ 14:1–4) በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት የሚሰጠንን አመራር እንቀበላለንን? በታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል አማካኝነት እየተዘጋጀ የሚቀርበውን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ማዕድ ስንመለከት ኢየሱስ ‘ምግቡን በጊዜው’ ለማከፋፈል ማንን እየተጠቀመ እንዳለ በግልጽ መረዳት እንችላለን። (ማቴዎስ 24:45) በሙሉ ነፍሳችን ራሳችንን ለይሖዋ በመወሰን የገባነው ቃል ለተሾሙ አገልጋዮቹ አክብሮት እንድናሳይ ይጠይቅብናል። በምሳሌያዊ አነጋገር እንደገና መልሶ ወደ ዓለም የሚመራቸውን አዲስ አለቃ ፍለጋ ፊታቸውን እንዳዞሩ አንዳንድ ዘመናዊ አጉረምራሚዎች አንሁን።
የምችለውን ሁሉ እያደረግሁ ነውን?
16. ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ አገልጋዮች ራሳቸውን ምን እያሉ መጠየቅ ይፈልጉ ይሆናል?
16 እስራኤላውያን ራሳቸውን ለይሖዋ ሲወስኑ የገቡት ቃል ገደብ የሌለው መሆኑን ቢያስታውሱ ኖሮ እንዲህ ዓይነት ከባድ ስህተቶችን ባልሠሩ ነበር። ከእነዚህ እምነት የለሽ እስራኤላውያን በተለየ መልኩ ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ መጨረሻ ድረስ፣ ራሱን ሲወስን ከገባው ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል። የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት” ባለመኖር በሙሉ ነፍሱ ለአምላክ ያደረ በመሆን ያሳየውን ምሳሌ እንኮርጃለን። (1 ጴጥሮስ 4:2፤ ከ2 ቆሮንቶስ 5:15 ጋር አወዳድር።) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያውቁ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:4 አዓት) ይህን ግብ በመያዝ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ መስበክ አለብን። (ማቴዎስ 24:14) ይህን አገልግሎት ለማከናወን ምን ያህል ጥረት እናደርጋለን? ራሳችንን ‘የምችለውን ሁሉ እያደረግሁ ነውን?’ ብለን መጠየቅ እንፈልግ ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) ሁኔታዎች ከሰው ወደ ሰው ይለያያሉ። ይሖዋ ደስ የሚሰኘው አንድ ሰው ‘እንዳለው መጠን እንጂ እንደሌለው መጠን’ ሲያገለግለው አይደለም። (2 ቆሮንቶስ 8:12፤ ሉቃስ 21:1–4) ማንም ሰው ሌላው ሰው ራሱን ለአምላክ ሲወስን የገባው ቃል ምን ያህል ከልብ የመነጨ እንደሆነ መገምገም የለበትም። እያንዳንዱ በግሉ ለይሖዋ ምን ያህል ያደረ እንደሆነ መመዘን ይኖርበታል። (ገላትያ 6:4) ለይሖዋ ያለን ፍቅር ‘ይሖዋን ላስደስተው የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን እንድንጠይቅ ሊገፋፋን ይገባል።
17. ለአምላክ በማደርና በአድናቆት መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? አብራራ።
17 ለይሖዋ ያለን አድናቆት እየጨመረ ሲመጣ ይበልጥ ለእሱ ያደርን እየሆን እንሄዳለን። በጃፓን ውስጥ የሚገኝ አንድ የ14 ዓመት ልጅ ራሱን ለይሖዋ ወሰነና ራሱን መወሰኑን በውኃ ጥምቀት አሳየ። ከጊዜ በኋላ ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተልና ሳይንቲስት ለመሆን ፈለገ። ስለ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት በፍጹም አስቦ አያውቅም ነበር፤ ሆኖም ራሱን የወሰነ አገልጋይ እንደ መሆኑ መጠን ይሖዋንና የሚታየውን ድርጅቱን መተው አልፈለገም። በሥራ መስክ ያወጣውን ግብ ዳር ለማድረስ ዩኒቨርሲቲ ገባ። በዚያም የዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች ሁኔታው ለሚሠሩበት ድርጅት ወይም ለምርምር ሥራቸው መላ ሕይወታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ሲያስገድዳቸው ተመለከተ። ‘እኔ እዚህ ምን እየሠራሁ ነው? የእነርሱን የአኗኗር መንገድ ለመከተልና ራሴን ለዓለማዊ ሥራ ሙሉ በሙሉ አሳልፌ ለመስጠት እችላለሁን? ራሴን ለይሖዋ ወስኜ የለም እንዴ?’ ሲል አሰበ። አድናቆቱን እንደ አዲስ በመገንባት የዘወትር አቅኚ ሆነ። ራሱን ሲወስን ስለ ገባው ቃል ያለው ግንዛቤ ጥልቀት እያገኘ ሄደና ወደ ተፈለገበት ቦታ ሄዶ ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እንዲያደርግ ገፋፋው። የአገልጋይነት ሥራ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተካፈለና እንደ ሚስዮናዊ ሆኖ በውጪ አገር እንዲያገለግል ተመደበ።
18. (ሀ) ራሳችንን ለይሖዋ የምንወስነው እስከምን ድረስ ነው? (ለ) ራሳችንን ለይሖዋ በመወሰናችን ምን በረከት እናጭዳለን?
18 ራስን መወሰን መላ ሕይወታችንን የሚያካትት ነገር ነው። ራሳችንን መካድና “ዕለት ዕለት” የኢየሱስን ግሩም ምሳሌ መከተል አለብን። (ሉቃስ 9:23) ራሳችንን ስለካድን ለተወሰነ ጊዜ ወጣ ብለን የምንመለስበት ፈቃድ እንዲሰጠን ይሖዋን አንጠይቀውም። ኑሯችን ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ካወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ነው። ሌላው ቀርቶ የግል ምርጫ ልናደርግባቸው በምንችልባቸው ሁኔታዎችም እንኳ ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ ኑሮ መኖራችንንና አለመኖራችንን ማጤናችን ጠቃሚ ነው። እርሱን ለማስደሰት የምንችለውን ሁሉ እያደረግን ዕለት ዕለት ስናገለግለው ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ስኬታማ ይሆናል፤ እንዲሁም በሙሉ ነፍሳችን ልናመልከው የሚገባው ይሖዋ በደስታ ስለሚቀበለን እንባረካለን።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን መወሰኑ ምን ነገር ማድረግንም ይጠይቅበት ነበር?
◻ በይሖዋ ላይ ከማጉረምረም መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው?
◻ የጣዖት አምልኮ ሕይወታችንን ቀስ በቀስ እንዳይቦረቡረው ማድረግ የምንችለው በምን መንገድ ነው?
◻ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ ‘እንዳንዝል’ ምን ነገር ማስታወሳችን ይረዳናል?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች ‘መልካም ነገር ለማድረግ አይታክቱም’