የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ጥቅምት 2020
ከጥቅምት 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 31–32
“ከጣዖት አምልኮ ሽሹ”
(ዘፀአት 32:1) በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይወርድ እንደቆየ አየ። በመሆኑም አሮንን ከበው እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት ስለማናውቅ በል ተነስተህ ከፊት ከፊታችን የሚሄድ አምላክ ሥራልን።”
“ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል”—ወደ ጉልምስና ግፉ
11 ከቅዱሳን ጽሑፎች ያገኘነውን ትምህርት በተግባር ማዋል በተለይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ከባድ ሊሆን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣቸው ብዙም ሳይቆይ ሕዝቡ ‘ሙሴን የተጣሉት’ ከመሆኑም ሌላ ‘ይሖዋን ተፈታተኑት።’ ይህን ያደረጉት ለምን ነበር? የሚጠጡት ውኃ በማጣታቸው ነበር። (ዘፀ. 17:1-4) እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር ቃል ኪዳን ከገቡ እንዲሁም ‘የይሖዋን ቃሎች ሁሉ’ ለመፈጸም ከተስማሙ ሁለት ወር እንኳ ሳይሞላቸው ጣዖት በማምለክ ሕጉን አፈረሱ። (ዘፀ. 24:3, 12-18፤ 32:1, 2, 7-9) ይህን ያደረጉት ሙሴ፣ መመሪያ ለመቀበል ወደ ኮሬብ ተራራ ወጥቶ ረዘም ላለ ጊዜ በመቆየቱ ፍርሃት አድሮባቸው ይሆን? አማሌቃውያን በድጋሚ ጥቃት ቢሰነዝሩባቸው ቀደም ሲል እጆቹን ወደ ላይ በማንሳት እንዲያሸንፉ የረዳቸው ሙሴ አብሯቸው ባለመሆኑ የሚረዳቸው እንደማይኖር ተሰምቷቸው ይሆን? (ዘፀ. 17:8-16) እንደዚያ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል፤ ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን እስራኤላውያን “ለመታዘዝ ፈቃደኞች አልሆኑም።” (ሥራ 7:39-41) ጳውሎስ፣ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በፈሩበት ወቅት እንዳልታዘዙ ከገለጸ በኋላ ክርስቲያኖች ይህንን ‘ያለመታዘዝ ምሳሌ ተከትለው ላለመውደቅ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ’ አሳስቧቸዋል።—ዕብ. 4:3, 11
(ዘፀአት 32:4-6) እሱም ወርቁን ከእነሱ ወስዶ በቅርጽ ማውጫ ቅርጽ አወጣለት፤ የጥጃ ሐውልትም አድርጎ ሠራው። እነሱም “እስራኤል ሆይ፣ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው” ይሉ ጀመር። 5 አሮንም ይህን ሲያይ በምስሉ ፊት መሠዊያ ሠራ። ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ “ነገ ለይሖዋ የሚከበር በዓል አለ” ሲል ተናገረ። 6 በመሆኑም በማግስቱ በማለዳ ተነስተው የሚቃጠል መባና የኅብረት መሥዋዕት ያቀርቡ ጀመር። ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ። ከዚያም ሊጨፍሩ ተነሱ።
አምላክን በመታዘዝ በመሐላ ከገባው ቃል ተጠቃሚ ሁኑ
12 ይሖዋ ወዲያውኑ ለአምልኮ የሚያገለግል ድንኳንና ኃጢአተኛ የሆኑት የሰው ልጆች ወደ እሱ መቅረብ የሚችሉበትን የክህነት ሥርዓት በማዘጋጀት ከሕጉ ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ጀመረ። በአንጻሩ ግን እስራኤላውያን ለአምላክ የገቡትን ቃል ወዲያው በመርሳት ‘የእስራኤልን ቅዱስ አስቈጡት።’ (መዝ 78:41) ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ተጨማሪ መመሪያዎችን በመቀበሉ ሥራ ተጠምዶ እያለ እስራኤላውያን ሙሴ እንደተዋቸው በማሰብ ትዕግሥታቸው የተሟጠጠ ከመሆኑም በላይ በአምላክ ላይ እምነት አጡ። በመሆኑም የወርቅ ጥጃ ሠርተው ለሕዝቡ “እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ያወጡህ አማልክት እነዚህ ናቸው” አሏቸው። (ዘፀ 32:1, 4) ከዚያም ‘የእግዚአብሔር በዓል’ ብለው የጠሩትን ክብረ በዓል አዘጋጅተው በሰው እጅ ለተሠራው ምስል ሰገዱ፤ እንዲሁም መሥዋዕት አቀረቡ። ይሖዋ ይህን ሲመለከት ሙሴን “ካዘዝኋቸው ፈቀቅ ለማለት ፈጣኖች ሆኑ” አለው። (ዘፀ 32:5, 6, 8) የሚያሳዝነው ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስራኤላውያን ለአምላክ የገቧቸውን መሐላዎች በተደጋጋሚ አፍርሰዋል።—ዘኍ 30:2
(ዘፀአት 32:9, 10) ይሖዋም በመቀጠል ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሕዝብ ግትር መሆኑን ተመልክቻለሁ። 10 እንግዲህ አሁን ቁጣዬ እንዲነድባቸውና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ አንተን በእነሱ ምትክ ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ።”
“ከይሖዋ ጎን የሚቆም ማን ነው?”
14 እስራኤላውያን ጣዖት አምልኮ ይሖዋን የሚያሳዝን ከባድ ኃጢአት እንደሆነ ያውቁ ነበር። (ዘፀ. 20:3-5) ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የወርቅ ጥጃ ማምለክ ጀመሩ! እስራኤላውያን እንዲህ ባለ ግልጽ የሆነ መንገድ የይሖዋን ትእዛዝ ቢጥሱም አሁንም ከይሖዋ ጎን እንደሆኑ አድርገው በማሰብ ራሳቸውን አታለው ነበር። እንዲያውም አሮን የጥጃ አምልኳቸውን “ለይሖዋ የሚከበር በዓል” በማለት ጠርቶታል! ይሖዋ ምን ተሰማው? ሕዝቡ የፈጸመውን ድርጊት እንደ ክህደት ቆጥሮታል። እስራኤላውያን “ምግባረ ብልሹ [እንደሆኑ]” እንዲሁም ‘እንዲሄዱበት ካዘዛቸው መንገድ ዞር እንዳሉ’ ለሙሴ ነግሮታል። ይሖዋ ‘ቁጣው ከመንደዱ’ የተነሳ አዲስ የተቋቋመውን የእስራኤልን ብሔር ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አስቦ ነበር።—ዘፀ. 32:5-10
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 31:17) በእኔና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ያለ ዘላለማዊ ምልክት ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ በማጠናቀቅ ሥራውን ያቆመውና ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነው።’”
ለሥራም ሆነ ለእረፍት “ጊዜ አለው”
4 ይሖዋ እና ኢየሱስ ተግቶ በመሥራት ረገድ የተዉት ምሳሌ እረፍት ማድረግ እንደማያስፈልገን የሚያሳይ ነው? በፍጹም። ይሖዋ ፈጽሞ ስለማይደክመው እረፍት ማድረግ አያስፈልገውም። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ሰማያትንና ምድርን ከፈጠረ በኋላ ‘ሥራውን እንዳቆመና እንዳረፈ’ ይናገራል። (ዘፀ. 31:17) ሆኖም ይህ ሐሳብ ይሖዋ ሥራውን ቆም አድርጎ፣ ያከናወነውን ነገር በመመልከት በሥራው እንደተደሰተ የሚጠቁም ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስም ቢሆን ምድር ላይ ሳለ ተግቶ ቢሠራም እረፍት ለማድረግና ከወዳጆቹ ጋር ለመመገብ የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ይጥር ነበር።—ማቴ. 14:13፤ ሉቃስ 7:34
(ዘፀአት 32:32, 33) ሆኖም አሁን ፈቃድህ ከሆነ ኃጢአታቸውን ይቅር በል፤ ካልሆነ ግን እባክህ እኔን ከጻፍከው መጽሐፍህ ላይ ደምስሰኝ።” 33 ይሁንና ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በእኔ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሁሉ ከመጽሐፌ ላይ እደመስሰዋለሁ።
w87 9/1 29
የአንባቢያን ጥያቄዎች
አንድ ሰው በአምላክ ዘንድ መታወሱና የእሱን ሞገስ ማግኘቱ (ስሙ “በሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ መጻፉ) ዕድሉ አስቀድሞ እንደተወሰነ ወይም ስሙ በማይሻር መንገድ እንደተጻፈ አያመለክትም፤ በሌላ አባባል የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝ ዋስትና አይሰጠውም። ሙሴ እስራኤላውያንን በተመለከተ ለይሖዋ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፦ “አሁን ፈቃድህ ከሆነ ኃጢአታቸውን ይቅር በል፤ ካልሆነ ግን እባክህ እኔን ከጻፍከው መጽሐፍህ ላይ ደምስሰኝ።” አምላክም “በእኔ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሁሉ ከመጽሐፌ ላይ እደመስሰዋለሁ” በማለት መልሶለታል። (ዘፀአት 32:32, 33) በእርግጥም አንድ ሰው የአምላክን ሞገስ አግኝቶ ስሙ በአምላክ “መጽሐፍ” ላይ ከተጻፈም በኋላ ታዛዥነት ሊያጓድል ወይም እምነቱን ሊተው ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመ አምላክ “ስሙን ከሕይወት መጽሐፍ” ይደመስሰዋል።—ራእይ 3:5
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 32:15-35) ከዚያም ሙሴ ሁለቱን የምሥክር ጽላቶች በእጁ እንደያዘ ተመልሶ ከተራራው ወረደ። ጽላቶቹም በሁለቱም በኩል ተቀርጾባቸው ነበር፤ በፊትም ሆነ በጀርባ ተጽፎባቸው ነበር። 16 ጽላቶቹ የአምላክ ሥራ ነበሩ፤ በጽላቶቹ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍም የአምላክ ጽሑፍ ነበር። 17 ኢያሱም ሕዝቡ ይጮኽ ስለነበር ጫጫታውን ሲሰማ ሙሴን “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ሁካታ ይሰማል” አለው። 18 ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “ይህ ድምፅ የድል መዝሙር አይደለም፤ ይህ ድምፅ በሽንፈት ምክንያት የሚሰማ የለቅሶ ድምፅም አይደለም፤ ይህ የምሰማው ድምፅ የተለየ መዝሙር ድምፅ ነው።” 19 ሙሴም ወደ ሰፈሩ ሲቃረብ ጥጃውንና ጭፈራውን አየ፤ በዚህ ጊዜ ቁጣው ነደደ። ጽላቶቹንም ከእጁ ወርውሮ በተራራው ግርጌ ሰባበራቸው። 20 የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ሰባብሮም ዱቄት አደረገው፤ ከዚያም በውኃው ላይ በመበተን እስራኤላውያን እንዲጠጡት አደረገ። 21 ሙሴም አሮንን “ይህን ከባድ ኃጢአት ያመጣህበት ይህ ሕዝብ ምን ቢያደርግህ ነው?” አለው። 22 በዚህ ጊዜ አሮን እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ አትቆጣ። መቼም ይህ ሕዝብ ወደ ክፋት ያዘነበለ እንደሆነ አንተ ራስህ በሚገባ ታውቃለህ። 23 ስለዚህ ‘ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት ስለማናውቅ ከፊት ከፊታችን የሚሄድ አምላክ ሥራልን’ አሉኝ። 24 በመሆኑም ‘ወርቅ ያለው ሁሉ አውልቆ ይስጠኝ’ አልኳቸው። ከዚያም ወርቁን እሳቱ ውስጥ ጣልኩት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።” 25 በተቃዋሚዎቻቸው ፊት መሳለቂያ እንዲሆኑ አሮን ሕዝቡን መረን ስለለቀቃቸው ሙሴ ሕዝቡ መረን እንደተለቀቀ አስተዋለ። 26 ከዚያም ሙሴ በሰፈሩ መግቢያ ላይ ቆሞ “ከይሖዋ ጎን የሚቆም ማን ነው? ወደ እኔ ይምጣ!” አለ። በዚህ ጊዜ ሌዋውያን በሙሉ በዙሪያው ተሰበሰቡ። 27 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እያንዳንዳችሁ ሰይፋችሁን ታጠቁ፤ ከአንዱ በር ወደ ሌላው በር በመሄድና በሰፈሩ ውስጥ በማለፍ እያንዳንዱ ሰው ወንድሙን፣ ጎረቤቱንና የቅርብ ጓደኛውን ይግደል።’” 28 ሌዋውያኑም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ። በመሆኑም በዚያ ዕለት 3,000 ገደማ የሚሆኑ ወንዶች ተገደሉ። 29 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እያንዳንዳችሁ በገዛ ልጃችሁና በገዛ ወንድማችሁ ላይ ስለተነሳችሁ ዛሬ ራሳችሁን ለይሖዋ ለዩ፤ እሱም ዛሬ በረከትን ያፈስላችኋል።” 30 በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “ከባድ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ እንግዲህ አሁን ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ አንድ ነገር ማድረግ እችል እንደሆነ ለማየት ወደ ይሖዋ እወጣለሁ።” 31 በመሆኑም ሙሴ ወደ ይሖዋ ተመልሶ እንዲህ አለ፦ “ይህ ሕዝብ የፈጸመው ኃጢአት ምንኛ ከባድ ነው! የወርቅ አምላክ ሠርተዋል። 32 ሆኖም አሁን ፈቃድህ ከሆነ ኃጢአታቸውን ይቅር በል፤ ካልሆነ ግን እባክህ እኔን ከጻፍከው መጽሐፍህ ላይ ደምስሰኝ።” 33 ይሁንና ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በእኔ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሁሉ ከመጽሐፌ ላይ እደመስሰዋለሁ። 34 በል አሁን ሄደህ ሕዝቡን ወደነገርኩህ ስፍራ እየመራህ ውሰዳቸው። እነሆ መልአኬ ከፊት ከፊትህ ይሄዳል፤ ሕዝቡን በምመረምርበትም ቀን ስለሠሩት ኃጢአት ቅጣት አመጣባቸዋለሁ።” 35 ከዚያም ይሖዋ፣ በሠሩት ጥጃ ይኸውም አሮን በሠራላቸው ጥጃ ምክንያት ሕዝቡን በመቅሰፍት መታ።
ከጥቅምት 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 33–34
“የይሖዋ ማራኪ ባሕርያት”
(ዘፀአት 34:5) ከዚያም ይሖዋ በደመና ውስጥ ወርዶ በዚያ ከእሱ ጋር ሆነ፤ ይሖዋ የተባለውንም ስሙን አወጀ።
it-2 466-467
ስም
ፍጥረት የአምላክን መኖር ቢመሠክርም ስሙን ግን አይገልጥም። (መዝ 19:1፤ ሮም 1:20) የአምላክን ስም ማወቅ መጠሪያውን ከማወቅ ያለፈ ነገርን ያካትታል። (2ዜና 6:33) ማንነቱን ማለትም በአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጸውን ዓላማውን፣ የሚያደርጋቸውን ነገሮች እንዲሁም ባሕርያቱን ማወቅን ይጨምራል። (ከ1ነገ 8:41-43፤ 9:3, 7፤ ነህ 9:10 ጋር አወዳድር።) የሙሴ ሁኔታ ይህን ያሳያል፤ ይሖዋ ሙሴን ‘በስም ያውቀው’ ማለትም በደንብ ያውቀው ነበር። (ዘፀ 33:12) ሙሴ የአምላክን ክብር የማየትና ‘ይሖዋ የተባለው ስሙ ሲታወጅ’ የመስማት መብት አግኝቶ ነበር። (ዘፀ 34:5) አምላክ ስሙን ያወጀው ይሖዋ የሚለውን መጠሪያ በመደጋገም ሳይሆን ስለ ባሕርያቱና ስለሚያከናውናቸው ነገሮች በመናገር ነው። “ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ፣ ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ፣ ስህተትን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል፣ ጥፋተኛውን ግን በምንም ዓይነት ሳይቀጣ የማያልፍ እንዲሁም አባቶች ለሠሩት ስህተት በልጆች፣ በልጅ ልጆች፣ በሦስተኛና በአራተኛ ትውልድ ላይ ቅጣትን የሚያመጣ።” (ዘፀ 34:6, 7) በተመሳሳይም ሙሴ በመዝሙሩ ውስጥ “የይሖዋን ስም አውጃለሁና” ብሎ ነበር፤ ይህ መዝሙር አምላክ ለእስራኤላውያን ያደረገላቸውን ነገርና ባሕርያቱን የሚገልጽ ነው።—ዘዳ 32:3-44
(ዘፀአት 34:6) ይሖዋም በፊቱ እያለፈ እንዲህ ሲል አወጀ፦ “ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ፣
ይሖዋ ባሕርያቱን ሲገልጽ
ይሖዋ ስለ ራሱ የገለጠው የመጀመሪያው ነገር “መሐሪና ቸር የሆነ አምላክ” መሆኑን ነው። (ቁጥር 6 NW) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንደገለጹት “መሐሪ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አምላክ “አባት ለልጆቹ የሚያሳየው ዓይነት ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ” እንዳለው የሚጠቁም ነው። “ቸር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ደግሞ “አንድ ሰው ችግር ላይ የወደቀ ግለሰብን ለመርዳት ሲል ከልቡ ተነሳስቶ የሚወስደውን እርምጃ” ከሚገልጽ ግስ ጋር ተዛማጅነት አለው። ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ይሖዋ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በሚይዙበት መንገድ እሱም አገልጋዮቹን እንደሚንከባከባቸው እንድናውቅ ይፈልጋል። ወላጆች ለልጆቻቸው ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸውና ልባዊ አሳቢነት እንደሚያሳዩአቸው ሁሉ ይሖዋም አምላኪዎቹን በዚህ መንገድ ይንከባከባቸዋል።—መዝሙር 103:8, 13
በመቀጠልም ይሖዋ “ለቍጣ የዘገየ” መሆኑን ገልጿል። (ቁጥር 6) በምድር ባሉ አገልጋዮቹ ላይ በቀላሉ አይቆጣም። ይልቁንም ከኃጢአት ጎዳናቸው እንዲመለሱ ጊዜ በመስጠት ድክመታቸውን ይታገሣል።—2 ጴጥሮስ 3:9
አምላክ “ፍቅራዊ ደግነቱና እውነቱ እጅግ የበዛ” መሆኑንም ገልጿል። (ቁጥር 6 NW) ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር፣ በይሖዋና በሕዝቦቹ መካከል የጸና እንዲሁም ምንጊዜም የማይለወጥ ትስስር እንዲፈጠር የሚያደርግ ግሩም ባሕርይ ነው። (ዘዳግም 7:9) ከዚህም በላይ ይሖዋ የእውነት ምንጭ ነው። ይሖዋ አያታልልም፤ በሌሎችም አይታለልም። “የእውነት አምላክ” ስለሆነ ስለወደፊቱ ጊዜ የሰጣቸውን ተስፋዎች ጨምሮ የተናገራቸውን ነገሮች ሁሉ እንደሚፈጽም ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን።—መዝሙር 31:5
(ዘፀአት 34:7) ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ፣ ስህተትን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል፣ ጥፋተኛውን ግን በምንም ዓይነት ሳይቀጣ የማያልፍ እንዲሁም አባቶች ለሠሩት ስህተት በልጆች፣ በልጅ ልጆች፣ በሦስተኛና በአራተኛ ትውልድ ላይ ቅጣትን የሚያመጣ።”
ይሖዋ ባሕርያቱን ሲገልጽ
ይሖዋ ስለ እሱ እንድናውቀው የሚፈልገው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሌላው ሐቅ ደግሞ “በደልን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል” አምላክ መሆኑን ነው። (ቁጥር 7 NW) ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ‘ይቅር ለማለት’ ዝግጁ የሆነ አምላክ ነው። (መዝሙር 86:5) ይህ ሲባል ግን ክፋትን በቸልታ ያልፋል ማለት አይደለም። ይሖዋ ‘በደለኛውን ሳይቀጣ ዝም ብሎ እንደማይተው’ ገልጿል። (ቁጥር 7) ቅዱስና ፍትሐዊ የሆነው አምላክ ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎችን ሳይቀጣ አያልፍም። ይዋል ይደር እንጂ የተከተሉት የኃጢአት ጎዳና የሚያስከትለውን መዘዝ ማጨዳቸው አይቀርም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 33:11) አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር እንደሚነጋገር ይሖዋ ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር። ሙሴ ወደ ሰፈሩ በሚመለስበት ጊዜ አገልጋዩና ረዳቱ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር።
(ዘፀአት 33:20) ሆኖም “ማንም ሰው አይቶኝ በሕይወት መኖር ስለማይችል ፊቴን ማየት አትችልም” አለው።
የዘፀአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
33:11, 20—አምላክ ከሙሴ ጋር “ፊት ለፊት” ይነጋገር የነበረው እንዴት ነው? ይህ አገላለጽ አፍ ለአፍ መነጋገርን የሚያመለክት ነው። ሙሴ ከአምላክ ወኪል ጋር ይነጋገር የነበረ ከመሆኑም በላይ በእርሱ በኩል ከይሖዋ የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብሏል። ሆኖም ‘ማንም አምላክን አይቶ መኖር ስለማይችል’ ሙሴ ይሖዋን አልተመለከተውም። እንዲያውም ይሖዋ ሙሴን በቀጥታ አላነጋገረውም። ገላትያ 3:19 ሕጉ “የመጣው በመላእክት በኩል፣ በአንድ መካከለኛ እጅ” እንደሆነ ይናገራል።
(ዘፀአት 34:23, 24) “የአንተ የሆነ ሰው ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ የእስራኤል አምላክ በሆነው በእውነተኛው ጌታ በይሖዋ ፊት ይቅረብ። 24 ብሔራትን ከፊትህ አስወጣለሁና፤ ክልልህንም ሰፊ አደርገዋለሁ፤ የአምላክህን የይሖዋን ፊት ለማየት በዓመት ሦስቴ በምትወጣበት ጊዜ ማንም ምድርህን አይመኝም።
ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ ስጡ!
በዓመት ሦስት ጊዜ እያንዳንዱ እስራኤላዊ ወንድና በአገሩ የሚኖር ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠ ወንድ ሁሉ በይሖዋ ፊት እንዲታይ ታዝዞ ነበር። መላው የቤተሰቡ አባላት ከዚህ ዝግጅት ጥቅም እንደሚያገኝ ስለተገነዘቡ ብዙዎቹ የቤት ራሶች ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ይሄዱ ነበር። ይሁን እንጂ ቤተሰቡ ርቆ በሚሄድበት ወቅት ቤታቸውንና እርሻቸውን ከጠላት የሚጠብቅላቸው ማን ነው? ይሖዋ “በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት በዓመት ሦስት ጊዜ ስትወጣ ማንም ምድርህን አይመኝም” በማለት ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘጸአት 34:24) እስራኤላውያን መንፈሳዊ ነገሮችን ካስቀደሙ ቁሳዊ ነገሮች እንደማይጎድልባቸው አምነው ለመቀበል እምነት ጠይቆባቸው ነበር። ታዲያ ይሖዋ እንዳለው አድርጓል? አዎን፣ አድርጓል!
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 33:1-16) በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብፅ መርተህ ካወጣኸው ሕዝብ ጋር ከዚህ ተነስተህ ሂድ። ‘ለዘርህ እሰጠዋለሁ’ በማለት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ወደማልኩላቸውም ምድር ተጓዝ። 2 እኔም ከአንተ አስቀድሜ መልአክ በመላክ ከነአናውያንን፣ አሞራውያንን፣ ሂታውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ሂዋውያንንና ኢያቡሳውያንን አስወጣለሁ። 3 ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር ሂዱ። ሆኖም እናንተ ግትር ሕዝብ ስለሆናችሁ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋችሁ በመካከላችሁ ሆኜ አብሬያችሁ አልሄድም።” 4 ሕዝቡም ይህን ኃይለኛ ንግግር ሲሰሙ በሐዘን ተዋጡ፤ ከመካከላቸውም ማንም ጌጡን አላደረገም። 5 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እናንተ ግትር ሕዝብ ናችሁ። ለአንድ አፍታ በመካከላችሁ አልፌ ላጠፋችሁ እችል ነበር። በእናንተ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እስክወስን ድረስ ጌጣጌጣችሁን አውልቁ።’” 6 ስለዚህ እስራኤላውያን ከኮሬብ ተራራ አንስቶ ጌጣጌጣቸውን ማድረግ ተዉ። 7 ሙሴም የራሱን ድንኳን ወስዶ ከሰፈሩ ውጭ ማለትም ከሰፈሩ ትንሽ ራቅ አድርጎ ተከለው፤ ድንኳኑንም የመገናኛ ድንኳን ብሎ ጠራው። ይሖዋን የሚጠይቅ ማንኛውም ሰው ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው የመገናኛ ድንኳን ይሄድ ነበር። 8 ሙሴ ወደ ድንኳኑ ሲሄድ ሕዝቡ በሙሉ ተነስተው በየድንኳናቸው መግቢያ ላይ በመቆም ሙሴ ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ትክ ብለው ይመለከቱት ነበር። 9 ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ አምላክ ከሙሴ ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ የደመናው ዓምድ ወርዶ በድንኳኑ መግቢያ ላይ ይቆማል። 10 ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ መግቢያ ላይ ቆሞ ሲመለከት እያንዳንዳቸው ተነስተው በየድንኳናቸው መግቢያ ላይ ይሰግዱ ነበር። 11 አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር እንደሚነጋገር ይሖዋ ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር። ሙሴ ወደ ሰፈሩ በሚመለስበት ጊዜ አገልጋዩና ረዳቱ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር። 12 ሙሴም ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ ‘ይህን ሕዝብ ምራ’ እያልከኝ ነው፤ ሆኖም ከእኔ ጋር ማንን እንደምትልክ አላሳወቅከኝም። ከዚህም በላይ ‘በስም አውቄሃለሁ፤ ደግሞም በፊቴ ሞገስ አግኝተሃል’ ብለኸኝ ነበር። 13 እባክህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እንዳውቅህና በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንድኖር መንገድህን አሳውቀኝ። እንዲሁም ይህ ብሔር ሕዝብህ እንደሆነ አስብ።” 14 በመሆኑም እሱ “እኔ ራሴ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ እረፍትም እሰጥሃለሁ” አለው። 15 ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “አንተ ራስህ ከእኛ ጋር የማትሄድ ከሆነ ይህን ቦታ ለቅቀን እንድንሄድ አታድርገን። 16 ታዲያ እኔም ሆንኩ ሕዝብህ በፊትህ ሞገስ እንዳገኘን የሚታወቀው እንዴት ነው? እኔም ሆንኩ ሕዝብህ በምድር ላይ ካሉ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየን እንድንሆን ስትል አብረኸን በመሄድህ አይደለም?”
ከጥቅምት 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 35–36
“የይሖዋን ሥራ ለመሥራት ብቁ መሆን”
(ዘፀአት 35:25, 26) ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሴቶችም ሁሉ በእጃቸው ይፈትሉ ነበር፤ እነሱም የሚከተሉትን ነገሮች ፈትለው አመጡ፦ ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍ፣ ደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም ጥሩ በፍታ። 26 ጥሩ ችሎታ ያላቸው ልባቸው ያነሳሳቸው ሴቶች ሁሉ የፍየል ፀጉሩን ይፈትሉ ነበር።
ይሖዋ በፈቃደኝነት የሚሰጡትን አብዝቶ ይባርካል
ይሖዋን ይበልጥ ያስደሰተው ግን ሕዝቡ ያመጡት ቁሳዊ ነገር ሳይሆን በዚህ መንገድ እውነተኛውን አምልኮ የደገፉት ሰዎች ያሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ ነበር። ሕዝቡ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን እንዲሰጡም ልባቸው አነሳስቷቸው ነበር። ዘገባው “ጥበበኞች የሆኑ ሴቶች ሁሉ በእጃቸው ፈተሉ” ይላል። “ፈቃደኛ የነበሩና ጥበቡ ያላቸው ሴቶች ሁሉ የፍየል ጠጕር ፈተሉ።” ከዚህም ሌላ ይሖዋ፣ ባስልኤል “በጥበብ፣ በችሎታና በዕውቀት፣ በማናቸውም ዐይነት ሙያ” የተካነ እንዲሆን አድርጎ ነበር። እንዲያውም ባስልኤልና ኤልያብ የታዘዙትን ነገር ሁሉ ለመሥራት የሚያስፈልጋቸውን ችሎታ የሰጣቸው አምላክ ነው።—ዘፀ. 35:25, 26, 30-35
(ዘፀአት 35:30-35) ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ “እንደምታዩት ይሖዋ ከይሁዳ ነገድ የሆነው የሁር ልጅ ዖሪ የወለደውን ባስልኤልን መርጦታል። 31 ደግሞም በማንኛውም ዓይነት የእጅ ሙያ ማስተዋል፣ ጥበብና እውቀት በመስጠት በአምላክ መንፈስ ሞልቶታል። 32 ይኸውም የተለያዩ ንድፎችን እንዲያወጣ እንዲሁም በወርቅ፣ በብርና በመዳብ የተለያዩ ነገሮችን እንዲሠራ፣ 33 ፈርጥ የሚሆኑትን ድንጋዮች እንዲቀርጽና በቦታቸው እንዲያስቀምጥ እንዲሁም ድንቅ የሆኑ ልዩ ልዩ የእንጨት ቁሳቁሶችን እንዲሠራ ነው። 34 አምላክም ለእሱና ከዳን ነገድ ለሆነው ለአሂሳማክ ልጅ ለኤልያብ ሌሎችን የማስተማር ችሎታ ሰጥቷቸዋል። 35 የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣ የጥልፍ ባለሙያ እንዲሁም በሰማያዊ ክር፣ በሐምራዊ ሱፍ፣ በደማቅ ቀይ ማግና በጥሩ በፍታ የሚሸምን የጥበብ ባለሙያ ብሎም የሽመና ባለሙያ የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች በሙሉ እንዲሠሩ ጥሩ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። እነዚህ ሰዎች ሁሉንም ዓይነት ሥራዎች የሚሠሩና ሁሉንም ዓይነት ንድፎች የሚያወጡ ነበሩ።
በአምላክ መንፈስ የተመሩ በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ አገልጋዮች
6 በሙሴ ዘመን ይኖር የነበረው ባስልኤል በሕይወቱ ያጋጠመው ነገር የአምላክ መንፈስ ስለሚሠራበት መንገድ ተጨማሪ ግንዛቤ ይሰጠናል። (ዘፀአት 35:30-35ን አንብብ።) ባስልኤል ለማደሪያው ድንኳን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ግንባር ቀደም ሆኖ እንዲሠራ ተሹሞ ነበር። ለመሆኑ ይህን ከባድ ኃላፊነት ከመቀበሉ በፊት እንዲህ ዓይነት ሥራ ለማከናወን የሚያስችል የእጅ ጥበብ ሙያ ነበረው? ይኖረው ይሆናል፤ ይሁንና ከዚህ በፊት የተሰማራበት የሥራ መስክ ለግብፃውያን ጡብ ከመሥራት የዘለለ እንደማይሆን መገመት ይቻላል። (ዘፀ. 1:13, 14) ታዲያ ባስልኤል ይህን ውስብስብ ሥራ መወጣት የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ‘ጥበብ፣ ችሎታና እውቀት እንዲሁም ማናቸውም ዓይነት ሙያ’ እንዲኖረው መንፈሱን ሞላበት፤ ይህንንም ያደረገው “የጥበብ ሥራ እንዲሠራ” እንዲሁም “ማንኛውንም ዐይነት የጥበብ ሙያ እንዲያከናውን ነው።” ባስልኤል በተፈጥሮው ምንም ዓይነት ተሰጥኦ ይኑረው መንፈስ ቅዱስ ይህን ችሎታውን ይበልጥ አሳድጎለታል። የኤልያብ ሁኔታም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ባስልኤልና ኤልያብ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ብቻ ሳይወሰኑ ሌሎችንም ማስተማራቸው በሙያው በደንብ የተካኑ እንዲሆኑ መንፈስ ቅዱስ ረድቷቸው እንደነበር ይጠቁማል። አዎን፣ አምላክ የማስተማር ችሎታ ሰጥቷቸው ነበር።
(ዘፀአት 36:1, 2) “ባስልኤል ከኤልያብና ጥሩ ችሎታ ካላቸው ወንዶች ሁሉ ጋር ይሠራል፤ እነዚህ ወንዶች ቅዱስ ከሆነው አገልግሎት ጋር የተያያዘው ሥራ በሙሉ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት እንዴት እንደሚከናወን ማወቅ ይችሉ ዘንድ ይሖዋ ጥበብና ማስተዋል የሰጣቸው ናቸው።” 2 ከዚያም ሙሴ ባስልኤልንና ኤልያብን እንዲሁም ይሖዋ በልባቸው ጥበብን ያኖረላቸውን ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ወንዶች ሁሉ ይኸውም ሥራውን ለመሥራት በፈቃደኝነት ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ልባቸው ያነሳሳቸውን ሁሉ ጠራ።
በአምላክ መንፈስ የተመሩ በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ አገልጋዮች
7 ባስልኤልና ኤልያብ በአምላክ መንፈስ ይመሩ እንደነበር የሚያሳየው ሌላው ማስረጃ የሥራቸው ውጤት በጣም ጠንካራ መሆኑ ነው። የሠሯቸው ነገሮች 500 ለሚያህሉ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። (2 ዜና 1:2-6) ዘመናዊ የሆኑ ድርጅቶች በምርታቸው ላይ ስማቸውን ወይም የንግድ ምልክታቸውን እንደሚያኖሩት ባስልኤልና ኤልያብ ይህን የማድረግ ፍላጎት አልነበራቸውም። በሠሩት ሥራ እንዲወደስ ያደረጉት ይሖዋን ነው።—ዘፀ. 36:1, 2
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 35:1-3) በኋላም ሙሴ የእስራኤልን ማኅበረሰብ ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ እንድትፈጽሟቸው ያዘዛችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፦ 2 ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእናንተ የተቀደሰ ይሆናል፤ ለይሖዋም ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ይሆናል። በዚህ ቀን ሥራ የሚሠራ ማንም ሰው ይገደላል። 3 በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በሰንበት ቀን እሳት አታቀጣጥሉ።”
የይሖዋን መንገድ መማር
14 ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ስጡ። እስራኤላውያን ሥጋዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት በመሯሯጥ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ትኩረት መስጠት እንዲሳናቸው መፍቀድ አልነበረባቸውም። እስራኤላውያን ሕይወታቸው ተራ ጉዳዮችን በማሳደድ ላይ ብቻ ማተኮር አልነበረበትም። ይሖዋ በሳምንቱ ውስጥ የተወሰነ ጊዜ የተቀደሰ እንዲሆንና ለእውነተኛው አምላክ ከሚቀርበው አምልኮ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ብቻ እንዲውል መድቦ ነበር። (ዘፀአት 35:1-3፤ ዘኍልቊ 15:32-36) በየዓመቱ ለሚካሄዱት ቅዱስ ስብሰባዎች ተጨማሪ ጊዜ እንዲመድቡ ተነግሯቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 23:4-44) እነዚህ ስብሰባዎች የይሖዋን ታላላቅ ሥራዎች ለማውሳት፣ መንገዱን በተመለከተ ማሳሰቢያ ለማግኘትና ለጥሩነቱ በሙሉ ምስጋና ለማቅረብ አጋጣሚ ይሰጣሉ። እስራኤላውያን ለይሖዋ ያደሩ መሆናቸውን ሲያሳዩ ለእርሱ ያላቸው ፍርሃትና ፍቅር የሚያድግ ከመሆኑም ሌላ በመንገዱ ለመሄድ እርዳታ ያገኛሉ። (ዘዳግም 10:12, 13) በእነዚህ መመሪያዎች ውስጥ የታቀፉት መሠረታዊ ሥርዓቶች በዛሬው ጊዜ ላሉት የይሖዋ ሕዝቦች ጠቃሚ ናቸው።—ዕብራውያን 10:24, 25
(ዘፀአት 35:21) ከዚያም ልባቸው የገፋፋቸውና መንፈሳቸው ያነሳሳቸው ሁሉ መጥተው ለመገናኛ ድንኳኑ ሥራና በዚያ ለሚከናወነው ማንኛውም አገልግሎት እንዲሁም ለቅዱሶቹ ልብሶች እንዲሆን መዋጮአቸውን ለይሖዋ አመጡ።
የተትረፈረፈ ልግስና ደስታ ያስገኛል
በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ምን እንደተሰማቸው ገምት። በርካታ ትውልዶች በአስከፊ ባርነትና ድህነት ማቅቀዋል። አሁን ነፃ ወጥተው በርካታ ቁሳዊ ንብረቶች አካብተዋል። ከእነዚህ ንብረቶች ውስጥ የተወሰነውን ስለ መስጠት ያላቸው ስሜት ምን ይሆን? ለፍተው ያገኙት እንደሆነና ለራሳቸው የመጠቀም መብት እንዳላቸው ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ንጹሕ አምልኮን ለመደገፍ የገንዘብ መዋጮ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ መዋጮ ያደረጉት እያቅማሙ ወይም እየሰሰቱ አልነበረም! በእጃቸው ያሉትን ቁሳዊ ነገሮች እንዲያገኙ ያስቻላቸው ይሖዋ መሆኑን አልዘነጉም። በመሆኑም የነበራቸውን ብር፣ ወርቅና ከብት በልግስና ሰጥተዋል። ‘ልባቸው ፈቅዶ ነበር።’ ‘ልባቸው አነሣስቷቸዋል፣ መንፈሳቸውም እሺ አሰኝቷቸዋል።’ በእርግጥም “ለእግዚአብሔር ስጦታ በፈቃዳቸው” አምጥተው ነበር።—ዘጸአት 25:1-9፤ 35:4-9, 20-29፤ 36:3-7
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 35:1-24) በኋላም ሙሴ የእስራኤልን ማኅበረሰብ ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ እንድትፈጽሟቸው ያዘዛችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፦ 2 ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእናንተ የተቀደሰ ይሆናል፤ ለይሖዋም ሙሉ በሙሉ የሚታረፍበት ሰንበት ይሆናል። በዚህ ቀን ሥራ የሚሠራ ማንም ሰው ይገደላል። 3 በምትኖሩበት በየትኛውም ቦታ በሰንበት ቀን እሳት አታቀጣጥሉ።” 4 ከዚያም ሙሴ ለእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እንዲህ ሲል አዟል፦ 5 ‘ካላችሁ ነገር ለይሖዋ መዋጮ አምጡ። ልቡ ያነሳሳው ማንኛውም ሰው የሚከተሉትን ነገሮች ለይሖዋ መዋጮ አድርጎ ያምጣ፦ ወርቅ፣ ብር፣ መዳብ፣ 6 ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍ፣ ደማቅ ቀይ ማግ፣ ጥሩ በፍታ፣ የፍየል ፀጉር፣ 7 ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፣ የአቆስጣ ቆዳ፣ የግራር እንጨት፣ 8 ለመብራት የሚሆን ዘይት፣ ለቅብዓት ዘይትና ጥሩ መዓዛ ላለው ዕጣን የሚሆን የበለሳን ዘይት፣ 9 በኤፉዱና በደረት ኪሱ ላይ የሚቀመጡ የኦኒክስ ድንጋዮችና ሌሎች ድንጋዮች። 10 “‘በመካከላችሁ ያሉ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ሁሉ መጥተው ይሖዋ ያዘዘውን ነገር ሁሉ ይሥሩ፤ 11 እነዚህም የማደሪያ ድንኳኑ ከተለያየ ቁሳቁሱና ከመደረቢያው ጋር፣ ማያያዣዎቹ፣ አራት ማዕዘን ቋሚዎቹ፣ አግዳሚ እንጨቶቹ፣ ዓምዶቹ፣ መሰኪያዎቹ፣ 12 ታቦቱና መሎጊያዎቹ፣ መክደኛው፣ ለመከለያ የሚሆነው መጋረጃ፣ 13 ጠረጴዛው እንዲሁም መሎጊያዎቹና ዕቃዎቹ በሙሉ፣ ገጸ ኅብስቱ፣ 14 የመብራት መቅረዙና ዕቃዎቹ፣ መብራቶቹ፣ ለመብራቱ የሚሆነው ዘይት፣ 15 የዕጣን መሠዊያውና መሎጊያዎቹ፣ የቅብዓት ዘይቱና ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን፣ ለማደሪያ ድንኳኑ መግቢያ የሚሆነው መከለያ፣ 16 የሚቃጠል መባ የሚቀርብበት መሠዊያ እንዲሁም የመዳብ ፍርግርጉ፣ መሎጊያዎቹና ዕቃዎቹ በሙሉ፣ ገንዳውና ማስቀመጫው፣ 17 የግቢው መጋረጃ እንዲሁም ቋሚዎቹና መሰኪያዎቹ፣ ለግቢው መግቢያ የሚሆነው መከለያ፣ 18 የማደሪያ ድንኳኑ ካስማዎችና የግቢው ካስማዎች እንዲሁም ገመዶቻቸው፣ 19 በመቅደሱ ለማገልገል የሚለበሱት በጥሩ ሁኔታ የተሸመኑት ልብሶች፣ የካህኑ የአሮን ቅዱስ ልብሶች እንዲሁም ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸው ልብሶች ናቸው።’” 20 ከዚያም የእስራኤል ማኅበረሰብ በሙሉ ከሙሴ ፊት ሄደ። 21 ከዚያም ልባቸው የገፋፋቸውና መንፈሳቸው ያነሳሳቸው ሁሉ መጥተው ለመገናኛ ድንኳኑ ሥራና በዚያ ለሚከናወነው ማንኛውም አገልግሎት እንዲሁም ለቅዱሶቹ ልብሶች እንዲሆን መዋጮአቸውን ለይሖዋ አመጡ። 22 ፈቃደኛ ልብ ያላቸው ሁሉ፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የደረት ጌጥ፣ የጆሮ ጌጥ፣ ቀለበትና ሌላ ጌጣጌጥ እንዲሁም ሁሉንም ዓይነት ከወርቅ የተሠራ ጌጣጌጥ ይዘው ይመጡ ነበር። ሁሉም የወርቅ መባዎቻቸውን ለይሖዋ አቀረቡ። 23 ደግሞም ሰማያዊ ክር፣ ሐምራዊ ሱፍ፣ ደማቅ ቀይ ማግ፣ ጥሩ በፍታ፣ የፍየል ፀጉር፣ ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ እንዲሁም የአቆስጣ ቆዳ ያላቸው ሁሉ እነዚህን አመጡ። 24 ብርና መዳብ የሚያዋጡ ሁሉ ለይሖዋ የሚሆነውን መዋጮ አመጡ፤ ለመገናኛው ድንኳን ሥራ የሚውል የግራር እንጨት ያላቸውም ሁሉ ይህን አመጡ።
ከጥቅምት 26–ኅዳር 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 37–38
“የማደሪያ ድንኳኑ መሠዊያዎች በእውነተኛው አምልኮ ውስጥ የነበራቸው ሚና”
(ዘፀአት 37:25) ከዚያም ከግራር እንጨት የዕጣን መሠዊያውን ሠራ። ርዝመቱ አንድ ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ ሆኖ አራቱም ጎኖቹ እኩል ሲሆኑ ከፍታው ደግሞ ሁለት ክንድ ነበር። ቀንዶቹ ከዚያው ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ።
it-1 82 አን. 3
መሠዊያ
የዕጣን መሠዊያ። የዕጣን መሠዊያው (“የወርቅ መሠዊያ” ተብሎም ይጠራል [ዘፀ 39:38]) የተሠራው ከግራር እንጨት ሲሆን ላዩና ጎኖቹ በወርቅ ተለብጠው ነበር። ዙሪያውን የወርቅ ክፈፍ ተሠርቶለታል። መሠዊያው ርዝመቱና ወርዱ 44.5 ሴንቲ ሜትር፣ ከፍታው ደግሞ 89 ሴንቲ ሜትር ነው፤ እንዲሁም በአራቱም ጫፍ ‘ቀንዶች’ አሉት። በግራር እንጨት ተሠርተው በወርቅ የተለበጡ ለመሸከም የሚያገለግሉ መሎጊያዎች የሚገቡባቸው ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ተሠርተው ነበር፤ እነዚህ ቀለበቶች የተሠሩት በመሠዊያው ሁለት ተቃራኒ ጎኖች ላይ ከክፈፉ በታች ነበር። (ዘፀ 30:1-5፤ 37:25-28) በዚህ መሠዊያ ላይ በቀን ሁለቴ ማለትም ጠዋትና ማታ ልዩ ዕጣን ይጨስ ነበር። (ዘፀ 30:7-9, 34-38) በሌሎች ጥቅሶች ላይ ዕጣን ለማጨስ የሚያገለግል ዕጣን ማጨሻ ወይም ጥና ተጠቅሷል፤ ይህ ጥና ከዕጣን መሠዊያው ጋር ተያይዞ ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ይመስላል። (ዘሌ 16:12, 13፤ ዕብ 9:4፤ ራእይ 8:5፤ ከ2ዜና 26:16, 19 ጋር አወዳድር።) የዕጣን መሠዊያው የሚቀመጠው በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ልክ ከቅድስተ ቅዱሳኑ መጋረጃ በፊት በመሆኑ “ከምሥክሩ ታቦት በፊት” እንደተቀመጠ ተገልጿል።—ዘፀ 30:1, 6፤ 40:5, 26, 27
(ዘፀአት 37:29) በተጨማሪም ቅዱሱን የቅብዓት ዘይትና በብልሃት የተቀመመውን ጥሩ መዓዛ ያለውን ንጹሕ ዕጣን አዘጋጀ።
it-1 1195
ዕጣን
በምድረ በዳ በነበረው የማደሪያ ድንኳን ውስጥ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ቅዱሱ ዕጣን የተዘጋጀው እስራኤላውያን መዋጮ አድርገው ካመጧቸው ውድ ንጥረ ነገሮች ነበር። (ዘፀ 25:1, 2, 6፤ 35:4, 5, 8, 27-29) ይሖዋ የአራት ነገሮች ውህድ የሆነው ይህ ዕጣን የሚቀመምበትን መንገድ ለሙሴ ሲነግረው እንዲህ ብሎታል፦ “አንተም ጥሩ መዓዛ ካላቸው ቅመሞች ይኸውም ከሚንጠባጠብ ሙጫ፣ ከኦኒካ፣ ከሚሸት ሙጫ እንዲሁም ከንጹሕ ነጭ ዕጣን እኩል መጠን ውሰድ። ከዚያም ዕጣን አድርገህ አዘጋጀው፤ ይህም ዕጣን በብልሃት የተቀመመ፣ ጨው የተጨመረበት፣ ንጹሕና ቅዱስ መሆን ይኖርበታል። ከእሱም የተወሰነውን ወቅጠህ በማላም ራሴን ለአንተ በምገልጥበት በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ባለው ምሥክር ፊት ታስቀምጠዋለህ። ይህም ለእናንተ እጅግ ቅዱስ መሆን ይኖርበታል።” አክሎም ይሖዋ ዕጣኑ እሱ ለፈለገው ዓላማ ብቻ መዋል እንዳለበትና ቅዱስ እንደሆነ ለማጉላት እንዲህ ብሏል፦ “በመዓዛው ለመደሰት ሲል ይህን የመሰለ ዕጣን የሚያዘጋጅ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።”—ዘፀ 30:34-38፤ 37:29
(ዘፀአት 38:1) እሱም የሚቃጠል መባ የሚቀርብበትን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ። ርዝመቱ አምስት ክንድ፣ ወርዱም አምስት ክንድ ሲሆን አራቱም ጎኖቹ እኩል ነበሩ፤ ከፍታው ደግሞ ሦስት ክንድ ነበር።
it-1 82 አን. 1
መሠዊያ
የማደሪያ ድንኳኑ መሠዊያዎች። የማደሪያ ድንኳኑ ሲተከል በመለኮታዊ ንድፍ መሠረት ሁለት መሠዊያዎች ተሠርተው ነበር። የሚቃጠል መባ የሚቀርብበት መሠዊያ (“የመዳብ መሠዊያ” ተብሎም ይጠራል [ዘፀ 39:39]) ከግራር እንጨት እንደ ሣጥን ሆኖ የተሠራ ነበር፤ ከላዩም ሆነ ከታቹ ክፍት የነበረ ይመስላል። ርዝመቱና ወርዱ 2.2 ሜትር፣ ከፍታው ደግሞ 1.3 ሜትር ሲሆን በላይኞቹ አራት ጫፎች ላይ ‘ቀንዶች’ ነበሩት። ሁሉም ጎኖቹ በመዳብ ተለብጠው ነበር። ከመሠዊያው ጠርዝ “ወደ ታች ወረድ ብሎ” “መሃል አካባቢ” እንደ መረብ ያለ የመዳብ ፍርግርግ ተቀምጦበት ነበር። በመዳብ ፍርግርጉ አጠገብ በአራቱ ጫፎች ላይ አራት ቀለበቶች ተሠርተውለታል፤ እነዚህ ቀለበቶች በግራር እንጨት ተሠርተው በመዳብ የተለበጡት ለመሸከም የሚያገለግሉ ሁለት መሎጊያዎች የሚገቡባቸው ቀለበቶች ሳይሆኑ አይቀሩም። ይህም ሲባል በመሠዊያው ሁለት ጎኖች ላይ ቀዳዳ በመሥራት ፍርግርጉ እንዲገባና በሁለቱ ጎኖች ቀለበቶቹ ወደ ውጭ እንዲወጡ ተደርጎ ሊሆን ይችላል። ምሁራን ስለዚህ ጉዳይ ያላቸው አመለካከት የተለያየ ነው፤ ብዙዎች ስምንት ቀለበቶች እንደነበሩና አራቱ ቀለበቶች በውጭ በኩል በመሠዊያው ላይ በቀጥታ እንደተሠሩ እንዲሁም መሎጊያዎቹን ለማስገባት ያገለግሉ እንደነበር ያምናሉ። መሠዊያው ከመዳብ የተሠሩ የተለያዩ ቁሳቁሶች ነበሩት፤ ከዚህም መካከል አመዱን ለመጥረግ የሚያገለግሉ ባልዲዎችና አካፋዎች፣ የእንስሳቱን ደም ለመያዝ የሚሆኑ ሳህኖች፣ ሥጋውን ለመያዝ የሚያስችሉ ሹካዎች እንዲሁም መኮስተሪያዎች ይገኙበታል።—ዘፀ 27:1-8፤ 38:1-7, 30፤ ዘኁ 4:14
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 37:1) ከዚያም ባስልኤል ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ። ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር።
(ዘፀአት 37:10) ከዚያም ከግራር እንጨት ጠረጴዛውን ሠራ። ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ ከፍታው ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር።
(ዘፀአት 37:25) ከዚያም ከግራር እንጨት የዕጣን መሠዊያውን ሠራ። ርዝመቱ አንድ ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ ሆኖ አራቱም ጎኖቹ እኩል ሲሆኑ ከፍታው ደግሞ ሁለት ክንድ ነበር። ቀንዶቹ ከዚያው ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ።
it-1 36
ግራር
የግራር ዛፍ ከተንዠረገጉ ቅርንጫፎቹ የሚወጡ ብዙ ረጃጅም እሾሆች አሉት። እነዚህ ቅርንጫፎች አብዛኛውን ጊዜ አጠገባቸው ካሉ የግራር ዛፎች ጋር በመጠላለፍ ችምችም ብለው ያድጋሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ሺቲም የሚለውን ቃል ሁልጊዜ ማለት ይቻላል በብዙ ቁጥር የሚጠቀምበት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። የግራር ዛፍ ከ6 እስከ 8 ሜትር ሊያድግ ይችላል፤ ሆኖም ብዙውን ጊዜ የቁጥቋጦ መልክ አለው። ለስላሳ የሆኑ ቀጫጭን ቅጠሎች ያሉት ሲሆን ደስ የሚል መዓዛ ያለው ቢጫ አበባ ያወጣል፤ እንዲሁም ፍሬው ያልተፈለፈለ ባቄላ ይመስላል። ግንዱ ጥቅጥቅ ያለ፣ ጠንካራና በነፍሳት በቀላሉ የማይጠቃ ሲሆን ቅርፊቱ ደግሞ ጥቁርና ሻካራ ነው። የግራር ዛፍ እነዚህ ባሕርያት ያሉት መሆኑ እንዲሁም በረሃ ውስጥ በቀላሉ የሚገኝ መሆኑ የማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን ቁሳቁሶች ለመሥራት ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል። የቃል ኪዳኑ ታቦት (ዘፀ 25:10፤ 37:1)፣ የገጸ ኅብስቱ ጠረጴዛ (ዘፀ 25:23፤ 37:10)፣ መሠዊያዎቹ (ዘፀ 27:1፤ 37:25፤ 38:1)፣ ለሸክም የሚያገለግሉት መሎጊያዎች (ዘፀ 25:13, 28፤ 27:6፤ 30:5፤ 37:4, 15, 28፤ 38:6)፣ የመጋረጃውና የመከለያው ዓምድ (ዘፀ 26:32, 37፤ 36:36) እንዲሁም የድንኳኑ ቋሚዎች (ዘፀ 26:15፤ 36:20) እና አግዳሚ እንጨቶች (ዘፀ 26:26፤ 36:31) የተሠሩት ከግራር እንጨት ነው።
(ዘፀአት 38:8) ከዚያም የመዳቡን ገንዳና ከመዳብ የተሠራውን ማስቀመጫውን ሠራ፤ ለዚህም በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ በተደራጀ መልክ ያገለግሉ የነበሩትን ሴት አገልጋዮች መስተዋቶች ተጠቀመ።
ይህን ያውቁ ኖሯል?
በዘመናችን ካሉት የብርጭቆ መስተዋቶች በተለየ መልኩ በጥንት ዘመን መስተዋት የሚሠራው በደንብ ከታሹ ማዕድናት ነበር፤ አብዛኛውን ጊዜ ይጠቀሙበት የነበረው ማዕድን ነሐስ ሲሆን ከመዳብ፣ ከብር፣ ከወርቅ ወይም ኤሌክትረም ከተባለ በተፈጥሮ የሚገኝ የወርቅና የብር ቅይጥም ሊሠራ ይችል ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ፣ መስተዋት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው የማደሪያው ድንኳን ተብሎ ከሚጠራው የእስራኤላውያን የአምልኮ ማዕከል ግንባታ ጋር በተያያዘ ነው። ለቅዱስ አገልግሎት ይውል የነበረውን የመዳብ ገንዳና ማስቀመጫውን ለመሥራት ሴቶች መስተዋታቸውን ሰጥተው ነበር። (ዘፀአት 38:8) መስተዋቶቹ ለዚህ ሥራ የዋሉት ከቀለጡ በኋላ ሳይሆን አይቀርም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 37:1-24) ከዚያም ባስልኤል ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ። ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር። 2 ውስጡንና ውጭውንም በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ሠራለት። 3 ከአራቱ እግሮቹ በላይ የሚሆኑ አራት የወርቅ ቀለበቶችን ሠራለት፤ ሁለቱን ቀለበቶች በአንድ ጎኑ፣ ሁለቱን ቀለበቶች ደግሞ በሌላኛው ጎኑ በኩል አደረጋቸው። 4 ከዚያም ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሠራ፤ በወርቅም ለበጣቸው። 5 ታቦቱንም ለመሸከም እንዲያገለግሉ መሎጊያዎቹን በታቦቱ ጎንና ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው። 6 እሱም ከንጹሕ ወርቅ መክደኛውን ሠራ። ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል ወርዱ ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር። 7 በተጨማሪም በመክደኛው ጫፍና ጫፍ ላይ ከተጠፈጠፈ ወርቅ ሁለት ኪሩቦችን ሠራ። 8 አንዱ ኪሩብ በአንዱ ጫፍ ሌላኛው ኪሩብ ደግሞ በሌላኛው ጫፍ ላይ ነበር። ኪሩቦቹን በሁለቱም የመክደኛው ጫፎች ላይ ሠራቸው። 9 ሁለቱ ኪሩቦችም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት መክደኛውን በክንፎቻቸው ከልለውት ነበር። እርስ በርስ ትይዩ ነበሩ፤ ፊታቸውንም ወደ መክደኛው አጎንብሰው ነበር። 10 ከዚያም ከግራር እንጨት ጠረጴዛውን ሠራ። ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ ከፍታው ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ነበር። 11 በንጹሕ ወርቅም ለበጠው፤ ዙሪያውንም የወርቅ ክፈፍ ሠራለት። 12 ከዚያም በዙሪያው አንድ ጋት ስፋት ያለው ጠርዝ ሠራለት፤ ለጠርዙም ዙሪያውን የወርቅ ክፈፍ ሠራለት። 13 በተጨማሪም አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠራለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ በሚገኙባቸው አራት ማዕዘኖች ላይ አደረጋቸው። 14 ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች የሚይዙት ቀለበቶች በጠርዙ አጠገብ ነበሩ። 15 ከዚያም ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። 16 በኋላም በጠረጴዛው ላይ የሚሆኑትን ዕቃዎች ይኸውም ሳህኖቹንና ጽዋዎቹን እንዲሁም ለመጠጥ መባ ማፍሰሻ የሚያገለግሉትን ጎድጓዳ ሳህኖቹንና ማንቆርቆሪያዎቹን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። 17 ከዚያም መቅረዙን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። መቅረዙን ጠፍጥፎ ሠራው። የመቅረዙ መቆሚያ፣ ግንዱ፣ አበባ አቃፊዎቹ፣ እንቡጦቹና የፈኩት አበቦች ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ። 18 መቅረዙ ከግንዱ ላይ የወጡ ስድስት ቅርንጫፎች ነበሩት፤ ሦስቱ ቅርንጫፎቹ ከአንዱ ጎን ሦስቱ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ከሌላው ጎን የወጡ ነበሩ። 19 በአንዱ በኩል ባሉት ቅርንጫፎች በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎች ከእንቡጦችና ከፈኩ አበቦች ጋር በማፈራረቅ ተሠርተው ነበር፤ በሌላኛው በኩል ባሉት ቅርንጫፎችም በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎች ከእንቡጦችና ከፈኩ አበቦች ጋር በማፈራረቅ ተሠርተው ነበር። ከመቅረዙ ግንድ በሚወጡት ስድስት ቅርንጫፎች ላይ የተደረገው ይህ ነበር። 20 በመቅረዙም ግንድ ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ አራት የአበባ አቃፊዎች ከእንቡጦችና ከፈኩ አበቦች ጋር በማፈራረቅ ተሠርተው ነበር። 21 ከግንዱ በሚወጡት በመጀመሪያዎቹ ጥንድ ቅርንጫፎች ሥር አንድ እንቡጥ፣ ቀጥሎ ባሉት ጥንድ ቅርንጫፎች ሥር አንድ እንቡጥ እንዲሁም ቀጥሎ ባሉት ጥንድ ቅርንጫፎች ሥር አንድ እንቡጥ ነበር፤ ከመቅረዙ ግንድ ለሚወጡት ስድስት ቅርንጫፎች እንዲሁ ተደርጎላቸው ነበር። 22 እንቡጦቹም ሆኑ ቅርንጫፎቹ፣ መላው መቅረዙ ከንጹሕ ወርቅ ተጠፍጥፎ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበር። 23 ከዚያም ሰባቱን መብራቶች እንዲሁም መቆንጠጫዎቹንና መኮስተሪያዎቹን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ። 24 መቅረዙን ከዕቃዎቹ ሁሉ ጋር የሠራው ከአንድ ታላንት ንጹሕ ወርቅ ነበር።