ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መቅናት
“ስሙ ቀናተኛ የሆነ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] ቅንዓት ያለው አምላክ ነው።”—ዘጸአት 34:14
1. የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ ምንድን ነው? ከአምላክ ቅናት ጋር የሚዛመደውስ እንዴት ነው?
ይሖዋ ራሱን ‘ቀናተኛ አምላክ’ በማለት ገልጿል። ‘ቅናት’ የተባለው ቃል አሉታዊ ትርጉም ስላለው እንዲህ ያለበት ምክንያት አይገባህ ይሆናል። የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር መሆኑ የተረጋገጠ ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) በመሆኑም ይሖዋ የሚሰማው ቅናት ሁሉ ለሰው ልጆች ጠቀሜታ የሚያመጣ መሆን አለበት። እንዲያውም የአምላክ ቅናት ለአጽናፈ ዓለሙ ሰላምና ስምምነት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ወደፊት እንመለከታለን።
2. ቅናትን ለማመልከት የገባው ግሪክኛ ቃል የሚተረጎምባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
2 በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከ“ቅናት” ጋር የሚዛመዱት የዕብራይስጥ ቃላት ከ80 ጊዜ በላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ወደ ግምሽ የሚያህሉት የተጠቀሱት ለይሖዋ አምላክ ነው። ጂ ኤች ሊቪንግስቶን የተባሉ ጸሐፊ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ሲሰጡ “ቅናት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ለአምላክ በሚሠራበት ወቅት መጥፎ ትርጉም የሚያስተላልፍ ሳይሆን ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እንዲቀርብ መጠየቅን የሚያመለክት ነው” ብለዋል። (ዘ ፔንታቱች ኢን ኢትስ ከልቸራል ኢንቫሮመንት) በመሆኑም አዲሲቱ ዓለም ትርጉም አንዳንድ ጊዜ ቅናትን የሚያመለክተው የዕብራይስጥ ስም “ለራስ ብቻ የተወሰኑ መሆንን የሚጠይቅ” ብሎ ተርጉሞታል። (ሕዝቅኤል 5:13) ሌሎች ተስማሚ የሆኑት ትርጉሞቹ “የጋለ ስሜት” ወይም “ቅንዓት” የሚሉት ናቸው።—መዝሙር 79:5፤ ኢሳይያስ 9:7
3. ቅናት አንዳንድ ጊዜ ለመልካም ዓላማ የሚያገለግለው እንዴት ነው?
3 ሰው የተፈጠረው ቅናት የማሳየት ችሎታ ኖሮት ነው፤ ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በኃጢአት ሥር መውደቁ የተሳሳተ ቅናት እንዲያሳይ አድርጓል። ያም ሆኖ ግን ሰብዓዊ ቅናት ለመልካም ዓላማ ሊያገለግል ይችላል። አንድ ግለሰብ የሚወደውን ሰው ከመጥፎ ተጽዕኖዎች እንዲጠብቀው ሊገፋፋው ይችላል። ከዚህም በላይ ሰዎች ለይሖዋና ለአምልኮው ተገቢ ቅናት ሊያሳዩ ይችላሉ። (1 ነገሥት 19:10) እንዲህ ዓይነቱን ቅናት ለይሖዋ ማሳየት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ለመግለጽ የዕብራይስጡ ስም እርሱን “የሚቀናቀነውን ፈጽሞ አለመታገሥ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።—2 ነገሥት 10:16
የወርቅ ጥጃ
4. አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጣቸው ሕግ ላይ ጎልቶ የታየው ትክክለኛ ቅናትን የሚመለከት ትእዛዝ የትኛው ነበር?
4 እስራኤላውያን በሲና ተራራ ላይ ሕጉን ከተቀበሉ በኋላ የተፈጸመው ነገር ለትክክለኛው ቅናት ምሳሌ የሚሆን ነው። ሰው ሠራሽ ጣዖታትን እንዳያመልኩ በተደጋጋሚ ጊዜያት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር። ይሖዋ “እኔ ይሖዋ አምላክህ ፈጽሞ ለእኔ ብቻ የተወሰነ አምልኮ የምፈልግ አምላክ ነኝ፤ [ወይም “ቀናተኛ (ቀናኢ) አምላክ ነኝ፤ ተቀናቃኝን የማልታገሥ አምላክ ነኝ”]” በማለት ነግሯቸዋል። (ዘጸአት 20:5 አዓት፣ የግርጌ ማስታወሻ፤ ከዘጸአት 20:22, 23፤ 22:20 እና 23:13, 24, 32, 33 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ እነሱን ለመባረክና ወደ ተስፋይቱ ምድር ለማስገባት ቃል በመግባት ከእስራኤላውያን ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። (ዘጸአት 23:22, 31) ሕዝቡም “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም” አሉ።—ዘጸአት 24:7
5, 6. (ሀ) እስራኤላውያን በሲና ተራራ ላይ በሰፈሩበት ወቅት ከባድ ኃጢአት የሠሩት እንዴት ነበር? (ለ) ይሖዋና ታማኝ አምላኪዎቹ በሲና ተራራ ትክክለኛ ቅናት ያሳዩት እንዴት ነበር?
5 ሆኖም እስራኤላውያን ወዲያውኑ በአምላክ ላይ ኃጢአት ሠሩ። ሕዝቡ ገና ከሲና ተራራ በታች ሰፍረው ነበር። ሙሴ ከአምላክ ተጨማሪ መመሪያ እየተቀበለ በተራራው ላይ ለብዙ ቀናት ቆይቶ ነበር፤ ሕዝቡም የሙሴ ወንድም የሆነውን አሮንን አምላክ እንዲሠራላቸው አስገደዱት። አሮን ተስማማና ሕዝቡ በሰጡት ወርቅ ተጠቅሞ ጥጃ ሠራ። ይህ ጣዖት ይሖዋን ይወክላል ተባለ። (መዝሙር 106:20 የ1980 ትርጉም) በሚቀጥለው ቀን መሥዋዕቶችን አቀረቡና ‘ሰገዱለት።’ ከዚያም ‘ሊዘፍኑ ተነሡ።’—ዘጸአት 32:1, 4, 6, 8, 17–19
6 እስራኤላውያን ገና በዓሉን እያከበሩ ሳሉ ሙሴ ከተራራው ወረደ። ይህን አሳፋሪ ተግባራቸውን ሲመለከት “የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ!” አለ። (ዘጸአት 32:25, 26) የሌዊ ልጆች ወደ ሙሴ ተሰበሰቡ፤ እርሱም ተቀናቃኞቹን ጣዖት አምላኪዎች በሰይፍ እንዲገድሏቸው አዘዛቸው። ሌዋውያን ለአምላክ ንጹሕ አምልኮ ያላቸውን ቅናት በማሳየት በዚህ መጥፎ አድራጎት የተሳተፉትን 3,000 ወንድሞቻቸውን ገደሉ። ይሖዋ በሕይወት በተረፉት ላይ መቅሠፍት በማውረድ ይህን እርምጃ አጠናከረው። (ዘጸአት 32:28, 35) ከዚያም አምላክ “ስሙ ቀናተኛ የሆነ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] ቅንዓት ያለው አምላክ ነውና ለሌላ አምላክ አትስገድ” የሚለውን ትእዛዝ ደገመው።—ዘጸአት 34:14
ብዔልፌጎር
7, 8. (ሀ) ብዙ እስራኤላውያን ከብዔልፌጎር ጋር በተያያዘ መልኩ በከባድ የጣዖት አምልኮ ውስጥ የወደቁት እንዴት ነበር? (ለ) ከይሖዋ የመጣው መቅሠፍት ሊቆም የቻለው እንዴት ነበር?
7 ከ40 ዓመታት በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገባ ሲቃረብ በጣም ውብ የሆኑ የሞዓባውያንና የምድያማውያን ሴቶች ወደ እነርሱ መጥተው በመስተንግዷቸው እንዲደሰቱ ብዙ እስራኤላውያንን አግባቡ። እስራኤላውያን ከሐሰተኛ አማልክት አምላኪዎች ጋር የተቀራረበ ግንኙነት መፍጠር አይገባቸውም ነበር። (ዘጸአት 34:12, 15) ከዚህ ይልቅ ‘በሬ ለመታረድ እንደሚነዳ’ ከሴቶቹ ጋር ዝሙት ለመፈጸምና አብረዋቸው ለብዔልፌጎር ለመስገድ ተጣደፉ።—ምሳሌ 7:21, 22፤ ዘኁልቁ 25:1–3
8 ይሖዋ በዚህ አሳፋሪ የጾታ አምልኮ ውስጥ የተሳተፉትን ለመፍጀት መቅሠፍት አወረደ። በተጨማሪም አምላክ ንጹሕ እስራኤላውያን በድርጊቱ የተሳተፉትን ወንድሞቻቸውን እንዲገድሉ አዘዘ። ዘምሪ የተባለ አንድ እስራኤላዊ የሕዝብ አለቃ በዕብሪት ተነሣስቶ ከአንዲት ምድያማዊት ልዕልት ጋር የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ወደ ድንኳኑ ይዟት ገባ። ፈሪሃ አምላክ የነበረው ካህኑ ፊንሐስ ይህን ነገር ሲመለከት እነዚህን ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት የፈጸሙ ወንድና ሴት ገደላቸው። በዚህ ጊዜ መቅሠፍቱ ተከለከለና አምላክ “ፊንሐስ . . . ቁጣዬን ከእስራኤላውያን እንድመልስ አድርጓል፤ እኔን ያንቀሳቀሰኝን ዓይነት የቅናት ቁጣ በመካከላቸው ስላሳየ በቅናቴ እስራኤላውያንን አላጠፋሁም” በማለት ተናገረ። (ዘኁልቁ 25:11፣ ዘ ኒው እንግሊሽ ባይብል) ሕዝቡ ጨርሶ ከመጥፋት ቢድንም ቢያንስ ወደ 23,000 የሚጠጉ እስራኤላውያን ሞተዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:8) ለረጅም ጊዜ እንደ ውድ ተስፋ አድርገው ሲጠባበቁት የነበረውን ወደ ተስፋይቱ ምድር የመግባት መብት ሳያገኙ ቀርተዋል።
የማስጠንቀቂያ ትምህርት
9. የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝቦች ለይሖዋ እውነተኛ አምልኮ ባለመቅናታቸው ምክንያት ምን ደረሰባቸው?
9 እስራኤላውያን እነዚህን ትምህርቶች ወዲያውኑ መርሳታቸው ያሳዝናል። ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ የሚቀኑ ሆነው አልተገኙም። “በተቀረጹ ምስሎቻቸውም [አምላክን] አስቀኑት።” (መዝሙር 78:58) በዚህም ምክንያት ይሖዋ አሥሩ የእስራኤል ነገዶች በ740 ከዘአበ በአሦራውያን እጅ እንዲማረኩ ፈቀደ። ቀሪዎቹ ሁለቱ የይሁዳ ነገዶችም ዋና ከተማቸው ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ስትጠፋ ተመሳሳይ ቅጣት ደርሶባቸዋል። ብዙዎች የተገደሉ ሲሆን በሕይወት የተረፉት ደግሞ ተማርከው ወደ ባቢሎን ተወሰዱ። በአሁኑ ወቅት ላሉት ክርስቲያኖች በሙሉ እንዴት ያለ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ነው!—1 ቆሮንቶስ 10:6, 11
10. ንስሐ በማይገቡ ጣዖት አምላኪዎች ላይ ምን ይደርስባ ቸዋል?
10 በአሁኑ ወቅት ወደ 1,900 ሚልዮን የሚጠጋው አንድ ሦስተኛው የምድር ሕዝብ ክርስቲያን ነኝ ይላል። (1994 ብሪታኒካ ቡክ ኦቭ ዘ ይር) ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ሥዕላ ሥዕሎችን፣ የተቀረጹ ምስሎችንና መስቀሎችን ለአምልኮ የሚጠቀሙ አብያተ ክርስቲያናት አባላት ናቸው። ይሖዋ በጣዖት አምልኳቸው ያስቀኑትን የራሱን ሕዝቦች አልማረም። በቁሳዊ ነገሮች እርዳታ የሚያመልኩትን ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎችንም ቢሆን አይምርም። ኢየሱስ ክርስቶስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” ብሎአል። (ዮሐንስ 4:24) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ከጣዖት አምልኮ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ያስጠነቅቃል። (1 ዮሐንስ 5:21) የአምላክን መንግሥት ከማይወርሱት ሰዎች መካከል ንስሐ የማይቡ ጣዖት አምላኪዎች ይገኙበታል።—ገላትያ 5:20, 21
11. አንድ ክርስቲያን ለጣዖት ባይሰግድም በጣዖት አምላኪነት ሊጠየቅ የሚችለው እንዴት ነው? አንድ ሰው ከዚህ ዓይነቱ የጣዖት አምልኮ እንዲርቅ ሊረዳው የሚችለው ምንድን ነው? (ኤፌሶን 5:5)
11 አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ምንም እንኳን ለጣዖት ባይሰግድም አምላክ እንደ ጣዖት አምልኮ፣ ርኩስና ኃጢአት እንደሆነ አድርጎ ከሚመለከተው ከማንኛውም ነገር መራቅ ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል፦ “በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቁጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል።” (ቆላስይስ 3:5, 6፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) እነዚህን ቃላት ለመታዘዝ ሥነ ምግባር ከጎደለው አድራጎት መራቅ ያስፈልጋል። ይህም ከረከሱና የጾታ ስሜት ለመቀስቀስ ታስበው ከሚዘጋጁ መዝናኛዎች መራቅን ይጠይቃል። እውነተኛ ክርስቲያኖች እነዚህን ፍላጎቶች ከማርካት ይልቅ ለአምላክ እውነተኛ አምልኮ ይቀናሉ።
ሌሎች የአምላካዊ ቅናት ምሳሌዎች
12, 13. ኢየሱስ ለአምላክ ንጹሕ አምልኮ ቅናት በማሳየት ረገድ የላቀ ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው?
12 ለአምላክ ንጹሕ አምልኮ በመቅናት ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የሚሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በአገልግሎቱ የመጀመሪያ ዓመት በቤተ መቅደሱ አደባባይ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን ስግብግብ ነጋዴዎች ተመለከተ። ከሌላ አገር የመጡ አይሁዳውያን ከውጪ አገር ያመጡትን ገንዘብ በቤተ መቅደስ ተቀባይነት ያለው ቀረጥ አድርገው ለማቅረብ እንዲችሉ ገንዘብ ለዋጮች የሚሰጡት አገልግሎት አስፈልጓቸው ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የአምላክ ሕግ የሚጠይቀውን መሥዋዕት ለማቅረብ እንስሳትንና የተለያዩ ዓይነት ወፎችን መግዛት ያስፈልጋቸው ነበር። እንደነዚህ ዓይነቶቹ የንግድ ጉዳዮች ከቤተ መቅደሱ አደባባይ ውጪ መደረግ ነበረባቸው። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ከዚህ የከፋው ነገር ነጋዴዎቹ ከመጠን በላይ የሆነ ዋጋ እየጠየቁ ወንድሞቻቸው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለማከናወን የግድ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች እንደ መሣሪያ በመጠቀም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ማግኘታቸው ነው። ኢየሱስ ለአምላክ ንጹሕ አምልኮ ባለው ቅናት ተቃጥሎ በጎቹንና ከብቶቹን በጅራፍ እየገረፈ ከቤተ መቅደሱ አስወጣቸው። በተጨማሪም የገንዘብ ለዋጮቹን ጠረጴዛዎች ገልብጦ “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው።” (ዮሐንስ 2:14–16) በዚህ መንገድ ኢየሱስ በመዝሙር 69:9 ላይ አስቀድመው የተተነበዩትን “የቤትህ ቅንዓት በልታኛለች” የሚሉትን ቃላት ፈጸማቸው።
13 ከሦስት ዓመት በኋላ ስግብግብ ነጋዴዎች በቤተ መቅደስ ሲነግዱ ኢየሱስ ተመለከተ። ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ቤተ መቅደሱን ያጸዳ ይሆን? በዚያን ወቅት ለአምላክ ንጹሕ አምልኮ የነበረው ቅናት አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት እንደ ነበረው ቅናት የጋለ ነበር። ሻጮቹንም ሆነ ገዢዎቹን ከቤተ መቅደሱ አስወጣቸው። እንዲያውም “ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችሁት” በማለት ይህን እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳውን ቀደም ሲል ካቀረበው ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ምክንያት አቀረበ። (ማርቆስ 11:17) አምላካዊ ቅናት በማሳየት ረገድ እንዴት ያለ አስደናቂ የመንፈሰ ጠንካራነት ምሳሌ ነው!
14. ኢየሱስ ለንጹሕ አምልኮ ያለው ቅናት እንዴት ሊነካን ይገባል?
14 በአሁኑ ወቅት ክብር ተጎናጽፎ የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም አልተለወጠም። (ዕብራውያን 13:8) በምድር በነበረበት ወቅት ይቀና የነበረውን ያህል በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመንም ለአባቱ ንጹሕ አምልኮ ይቀናል። ኢየሱስ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ለተጠቀሱት ለሰባቱ ጉባኤዎች ከላከላቸው መልእክቶች ይህን መረዳት ይቻላል። እነዚህ መልእክቶች አሁን በምንኖርበት “የጌታ ቀን” ውስጥ ከፍተኛ ተፈጻሚነት አላቸው። (ራእይ 1:10፤ 2:1 እስከ 3:22) ሐዋርያው ዮሐንስ ክብር የተጎናጸፈውን ኢየሱስ ክርስቶስን “ዓይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል” ሆነው በራእይ አይቶታል። (ራእይ 1:14) ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ጉባኤዎች ንጹሕና ለይሖዋ አገልግሎት ተቀባይነት ያላቸው ሆነው መቀጠላቸውን ሲመረምር ሳያስተውለው የሚያልፈው ነገር እንደሌለ ያመለክታል። በአሁኑ ወቅት ያሉ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ለሁለት ጌቶች ማለትም ለአምላክና ለሀብት መገዛት እንደማይቻል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በአእምሯቸው መያዝ ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 6:24) ኢየሱስ ቁሳዊ አስተሳሰብ ለተጠናወታቸው የሎዶቅያ ጉባኤ አባላት “እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። . . . እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ” ብሏቸው ነበር። (ራእይ 3:14–19) የተሾሙ የጉባኤ ሽማግሌዎች በሚናገሩት ቃልም ሆነ በሚያሳዩት ምሳሌነት መሰል አማኞች ከቁሳዊ አስተሳሰብ ወጥመድ እንዲርቁ መርዳት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ሽማግሌዎች የጾታ ስሜት ከተጠናወተው ከዚህ ዓለም የሥነ ምግባር ርኩሰት መንጋውን መጠበቅ አለባቸው። ከዚህም በላይ የአምላክ ሕዝቦች ማናቸውንም ዓይነት የኤልዛቤል ተጽዕኖ በጉባኤው ውስጥ እንዲገባ በጭራሽ አይፈቅዱም።—ዕብራውያን 12:14, 15፤ ራእይ 2:20
15. ሐዋርያው ጳውሎስ ለይሖዋ አምልኮ ቅናት በማሳየት ረገድ ኢየሱስን የመሰለው እንዴት ነው?
15 ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቶስን ምሳሌነት ተከትሏል። አዲስ ተጠማቂ ክርስቲያኖችን በመንፈሳዊ መጥፎ ከሆኑ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ ሲል “በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁ” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 11:2) ከዚህ ቀደም ጳውሎስ ለንጹሕ አምልኮ የነበረው ቅናት ጉባኤውን የመበከል ተጽዕኖ የነበረው አንድ ንስሐ ያልገባ ዘማዊ ሰውን እንዲያስወግድ ለዚሁ ጉባኤ መመሪያ እንዲሰጥ ገፋፍቶት ነበር። በዚያ ወቅት በመንፈስ አነሣሽነት የተሰጡት መመሪያዎች በዘመናችን ያሉት ሽማግሌች ከ75,500 በላይ የሆኑትን የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በንጽሕና ለመጠበቅ በሚጥሩበት ወቅት ከፍተኛ እርዳታ ሲያበረክቱላቸው ቆይተዋል።—1 ቆሮንቶስ 5:1, 9–13
የአምላክ ቅናት ሕዝቦቹን ይጠቅማል
16, 17. (ሀ) አምላክ የጥንቷን ይሁዳ ሲቀጣ ብሔራት ምን ዝንባሌ አሳይተው ነበር? (ለ) ይሁዳ ለ70 ዓመታት ባድማ ከሆነች በኋላ ይሖዋ ለኢየሩሳሌም መቅናቱን ያሳየው እንዴት ነው?
16 አምላክ የይሁዳ ሰዎችን ወደ ባቢሎን በምርኮ እንዲወሰዱ በመፍቀድ ሲቀጣቸው ሕዝቡ መሳለቂያ ሆነ። (መዝሙር 137:3) እንዲያውም ኤዶማውያን ከቅናት በመነጨ ጥላቻ በአምላክ ሕዝብ ላይ መከራ ለማምጣት ባቢሎናውያንን ረድተዋቸው ነበር፤ ይሖዋም ይህን ተመለከተ። (ሕዝቅኤል 35:11፤ 36:15) ሕይወታቸው በምርኮ የተረፈላቸው ሰዎች ንስሐ ገቡና ይሖዋ ከ70 ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው መለሳቸው።
17 መጀመሪያ ላይ የይሁዳ ሰዎች ተስፋ አስቆራጭ በሆነ መከራ ውስጥ ነበሩ። የኢየሩሳሌም ከተማና ቤተ መቅደሷ የፍርስራሽ ክምር ሆነው ነበር። ይሁን እንጂ በአካባቢው የነበሩት ብሔራት ቤተ መቅደሱ እንዲሠራ የሚደረገውን ጥረት በሙሉ ይቃወሙ ነበር። (ዕዝራ 4:4, 23, 24) ይሖዋ ስለዚህ ጉዳይ ምን ተሰምቶት ነበር? በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው መዝገብ እንዲህ ይላል፦ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ በታላቅ ቅንዓት በኢየሩሳሌምና በጽዮን ላይ ቀንቻለሁ። እኔ ጥቂት ብቻ ተቆጥቼ ሳለሁ እነርሱ ክፋትን ስላገዙት፣ ባልተቸገሩት አሕዛብ ላይ እጅግ ተቆጥቻለሁ። ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ፤ ቤቴ ይሠራባታል፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ገመድ ይዘረጋባታል፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” (ዘካርያስ 1:14–16) በዚህ ተስፋ መሠረት ቤተ መቅደሱና ኢየሩሳሌም በተሳካ መንገድ ተሠሩ።
18. እውነተኛ ክርስቲያኖች በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ምን ደረሰባቸው?
18 በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የእውነተኛው ክርስቲያን ጉባኤ ተመሳሳይ ተሞክሮ አጋጥሞታል። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ለዚህ ዓለማዊ ግጭት ቁርጥ ያለ የገለልተኝነት አቋም ስላልያዙ ይሖዋ ሕዝቡን ቀጥቶ ነበር። (ዮሐንስ 17:16) የፖለቲካ ኃይላት እንዲጨቁኗቸው አምላክ ሲፈቅድ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በዚህ መከራቸው ተደሰቱ። እንዲያውም በዚያን ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ ፖለቲከኞች እንዲያግዱ በማድረግ ረገድ ቀሳውስት ግምባር ቀደም ነበሩ።—ራእይ 11:7, 10
19. ይሖዋ ከ1919 ጀምሮ ለአምልኮቱ የቀናው እንዴት ነው?
19 ሆኖም ይሖዋ ለአምልኮው በመቅናት ንስሐ የገቡ ሕዝቦቹን ከጦርነቱ በኋላ በ1919 መልሶ አቋቋማቸው። (ራእይ 11:11, 12) በዚህም ምክንያት በ1918 ከ4,000 ያንስ የነበረው የይሖዋ አወዳሾች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ወደ 5 ሚልዮን የሚጠጋ ሆኗል። (ኢሳይያስ 60:22) በቅርቡ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮው ያለው ቅናት ይበልጥ አስደናቂ በሆኑ መንገዶች ይገለጻል።
ወደፊት መለኮታዊ ቅናት የሚታይባቸው ድርጊቶች
20. ይሖዋ ለእውነተኛ አምልኮ እንደሚቀና ለማሳየት በቅርቡ ምን ያደርጋል?
20 የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስትያናት ይሖዋን ያስቀኑትን ከሃዲ አይሁዳውያን መንገድ ለብዙ መቶ ዘመናት ሲከተሉ ቆይተዋል። (ሕዝቅኤል 8:3, 17, 18) በቅርቡ ይሖዋ አምላክ በተባበሩት መንግሥታት አባላት ልብ ውስጥ አንድ ሐሳብ በድንገት በማስገባት እርምጃ ይወስዳል። ይህ ሐሳብ እነዚህ የፖለቲካ ኃይላት ሕዝበ ክርስትናንና ቀሪውን የሐሰት ሃይማኖት ባድማ እንዲያደርጉ ያንቀሳቅሳቸዋል። (ራእይ 17:16, 17) እውነተኛ አምላኪዎች ከዚያ አስፈሪ መለኮታዊ ፍርድ በሕይወት ይተርፋሉ። “ሃሌ ሉያ፤ በዝሙትዋ [የሐሰት ትምህርቶቿና የረከሰውን ፖለቲካ በመደገፏ] ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ [የሐሰት ሃይማኖት] ስለ ፈረደባት፣ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ” ለሚሉት ሰማያዊ ፍጥረታት ለሚያስተጋቡት ቃላት አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ።—ራእይ 19:1, 2
21. (ሀ) የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ ሰይጣንና ሥርዓቱ ምን ያደርጋሉ? (ለ) አምላክ ምን እርምጃ ይወስዳል?
21 የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከጠፋች በኋላ ምን ይሆናል? ሰይጣን የፖለቲካ ኃይላት በይሖዋ ሕዝቦች ላይ የተባበረ ዓለም አቀፋዊ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ይገፋፋቸዋል። ሰይጣን እውነተኛውን አምልኮ ከምድረ ገጽ ጠራርጎ ለማጥፋት ለሚያደርገው ለዚህ ጥረት እውነተኛው አምላክ እንዴት ያለ ምላሽ ይሰጣል? ሕዝቅኤል 38:19–23 እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “[እኔ ይሖዋ] በቅንዓቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፦ . . . [በሰይጣን ላይ] በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍም የበረዶም ድንጋይ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ። ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”—በተጨማሪም ሶፎንያስ 1:18ን እና 3:8ን ተመልከት።
22. ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ እንደምንቀና ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
22 የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ቅናት ለእውነተኛ አምላኪዎቹ ጥቅም እንደሚያስገኝ ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይገባናል ለማንለው ደግነቱ ካለን ጥልቅ አድናቆት የተነሣ ለይሖዋ አምላክ እውነተኛ አምልኮ እንቅና። በቅንዓት ምሥራቹን መስበካችንን እንዲሁም ይሖዋ ታላቅ ስሙን ከፍ ከፍ የሚያደርግበትንና የሚቀድስበትን ቀን በትምክህት መጠባበቃችንን እንቀጥል።—ማቴዎስ 24:14
የምናሰላስልባቸው ነጥቦች
◻ ለይሖዋ መቅናት ማለት ምን ማለት ነው?
◻ የጥንት እስራኤላውያን ከተዉልን ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?
◻ ይሖዋን እንዳናስቀናው መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ አምላክና ክርስቶስ ለንጹሕ አምልኮ የቀኑት እንዴት ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ፍቅር አይቀናም
የ19ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት አልበርት ባርነስ ምቀኝነትን በተመለከተ ሲጽፉ “ክፋት ከሚገለጽባቸው በሰፊው ከሚታወቁ ነገሮች አንዱ ምቀኝነት ሲሆን የሰውን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ውድቀት በግልጽ የሚያሳይ ነገር ነው” ብለው ነበር። አክለውም እንዲህ በማለት ተናገሩ፦ “የጦርነቶችን፣ የግጭቶችንና ዓለማዊ እቅዶችን ሌላው ቀርቶ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች እንኳ የሚያወጧቸውን ሃይማኖታቸውን የሚያረክሱና ዓለማዊ አስተሳሰብ እንዲጠናወታቸው የሚያደርጉ እቅዶችና ትልሞች ከሥር መሠረታቸው መርምሮ ለመረዳት የቻለ ሰው ለዚህ ሁሉ ምቀኝነት ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳለው ሲገነዘብ በጣም ይገረማል። ሌሎች ሰዎች ከእኛ የበለጠ ሲበለጽጉ እናዝናለን፤ መብቱ ባይኖረንም እንኳ ሌሎች ያሏቸውን ነገሮች ለማግኘት እንመኛለን፤ ይህም ከዚያ ነገር የሚያገኙትን ደስታ ለመቀነስ ወይም ያንን ነገር እኛ ራሳችን ለማግኘት ወይም ብዙውን ጊዜ የሚታሰበውን ያህል እንደ ሌላቸው ለማሳየት የታቀዱ የተለያዩ መጥፎ መንገዶችን ወደ መከተል ይመራናል። . . . በዚህ መንገድ በልባችን ውስጥ ያለውን የምቀኝነት ዝንባሌ እናረካለን።”—ሮሜ 1:29፤ ያዕቆብ 4:5
ከዚህ ጋር በሚጻረር መንገድ ባርነስ ‘የማይመቀኘውን’ ፍቅር በተመለከተ ይህን ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ገልጸዋል። (1 ቆሮንቶስ 13:4 ኪንግ ጄምስ ቨርሽን) እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ፍቅር ሌሎች ሰዎች ባላቸው ደስታ አይመቀኝም፤ በደኅንነታቸው ይደሰታል፤ የእነርሱ ደስታ እየጨመረ ሲሄድ . . . በፍቅር የሚመሩ ሰዎች . . . ደስታቸውን አይቀንሱባቸውም፤ እነርሱ ጥቅም ስላገኙ አያዝኑም፤ ሁኔታው ደስታቸውን አይነጥቅባቸውም፤ እነርሱ ራሳቸው ያን ያህል የታደሉ ባለመሆናቸው አያጉረመርሙም ወይም አያዝኑም። . . . ሌሎችን ካፈቀርናቸውና በደስታቸው ከተደሰትን ልንመቀኛቸው አይገባም።”
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፊንሐስ ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ቀንቷል