ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ ስጡ!
ማታ ስብሰባ አለ፣ ግን የምትሠራው ሥራ አለህ። ታዲያ የምታስቀድመው የትኛውን ነው?
ባለትዳርና የልጆች አባት ነህ እንበል። ረዥሙና አድካሚው የቀኑ ሥራ እየተጠናቀቀ ሲመጣ አእምሮህ ምሽት ላይ የሚደረገውን የጉባኤ ስብሰባ ማውጠንጠን ይጀምራል። የሥራ ሰዓት እንዳበቃ ወዲያው ወደ ቤት ከሄድክ ስብሰባ ከመሄድህ በፊት ገላህን ለመታጠብ፣ ልብስህን ለመቀየርና ጥቂት መክሰስ ለመቀማመስ ጊዜ ይኖርሃል ማለት ነው። በድንገት አሠሪህ ይመጣና ተጨማሪ ሰዓት እንድትሠራ ይጠይቅሃል። ለትርፍ ሰዓቱ ሥራ ብዙ ገንዘብ እንደሚከፍልህም ያረጋግጥልሃል። ገንዘቡ ደግሞ ያስፈልግሃል።
ወይም የቤት እመቤት ነሽ እንበል። እራት እየሠራሽ እያለ ዓይንሽ በድንገት ሳይተኮሱ ተከምረው በተቀመጡ ልብሶች ላይ ያርፋል። አንዳንዶቹ ልብሶች ደግሞ ለነገ የሚያስፈልጉ ናቸው። ራስሽን እንዲህ እያልሽ ትጠይቂያለሽ:- ‘ዛሬ ማታ ወደ ስብሰባ ከሄድኩ ልብሶቹን መቼ ልተኩሳቸው ነው?’ በቅርቡ የሙሉ ቀን ሥራ በመጀመርሽ የመተዳደሪያ ገቢ ለማግኘት ውጭ እየሠሩ የቤቱን ሥራ ማከናወኑ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ተሰምቶሻል።
ወይም ተማሪ ነህ እንበል። የቤት ሥራ ተከምሮብሃል። አብዛኞቹ የቤት ሥራዎች የተሰጡህ ከጥቂት ቀናት በፊት ነው። ሆኖም ዛሬ ነገ እያልክ ሳትሠራው በመቅረትህ አሁን የምትሠራቸው የቤት ሥራዎች በዝተውብሃል። ከስብሰባ ቀርተህ የቤት ሥራዎችህን ለመሥራት እንድትችል ወላጆችህን ለማስፈቀድ እያቅማማህ ነው።
አንተ በግልህ ቅድሚያ የምትሰጠው ለየትኛው ነው? የትርፍ ሰዓት ሥራውን፣ ልብስ መተኮሱን፣ የቤት ሥራ መሥራቱን ወይስ የጉባኤ ስብሰባውን? በመንፈሳዊ አባባል ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ቅድሚያ መስጠት ማለት ምን ማለት ነው? ይሖዋስ ስለዚህ ጉዳይ ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
እስራኤላውያን አሥርቱን ትእዛዛት ከተቀበሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም ተገኘ። ሕጉ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት አጥብቆ ይከለክል ነበር። (ዘኁልቁ 15:32-34፤ ዘዳግም 5:12-15) ይህን ጉዳይ እንድትዳኝ ጥያቄ ቀርቦልህ ቢሆን ኖሮ ምን ዓይነት ፍርድ ትሰጥ ነበር? ይህ ሰው እኮ የቅንጦት ኑሮ ለመምራት ብሎ ሳይሆን ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ደፋ ቀና ሲል ነው የተገኘው በማለት በነፃ እንዲለቀቅ ታደርግ ነበር? በአንድ ዓመት ውስጥ የሰንበትን ቀን ለመጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ቀናት አሉ፤ ታዲያ ምናልባት ሰውየው አስቀድሞ እቅድ ባለማውጣቱ ምክንያት አንድ ቀን ቢስት ምን ክፋት አለው በማለት በቀላሉ ምሕረት ታደርግለት ነበር?
ይሖዋ ጉዳዩን እንዲህ አቅልሎ አልተመለከተውም። “እግዚአብሔርም ሙሴን:- ሰውየው ፈጽሞ ይገደል . . . አለው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘኁልቁ 15:35) ይሖዋ ሰውዬው ያደረገውን ነገር ይህን ያህል አክብዶ የተመለከተው ለምንድን ነው?
ሕዝቡ እንጨት ለመልቀምም ሆነ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ለማግኘት የሚሠሩባቸው ስድስት ቀናት አሏቸው። ሰባተኛውን ቀን ግን ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ማዋል ነበረባቸው። እንጨት መልቀሙ ምንም ስህተት የሌለበት ቢሆንም ለይሖዋ አምልኮ የተወሰነውን ጊዜ ለዚህ ሥራ ማዋሉ ግን ፈጽሞ ስህተት ነበር። ምንም እንኳ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም ይህ ሁኔታ በዛሬው ጊዜ ቅድሚያ ልንሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች ጥሩ ትምህርት አይሰጠንም?—ፊልጵስዩስ 1:10
እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ከቆዩ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚገቡበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። አንዳንዶቹ አምላክ በተአምር ይሰጣቸው የነበረውን መና መብላት ሰልችቷቸው ስለነበር ሌላ ምግብ መመገብ የሚጀምሩበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። “ወተትና ማር ወደምታፈስሰው” ምድር በሚገቡበት ጊዜ ተገቢ የሆነ አመለካከት እንዲይዙ ሲል ይሖዋ “ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት” አይኖርም በማለት አሳሰባቸው።—ዘጸአት 3:8፤ ዘዳግም 8:3
እስራኤላውያን “ወተትና ማር” ለማግኘት ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸው ነበር። ድል መደረግ የነበረባቸው ሠራዊቶች፣ መሠራት የነበረባቸው ቤቶችና መልማት የነበረባቸው መስኮች ነበሩ። ሆኖም ይሖዋ በየቀኑ መንፈሳዊ ነገሮችን የሚያሰላስሉበት ጊዜ እንዲመድቡ አዟቸዋል። እንዲሁም የአምላክን መንገዶች ለልጆቻቸው ለማስተማር ጊዜ መመደብ ነበረባቸው። ይሖዋ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ልጆቻችሁንም [ትእዛዛቴን] አስተምሯቸው፣ በቤትህም ስትቀመጥ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም ስትነሣም አጫውቱአቸው።”—ዘዳግም 11:19
በዓመት ሦስት ጊዜ እያንዳንዱ እስራኤላዊ ወንድና በአገሩ የሚኖር ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠ ወንድ ሁሉ በይሖዋ ፊት እንዲታይ ታዝዞ ነበር። መላው የቤተሰቡ አባላት ከዚህ ዝግጅት ጥቅም እንደሚያገኝ ስለተገነዘቡ ብዙዎቹ የቤት ራሶች ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ይሄዱ ነበር። ይሁን እንጂ ቤተሰቡ ርቆ በሚሄድበት ወቅት ቤታቸውንና እርሻቸውን ከጠላት የሚጠብቅላቸው ማን ነው? ይሖዋ “በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት በዓመት ሦስት ጊዜ ስትወጣ ማንም ምድርህን አይመኝም” በማለት ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘጸአት 34:24) እስራኤላውያን መንፈሳዊ ነገሮችን ካስቀደሙ ቁሳዊ ነገሮች እንደማይጎድልባቸው አምነው ለመቀበል እምነት ጠይቆባቸው ነበር። ታዲያ ይሖዋ እንዳለው አድርጓል? አዎን፣ አድርጓል!
መንግሥቱን ማስቀደማችሁን ቀጥሉ
ኢየሱስ ከምንም ነገር በፊት መንፈሳዊ ጉዳዮችን እንዲያስቀድሙ ተከታዮቹን አስተምሯል። በተራራ ስብከቱ አድማጮቹን እንዲህ በማለት መክሯቸዋል:- “ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ . . . አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ [አስፈላጊ ነገሮች] ይጨመርላችኋል።” (ማቴዎስ 6:31, 33) አዲስ የተጠመቁ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ሞት በኋላ ወዲያው ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል። በ33 እዘአ የተከበረውን የጰንጠቆስጤ በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት አብዛኞቹ ሰዎች አይሁዳውያን ወይም ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ነበሩ። እዚያው እያሉ አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነገረውን ምሥራች ሰምተው ተቀበሉ። ስለ አዲሱ እምነታቸው ተጨማሪ እውቀት ለመቅሰም ስለጓጉ በኢየሩሳሌም ከረሙ። የያዙት ስንቅ እያለቀ ቢሄድም ቁሳዊ ምቾት ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጠው ነገር ነበር። መሲሑን አግኝተዋል! ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ያላቸውን ቁሳዊ ነገር አካፍለዋቸው ስለነበር ‘በሐዋርያትም ትምህርትና በየጸሎቱም መትጋታቸውን’ ቀጠሉ።—ሥራ 2:42
ከጊዜ በኋላ አንዳንድ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ያለውን ጠቀሜታ ችላ ማለት ጀመሩ። (ዕብራውያን 10:23-25) ይህ የሆነበት ምክንያት ፍቅረ ነዋይ ተጠናውቷቸው ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የሚሆናቸውን ገንዘብ ለማግኘት ሲባክኑ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ችላ ብለው ሊሆን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስብሰባዎችን ቸል እንዳይሉ ወንድሞቹን ካበረታታ በኋላ እንዲህ በማለት ጻፈ:- “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፣ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ:- አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና።”—ዕብራውያን 13:5
ጳውሎስ የሰጠው ምክር በጣም ወቅታዊ ነበር። ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች ደብዳቤውን ከጻፈ ከአምስት ዓመት አካባቢ በኋላ በሴስቲየስ ጋለስ ይመራ የነበረው የሮማ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከበበ። የታመኑ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ አስታውሰዋል:- “[ይህን] ብታዩ፣ . . . በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፣ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።” (ማርቆስ 13:14-16) በሕይወት መትረፋቸው የተመካው ባላቸው ቋሚ ሥራ ወይም ባካበቱት ቁሳዊ ሃብት ሳይሆን ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ በመታዘዛቸው ላይ መሆኑን ያውቁ ነበር። ጳውሎስ ለሰጠው ምክር አዎንታዊ ምላሽ የሰጡና መንፈሳዊ ጉዳዮችን ያስቀደሙ ሁሉ የገንዘብ ፍቅር ከነበራቸው ሰዎች ይልቅ ቤታቸውን፣ ሥራቸውን፣ ልብሳቸውንና ጥረው ግረው ያካበቱትን ሃብት ትተው ለመሄድና ወደ ተራራዎች ለመሸሽ ቀላል እንደሆነላቸው ምንም አይካድም።
በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች መቅደም ያለባቸውን ነገሮች ያስቀደሙት እንዴት ነው?
በዛሬው ጊዜ ያሉ ታማኝ ክርስቲያኖች ከወንድሞቻቸው ጋር ዘወትር አንድ ላይ መሆንን ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱት በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ሲሉ ብዙዎቹ በርካታ ነገሮችን ይሠዋሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ተቀጥረው የሚሠሩት በፈረቃ በሚሠራባቸው መሥሪያ ቤቶች ሊሆን ይችላል። አንድ ወንድም ስብሰባ ባለው ቀን የሥራ ባልደረቦቹ ተክተውት እንዲሠሩለት ለማድረግ በአካባቢው ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ለመዝናኛ በሚመርጡት ቅዳሜ ምሽት ተክቷቸው ይሠራል። በፈረቃ የሚሠሩ ሌሎች ወንድሞች የሥራ ጠባያቸው በራሳቸው የጉባኤ ስብሰባ እንዳይገኙ እንቅፋት የሚሆንባቸው ከሆነ አቅራቢያቸው በሚገኝ ሌላ ጉባኤ ይሰበሰባሉ። እንዲህ እያደረጉ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ይገኛሉ። በካናዳ የምትኖር ፍላጎት ያሳየች አንዲት ሴት ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጡ ወዲያው ተገነዘበች። ይሁን እንጂ የሥራ ሰዓቷ ከስብሰባው ሰዓት ጋር የሚጋጭ ነበር። ስለዚህም ጠቃሚ በሆኑት በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ስትል ለአንዲት የሥራ ባልደረባዋ ገንዘብ በመክፈል እርሷን ተክታ እንድትሠራ አደረገች።
ሥር የሰደደ ሕመም ያለባቸው በርካታ ሰዎች እንኳ አዘውትረው በስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። ወደ መንግሥት አዳራሹ መሄድ በማይችሉበት ጊዜ ቤታቸው ሆነው ከመንግሥት አዳራሹ ጋር በተያያዘ የስልክ መስመር አማካኝነት ስብሰባውን ይከታተላሉ ወይም በቴፕ አስቀድተው ያዳምጣሉ። ይሖዋ በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል ለሚያቀርበው መንፈሳዊ ዝግጅት ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸው ያሳያሉ! (ማቴዎስ 24:45) በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን የሚንከባከቡ ክርስቲያኖች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ይችሉ ዘንድ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ወላጆቻቸውን ቢጠብቁላቸው አመስጋኞች ናቸው።
አስቀድማችሁ እቅድ አውጡ!
ለመንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸው ንቁ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አድናቆት እንዲኖራቸው ይረዷቸዋል። ልጆቻቸው ትምህርት ቤት የሚሰጣቸውን የቤት ሥራ ዛሬ ነገ እያሉ ከመቆለል ይልቅ በወቅቱ እንዲሠሩ ያደርጋሉ። ልጆቹ ከትምህርት ቤት እንደተመለሱ ምሽት ላይ የሚደረገው የስብሰባ ሰዓት ከመድረሱ በፊት የቤት ሥራቸውን ይሠራሉ። በትርፍ ጊዜ የሚሠሩ ሥራዎችና ሌሎች እንቅስቃሴዎች በጉባኤ ስብሰባ ላይ እንዳይገኙ እንቅፋት ሊሆኑባቸው አይገባም።
ባለትዳርና የልጆች አባት እንደመሆንህ መጠን ለስብሰባዎች ቀዳሚውን ቦታ ትሰጣለህን? የቤት እመቤት ከሆንሽ ከስብሰባ ላለመቅረት ስትዪ ጉዳዮችሽን ቀደም ብለሽ ታጠናቅቂያለሽ? ልጅ ከሆንክ የመጀመሪያውን ቦታ የምትሰጠው ለቤት ሥራህ ነው ወይስ ለስብሰባዎች?
የጉባኤ ስብሰባ የይሖዋ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው። በዚህ ዝግጅት ለመጠቀም ማንኛውም ጥረት መደረግ ይኖርበታል። ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ የምትሰጡ ከሆነ ይሖዋ አብዝቶ ይባርካችኋል!