የይሖዋን ታላቅ ስም አክብሩ
“ስምህንም ለዘላለም አከብራለሁ።” —መዝ. 86:12
1, 2. የይሖዋ ምሥክሮች ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በተለየ መልኩ ለአምላክ ስም ምን አመለካከት አላቸው?
በጥቅሉ ሲታይ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በአምላክ ስም ለመጠቀም አሻፈረን ብለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርዥን የተሰኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በመቅድሙ ላይ እንዲህ ይላል፦ “ብቸኛ የሆነውን አምላክ . . . በተጸውኦ ስም መጥራት ለዓለም አቀፉ የክርስትና እምነት ፈጽሞ ተገቢ አይደለም።”
2 በአንጻሩ ግን የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ስም መሸከምና ማክበር በመቻላቸው ኩራት ይሰማቸዋል። (መዝሙር 86:12ን እና ኢሳይያስ 43:10ን አንብብ።) በተጨማሪም የስሙን ትርጉም እንዲሁም ከስሙ ቅድስና ጋር በተያያዘ በአጽናፈ ዓለም ደረጃ የተነሳውን አከራካሪ ጉዳይ ማወቅ መቻላችን ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማናል። (ማቴ. 6:9) ይህን መብታችንን አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። በመሆኑም የሚከተሉትን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሦስት ጥያቄዎች መመርመራችን ተገቢ ነው፦ የአምላክን ስም ማወቅ ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋ እንደ ታላቅ ስሙ መሆኑን ያሳየው ብሎም ስሙን ይበልጥ ክብር ያጎናጸፈው እንዴት ነው? በይሖዋ ስም መሄድ የምንችለውስ እንዴት ነው?
የአምላክን ስም ማወቅ ሲባል ምን ማለት ነው?
3. የአምላክን ስም ማወቅ ሲባል ምን ማለት ነው?
3 የአምላክን ስም ማወቅ “ይሖዋ” የሚለውን ቃል ከማወቅ ያለፈ ነገር ይጠይቃል። ይሖዋ ያተረፈውን ስም እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን ባሕርያቱን፣ ዓላማውንና አገልጋዮቹን የያዘበትን መንገድ ጨምሮ ያከናወናቸውን ነገሮች ማወቅን ያካትታል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ይህን ጥልቅ ማስተዋል የሚሰጠው ከዓላማው አፈጻጸም ጋር በሚስማማ መንገድ ደረጃ በደረጃ ነው። (ምሳሌ 4:18) ይሖዋ ስሙን ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ገልጦላቸዋል፤ በመሆኑም ሔዋን ቃየንን ከወለደች በኋላ በዚህ ስም ተጠቅማለች። (ዘፍ. 4:1 NW) ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የነበሩት ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ የአምላክን ስም ያውቁ ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ ሲባርካቸው፣ ሲንከባከባቸውና ከእነሱ ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ ሲገልጽላቸው ስለ ስሙ ያላቸው ግንዛቤ እያደገ ሄዷል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሙሴ ከአምላክ ስም ጋር በተያያዘ ጥልቅ ማስተዋል አግኝቷል።
4. ሙሴ አምላክን ስለ ስሙ የጠየቀው ለምንድን ነው? ሙሴ መጨነቁ አያስገርምም ሊባል የሚችለውስ ለምንድን ነው?
4 ዘፀአት 3:10-15ን አንብብ። ሙሴ 80 ዓመት በሆነው ጊዜ አምላክ ‘ሕዝቡን የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር እንዲያወጣቸው’ ከባድ ኃላፊነት ሰጠው። ሙሴም በምላሹ አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ ልዩ ትርጉም ያዘለ ጥያቄ አቅርቧል። ሙሴ ‘ስምህ ማን ነው?’ ብሎ የጠየቀ ያህል ነበር። የአምላክ ስም ለረጅም ጊዜ ይታወቅ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ሙሴ ይህን ጥያቄ የጠየቀው ለምን ነበር? ሙሴ ስሙ የሚወክለውን አካል በተመለከተ ይበልጥ ማወቅ ፈልጎ እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ በሌላ አነጋገር ሕዝቡ አምላክ ነፃ እንደሚያወጣቸው አምነው እንዲቀበሉ የሚያደርግ መረጃ ማቅረብ ፈልጎ ነበር። እስራኤላውያን በባርነት መገዛት ከጀመሩ በርካታ ዓመታት ተቆጥረው ስለነበር ሙሴ ይህን ያህል መጨነቁ ምንም አያስገርምም። እስራኤላውያን የአባቶቻቸው አምላክ ሊያድናቸው ይችል እንደሆነ ጥርጣሬ ሊያድርባቸው እንደሚችል መገመት አያዳግትም። እንዲያውም አንዳንድ እስራኤላውያን የግብፃውያንን አማልክት እስከ ማምለክ ደርሰው ነበር!—ሕዝ. 20:7, 8
5. ይሖዋ ለሙሴ በሰጠው መልስ ላይ የስሙን ትርጉም በተመለከተ ተጨማሪ ብርሃን የፈነጠቀው እንዴት ነው?
5 ይሖዋ ሙሴ ላነሳው ጥያቄ የሰጠው መልስ ምን ነበር? ይሖዋ “እስራኤላውያንን ‘“እሆናለሁ” የሚል ስም ያለው ወደ እናንተ ልኮኛል’ በላቸው” (NW) የሚል መልስ ሰጥቶታል።a አክሎም ‘የአባቶቻችሁ አምላክ የሆነው ይሖዋ ወደ እናንተ ልኮኛል’ እንዲላቸው ነገረው። አምላክ ዓላማውን ዳር ለማድረስ መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ መሆን እንደሚችል ማለትም ምንጊዜም የገባውን ቃል እንደሚጠብቅ ነገረው። በመሆኑም በቁጥር 15 ላይ ይሖዋ ራሱ “ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤ ወደፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው” ብሏል። እነዚህ ቃላት የሙሴን እምነት በእጅጉ እንዳጠነከሩት ብሎም በአክብሮትና በአድናቆት ስሜት እንዲዋጥ እንዳደረጉት ጥርጥር የለውም!
ይሖዋ እንደ ስሙ መሆኑን አሳይቷል
6, 7. ይሖዋ እንደ ታላቅ ስሙ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ ለሙሴ ተልእኮውን ከሰጠው በኋላ ብዙም ሳይቆይ የእስራኤላውያን ነፃ አውጪ ‘በመሆን’ እንደ ስሙ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። አሥር አውዳሚ መቅሰፍቶችን በማምጣት ግብፅን ያዋረደ ከመሆኑም ሌላ ፈርዖንን ጨምሮ የግብፃውያን አማልክት አቅመ ቢስ እንደሆኑ አሳይቷል። (ዘፀ. 12:12) ከዚያም ይሖዋ ቀይ ባሕርን በመክፈል እስራኤላውያን በመካከሉ እንዲያልፉ ካደረገ በኋላ ፈርዖንን ከነሠራዊቱ አሰጠመው። (መዝ. 136:13-15) ይሖዋ “ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ” ውስጥ ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱትን ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑትን ሕዝቡን ምግብና ውኃ በማቅረብ ሕይወታቸውን የሚጠብቅ አምላክ መሆኑን አሳይቷል! ልብሳቸውና ጫማቸው እንኳ እንዳያልቅ አድርጓል። (ዘዳ. 1:19፤ 29:5) አዎ፣ ይሖዋ አቻ ከሌለው ስሙ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ቃሉን ከመፈጸም ሊያግደው የሚችል ነገር የለም። ከጊዜ በኋላ ኢሳይያስን ‘እኔ፣ እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም’ ብሎታል።—ኢሳ. 43:11
7 በሙሴ እግር የተተካው ኢያሱም ቢሆን ይሖዋ በግብፅና በምድረ በዳ ያከናወናቸውን እጅግ አስደናቂ የሆኑ ነገሮች ተመልክቷል። ስለሆነም ኢያሱ በሕይወቱ ማብቂያ ላይ ለእስራኤላውያን በልበ ሙሉነት እንደሚከተለው ማለት ችሏል፦ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።” (ኢያሱ 23:14) አዎ፣ ይሖዋ ምንም በማያወላዳ መልኩ ቃሉን በመፈጸም ‘መሆን የሚያስፈልገውን ሆኗል።’
8. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እንደ ስሙ መሆኑን እያሳየ ያለው እንዴት ነው?
8 ዛሬም ይሖዋ የገባውን ቃል በመፈጸም ላይ ይገኛል። በመጨረሻዎቹ ቀናት የመንግሥቱ መልእክት “በመላው ምድር” እንደሚሰበክ በልጁ አማካኝነት አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴ. 24:14) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ካልሆነ በስተቀር ስለዚህ ሥራ አስቀድሞ መናገር፣ ትንቢቱ እንዲፈጸም ማድረግና “ያልተማሩ ተራ” ሰዎችን በመጠቀም ይህን ሥራ ማከናወን የሚችል ማን ሊኖር ይችላል? (ሥራ 4:13) በመሆኑም በዚህ ሥራ ስንካፈል የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው ማለት ይቻላል። እንዲህ ስናደርግ አባታችንን የምናከብር ከመሆኑም ሌላ “ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ብለን የምናቀርበው ጸሎት ከልብ የመነጨ መሆኑን እናሳያለን።—ማቴ. 6:9, 10
ስሙ ታላቅ ነው
9, 10. ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት የስሙን ትርጉም ይበልጥ ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?
9 እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ሌላ ሚና በመጫወት ሕዝቡ ስለ እሱ ተጨማሪ ግንዛቤ እንዲያገኙ አድርጓል። በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት ‘ባለቤታቸው’ ሆኗል፤ ይህ ሚና የሚያስከትለውን ኃላፊነት ሁሉ ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኖ ነበር። (ኤር. 3:14) እስራኤላውያንም ምሳሌያዊ ሚስቱ ማለትም በስሙ የሚጠሩ ሕዝቡ ሆኑ። (ኢሳ. 54:5, 6) በፈቃደኝነት ለእሱ ሲገዙና ትእዛዙን ሲያከብሩ ፍጹም ‘ባል’ ይሆንላቸው ነበር። ይባርካቸው፣ ይጠብቃቸውና ሰላም ይሰጣቸው ነበር። (ዘኍ. 6:22-27) በመሆኑም የይሖዋ ታላቅ ስም በብሔራት መካከል ይከበር ነበር። (ዘዳግም 4:5-8ን እና መዝሙር 86:7-10ን አንብብ።) በእርግጥም በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ በርካታ መጻተኞች እውነተኛውን አምልኮ ተቀላቅለዋል። እነዚህ መጻተኞች ሞዓባዊቷ ሩት ለኑኃሚን “ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል” በማለት የተናገረችውን ቃል ያስተጋቡ ያህል ነው።—ሩት 1:16
10 ይሖዋ ለ1,500 ዓመታት ገደማ ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት ማንነቱን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ በርካታ ባሕርያቱን ገልጧል። ብሔሩ ዓመፀኛ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ በተደጋጋሚ ጊዜያት “ሩኅሩኅ” እንዲሁም “ለቍጣ የዘገየ” አምላክ መሆኑን አሳይቷል። እጅግ ታጋሽና ቻይ አምላክ ነበር። (ዘፀ. 34:5-7) ይሁንና የይሖዋ ትዕግሥት ገደብ አለው፤ በመሆኑም የአይሁድ ብሔር ልጁን አንቀበልም ብለው በገደሉት ጊዜ ትዕግሥቱ አለቀ። (ማቴ. 23:37, 38) ሥጋዊ እስራኤላውያን በአምላክ ስም የሚጠሩ ሕዝቦች መሆናቸው አከተመ። በጥቅሉ ሲታይ እንደ ደረቀ ዛፍ በመንፈሳዊ በድን ሆኑ። (ሉቃስ 23:31) ይህ ሁኔታ ለመለኮታዊው ስም ባላቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?
11. የአይሁድ ብሔር በአምላክ ስም መጠቀም ያቆመው እንዴት ነው?
11 ታሪክ እንደሚያሳየው አይሁዳውያን ከጊዜ በኋላ የአምላክን ስም መጥራት እንደማይገባቸው አድርገው በማሰብ ከአምላክ ስም ጋር በተያያዘ አጉል እምነት መከተል ጀመሩ። (ዘፀ. 20:7) በመሆኑም አይሁዳውያን ቀስ በቀስ የአምላክን ስም ጨርሶ መጥራት አቆሙ። ለስሙ አክብሮት ማጣታቸው ይሖዋን አሳዝኖት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 78:40, 41) ይሁንና “ስሙ ቀናተኛ የሆነው” አምላክ እሱን ከካዱና እሱም ከካዳቸው ሰዎች ጋር ስሙ ለዘላለም ተቆራኝቶ እንዲኖር እንደማይፈቅድ የታወቀ ነው። (ዘፀ. 34:14) ይህን ማወቃችን የፈጣሪያችንን ስም በታላቅ አክብሮት ልንጠቀምበት እንደሚገባ ያስገነዝበናል።
በአምላክ ስም የተጠራ አዲስ ሕዝብ
12. ይሖዋ ትንቢት የተነገረለትን በስሙ የሚጠራ ሕዝብ ያቋቋመው እንዴት ነው?
12 ይሖዋ ከአዲስ ብሔር ማለትም ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር “አዲስ ቃል ኪዳን” ለመግባት ያለውን ዓላማ በኤርምያስ በኩል አስታውቆ ነበር። ኤርምያስ የዚህ ብሔር አባላት ‘ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ፣ ሁሉም ይሖዋን እንደሚያውቁ’ አስቀድሞ ተናግሯል። (ኤር. 31:31, 33, 34) ይህ ትንቢት አምላክ አዲሱን ቃል ኪዳን ባቋቋመበት በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት መፈጸም ጀምሯል። አይሁዳውያንንም ሆነ አይሁዳውያን ያልሆኑትን ያቀፈው የአዲሱ ብሔር ይኸውም ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት “[ለአምላክ ስም] የሚሆኑ ሰዎች” ተብለው ተጠርተዋል፤ ይሖዋም ‘በስሜ የተጠሩ’ በማለት ገልጿቸዋል።—ገላ. 6:16፤ የሐዋርያት ሥራ 15:14-17ን አንብብ፤ ማቴ. 21:43
13. (ሀ) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በአምላክ ስም ይጠቀሙ ነበር? አብራራ። (ለ) በአገልግሎት የይሖዋን ስም የመጠቀም መብትህን እንዴት ትመለከተዋለህ?
13 የዚህ መንፈሳዊ ብሔር አባላት ‘በአምላክ ስም የተጠሩ’ እንደመሆናቸው መጠን በመለኮታዊው ስም ይጠቀሙ ነበር፤ ለምሳሌ ያህል ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ሲጠቅሱ ይህን ያደርጉ እንደነበር የታወቀ ነው።b በመሆኑም ሐዋርያው ጴጥሮስ በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ከተለያየ ቦታ ለመጡ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ንግግር ሲያቀርብ የአምላክን ስም በተደጋጋሚ ጊዜ ጠቅሷል። (ሥራ 2:14, 20, 21, 25, 34) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይሖዋን አክብረዋል፤ እሱም በስብከቱ ሥራ የሚያደርጉትን ጥረት ባርኮላቸዋል። ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋን ስም በልበ ሙሉነት ስናውጅና ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ከተቻለ በራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ስሙን ስናሳያቸው ይሖዋ አገልግሎታችንን ይባርክልናል። በዚህ መንገድ እውነተኛውን አምላክ እንዲያውቁ እንረዳቸዋለን። ይህ ለእነሱም ሆነ ለእኛ እንዴት ያለ መብት ነው! አንድ ሰው በዚህ ሁኔታ እውነተኛውን አምላክ ሲያውቅ ከይሖዋ ጋር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚሄድና ለዘላለም የሚዘልቅ ጥሩ ዝምድና ሊመሠርት ይችላል።
14, 15. ክህደት ቢስፋፋም እንኳ ይሖዋ ከሚታወስበት ስሙ ጋር በተያያዘ ምን ነገር አድርጓል?
14 ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ በተለይ ደግሞ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ክህደት መስፋፋት ጀመረ። (2 ተሰ. 2:3-7) እንዲያውም የሐሰት አስተማሪዎች የአምላክን ስም መጠቀም ተገቢ አይደለም የሚለውን የአይሁዳውያን ወግ መከተል ጀመሩ። ይሁንና ይሖዋ የሚታሰብበት ስሙ ጨርሶ እንዲጠፋ ይፈቅዳል? በፍጹም! እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ ትክክለኛ አጠራሩን አናውቀው ይሆናል፤ ይሁንና ስሙ ጸንቶ ኖሯል። ባለፉት ዘመናት የአምላክ ስም በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችና አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ባዘጋጇቸው ጽሑፎች ላይ ተጠቅሷል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1757 ቻርልስ ፔተርስ “ይሖዋ” የሚለው ስም ከሌሎች በርካታ የአምላክ የማዕረግ ስሞች ጋር ሲነጻጸር “ማንነቱን ከሁሉ በተሻለ ሁኔታ የሚገልጽ” ስም ነው በማለት ጽፏል። በ1797 ሆፕተን ሄይንዝ የአምላክን አምልኮ በተመለከተ በጻፈው መጽሐፍ 7ኛ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ “ይሖዋ፣ አይሁዳውያን የሚጠቀሙበት የአምላክ የተጸውኦ ስም ሲሆን አይሁዳውያንም ሆኑ ክርስቶስና ሐዋርያቱ እሱን ብቻ ያመልኩ ነበር” ሲል ገልጿል። ሄንሪ ግሩ (1781-1862) በአምላክ ስም ከመጠቀሙም በላይ ስሙ ነቀፋ እንደደረሰበትና መቀደስ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። በተመሳሳይም የቻርልስ ቴዝ ራስል የቅርብ አጋር የነበረው ጆርጅ ስቶርዝ (1796-1879) ራስል ያደርግ እንደነበረው በአምላክ ስም ይጠቀም ነበር።
15 በአምላክ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ 1931 ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ዓመት ነው፤ ምክንያቱም በወቅቱ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን የይሖዋ ምሥክሮች የሚል ስያሜ ያገኙት በዚህ ዓመት ነበር። (ኢሳ. 43:10-12) በዚህ ስያሜ በመጠራት፣ ብቸኛ የሆነው እውነተኛ አምላክ አገልጋዮች ይኸውም “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች” ለመባል በመብቃታቸውና ስሙን ማወደስ በመቻላቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ለዓለም አሳውቀዋል። (ሥራ 15:14) እነዚህ ክንውኖች ይሖዋ በሚልክያስ 1:11 ላይ “ከፀሓይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ፣ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ያስታውሱናል።
በይሖዋ ስም መሄድ
16. በይሖዋ ስም መሄድ መቻላችንን እንደ ትልቅ ክብር ልናየው የሚገባን ለምንድን ነው?
16 ነቢዩ ሚክያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አሕዛብ ሁሉ፣ በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።” (ሚክ. 4:5) ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በስሙ እንዲጠሩ መፍቀዱ ታላቅ ክብር ከመሆኑም በላይ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኙ የሚያሳይ ማረጋገጫ ነበር። (ሚልክያስ 3:16-18ን አንብብ።) አንተስ በበኩልህ ምን ይሰማሃል? ‘በይሖዋ ስም ለመሄድ’ የተቻለህን ሁሉ ጥረት እያደረግክ ነው? ይህ ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ተገንዝበሃል?
17. በአምላክ ስም ለመሄድ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
17 በአምላክ ስም ለመሄድ ቢያንስ ሦስት ነገሮች ማድረግ ያስፈልገናል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ‘የሚድኑት የይሖዋን ስም የሚጠሩ’ ብቻ እንደሆኑ በመገንዘብ ስሙን ለሌሎች ማወጅ ይኖርብናል። (ሮም 10:13) በሁለተኛ ደረጃ፣ የይሖዋን ባሕርያት በተለይ ፍቅሩን ማንጸባረቅ አለብን። (1 ዮሐ. 4:8) በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ለጽድቅ መሥፈርቶቹ በደስታ የምንገዛ ከሆነ በአምላክ ስም እንሄዳለን፤ አለዚያ የአባታችንን ቅዱስ ስም እናስነቅፋለን። (1 ዮሐ. 5:3) “በይሖዋ ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም” ለመሄድ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?
18. የይሖዋን ታላቅ ስም የሚያከብሩ ሁሉ የወደፊቱን ጊዜ በእምነት መጠባበቅ የሚችሉት ለምንድን ነው?
18 ይሖዋን ችላ የሚሉ ወይም በእሱ ላይ የሚያምፁ ሰዎች ሁሉ በቅርቡ ማንነቱን ለማወቅ ይገደዳሉ። (ሕዝ. 38:23) ከእነዚህም መካከል፣ ‘እታዘዘው ዘንድ ለመሆኑ ይሖዋ ማነው?’ ሲል እንደተናገረው እንደ ፈርዖን ያሉ ሰዎች ይገኙበታል። ፈርዖን ብዙም ሳይቆይ የይሖዋን ማንነት ለማወቅ ተገዷል! (ዘፀ. 5:1, 2፤ 9:16፤ 12:29) እኛ ግን በገዛ ፈቃዳችን ይሖዋን አውቀነዋል። ስሙን በመሸከማችንና በስሙ የምንጠራ ታዛዥ ሕዝቡ በመሆናችን ኩራት ይሰማናል። በመሆኑም በመዝሙር 9:10 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው በሚከተለው ተስፋ በመተማመን የወደፊቱን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን፦ “ስምህን የሚያውቁ ይታመኑብሃል፤ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ የሚሹህን አትተዋቸውምና።”
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የአምላክ ስም “መሆን” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ግስ የተገኘ ነው። በመሆኑም “ይሖዋ” የሚለው ስም “ይሆናል” የሚል ትርጉም አለው።—ዘፍ. 2:4 ባለማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ
b የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይጠቀሙበት የነበረው የዕብራይስጥ ጽሑፍ መለኮታዊው ስም የሚጻፍባቸውን አራት የዕብራይስጥ ፊደላት የያዘ ነበር። በተጨማሪም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ግሪክኛ ትርጉም ማለትም የሰብዓ ሊቃናት ጥንታዊ ቅጂዎች የይሖዋን ስም የያዙ እንደነበሩ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።