በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው በዓላት
“በዓመት ሦስት ጊዜ . . . ወንዶችህ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እርሱ በመረጠው ስፍራ ይታዩ። በእግዚአብሔርም ፊት ባዶ እጃቸውን አይታዩ።” —ዘዳግም 16:16
1. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይከበሩ ስለነበሩ በዓላት ምን ማለት ይቻላል?
ስለ በዓል በሚነሳበት ጊዜ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? በጥንት ዘመን ይከበሩ በነበሩ አንዳንድ በዓላት ላይ ሰዎች አለመጠን ይበሉና ይጠጡ፣ እንዲሁም ብዙ ብልግና ይፈጽሙ ነበር። በዘመናችን በሚደረጉ አንዳንድ በዓሎች ላይም እንደነዚህ ያሉ ድርጊቶች ይፈጸማሉ። አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ውስጥ የታዘዙት በዓላት ግን ከእነዚህ የተለዩ ነበሩ። የበዓሎቹ አክባሪዎች የሚደሰቱባቸው ወቅቶች ቢሆኑም “የተቀደሰ ጉባኤ” ተብለው ሊጠሩ የሚችሉ ነበሩ።—ዘሌዋውያን 23:2
2. (ሀ) እስራኤላውያን ወንዶች በየዓመቱ ሦስት ጊዜ ምን እንዲያደርጉ ይፈለግባቸው ነበር? (ለ) በዘዳግም 16:16 መሠረት “በዓል” ምንድን ነው?
2 እስራኤላውያን ወንዶች፣ አብዛኛውን ጊዜ በቤተሰቦቻቸው ታጅበው ሦስት ታላላቅ በዓሎችን ለማክበር ‘ይሖዋ ወደ መረጠው ሥፍራ’ ወደ ኢየሩሳሌም በሚጓዙበት ጊዜ በጣም ከመደሰታቸውም በተጨማሪ ለበዓሎቹ የሚያስፈልገውን በቸርነት ይለግሱ ነበር። (ዘዳግም 16:16) ኦልድ ቴስታመንት ወርድ ስተዲስ የተባለው መጽሐፍ በዘዳግም 16:16 ላይ “በዓል” ተብሎ ለተተረጎመው ቃል “በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ የአምላክ ሞገስ የታዩባቸው ሁኔታዎች፣ መሥዋዕት በማቅረብና ግብዣ በማድረግ የሚከበርበት . . . የደስታ ወቅት” የሚል ፍቺ ይሰጣል።a
ታላላቆቹ በዓላት ያስገኟቸው ጥቅሞች
3. ሦስቱ ዓመታዊ በዓላት የትኞቹን በረከቶች ያስታውሱናል?
3 የእስራኤል ማኅበረሰብ በግብርና የሚተዳደር ስለነበረ ሕልውናቸው አምላክ በሚሰጣቸው ዝናብ ላይ የተመካ ነበር። በሙሴ ሕግ ውስጥ የታዘዙት ሦስት ትላልቅ በዓላት በጸደይ ወራት መጀመሪያ ላይ ከሚከናወነው የገብስ መከር፣ በጸደይ ወራት መጨረሻ ላይ ከሚከናወነው የስንዴ መከር እንዲሁም በበጋው ወራት መገባደጃ ላይ ከሚከናወነው የመጨረሻ መከር ጋር ይጋጠሙ ነበር። እነዚህ ወቅቶች እስራኤላውያን በጣም የሚደሰቱባቸውና የዝናብ ዑደት እንዳይቋረጥ ለሚያደርገውና ምርት የምታስገኝላቸውን ምድር ለፈጠረው አምላካቸው ያላቸውን አመስጋኝነት የሚገልጹባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሁን እንጂ የበዓሎቹ ዓላማ ይህ ብቻ አልነበረም።—ዘዳግም 11:11-14
4. በመጀመሪያው በዓል የተከበረው የትኛው ታሪካዊ ክንውን ነበር?
4 የመጀመሪያው በዓል ይደረግ የነበረው በጥንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቀን አቆጣጠር የመጀመሪያ ወር በሆነው በኒሳን 15 እስከ 21 ሲሆን በእኛ አቆጣጠር ከመጋቢት መጨረሻ እስከ ሚያዝያ መጀመሪያ ባለው ጊዜ ነበር። በዓሉ የቂጣ በዓል ተብሎ የሚጠራ ከመሆኑም በተጨማሪ ኒሳን 14 ቀን ከሚከበረው የማለፍ በዓል ቀጥሎ የሚከበር ስለሆነ “የማለፍ በዓል” ተብሎም ይጠራል። (ሉቃስ 2:41፤ ዘሌዋውያን 23:5, 6) ይህ በዓል እስራኤላውያን በግብጽ ይደርስባቸው የነበረውን መከራ ያስታውሳቸው ነበር። የሚበሉት ቂጣ “የመከራ እንጀራ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዘዳግም 16:3) ከግብጽ የወጡት በጣም ተጣድፈው ስለነበረ ሊጣቸው ውስጥ እርሾ ለመጨመርና እስኪቦካ ድረስ ለመጠበቅ የሚበቃ ጊዜ እንዳልነበረ ያስታውሳቸው ነበር። (ዘጸአት 12:34) ይህ በዓል በሚከበርበት ጊዜ በማንም እስራኤላዊ ቤት ውስጥ የቦካ እንጀራ መገኘት አልነበረበትም። ማንኛውም በዓል አክባሪ፣ መጻተኛም ጭምር የቦካ እንጀራ ቢበላ በሞት ይቀጣ ነበር።—ዘጸአት 12:19
5. ሁለተኛው በዓል የትኛው መብት እንዲታወስ ሊያደርግ ይችላል? በዚህ ደስታስ እነማን ጭምር መካፈል ነበረባቸው?
5 ሁለተኛው በዓል ይከበር የነበረው ከኒሳን 16 ሰባት ሳምንት (49 ቀን) ቆይቶ ሲሆን ሦስተኛ ወር በሆነው በሲቫን 6ኛ ቀን ወይም በእኛ አቆጣጠር በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ የሚውል ነበር። (ዘሌዋውያን 23:15, 16) በዓሉ የሳምንታት በዓል ተብሎ የሚጠራ ሲሆን (በኢየሱስ ዘመን ጰንጠቆስጤ ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን በግሪክኛ “ሃምሳኛ” ማለት ነው) የእስራኤል ብሔር በሲና ተራራ የሕግ ቃል ኪዳን በገባበት ጊዜ አካባቢ ይከበር ነበር። (ዘጸአት 19:1, 2) በዚህ በዓል ላይ ታማኝ እስራኤላውያን የአምላክ ቅዱስ ብሔር ሆነው በመለየት ስላገኙት ታላቅ መብት ሊያሰላስሉ ይችሉ ነበር። የአምላክ ልዩ ሕዝቦች መሆናቸው ችግረኞች ጭምር በበዓሉ እንዲደሰቱ ቸርነት ማድረግን የሚጨምረውን የአምላክ ሕግ እንዲታዘዙ ይጠይቅባቸው ነበር።—ዘሌዋውያን 23:22፤ ዘዳግም 16:10-12
6. ሦስተኛው በዓል የአምላክ ሕዝቦች የትኛውን ተሞክሮ እንዲያስታውሱ ያደርጋቸው ነበር?
6 ከሦስቱ ታላላቅ በዓላት የመጨረሻው የመሰብሰቢያ በዓል ወይም የዳስ በዓል ተብሎ ይጠራ ነበር። ቲሽሪ ወይም ኢታኒም ይባል በነበረው ሰባተኛ ወር ከ15ኛው እስከ 21ኛው ቀን የሚውል ሲሆን ከእኛ የጥቅምት ወር መጀመሪያ ጋር አንድ ነው። (ዘሌዋውያን 23:34) በዚህ ወቅት የአምላክ ሕዝቦች ከቤታቸው ውጭ ወይም በጣሪያቸው ላይ ከዛፍ ቅርንጫፎችና ቅጠሎች በተሠሩ ዳሶች ውስጥ ይቀመጡ ነበር። ይህም እስራኤላውያን በየዕለቱ ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች በአምላክ መታመንን የተማሩባቸውንና ከግብጽ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመድረስ በጉዞ ያሳለፏቸውን 40 ዓመታት ያስታውሳቸው ነበር።—ዘሌዋውያን 23:42, 43፤ ዘዳግም 8:15, 16
7. በጥንት እስራኤል የተደረጉትን በዓላት አከባበር መለስ ብለን መመልከታችን ምን ጥቅም ይሰጠናል?
7 በአምላክ የጥንት ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የተሰጣቸውን አንዳንድ በዓላት መለስ ብለን እንመልከት። ይህን ማድረጋችን በዛሬው ጊዜ የምንኖረውን ሊያጽናናን ይገባል። ምክንያቱም እኛም ዘወትር በየሳምንቱና በዓመት ሦስት ጊዜ በትላልቅ ስብሰባዎች እንድንገኝ ተጋብዘናል።—ዕብራውያን 10:24, 25
የዳዊት ተወላጆች በሆኑ ነገሥታት ዘመን
8. (ሀ) በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ምን ታሪካዊ በዓል ተደርጎ ነበር? (ለ) በጉጉት የምንጠብቀው የትኛውን የእውነተኛው የዳስ በዓል ታላቅ ፍጻሜ ነው?
8 እስራኤላውያን በጣም በልጽገው በነበረበት በዳዊት ልጅ በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን በጣም ታሪካዊ የሆነ የዳስ በዓል ተከብሯል። ከተስፋይቱ ምድር አራት ማዕዘናት የመጣ “እጅግ ታላቅ ጉባኤ” ቤተ መቅደሱ ለይሖዋ አገልግሎት በሚወሰንበት ሥነ ሥርዓትና በዳስ በዓል ላይ ተገኝቶ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 7:8) በዓሉ ከተፈጸመ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን በዚያ የተገኙትን በዓል አክባሪዎች በሙሉ ሲያሰናብት “እነርሱም ንጉሡን መረቁ፣ እግዚአብሔርም ለባሪያው ለዳዊትና ለሕዝቡ ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ በልባቸው ተደስተው ሐሤትም አድርገው ወደ ስፍራቸው ሄዱ።” (1 ነገሥት 8:66) በእርግጥም ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው በዓል ነበር። ዛሬም ቢሆን የአምላክ አገልጋዮች በታላቁ ሰሎሞን በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ የሚሆነውን የእውነተኛው የዳስ በዓል ታላቅ ድምድማት በናፍቆት ይጠባበቃሉ። (ራእይ 20:3, 7-10, 14, 15) በዚያ ጊዜ በሁሉም የምድር ማዕዘናት የሚኖሩ ሰዎች፣ ከሙታን የሚነሱትና አርማጌዶንን በሕይወት የተሻገሩት ጭምር አስደሳች በሆነው የይሖዋ አምልኮ አንድ ይሆናሉ።—ዘካርያስ 14:16
9-11. (ሀ) በንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመን ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው በዓል እንዲደረግ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? (ለ) ከሰሜናዊው የአሥሩ ነገድ መንግሥት የመጡ ሰዎች እንዴት ያለ ጥሩ ምሳሌነት አሳይተዋል? ይህስ በዚህ ዘመን ለምንኖረው ምን ያሳስበናል?
9 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዚህ ቀጥሎ በግንባር ቀደምትነት የተጠቀሰው በዓል ቤተ መቅደሱን ከዘጋውና የይሁዳን መንግሥት ወደ ክህደት ከመራው ከንጉሥ አካዝ ዘመን በኋላ የተከበረው በዓል ነው። በአካዝ እግር የተተካው መልካሙ ንጉሥ ሕዝቅያስ ነበር። ሕዝቅያስ በ25 ዓመት ዕድሜው በዘመነ መንግሥቱ የመጀመሪያ ዓመት ታላቅ የሆነ የተሐድሶ ፕሮግራም ማካሄድ ጀመረ። ወዲያውኑ ቤተ መቅደሱን ከፈተና አስፈላጊው እድሳት በሙሉ እንዲደረግለት አዘዘ። ከዚያም ንጉሡ ባላጋራቸው በሆነው በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ይኖሩ ለነበሩ እስራኤላውያን ደብዳቤ ልኮ እንዲመጡና የማለፍንና የቂጣን በዓል እንዲያከብሩ ጋበዘ። ብዙዎቹ የወገኖቻቸውን ዘለፋ ከጉዳይ ሳይቆጥሩ ወደ በዓሉ መጡ።—2 ዜና መዋዕል 30:1, 10, 11, 18
10 ታዲያ በዓሉ የተሳካ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በኢየሩሳሌምም ተገኝተው የነበሩ የእስራኤል ልጆች የቂጣውን በዓል በታላቅ ደስታ ሰባት ቀን አደረጉ፤ ሌዋውያኑና ካህናቱም በዜማ ዕቃ ለእግዚአብሔር እየዘመሩ ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።” (2 ዜና መዋዕል 30:21) በዛሬው ጊዜ የሚደርስባቸውን ተቃውሞ በሙሉ አሸንፈውና ረዥም መንገድ ተጉዘው ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች እነዚህ እስራኤላውያን እንዴት ያለ ጥሩ ምሳሌ ትተዋል!
11 ለምሳሌ ያህል በ1989 በፖላንድ የተደረጉትን “ለአምላክ ማደር” የተባሉ ሦስት የአውራጃ ስብሰባዎች እንውሰድ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ከተገኙት 166,518 ሰዎች መካከል በወቅቱ ሥራው በእገዳ ሥር ከነበረባቸው ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረትና ከሌሎች የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች የመጡ በርካታ ወንድሞች ነበሩ። የይሖዋ ምሥክሮች፣ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎችb (የእንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ሪፖርት እንዳደረገው “በዚህ ስብሰባ ላይ ከተገኙት መካከል አንዳንዶቹ ከ15 ወይም ከ20 የሚበልጡ የይሖዋ ሕዝቦች በተሰበሰቡበት ሲገኙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር። በስታዲየሞቹ ውስጥ የተሰበሰቡትን በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲመለከቱ፣ እንዲሁም በአንድ ድምፅ የውዳሴ መዝሙር ሲያሰሙና አብረው ሲጸልዩ ልባቸው በታላቅ አድናቆት ተሞልቶ ነበር።”—ገጽ 279
12. በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን ለተከበረው ከፍተኛ በዓል ምክንያት የሆነው ምንድን ነው?
12 ሕዝቅያስ ከሞተ በኋላ አይሁዳውያን በምናሴና በአሞን ዘመነ መንግሥት ዳግመኛ በሐሰት አምልኮ ቀንበር ሥር ወደቁ። ከዚያ በኋላ ግን ኢዮስያስ የተባለ ጥሩ ንጉሥ ተነስቶ የድፍረት እርምጃዎች በመውሰድ እውነተኛውን አምልኮ መልሶ አቋቋመ። ኢዮስያስ በ25 ዓመት ዕድሜው ቤተ መቅደሱ እንዲታደስ አዘዘ። (2 ዜና መዋዕል 34:8) ጥገና በሚካሄድበት ጊዜ ሙሴ የጻፈው ሕግ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ተገኘ። የንጉሥ ኢዮስያስ ልብ በአምላክ ቃል ውስጥ ባነበበው ነገር በጣም ስለተነካ ለመላው ሕዝብ እንዲነበብ አደረገ። (2 ዜና መዋዕል 34:14, 30) ከዚያም የማለፍ በዓል በሕጉ ውስጥ በተጻፈው መሠረት የሚከበርበትን ዝግጅት አደረገ። በተጨማሪም ንጉሡ ለበዓሉ የሚያስፈልጉትን በልግስና በመስጠት ጥሩ ምሳሌ ሆነ። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ “ከነቢዩም ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልተደረገም” ይላል።—2 ዜና መዋዕል 35:7, 17, 18
13. ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ያደረጓቸው ታላላቅ በዓላት ምን ነገር ያሳስቡናል?
13 ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ያካሄዱት ተሐድሶ ኢየሱስ ክርስቶስ ከነገሠ ከ1914 ወዲህ በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ከተከናወነው የእውነተኛ አምልኮ ተሐድሶ ጋር ይመሳሰላል። ይህ በዘመናችን የተከናወነው ተሐድሶ በተለይ በኢዮስያስ ዘመን እንደተከናወነው ተሐድሶ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ነው። በተጨማሪም የዘመናችን ተሐድሶ አስደናቂ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በተብራሩባቸውና ወቅታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ሥራ ላይ እንደሚውሉ በተገለጹባቸው ትላልቅ ስብሰባዎች ተለይቶ የሚታወቅ በመሆኑ ከሕዝቅያስና ከኢዮስያስ ዘመን ጋር ይመሳሰላል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መጠመቃቸውም እነዚህን ትምህርታዊ ወቅቶች ይበልጥ አስደሳች አድርጓል። እነዚህ አዳዲስ ተጠማቂዎች በሕዝቅያስና በኢዮስያስ ዘመን እንደነበሩት ንሥሐ የገቡ እስራኤላውያን ለሕዝበ ክርስትናና ለቀረው የሰይጣን ዓለም ክፉ አድራጎቶች ጀርባቸውን ሰጥተዋል። በ1997 ከ375,000 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ለቅዱሱ አምላክ ለይሖዋ የወሰኑ መሆናቸውን ለማሳየት ተጠምቀዋል። በየቀኑ በአማካይ ከ1,000 የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀዋል ማለት ነው።
ከግዞት በኋላ
14. በ537 ከዘአበ ከፍተኛ በዓል የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው?
14 ኢዮስያስ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ብሔር እንደገና ወራዳ ወደሆነ የሐሰት አምልኮ ተመለሰ። በመጨረሻም በ607 ከዘአበ ይሖዋ የባቢሎናውያን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ እንዲዘምት በማድረግ ሕዝቡን ቀጣ። ከተማይቱና ቤተ መቅደስዋ ወደሙ፤ ምድሪቱም ባድማ ሆነች። ከዚያ በኋላም አይሁድ ለ70 ዓመታት በባቢሎን ግዞተኛ ሆነው ኖሩ። ከዚያ በኋላ ግን አምላክ ንሥሐ የገቡ አይሁዳውያን ቀሪዎችን በማነሳሳት ወደ ተስፋይቱ ምድር ተመልሰው እውነተኛውን አምልኮ መልሰው እንዲያቋቁሙ አደረገ። ባድማ ሆና ወደቆየችው ከተማ የተመለሱት በ537 ከዘአበ በሰባተኛው ወር ነበር። ወዲያው እንደተመለሱ ያደረጉት የመጀመሪያ ነገር በሕጉ ቃል ኪዳን በታዘዘው መሠረት የየሠርኩ መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠውያ መሥራት ነበር። ወዲያው ሳይዘገዩ ሌላውን ታሪካዊ የሆነ ታላቅ በዓል አደረጉ። “እንደ ተጻፈውም የዳስ በዓል አደረጉ።”—ዕዝራ 3:1-4
15. በ537 ከዘአበ ከግዞት የተመለሱት ቀሪዎች ከፊታቸው ምን ዓይነት ሥራ ይጠብቃቸው ነበር? በ1919ስ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሁኔታ የታየው እንዴት ነው?
15 እነዚህ ከግዞት የተመለሱ አይሁዳውያን ቀሪዎች ከፊታቸው በጣም ታላቅ የሆነ ሥራ ይጠብቃቸው ነበር። የአምላክን ቤተ መቅደስና ኢየሩሳሌምን ከነቅጥሮችዋ ዳግመኛ መሥራት ነበረባቸው። ምቀኛ የሆኑ ጎረቤቶቻቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ያደርጉባቸው ነበር። ቤተ መቅደሱ በመሠራት ላይ በነበረበት ጊዜ “የጥቂቱ ነገር ቀን” ነበር። (ዘካርያስ 4:10) በዚህ ጊዜ የነበረው ሁኔታ ታማኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1919 ከነበሩበት ሁኔታ ጋር በጣም ይመሳሰላል። በዚህ ታሪካዊ ዓመት ከነበሩበት የዓለም ሐሰት ሃይማኖት ግዛት፣ ማለትም ከታላቂቱ ባቢሎን መንፈሳዊ ግዞት ነጻ ወጡ። ቁጥራቸው ከጥቂት ሺህዎች ያላለፈ ሲሆን መላው ዓለም በጠላትነት ተሰልፎባቸው ነበር። ታዲያ የአምላክ ጠላቶች የእውነተኛውን አምልኮ መስፋፋት ሊገቱ ይችሉ ይሆን? የዚህ ጥያቄ መልስ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን የመጨረሻ ሁለት በዓሎች ያስታውሰናል።
16. በ515 ከዘአበ የተደረገውን በዓል ልዩ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?
16 በመጨረሻ ቤተ መቅደሱ ለሁለተኛ ጊዜ በ515 ከዘአበ በአዳር ወር ተሠርቶ አለቀና በኒሳን ወር ለሚደረገው የጸደይ በዓል ዝግጁ ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን “እግዚአብሔር ደስ አሰኝቶአቸዋልና የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ።”—ዕዝራ 6:22
17, 18. (ሀ) በ455 ከዘአበ የትኛው ከፍተኛ በዓል ተደረገ? (ለ) ዛሬስ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ያለነው እንዴት ነው?
17 በ455 ከዘአበ ከስልሳ ዓመት በኋላ ሌላ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው በዓል ተደረገ። በዚህ ዓመት የተከበረው የዳስ በዓል የኢየሩሳሌም ቅጥሮች ተሠርተው ያለቁበት ጊዜ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ይላል:- “ከምርኮም የተመለሱት ማኅበር ሁሉ ዳስ ሠሩ፣ በዳሱም ውስጥ ተቀመጡ። ከነዌም ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያ ቀን ድረስ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለ አላደረጉም ነበር። እጅግም ታላቅ ደስታ ሆነ።”—ነህምያ 8:17
18 እንዴት ያለ ሊዘነጋ የማይችልና ከፍተኛ በሆነ ተቃውሞ ሊበገር ያልቻለ የእውነተኛው አምልኮ ተሐድሶ ነው! ዛሬም ያለው ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። በጣም ከፍተኛ የሆነ የስደትና የተቃውሞ ማዕበል ቢነሳም የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩ ታላቅ ሥራ እስከ ምድር ማዕዘናት ተዳርሶ የአምላክ የፍርድ መልእክት በመላይቱ ምድር በመሰማት ላይ ነው። (ማቴዎስ 24:14) በ144,000ዎቹ ቅቡዓን ቀሪዎች ላይ የሚደረገው የመጨረሻ ማህተም ሊፈጸም ተቃርቧል። ከአምስት ሚልዮን የሚበልጡት ከ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ ባልደረቦቻቸው ከዓለም ብሔራት በሙሉ ተሰብስበው ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር “አንድ መንጋ” ሆነዋል። (ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 7:3, 9, 10) የዳስ በዓል ትንቢታዊ ጥላ የሆነለት እንዴት ያለ አስደናቂ ክንውን ነው! ይህ ታላቅ የሆነ የመሰብሰብ ሥራ በቢልዮን የሚቆጠሩ ከሙታን የሚነሱ ሰዎች እውነተኛውን የዳስ በዓል እንዲያከብሩ በሚጋበዙበት በአዲሱ ዓለም ጭምር ይቀጥላል።—ዘካርያስ 14:16-19
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ
19. በ32 እዘአ የተከበረው የዳስ በዓል ልዩ ግምት የሚሰጠው የሆነው ለምንድን ነው?
19 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጎላ ብለው ከተመዘገቡት በዓላት መካከል የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘባቸው በዓላት እንደሚገኙ ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በ32 እዘአ የተገኘበትን የዳስ በዓል እንውሰድ። በዚህ አጋጣሚ በጣም አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን ሲያስተምር ለትምህርቱ ድጋፍ የሚሆኑ ጥቅሶችን ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጠቅሷል። (ዮሐንስ 7:2, 14, 37-39) በዚህ በዓል ላይ ከሚፈጸሙት ሥርዓቶች አንዱ በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ አደባባይ ውስጥ አራት ታላላቅ መቅረዞችን ማብራት ነበር። ይህ መደረጉ ሌሊቱን በሙሉ ለሚዘልቀው የበዓሉ ዝግጅት ተጨማሪ ድምቀት ይሰጥ ነበር። ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ያለው እነዚህን ታላላቅ መብራቶች አስመልክቶ እንደሆነ ግልጽ ነው።—ዮሐንስ 8:12
20. በ33 እዘአ የተከበረው የማለፍ በዓል ልዩ የሆነው በምን ምክንያት ነው?
20 በኋላም በጣም ታሪካዊ በሆነው በ33 እዘአ የተከበረው የማለፍና የቂጣ በዓል መጣ። በዚህ የማለፍ በዓል ዕለት ኢየሱስ በጠላቶቹ ተገድሎ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ” እውነተኛ የማለፍ በግ ሆነ። (ዮሐንስ 1:29፤ 1 ቆሮንቶስ 5:7) ከሦስት ቀናት በኋላ፣ ኒሳን 16 ቀን አምላክ ለኢየሱስ የማይሞት አካል ሰጥቶ አስነሳው። ይህ የሆነው በሕጉ መሠረት የሚቀርበው የገብስ መከር በኩራት በሚቀርብበት ቀን ነው። በዚህ መንገድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል።”—1 ቆሮንቶስ 15:20
21. በ33 እዘአ በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ምን ሆነ?
21 በ33 እዘአ የተከበረውም የጰንጠቆስጤ በዓል ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው። በዚህ ቀን 120 የሚያክሉትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጨምሮ በርካታ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ነበር። በዓሉ በመካሄድ ላይ እንዳለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ በ120ዎቹ ላይ አፈሰሰ። (ሥራ 1:15፤ 2:1-4, 33) በዚህ መንገድ በመቀባታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛ በሆነለት አዲስ ቃል ኪዳን አማካኝነት የአምላክ ምርጥ ብሔር ሆኑ። የአይሁድ ሊቀ ካህናት በዚሁ በዓል ላይ ከስንዴው መከር በኩራት የተዘጋጁ ሁለት ኅብስቶች ለአምላክ አቅርቦ ነበር። (ዘሌዋውያን 23:15-17) እነዚህ ቦክተው የተጋገሩ ኅብስቶች ኢየሱስ “መንግሥትና ካህናት” ሆነው እንዲያገለግሉና ‘በምድር ላይ እንዲነግሡ ለአምላክ የዋጃቸውን’ 144,000 ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ያመለክታሉ። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3) ኅብስቶቹ ሁለት መሆናቸው እነዚህ ሰማያዊ ገዥዎች ከሁለት ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጅ ግንዶች፣ ማለትም ከአይሁድና ከአሕዛብ የተውጣጡ መሆናቸውን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
22. (ሀ) ክርስቲያኖች በሕጉ ቃል ኪዳን የታዘዙትን በዓላት የማያከብሩት ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ስለ ምን ነገር እንመለከታለን?
22 አዲሱ ቃል ኪዳን በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ሥራ ላይ መዋሉ አሮጌው የሕግ ቃል ኪዳን በአምላክ ዘንድ የነበረውን ዋጋ ጨርሶ ማጣቱን ያመለክታል። (2 ቆሮንቶስ 3:14፤ ዕብራውያን 9:15፤ 10:16) እንዲህ ሲባል ግን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት ሕግ የላቸውም ማለት አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረውና በልባቸው ላይ በተጻፈው መለኮታዊ ሕግ ይገዛሉ። (ገላትያ 6:2) ስለዚህ ሦስቱ ዓመታዊ በዓሎች የአሮጌው የሕግ ቃል ኪዳን ክፍሎች በመሆናቸው ክርስቲያኖች አያከብሯቸውም። (ቆላስይስ 2:16, 17) ይሁን እንጂ የቅድመ ክርስትና የአምላክ አገልጋዮች ለበዓሎቻቸውና ለሌሎች የአምልኮ ስብሰባዎቻቸው ከነበራቸው ዝንባሌ ብዙ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። በሚቀጥለው ርዕስ ሁላችንም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር እንድንገኝ የሚያነሳሱን ምሳሌዎች እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በተጨማሪም ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (የእንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 820 አንደኛ አምድ አንቀጽ 1 እና 3 ላይ “በዓል” በሚል ርዕስ ሥር የሠፈረውን ተመልከት።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ እስራኤላውያን ያከብሯቸው የነበሩት ሦስት ትላልቅ በዓላት ለምን ዓላማ አገልግለዋል?
◻ በሕዝቅያስና በኢዮስያስ ዘመን የተደረጉትን በዓላት ልዩ ያደረጓቸው ነገሮች ምን ነበሩ?
◻ በ455 ከዘአበ የተከበረው ምን ታሪካዊ ክንውን ነበር? ይህስ እኛን የሚያጽናናን እንዴት ነው?
◻ በ33 እዘአ የተከበሩትን የማለፍና የጰንጠቆስጤ በዓላት ልዩ ያደረጓቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በዚህ ዘመን የምንኖር ሁሉ ከበዓል የምናገኘው ትምህርት
ከኃጢአት ከሚያነጻው የኢየሱስ መሥዋዕት ዘላቂ ጥቅም ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ የቂጣ በዓል ምሳሌ ከሆነለት ነገር ጋር ተስማምተው መኖር አለባቸው። ይህ በዓል ጥላ የሆነው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከዚህ ክፉ ዓለምና ከኃጢአት ኩነኔ በኢየሱስ ቤዛ አማካኝነት ላገኙት ነፃነት የሚሰማቸውን ደስታ ነው። (ገላትያ 1:4፤ ቆላስይስ 1:13, 14) የጥንቱ በዓል ይቆይ የነበረው ለሰባት ቀናት ሲሆን ሰባት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈሳዊ ምልዓትን የሚያመለክት ቁጥር ነው። የዚህ ጥላ እውነተኛ ፍጻሜ የሆነው በዓል ግን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ በምድር ላይ በሚኖርበት ዘመን ሁሉ የሚቆይ ሲሆን ‘በቅንነትና በእውነት’ መከበር ይኖርበታል። ይህ ማለት ምሳሌያዊ እርሾ እንዳይገባ ዘወትር መጠንቀቅ ያስፈልጋል ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርሾ የሚያመለክተው ጠማማ ትምህርቶችን፣ ግብዝነትንና ክፋትን ነው። የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች እንደነዚህ ያሉትን እርሾዎች መጥላት፣ የራሳቸውን አኗኗርም ሆነ የክርስቲያን ጉባኤን ንጽሕና እንዳያበላሹ መጠንቀቅ አለባቸው።—1 ቆሮንቶስ 5:6-8፤ ማቴዎስ 16:6, 12
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በየዓመቱ ኒሳን 16 ቀን፣ ማለትም ኢየሱስ ከሞት በተነሳበት ቀን ከአዲሱ የስንዴ መከር የተወሰደ ነዶ ይቀርብ ነበር
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ “የዓለም ብርሃን” ነኝ ባለ ጊዜ በዳስ በዓል የሚለኮሱትን መብራቶች አስመልክቶ መናገሩ ሳይሆን አይቀርም