የጥናት ርዕስ 49
የዘሌዋውያን መጽሐፍ ሌሎችን ስለምንይዝበት መንገድ ምን ያስተምረናል?
“ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።”—ዘሌ. 19:18
መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ
ማስተዋወቂያa
1-2. ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ምን ተመልክተናል? በዚህ ርዕስ ላይስ ምን እንመረምራለን?
በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የሚገኙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ተመልክተናል። ለምሳሌ ቁጥር 3 እንደሚገልጸው እስራኤላውያን ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ ይሖዋ እንዳሳሰባቸው ተመልክተን ነበር። በዛሬው ጊዜም የወላጆቻችንን አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት በማሟላት ይህን ምክር እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል አይተናል። በዚሁ ጥቅስ ላይ የአምላክ ሕዝብ ሰንበትን እንዲጠብቁ ታዘዋል። በዛሬው ጊዜ ሰንበትን እንድናከብር ባይጠበቅብንም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቋሚ ፕሮግራም በመመደብ መሠረታዊ ሥርዓቱን ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል ተምረናል። ይህን ስናደርግ በዘሌዋውያን 19:2 እና በ1 ጴጥሮስ 1:15 ላይ በተመከርነው መሠረት ቅዱስ ለመሆን ጥረት እያደረግን መሆናችንን እናሳያለን።
2 በዚህ ርዕስ ላይም ዘሌዋውያን ምዕራፍ 19ን መመርመራችንን እንቀጥላለን። ይህ ምዕራፍ የአካል ጉዳት ላለባቸው አሳቢነት ስለማሳየት፣ ከንግድ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሐቀኛ ስለመሆን እንዲሁም ባልንጀራችንን ስለመውደድ ምን ያስተምረናል? አምላክ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እኛም ቅዱስ መሆን እንፈልጋለን። እንግዲያው ከዚህ ምዕራፍ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።
ለአካል ጉዳተኞች አሳቢነት ማሳየት
3-4. በዘሌዋውያን 19:14 መሠረት እስራኤላውያን መስማት የተሳናቸውን እና ዓይነ ስውራንን እንዴት እንዲይዟቸው ይጠበቅባቸው ነበር?
3 ዘሌዋውያን 19:14ን አንብብ። ይሖዋ፣ ሕዝቡ ለአካል ጉዳተኞች አሳቢነት እንዲያሳዩ ይጠብቅባቸው ነበር። ለምሳሌ እስራኤላውያን መስማት የተሳነውን እንዳይረግሙ ታዘው ነበር። መርገም የሚለው ሐሳብ በግለሰቡ ላይ ዛቻ መሰንዘርን ወይም መጥፎ ነገር እንዲደርስበት መመኘትን ያመለክታል። መስማት በተሳነው ሰው ላይ እንዲህ ማድረግ ምንኛ አሳፋሪ ነው። ግለሰቡ እየተወራ ያለውን ነገር ስለማይሰማ ለራሱ መከላከያ ማቅረብ አይችልም።
4 የአምላክ አገልጋዮች በቁጥር 14 ላይ “በዓይነ ስውሩ ፊት እንቅፋት አታስቀምጥ” የሚል መመሪያም ተሰጥቷቸዋል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው “በጥንት ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ የአካል ጉዳተኞች መጠቀሚያ ይደረጉ እንዲሁም ጥቃት ይሰነዘርባቸው ነበር።” ምናልባትም አንዳንዶች በክፋት ተነሳስተው ወይም ሌሎችን ለማሳቅ ብለው በዓይነ ስውራን ፊት እንቅፋት ያስቀምጡ ይሆናል። ይህ እንዴት ያለ ጭካኔ ነው! ይሖዋ ለሕዝቡ እንዲህ ያለ መመሪያ በመስጠት፣ ለአካል ጉዳተኞች ርኅራኄ እንዲያሳዩ እንደሚጠብቅባቸው አስተምሯቸዋል።
5. ለአካል ጉዳተኞች ርኅራኄ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ ለአካል ጉዳተኞች ርኅራኄ አሳይቷል። ለመጥምቁ ዮሐንስ የላከውን መልእክት እናስታውስ፦ “ዓይነ ስውሮች እያዩ ነው፤ አንካሶች እየተራመዱ ነው፤ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፤ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ ነው፤ [እንዲሁም] ሙታን እየተነሱ ነው” ብሎት ነበር። “ሕዝቡም ሁሉ” ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራት ሲያዩ “አምላክን አወደሱ።” (ሉቃስ 7:20-22፤ 18:43) ክርስቲያኖች ለአካል ጉዳተኞች ርኅራኄ በማሳየት ኢየሱስን መምሰል ይፈልጋሉ። በመሆኑም እንዲህ ላሉ ሰዎች ደግነት፣ አሳቢነትና ትዕግሥት እናሳያለን። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ተአምራት የመፈጸም ኃይል አልሰጠንም። ያም ቢሆን ቃል በቃልም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ለታወሩ ሰዎች ምሥራች የመናገር መብት ተሰጥቶናል፤ ይህ ምሥራች፣ ሁሉም ሰው የተሟላ አካላዊና መንፈሳዊ ጤንነት የሚያገኝበት ገነት እንደሚመጣ የሚገልጽ ነው። (ሉቃስ 4:18) ምሥራቹ በአሁኑ ጊዜም ብዙዎች አምላክን እንዲያወድሱ እያነሳሳቸው ነው።
በንግድ ጉዳዮች ረገድ ሐቀኛ መሆን
6. በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የሚገኘው ሐሳብ አሥርቱን ትእዛዛት ይበልጥ ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው?
6 በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የሚገኙ አንዳንድ ሐሳቦች አሥርቱን ትእዛዛት በተሻለ መንገድ ለመረዳት ያስችላሉ። ለምሳሌ ስምንተኛው ትእዛዝ “አትስረቅ” ይላል። (ዘፀ. 20:15) አንድ ሰው የሌላን ሰው ንብረት እስካልወሰደ ድረስ ይህን ሕግ እንደታዘዘ ይሰማው ይሆናል። ይሁንና በሌሎች መንገዶች ይሰርቅ ይሆናል።
7. አንድ ነጋዴ “አትስረቅ” የሚለውን ስምንተኛውን ትእዛዝ ሊጥስ የሚችለው እንዴት ነው?
7 ለምሳሌ አንድ ነጋዴ የሌላን ሰው ንብረት እስካልወሰደ ድረስ እንዳልሰረቀ ይሰማው ይሆናል። ይሁንና ከንግድ እንቅስቃሴው ጋር በተያያዘስ ምን ማለት ይቻላል? በዘሌዋውያን 19:35, 36 ላይ ይሖዋ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ርዝመትን፣ ክብደትን ወይም መጠንን ስትለኩ በተጭበረበረ መለኪያ አትጠቀሙ። ትክክለኛ ሚዛን፣ ትክክለኛ የሚዛን ድንጋዮች፣ ትክክለኛ የደረቅ ነገር መስፈሪያና ትክክለኛ የፈሳሽ ነገር መለኪያ ሊኖራችሁ ይገባል።” ትክክለኛ ያልሆነ ሚዛን ወይም መለኪያ በመጠቀም ደንበኞቹን የሚያታልል ነጋዴ ከእነሱ እየሰረቀ ነው ሊባል ይችላል። በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የሚገኙ ሌሎች ጥቅሶችም ይህንን ይበልጥ ግልጽ ያደርጉልናል።
8. በዘሌዋውያን 19:11-13 ላይ የሚገኘው ሐሳብ አይሁዳውያን በስምንተኛው ትእዛዝ ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚረዳቸው እንዴት ነበር? እኛስ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
8 ዘሌዋውያን 19:11-13ን አንብብ። ዘሌዋውያን 19:11 የሚጀምረው “አትስረቁ” በማለት ነው። ቁጥር 13 ደግሞ “ባልንጀራህን አታጭበርብር” ይላል፤ ይህም በስርቆትና ሐቀኝነት በጎደለው ንግድ መካከል ያለውን ግንኙነት ይጠቁማል። ስለዚህ አንድ ሰው ከንግድ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚያጭበረብር ከሆነ እየሰረቀ ነው ማለት ነው። ስምንተኛው ትእዛዝ መስረቅ ስህተት መሆኑን በግልጽ ይናገራል፤ በዘሌዋውያን መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ተጨማሪ ማብራሪያ ደግሞ ከዚህ ሕግ በስተ ጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ ለአይሁዳውያን ጠቁሟቸዋል። እኛም ይሖዋ ሐቀኝነት ስለ ማጉደልና ስለ መስረቅ ባለው አመለካከት ላይ ቆም ብለን ማሰባችን ይጠቅመናል። ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በዘሌዋውያን 19:11-13 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ አንጻር በሕይወቴ ውስጥ ላስተካክለው የሚገባ ነገር አለ? ከንግድ እንቅስቃሴዬ ወይም ከሥራ ልማዴ ጋር በተያያዘ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገኝ ይሆን?’
9. በዘሌዋውያን 19:13 ላይ የሚገኘው ሕግ ቅጥር ሠራተኞችን የሚጠቅማቸው እንዴት ነበር?
9 ሌሎችን ቀጥሮ የሚያሠራ አንድ ክርስቲያን ከሐቀኝነት ጋር በተያያዘ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሌላም ጉዳይ አለ። ዘሌዋውያን 19:13 “የቅጥር ሠራተኛውን ደሞዝ ሳትከፍል አታሳድር” ይላል። በግብርና በሚተዳደረው የእስራኤል ማኅበረሰብ ውስጥ ቅጥር ሠራተኞች ደሞዛቸው የሚከፈላቸው በእያንዳንዱ ቀን ማብቂያ ላይ ነበር። በመሆኑም አንድ አሠሪ ለቅጥር ሠራተኛው ደሞዙን ሳይከፍለው ቢቀር ይህ ሠራተኛ በዚያ ዕለት ቤተሰቡን ለመመገብ የሚያስፈልገው ገንዘብ አይኖረውም። ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “ችግረኛ በመሆኑና ሕይወቱ የተመካው በደሞዙ ላይ ስለሆነ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ስጠው።”—ዘዳ. 24:14, 15፤ ማቴ. 20:8
10. ከዘሌዋውያን 19:13 ምን ትምህርት እናገኛለን?
10 በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ቅጥር ሠራተኞች የሚከፈላቸው በየቀኑ ሳይሆን በየወሩ ወይም በየሁለት ሳምንቱ ነው። ያም ቢሆን በዘሌዋውያን 19:13 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ዛሬም ይሠራል። አንዳንድ ቀጣሪዎች ለሠራተኞቻቸው ከሚገባቸው በጣም ያነሰ ደሞዝ በመክፈል መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል። አሠሪዎቹ ይህን የሚያደርጉት ሠራተኞቹ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸውና የሚከፈላቸው ደሞዝ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ ስለሚያውቁ ነው። እንዲህ ያሉት አሠሪዎች “የቅጥር ሠራተኛውን ደሞዝ [አልከፈሉም]” ሊባል ይችላል። ሌሎችን ቀጥሮ የሚያሠራ አንድ ክርስቲያን ሠራተኞቹን በተገቢው መንገድ ለመያዝ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ከዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 የምናገኘውን ሌላም ትምህርት እስቲ እንመልከት።
ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን መውደድ
11-12. ኢየሱስ ከዘሌዋውያን 19:17, 18 በመጥቀስ የትኛውን ነጥብ ጎላ አድርጎ ተናግሯል?
11 አምላክ የሚጠብቅብን ሌሎችን ከመጉዳት እንድንቆጠብ ብቻ አይደለም። በዘሌዋውያን 19:17, 18 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ይህንን በግልጽ ያሳየናል። (ጥቅሱን አንብብ።) ጥቅሱ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ይላል። አንድ ክርስቲያን አምላክን ማስደሰት ከፈለገ ይህን ማድረጉ የግድ አስፈላጊ ነው።
12 ኢየሱስ በዘሌዋውያን 19:18 ላይ የሚገኘው ትእዛዝ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን የጠቆመው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በአንድ ወቅት አንድ ፈሪሳዊ ኢየሱስን “ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” በማለት ጠይቆት ነበር። ኢየሱስም “ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ” ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችንና በሙሉ አእምሯችን መውደድ እንደሆነ ነገረው። ከዚያም ኢየሱስ ዘሌዋውያን 19:18ን በመጥቀስ “ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል” አለው። (ማቴ. 22:35-40) ባልንጀራችንን እንደምንወድ ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ አንዳንዶቹን መመልከት እንችላለን።
13. በዘሌዋውያን 19:18 ላይ ከሚገኘው ምክር ጋር በሚስማማ መልኩ ዮሴፍ ምን እርምጃ ወስዷል?
13 ለባልንጀራችን ፍቅር ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ በዘሌዋውያን 19:18 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ነው። ጥቅሱ “አትበቀል፤ . . . ቂም አትያዝ” ይላል። አብዛኞቻችን በሥራ ባልደረባቸው፣ አብሯቸው በሚማር ልጅ፣ በዘመዳቸው ወይም በቤተሰባቸው አባል ላይ ቂም ይዘው የቆዩ ሰዎችን እናውቃለን፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ቂም የያዙት ለዓመታት ነው! የዮሴፍ አሥር ወንድሞች በእሱ ላይ ቂም ይዘው እንደነበረ እናስታውሳለን፤ ይህም ውሎ አድሮ፣ ጥላቻ የሚንጸባረቅበት ድርጊት ወደመፈጸም መርቷቸዋል። (ዘፍ. 37:2-8, 25-28) ዮሴፍ ግን እንደ ሥራቸው አላደረገባቸውም! ሥልጣን ባገኘበት ወቅት ወንድሞቹን መበቀል ይችል ነበር፤ እሱ ግን ምሕረት አሳይቷቸዋል። ዮሴፍ ቂም አልያዘም። ከዚህ ይልቅ፣ ከጊዜ በኋላ በዘሌዋውያን 19:18 ላይ ከተመዘገበው ምክር ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስዷል።—ዘፍ. 50:19-21
14. በዘሌዋውያን 19:18 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜም እንደሚሠራ የሚያሳየው ምንድን ነው?
14 አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ክርስቲያኖች የዮሴፍን ምሳሌ በመከተል፣ ቂም ከመያዝ ወይም ከመበቀል ይልቅ ይቅር ይላሉ። ኢየሱስም ቢሆን በጸሎት ናሙናው ላይ የበደሉንን ይቅር እንድንል አበረታቶናል። (ማቴ. 6:9, 12) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ” በማለት ለክርስቲያኖች ምክር ሰጥቷል። (ሮም 12:19) ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን እንደሚከተለው በማለትም አበረታቷቸዋል፦ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።” (ቆላ. 3:13) የይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች አይለወጡም። በዘሌዋውያን 19:18 ላይ ከሚገኘው ሕግ በስተ ጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜም ይሠራል።
15. በደል ያደረሰብንን ሰው ይቅር ማለትና ጉዳዩን መርሳት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
15 አንድ ምሳሌ እንመልከት። የስሜት መጎዳት ከቁስል ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንዳንዱ ቁስል ቀላል ነው፤ አንዳንዱ ግን ከባድ ነው። ለምሳሌ ሽንኩርት ስንከትፍ ቢላው ጣታችንን ይቆርጠን ይሆናል። በዚህ ጊዜ ቢያመንም ብዙም ሳይቆይ ቁስሉ ይድናል። ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ የት ጋ እንደተቆረጥን እንኳ አናስታውሰው ይሆናል። በተመሳሳይም አንዳንድ ጊዜ የሚደርስብን በደል ቀላል ነው። ለምሳሌ ጓደኛችን የሚጎዳን ነገር ይናገር ወይም ያደርግ ይሆናል፤ ሆኖም በደሉን ይቅር ማለት አይከብደንም። ቢላው በደንብ ጎድቶን ከሆነ ግን ቁስሉ መሰፋት እና በፋሻ መታሸግ ሊያስፈልገው ይችላል። በዚህ ጊዜ ቁስሉን የምንነካካው ከሆነ ቁስሉ ይበልጥ እንዲያመረቅዝ እናደርገዋለን። አንድ ሰው ስሜቱ በጥልቅ ሲጎዳ እንዲህ ያለ ነገር ያደርግ ይሆናል፤ ይህ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! ስለደረሰበት በደል ነጋ ጠባ እያሰበ ይብሰለሰል ይሆናል። ይሁንና ቂም የሚይዙ ሰዎች የሚጎዱት ራሳቸውን ነው። ቂም ከመያዝ ይልቅ በዘሌዋውያን 19:18 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ምንኛ የተሻለ ነው!
16. በዘሌዋውያን 19:33, 34 መሠረት እስራኤላውያን በመካከላቸው የሚኖሩ የባዕድ አገር ሰዎችን እንዴት ሊይዟቸው ይገባ ነበር? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?
16 ይሖዋ እስራኤላውያን ባልንጀራቸውን እንዲወዱ መመሪያ ሲሰጣቸው ሌሎች እስራኤላውያንን ብቻ እንዲወዱ ማዘዙ አልነበረም። እስራኤላውያን በመካከላቸው የሚኖሩትን የባዕድ አገር ሰዎችም እንዲወዱ ታዘዋል። በዘሌዋውያን 19:33, 34 ላይ ይህ መመሪያ በግልጽ ሰፍሯል። (ጥቅሱን አንብብ።) እስራኤላውያን የባዕድ አገር ሰዎችን ‘እንደ አገራቸው ተወላጅ አድርገው ሊመለከቷቸው’ እንዲሁም ‘እንደ ራሳቸው አድርገው ሊወዷቸው’ ይገባ ነበር። ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን የባዕድ አገር ሰዎችንም ሆነ በአገራቸው ያሉ ድሆችን ከእርሻቸው እንዲቃርሙ ሊፈቅዱላቸው እንደሚገባ ሕጉ ያዝዝ ነበር። (ዘሌ. 19:9, 10) የባዕድ አገር ሰዎችን ስለመውደድ የሚገልጸው መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖችም ይሠራል። (ሉቃስ 10:30-37) እንዴት? በዛሬው ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአገራቸው ተሰደዋል፤ ምናልባትም አንተ በምትኖርበት አካባቢ አንዳንድ ስደተኞች ይኖሩ ይሆናል። እነዚህን ሰዎች በአክብሮት ልንይዛቸው ይገባል።
በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ ያልተካተተ አስፈላጊ ሥራ
17-18. (ሀ) ዘሌዋውያን 19:2 እና 1 ጴጥሮስ 1:15 ምን እንድናደርግ ያበረታቱናል? (ለ) ሐዋርያው ጴጥሮስ የትኛውን በጣም አስፈላጊ ሥራ እንድናከናውን መክሮናል?
17 ዘሌዋውያን 19:2ም ሆነ 1 ጴጥሮስ 1:15 የአምላክ ሕዝቦች ቅዱስ እንዲሆኑ ያበረታታሉ። በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የሚገኙ ሌሎች በርካታ ጥቅሶችም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ይጠቁሙናል። እስካሁን የተመለከትነው፣ ማድረግ ያለብንን መልካም ነገሮች እና ማድረግ የሌለብንን መጥፎ ነገሮች የሚጠቁሙ ጥቂት ጥቅሶችን ብቻ ነው።b የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትም ይሖዋ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ እንድናደርግ እንደሚፈልግ ያሳያሉ። ይሁንና ሐዋርያው ጴጥሮስ ይሖዋ የሚጠብቅብንን ሌላም ነገር ተናግሯል።
18 በተለያዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንካፈል እንዲሁም በርካታ መልካም ሥራዎችን እናከናውን ይሆናል። ሆኖም ጴጥሮስ ክርስቲያኖች በዋነኝነት ሊያከናውኑት የሚገባ አንድ ሥራ እንዳለ ገልጿል፤ በምግባራችን ሁሉ ቅዱሳን እንድንሆን ከማበረታታቱ አስቀድሞ “አእምሯችሁን ዝግጁ በማድረግ ለሥራ ታጠቁ” ብሎ ነበር። (1 ጴጥ. 1:13, 15) ይህ ሥራ ምንድን ነው? ጴጥሮስ የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች ‘የጠራቸውን የእሱን ድንቅ ባሕርያት በየቦታው እንደሚያውጁ’ ተናግሯል። (1 ጴጥ. 2:9) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ በዚህ በጣም አስፈላጊ ሥራ የመካፈል መብት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ሥራ ከሁሉ የላቀ ጥቅም ያስገኛል። ቅዱስ የሆኑት የአምላክ ሕዝቦች በስብከቱ እና በማስተማሩ ሥራ አዘውትረው በቅንዓት የመካፈል ልዩ መብት ተሰጥቷቸዋል! (ማር. 13:10) በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ለማዋል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ አምላካችንንም ሆነ ባልንጀራችንን እንደምንወድ እናሳያለን። እንዲሁም ‘በምግባራችን ሁሉ ቅዱሳን መሆን’ እንደምንፈልግ በግልጽ ይታያል።
መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች
a ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም። ሆኖም ሕጉ፣ ማድረግ የሚገቡንን ወይም የማይገቡንን ነገሮች በተመለከተ ብዙ ትምህርት ይሰጠናል። ስለ እነዚህ ነገሮች መመርመራችን ለሌሎች ፍቅር ለማሳየት እንዲሁም አምላክን ለማስደሰት ያስችለናል። ይህ ርዕስ በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ የሚገኙ አንዳንድ ትምህርቶችን በሕይወታችን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል ያብራራል።
b ቀደም ባለውና በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተመለከትናቸው ጉዳዮች ውጭ ዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ከአድልዎ፣ ስም ከማጥፋትና ደም ያለበት ነገር ከመብላት እንዲሁም ከመናፍስታዊ ድርጊቶች፣ ከጥንቆላ እና ከፆታ ብልግና ስለመራቅ ይናገራል።—ዘሌ. 19:15, 16, 26-29, 31—በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚገኘውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ የይሖዋ ምሥክር መስማት የተሳነውን የእምነት አጋሩን ከሐኪም ጋር ለመነጋገር ሲያግዘው።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ ቀለም በመቀባት ሙያ ላይ የተሰማራ አንድ ወንድም ለተቀጣሪው ደሞዙን ሲከፍለው።
e የሥዕሉ መግለጫ፦አንዲት እህት ትንሽ ነገር ቢቆርጣት ቁስሉ መኖሩን እንኳ ልትረሳው ትችላለች። ከበድ ያለ ጉዳት ቢደርስባትስ ተመሳሳይ ነገር ታደርግ ይሆን?