የዋህነት—እጅግ አስፈላጊ የሆነ ክርስቲያናዊ ባሕርይ
“የዋህነትን . . . ልበሱ።”—ቆላስይስ 3:12
1. የዋህነት ግሩም ባሕርይ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
አንድ ሰው የዋህ ወይም ገራገር ከሆነ ሰዎች ከእርሱ ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። በሌላ በኩል ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የገራም ምላስ አጥንትን ይሰብራል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 25:15) የዋህነት በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ መሆንንና የመንፈስ ጥንካሬን አጣምሮ የያዘ ግሩም ባሕርይ ነው።
2, 3. በየዋህነትና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ምን ዝምድና አለ? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ 5:22, 23 ላይ ከጠቀሰው “የመንፈስ ፍሬ” ዝርዝር ውስጥ የዋህነትም ይገኝበታል። ቁጥር 23 ላይ ‘የዋህነት’ ተብሎ የተተረጎመውን የግሪክኛ ቃል አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች በብዙ ቦታዎች ላይ “ትሕትና” ወይም “ገርነት” ብለው ተርጉመውታል። ሌሎች በርካታ ቋንቋዎች ቃሉን በትክክል ሊገልጽ የሚችል አቻ የሆነ ቃል የላቸውም። ይህ የሆነበት ምክንያት ግሪክኛው ቃል የሚያመለክተው እንዲሁ ገራገር መሆንን ሳይሆን ከውስጥ የመነጨ የየዋህነትና የአሳቢነት ስሜትን የሚያሳይ የአእምሮና የልብ ሁኔታን በመሆኑ ነው።
3 የዋህነት የሚለው ቃል ያለውን ትርጉምና አስፈላጊነት ሙሉ በሙሉ መገንዘብ እንድንችል አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመለከታለን። (ሮሜ 15:4) በእነዚህ ምሳሌዎች አማካኝነት የዋህነት ምን ማለት እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ይህን ባሕርይ እንዴት ማዳበርና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ሁሉ እንዴት ማሳየት እንደምንችል እንማራለን።
“በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ”
4. ይሖዋ ለየዋህነት ከፍ ያለ ግምት እንደሚሰጥ እንዴት እናውቃለን?
4 የዋህነት የአምላክ መንፈስ ፍሬ በመሆኑ አምላክ ካሉት ግሩም ባሕርያት ጋር በቅርብ የተዛመደ እንደሚሆን መጠበቃችን ምክንያታዊ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የዋህና ዝግተኛ መንፈስ” “በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ” መሆኑን ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:4) በእርግጥም ይሖዋ ይህን ባሕርይ የሚያንጸባርቅ ከመሆኑም በላይ ለዚህ ባሕርይ ከፍተኛ ግምት ይሰጣል። ይህ በራሱ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ የዋህነትን እንዲያዳብሩ የሚገፋፋ በቂ ምክንያት ነው። ይሁንና በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጨረሻውን ሥልጣን የያዘው ሁሉን ቻይ አምላክ የዋህነትን የሚያሳየው እንዴት ነው?
5. ይሖዋ የዋህነትን በማንጸባረቁ ምክንያት ምን ተስፋ አግኝተናል?
5 የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አዳምና ሔዋን መልካሙንና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ እንዳይበሉ አምላክ የሰጣቸውን የማያሻማ ትእዛዝ የጣሱት ሆን ብለው ነው። (ዘፍጥረት 2:16, 17) ይህ እያወቁ የፈጸሙት ጥፋት በእነርሱም ሆነ በዘሮቻቸው ላይ ኃጢአትና ሞት ያስከተለባቸው ከመሆኑም በላይ የአምላክ ልጆች የመሆን መብት አሳጥቷቸዋል። (ሮሜ 5:12) ምንም እንኳ ይሖዋ እንዲህ ያለውን እርምጃ ለመውሰድ አጥጋቢ ምክንያት ቢኖረውም የሰው ዘር ፈጽሞ ሊስተካከልና ሊቤዥ እንደማይችል ቆጥሮ ያለ ምንም ምሕረት እርግፍ አድርጎ አልተወውም። (መዝሙር 130:3) ፍርዱን በጥብቅ ከማስፈጸም ይልቅ የየዋህነት መግለጫ የሆኑትን አሳቢነትና ፈቃደኝነት በማሳየት ኃጢአተኛ የሆነው የሰው ዘር ወደ እርሱ የሚቀርብበትንና ሞገሱን የሚያገኝበትን ዝግጅት አድርጓል። አዎን፣ ይሖዋ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ሳንፈራና ሳንሸማቀቅ ወደ ታላቅ ዙፋኑ መቅረብ የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል።—ሮሜ 6:23፤ ዕብራውያን 4:14-16፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10, 18
6. አምላክ ከቃየን ጋር በነበረው ግንኙነት የዋህነትን ያሳየው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት የአዳም ልጆች ቃየንና አቤል ለአምላክ መሥዋዕት ባቀረቡበት ወቅት የይሖዋ የዋህነት ታይቷል። ይሖዋ የልባቸውን ሁኔታ በማየት የአቤልን መሥዋዕት ተቀብሎ የቃየንን መሥዋዕት ግን ሳይቀበል ቀረ። አምላክ የታማኙን የአቤልን መሥዋዕት በደስታ መቀበሉ ቃየንን አስከፋው። የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ “ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ” ይላል። ይሖዋ ምን ተሰማው? ቃየን ያሳየው መጥፎ ዝንባሌ ይሖዋን አስቆጥቶት ይሆን? በፍጹም። ይሖዋ፣ ለቃየን የዋህነት በማሳየት ለምን እንደተናደደ ጠየቀው። ከዚህም በላይ ደስታ ሊያገኝ የሚችልበትን መንገድ ገለጸለት። (ዘፍጥረት 4:3-7) ይሖዋ የየዋህነትን ባሕርይ የተላበሰ ለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም።—ዘጸአት 34:6
የዋህነት ማራኪና መንፈስ የሚያድስ ባሕርይ ነው
7, 8. (ሀ) ይሖዋ የዋህ መሆኑን መረዳት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ማቴዎስ 11:27-29 ስለ ይሖዋ እና ስለ ኢየሱስ ምን ያሳውቀናል?
7 የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወትና አገልግሎት መመርመር ወደር የሌላቸውን የይሖዋን ባሕርያት ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድንገነዘብ ያስችለናል። (ዮሐንስ 1:18፤ 14:6-9) ኢየሱስ በስብከት ዘመቻው ሁለተኛ ዓመት ላይ በገሊላ አውራጃ በነበረበት ወቅት በኮራዚን፣ በቤተ ሳይዳ፣ በቅፍርናሆም እና በአካባቢው በሚገኙ ከተሞች ብዙ ተአምራት አከናውኖ ነበር። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች ትዕቢተኞችና ግድየለሾች በመሆናቸው መሲሕነቱን ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን ተሰማው? እምነት የለሽነታቸው የሚያስከትልባቸውን መዘዝ በጥብቅ የነገራቸው ቢሆንም አምሃአሬትስ ብለው የሚጠሯቸው ድኻና ተራ የሆኑት የኅብረተሰቡ ክፍሎች የነበሩበትን አስከፊ መንፈሳዊ ሁኔታ ሲመለከት ጥልቅ የሐዘን ስሜት ተሰምቶታል።—ማቴዎስ 9:35, 36፤ 11:20-24
8 ኢየሱስ ከዚያ በኋላ ያደረገው ነገር ‘አብን በሚገባ እንደሚያውቅ’ እና ባሕርይውን እንደሚኮርጅ ያሳያል። ለተራው ሕዝብ የሚከተለውን ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርቦላቸዋል:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።” ተረግጠውና ተጨቁነው የነበሩት ሰዎች እነዚህን ቃላት ሲሰሙ ምንኛ መጽናኛና እረፍት አግኝተው ይሆን! ለእኛም ቢሆን መጽናኛና እረፍት ያስገኙልናል። በእርግጥ የዋህነትን የምንለብስ ከሆነ ‘ወልድ በፈቃደኝነት አብን ከሚገልጥላቸው’ ሰዎች መካከል እንሆናለን።—ማቴዎስ 11:27-29
9. ከየዋህነት ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው ባሕርይ የትኛው ነው? በዚህ ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?
9 የዋህነት ከትሕትና ጋር በጣም ይዛመዳል። በአንጻሩ ደግሞ ኩራት ራስን ከፍ ከፍ ወደማድረግ ስለሚመራ ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ለሌሎች ደግነትና አሳቢነት እንዳያሳይ ያደርገዋል። (ምሳሌ 16:18, 19) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ትሕትናን አሳይቷል። ከመሞቱ ከስድስት ቀናት በፊት የአይሁድ ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ደማቅ አቀባበል በተደረገለት ጊዜም እንኳ ኢየሱስ ከዓለም መሪዎች ፈጽሞ የተለየ ዝንባሌ አሳይቷል። ዘካርያስ “እነሆ፣ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” ሲል ስለ መሲሑ የተናገረውን ትንቢት ፈጽሟል። (ማቴዎስ 21:5፤ ዘካርያስ 9:9) ታማኙ ነቢይ ዳንኤል ይሖዋ ለልጁ የመግዛት ሥልጣን ሲሰጠው በራእይ ተመልክቷል። ዳንኤል ከዚህ ቀደም ሲል በተናገረው ትንቢት ላይ ኢየሱስ “ከሰውም ሁሉ ትሑት” መሆኑን ገልጿል። በእርግጥም የዋህነትና ትሕትና የማይነጣጠሉ ባሕርያት ናቸው።—ዳንኤል 4:17 NW፤ 7:13, 14
10. የዋህነት የደካማነት ምልክት ያልሆነው እንዴት ነው?
10 ይሖዋና ኢየሱስ የሚያሳዩት ማራኪ የሆነው የየዋህነት ባሕርይ ወደ እነርሱ እንድንቀርብ ይረዳናል። (ያዕቆብ 4:8) እርግጥ ነው፣ የዋህነት የደካማነት ምልክት ተደርጎ መወሰድ አይኖርበትም! ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ ኃይል አለው። በክፉ አድራጊዎች ላይ በጣም ይቆጣል። (ኢሳይያስ 30:27፤ 40:26) በተመሳሳይም ኢየሱስ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ በተደጋጋሚ በፈተነው ጊዜ ከአቋሙ ፍንክች ላለማለት ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የሚያካሂዱትን አግባብነት የሌለው የንግድ እንቅስቃሴ በቸልታ አላለፈም። (ማቴዎስ 4:1-11፤ 21:12, 13፤ ዮሐንስ 2:13-17) ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ ሲሳሳቱ በየዋህነት ይይዛቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ድክመታቸውን በትዕግሥት ያልፍ ነበር። (ማቴዎስ 20:20-28) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር “ገርነት የውስጣዊ ጥንካሬ መገለጫ ነው” በማለት በትክክል ገልጸውታል። እንግዲያው ክርስቶስ ያሳየው ዓይነት የየዋህነት ባሕርይ እናሳይ።
በዘመኑ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ የዋህ ሰው
11, 12. ሙሴ ካደገበት ሁኔታ አንጻር ሲታይ የዋህነት መላበሱ አስደናቂ የሚሆነው ለምንድን ነው?
11 ሦስተኛው ምሳሌያችን ሙሴ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴ ‘በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ የዋህ ሰው’ እንደነበረ ይገልጻል። (ዘኍልቍ 12:3 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ይህ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መግለጫ ነው። ሙሴ ያሳየው የላቀ የየዋህነት ባሕርይ የይሖዋን መመሪያ እንዲቀበል አስችሎታል።
12 የሙሴ አስተዳደግ ለየት ያለ ነበር። ግፍና ግድያ ነግሦ በነበረበት ዘመን ይሖዋ ከታማኝ ዕብራውያን የተወለደውን ይህን ልጅ ከሞት አድኖታል። ሙሴ የሕፃንነት ዕድሜውን ያሳለፈው በእናቱ እንክብካቤ ሥር ሲሆን እርሷም ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋ በሚገባ አስተምራዋለች። በኋላም ከቤተሰቦቹ ተነጥሎ ፍጹም በተለየ አካባቢ መኖር ጀመረ። ሰማዕቱ ክርስቲያን እስጢፋኖስ ሙሴ “የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፣ በቃሉና በሥራውም የበረታ ሆነ” በማለት ተርኳል። (ሥራ 7:22) የፈርዖን አገልጋዮች በባርነት ሥር በነበሩት ወንድሞቹ ላይ የሚፈጽሙትን በደል ሲመለከት እምነቱን በተግባር አሳየ። አንድን ዕብራዊ ሲደበድብ የነበረውን ግብፃዊ በመግደሉ ሙሴ ከግብፅ ወደ ምድያም ሸሽቶ ለመሄድ ተገደደ።—ዘጸአት 1:15, 16፤ 2:1-15፤ ዕብራውያን 11:24, 25
13. ሙሴ በምድያም ባሳለፋቸው 40 ዓመታት የትኛውን ባሕርይ አዳብሯል?
13 ሙሴ 40 ዓመት ሲሆነው በምድረ በዳ ራሱን ችሎ መኖር ጀመረ። በምድያም የራጉኤልን ሰባት ሴቶች ልጆች አግኝቶ የአባታቸውን መንጋ ውኃ በማጠጣት ረዳቸው። ሴቶቹ ወደ ቤታቸው ሲደርሱ ሲያስቸግሯቸው ከነበሩ እረኞች “አንድ የግብፅ ሰው” እንዳስጣላቸው ለአባታቸው ነገሩት። ራጉኤልም ሙሴ ከቤተሰቡ ጋር እንዲኖር ፈቀደለት። የደረሰበት መከራ እንዲማረርም ሆነ በአዲስ አካባቢ መኖርን እንዳይላመድ አላደረገውም። የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ያለው ፍላጎት አልቀነሰም። ሙሴ የራጉኤል በግ ጠባቂ ሆኖ ባሳለፋቸው 40 ዓመታት ውስጥ ሲፓራን አግብቶ ልጆች ወለደ እንዲሁም ለይቶ የሚያሳውቀውን ባሕርይ ይበልጥ እያዳበረ ሄደ። አዎን፣ ሙሴ ካሳለፈው መከራ የዋህነትን አዳብሯል።—ዘጸአት 2:16-22፤ ሥራ 7:29, 30
14. ሙሴ የእስራኤል መሪ በነበረበት ወቅት የዋህነት ያሳየበትን ሁኔታ ግለጽ።
14 ይሖዋ የእስራኤል ብሔር መሪ አድርጎ ከሾመው በኋላም የሙሴ ባሕርይ አልተለወጠም። ይሖዋ የሙሴ ረዳት ሆነው እንዲያገለግሉ በተመረጡት 70 ሽማግሌዎች ላይ መንፈሱን ሲያፈስስ በቦታው ያልነበሩት ኤልዳድ እና ሞዳድ በሰፈሩ ውስጥ ትንቢት መናገራቸውን አንድ ወጣት ለሙሴ ነገረው። ኢያሱ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፣ ከልክላቸው” ባለው ጊዜ ሙሴ “የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፣ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያወርድ፤ አንተ ስለ እኔ ትቀናለህን?” ሲል በትሕትና መለሰለት። (ዘኍልቍ 11:26-29) ሙሴ የዋህነት ማሳየቱ ውጥረቱን ለማርገብ አስችሏል።
15. ሙሴ ፍጽምና የሚጎድለው ቢሆንም ግሩም ምሳሌ ትቶልናል የምንለው ለምንድን ነው?
15 ሙሴ በአንድ ወቅት የዋህነትን ማሳየት ተስኖት ነበር። በቃዴስ አቅራቢያ በሚገኘው በመሪባ ተአምር ለሠራው ለይሖዋ ክብር ሳይሰጥ ቀርቷል። (ዘኍልቍ 20:1, 9-13) ሙሴ ፍጽምና የሚጎድለው ቢሆንም ጽኑ እምነቱ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ያጠነከረው ከመሆኑም በላይ ያንጸባረቀው የላቀ የየዋህነት ባሕርይ የእኛንም ስሜት በጥልቅ ይነካል።—ዕብራውያን 11:23-28
ክፋትና የዋህነት
16, 17. ስለ ናባልና ስለ አቢግያ ከሚገልጸው ታሪክ ምን የማስጠንቀቂያ ትምህርት እናገኛለን?
16 በዳዊት ዘመን የአምላክ ነቢይ የነበረው ሳሙኤል ከሞተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የተፈጸመው ታሪክ ጥሩ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆነናል። ታሪኩ ባልና ሚስት በሆኑት በናባልና በአቢግያ ላይ ያተኩራል። በሁለቱ መካከል ከፍተኛ የባሕርይ ልዩነት አለ። አቢግያ አስተዋይ ሴት ስትሆን ባልዋ ግን ባለጌና ምግባረ ብልሹ ሰው ነበር። ናባል ስንቅ እንዲሰድለት ዳዊት የላካቸውን ሰዎች ክፉ ቃል ተናግሮ ባዶ እጃቸውን መለሳቸው። እነዚህ መልእክተኞች የናባልን መንጋ ከዘራፊዎች በመጠበቅ እርዳታ አድርገውለት ነበር። ዳዊት ሁኔታው በጣም ስላበሳጨው ሰይፍ የታጠቁ ሰዎችን አስከትሎ ናባልን ለማጥቃት ተነሳ።—1 ሳሙኤል 25:2-13
17 አቢግያ ስለ ሁኔታው ስትሰማ እንጀራ፣ የወይን ጠጅ፣ የበግ ሥጋ፣ ዘቢብና በለስ በፍጥነት አዘጋጅታ ወደ ዳዊት ሄደች። “ጌታዬ ሆይ፣ ይህ ኃጢአት በእኔ ላይ ይሁን እኔ ባሪያህ በጆሮህ ልናገር፣ የባሪያህንም ቃል አድምጥ” በማለት ተማጸነችው። ዳዊት አቢግያ በየዋህነት መንፈስ ያቀረበችውን ልመና ሲሰማ ከቁጣው መለስ አለ። ዳዊት ቃሏን ከሰማ በኋላ አቢግያን “ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። ወደ ደም እንዳልሄድ፣ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፣ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ” አላት። (1 ሳሙኤል 25:18, 24, 32, 33) ናባል ክፉ ሰው መሆኑ የኋላ ኋላ ለሞት ዳርጎታል። አቢግያ ግሩም ባሕርያት የነበሯት ሴት መሆኗ በመጨረሻ የዳዊት ሚስት የመሆን አስደሳች አጋጣሚ አስገኝቶላታል። ያሳየችው የየዋህነት ባሕርይ በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ለሚያገለግሉ ሁሉ ግሩም ምሳሌ ነው።—1 ሳሙኤል 25:36-42
የዋህነትን ተከታተል
18, 19. (ሀ) የዋህነትን ስንለብስ ምን ለውጥ ይታይብናል? (ለ) ራሳችንን በጥሩ ሁኔታ እንድንገመግም የሚረዳን ምንድን ነው?
18 እንግዲያው የዋህነት የግድ ልናዳብረው የሚገባ ባሕርይ ነው። የዋህነት ሲባል ገራገርነት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች እፎይታ የሚያስገኝ ከልብ የሚመነጭ ማራኪ ባሕርይ ነው። ከዚህ ቀደም ኃይለ ቃል መናገር እና ክፉ ማድረግ የሚቀናን ሰዎች ልንሆን እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከተማርን በኋላ ግን ለውጥ በማድረግ በሌሎች ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅና ተቀራቢ መሆን ችለናል። ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ” ብሎ ባሳሰባቸው ጊዜ ስለዚህ ለውጥ ተናግሯል። (ቆላስይስ 3:12) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ለውጥ እንደ ተኩላ፣ ነብር፣ አንበሳ፣ ድብና እባብ ያሉ ጨካኝ አራዊት ለውጥ አድርገው እንደ በግ፣ ፍየል፣ ላምና ጥጃ ያሉ ሰላማዊ የቤት እንስሳትን ከሚመስሉበት ሁኔታ ጋር አዛምዶታል። (ኢሳይያስ 11:6-9፤ 65:25) ሰዎች እንዲህ ያለ ጉልህ የባሕርይ ለውጥ በማድረጋችን መደነቃቸው አይቀርም። ይሁንና የዋህነትን ጨምሮ ሌሎች ግሩም የሆኑ ባሕርያት እንድናፈራና ለውጥ እንድናደርግ ያስቻለን የአምላክ መንፈስ መሆኑን እንገልጽላቸዋለን።
19 ታዲያ ይህ ሲባል አስፈላጊውን ለውጥ አድርገን ራሳችንን ለይሖዋ ከወሰንን በኋላ የዋህነትን በማዳበር ረገድ ጥረት ማድረግ አያስፈልገንም ማለት ነው? በፍጹም። አዲስ ልብስ እንኳ ንጹሕና ማራኪ እንዲሆን በየጊዜው መታጠብና መተኮስ ያስፈልገዋል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ምሳሌዎች ማጥናታችንና በዚያም ላይ ማሰላሰላችን ራሳችንን በየጊዜው በዓላማ እንድንገመግም ይረዳናል። እንደ መስተዋት የሚያገለግለው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ስለ ራስህ ምን ያስገነዝብሃል?—ያዕቆብ 1:23-25
20. የዋህነትን በማሳየት ረገድ ሊሳካልን የሚችለው እንዴት ነው?
20 ሰዎች በተፈጥሯቸው የተለያየ ባሕርይ አላቸው። አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች እንደ ሌሎች የዋህነትን ማንጸባረቅ አይከብዳቸውም። ይሁን እንጂ ሁሉም ክርስቲያኖች የዋህነትን ጨምሮ የአምላክን የመንፈስ ፍሬ ማፍራት ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል” የሚል ፍቅራዊ ማበረታቻ ሰጥቶታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:11) “ተከታተል” የሚለው ቃል የጥረትን አስፈላጊነት ያሳያል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ቃል ‘ልባዊ ጥረት አድርግ’ ብሎ ተርጉሞታል። (በጄ ቢ ፊሊፕስ የተዘጋጀው ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ ) በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት ግሩም ምሳሌዎች ላይ ለማሰላሰል ጥረት ካደረግህ እነዚህ ባሕርያት በውስጥህ የተተከሉ ያህል ይሆናሉ። አስተሳሰብህን የሚቀርጹልህ ከመሆኑም በላይ ለሕይወትህ መመሪያ ይሆኑሃል።—ያዕቆብ 1:21
21. (ሀ) የዋህነትን መከታተል ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን ይብራራል?
21 ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የምናሳየው ባሕርይ የዋህነትን በማንጸባረቅ ረገድ ምን ያህል እንደተሳካልን ያሳያል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው?” ሲል ከጠየቀ በኋላ ‘በመልካም አኗኗሩ ሥራውን ከጥበብ በመነጨ የዋህነት ያሳይ’ የሚል መልስ ሰጥቷል። (ያዕቆብ 3:13) በቤታችን፣ በአገልግሎት ላይና በጉባኤ ውስጥ ይህን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ጠቃሚ መመሪያ ይዟል።
ለክለሳ ያህል
• የዋህነትን በተመለከተ
• ይሖዋ፣
• ኢየሱስ፣
• ሙሴና
• አቢግያ ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
• የዋህነትን መከታተል ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የአቤልን መሥዋዕት የተቀበለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የዋህነትና ትሕትና የማይነጣጠሉ ባሕርያት መሆናቸውን አሳይቷል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴ የዋህነት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቷል